“በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን”
“በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን”
“የካቶሊክ እምነት አራት የመጨረሻ ዕጣዎች እንዳሉ ይገልጻል:- ሞት፣ ፍርድ፣ ሲኦልና ሰማይ።”—የካቶሊክ እምነት፣ በጆርጅ ብራንትል የተዘጋጀ
የሰው ዘር የመጨረሻ ዕጣዎች ናቸው ከተባሉት ነገሮች መካከል ምድር አለመጠቀሷን ልብ በል። እንደ ሌሎች በርካታ ሃይማኖቶች ሁሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም፣ አንድ ቀን ምድር ትጠፋለች ብላ ስለምታምን ይህ መሆኑ አያስደንቅም። ዲክስዮኔር ደ ቴኦሎዢ ካቶሊክ የተባለው መዝገበ ቃላት ይህን ጉዳይ አስመልክቶ “የዓለም መጨረሻ” በሚለው ርዕስ ሥር የሚከተለውን አስፍሯል:- “የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው ዓለም አምላክ እንደፈጠረውና አሁን እንዳለው ሆኖ እስከ መጨረሻው እንደማይቀጥል ታምናለች፤ ይህንንም ታስተምራለች።” በቅርቡ የወጣ የካቶሊክ ሃይማኖት ትምህርቶችን የሚያብራራ አንድ ጽሑፍ “ዓለማችን . . . መጥፋቱ አይቀርም” ብሏል። ታዲያ ፕላኔታችን የምትጠፋ ከሆነ ምድር ገነት እንደምትሆን የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ እንዴት ይፈጸማል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ወደፊት ገነት እንደምትሆን በግልጽ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ምድርና ነዋሪዎቿን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ኢሳይያስ 65:21, 22) እነዚህን ተስፋዎች ከአምላክ የተቀበሉት አይሁዳውያን፣ በአንድ ወቅት መላዋ ምድር ለሰው ዘር ዘላቂ ጥቅም የምታስገኝ ገነት መሆኗ እንደማይቀር እርግጠኞች ነበሩ።
ፍሬውንም ይበላሉ። ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ፣ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይረዝማል፤ እኔ የመረጥኋቸው፣ በእጃቸው ሥራ ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37 ይህ ተስፋ መፈጸሙ እንደማይቀር ያረጋግጣል። “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ” ይላል። (መዝሙር 37:11) ይህ ጥቅስ እስራኤላውያን ለጊዜው ወደ ተስፋይቱ ምድር ስለመመለሳቸው ብቻ የሚገልጽ አይደለም። ይኸው መዝሙር “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ሁኔታውን ግልጽ ያደርገዋል። (መዝሙር 37:29) a መዝሙሩ፣ በምድር ላይ ለዘላለም መኖር “ገሮች” ወይም የዋህ የሆኑ ሰዎች የሚያገኙት ስጦታ እንደሆነ መናገሩን ልብ በል። በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተጻፈ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በዚህ ጥቅስ ላይ ያለውን “ገሮች” ወይም የዋሆች የሚለውን ቃል ሲያብራራ እንደሚከተለው ብሏል:- “በተለያዩ ትርጉሞች ውስጥ ከተሰጠው ትርጉም የበለጠ ሰፋ ያለ ፍቺ አለው። ይህም ምስኪኖችን፣ ለያህዌህ ሲሉ ለመከራ ወይም ለስደት የተዳረጉትን እንዲሁም ለአምላክ ተገዥ የሆነ ትሑት ልብ ያላቸውን ያጠቃልላል።”
በምድር ወይስ በሰማይ?
ከላይ ያሉት ጥቅሶች ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” በማለት የተናገረውን አባባል ያስታውሱናል። (ማቴዎስ 5:5) አሁንም በድጋሚ፣ ምድር ታማኝ ለሆኑ ሰዎች የምትሰጥ ዘላቂ ስጦታ እንደሆነች ተጠቅሷል። ይሁንና ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ‘በአባቱ ቤት’ ስፍራ እንደሚያዘጋጅላቸውና ከእርሱ ጋር በሰማይ እንደሚኖሩ ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 14:1, 2፤ ሉቃስ 12:32፤ 1 ጴጥሮስ 1:3, 4) ታዲያ በምድር ስለሚኖሩት በረከቶች የሚናገረውን ተስፋ እንዴት ልንመለከተው ይገባል? በዛሬው ጊዜ ስለ እነዚህ በረከቶች መነገሩ አስፈላጊ ነው? ተፈጻሚነታቸውን የሚያገኙትስ በእነማን ላይ ነው?
በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን በመዝሙር 37 ላይ የሚገኘውም ሆነ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የጠቀሰው “ምድር” ምሳሌያዊ እንደሆነ ይናገራሉ። ፉልክራ ቪገረ፣ ቢብል ደ ግሌር በተባለው መጽሐፍ ላይ እነዚህ ጥቅሶች “የሰማይና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ” እንደሆኑ ገልጸዋል። ፈረንሳዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ ማሪ-ዦሴፍ ላግራንዥ ደግሞ ይህ ተስፋ “የዋሆች፣ የሚኖሩበትን ምድር አሁን ባለበት ሁኔታም ይሁን ወደፊት ፍጹም የሆነ አገዛዝ ሰፍኖበት ሊወርሱት እንደሚችሉ የሚያሳይ ሳይሆን ቦታው የትም ይሁን የት የዋሆች መንግሥተ ሰማያትን እንደሚወርሱ የሚያመለክት ነው” ብለዋል። አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እነዚህ ጥቅሶች “በምድር ላይ ያሉትን ነገሮች በመጠቀም ሰማይን ለማመልከት የተሠራባቸው ምሳሌያዊ አነጋገሮች” ናቸው የሚል እምነት አለው። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎች ደግሞ እንዲህ ይላሉ:- “ተስፋይቱ ምድር ወይም ከነዓን መንፈሳዊ ትርጉም ያላት ስትሆን እርሷም የዋሆች የሚወርሷትን በሰማይ ያለች አገር ማለትም የአምላክን መንግሥት ታመለክታለች። መዝሙር 37ም ሆነ ሌሎች ጥቅሶች የሚናገሩት ስለዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ነው።” ታዲያ፣ አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ የሰጣቸው ተስፋዎች ግዑዟን ምድር አያካትቱም ብለን በችኮላ መደምደማችን ተገቢ ነው?
አምላክ ለምድር ያለው ዘላለማዊ ዓላማ
ገና ከጅምሩ ምድር፣ አምላክ ለሰው ልጆች ካለው ዓላማ ጋር በጥብቅ ተቆራኝታለች። መዝሙራዊው “ሰማየ ሰማያት የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 115:16) በመሆኑም አምላክ ለሰው ልጆች ያለው የመጀመሪያ ዓላማ ከሰማይ ሳይሆን ከምድር ጋር የተያያዘ ነው። ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት የኤድንን የአትክልት ስፍራ በማስፋት መላውን ምድር ገነት የማድረግ ተልእኮ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) ይህ ዓላማ ጊዜያዊ አልነበረም። ይሖዋ ምድር ለዘላለም ጸንታ እንደምትኖር ሲገልጽ በቃሉ ላይ የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጥቷል:- “ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—መክብብ 1:4፤ 1 ዜና መዋዕል 16:30፤ ኢሳይያስ 45:18
አምላክ ሉዓላዊ በመሆኑና ቃሉ እንደሚፈጸም ዋስትና በመስጠቱ መቼም ቢሆን ዓላማው ከግብ መድረሱ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች መፈጸማቸው እንደማይቀር ለማስረዳት ተፈጥሯዊውን የውኃ ዑደት እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀማል። “ዝናምና በረዶ ከሰማይ ወርዶ፣ ምድርን በማራስ፣ እንድታበቅልና እንድታፈራ ለዘሪው ዘር፣ ለበላተኛም እንጀራ እንድትሰጥ ሳያደርግ፣ ወደ ላይ እንደማይመለስ ሁሉ፣ ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ [የአምላክ ቃል]፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።” (ኢሳይያስ 55:10, 11) አምላክ ለሰው ልጆች ቃል ገብቶላቸዋል። እነዚህ ቃላት የሚፈጸሙበት ጊዜ ሊዘገይ ቢችልም ከንቱ ሆነው ግን አይቀሩም። ከዚህ ይልቅ የተላኩበትን ዓላማ ፈጽመው ወደ እርሱ ‘ይመለሳሉ።’
እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ምድርን ለሰው ልጆች በመፍጠሩ ደስ ተሰኝቷል። በመሆኑም የፍጥረት ሥራውን ባጠናቀቀበት በስድስተኛው ቀን ላይ ሁሉም ነገር “እጅግ መልካም” እንደነበረ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 1:31) ምድር ለዘለቄታው ወደ ገነትነት የመለወጧ ሂደት እስካሁን ድረስ ፍጻሜውን ያላገኘ የመለኮታዊው ዓላማ ክፍል ነው። ሆኖም አምላክ የገባው ቃል ‘በከንቱ ወደ እርሱ አይመለስም።’ የሰው ልጆች ሰላምና ደኅንነት አግኝተው ለዘላለም እንደሚኖሩ የሚገልጹትን ጨምሮ በምድር ላይ ስለሚኖረው ፍጹም ሕይወት የተነገሩት ተስፋዎች በሙሉ ይፈጸማሉ።—መዝሙር 135:6፤ ኢሳይያስ 46:10
የአምላክ ዓላማ ያለምንም እንከን ይፈጸማል
የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት፣ አምላክ ምድርን ገነት ለማድረግ ያወጣው የመጀመሪያ ዓላማ ለጊዜው እንዲስተጓጎል አድርገዋል። እነዚህ ወላጆቻችን ለመታዘዝ እምቢተኛ በመሆናቸው ከኤድን የአትክልት ስፍራ ተባረሩ። በመሆኑም ምድርን ፍጹማን በሆኑ ሰዎች የተሞላች ገነት ለማድረግ አምላክ ያወጣው ዓላማ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አስተዋጽኦ የማድረግ መብት አግኝተው የነበረ ቢሆንም ይህን መብታቸውን አጡ። ሆኖም አምላክ ዓላማውን ለመፈጸም ሌላ ዝግጅት አደረገ። እንዴት?—ዘፍጥረት 3:17-19, 23
በኤድን ውስጥ የተከሰተው ሁኔታ እጅግ ማራኪ በሆነ አካባቢ ቤቱን መገንባት ከጀመረ ሰው ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሰውየው የቤቱን መሠረት ገንብቶ እንደጨረሰ አንድ ሌላ ሰው መጥቶ የሠራውን ሁሉ አፈረሰበት እንበል። ይህ ሰው የጀመረውን ግንባታ እርግፍ አድርጎ ከመተው ይልቅ ቤቱ ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉትን አንዳንድ አስፈላጊ እርምጃዎች ይወስዳል። ይህ ተጨማሪ ሥራ ሌላ ወጪ ቢጠይቅበትም የሥራው መስተጓጎል የፕሮጀክቱን ትክክለኛነት አጠያያቂ አያደርገውም።
በተመሳሳይም፣ አምላክ ዓላማው መፈጸሙ እንደማይቀር ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አንዳንድ ዝግጅቶችን አድርጓል። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በኃጢአት ከወደቁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ለልጆቻቸው ተስፋ የሚሆንና የደረሰውን ጉዳት የሚያስወግድ ‘ዘር’ እንደሚመጣ አስታወቀ። ቆየት ብሎም ይህን ትንቢት ከፍጻሜ የሚያደርሰው ዘር ዋነኛ ክፍል፣ የሰው ልጆችን ለመዋጀት ወደ ምድር በመምጣት ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ የሰጠው የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ መሆኑ ግልጽ ሆነ። (ገላትያ 3:16፤ ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በመንግሥቱ ላይ ነግሦአል። በመሆኑም የዋህ የሆነው ኢየሱስ፣ በሰማይ በሚገኘው መንግሥት ተባባሪ ገዢዎች ለመሆን ትንሣኤ ካገኙት ታማኝ ሰዎች ጋር ሆኖ ምድርን በቀዳሚነት ይወርሳል። (መዝሙር 2:6-9) ከጊዜ በኋላ ይህ መንግሥት የአምላክን የመጀመሪያ ዓላማ ከግብ ለማድረስና ፕላኔታችንን ወደ ገነትነት ለመለወጥ ምድርን ይቆጣጠራል። ከዚያም ስፍር ቁጥር የሌላቸው የዋህ የሆኑ ሰዎች፣ ኢየሱስ ክርስቶስና ተባባሪ ገዥዎቹ ነገሥታት የሆኑበት መንግሥት ከሚያስገኘው በረከት ተካፋዮች በመሆን “ምድርን ይወርሳሉ።”—ዘፍጥረት 3:15፤ ዳንኤል 2:44፤ የሐዋርያት ሥራ 2:32, 33፤ ራእይ 20:5, 6
“በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን”
ሐዋርያው ዮሐንስ ከጥፋት የሚድኑ ሰዎች የሚያገኟቸውን ሁለት ዓይነት ተስፋዎች በራእይ አይቷል። ከክርስቶስ ታማኝ ደቀ መዛሙርት መካከል ተመርጠው በሰማይ በዙፋን ላይ የተቀመጡ ነገሥታትን ተመልክቷል። መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ ተባባሪዎች የሆኑት እነዚህ ሰዎች ‘በምድር ላይ እንደሚነግሡ’ በግልጽ ይናገራል። (ራእይ 5:9, 10) በመሆኑም የአምላክ ዓላማ ፍጻሜ ጥምር ገጽታ እንዳለው ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስና ተባባሪ ወራሾቹ በሚያስተዳድሯት ሰማያዊ መንግሥት አማካኝነት ምድር ዳግም እንደምትታደስ ልብ በል። እነዚህ መለኮታዊ ዝግጅቶች አምላክ ካወጣው የመጀመሪያ ዓላማ ጋር በሚስማማ መልኩ ምድር ገነት እንድትሆን ያደርጋሉ።
ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ ደቀ መዛሙርቱን የአምላክ ፈቃድ “በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ምድር የምትጠፋ ቢሆን ወይም ደግሞ የሰማይ ምሳሌ ብትሆን ኖሮ እነዚህ ቃላት ትርጉም ይኖራቸዋል? ሁሉም ጻድቃን ወደ ሰማይ ቢሄዱስ? አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ከፍጥረት ዘገባ አንስቶ እስከ ራእይ መጽሐፍ ድረስ ባሉት የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎች ውስጥ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል። አምላክ እንዳሰበው ምድር ገነት ትሆናለች። ይህ አምላክ እፈጽመዋለሁ ብሎ ቃል የገባው ፈቃዱ ነው። በምድር ላይ የሚኖሩ ታማኝ ሰዎችም ይህ ፈቃዱ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ይጸልያሉ።
ፈጣሪያችን የሆነውና ‘የማይለወጠው’ አምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። (ሚልክያስ 3:6፤ ዮሐንስ 17:3፤ ያዕቆብ 1:17) መጠበቂያ ግንብ የተባለው ይህ መጽሔት መለኮታዊው ዓላማ ፍጻሜ እንዲያገኝ የሚያስችሉትን እነዚህን ሁለት ገጽታዎች ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት ሲያሳውቅ ቆይቷል። ይህም ዳግም የምትታደሰውን ምድር አስመልክቶ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተሰጡትን ተስፋዎች እንድንገነዘብ ይረዳናል። በመሆኑም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመወያየት ወይም የዚህ መጽሔት አዘጋጆች ወደሆኑት ሰዎች በመጻፍ ጉዳዩን ጠለቅ ብለህ እንድትመረምር እናበረታታሃለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ኤሬትስ የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል “ምድር” በማለት ፋንታ “መሬት” ብለው ስለተረጎሙት ብቻ መዝሙር 37:11, 29 ላይ የሚገኘው ኤሬትስ የሚያመለክተው ለእስራኤላውያን የተሰጣቸውን ውስን መሬት ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም። በዊልያም ዊልሰን የተዘጋጀ ኦልድ ቴስታመንት ዎርድ ስተዲስ የተባለ መጽሐፍ ኤሬትስ ለሚለው ቃል እንዲህ የሚል ፍቺ ሰጥቶታል:- “በደፈናው ሲታይ ቃሉ ሰዎች የሚኖሩበትንም ሆነ የማይኖሩበትን መላውን ምድር የሚያመለክት ሲሆን በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ አንድን የተወሰነ የምድር ክፍል፣ መሬት ወይም አገር ለማመልከት ተሠርቶበታል።” በመሆኑም የዕብራይስጡ ቃል ዋነኛ ፍቺ የሚያመለክተው ፕላኔታችንን ወይም መላዋን ምድር ነው።—የጥር 1, 1986 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 31ን ተመልከት።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ ምድራችን ዳግም ገነት እንደምትሆን በግልጽ ይናገራል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምድር የምትጠፋ ከሆነ የኢየሱስ የናሙና ጸሎት ትርጉም ይኖረዋል?