በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘አታጉረምርሙ’

‘አታጉረምርሙ’

‘አታጉረምርሙ’

“ማንኛውንም ነገር ሳታጒረመርሙ . . . አድርጉ።”—ፊልጵስዩስ 2:14

1, 2. ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስና በቆሮንቶስ ለነበሩት ክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጥቷቸዋል? ለምንስ?

 ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በጻፈው ደብዳቤ ላይ በፊልጵስዩስ ለነበረው ክርስቲያን ጉባኤ ሞቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል። በዚያ ከተማ ይኖሩ የነበሩ የእምነት ባልንጀሮቹን ለልግስናቸውና ለቅንዓታቸው አመስግኗቸዋል፤ እንዲሁም በመልካም ሥራዎቻቸው ምክንያት የተሰማውን ደስታ ገልጾላቸዋል። ይሁንና “ማንኛውንም ነገር ሳታጒረመርሙ . . . አድርጉ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ፊልጵስዩስ 2:14) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ምክር የሰጣቸው ለምንድን ነው?

2 ጳውሎስ ማጉረምረም ለምን ነገር እንደሚዳርግ ያውቃል። ይህንን ምክር ከመስጠቱ ከጥቂት ዓመታት በፊት ማጉረምረም ጎጂ እንደሆነ በቆሮንቶስ ለሚገኘው ጉባኤ ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር። ጳውሎስ፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ እያሉ በተደጋጋሚ ይሖዋን ያስቆጡት እንደነበረ ጠቅሷል። ያስቆጡት እንዴት ነው? ክፉ ነገሮችን በመመኘት፣ ጣዖት በማምለክ፣ ዝሙት በመፈጸም፣ ይሖዋን በመፈታተንና በማጉረምረም ነበር። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከእነዚህ ምሳሌዎች ትምህርት እንዲያገኙ አበረታቷቸዋል። “ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳጕረመረሙና በአጥፊው እንደ ጠፉ፣ አታጕረምርሙ” ብሎ ጽፏል።1 ቆሮንቶስ 10:6-11

3. በዛሬው ጊዜ ስለ ማጉረምረም ማንሳት ለምን አስፈለገ?

3 እኛም የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በፊልጵስዩስ ከነበረው ጉባኤ ጋር የሚመሳሰል መንፈስ እናሳያለን። ለመልካም ሥራዎች የምንቀና ከመሆናችንም በላይ እርስ በርሳችን እንዋደዳለን። (ዮሐንስ 13:34, 35) ነገር ግን ማጉረምረም፣ ባለፉት ዘመናት በኖሩ የአምላክ አገልጋዮች ላይ ያስከተለውን ጉዳት ስንመለከት “ማንኛውንም ነገር ሳታጒረመርሙ . . . አድርጉ” ለሚለው ምክር ትኩረት የምንሰጥበት በቂ ምክንያት እናገኛለን። እስቲ በመጀመሪያ ማጉረምረምን በተመለከተ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱትን ምሳሌዎች እንመልከት። ከዚያም ማጉረምረም ከሚያስከትለው ጉዳት ራሳችንን ለመጠበቅ ማድረግ የምንችላቸውን አንዳንድ ነገሮች እናያለን።

በይሖዋ ላይ ያጉረመረመ ክፉ ማኅበረሰብ

4. እስራኤላውያን በምድረ በዳ ያጉረመረሙት በምን ምክንያት ነው?

4 ‘ማጉረምረም፣ ማማረርና ማጉተምተም’ የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩባቸው 40 ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱት ነገሮች ጋር በተያያዘ ተገልጿል። በዚያ ወቅት እስራኤላውያን በሁኔታቸው ቅር ስለተሰኙ አጉረምርመው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ “መላው ማኅበር በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ።” እስራኤላውያን ምግብን በተመለከተ እንዲህ ሲሉ አማርረዋል:- “በሥጋ መቀቀያው ምንቸት ዙሪያ ተቀምጠን የፈለግነውን ያህል ምግብ መመገብ በምንችልበት በግብፅ ሳለን፣ ምነው በእግዚአብሔር እጅ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! እናንተ ግን ይህ ሁሉ ጉባኤ በራብ እንዲያልቅ ወደዚህ ምድረ በዳ አመጣችሁን።”ዘፀአት 16:1-3

5. እስራኤላውያን ባማረሩበት ወቅት በእርግጥ ያጉረመረሙት በማን ላይ ነበር?

5 እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይሖዋ እስራኤላውያን በምድረ በዳ እያሉ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በመስጠት ደግፏቸው ነበር፤ በፍቅር ተነሳስቶ ምግብና ውኃ አቅርቦላቸዋል። ስለዚህ እስራኤላውያን በምድረ በዳ በረሃብ ያልቃሉ የሚል ስጋት የሚፈጥር ምንም ምክንያት አልነበረም። ሆኖም ባገኙት ነገር አለመርካታቸው የነበሩበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አጋንነው እንዲመለከቱና ማጉረምረም እንዲጀምሩ አደረጋቸው። ያማረሩት በሙሴና በአሮን ላይ ቢሆንም ይሖዋ በእርሱ ላይ እንዳጉረመረሙ አድርጎ ቆጥሮታል። ሙሴ “በእርሱ ላይ ማጕረምረማችሁን ሰምቶአል . . . እኛ ማን ነን? በእኛ ላይ አይደለም ያጕረመረማችሁት፤ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ” በማለት ለእስራኤላውያን ነግሯቸው ነበር።ዘፀአት 16:4-8

6, 7. በዘኍልቍ 14:1-3 ላይ እንደታየው እስራኤላውያን አመለካከታቸው የተቀየረው እንዴት ነው?

6 ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ሕዝቡ በድጋሚ አጉረመረመ። ሙሴ ተስፋይቱን ምድር እንዲሰልሉ 12 ሰዎችን ልኮ ነበር። ከእነዚህ መካከል አሥሩ ሰዎች መጥፎ ዜና ይዘው ተመለሱ። ይህ ምን አስከተለ? “እስራኤላውያን በሙሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ እንዲህ አሉአቸው፤ ‘ምነው በግብፅ ወይም በዚህ ምድረ በዳ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! እግዚአብሔር ወደዚች ምድር [ከነዓን] የሚያመጣን ለምንድነው? በሰይፍ እንድንወድቅ ነውን? ሚስቶቻችንና ልጆቻችንም ይማረካሉ፤ ታዲያ ወደ ግብፅ መመለሱ አይሻለንም?’”ዘኍልቍ 14:1-3

7 የእስራኤላውያን አመለካከት ምንኛ ተለውጦ ነበር! ቀደም ሲል፣ ይሖዋ ከግብፅ ስላወጣቸውና ቀይ ባሕርን በተአምር ስላሻገራቸው የተሰማቸው የአመስጋኝነት መንፈስ በመዝሙር እንዲያወድሱት አነሳስቷቸው ነበር። (ዘፀአት 15:1-21) ነገር ግን በምድረ በዳ ችግር ስላጋጠማቸውና ከነዓናውያንን በመፍራታቸው ምክንያት የአመስጋኝነት መንፈሳቸው ወደ ቅሬታ ተቀየረ። ላገኙት ነፃነት አምላክን ከማመስገን ይልቅ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደነፈጋቸው አድርገው በተሳሳተ መንገድ ነቅፈውታል። ማጉረምረማቸው ለይሖዋ ዝግጅቶች አድናቆት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው። ይሖዋ “ይህ ክፉ ማኅበረ ሰብ በእኔ ላይ የሚያጕረመርመው እስከ መቼ ነው?” ብሎ መናገሩ ምንም አያስገርምም።ዘኍልቍ 14:27፤ 21:5

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የታየ የአጉረምራሚነት መንፈስ

8, 9. በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት ታሪኮች መካከል ማጉረምረምን በተመለከተ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

8 አጉረምራሚነትን በተመለከተ ከላይ ባየናቸው ምሳሌዎች ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች ቅሬታቸውን ያሰሙት በግልጽ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ በ32 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የዳስ በዓልን ለማክበር ኢየሩሳሌም በነበረበት ወቅት የነበረው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው፤ “ስለ እርሱ በሕዝቡ መካከል ብዙ ጕምጕምታ ነበር።” (ዮሐንስ 7:12, 13, 32) አንዳንዶቹ ደግ ሰው ነው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ አይደለም በማለት ስለ እርሱ በሹክሹክታ ይነጋገሩ ነበር።

9 በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በቀረጥ ሰብሳቢው በሌዊ ወይም በማቴዎስ ቤት ተጋብዘው ነበር። “ፈሪሳውያንና ጸሐፍታቸውም ‘ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና “ከኀጢአተኞች” ጋር የምትበሉትና የምትጠጡት ለምንድን ነው?’ እያሉ በደቀ መዛሙርቱ ላይ አጕረመረሙ።” (ሉቃስ 5:27-30) ከጥቂት ጊዜ በኋላ በገሊላ የሚኖሩ “አይሁድም፣ [ኢየሱስ] ‘ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ’ በማለቱ ያጕረመርሙበት ጀመር።” አንዳንድ የኢየሱስ ተከታዮች እንኳን እርሱ በተናገረው ነገር ቅር በመሰኘታቸው ማጉረምረም ጀምረው ነበር።ዮሐንስ 6:41, 60, 61

10, 11. ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑት አይሁዳውያን ያጉረመረሙት ለምን ነበር? የጉባኤ ሽማግሌዎች ለተፈጠረው ቅሬታ መፍትሄ ከተሰጠበት መንገድ ምን ጥቅም ያገኛሉ?

10 በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ፣ የጰንጠቆስጤ በዓል ከተከበረ ብዙም ሳይቆይ ተከስቶ የነበረው ማጉረምረም ጠቃሚ ውጤት አስገኝቷል። ከእስራኤል ውጪ ይኖሩ የነበሩ በርካታ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት በይሁዳ በሚኖሩ የእምነት ባልንጀሮቻቸው አቀባበል የተደረገላቸው ቢሆንም ያለውን ነገር ከመከፋፈል ጋር በተያያዘ ችግር ተፈጥሮ ነበር። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ከግሪክ አገር የመጡ አይሁድ በይሁዳ ይኖሩ በነበሩት አይሁድ ላይ አጕረመረሙ፤ ምክንያቱም በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማደል አሠራር ላይ ከእነርሱ ወገን የሆኑት መበለቶች ችላ ተብለው ነበር።”የሐዋርያት ሥራ 6:1

11 የእነዚህ ክርስቲያኖች ማጉረምረም ከእስራኤላውያን የተለየ ነበር። ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑት አይሁዳውያን ባጋጠማቸው ሁኔታ ቅር መሰኘታቸውን የገለጹት ከራስ ወዳድነት በመነጨ ስሜት ተነሳስተው አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንዳንድ መበለቶች ችላ መባላቸው እንዲስተዋል አድርገዋል። በተጨማሪም ያጉረመረሙት ሰዎች ችግር አልፈጠሩም፤ እንዲሁም ይሖዋን አላማረሩም። ስሞታቸውን ያቀረቡት ለሐዋርያት ነበር፤ የቀረበው ቅሬታ ተገቢ በመሆኑ ምክንያት ሐዋርያት ፈጣን እርምጃ እንዲወሰድ ዝግጅት አደረጉ። ሐዋርያትም በዛሬው ጊዜ ላሉት የጉባኤ ሽማግሌዎች ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ! እነዚህ መንፈሳዊ እረኞች ‘የድኾችን ጩኸት ላለመስማት ጆሯቸውን እንዳይዘጉ’ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።ምሳሌ 21:13፤ የሐዋርያት ሥራ 6:2-6

ለጥፋት ከሚዳርግ ማጉረምረም ተጠበቁ

12, 13. (ሀ) ማጉረምረም ምን እንደሚያስከትል በምሳሌ አስረዳ። (ለ) አንድ ሰው እንዲያጉረመርም የሚገፋፋው ምን ሊሆን ይችላል?

12 ከላይ ከተመለከትናቸው ታሪኮች ውስጥ አብዛኞቹ እንደሚያሳዩት ማጉረምረም ቀደም ባሉት ጊዜያት በነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ላይ ከባድ ጉዳት አስከትሏል። ስለዚህ ማጉረምረም በዘመናችንም ጎጂ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ልብ ማለት ይገባናል። የሚከተለው ምሳሌ ማጉረምረም ምን ጎጂ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ለማስተዋል ይረዳናል። አብዛኞቹ የብረት ዓይነቶች የመዛግ ባሕርይ አላቸው። ብረት የመዛግ ምልክት ሲታይበት ችላ ከተባለ ዳግም እንደማይጠቅም ሆኖ ሊበላሽ ይችላል። ስፍር ቁጥር የሌላቸው መኪኖች ከጥቅም ውጪ የሚሆኑት የሞተር ችግር እያጋጠማቸው ሳይሆን የተሠሩበት ብረት በጣም በመዛጉ ምክንያት አደጋ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ነው። ይህንን ምሳሌ ከማጉረምረም ጋር ልናያይዘው የምንችለው እንዴት ነው?

13 አንዳንድ የብረት ዓይነቶች የመዛግ ባሕርይ እንዳላቸው ሁሉ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችም የማጉረምረም ዝንባሌ አላቸው። ስለዚህ ማንኛውም ዓይነት የማጉረምረም ዝንባሌ ይኖርብን እንደሆነ ራሳችንን መመርመር አለብን። እርጥበትና ጨዋማ አየር ዝገትን እንደሚያፋጥኑ ሁሉ መከራም ይበልጥ አጉረምራሚዎች እንድንሆን ያደርገናል። የአእምሮ ውጥረት መጠነኛ የሆነ ቁጣ ወደ ከፍተኛ ቅሬታ እንዲለወጥ ሊያደርግ ይችላል። በዚህ የመጨረሻ ዘመን መገባደጃ ላይ ሁኔታዎች እየከፉ ሲመጡ ለቅሬታ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች መጨመራቸው አይቀርም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ስለዚህ አንዱ የይሖዋ አገልጋይ በሌላው ላይ ማጉረምረም ሊጀምር ይችላል። ለዚህም መንስኤው በአንድ ሰው ድክመት፣ ባለው ችሎታ ወይም ባገኛቸው ልዩ የአገልግሎት መብቶች መከፋትን የመሰለ ቀላል ነገር ሊሆን ይችላል።

14, 15. የማማረር ዝንባሌያችንን መቆጣጠር ያለብን ለምንድን ነው?

14 ደስ ያልተሰኘንበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን የማማረር ዝንባሌያችንን ካልተቆጣጠርነው በምንም ነገር የማንረካ ልንሆንና የማጉረምረም ልማድ ሊጠናወተን ይችላል። አዎን፣ ማጉረምረም የሚያስከትለው መንፈሳዊ ጉዳት ሙሉ በሙሉ አቋማችንን ሊያበላሽብን ይችላል። እስራኤላውያን በምድረ በዳ ኑሯቸው ምክንያት ባጉረመረሙበት ወቅት ይሖዋን እስከመውቀስ ደርሰዋል። (ዘፀአት 16:8) እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብን!

15 የብረትን የመዛግ አጋጣሚ ለመቀነስ ዝገት መከላከያ ቀለም መቀባትና የዛጉ ነጠብጣቦችን በፍጥነት ማጽዳት ይቻላል። በተመሳሳይም የማማረር ባሕርይ እንዳለብን ስናስተውል ወዲያውኑ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን በጸሎት ካሰብንበት ልንቆጣጠረው እንችላለን። እንዴት?

ነገሮችን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ተመልከቱ

16. የማማረር ዝንባሌ ካለን እንዴት ልናሸንፈው እንችላለን?

16 ማጉረምረም ስለ ራሳችንና ስለ ችግሮቻችን ብቻ እንድናስብ ሊያደርገን እንዲሁም የይሖዋ ምሥክር በመሆናችን ምክንያት ያገኘናቸው በርካታ በረከቶች ፈጽሞ እንዳይታዩን ሊያደርገን ይችላል። የማማረር ዝንባሌ ኖሮብን ልናሸንፈው የምንፈልግ ከሆነ የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን ምክንያት ያገኘናቸውን በረከቶች ማስታወስ ይገባናል። ለምሳሌ ያህል፣ እያንዳንዳችን የይሖዋን የግል ስም የመሸከም ድንቅ መብት አለን። (ኢሳይያስ 43:10) ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት እንችላለን፤ በተጨማሪም ‘ጸሎትን የሚሰማውን’ ይሖዋን በማንኛውም ጊዜ ማነጋገር እንችላለን። (መዝሙር 65:2፤ ያዕቆብ 4:8) ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነትን በተመለከተ የተነሳውን ጉዳይ ስለምናውቅና ለአምላክ ታማኝ ሆኖ የመቆም መብት ስላለን ሕይወታችን እውነተኛ ትርጉም አለው። (ምሳሌ 27:11) አዘውትረን የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ እንችላለን። (ማቴዎስ 24:14) በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ያለን እምነት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረን ያስችለናል። (ዮሐንስ 3:16) ምንም ዓይነት ችግር ቢኖርብን እነዚህን በረከቶች እያገኘን ነው።

17. እንድናማርር የሚያደርገን በቂ ምክንያት ቢኖረንም ነገሮችን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ለማየት መሞከር ያለብን ለምንድን ነው?

17 ነገሮችን ከራሳችን ሳይሆን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ለማየት እንሞክር። መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 25:4) እንድናማርር የሚያደርገን በቂ ምክንያት ካለ ይሖዋ እንደሚያየው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ወዲያውኑ ለችግሩ እልባት ሊያበጅለት ይችላል። ታዲያ አንዳንድ ጊዜ መከራ እንዲቀጥል የሚፈቅደው ለምንድን ነው? ይህ የሚሆነው እንደ ትዕግሥት፣ ጽናት፣ እምነትና ቻይነት የመሳሰሉትን መልካም ባሕርያት እንድናፈራ ለመርዳት ሊሆን ይችላል።ያዕቆብ 1:2-4

18, 19. ችግሮችን ያለምንም ማማረር መቋቋማችን ምን ውጤቶችን ሊያስገኝ እንደሚችል በምሳሌ አስረዳ።

18 ችግሮችን ያለምንም ማማረር መቋቋማችን ባሕርያችንን ለማሻሻል ከመርዳትም አልፎ ጸባያችንን የሚመለከቱ ሰዎችን ልብ ሊነካ ይችላል። አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን በ2003 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከጀርመን ወደ ሃንጋሪ በአውቶብስ ተጉዞ ነበር። የአውቶብሱ ሹፌር የይሖዋ ምሥክር ባለመሆኑ አሥር ቀናት ከእነርሱ ጋር ማሳለፉ ብዙም አላስደሰተውም ነበር። ነገር ግን ጉዟቸውን ሲጨርሱ አመለካከቱ ሙሉ በሙሉ ተቀየረ። ለምን?

19 በጉዞው ወቅት በርካታ ችግሮች ተከስተው ነበር። ተጓዦቹ ግን ምንም አላማረሩም። ሹፌሩ ከዚያ ቀደም እንዲህ ያሉ ተጓዦች ፈጽሞ አጋጥመውት እንደማያውቁ ተናገረ! እንዲያውም ከዚያ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቱ ሲመጡ እንዲገቡ እንደሚጋብዛቸውና የሚናገሩትን በጥንቃቄ እንደሚያዳምጥ ቃል ገብቷል። ተጓዦቹ ‘ማንኛውንም ነገር ሳያጒረመርሙ’ በማድረጋቸው በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል!

ይቅር ባይነት አንድነትን ያጠናክራል

20. እርስ በርሳችን ይቅር መባባል ያለብን ለምንድን ነው?

20 በእምነት ባልንጀራችን ላይ ቅሬታ ቢኖረንስ? ጉዳዩ ከባድ ከሆነ በማቴዎስ 18:15-17 ላይ የሚገኙትን ኢየሱስ የተናገራቸውን መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋል ይገባናል። ነገር ግን በአብዛኛው የሚፈጠሩት ቅሬታዎች ቀላል ስለሚሆኑ ሁልጊዜ እንዲህ ማድረግ ላያስፈልግ ይችላል። እነዚህን ሁኔታዎች፣ የይቅር ባይነትን ባሕርይ ለማሳየት አጋጣሚ እንደሚሰጡን አድርገን ለምን አንመለከታቸውም? ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።” (ቈላስይስ 3:13, 14) ታዲያ ልባችን ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው? ይሖዋስ በእኛ ላይ ቅር የሚሰኝበት ምክንያት የለውም? ምክንያት ቢኖረውም እንኳን በተደጋጋሚ ርኅራኄ ያሳየናል፤ ይቅርታም ያደርግልናል።

21. አንድ ሰው ሲያጉረመርም የሚያዳምጡ ሰዎች ምን ሊሰማቸው ይችላል?

21 ምንም ዓይነት ቅሬታ ቢኖር እንኳን ማጉረምረም ችግሩን አይፈታም። “ማጉረምረም” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል “ማጉተምተም” የሚል ፍቺም ሊሰጠው ይችላል። ሁልጊዜ ከሚያጉረመርም ሰው ጋር መሆን ደስ ስለማይለን ከእንዲህ ዓይነት ሰው ለመራቅ እንጥራለን። እኛም በበኩላችን አጉረምራሚ ወይም አጉተምታሚ ከሆንን የሚያዳምጡን ሰዎች ተመሳሳይ ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል። እንዲያውም ከእኛ መራቅ እስኪፈልጉ ድረስ በጣም ልንከብዳቸው እንችላለን! ስናጉረመርም የአንድን ሰው ትኩረት መሳብ እንችል ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ ባሕርይ ሰውየው ከእኛ ጋር እንዲቀራረብ አይጋብዘውም።

22. አንዲት ልጃገረድ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን ብላለች?

22 የይቅር ባይነት መንፈስ በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ትልቅ ግምት የሚሰጠውን አንድነት ያጠናክራል። (መዝሙር 133:1-3) በአንድ የአውሮፓ አገር ውስጥ የምትኖርና የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆነች የ17 ዓመት ልጃገረድ ለይሖዋ ምሥክሮች ያላትን አድናቆት ገልጻለች። ይህቺ ወጣት “በጥላቻ፣ በስግብግብነት፣ ባለመቻቻል፣ በራስ ወዳድነት ወይም ባለመስማማት ምክንያት አባላቱ ያልተከፋፈሉበት እንዲህ ያለ ድርጅት አይቼ አላውቅም” በማለት ለይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ጽፋለች።

23. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን ይብራራል?

23 የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን ምክንያት ላገኘናቸው በረከቶች ሁሉ ያለን አድናቆት፣ አንድነታችንን እንድናጠናክርና ስለ ግል ጉዳዮች አንስተን በሌሎች ላይ ከማጉረምረም እንድንጠበቅ ይረዳናል። አምላካዊ ባሕርያትን ማዳበራችን ይበልጥ አደገኛ ከሆነ የማጉረምረም ዓይነት እንዴት እንደሚጠብቀን በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል፤ ይህም በይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ላይ ማጉረምረም ነው።

ታስታውሳለህ?

• ማጉረምረም ሲባል ምንን ያጠቃልላል?

• ማጉረምረም ምን ውጤት እንደሚያስከትል እንዴት በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል?

• ያለብንን የማጉረምረም ዝንባሌ ለማሸነፍ ምን ሊረዳን ይችላል?

• ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆን ከማጉረምረም እንድንጠበቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤላውያን ያጉረመረሙት በይሖዋ ላይ ነበር!

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነገሮችን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ለማየት ትሞክራለህ?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይቅር ባይነት ክርስቲያናዊ አንድነትን ያጠናክራል