በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁሉም ሰው ክብር ያገኛል

ሁሉም ሰው ክብር ያገኛል

ሁሉም ሰው ክብር ያገኛል

“የሰው ልጅ ለዘላለም ክብሩ የማይነካበት አዲስና ከሁሉ የተሻለ ዓለም መፍጠር ይኖርብናል።”—የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ሃሪ ትሩማን፣ ሳን ፍራንሲስኮ ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሚያዝያ 25, 1945

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በነበሩት ዓመታት ብዙ ሰዎች እንደተሰማቸው ሁሉ ፕሬዚዳንት ትሩማንም የሰው ልጅ ካሳለፈው ታሪክ ተምሮ ሁሉም ሰው ክብር የሚያገኝበት ‘አዲስ ዓለም’ እንደሚፈጥር እምነት ነበራቸው። ዘመናዊውን ታሪክ ስንመለከት ግን ሁኔታው የተገላቢጦሽ መሆኑ ያሳዝናል። የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ሰው ሳይሆን የሰው ዘር ቀንደኛ ጠላት የሆነው አካል በመሆኑ ‘የሰው ልጅ ዘላለማዊ ክብር’ አሁንም እየተገፈፈ ነው።

የችግሩ ዋነኛ መንስኤ

መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ጠላት ከሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ የአምላክን የመግዛት መብት እየተገዳደረ ያለው ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ማለትም ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ይናገራል። ሰይጣን በኤደን ገነት ከሔዋን ጋር ከተነጋገረ ጀምሮ ዓላማው የሰው ልጆች ፈጣሪያቸውን ከማምለክ ዞር እንዲሉ ማድረግ ነው። (ዘፍጥረት 3:1-5) አዳምና ሔዋን የዲያብሎስን ምክር ሰምተው እርምጃ ሲወስዱ በእነርሱ ላይ የደረሰውን አሳዛኝ ወጤት እስቲ አስብ! ከተከለከለው ፍሬ በመብላት የአምላክን ሕግ ለመታዘዝ ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው ‘ከእግዚአብሔር አምላክ ፊት እንዲሸሸጉ’ አድርጓቸዋል። ለምን? አዳም “ዕራቍቴን ስለ ሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም” በማለት ተናግሯል። (ዘፍጥረት 3:8-10) አዳም በሰማይ ከሚኖረው አባቱ ጋር የነበረው ዝምድና ከመበላሸቱም በላይ ለራሱ ያለው አመለካከትም ተለወጠ። በዚህም ምክንያት አዳም እፍረት ስለተሰማው በይሖዋ ፊት መቆም ከበደው።

ዲያብሎስ አዳም ለራሱ የነበረው ግምት ሲቀንስ ማየት የፈለገው ለምን ነበር? ሰው የአምላከን ክብር ማንጸባረቅ እንዲችል ተደርጎ በእርሱ መልክ የተፈጠረ ሲሆን ሰይጣን ደግሞ የሰው ልጅ ይህን ክብር ማንጸባረቅ ሳይችል በመቅረቱ ይደሰታል። (ዘፍጥረት 1:27፤ ሮሜ 3:23) ይህም የሰው ልጅ ታሪክ በሰብዓዊ ክብር ረገጣ የተሞላው ለምን እንደሆነ እንድንረዳ ያስችለናል። ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” እንደመሆኑ መጠን “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ” በሆነበት በዚህ ዘመን ይህ መንፈስ ይበልጥ እንዲስፋፋ አድርጓል። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ መክብብ 8:9፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ይህ ሲባል ግን የሰው ልጅ መቼም ቢሆን ክብር አያገኝም ማለት ነው?

ይሖዋ ፍጥረታቱን ያከብራል

አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት በኤደን ገነት የነበረውን ሁኔታ እስቲ መለስ ብለህ አስብ። በቂ ምግብና አርኪ ሥራ የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ እነርሱም ሆኑ ልጆቻቸው የተሟላ ጤንነት አግኝተው ለዘላለም የመኖር ተስፋ ከፊታቸው ተዘርግቶላቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) ሕይወታቸው በሙሉ የአምላክን ፍቅር እንዲሁም ለሰው ልጅ የነበረውን የተከበረ ዓላማ ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ነበር።

አዳምና ሔዋን በኃጢአት ሲወድቁ ይሖዋ ለሰው ልጅ ክብር የነበረው አመለካከት ተለውጧል? በፍጹም። ራቁታቸውን በመሆናቸው የተሰማቸውን እፍረት በመገንዘብ አሳቢነት አሳይቷቸዋል። አዳምና ሔዋን የበለስ ቅጠል ሰፍተው ያገለደሙ ቢሆንም አምላክ በደግነት “ከቈዳ ልብስ አዘጋጅቶ” አለበሳቸው። (ዘፍጥረት 3:7, 21) አፍረውና ተሸማቀው እንዲቀሩ አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ ክብራቸውን ጠብቆላቸዋል።

ከዚያም በኋላ ቢሆን ይሖዋ ከእስራኤል ብሔር ጋር በነበረው ግንኙነት ረገድ በማኅበረሰቡ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ይበልጥ ለጥቃት ለተጋለጡት ክፍሎች ማለትም ወላጅ ለሌላቸው ልጆች፣ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶችና ለመጻተኞች ርኅራኄ አሳይቷል። (መዝሙር 72:13) ለምሳሌ እስራኤላውያን ሰብል በሚያጭዱበት፣ የወይራ ዛፍ ፍሬ በሚያራግፉበት እንዲሁም የወይን ፍሬ በሚሰበስቡበት ጊዜ ቃርሚያውን ለመሰብሰብ መመለስ እንደሌለባቸው ተነግሯቸው ነበር። ከዚህ ይልቅ አምላክ፣ ቃርሚያውን “ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው” በማለት አዟቸዋል። (ዘዳግም 24:19-21) ይህን ሕግ በተግባር ላይ ማዋል የሚለምን ሰው እንዳይኖር ከማድረጉም በላይ ድሃ የሆኑት ሰዎችም ጭምር የተከበረ ሥራ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

ኢየሱስ ሌሎችን አክብሯል

የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር በነበረበት ወቅት ሌሎችን በአክብሮት ይይዝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በገሊላ በነበረበት ወቅት በሥጋ ደዌ በሽታ በጣም የተጎዳ ሰው ወደ እርሱ ቀረበ። በሙሴ ሕግ መሠረት በሽታው ወደ ሌላ ሰው እንዳይተላለፍ ግለሰቡ “ርኩስ ነኝ! ርኩስ ነኝ!” እያለ ጮኾ መናገር ይጠበቅበት ነበር። (ዘሌዋውያን 13:45) ይሁን እንጂ ይህ ሰው ሌሎች ወደ እርሱ እንዳይጠጉ ማስጠንቀቂያ ማሰማቱን ትቶ ወደ ኢየሱስ በመቅረብ በፊቱ ተደፋና “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎ ለመነው። (ሉቃስ 5:12) ታዲያ የኢየሱስ ምላሽ ምን ይመስል ነበር? ኢየሱስ ሰውየው ሕጉን በመጣሱ አልተቆጣውም፤ ወይም ችላ ብሎ አላለፈውም እንዲሁም አልሸሸውም። ከዚህ ይልቅ ለምጽ ያለበትን ይህን ሰው በእጁ በመንካት እንዲሁም “እፈቅዳለሁ፤ ንጻ!” በማለት አክብሮታል።—ሉቃስ 5:13

ምንም እንኳ ኢየሱስ በሌሎች ወቅቶች ሰዎችን ሳይነካቸው፣ አንዳንድ ጊዜም በሩቅ እያሉ መፈወስ እንደሚችል ያሳየ ቢሆንም በዚህ ጊዜ ግን ግለሰቡን በመዳሰስ ለመፈወስ መርጧል። (ማቴዎስ 15:21-28፤ ማርቆስ 10:51, 52፤ ሉቃስ 7:1-10) ይህ ሰው ሕመሙ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ እንደመሆኑ መጠን ለረጅም ጊዜ ከማንም ሰው ጋር ተነካክቶ አያውቅም። ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደገና ሰው ሲነካው እንዴት ይደሰት ይሆን! ግለሰቡ ከበሽታው ከመፈወስ በስተቀር ኢየሱስ ይዳስሰኛል ብሎ ጨርሶ አላሰበ ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ ሰውየውን የፈወሰበት መንገድ ግለሰቡ ለራሱ ያለው ግምት ከፍ እንዲል እንደረዳው ምንም ጥርጥር የለውም። በዛሬው ጊዜስ ለሌሎች ክብር የሚያስቡ ሰዎች ይኖራሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው? ከሆነ ለሌሎች አክብሮት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?

ሌሎችን እንድናከብር የሚረዳ ሕግ

ኢየሱስ “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው፤ ኦሪትም፣ ነቢያትም በዚህ ይጠቃለላሉና” በማለት የሰጠውን ትምህርት ብዙዎች በሰብዓዊ ግንኙነት ረገድ በጣም የታወቀ መመሪያ እንደሆነ ይቆጥሩታል። (ማቴዎስ 7:12) ብዙውን ጊዜ ወርቃማው ሕግ በመባል የሚጠራው ይህ ሕግ አንድ ግለሰብ መከበር እንደሚፈልግ ሁሉ እርሱም ሌሎችን እንዲያከብር የሚያበረታታ ነው።

ከታሪክ መመልከት እንደሚቻለው ሰዎች ይህን ሕግ በተግባር ላይ ከማዋል ይልቅ ተቃራኒውን ማድረግ ይቀናቸዋል። ሃሮልድ (እውነተኛ ስሙ አይደለም) የተባለ አንድ ሰው “ሰውን ማዋረድ ደስታ ይሰጠኝ ነበር” በማለት ተናግሯል። አክሎም “ሰዎችን ጥቂት ቃላት በመናገር ብቻ ግራ አጋባቸው እንዲሁም እንባቸው እስኪመጣ ድረስ አሳፍራቸው ነበር” ብሏል። ይሁን እንጂ ሃሮልድ ሌሎችን በሚይዝበት መንገድ ላይ ለውጥ እንዲያደርግ የረዳው አንድ ነገር ተፈጠረ። “ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ያነጋግሩኝ ጀመር። የተናገርኳቸውን ነገሮች እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ እነርሱን የያዝኩበትን መንገድ መለስ ብዬ ሳስበው ያሳፍረኛል። ነገር ግን እነዚህ ክርስቲያኖች ተስፋ አልቆረጡም፤ ቀስ በቀስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልቤን ስለነካው እንድቀየር አደረገኝ።” ዛሬ ሃሮልድ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል።

“የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል” ለሚለው ቃል እውነተኝነት ሃሮልድ ሕያው ምሥክር ነው። (ዕብራውያን 4:12) የአምላክ ቃል የሰዎችን ልብ የመንካት ብሎም አስተሳሰብንና ባሕርይን የመለወጥ ኃይል አለው። ሌሎችን ለማክበር ቁልፍ የሆነው ነገር፣ ሰዎችን ከመጉዳት ይልቅ ለመርዳት እንዲሁም ከማዋረድ ይልቅ ክብራቸውን ለመጠበቅ ልባዊ ፍላጎት ማዳበር ነው።—የሐዋርያት ሥራ 20:35፤ ሮሜ 12:10

ሁሉም ሰው የሚከበርበት ጊዜ ይመጣል

የይሖዋ ምሥክሮች ከላይ የተገለጸው ዓይነት ዝንባሌ ስላላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን አስደሳች ተስፋዎች ለሌሎች ይናገራሉ። (የሐዋርያት ሥራ 5:42) ለአንድ ሰው ‘መልካም ዜና ከማብሰር’ የበለጠ ክብር ማሳየት የሚቻልበት የተሻለ መንገድ የለም። (ኢሳይያስ 52:7) ይህ “መልካም ዜና” ሌሎችን የማዋረድን “ክፉ ምኞት” በመግደል “አዲሱን ሰው” መልበስን ይጨምራል። (ቈላስይስ 3:5-10) በተጨማሪም ይህ “መልካም ዜና” ይሖዋ የሰውን ክብር የሚያዋርዱ ሁኔታዎችንና ዝንባሌዎችን እንዲሁም የችግሩ ጠንሳሽ የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስን በቅርቡ ለማስወገድ ያለውን ዓላማ ያጠቃልላል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ ራእይ 20:1, 2, 10) “ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ” ስትሞላ የሰው ልጅ በሙሉ ክብር ይኖረዋል።—ኢሳይያስ 11:9

ስለዚህ አስደሳች ተስፋ ይበልጥ እንድትማር እንጋብዝሃለን። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አብረህ የምትሰበሰብ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ሰዎችን ለማክበር እንዴት እንደሚረዳ ትመለከታለህ። እንዲሁም በቅርቡ የአምላክ መንግሥት “የሰው ልጅ ለዘላለም ክብሩ የማይነካበት አዲስና ከሁሉ የተሻለ ዓለም” እንዴት እንደሚያመጣ መማር ትችላለህ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በአቋማቸው በመጽናት ክብራቸውን ጠብቀዋል

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከ2,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት ናዚ ወደ ሠራቸው የማጎሪያ ካምፖች ተልከው ነበር። በራቨንስብሩክ ካምፕ ታስረው የነበሩት ጌማ ለ ጎርዲያ ግለክ የተባሉ ሴት ማይ ስቶሪ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ስላሳዩት ጽናት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “በአንድ ወቅት ላይ ጌስታፖዎች ማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እምነቱን ቢክድና ይህንንም ለማሳየት በተዘጋጀለት ቅጽ ላይ ቢፈርም ነጻ መውጣት እንደሚችል ብሎም ከዚያ በኋላ ስደት እንደማይገጥመው ተናግረው ነበር።” እምነታቸውን መካዳቸውን በሚገልጸው ቅጽ ላይ ለመፈረም ፈቃደኛ ያልሆኑትን በተመለከተ ደግሞ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “መከራን ለመቀበልና ነጻ የሚወጡበትን ጊዜ በትዕግሥት ለመጠበቅ ቆርጠዋል።” እንዲህ ያለውን አቋም እንዲወስዱ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? በመጀመሪያው ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱትና በአሁኑ ወቅት በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ማግዳሌና “ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ መገኘት ማንኛውንም መሥዋዕትነት ከፍሎ በሕይወት ከመቆየት ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው” በማለት ምክንያቱን ተናግረዋል። አክለውም “ለእኛ በአቋማችንን መጽናት ማለት ክብራችንን መጠበቅ ማለት ነው” ብለዋል። a

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስለ ኩሰሮ ቤተሰብ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት መስከረም 1, 1985 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 10-15 እንዲሁም ፐርፕል ትራያንግልስ የተባለውን የቪዲዮ ፊልም ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የፈወሳቸውን ሰዎች አክብሯቸዋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች “መልካም ዜና” በማብሰር ሰዎችን ያከብራሉ