በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማቅ መልበስና መንፈሳዊነት

ማቅ መልበስና መንፈሳዊነት

ማቅ መልበስና መንፈሳዊነት

የፈረንሳዩ ንጉሥ ሉዊስ ዘጠነኛ ማቅ ይለብሱ ነበር። ሰር ቶማስ ሞር የሕግ ትምህርት እያጠኑ በነበሩበት የወጣትነት ዕድሜያቸው ለበርካታ ወራት በቀን ውስጥ ከ19-20 የሚደርሱ ሰዓታትን በጥናት ሊያሳልፉ የቻሉት ማቅ በመልበሳቸው ነበር። እንዲያውም ሰር ቶማስ ሞር አብዛኛውን የሕይወታቸውን ክፍል ማቅ በመልበስ ይታወቃሉ። እንዲሁም የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ቶማስ ቤኬት ካንተርበሪ በሚገኝ አንድ ካቴድራል ውስጥ በተገደሉበት ወቅት ከልብሳቸው ሥር ማቅ ለብሰው እንደነበር ታይቷል። እነዚህ በታሪክ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው? ማቅ ለብሰው የገዛ አካላቸውን በማሠቃየት ሥጋዊ ፍላጎቶቻቸውን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገዋል።

ማቅ ከእንስሳት ጠጉር የሚሠራ የሚኮሰኩስ ልብስ ሲሆን ከውስጥ በሚለበስበት ጊዜ ቆዳን እየፈገፈገ የሕመም ስሜት ስለሚፈጥር ምቾት አይሰጥም። ከዚህም በላይ ለቅማል መራቢያነት አመቺ ነው። ቶማስ ቤኬት ከእንስሳት ጠጉር የተሠራ ልብስና የውስጥ ሱሪ ይጠቀሙ ስለነበር የለበሱት ማቅ “ተባይ እስኪወርሰው ድርስ” ራሳቸውን ጥለው እንደነበር ይነገራል። ከ16ኛው መቶ ዘመን በኋላ አንዳንድ ሰዎች ከእንስሳት ጠጉር የሚሠራውን ማቅ በቀጫጭን እሾሃማ ሽቦ በተሠራ ልብስ መተካት ጀመሩ። በዚህ መልክ የተሠራው ልብስ ለባሹን ይበልጥ ያሠቃየው ነበር።

አንድ መዝገበ ቃላት የራስን አካል ለማሠቃየት እንደሚያገለግሉ ሌሎች መንገዶች ሁሉ ማቅ የሚለበስበትም ዓላማ “ኃጢአተኛ የሆነውን ሥጋችንን ምኞት ለማሸነፍና በምትኩ አምላክን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ ሕይወት ለመምራት” እንደሆነ ተናግሯል። ይህን ልብስ ባሕታውያን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ሰዎችም ሌላው ቀርቶ በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያሉ ጭምር ይለብሱታል። ዛሬም ቢሆን አንዳንድ ሃይማኖታዊ ሥርዓተ ማኅበራት ማቅ የመልበስ ልማድ አላቸው።

ማቅ መልበስ ወይም ሰውነት የሚያስፈልገውን ነገር በመንሳት ራስን እያሠቃዩ መጽናት አንድን ሰው መንፈሳዊ ያደርገዋል? በፍጹም፤ መንፈሳዊ ሰው መሆን እነዚህን ነገሮች በማድረግ ላይ የተመካ አይደለም። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ተግባር ማለትም ‘ሰውነትን መጨቈንን’ አውግዟል። (ቈላስይስ 2:23) a በተቃራኒው እውነተኛ መንፈሳዊነት የሚገኘው ስለ አምላክ እውቀት ለማግኘት የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናትና ያገኙትንም እውቀት በሕይወት ውስጥ በተግባር ላይ በማዋል ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እንዲህ ስለመሰለው ድርጊት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት:- ጥበብ ለማግኘት ቁልፉ ብሕትውና ነው?” የሚል ርዕስ የያዘውን የጥቅምት 8, 1997 (እንግሊዝኛ) ንቁ! መጽሔት ተመልከት።

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከላይ፣ ንጉሥ ሉዊስ ዘጠነኛ:- ግሬት ሜን ኤንድ ፌመስ ዉሜን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ፤ መሃል፣ ቶማስ ቤኬት:- ራይድፓዝስ ሂስትሪ ኦፍ ዘ ወርልድ (ጥራዝ 4) ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ፤ ከታች፣ ቶማስ ሞር:- 1904 ከታተመው ሂሮስ ኦፍ ዘ ሪፎርሜሽን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ