በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውብ በሆነች ደሴት ላይ የታየ አስደሳች እድገት

ውብ በሆነች ደሴት ላይ የታየ አስደሳች እድገት

ውብ በሆነች ደሴት ላይ የታየ አስደሳች እድገት

ጎብኚዎች ልምላሜ የተላበሰችውንና ሞቃታማ አየር ያላትን የታይዋንን ደሴት ሲመለከቱ መደነቃቸው አይቀርም። አረንጓዴ የነበረው የሩዝ ማሳ በመከር ወቅት ወርቃማ መልክ ይኖረዋል። ተራሮቹ ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች ተሸፍነዋል። በከተሞች ውስጥ ካለው መጨናነቅ በተለየ በመስኩና በተራራው ላይ የሚታየው ልምላሜ መንፈስን በእጅጉ የሚያድስ ነው። ደሴቲቷን ያያት የመጀመሪያው ምዕራባዊ ሰው ኢልሃ ፎርሞሳ ወይም “ውቢቷ ደሴት” በሚል ስም የጠራት በዚህ ምክንያት ነው።

አዎን፣ ታይዋን እጅግ ውብ የሆነች ትንሽ ደሴት ናት፤ የታይዋን የቆዳ ስፋት 390 ኪሎ ሜትር በ160 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። አብዛኛው የደሴቲቱ ክፍል ተራራማ ነው። ዩ ሻን (የሞሪሰን ተራራ) ከፍታው በጃፓን ከሚገኘው የፉጂ ተራራ ወይም በኒው ዚላንድ ከሚገኘው የኩክ ተራራ ይበልጣል። በደሴቲቷ መካከል በሚገኙ ተራሮች ዙሪያ እስከ ባሕሩ ዳርቻ ተንጣለው የሚታዩት ሜዳማ ቦታዎች ከ22 ሚሊዮን በላይ በሚሆነው የታይዋን ሕዝብ ተጨናንቀዋል።

መንፈሳዊ እድገት

በታይዋን የሚታየው መንፈሳዊ እድገት ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ይህ ዓይነቱ መንፈሳዊ እድገት ደግሞ ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ሲያውቁ በሚያሳዩት ቅንዓት ይገለጻል። ሌሎች ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው እንዲያውቁ ለመርዳት በቅንዓት የሚሠሩት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደጨመረ መመልከቱ እውነትም አስደናቂ ነው።

እድገት ካለ ደግሞ መስፋፋት ይኖራል። በታኅሣሥ 1990 ሠፊ የሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ለመሥራት የሚያስችል መሬት ተገዛ። በዚያን ጊዜ በታይዋን የነበሩት 1,777 የመንግሥቱ አስፋፊዎች የሚያከናውኑትን ሥራ በበላይነት ለመምራት በታይፔ የነበረው የቀድሞ ሕንጻ በጣም አነስተኛ ነበር። በተለያየ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከዓለም ዙሪያ የመጡና የአገሬው ተወላጆች የሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች ለዓመታት ካከናወኑት ትጋት የታከለበት ሥራ በኋላ በነሐሴ ወር 1994 በሲንዉ የተሠሩት የሚያማምሩ አዳዲስ ሕንጻዎች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። በዚያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ምሥራች የሚሰብኩ ሰዎች ቁጥር 2,515 ደርሶ ነበር። ከአሥር ዓመት በኋላ ቁጥሩ ከእጥፍ በላይ ያደገ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በታይዋን ከ5,500 የሚበልጡ አስፋፊዎች ይገኛሉ፤ ከእነዚህም ውስጥ አንድ አራተኛ የሚሆኑት በየወሩ ሙሉ ጊዜያቸውን በአገልግሎት ያሳልፋሉ። ከእነዚህ መካከል በጠዋት እንደሚታየው መንፈስን የሚያድስ “ጠል” የሆኑት ወጣት ወንዶችና ሴቶች ትኩረት የሚስቡ ናቸው።—መዝሙር 110:3

ልጆች የሚያደርጉት መንፈሳዊ እድገት

የምሥራቹን በቅንዓት ከሚያውጁት አስፋፊዎች መካከል አብዛኞቹ ልጆች ሲሆኑ አንዳንዶቹ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በሰሜናዊ ታይዋን በምትገኝ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት፣ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች እንዴት ማስተማር እንዳለባቸው በሚሠለጥኑበት ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ እንዲገኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጋበዙ። እነዚህ ባልና ሚስት፣ ዌጁን የተባለ አንድ ትንሽ ልጅ መድረክ ላይ ወጥቶ ከብዙ አዋቂዎች በበለጠ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስን አቀላጥፎ ሲያነብ ሲመለከቱ በጣም ተገረሙ። ከዚያም በቀጣዩ ስብሰባ ላይ ሲገኙ፣ ገና ትምህርት ቤት ያልገቡ ልጆች እንኳ የሚሰጡትን ግሩም መልስ ሲሰሙ እጅግ ተደነቁ። ባልና ሚስቱ በመንግሥት አዳራሹ የሚገኙት ልጆች ሥርዓታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አብዛኛው ሕዝብ የቡድሂዝምና የታኦይዝም እምነት ተከታይ በሆነበት በዚህ አገር ውስጥ የሚኖሩት እነዚህ ልጆች ትኩረታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ ያደረጉት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ክርስቲያን የሆኑት ወላጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረጋቸውና ከይሖዋ ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ ያተኮረ ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት በመመሥረታቸው ነው። የዌጁን ወላጆች፣ የቤተሰቡን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና በመስክ አገልግሎት የሚያደርገውን ተሳትፎ አስደሳች ለማድረግ በመጣራቸው የዌጁን ታላቅ ወንድምና እህት የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ለመሆን ችለዋል። ዌጁን በቅርቡ ለሕዝብ በመመሥከሩ ሥራ መሳተፍ ይችል እንደሆነ በጠየቀበት ወቅት እናቱ፣ በዚያን ወር የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ካበረከቷቸው የሚበልጥ ብዛት ያላቸው መጽሔቶችን እንዳበረከተ ገልጻለች። ዌጁን ስለ እውነት መናገር፣ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠትና የተማረውን ነገር ለሌሎች ማካፈል በጣም ያስደስተዋል።

ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ

እነዚህ ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ምን ያደርጋሉ? አብዛኞቹ ለይሖዋም ሆነ ለአገልግሎቱ እውነተኛ ፍቅር ማሳየታቸውን ይቀጥላሉ። ለምሳሌ፣ ህዌፒንግ የተባለችውን ተማሪ እንመልከት። አንድ ቀን የሄማቶሎጂ (በደም ላይ የሚደረግ ምርምር) አስተማሪዋ ማንነታቸውን በውል የማያውቃቸው፣ ደም የማይወስዱ የአንድ ሃይማኖት አባላት እንዳሉ ተናገረ። የትምህርት ክፍለ ጊዜው እንዳበቃ ይህች ወጣት ክርስቲያን ለአስተማሪዋ እነዚህ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑና ይህንን አቋም የሚወስዱበትን ምክንያት አብራራችለት።

ሌላዋ አስተማሪ ደግሞ በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን በተመለከተ የተዘጋጀ የቪዲዮ ፊልም አሳየቻቸው። ፊልሙ 1 ቆሮንቶስ 6:9ን ቢጠቅስም አስተማሪዋ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን እንደማያወግዝ ተናገረች። ህዌፒንግ በዚህ ጊዜም አምላክ ለግብረ ሰዶም ያለውን አመለካከት ለአስተማሪዋ ለማስረዳት ችላለች።

ከህዌፒንግ ጋር አብራ የምትማረው ሹሻ በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጸምን ዓመጽ በተመለከተ ሪፖርት በምታዘጋጅበት ወቅት ህዌፒንግ “ድብደባ ለሚፈጸምባቸው ሴቶች የሚሆን እርዳታ” የሚል ርዕስ ያለውን የታኅሣሥ 2001 ንቁ! መጽሔት ከሰጠቻት በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መረጃዎችን እንደያዘም ነገረቻት። ከጊዜ በኋላ ሹሻ ያልተጠመቀች አስፋፊ ሆነች። በአሁኑ ጊዜ ሹሻና ህዌፒንግ ምሥራቹን ለሌሎች ያካፍላሉ።

በርካታ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመሩ መሆናቸውን በትምህርት ቤት ውስጥ ለማሳወቅ ይቸገራሉ። በተለይ ደግሞ በትንንሽ የገጠር ከተሞች ውስጥ ይህን ማድረግ ይበልጥ ያስቸግራል። ሲሃው በእምነቱና በስብከት እንቅስቃሴው ምክንያት የእኩዮች ተጽዕኖ ያጋጥመዋል። ሲሃው እንዲህ ይላል:- “አገልግሎት ላይ ሆኜ አብረውኝ የሚማሩትን ልጆች እንዳላገኝ እፈራ ነበር። አንዳንድ ጊዜ አሥር የሚሆኑት ተሰብስበው ይቀልዱብኛል!” አንድ ቀን የትምህርት ቤት አስተማሪው ሲሃውን በክፍሉ ለሚገኙት ተማሪዎች ስለ ሃይማኖቱ እንዲናገር ጠየቀው። “ንግግሬን በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ለመጀመር ወሰንኩ፣ ከዚያም ምድርንና በምድር ውስጥ ያሉትን ነገሮች የፈጠረው ማን ነው? የሰው ልጅ እንዴት ተገኘ? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ውይይት ጀመርኩ። ጥቅሶችን እያወጣሁ ማንበብ እንደጀመርኩ አንዳንዶቹ አጉል እምነት እንዳለኝ በመናገር ይስቁብኝ ጀመር። ሆኖም የጀመርኩትን በመቀጠል ንግግሬን አቀረብኩ። ከዚያም እምነታችንንና ሥራችንን በተመለከተ ከአንዳንድ ተማሪዎች ጋር በግል ለመነጋገር አጋጣሚ አገኘሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አብረውኝ የሚማሩ ልጆች አገልግሎት ላይ ሲያዩኝ መቀለዳቸውን አቆሙ!”

ሲሃው በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆኑ ጠዋት ጠዋት በዕለት ጥቅሱ ላይ አብረን እንወያያለን። አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠና ከመሆኑም በላይ በስብሰባዎች ላይ እንገኛለን። አጽናኝ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለሌሎች በምናገርበት ጊዜ ሊያፌዙብኝ የሚሞክሩ ሰዎች ቢያጋጥሙኝም ለመጽናት የቻልኩት በዚህ ምክንያት ነው።”

ቲንግሜ የምትማረው በልጃገረዶች የሙያ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው። አብረዋት ከሚማሩ ልጆችና ከወንዶች ትምህርት ቤት ከመጡ ተማሪዎች ጋር ሽርሽር እንድትሄድ ተጋበዘች። በዚህ ዓይነቱ ዝግጅት ወቅት ከሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ሊያጋጥማት የሚችለውን አደጋ በማስተዋል ላለመሄድ ወሰነች። ምንም እንኳ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች a ከተባለው መጽሐፍ ላይ ግሩም የሆኑ ነጥቦችን አብረዋት ከሚማሩት ልጆች ጋር ብትወያይም በእንዲህ ዓይነቱ ግብዣ ላይ እንድትገኝ ሁልጊዜ ይጠይቋት ነበር። ልጃገረዶቹ፣ ቲንግሜ ኋላ ቀር እንደሆነች በመናገር ያሾፉባት ነበር። ሆኖም ከእነዚህ ልጆች መካከል አንዷ አርግዛ ማስወረዷ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል ጥበብ እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል። ቲንግሜ እንዲህ ትላለች:- “ይሖዋ ለሚሰጠን መመሪያ ታዛዥ መሆኔ ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረኝ አስችሎኛል። በዚህም ምክንያት ውስጣዊ ደስታና ጥልቅ እርካታ ለማግኘት ችያለሁ።”

ለእድገት እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ማሸነፍ

ሬውን የቲንግሜ የቅርብ ጓደኛ ነች። ሬውን ልጅ ሳለች ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መሄድና በመስክ አገልግሎት መካፈል አሰልቺ ሥራ ሆኖባት ነበር። ሆኖም በጉባኤዋ ውስጥ የምታየው እውነተኛ ፍቅርና የክፍል ጓደኞቿ የሚያሳዩት ከአንገት በላይ የሆነ ጓደኝነት ፍጹም ተቃራኒ መሆኑን በመመልከቷ በሕይወቷ ውስጥ ለውጥ ማድረግ እንዳለባት ተሰማት። ሬውን አብረዋት ለሚማሩት ልጆች መመሥከር የጀመረች ሲሆን ምን ማድረግ እንዳለባትም ይበልጥ ተገነዘበች። በወር ውስጥ ከ50 ሰዓት በላይ በአገልግሎት በማሳለፍ ረዳት አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። በኋላም በየወሩ ከ70 ሰዓታት በላይ በማገልገል የዘወትር አቅኚ ሆነች። ሬውን እንዲህ ትላለች:- “ይሖዋ ላደረገልኝ ነገሮች እጅግ አመስጋኝ ነኝ። በእኔ በፍጹም ተስፋ ቆርጦ አያውቅም። ይሖዋን የሚያሳዝኑ ነገሮችን ብፈጽምም ይወደኛል። እናቴም ሆነች በጉባኤያችን የሚገኙ ሌሎች ተመሳሳይ ፍቅር አሳይተውኛል። በአሁኑ ጊዜ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን የምመራ ሲሆን እጅግ አርኪ በሆነ ሥራ ላይ እንደተሰማራሁ ይሰማኛል።”

በአንድ ገጠራማ አካባቢ በሚገኝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሁለት ልጆች ትምህርት ቤቱን ወክለው በባሕላዊ ጭፈራ ውድድር እንዲካፈሉ ተመደቡ። እነዚህ ልጆች ውድድሩ ምን እንደሚመስል ሲያውቁ ግን በእንደዚህ ዓይነቱ ዝግጅት መካፈል ክርስቲያናዊ ሕሊናቸውን እንደሚያቆሽሽ ተሰማቸው። አመለካከታቸውን በማስረዳት በውድድሩ ላለመካፈል ቢጠይቁም ጥያቄያቸው ውድቅ ሆነባቸው። ከዚህ ይልቅ አንድ ጊዜ ስለተመደቡ በውድድሩ ላይ መካፈል እንዳለባቸው አስተማሪዎቹ ነገሯቸው። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች አቋማቸውን ባለማላላት፣ የትምህርት ክፍሉ ድረ ገጽ ውስጥ ገብተው ችግራቸው ምን እንደሆነ በመግለጽ ደብዳቤ ጻፉ። ወጣቶቹ በቀጥታ መልስ ባይሰጣቸውም ብዙም ሳይቆይ ትምህርት ቤቱ ማንንም ተማሪ በእንደዚህ ዓይነቱ ውድድር እንዲሳተፍ ማስገደድ እንደሌለበት የሚገልጽ መመሪያ ደረሰው። እነዚህ ሁለት ልጆች ያገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጠና፣ አስተሳሰባቸውን ከመቅረጽም አልፎ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ጥንካሬ ሰጥቷቸዋል!

የአቅም ገደብ ያለባቸው ሰዎችም ቢሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስን ተስፋ ለሌሎች በማካፈል ደስታ ያገኛሉ። ሚንዩ ከተወለደችበት ጊዜ አንስቶ ሰውነቷን ማንቀሳቀስ አትችልም። ጥቅስ ለማንበብ ስትፈልግ እጆቿን መጠቀም ስለማትችል የመጽሐፍ ቅዱሱን ገጾች በምላሷ ትገልጣለች። ሚንዩ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚሰጧትን ክፍሎች ለበሽተኞች በተዘጋጀ አጠር ያለ አልጋ ላይ ጋደም ብላ ታቀርባለች፤ አብራት የምትመደበው እህት ደግሞ አጭር በርጩማ ላይ ተቀምጣ ማይክሮፎን ትይዝላታለች። ሚንዩ የሚሰጧትን ክፍሎች ለማቅረብ የምታደርገውን ጥረት መመልከት እንዴት የሚያስደስት ነው!

ሚንዩ የመንግሥቱ አስፋፊ ለመሆን ስትፈልግ በጉባኤዋ ውስጥ የሚገኙ እህቶች በስልክ የሚሰጥ ምሥክርነት እንዴት እንደሚከናወን በመማር ሚንዩን ለመርዳት ችለዋል። ሚንዩ የስልኩን ቁጥሮች በምላሷ በመንካት ስትደውል እህቶች ደግሞ ያነጋገረቻቸውን ሰዎች ይመዘግቡላት ነበር። በዚህ ዓይነት በምታከናውነው አገልግሎት በጣም ስለምትደሰት ስለ አምላክ መንግሥት በስልክ በመመሥከር በወር ውስጥ ከ50 እስከ 60 ሰዓታት በማሳለፍ ረዳት አቅኚ ሆና ማገልገል ጀምራለች። ለአንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማበርከት ከመቻሏም ሌላ በስልክ ተመላልሶ መጠየቅ ልታደርግላቸው ችላለች። አሁን፣ በዚህ መልኩ ያገኘቻቸውን ሦስት ግለሰቦች መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናለች።

አዎን፣ በታይዋን በሚገኙ 78 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ መንፈስን እንደሚያድስ ጠል የሆኑ ወጣት ወንዶችና ሴቶች አሉ። እነዚህ ወጣት ምሥክሮች ሕዝብ በበዛባት በዚህች ደሴት ላይ ለሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አድን የሆነውን የመንግሥት ምሥራች በፈቃደኝነትና በቅንዓት እያካፈሉ ነው። “ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣ ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል፤ ከንጋት ማሕፀን፣ በቅዱስ ግርማ ደምቀህ፣ የጐልማሳነትህን ልምላሜ እንደ ጠል ትቀበላለህ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍጻሜውን እያገኘ ሲሆን በታይዋን የታየው እድገት የዚህ ክፍል ነው። (መዝሙር 110:3) እነዚህ ወጣቶች አብረዋቸው ለሚያገለግሉት አረጋውያን የብርታት ምንጭ ሲሆኑ ከሁሉ በላይ ደግሞ በሰማይ ለሚኖረው አባታቸው ለይሖዋ አምላክ የደስታ ምንጭ ናቸው!—ምሳሌ 27:11

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ

በታይዋን የሚገኙ አስፋፊዎች ቁጥራቸው እያደገ በመሆኑ በቂ የመንግሥት አዳራሾች ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሆኗል። ለምን? በአንዳንድ ገጠራማ ቦታዎች ካልሆነ በስተቀር የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት አመቺ የሆነ ቦታ የለም ለማለት ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ የመሬት ዋጋ በጣም ውድ ከመሆኑም ሌላ ከመሬት ጋር በተያያዘ የአገሩ ሕግ ጥብቅ ነው። በትልልቅ ከተሞች ውስጥ ያለው ብቸኛ አማራጭ ለቢሮ ተብለው የተሠሩ ቤቶችን ገዝቶ ወደ መንግሥት አዳራሾች መለወጥ ነው። እንደዚህም ሆኖ አብዛኞቹ ቢሮዎች ዝቅ ያሉ ጣሪያዎች ያሏቸውና ለጥገና ብዙ ወጪ የሚጠይቁ ከመሆናቸውም በላይ ከፍተኛ ጥበቃ ስለሚደረግባቸው በቀላሉ ለመግባት አይቻልም። በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ እነዚህን ቦታዎች የመንግሥት አዳራሾች አድርጎ መጠቀም አመቺ አይደለም።

ያም ቢሆን በቅርብ ዓመታት ውስጥ በታይዋን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በርከት ያሉ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾችን ለማግኘት ችለዋል። የመሬት ዋጋ ቢንርም በታይዋን የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በፈቃደኝነት የገንዘብ መዋጮ ስለሚያደርጉና በግንባታ ሥራ ስለሚሠለጥኑ አዳዲስ ቦታዎችን ለማግኘት የሚያደርጉትን ፍለጋ ቀጥለዋል።