በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልታጠራቅመው ስለማትችል በሚገባ ተጠቀምበት

ልታጠራቅመው ስለማትችል በሚገባ ተጠቀምበት

ልታጠራቅመው ስለማትችል በሚገባ ተጠቀምበት

ጊዜ ወርቅ ነው። ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር በተደጋጋሚ ጊዜ ይሰማል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ጊዜ ከወርቅም ሆነ ከሌሎች ቁሳዊ ነገሮች በጣም ይለያል። ወደፊት ይጠቅመኛል ብለህ በማሰብ ወርቅን፣ ገንዘብን፣ ምግብንና ነዳጅን ወይም ሌሎች በርካታ ነገሮችን እንደምታጠራቅመው ጊዜን ልታጠራቅመው አትችልም። ጊዜን ሳይጠቀሙበት በመቅረት ለማጠራቀም የሚደረግ ማንኛውም ጥረት ከንቱ ነው። በቀን ውስጥ ስምንት ሰዓት ያህል ከተኛህ በኋላ የቀረውን ጊዜ ምንም ሳትሠራበት ልታጠራቅመው ብትሞክር ምን ይሆናል? በቀኑ መጨረሻ ላይ በጥቅም ላይ ያልዋሉት ሰዓታት ሁሉ ባክነው ይቀራሉ።

ጊዜን ከአንድ ትልቅ ወራጅ ወንዝ ጋር ልናነጻጽረው እንችላለን። ወራጅ ውኃ ሁልጊዜ የሚፈሰው ወደፊት ብቻ ነው። ወንዙን ልታቆመውም ሆነ የሚፈሰውን እያንዳንዱን ጠብታ ምንም ሳይባክን ልትጠቀምበት አትችልም። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት፣ ሰዎች በውኃ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ሽክርክሪቶችን በወንዝ ዳርቻዎች ላይ ተከሉ። በእነዚህ ሽክርክሪቶች አማካኝነት ከወራጁ ውኃ ያመነጩትን ኃይል ወፍጮዎችንና የእንጨት መሰንጠቂያዎችን እንዲሁም ፓምፖችንና የብረት መቀጥቀጫ መዶሻዎችን ለማንቀሳቀስ ተጠቅመውበታል። አንተም በተመሳሳይ ጊዜን ለማጠራቀም ከመሞከር ይልቅ ጠቃሚ ሥራ ለማከናወን ልትጠቀምበት ትችላለህ። ይሁን እንጂ እንዲህ ለማድረግ ሁለቱን ቀንደኛ የጊዜ ሌባዎች መቋቋም ይኖርብሃል። እነዚህም ዛሬ ነገ ማለት እና ከእርሱ ጋር የሚዛመደው ኮተት ማብዛት ናቸው። ዛሬ ነገ የማለትን አባዜ እስቲ እንመልከት።

ዛሬ ነገ የማለትን አባዜ አስወግድ

‘ዛሬ ማከናወን የምትችለውን ነገር ለነገ አታሳድረው’ የሚል የታወቀ አባባል አለ። ይሁንና አንዳንድ ሰዎች ይህን አባባል ‘ለዛሬ ሳምንት ማቆየት የምትችለውን ነገር ለነገ አታስተላልፈው’ በማለት ሊያስተካክሉት ይሞክራሉ። ወሳኝ የሆነ አንድ ሥራ ሲያጋጥማቸው ለሌላ ጊዜ በማስተላለፍ ለመገላገል ይሞክራሉ። “ዛሬ ነገ ማለት” የሚለው ሐረግ “አንድን ነገር ሆነ ብሎ የማዘግየት ልማድ፤ መከናወን ያለበትን ነገር ሆነ ብሎ ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ” ተብሎ ተተርጉሟል። ዛሬ ነገ የሚል ሰው ነገሮችን ማዘግየት ልማድ ሆኖበታል። ውጥረትና ጭንቀት እየበዛበት ሲመጣ ሥራውን ለሌላ ጊዜ በማስተላለፍ እፎይ ለማለት ይሞክራል። ከዚያም ውጥረቱ እንደገና አይሎ እስኪያስጨንቀው ድረስ አዲስ ባገኘው “ነጻ ጊዜ” ዘና ይላል።

አንዳንድ ጊዜ በአካላዊና በስሜታዊ ሁኔታችን የተነሳ የተወሰነውን፣ ሌላው ቀርቶ ሁሉንም ሥራችንን እንኳ ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ግድ ሊሆንብን ይችላል። በተጨማሪም እያንዳንዱ ሰው ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው አልፎ አልፎ ማረፍ ይኖርበታል። የአምላክ ልጅ እንኳ ሳይቀር እረፍት አስፈልጎት ነበር። ኢየሱስ በአገልግሎቱ በጣም የተጠመደ ቢሆንም እርሱም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ አረፍ የሚሉበት ጊዜ እንዲኖራቸው ያደርግ ነበር። (ማርቆስ 6:31, 32) እንዲህ ዓይነቱ ፋታ ጠቃሚ ነው። ዛሬ ነገ ማለት ግን ከዚህ የተለየ ነገር ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም ጎጂ ነው። አንድ ምሳሌ እንውሰድ።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ተማሪ የሒሳብ ፈተና ለመውሰድ ሦስት ሳምንት ቀርቷታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በርካታ ደብተሮችንና መጽሐፎችን መከለስ ይኖርባታል። በመሆኑም ጭንቅ ብሏታል። ዛሬ ላድርገው ነገ ከሚል ስሜት ጋር ስትታገል ከቆየች በኋላ መጨረሻ ላይ ተሸነፈች። ትምህርቷን ከማጥናት ይልቅ ቴሌቪዥን ትመለከት ጀመር። ፈተናውን ለማለፍ ማጥናት ያለባትን ነገር ለሚቀጥለው ቀን ማስተላለፏን ቀጠለች። በመጨረሻም በፈተናው ዋዜማ ምሽት ላይ ማጥናት የሚኖርባትን ሁሉ በአንድ ቀን ለማንበብ ተገደደች። ጠረጴዛዋ አጠገብ ቁጭ ብላ ማስታወሻ ደብተሮቿንና መጽሐፎቿን ማንበብ ጀመረች።

በዚህ ሁኔታ ሰዓታት አለፉ። ሌሎቹ የቤተሰቧ አባላት ድብን ያለ እንቅልፍ በወሰዳቸው ሰዓት እርሷ ግን የተለያዩ ፎርሙላዎችን ለመሸምደድ ትታገል ነበር። በሚቀጥለው ቀን ለፈተና ስትቀርብ፣ የዛለው አእምሮዋ ሊመልስ ከማይችላቸው ጥያቄዎች ጋር መፋጠጥ ጀመረች። በኋላም ውጤቷ ዝቅተኛ በመሆኑ በሒሳብ ትምህርት ወደቀች። ትምህርቱን እንደገና መውሰድ የሚኖርባት ከመሆኑም ሌላ ወደሚቀጥለው ክፍል ላትዘዋወር ትችላለች።

ይህች ተማሪ ዛሬ ነገ ማለቷ ከባድ ኪሳራ ላይ እንደጣላት እሙን ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ልጅቷ የደረሰባትን ሁኔታ ለማስወገድ የሚረዳ መሠረታዊ ሥርዓት ይዟል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ጥበብ እንደ ሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 5:15, 16) እዚህ ላይ ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸውን ለማከናወን ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት እያሳሰባቸው ነው። ሆኖም ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት ወሳኝ በሆኑ በርካታ የሕይወት ዘርፎች ላይ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ አንድን ሥራ መቼ ማከናወን እንዳለብን መወሰን ስለምንችል ምቹ አሊያም ተገቢ የሆነውን ጊዜ ከመረጥን አጥጋቢ ውጤቶችን ማግኘትም ሆነ ሥራችንን አቀላጥፈን መጨረስ እንችላለን። ጥቅሱ እንደሚያሳየን አመቺ የሆነውን ጊዜ የሚመርጡ ሰዎች “ጥበበኞች” ናቸው።

ለወጣቷ ተማሪ ትምህርቷን ለማጥናት ምቹ የሆነው ጊዜ መቼ ነበር? በየቀኑ ማታ ማታ ለ15 ደቂቃ ያህል ብታጠና ኖሮ ትምህርቷን ቀስ በቀስ መሸፈን ትችል ነበር። እንዲህ ብታደርግ ኖሮ በጥሩ እንቅልፍ ልታሳልፈው የሚገባትን ሌሊት ስታጠናበት ባላደረች ነበር። በፈተናው ዕለት አርፋና ዝግጁ ሆና መገኘት የምትችል ከመሆኑም ሌላ ጥሩ ውጤትም ታመጣ ነበር።

ስለዚህ አንድ ሥራ ሲሰጥህ አመቺ የሆነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ወስን፤ ከዚያም በወሰንከው ጊዜ አከናውነው። እንዲህ ካደረግህ ዛሬ ነገ የማለትን አባዜ ማስወገድም ሆነ የሚያስከትላቸውን መዘዞች ማስቀረት ትችላለህ። በተጨማሪም በሚገባ ባከናወንከው ሥራ እርካታ ታገኛለህ። በተለይ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንደሚሰጡን ኃላፊነቶች ያሉ የሌሎችን ሕይወት የሚነኩ ሥራዎች በሚኖሩን ጊዜ እንዲህ ማድረጋችን ይበልጥ አስፈላጊ ነው።

ኮተት አታብዛ

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ውድ ጊዜያችንን በአግባቡ ለመጠቀም የሚረዳን ሁለተኛው ዘዴ ኮተት ማስወገድ ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው ዕቃዎችን ማስተካከል፣ ጥቅም ላይ ማዋል፣ ማጽዳት፣ አንድ ቦታ ላይ ማስቀመጥ እንዲሁም ፈልጎ ማግኘት ጊዜ ይወስዳል። ዕቃዎች በበዙ ቁጥር ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋል። አንድን ሥራ ባልተጨናነቀና ባልተዝረከረከ ቤት ውስጥ ከማከናወን ይልቅ ዕቃዎች ባጣበቡት ክፍል ውስጥ መሥራት ጊዜ የሚያባክን ከመሆኑም በላይ ያሰለቻል። ከዚህም በላይ ዕቃዎች እየበዙ በሄዱ ቁጥር የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት የሚወስድብን ጊዜም እየጨመረ ይመጣል።

የቤት አያያዝ ባለሙያዎች እንደተናገሩት ሰዎች በጽዳት ላይ ከሚያሳልፉት ጊዜ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሚቃጠለው “የተዝረከረኩ ነገሮችን በማስተካከልና ቦታ በማስያዝ እንዲሁም ቆሻሻ በማስወገድ ነው።” ይህ ሁኔታ በሌሎቹ የሕይወታችን ዘርፎች ላይም ይከሰታል። ስለዚህ ጊዜህን በሚገባ የመጠቀም ፍላጎት ካለህ በዙሪያህ የሚገኙትን ነገሮች አጢን። ቤትህ በኮተት ብዛት ተጨናንቋል? እንደ ልብህ ወዲያ ወዲህ እንዳትልስ እንቅፋት ሆኖብሃል? ከሁሉም የከፋው ደግሞ፣ ጊዜህን እያባከነብህ ይሆን? ሁኔታው እንዲህ ከሆነ አላስፈላጊ ነገሮችን አስወግድ።

አላስፈላጊ ነገሮችን ማስወገድ ቀላል ላይሆን ይችላል። የምትወዳቸውን ሆኖም የማያስፈልጉህን ዕቃዎች መጣል፣ አንድ ወዳጅህን የማጣት ያህል ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። ታዲያ አንድን ዕቃ መጣል ይኑርብህ አይኑርብህ መወሰን የምትችለው እንዴት ነው? አንዳንድ ሰዎች የሚከተለውን ሕግ ይጠቀማሉ:- አንድን ነገር ለአንድ ዓመት ያህል ካልተጠቀምክበት ጣለው። ከአንድ ዓመት በኋላም ለመጣል የምታመነታ ከሆነስ? ለተጨማሪ ስድስት ወራት አስቀምጠው። ከዚያም ዕቃውን ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ ያህል እንዳልተጠቀምክበት ስታውቅ ዕቃውን ለመጣል ብዙም አትቸገርም። ያም ሆነ ይህ ዋናው ቁም ነገር ኮተቶችህን ቀንሰህ ጊዜህን በአግባቡ መጠቀምህ ነው።

እርግጥ ነው፣ ኮተት ማብዛት በአንድ ሰው ቤት ውስጥ ወይም የሥራ ቦታ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ልማድ አይደለም። ኢየሱስ፣ አንድ ሰው ምሥራቹን ተቀብሎ ፍሬ ‘እንዳያፈራ’ የአምላክን ‘ቃል ስለሚያንቁበት ስለዚህ ዓለም ጭንቀትና የብልጽግና ሐሳብ’ ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 13:22) የአንድ ሰው ሕይወት በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተጨናነቀ ከመሆኑ የተነሳ ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆኑትን መንፈሳዊ ነገሮች ለማከናወንና ሚዛኑን ጠብቆ ለመመላለስ የሚያስፈልገውን ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል። በዚህ ምክንያት መንፈሳዊ ቀውስ ሊገጥመው ይችላል፤ በመጨረሻም እውነተኛ እርካታና ደስታ የሚያስገኝለትን ሥራ ለማከናወን ዘላለማዊ የሆነ ጊዜ ወደሚያገኝበት ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ሳይገባ ይቀራል።—ኢሳይያስ 65:17-24፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

አንተስ የግድ ማድረግ ይኖርብኛል ብለህ የምታስባቸውን ነገሮች ለማከናወን ስትል ሁልጊዜ ፕሮግራምህን የማሸጋሸግ ልማድ አለህ? እነዚህ ጉዳዮች ከሥራህ፣ ከቤትህ፣ ከመኪናህ፣ ከመዝናኛና ከማኅበራዊ ጉዳዮችህ እንዲሁም ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ልማድህና በትርፍ ጊዜህ ከምታከናውናቸው ነገሮች ወይም ከተለያዩ ፍላጎቶችህ ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ከሆነ፣ ለመንፈሳዊ ነገሮች ተጨማሪ ጊዜ እንድታገኝ ኮተትህን እንዴት መቀነስ እንደምትችል ማሰብ ያስፈልግሃል።

በብዙዎች ዘንድ የተለመደው ሌላው አባባል ደግሞ ‘ጊዜ ቆሞ አይጠብቅም’ የሚለው ነው። ወራጅ ወንዝ ሳያቋርጥ እንደሚፈስ ሁሉ፣ ጊዜም እንዲሁ ያለማቋረጥ ይነጉዳል። ወደኋላ ሊመለስም ሆነ ሊጠራቀም ስለማይችል አንዴ ካመለጠህ አመለጠህ ነው። ያም ሆኖ ግን አንዳንድ ቀላል የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተከትለን ተግባራዊ እርምጃዎችን ከወሰድን፣ ጊዜያችንን ዘላለማዊ ጥቅም የሚያስገኝልንን ብሎም “ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና” የሚያመጣውን “ከሁሉ የሚሻለውን” ነገር ለማከናወን ልንጠቀምበት እንችላለን።—ፊልጵስዩስ 1:10, 11

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ወራጅ ወንዝ ሁሉ ጊዜም ጠቃሚ ሥራ ለማከናወን መዋል ይችላል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትምህርቷን ለማጥናት ምቹ የሆነው ጊዜ መቼ ነበር?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተዝረከረከ ቤት ውስጥ መሥራት ጊዜ የሚያባክን ከመሆኑም ባሻገር አድካሚ ነው