በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓመታት በኋላ ቤተሰባችን አንድ ሆነ!

ከዓመታት በኋላ ቤተሰባችን አንድ ሆነ!

የሕይወት ታሪክ

ከዓመታት በኋላ ቤተሰባችን አንድ ሆነ!

ሱሚኮ ሂራኖ እንደተናገረችው

ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት መንገድ ያገኘሁ ሲሆን ባለቤቴም በዚህ ጎዳና አብሮኝ እንዲጓዝ እፈልግ ነበር። ምኞቴ የተሳካው ግን ከአርባ ሁለት ዓመታት በኋላ ነው።

በ1951 ከባለቤቴ ጋር ስንጋባ 21 ዓመቴ ነበር። በአራት ዓመታት ውስጥ ሁለት ወንዶች ልጆች የወለድን ሲሆን በሁሉም አቅጣጫ ደስተኛ ሕይወት ያለኝ ይመስል ነበር።

በ1957 አንድ ቀን ታላቅ እህቴ፣ ሚስዮናዊ ሆና የምታገለግል አንዲት የይሖዋ ምሥክር እየመጣች እንደምታወያያት ነገረችኝ። እህቴ ቡድሂስት ብትሆንም እንኳ ከሚስዮናዊቷ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች፤ እኔም መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና ስታበረታታኝ ተስማማሁ። ፕሮቴስታንቶች ጋር እሄድ ስለነበር ለይሖዋ ምሥክሮቹ ስህተታቸውን አሳያቸዋለሁ ብዬ አሰብኩ።

ብዙም ሳይቆይ ግን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለኝ እውቀት በጣም አነስተኛ መሆኑን ተረዳሁ። የምሰበሰብበት ቤተ ክርስቲያን ይሖዋ በሚለው ስም ሲጠቀም ሰምቼ ስለማላውቅ ሚስዮናዊቷን “ይሖዋ ማን ነው?” ብዬ ጠየቅኋት። ዳፍኒ ኩክ (በኋላ ላይ ዳፍኒ ፔቲት) የተባለችው ይህች ሚስዮናዊት ኢሳይያስ 42:8ን [NW] ጠቅሳ ሁሉን የሚችለው አምላክ ስሙ ይሖዋ መሆኑን አሳየችኝ። ዳፍኒ መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ጥያቄዎቼን ሁሉ መለሰችልኝ።

ወደ ቤተ ክርስቲያናችን አገልጋይ ሄድኩና ተመሳሳይ ጥያቄዎች አቀረብሁለት። እሱም “ጥያቄ መጠየቅ ኃጢአት ነው። የተነገረሽን ዝም ብለሽ ተቀበይ” አለኝ። ጥያቄ መጠየቁ ስህተት እንደሆነ ባይሰማኝም ለስድስት ወራት ያህል በየሳምንቱ እሁድ ጠዋት ወደዚህ ቤተ ክርስቲያን እሄድና ከሰዓት በኋላ ደግሞ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እገኝ ነበር።

በትዳሬ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ

ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩት ነገር በጣም ስላስደሰተኝ ለባለቤቴ ለካዙሂኮ አካፍለው ጀመር። በእያንዳንዱ ጥናትና ስብሰባ ላይ የተማርኩትን ነገር እነግረው ነበር። ውሎ አድሮ ግን በመካከላችን “ነፋስ” ገባብን። ካዙሂኮ የይሖዋ ምሥክር እንድሆን አልፈለገም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን መማሬ በጣም ያስደስተኝ ስለነበር ጥናቴንም ሆነ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያለኝን ግንኙነት ቀጠልኩ።

ምሽት ላይ ስብሰባ በሚኖረኝ ጊዜ ከመሄዴ በፊት ለካዙሂኮ የሚወዳቸውን ምግቦች ባዘጋጅለትም እርሱ ግን ውጭ ወጥቶ መብላት ጀመረ። ከስብሰባ ስመለስ ጠባዩ የሚለወጥ ከመሆኑም ሌላ ያኮርፋል። ከሁለት ከሦስት ቀናት በኋላ ጠባዩ እየተሻሻለ ሲመጣ ደግሞ ቀጣዩ ስብሰባ ይደርሳል።

በዚህ ወቅት ከባለቤቴ ቤተሰብ ውስጥ በርካታ ሰዎችን በሞት የቀጠፈው የሳንባ ነቀርሳ በሽታ ያዘኝ። ካዙሂኮ በጣም ከመጨነቁ የተነሳ ሲሻለኝ የፈለግሁትን ሁሉ ማድረግ እንደምችል ነገረኝ። የጠየቅሁት ነገር ወደ ሳምንታዊ ስብሰባዎች ስሄድ ቅር እንዳይሰኝብኝ ብቻ ነበር። እርሱም በጉዳዩ ተስማማ።

ከበሽታዬ ለማገገም ስድስት ወራት የወሰደብኝ ሲሆን በዚህ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት አጠናሁ። አንድ ስህተት ባገኝ ጥናቴን ወዲያውኑ አቆማለሁ በሚል ስሜት የይሖዋ ምሥክሮች በሚሰጡት ትምህርት ላይ ስህተት መፈላለግ ጀመርኩ። ይሁንና አንድም ስህተት አላገኘሁም። ከዚህ ይልቅ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ስህተት ግልጽ ሆኖ ታየኝ። የይሖዋን ፍቅርም ሆነ ፍትሕ የተገነዘብኩ ከመሆኑም ሌላ ከሕግጋቱ ጋር ተስማምቶ መኖር ምን ጥቅም እንዳለው ተረዳሁ።

ከተሻለኝ በኋላ ባለቤቴ ቃሉን በመጠበቅ ወደ ስብሰባዎች ስሄድ መቃወሙን አቆመ። በመንፈሳዊ ማደጌን የቀጠልኩ ሲሆን ግንቦት 1958 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። ቤተሰቤም እውነተኛውን አምላክ አብሮኝ የሚያመልክበትን ጊዜ እናፍቅ ጀመር።

ልጆቼ በመንፈሳዊ እንዲያድጉ መርዳት

ወደ ስብሰባ ስሄድም ሆነ በስብከቱ ሥራ ላይ ስካፈል ልጆቼ ሁልጊዜ አብረውኝ ይሆኑ ነበር፤ ያም ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እያደጉ መሆናቸውን ያስተዋልኩት አንዳንድ ሁኔታዎች በተከሰቱ ጊዜ ነው። አንድ ቀን የስድስት ዓመቱ ልጄ ማሳሂኮ ደጅ ወጥቶ እየተጫወተ እያለ በድንገት ኃይለኛ ድምፅና የሰው ጩኸት ሰማሁ። አንዲት ጎረቤቴ ወደ እኔ እየሮጠች መጥታ ልጄ በመኪና መገጨቱን እየጮኸች ነገረችኝ። ሞቶ ይሆን? ብዬ አሰብኩ። ራሴን ለማረጋጋት እየጣርኩ በፍጥነት ወደ ውጭ ወጣሁ። የተጨራመተውን ብስክሌቱን ስመለከት ሰውነቴ መንቀጥቀጥ ጀመረ፤ ይሁን እንጂ ወደ እኔ ሲመጣ ብዙም እንዳልተጎዳ ተመለከትኩ። እላዬ ላይ ተጠምጥሞ “እማዬ፣ ይሖዋ ረድቶኛል አይደል?” አለኝ። በሕይወት እንደተረፈልኝ ስመለከትና እነዚህን አስደሳች ቃላት ስሰማ አለቀስኩ።

በሌላ ቀን ደግሞ አገልግሎት ላይ እያለን አንድ አረጋዊ ሰው “ይህን ትንሽ ልጅ እንዲህ እንዲያደርግ ስታስገድጂው ምንም አይሰማሽም? ልጁ በጣም ያሳዝናል” ሲሉ ጮኹብኝ። ገና መልስ ሳልሰጣቸው የስምንት ዓመቱ ልጄ ቶሞዮሺ “አባባ፣ እናቴ እንድሰብክ አላስገደደችኝም። እኔ የምሰብከው ይሖዋን ማገልገል ስለምፈልግ ነው” አላቸው። በዚህ ጊዜ ሰውየው በግርምት ከመመልከት በቀር ምንም ማለት አልቻሉም።

ከመንፈሳዊ ነገሮች አንጻር ልጆቼ አባት አልነበራቸውም። እኔ ራሴም ብዙ ማወቅ ቢያስፈልገኝም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለልጆቼ የማስተማሩ ኃላፊነት የወደቀው በእኔ ላይ ነበር። ፍቅሬን፣ ቅንዓቴንና እምነቴን በማሳደግ ምሳሌ ሆኜ ለመገኘት እጥር ነበር። በየቀኑ በልጆቼ ፊት ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። በስብከቱ ሥራ ላይ ያገኘኋቸውን ተሞክሮዎች እነግራቸዋለሁ። ይህ ደግሞ ያበረታታቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ፣ አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆኑት ለምን እንደሆነ ሲጠየቁ “እናታችን አቅኚ ሆና በማገልገሏ ደስተኛ ነበረች፤ እኛም ደስተኞች መሆን ስለፈለግን ነው” የሚል መልስ ሰጥተዋል።

አባታቸውንም ሆነ በጉባኤ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም ሰው ላለመንቀፍ በጣም እጠነቀቅ ነበር። ሐሜት በልጆቼ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተገንዝቤ ነበር። ለተነቀፈው ሰው ብቻ ሳይሆን ለነቃፊውም ጭምር አክብሮት ያጣሉ።

ለመንፈሳዊ እድገት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን መቋቋም

በ1963 ባለቤቴ ለሥራ ወደ ታይዋን በመዛወሩ ቤተሰባችን ወደዚያ ሄደ። በዚህ ወቅት ባለቤቴ፣ ታይዋን ለሚገኙት ጃፓናውያን መስበክ ከጀመርኩ ችግር ልፈጥር እንደምችል ነገረኝ። ወደ ጃፓን ተመልሰን እንድንሄድ ሊያደርጉን እንደሚችሉና ይህ ደግሞ በሚሠራበት ድርጅት ላይ ችግር እንደሚያመጣ ገለጸልኝ። ባለቤቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንዳንገናኝ ፈልጎ ነበር።

ታይዋን ውስጥ ሁሉም ስብሰባዎች የሚካሄዱት በቻይንኛ ነበር። በዚያም ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልን። በታይዋን ላሉት ጃፓናውያን ከመስበክ ይልቅ ለአገሬው ሰዎች መመሥከር እንድችል ቻይንኛ ለመማር ወሰንኩ። በዚህ መንገድ ባለቤቴ ያሳሰበውን ችግር ማስቀረት ቻልኩ።

ከታይዋን ወንድሞች ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት ጥንካሬ ሰጥቶናል። ሃርቬይ እና ካቲ ሎጋን የተባሉ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት ይህ ነው የማይባል እርዳታ አድርገውልናል። ወንድም ሎጋን ለልጆቼ በመንፈሳዊ አባት ሆነላቸው። ይሖዋን ማገልገል ማለት ደስታ የሌለበትና የማያፈናፍን ሕይወት አለመሆኑን አስገንዝቧቸዋል። ልጆቼ ይሖዋን ለማገልገል ውሳኔ ያደረጉት በታይዋን እያሉ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።

ቶሞዮሺና ማሳሂኮ ታይዋን በሚገኘው የአሜሪካውያን ትምህርት ቤት ስለገቡ እንግሊዝኛና ቻይንኛ ተማሩ። ይህ ትምህርት ደግሞ እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ለማገልገል ዝግጁ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይሖዋ በጣም አስቸጋሪ ሊሆንብን የሚችለውን በታይዋን ያሳለፍነውን ጊዜ ዘላቂ በረከት እንድናገኝበት ስላደረገልን ከልብ በመነጨ ስሜት አመሰግነዋለሁ። በታይዋን ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ያህል ከቆየን በኋላ አስደሳች ትዝታ ይዘን ወደ ጃፓን ተመለስን።

በዚህ ጊዜ ልጆቼ እየጎረመሱ ስለነበር ነጻነት መፈለግ ጀመሩ። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች አንስቼ ከእነርሱ ጋር በመወያየት በርካታ ሰዓታት አሳልፍ ነበር፤ ይሖዋም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ረዳታቸው ሆኗል። ቶሞዮሺ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ አቅኚ ሆነ። አቅኚ በሆነባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ውስጥ አራት ሰዎች ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ ረድቷል። ማሳሂኮም የታላቅ ወንድሙን ፈለግ በመከተል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰ አቅኚ ሆነ። ማሳሂኮ አቅኚ በሆነባቸው የመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ አራት ወጣቶች የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሆኑ ረድቷል።

ይሖዋ ልጆቼን አብልጦ ይባርካቸው ጀመር። ቶሞዮሺ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ካስተማርኳት አንዲት ሴት ባለቤት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። የእነዚህ ባልና ሚስት ሁለት ሴት ልጆችም የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። በኋላ ላይ ቶሞዮሺ ታላቅየዋን ኖቡኮን ያገባ ሲሆን ማሳሂኮ ደግሞ ታናሽዋን ማሳኮን አገባ። አሁን ቶሞዮሺና ኖቡኮ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ እያገለገሉ ነው። ማሳሂኮ እና ማሳኮ ደግሞ በፓራጓይ ሚስዮናውያን ሆነው ያገለግላሉ።

ባለቤቴ ቀስ በቀስ ለውጥ አሳየ

ባለቤቴ ባለፉት ዓመታት ሁሉ ለእምነታችን ምንም ግድ የሌለው ቢመስልም ለውጥ እንዳደረገ የሚያሳዩ አንዳንድ ሁኔታዎችን መመልከት ጀመርን። ሌሎች ሲቃወሙኝ ለእምነቴ የሚከራከር ከመሆኑም በላይ ሳይታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ደግፎ ይናገር ነበር። በችግር ላይ ላሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ቁሳዊ እርዳታ ያደርግ ነበር። ሁለተኛው ልጃችን ሲያገባ በሰጠው አጭር ንግግር ላይ እንዲህ ብሏል:- “ትክክለኛውን የሕይወት መንገድ ለሰዎች ማስተማር ከሁሉ የላቀ ሥራ ነው። የዚያኑ ያህል ደግሞ በጣም ከባድ ነው። ልጆቼና ባለቤቶቻቸው በሕይወታቸው ውስጥ ይህን ከባድ ሥራ ለማከናወን መርጠዋል። እርዳታችሁ እንዳይለያቸው እለምናችኋለሁ።” እነዚህ ሁኔታዎች ባለቤቴ ይሖዋን አብሮን ማገልገሉ አይቀርም ብዬ እንዳስብ አድርገውኛል።

የእምነት ባልንጀሮቼ ቤት መጥተው አብረውት እንዲጫወቱ ዝግጅት አደርግ ጀመር። በሳምንታዊውና በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ እንዲሁም በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኝ እጋብዘው ነበር። ሥራ የሌለው ጊዜ እያመነታም ቢሆን በእነዚህ በስብሰባዎች ላይ ይገኛል። ብዙ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ይስማማል በሚል ስሜት ክርስቲያን ሽማግሌዎችን እጋብዛለሁ። ይሁን እንጂ ለማጥናት ፈቃደኛ አልሆነም። ችግሩ ምን ላይ እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም።

በዚህ ጊዜ የሚከተሉት የሐዋርያው ጴጥሮስ ቃላት ትዝ አሉኝ:- “ሚስቶች ሆይ፤ . . . ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ አንዳንድ ለቃሉ የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው አኗኗር ተማርከው ይመለሳሉ፤ ይህም የሚሆነው ንጹሕና ፍጹም አክብሮት የተሞላውን ኑሮአችሁን ሲመለከቱ ነው።” (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ይህን ምክር ሁልጊዜ በተግባር ላይ አውዬዋለሁ ማለት እንደማልችል ተገነዘብኩ። ስለዚህ ሙሉ በሙሉ እንድሠራበት መንፈሳዊነቴን ማሳደግ ነበረብኝ።

የበለጠ መንፈሳዊ ሰው ለመሆን ስል በ1970 አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። አሥር ብሎም 20 ዓመታት አለፉ። ያም ሆኖ ባለቤቴ በመንፈሳዊ ረገድ ያሳየው አንድም ለውጥ አልነበረም። በአንድ ወቅት አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ “የገዛ ባለቤትሽን እንኳ መርዳት እያቃተሽ ሌሎችን ለመርዳት የምታደርጊው ጥረት ከባድ ሳይሆን አይቀርም” አለችኝ። ይህ ንግግር ተስፋ የሚያስቆርጥ ቢሆንም ጥረቴን አላቋረጥኩም።

በ1980ዎቹ መገባደጃ ላይ ወላጆቻችን በጣም አርጅተው ስለነበር እነርሱን እየተንከባከብኩ ሌሎች ሥራዎቼን መወጣት አድካሚ ብሎም ውጥረት የሚፈጥር ነበር። ለበርካታ ዓመታት እምነቴን የተቃወሙ ቢሆንም በጣም እንደምወዳቸው ለማሳየት የተቻለኝን ሁሉ እጥር ነበር። እናቴ በ96 ዓመቷ ሕይወቷ ከማለፉ በፊት “ሱሚኮ፣ ትንሣኤ የማገኝ ከሆነ የአንቺን ሃይማኖት እከተላለሁ” አለችኝ። በዚህ ወቅት ልፋቴ መና እንዳልቀረ ተገነዘብኩ።

ባለቤቴ ወላጆቻችንን ለመርዳት ያደረግሁትን ጥረት ሁሉ አስተውሎ ነበር። ለዚህም ያለውን አድናቆት ለማሳየት በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ጀመረ። ለበርካታ ዓመታት በስብሰባዎች ላይ ቢገኝም ምንም ዓይነት መንፈሳዊ እድገት አላደረገም። ያም ቢሆን እርሱን ለማስደሰት የማደርገውን ጥረት ቀጠልኩበት። ጓደኞቹን ሌላው ቀርቶ ከውጭ አገር የመጡ የሥራ ባልደረቦቹን እንኳ እቤታችን ምግብ አዘጋጅቼ እጋብዛቸው ነበር። እንዲሁም አብሬው እዝናና ነበር። አቅኚዎች በወር ውስጥ እንዲያሟሉት የሚጠበቅባቸው ሰዓት ወደ 70 ሲወርድ ከእሱ ጋር የበለጠ ጊዜ ማሳለፍ ጀመርኩ።

ባለቤቴ ጡረታ መውጣቱ ለውጥ አመጣ

በ1993 ባለቤቴ ጡረታ ወጣ። አሁን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ጊዜ ይኖረዋል ብዬ አሰብኩ። ሆኖም ጊዜ ስላለው ብቻ አምላክን ለማምለክ መነሳሳቱ አምላክን ማቃለል እንደሚሆን ነገረኝ። ከዚህ ይልቅ አምላክን የሚያመልከው ልቡ ባነሳሳው ጊዜ ስለሆነ እንዳልገፋፋው ጠየቀኝ።

አንድ ቀን ካዙሂኮ፣ ቀሪውን ሕይወቴን እርሱን ለማስደሰት ማዋል እችል እንደሆነ ጠየቀኝ። ከተጋባንበት ጊዜ ጀምሮ የምችለውን ሁሉ አድርጌለት ስለነበር ይህ አባባሉ በጣም አሳዘነኝ። እርሱን ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረት አደርግ የነበረ ቢሆንም ሕይወቴን ይሖዋን ለማገልገል ብቻ እንዳዋልኩት ተሰማው። በጉዳዩ ላይ ለተወሰነ ጊዜ ካሰብኩበት በኋላ ከዚህ በላይ ምንም ላደርግለት እንደማልችል ነገርኩት። ያም ሆኖ ግን በምሄድበት ጎዳና አብሮኝ የሚጓዝ ከሆነ ለተወሰኑ ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም የሚዘልቅ አስደሳች ሕይወት መጀመር እንደምንችል ነገርኩት። ለተወሰኑ ቀናት ያህል ምንም መልስ ሳይሰጠኝ ቆየ። በመጨረሻም “ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን አብረሽኝ ታጠኛለሽ?” ብሎ ጠየቀኝ። እነዚህን ቃላት ባስታወስኩ ቁጥር ልቤ በሐሴት ይሞላል።

መጀመሪያ ላይ ከአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ዝግጅት ባደርግም “ከአንቺ ጋር ካልሆነ በቀር ከማንም ጋር አላጠናም” አለኝ። ስለዚህ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርን። ቻይንኛ ጉባኤ ስለምካፈልና ባለቤቴም ይህን ቋንቋ አቀላጥፎ ስለሚናገር የምናጠናው በቻይንኛ ነበር። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስን ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አብረን አንብበን ጨረስን።

በዚህ ጊዜ በቻይንኛ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አንድ የጉባኤ ሽማግሌና ባለቤቱ አሳቢነት ያሳዩን ጀመር። በዕድሜ ከልጆቻችን ቢያንሱም እውነተኛ ጓደኞች ሆኑን። ሌሎች በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችም ለባለቤቴ የሚሰጡት ትኩረት የተለየ ነበር። ጥሩ መስተንግዶ የሚያደርጉልን ከመሆኑም በላይ ካዙሂኮን ልክ እንደ አባታቸው ያወያዩት ነበር። ይህ ደግሞ በጣም አስደሰተው።

በአንድ ወቅት አንድ የጉባኤያችን አባል ሲያገባ በባለቤቴ ስም የሠርግ መጋበዣ ወረቀት ደረሰን። የቤተሰቡ ራስ መሆኑን በመገንዘብ ወረቀቱን በእርሱ ስም መላካቸው በጥልቅ ስለነካው በሠርጉ ላይ ለመገኘት ወሰነ። ወዲያውኑም ከይሖዋ ምሥክሮቹ ጋር የተግባባ ሲሆን ከአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘቱ እንዲሁም ለጉባኤው የነበረው ፍቅር ጥሩ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ረድተውታል።

በመጨረሻም ቤተሰባችን አንድ ሆነ

ባለቤቴ፣ ታኅሣሥ 2000 ላይ ራሱን ለይሖዋ መወሰኑን በጥምቀት አሳየ። ልጆቼና ባለቤቶቻቸው በዚህ ዘመን የተፈጸመውን ይህን “ተአምር” ለመመልከት ከሩቅ ቦታ መጡ። አርባ ሁለት ዓመታት ቢወስድም በስተመጨረሻ ቤተሰባችን አንድ ሆነ።

አሁን ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ከባለቤቴ ጋር በዕለቱ ጥቅስ ላይ የምንወያይ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስንም አብረን እናነባለን። በየቀኑ መንፈሳዊ ውይይቶችን በማድረግና በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በመካፈል እንደሰታለን። በአሁኑ ጊዜ ባለቤቴ የጉባኤ አገልጋይ ሲሆን በቅርብ ጊዜም በቻይንኛ የሕዝብ ንግግር አቅርቧል። ይሖዋ አንድ እንድንሆን ስላደረገን አመሰግነዋለሁ። በጣም ከምወዳቸው ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ ጋር ሆኜ የይሖዋን ስምና ሉዓላዊነቱን ለዘላለም የማወድስበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቻይና

የኮሪያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ

ኮሪያ ሪፑብሊክ

የጃፓን ባሕር

ጃፓን

ቶኪዮ

የምሥራቅ ቻይና ባሕር

ታይዋን

ታይፔ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተጠመቅሁበት ዓመት፣ በ1958 ከቤተሰቤ ጋር

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከቶኪዮ ወደ ታይፔ በተዛወርንበት ወቅት እንደ ሃርቬይ እና ካቲ ሎጋን ያሉ ወዳጆቻችን በመንፈሳዊ አበረታትተውናል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዛሬ ቤተሰባችን በእውነተኛው አምልኮ አንድ ሆኗል