የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ዝሙት ወይም ብልግና መፈጸም ከክርስቲያን ጉባኤ ሊያስወግድ እንደሚችል ሁሉ ርኩሰት መፈጸምስ ሊያስወግድ ይችላል?
አዎን፣ አንድ ግለሰብ እንደ ዝሙት፣ አስነዋሪ ርኩሰት ወይም ብልግና የመሳሰሉትን ኃጢአቶች ቢሠራና ንስሐ ባይገባ ከክርስቲያን ጉባኤ ሊወገድ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የሥጋ ሥራ ግልጽ ነው:- ይኸውም ዝሙት፣ ርኵሰት፣ መዳራት [“ብልግና፣” NW] . . . እንዲሁም እነዚህን የመሰለው ነው። . . . አሁንም አስጠነቅቃችኋለሁ፤ በእንዲህ ሁኔታ የሚኖሩ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” ብሎ በጻፈበት ወቅት እነዚህን ሦስት ኃጢአቶች ለውገዳ ከሚያበቁ ሌሎች ድርጊቶች ጋር ጠቅሷቸዋል።—ገላትያ 5:19-21
ዝሙት (በግሪክኛው ፖርኒያ) የሚለው ቃል ቅዱስ ጽሑፋዊ ከሆነው ጋብቻ ውጭ የሚደረገውን ማንኛውንም ዓይነት ተገቢ ያልሆነ የፆታ ግንኙነት ያመለክታል። ይህም ምንዝርን፣ ዝሙት አዳሪነትን፣ ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚደረግ የፆታ ግንኙነትን፣ በአፍና በፊንጢጣ የሚደረግ ግንኙነትን እንዲሁም የፆታ ስሜትን ለማርካት ሲባል የትዳር ጓደኛ ያልሆነን ሰው የፆታ ብልት በማሻሸት የሚፈጸምን ወሲባዊ ድርጊት ያጠቃልላል። አንድ ግለሰብ ዝሙት ቢፈጽምና ንስሐ ባይገባ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ሆኖ መቀጠል አይችልም።
ብልግና (በግሪክኛው አሴሊያ) የሚለው ቃል “ልቅ መሆንን፣ ባለጌነትን፣ እፍረተ ቢስነትን እንዲሁም ወራዳ ምግባርን” ያመለክታል። ዘ ኒው ታየርስ ግሪክ-ኢንግሊሽ ሌክሲከን የተባለው መዝገበ ቃላት አሴሊያ የተባለውን የግሪክኛ ቃል “ገደብ የለሽ ወሲባዊ ፍላጎት፣ . . . ጋጠወጥነት፣ እፍረተ ቢስነት፣ ባለጌነት” በማለት ይፈታዋል። ሌላ መዝገበ ቃላት ደግሞ ብልግናን “በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ነውር የሚታይ” ጠባይ ብሎታል።
ከላይ የተጠቀሰው መዝገበ ቃላት የሰጠው ፍቺ እንደሚያመለክተው “ብልግና” ሁለት ገጽታዎች አሉት፤ እነርሱም:- (1) የአምላክን ሕግ በመጣስ ከባድ ኃጢአት መፈጸም (2) ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ ዓይን አውጣና እፍረተ ቢስ መሆኑ ናቸው።
ስለዚህ “ብልግና” ቀላል ጥፋቶችን አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን ሕጎች የሚያስጥሱ ከባድ ድርጊቶችን የሚያመለክት ከመሆኑም በላይ ለሥነ ሥርዓት፣ ለሕግ ወይም ለባለ ሥልጣን አክብሮት አለማሳየትን፣ ደንታ ቢስ መሆንን አሊያም ጭራሽ ንቀት ማሳየትንና ባለጌነትን ያንጸባርቃል። ጳውሎስ መዳራትን ወይም ብልግናን ከዝሙት ጋር አያይዞ ጠቅሶታል። (ሮሜ 13:13, 14) ብልግና በገላትያ 5:19-21 ላይ ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት እንቅፋት ከሚሆኑ በርካታ የኃጢአት ድርጊቶች ጋር ተዘርዝሮ ስለሚገኝ እንዲህ ያለውን ድርጊት መፈጸም ተግሣጽ የሚያሰጥ ከመሆኑም በላይ ከክርስቲያን ጉባኤ ሊያስወግድ ይችላል።
ርኩሰት (በግሪክኛ አካታርሲያ) የሚለው ቃል “ዝሙት”፣ “ርኵሰት” እና “ብልግና” ከሚሉት ቃላት የበለጠ ሰፊ ትርጉም አለው። ይህ ቃል ከፆታ ግንኙነት፣ ከአነጋገር፣ ከድርጊት እንዲሁም ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር በተያያዘ የጎደፉ መሆንን ያጠቃልላል። ስለዚህ “ርኵሰት” የተለያዩ ከባድ ኃጢአቶችን የሚያጠቃልል ቃል ነው።
በ2 ቆሮንቶስ 12:21 ላይ ጳውሎስ “ብዙዎች ከዚህ በፊት ስለሠሩት ኀጢአትና ስለ ፈጸሙትም ርኵሰት፣ ዝሙትና መዳራት ንስሓ ሳይገቡ” መቅረታቸውን ገልጿል። እዚህ ቦታ ላይ “ርኵሰት” ‘ከዝሙትና ከመዳራት ወይም ከብልግና’ ጋር አብሮ ስለተጠቀሰ አንዳንድ የርኩሰት ዓይነቶች በፍርድ ኮሚቴ ውሳኔ ሊሰጥባቸው እንደሚገባ ማስረጃ ይሆነናል። ነገር ግን ርኩሰት ብዙ ነገሮችን የሚያጠቃልል ቃል እንደመሆኑ መጠን በፍርድ ኮሚቴ መታየት የማያስፈልጋቸውን ነገሮችም ያካትታል። አንድ ቤት በመጠኑ ሊቆሽሽ ወይም በጣም ቆሽሾ ሊያስቀይም እንደሚችል ሁሉ ርኩሰትም ደረጃ አለው።
ጳውሎስ በኤፌሶን 4:19 ላይ “ኅሊናቸው ስለ ደነዘዘ በማይረካ ምኞት፣ በርኵሰት ሁሉ እንዳሻቸው ለመኖር ቅጥ ለሌለው ብልግና ራሳቸውን አሳልፈው” ስለ ሰጡ አንዳንድ ግለሰቦች ተናግሯል። እዚህ ላይ ጳውሎስ ‘ርኵሰትንና የማይረካ ምኞትን’ ከብልግና ጋር ፈርጇቸዋል። አንድ የተጠመቀ ወንድም “በማይረካ ምኞት” ተሸንፎ “ርኵሰት” ቢፈጽም ነገር ግን ንስሐ ባይገባ ይህ ድርጊቱ አስነዋሪ ርኩሰት በመሆኑ ከክርስቲያን ጉባኤ ሊወገድ ይችላል።
ሁለት ዕጮኛሞች በተደጋጋሚ ጊዜያት ተዳርተዋል እንበል። እነዚህ ግለሰቦች ምንም እንኳ እንደ ብልግና የሚቆጠር የእፍረተ ቢስነት ዝንባሌ ባያሳዩም ሽማግሌዎች ዕጮኛሞቹ በማይረካ ምኞት ተሸንፈው አስነዋሪ ርኩሰት ፈጽመዋል የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሱ ይሆናል። ስለዚህ ጉዳዩ በፍርድ ኮሚቴ እንዲታይ ሊወስኑ ይችላሉ። በተመሳሳይም በስልክ የብልግና ወሬ በግልጽ የሚያወራ አንድ አስፋፊ ይህንን ድርጊቱን እንዲያቆም ተደጋጋሚ ምክር ቢሰጠውና የተሰጠውን ምክር ችላ ብሎ በድርጊቱ ቢቀጥል አስነዋሪ ርኩሰት እንደፈጸመ ተቆጥሮ ፍርድ ኮሚቴ ፊት ሊቀርብ ይችላል።
ሽማግሌዎች እነዚህን የመሰሉ ጉዳዮችን በሚወስኑበት ጊዜ አስተዋይ መሆን ይኖርባቸዋል። አንድ ድርጊት በፍርድ ኮሚቴ መታየት የሚገባው መሆን አለመሆኑን በሚወስኑበት ወቅት የተፈጸመው ነገር ምን እንደሆነ እንዲሁም የድርጊቱን ክብደት በጥንቃቄ ማጤን አለባቸው። እንዲህ ሲባል ሽማግሌዎች የሚሰጡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ያልተቀበለ ሁሉ “ብልግና” ፈጽሟል ተብሎ ይከሰሳል ማለት አይደለም። አሊያም አንድ ድርጊት ብልግና ተብሎ እንዲፈረጅና በፍርድ ኮሚቴ እንዲታይ ይህን ያህል ጊዜ መደጋገም ይኖርበታል ብሎ የማስላት ጉዳይም አይደለም። ሽማግሌዎች የተፈጸመው ነገር ምን እንደሆነ፣ ምን ያህል እንደተደጋገመ፣ የድርጊቱን ባሕርይና ስፋት እንዲሁም ጥፋተኛው አስቦበት ያደረገው መሆን አለመሆኑንና ድርጊቱን እንዲፈጽም ያነሳሳው ውስጣዊ ግፊት ምን እንደሆነ እያንዳንዱን ሁኔታ በጥንቃቄ ማመዛዘን ይኖርባቸዋል።
አስነዋሪ ርኩሰት ከፆታ ጉዳዮች ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። ለምሳሌ አንድ የተጠመቀ ወጣት አስፋፊ ለአጭር ጊዜ ጥቂት ሲጋራዎች እንዳጨሰ ለወላጆቹ የነገራቸው ከመሆኑም ሌላ ሁለተኛ እንደማይደግመው ቃል ገባላቸው። ይህ ድርጊት ርኩሰት እንደሆነ አያጠያይቅም። ነገር ግን “በማይረካ ምኞት” የተፈጸመ “ርኵሰት” ወይም አስነዋሪ ርኩሰት የሚባለው ደረጃ ላይ አልደረሰም። ስለዚህ ልጁ ወላጆቹ 2 ቆሮንቶስ 7:1) ልጁ ንስሐ የማይገባ ከሆነ ይወገዳል።
በተገኙበት አንድ ወይም ሁለት ሽማግሌዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ቢሰጡት በቂ ነው። ነገር ግን አዘውትሮ የሚያጨስ ከሆነ ሆን ብሎ ሥጋውን እያረከሰ በመሆኑ አስነዋሪ ርኩሰት ፈጽሟል ተብሎ ፍርድ ኮሚቴ ሊቋቋም ይችላል። (አንዳንድ ክርስቲያኖች ወሲባዊ ፊልሞችን ወይም ስዕሎችን ያያሉ። ይህ ድርጊት በይሖዋ ፊት አስጸያፊ በመሆኑ ሽማግሌዎች አንድ የእምነት ባልንጀራቸው እንዲህ ያለውን ድርጊት እንደፈጸመ ሲሰሙ ይደነግጡ ይሆናል። ይሁንና አንድ ሰው ወሲባዊ ፊልም ወይም ስዕል ስላየ ብቻ ጉዳዩ በፍርድ ኮሚቴ አይታይም። ለምሳሌ አንድ ወንድም እምብዛም ዘግናኝ ያልሆነ ወሲባዊ ፊልም ደጋግሞ ተመልክቷል እንበል። በዚህ ድርጊት በጣም ከማፈሩም በላይ ኃጢአቱን ለሽማግሌ ተናዝዟል። እንዲሁም ይህን ድርጊት ላለመድገም ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። ይህን ጉዳይ የሰማው ሽማግሌ፣ ወንድም ያደረገው ነገር “በማይረካ ምኞት” የተፈጸመ ርኩሰት ወደሚባለው ደረጃ አልደረሰም ብሎ ሊያስብ ይችላል። አሊያም ወንድም ብልግና ፈጽሟል የሚያሰኝ የዓይን አውጣነት ባሕርይ አልታየበት ይሆናል። ጉዳዩ በፍርድ ኮሚቴ የሚታይ ባይሆንም ይህን ዓይነት ርኩሰት የፈጸመው ግለሰብ ጠንከር ያለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ያስፈልገዋል፤ በተጨማሪም የሽማግሌዎች ክትትል ሊያስፈልገው ይችላል።
በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ክርስቲያን ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርድ ዘግናኝ የሆነ ወሲባዊ ፊልም ለብዙ ዓመታት በስውር ሲመለከት ቆይቷል እንበል። ይህ ኃጢአት እንዳይታወቅበት የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። እንዲህ ያሉት የብልግና ፊልሞች በቡድን ሆኖ አስገድዶ መድፈርን፣ ግለሰቡን አስሮ የፆታ ግንኙነት መፈጸምን፣ እጅግ ዘግናኝ በሆነ መንገድ ሰውን ማሠቃየትን እንዲሁም ሴቶችን በጭቃኔ መደብደብን ወይም ሕፃናትን ጭምር ለወሲብ መጠቀሚያ ማድረግን የመሳሰሉ ድርጊቶችን የሚያሳዩ ናቸው። ይህ ወንድም ሌሎች እርሱ ያደረገውን መስማታቸውን ሲያውቅ ከፍተኛ እፍረት ተሰማው። ወንድም የደንታ ቢስነት ባሕርይ ባይታይበትም እንኳ ሽማግሌዎች ለመጥፎ ልማድ ‘ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል’ እንዲሁም በማይረካ ምኞት ተሸንፎ አስነዋሪ ርኵሰት ፈጽሟል የሚል መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ ጉዳዩ በፍርድ ኮሚቴ ሊታይ ይገባዋል። ጥፋተኛው ወሲባዊ ፊልም የማየት ልማዱን እርግፍ አድርጎ እንደሚተው ካላረጋገጠ እንዲሁም አምላካዊ ንስሐ ካላሳየ ከክርስቲያን ጉባኤ መወገድ ይኖርበታል። እንዲሁም ስለተመለከተው ነገር እየተናገረ ሌሎች ቤቱ መጥተው የብልግና ፊልሞችን እንዲያዩ የሚጋብዝ ከሆነ እፍረተ ቢስ ሆኗል ማለት ነው። ይህ ደግሞ የብልግና አንዱ ገጽታ ነው።
“ብልግና” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ምንጊዜም የሚያመለክተው ክብደት ያለውን ኃጢአት ነው። እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ ከወሲባዊ ድርጊት ጋር ይያያዛል። ሽማግሌዎች የተፈጸመው ድርጊት ብልግና መሆን አለመሆኑን ለመለየት ግለሰቡ ዘግናኝ ድርጊት ፈጽሞም እንኳ የዓይን አውጣነት፣ የነውረኝነትና፣ የእፍረተ ቢስነት ባሕርይ ይታይበት እንደሆነ ለማወቅ መጣር አለባቸው። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው የይሖዋን ሕግ በመጣስ ከባድ ኃጢአት በሚፈጽምበት ጊዜ የእፍረተ ቢስነት ዝንባሌ ባያሳይም እንኳ የፈጸመው ድርጊት ‘የማይረካ ምኞት’ የተንጸባረቀበት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉት ድርጊቶች አስነዋሪ ርኩሰት መሆናቸው ታውቆ በፍርድ ኮሚቴ መታየት ይኖርባቸዋል።
አንድ ሰው የፈጸመው ድርጊት ከአስነዋሪ ርኩሰት ወይም ከብልግና የሚፈረጅ መሆን አለመሆኑን መወሰን ከባድ ኃላፊነት ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ውሳኔ ከሰው ሕይወት ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮችን ለማየት በፍርድ ኮሚቴ ላይ የሚቀመጡ ወንድሞች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችላቸውን እውቀት፣ ማስተዋልና መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጣቸው ይሖዋን በጸሎት መጠየቅ ይገባቸዋል። ሽማግሌዎች የጉባኤውን ንጽሕና መጠበቅ አለባቸው። እንዲሁም ውሳኔያቸው ከይሖዋ ቃልና “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከሚያወጣው መመሪያ ጋር የተስማማ መሆን ይኖርበታል። (ማቴዎስ 18:18፤ 24:45 የ1954 ትርጉም) በተጨማሪም ሽማግሌዎች፣ በዚህ ክፉ ዘመን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ “እናንተ የምትፈርዱት ለሰው ሳይሆን፣ ፍርድ በምትሰጡበት ጊዜ ሁሉ ከእናንተ ጋር ለሆነው ለእግዚአብሔር ስለሆነ፣ በምትሰጡት ውሳኔ ሁሉ ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ” የሚሉትን ቃላት ልብ ማለት ይገባቸዋል።—2 ዜና መዋዕል 19:6