ይሖዋ መከራ የደረሰባቸውን ያድናል
ይሖዋ መከራ የደረሰባቸውን ያድናል
“የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል።”—መዝሙር 34:19
1, 2. አንዲት ታማኝ ክርስቲያን ምን ችግር አጋጥሟት ነበር? እኛም ተመሳሳይ ችግር ሊያጋጥመን የሚችለው ለምንድን ነው?
ኬይኮ a የምትባል ሴት ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት የይሖዋ ምሥክር ሆና ቆይታለች። በአንድ ወቅት የዘወትር አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ሆና ታገለግል ነበር። ይህንንም መብቷን ከፍ አድርጋ ትመለከተው ነበር። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ኬይኮ በተስፋ መቁረጥና በብቸኝነት ስሜት ተዋጠች። “ሥራዬ ማልቀስ ብቻ ነበር” ብላለች። አሉታዊ አስተሳሰቧን ማስወገድ እንድትችል የግል ጥናት ለማድረግ ከበፊቱ የበለጠ ጊዜ መደበች። “ቢሆንም አስተሳሰቤን ማስተካከል አልቻልኩም። ጭንቀቴ ከመባባሱ የተነሳ ሞቴን ተመኝቼ ነበር” ስትል ተናግራለች።
2 አንተስ ተመሳሳይ የተስፋ መቁረጥ ስሜት አጋጥሞህ ያውቃል? የይሖዋ ምሥክር እንደመሆንህ መጠን የምትደሰትባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ ይህም የሆነው መንፈሳዊ ሕይወት “ለአሁኑም ሆነ ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) አሁንም ቢሆን የምትኖረው በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው! እንዲህ ሲባል ግን ከማንኛውም ዓይነት መከራ ጥበቃ ታገኛለህ ማለት ነው? በጭራሽ! መጽሐፍ ቅዱስ “የጻድቅ መከራው ብዙ ነው” ይላል። (መዝሙር 34:19) ‘መላው ዓለም በክፉው’ ማለትም በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ስለሆነ እንዲህ መሆኑ አያስደንቅም። (1 ዮሐንስ 5:19) ሁላችንም ይነስም ይብዛ ዓለም በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር መሆኑ ያስከተላቸውን ውጤቶች እንቀምሳለን።—ኤፌሶን 6:12
መከራ የሚያስከትለው ውጤት
3. ከባድ ችግሮች ያጋጠሟቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች ምሳሌ ጥቀስ።
3 የሚደርስብን መከራ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ከሆነ አመለካከታችንን ሊያዛባብን ይችላል። (ምሳሌ 15:15) እስቲ ጻድቁን ሰው ኢዮብን እንመልከት። ከባድ መከራ እየደረሰበት በነበረበት ወቅት “ከሴት የተወለደ ሰው፣ ዘመኑ አጭርና በመከራ የተሞላ ነው” ብሎ ተናግሯል። (ኢዮብ 14:1) ኢዮብ ደስታው ተሟጦ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ይሖዋ እንደተወው ተሰምቶት ነበር። (ኢዮብ 29:1-5) ይሁን እንጂ ከባድ ሐዘን የደረሰበት የአምላክ አገልጋይ ኢዮብ ብቻ አይደለም። ሐና ልጅ ስላልወለደች “በነፍሷ ተመርራ” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (1 ሳሙኤል 1:9-11) ርብቃ ቤተሰቧ ውስጥ በነበረው ሁኔታ በጣም በመሰቃየቷ “መኖር አስጠልቶኛል” ብላለች። (ዘፍጥረት 27:46) ዳዊትም ስለፈጸማቸው ስህተቶች በማሰብ “ቀኑንም ሙሉ በትካዜ ተመላለስሁ” በማለት ተናግሮ ነበር። (መዝሙር ) እነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት በቅድመ ክርስትና ዘመን የኖሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ከከባድ ችግሮች ጋር ይታገሉ ነበር። 38:6
4. በዛሬው ጊዜ በክርስቲያኖች መካከል ‘የተጨነቁ ነፍሳት’ መኖራቸው የማያስደንቀው ለምንድን ነው?
4 ስለ ክርስቲያኖችስ ምን ለማለት ይቻላል? ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ‘የተጨነቁትን ነፍሳት እንዲያጽናኑ’ መንገር አስፈልጎት ነበር። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW) ‘የተጨነቁ ነፍሳት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በኑሮ ጭንቀት የተዋጡ ሰዎችን” እንደሚያመለክት አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይገልጻል። የጳውሎስ ቃላት እንደሚያሳዩት በተሰሎንቄ በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ ያሉ በአምላክ መንፈስ የተቀቡ አንዳንድ ክርስቲያኖች አዝነው ነበር። ዛሬም ቢሆን የተጨነቁ ክርስቲያኖች አሉ። ይሁንና የሚያዝኑት ለምንድን ነው? እስቲ ሦስቱን የተለመዱ ምክንያቶች እንመልከት።
ኃጢአተኛ መሆናችን ሊያስጨንቀን ይችላል
5, 6. በሮሜ 7:22-25 ላይ ካለው ሐሳብ ምን ማጽናኛ ማግኘት ይቻላል?
5 እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ‘ኅሊናቸው ከደነዘዘባቸው’ ምግባረ ብልሹ ሰዎች በተለየ በኃጢአተኝነታቸው ምክንያት ይጨነቃሉ። (ኤፌሶን 4:19) እነዚህ ክርስቲያኖች የሚከተለውን ሐሳብ እንደጻፈው እንደ ጳውሎስ ይሰማቸው ይሆናል:- “በውስጤ በእግዚአብሔር ሕግ ሐሤት አደርጋለሁ፤ ነገር ግን በብልቶቼ ውስጥ ለሚሠራው የኀጢአት ሕግ እኔን እስረኛ በማድረግ፣ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋ ሌላ ሕግ በብልቶቼ ውስጥ ሲሠራ አያለሁ።” ከዚያም ጳውሎስ “እኔ ምን ዐይነት ጐስቋላ ሰው ነኝ!” በማለት በግርምት ተናግሯል።—ሮሜ 7:22-24
6 አንተስ እንደ ጳውሎስ ተሰምቶህ ያውቃል? ፍጽምና እንደሚጎድልህ በሚገባ መገንዘብህ ምንም ስህተት የለውም፤ ምክንያቱም ይህ መሆኑ ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንድትረዳና ከክፋት ለመራቅ ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ እንድታጠናክር ያስችልሃል። ነገር ግን ባሉብህ ድክመቶች ምክንያት ሁልጊዜ መጨነቅ የለብህም። ጳውሎስ በጭንቀት ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ቃላት ከተናገረ በኋላ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን” ብሏል። (ሮሜ 7:25) አዎን፣ ጳውሎስ የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ከወረሰው ኃጢአት እንደሚያነጻው ይተማመን ነበር።—ሮሜ 5:18
7. አንድ ሰው በኃጢአተኝነት ዝንባሌው ምክንያት እንዳይጨነቅ ምን ሊረዳው ይችላል?
7 ኃጢአተኛ በመሆንህ ምክንያት የምትጨነቅ ከሆነ ሐዋርያው ዮሐንስ ከጻፋቸው ከሚከተሉት ቃላት ማበረታቻ ታገኛለህ:- “ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም።” (1 ዮሐንስ 2:1, 2) በኃጢአተኝነት ዝንባሌህ ምክንያት የምትጨነቅ ከሆነ ኢየሱስ የሞተው ለኃጢአተኞች እንጂ ለፍጹማን ሰዎች እንዳልሆነ ምንጊዜም አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” ይላል።—ሮሜ 3:23
8, 9. ራስን የመውቀስን ስሜት ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?
8 ይሁንና ቀደም ሲል ከባድ ኃጢአት ፈጽመህ ነበር እንበል። ጉዳዩን ለይሖዋ በጸሎት እንደምትገልጽ ምንም አያጠራጥርም፤ ምናልባትም በተደጋጋሚ እንዲህ አድርገህ ይሆናል። ከጉባኤ ሽማግሌዎችም መንፈሳዊ እርዳታ አግኝተሃል። (ያዕቆብ 5:14, 15) ከልብህ ንስሐ በመግባትህ ምክንያት የጉባኤው አባል ሆነህ መቀጠል ቻልክ። ወይም ደግሞ ለጥቂት ጊዜ ከአምላክ ድርጅት ከራቅህ በኋላ ንስሐ ገብተህ ንጹሕ አቋምህን ጠብቀህ መኖር ጀምረህ ይሆናል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ቀደም ሲል የሠራኸው ኃጢአት ትዝ እያለህ ሊያስጨንቅህ ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመህ ይሖዋ ከልባቸው ንስሐ ለሚገቡ ሰዎች ይቅርታው ‘ብዙ እንደሆነ’ አስታውስ። (ኢሳይያስ 55:7) ከዚህም በተጨማሪ ራስህን ከልክ በላይ እንድትኮንን አይፈልግም። እንዲህ እንዲሰማህ የሚፈልገው ሰይጣን ነው። (2 ቆሮንቶስ 2:7, 10, 11) ሰይጣን ጥፋት የሚገባው በመሆኑ በቅርቡ ይጠፋል፤ አንተም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ፍርድ ይገባኛል የሚል ስሜት እንዲኖርህ ይፈልጋል። (ራእይ 20:10) እምነትህን ለማጥፋት ሰይጣን የሸረበው ይህ ዘዴ እንዲሳካለት አትፍቀድ። (ኤፌሶን 6:11) ከዚህ ይልቅ በሌሎች ጉዳዮች እንደምታደርገው ሁሉ በዚህም ረገድ ‘ጸንተህ ተቃወመው።’—1 ጴጥሮስ 5:9
9 በራእይ 12:10 ላይ ሰይጣን “የወንድሞቻችን [የቅቡዓን ክርስቲያኖች] ከሳሽ” ተብሎ ተጠርቷል። እነዚህን ክርስቲያኖች በአምላክ ፊት ‘ቀንና ሌሊት ይከሳቸዋል።’ በዚህ ጥቅስ ላይ ማሰላሰልህ የሐሰት ከሳሽ የሆነው ሰይጣን ራስህን ብትከስና ብትነቅፍ እንደሚደሰት እንድትገነዘብ ይረዳሃል፤ ይሖዋ ግን አይከስህም ወይም አይወቅስህም። (1 ዮሐንስ 3:19-22) ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እስኪሰማህ ድረስ ለምን ስለ ድክመቶችህ ትጨነቃለህ? ሰይጣን ከአምላክ ጋር የመሠረትከውን ወዳጅነት እንዲያበላሽብህ አትፍቀድ። ዲያብሎስ፣ ይሖዋ “ሩኅሩኅ ቸር . . . ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ” አምላክ የመሆኑን ሐቅ እንድትዘነጋ እንዲያደርግህ በፍጹም ፈቃደኛ አትሁን።—ዘፀአት 34:6
ያለብን የአቅም ገደብ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል
10. ያለብን የአቅም ገደብ ተስፋ ሊያስቆርጠን የሚችለው እንዴት ነው?
10 አንዳንድ ክርስቲያኖች ያለባቸው የአቅም ገደብ ለአምላክ በሚያቀርቡት አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ ስለሚያደርግባቸው ተስፋ ቆርጠዋል። አንተስ እንዲህ ይሰማሃል? ምናልባት ከባድ ሕመም፣ የዕድሜ መግፋት ወይም ሌሎች ሁኔታዎች የቀድሞውን ያህል እንዳታገለግል አግደውህ ይሆናል። እውነት ነው፣ ክርስቲያኖች ለአምላክ አገልግሎት የሚያውሉትን ጊዜ እንዲዋጁ ተበረታተዋል። (ኤፌሶን 5:15, 16) ነገር ግን ያለብህ የአቅም ገደብ በአገልግሎትህ ብዙ ማከናወን እንዳትችል ቢያግድህና በዚህ ምክንያት ተስፋ ብትቆርጥስ?
11. በገላትያ 6:4 ላይ የሚገኘው ጳውሎስ የሰጠው ምክር የሚጠቅመን እንዴት ነው?
11 መጽሐፍ ቅዱስ ዳተኞች ከመሆን ይልቅ ‘በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድንመስል’ ያሳስበናል። (ዕብራውያን 6:12) እንዲህ ማድረግ የምንችለው እነርሱ የተዉትን መልካም ምሳሌ የምንመረምርና እምነታቸውን ለመኮረጅ የምንጣጣር ከሆነ ብቻ ነው። ነገር ግን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ራሳችንን ከሌሎች ጋር የምናወዳድርና የምናደርገው ነገር ሁሉ በቂ እንዳልሆነ የሚሰማን ከሆነ ምንም አንጠቀምም። ስለዚህ የሚከተለውን የጳውሎስ ምክር ተግባራዊ ብናደርግ የተሻለ ነው:- “እያንዳንዱ የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም በኋላ፣ ከሌላ ሰው ጋር ራሱን ሳያወዳድር፣ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል።”—ገላትያ 6:4
12. ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎት መደሰት የምንችለው ለምንድን ነው?
12 ክርስቲያኖች ከባድ ከሆኑ የጤና እክሎች የተነሳ የአቅም ገደብ ቢኖርባቸውም እንኳን የሚደሰቱበት በቂ ምክንያት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም . . . ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ዕብራውያን 6:10) በይሖዋ አገልግሎት የቀድሞውን ያህል እንቅስቃሴ እንዳታደርግ ያገዱህ ከአቅምህ በላይ የሆኑ ሁኔታዎች ይሆናሉ። ነገር ግን በይሖዋ እርዳታ በስልክና በደብዳቤ እንደ መመሥከር ባሉ አንዳንድ የክርስቲያናዊ አገልግሎት ዘርፎች ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ መካፈል ትችል ይሆናል። ይሖዋ አምላክ በፍጹም ነፍስህ ስታገለግለው እንዲሁም ለእርሱና ለሰዎች ፍቅር ስታሳይ እንደሚባርክህ እርግጠኛ ሁን።—ማቴዎስ 22:36-40
ያለንበት “የሚያስጨንቅ ጊዜ” ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል
13, 14. (ሀ) ያለንበት “የሚያስጨንቅ ጊዜ” ለስቃይ የሚዳርገን በምን መንገዶች ሊሆን ይችላል? (ለ) በዛሬው ጊዜ ፍቅር እንደጠፋ የሚያሳየው ምንድን ነው?
13 ጽድቅ በሰፈነበት በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ተስፋ የምናደርግ ቢሆንም አሁን ያለነው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) አሳዛኝ የሆኑ ክስተቶች መብዛት፣ ከመከራ የምንገላገልበት ጊዜ እንደቀረበ የሚያመለክት መሆኑን ማወቃችን ያጽናናናል። ነገር ግን በዙሪያችን ያሉት ሁኔታዎች እኛንም ይነኩናል። ለምሳሌ ያህል፣ ሥራ አጥ ብትሆንስ? ምናልባት ሥራ ሳታገኝ ወራት ቢያልፉ ይሖዋ ያለህበትን አስቸጋሪ ሁኔታ መመልከቱ ወይም ጸሎትህን መስማቱ ሊያጠራጥርህ ይችላል። ወይም ደግሞ መድልዎ ወይም አንድ ዓይነት ግፍ ይፈጸምብህ ይሆናል። የጋዜጦችን ርዕስ መመልከት ብቻ እንኳን እንደ ጻድቁ ሎጥ እንዲሰማህ ሊያደርግህ ይችላል። ሎጥ በዙሪያው በነበሩት ሰዎች መጥፎ ባሕርይ ምክንያት ‘ይሳቀቅ’ (‘ይጨነቅ፣’ የ1954 ትርጉም) ነበር።—2 ጴጥሮስ 2:7
14 ችላ ልንለው የማንችለው አንድ የተለየ የመጨረሻው ዘመን ገጽታም አለ። መጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ሰዎች “ፍቅር የሌላቸው” እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተንብዮአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:3) በበርካታ ቤቶች ውስጥ የቤተሰብ ፍቅር በእጅጉ ጠፍቷል። ፋሚሊ ቫዮለንስ የተባለ አንድ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ብዙውን ጊዜ ሰዎች የሚገደሉት እንዲሁም አካላዊ፣ ስሜታዊ ወይም ጾታዊ ጥቃት የሚፈጸምባቸው በሌሎች ሰዎች ሳይሆን በቤተሰባቸው አባላት ነው። . . . ሰዎች ፍቅር ሊያገኙበትና ደኅንነት ሊሰማቸው የሚያስፈልግበት ይህ ቦታ ለአንዳንድ አዋቂዎችና ልጆች ከየትኛውም ስፍራ የባሰ አደገኛ ቦታ ሆኗል።” መጥፎ የቤተሰብ ሁኔታ በሰፈነበት ቤት ውስጥ የኖሩ ሰዎች በኋለኞቹ ዓመታት ላይ ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ ሊያጋጥማቸው ይችላል። አንተ እንዲህ ያለ ችግር ቢኖርብህስ?
15. የይሖዋ ፍቅር ከማንኛውም ሰው ፍቅር የላቀ የሆነው እንዴት ነው?
15 መዝሙራዊው ዳዊት “አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 27:10) የይሖዋ ፍቅር ከማንኛውም ወላጅ ፍቅር እንደሚልቅ ማወቁ ምንኛ ያጽናናል! ወላጆችህ ችላ ያሉህ፣ የበደሉህ ወይም የተዉህ መሆኑ የስሜት ስቃይ የሚያስከትልብህ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ያለው ሁኔታ ይሖዋ ለአንተ ያለውን አሳቢነት አይቀንሰውም። (ሮሜ 8:38, 39) አምላክ የሚወዳቸውን ሰዎች ወደ ራሱ እንደሚስባቸው አስታውስ። (ዮሐንስ 3:16፤ 6:44) ሰዎች አንተን የሚይዙበት መንገድ ምንም ይሁን ምን የሰማዩ አባትህ ይወድሃል!
ጭንቀትን ለመቋቋም የሚጠቅሙ እርምጃዎች
16, 17. አንድ ሰው ጭንቀት ሲያጋጥመው መንፈሳዊ ጥንካሬውን እንዳያጣ ምን ማድረግ ይችላል?
16 ጭንቀትን ለመቋቋም የሚያስችሉ ጠቃሚ እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ ብርታት እንድታገኝ የሚያስችልህን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የምታደርግበት ፕሮግራም አውጣ። በተለይ ያለብህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ከአቅምህ በላይ እንደሆነ በሚሰማህ ጊዜ በአምላክ ቃል ላይ አሰላስል። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “እኔ፣ ‘እግሬ አዳለጠኝ’ ባልሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ደግፎ ያዘኝ። የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።” (መዝሙር 94:18, 19) መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ ማንበብ አእምሮህ በሚያጽናኑ ቃላትና በሚያበረታቱ ሐሳቦች እንዲሞላ ይረዳሃል።
17 ጸሎትም በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። አንተ የውስጥ ስሜትህን ለመግለጽ ብትቸገርም እንኳን ይሖዋ ምን ማለት እንደፈለግክ ያውቃል። (ሮሜ 8:26, 27) መዝሙራዊው “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም” በማለት በእርግጠኝነት ተናግሯል።—መዝሙር 55:22
18. ጭንቀት ያለበት ሰው ምን ጠቃሚ እርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል?
18 አንዳንዶች ተስፋ የሚቆርጡት ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ስላለባቸው ነው። b አንተም ከባድ ጭንቀት ካለብህ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ትኩረትህን ‘ታምሜአለሁ የሚል በማይኖርበት’ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ላይ አድርግ። (ኢሳይያስ 33:24) ያለብህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት አልፎ አልፎ ከሚያጋጥም መጠነኛ ትካዜ የከፋ ከሆነ ሐኪም ማማከሩ ጥሩ ሊሆን ይችላል። (ማቴዎስ 9:12) በተጨማሪም ለሰውነትህ እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ ነው። የተመጣጠነ ምግብ መመገብና ጥቂት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግም ሊጠቅም ይችላል። በቂ እረፍት አድርግ። ቴሌቪዥን እያየህ በጣም አታምሽ፤ ሰውነትህንም ሆነ ስሜትህን ከሚያደክሙ የመዝናኛ ዓይነቶች ተጠበቅ። ከሁሉም በላይ አምላክን የሚያስደስቱ ተግባሮችን ማከናወንህን ቀጥል! ምንም እንኳን ያለነው ይሖዋ ‘እንባን ሁሉ ከዐይን በሚያብስበት’ ጊዜ ላይ ባይሆንም እንድትጸና ይረዳሃል።—ራእይ 21:4፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13
“ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች” መኖር
19. ይሖዋ መከራ ለሚደርስባቸው ሰዎች ምን ቃል ገብቷል?
19 ጻድቅ ብዙ መከራ ቢደርስበትም “እግዚአብሔር . . . ከሁሉም ያድነዋል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። (መዝሙር 34:19) አምላክ ይህንን የሚያደርገው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ከነበረበት ‘የሥጋ መውጊያ’ ለመላቀቅ በተደጋጋሚ ሲለምን ይሖዋ “ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነው” ብሎት ነበር። (2 ቆሮንቶስ 12:7-9) ይሖዋ ለጳውሎስ ምን ቃል ገባለት? ለአንተስ የገባው ቃል ምንድን ነው? አምላክ ተስፋ የገባው ወዲያውኑ እንደሚፈውስ ሳይሆን መጽናት የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጥ ነው።
20. ችግሮች ቢደርሱብንም በ1 ጴጥሮስ 5:6, 7 ላይ ምን ማረጋገጫ ተሰጥቶናል?
20 ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።” (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) ይሖዋ ስለሚያስብልህ አይተውህም። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙህም እንኳን ይደግፍሃል። ታማኝ ክርስቲያኖች “ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች” እንደሆኑ አትዘንጋ። ይሖዋ ስናገለግለው ለመጽናት የሚረዳንን ጥንካሬ ይሰጠናል። ለእርሱ ታማኝ ከሆንን ዘላቂ መንፈሳዊ ጉዳት የሚያደርስብን ምንም ነገር አይኖርም። ስለዚህ እርሱ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ለማግኘትና መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች ለዘለቄታው ነጻ ሲያወጣቸው ለመመልከት እንድንችል ለይሖዋ ታማኝ እንደሆንን እንቀጥል!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ስሟ ተቀይሯል።
b ሥር የሰደደ የመንፈስ ጭንቀት፣ ከተስፋ መቁረጥ በከፋ መልኩ ለረጅም ጊዜ በሚዘልቅ ከፍተኛ የሐዘን ስሜት ተለይቶ ይታወቃል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የሚከተሉትን መጠበቂያ ግንቦች ተመልከት:- ጥቅምት 15, 1988 ገጽ 25-29 (እንግሊዝኛ)፣ ኅዳር 15, 1988 ገጽ 21-24 (እንግሊዝኛ) ወይም 22-109 ገጽ 21-23 እና መስከረም 1, 1996 ገጽ 30-31
ታስታውሳለህ?
• የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳን መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?
• አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች እንዲጨነቁ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
• ይሖዋ ያለብንን ጭንቀት እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?
• “ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች” የሆንነው በምን መንገድ ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ሕዝቦች ችግር ቢደርስባቸውም ደስ የሚሰኙበት ምክንያት አላቸው
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስልክ መመሥከር ለይሖዋ ምርጥህን መስጠት የምትችልበት አንዱ መንገድ ነው