በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እስራኤል ተብሎ ስለሚጠራው ሕዝብ የሚገልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ማስረጃ

እስራኤል ተብሎ ስለሚጠራው ሕዝብ የሚገልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ማስረጃ

እስራኤል ተብሎ ስለሚጠራው ሕዝብ የሚገልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ማስረጃ

ግብጽ በሚገኘው የካይሮ ሙዚየም ውስጥ የፈርዖን ሜርኔፕታን ድል የሚዘክር ከጠንካራ ድንጋይ የተሠራ ሐውልት አለ። ምሁራን ይህ የዳግማዊ ራምሴስ 13ተኛ ልጅ ከ1212 እስከ 1202 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ ግብጽን ይገዛ እንደነበረ ይገምታሉ፤ ይህም በጥንቷ እስራኤል መሳፍንት ይገዙ በነበረበት ጊዜ ማብቂያ አካባቢ ማለት ነው። በሜርኔፕታ ሐውልት ላይ የተጻፉት የመጨረሻ ሁለት መስመሮች እንዲህ ይላሉ:- “ከነዓን ተበዝብዛለች። አስቀሎና ተይዛለች፣ ጌዝር ተማርካለች፣ ያኖአም ደግሞ ድምጥማጧ ጠፍቷል። እስራኤል ባድማ ሆኗል፣ ዘሮቹም ጠፍተዋል።”

“እስራኤል” የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ መሠረት ትርጉሙ ምንድን ነው? ሥዕላዊውን የአጻጻፍ ዘዴ ስንመለከት ጽሑፉ ውስጥ የሚገኙት ተጨማሪ ምልክቶች ቃላቶቹ ከየትኛው ክፍል እንደሚመደቡ ይጠቁማሉ። ዘ ራይዝ ኦቭ ኤንሸንት ኢዝራኤል የተባለው ጽሑፍ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “ከአራቱ ስሞች ውስጥ በሦስቱ ማለትም በአስቀሎና፣ በጌዝርና በያኖአም ላይ የተጨመሩት ምልክቶች እነዚህ [ስሞች] ከተሞችን የሚያመለክቱ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። . . . ሆኖም እስራኤል በሚለው ቃል ላይ የተጨመረው ምልክት ሕዝቦችን የሚያመለክት ነው።”—በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

የዚህ ቃል ትርጉም ምንድን ነው? የአንድ መጽሔት አዘጋጅና ጸሐፊ የሆኑት ኸርሼል ሻንክስ መልሱን እንዲህ በማለት ይነግሩናል:- “የሜርኔፕታ ሐውልት፣ እስራኤል ተብሎ የሚጠራ ሕዝብ በ1212 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደነበረና የግብጹ ፈርዖን ስለ እስራኤል ከማወቁም በላይ ይህን ሕዝብ በውጊያ ድል በማድረጉ ሊኩራራ እንደሚገባው ተሰምቶት እንደነበረ ያሳያል።” በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የአርኪኦሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዊልያም ዴቨር እንዲህ ብለዋል:- “የሜርኔፕታ ሐውልት በከነዓን ምድር ራሱን ‘እስራኤል’ ብሎ የሚጠራ ሕዝብ እንደነበርና ይህ ሕዝብ በግብጻውያን ዘንድም ‘እስራኤል’ ተብሎ እንደሚጠራ በግልጽ ይነግረናል። ግብጻውያን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነት ለማረጋገጥ እንደማይሞክሩና ራሳቸውን ለማሳወቅ ብለው ‘እስራኤል’ የተባለ የተለየ ሕዝብ እንደማይፈጥሩ የታወቀ ነው።”

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስራኤል የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኘው ፓትሪያርኩ ያዕቆብ ይህ ስም እንደተሰጠው በሚናገርበት ቦታ ላይ ነው። የያዕቆብ 12 ወንዶች ልጆች ዝርያዎችም “የእስራኤል ልጆች” ተብለው ተጠርተዋል። (ዘፍጥረት 32:22-28, 32፤ 35:9, 10) ከዓመታት በኋላ ነቢዩ ሙሴም ሆነ የግብጹ ፈርዖን የያዕቆብን ዝርያዎች “እስራኤል” በሚለው ቃል ይጠሯቸው ነበር። (ዘፀአት 5:1, 2) ይህ የሜርኔፕታ ሐውልት እስራኤል ተብሎ ስለሚጠራው ሕዝብ የሚገልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ጥንታዊ ማስረጃ ነው።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሜርኔፕታ ሐውልት

የመጨረሻዎቹ ሦስት ምልክቶች (ከቀኝ ወደ ግራ) ማለትም ዱላው፣ ተቀምጠው የሚታዩት ወንድና ሴት አንድ ላይ ሲጣመሩ እስራኤል ባዕድ የሆነን ሕዝብ እንደሚያመለክት ያሳያሉ

[ምንጭ]

Egyptian National Museum, Cairo, Egypt/Giraudon/The Bridgeman Art Library