በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዕድሜ ቢገፉም ብቸኝነት አላጠቃቸውም

በዕድሜ ቢገፉም ብቸኝነት አላጠቃቸውም

በዕድሜ ቢገፉም ብቸኝነት አላጠቃቸውም

ብዙ ሰዎች ዕድሜያቸው ሲገፋ አቅማቸው እየደከመና ከኅብረተሰቡ እየተገለሉ ይሄዳሉ። በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ ይኖሩ የነበሩትና በ95 ዓመታቸው ያረፉት የፌርናንድ ሪቮሮል ሁኔታ ግን ከዚህ ይለያል። ባለቤታቸው በሞት ከተለዩዋቸውና ሴት ልጃቸው አግብታ የራሷን ኑሮ ከመሠረተች ጀምሮ ብቻቸውን ኖረዋል። ብዙውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከቤታቸው ሳይወጡ ቢሆንም ብቸኛ ግን አልነበሩም። አብዛኛውን ጊዜ ሳሎናቸው ውስጥ ተቀምጠው ስልክ በመደወል ከሰዎች ጋር መንፈሳዊ ጭውውቶችን ያደርጋሉ።

ፌርናንድ ባሳለፉት አስደሳች ሕይወት ውስጥ ቃል በቃል ከሰው ተገልለው የኖሩባቸው ጊዜያት ነበሩ። እንዴት? ፌርናንድና ባለቤታቸው የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ ብዙም ሳይቆይ በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ ፈነዳ። በዚህ ጊዜ ፌርናንድ ሌሎችን ላለመጉዳት ሲሉ በወሰዱት ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋም ጸኑ። በዚህም ምክንያት ከሥራቸው የተባረሩ ሲሆን ከባለቤታቸውና ከትንሿ ሴት ልጃቸው ተለይተው በጠቅላላው ለአምስት ዓመት ተኩል ያህል በእስር ለማሳለፍ ተገደዋል።

ፌርናንድ ሁኔታውን መለስ ብለው በማስታወስ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ብዙ ሰዎች አስተማማኝ የሆነውን ሥራዬን በመተው ቤተሰቦቼን ያለ ደጋፊ እንዳስቀረኋቸው ሆኖ ይሰማቸው ነበር። ሰዎች በጣም ይጠሉኝና እንደ ወንጀለኛም ያዩኝ ነበር። ያም ሆኖ ስለ እነዚያ አስቸጋሪ ዓመታት መለስ ብዬ ባሰብኩ ቁጥር ከሁሉም በላይ ይሖዋ እንዴት አድርጎ ይረዳን እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህ ከሆነ በርካታ ዓመታት ቢያልፉም በይሖዋ ላይ ያለኝ እምነት ግን አሁንም ጠንካራ ነው።”

ይህ ጠንካራ እምነት ፌርናንድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኙትን ተስፋ በስልክ ለሌሎች ሰዎች እንዲያካፍሉ ገፋፍቷቸዋል። ያነጋገሩት ሰው ውይይቱን ለመቀጠል ፈቃደኛ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በፖስታ ቤት በኩል ይልኩለታል። ቆየት ብለውም ለሰውየው በድጋሚ ይደውሉለትና ጽሑፉን አንብቦት እንደሆነ ይጠይቁታል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎቹ የምስጋና ደብዳቤ ይልኩላቸዋል፤ ይህ ደግሞ ፌርናንድን እጅግ ያስደስታቸዋል።

ምናልባት አንተም፣ በአካባቢህ ያለ እንደ ፌርናንድ ዓይነት ሰው ስልክ ደውሎልህ ይሆናል። ይህ ሰው በምን እንደሚያምን ለማወቅ ለምን አታዳምጠውም? የይሖዋ ምሥክሮች የሚያምኑባቸውን ትምህርቶች ሊያካፍሉህ ምንጊዜም ፈቃደኞች ናቸው።