በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በሺው ዓመት ማብቂያ ላይ ከሚኖረው የመጨረሻ ፈተና በኋላ ሰዎች ኃጢአት ሊሠሩና ሊሞቱ ይችላሉ?

በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ጥቅሶች ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጡናል:- “ከዚያም በኋላ ሞትና ሲኦል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ፤ የእሳቱ ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።” (ራእይ 20:14) “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”—ራእይ 21:4

ይህ የተነገረው ስለየትኛው ጊዜ እንደሆነ ልብ በል። “ሞትና ሲኦል” ወደ እሳት ባሕር የሚጣሉት፣ ከአርማጌዶን የተረፉትና ከሞት የተነሱት እንዲሁም ከአርማጌዶን በኋላ የተወለዱት ሰዎች “በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው” ማለትም ይሖዋ በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ የሰው ልጆች እንዲጠብቋቸው በሰጣቸው መሥፈርቶች ተመዝነው ከተፈረደባቸው በኋላ ነው። (ራእይ 20:12, 13) ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ምዕራፍ 21 ላይ በኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ውስጥ ፍጻሜውን የሚያገኝ ሌላም ራእይ ጠቅሷል። ይህ ራእይ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው በሺው ዓመት የፍርድ ቀን መደምደሚያ ላይ ነው። ኢየሱስ መንግሥቱን ለአባቱ ካስረከበ በኋላ፣ ይሖዋ የማንም አማላጅነት ሳያሻው ከሰው ልጆች ጋር ይኖራል። ይሖዋ በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘ከሕዝቦቹ ጋር’ ለዘለቄታው አብሯቸው ይኖራል፤ እንዲሁም የማንም መካከለኛነት ሳያስፈልገው ከሕዝቡ ጋር በቀጥታ መገናኘት ይችላል። የሰው ልጆች ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ በመሆን ፍጽምና ሲላበሱ ‘ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም’ የሚለው ተስፋ ሙሉ ፍጻሜውን ያገኛል።—ራእይ 21:3, 4

በመሆኑም ቀደም ባሉት ጥቅሶች ላይ የተገለጸውና በክርስቶስ ቤዛ የሚሻረው ሞት በአዳም ኃጢአት ምክንያት የመጣው ሞት ነው። (ሮሜ 5:12-21) የሰው ልጆች ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም የወረሱት ሞት ስለሚደመሰስ ልክ አዳም ሲፈጠር የነበረው ዓይነት ሁኔታ ይኖራቸዋል። አዳም ፍጹም ነበር፤ ይህ ማለት ግን በጭራሽ ሊሞት አይችልም ማለት አልነበረም። ይሖዋ ለአዳም “መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 2:17) እዚህ ላይ የተገለጸው፣ ሆን ተብሎ የሚሠራ ኃጢአት የሚያስከትለው ሞት ነው። በሺው ዓመት መደምደሚያ ላይ ከሚኖረው የመጨረሻ ፈተና በኋላም ቢሆን የሰው ልጆች የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ ነጻነት ይኖራቸዋል። (ራእይ 20:7-10) ይሖዋን ለማገልገልም ሆነ ላለማገልገል መምረጥ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ማንም ሰው ከአምላክ ፊቱን አይመልስም ብለን መናገር አንችልም፤ አንዳንዶች ልክ እንደ አዳም ላለመታዘዝ ይመርጡ ይሆናል።

አንድ ሰው ሞትም ሆነ ሲኦል በማይኖሩበት ከመጨረሻው ፈተና በኋላ ባለው ጊዜ በአምላክ ላይ ቢያምጽ ምን ይደርስበታል? በዚህ ጊዜ ከአዳም የተወረሰው ሞት አይኖርም። ከዚህም ባሻገር ሔድስ ማለትም የትንሣኤ ተስፋ ያላቸው ሙታንን የያዘው የሰው ልጆች መቃብርም የለም። ይሁንና ይሖዋ ማንኛውንም ዓመጸኛ የትንሣኤ ተስፋ ወደማያገኝበት የእሳት ባሕር በመጣል ሊያጠፋው ይችላል። ይህ ሞት አዳምና ሔዋን ያጋጠማቸው ዓይነት ሲሆን ሰዎች ከአዳም ከወረሱት ሞት የተለየ ነው።

ያም ሆኖ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል ብለን የምንጠብቅበት ምክንያት አይኖርም። የመጨረሻውን ፈተና የሚያልፉ ሰዎች ከአዳም የሚለያቸው አንድ ትልቅ ነገር አለ። እነዚህ ሰዎች እስከ መጨረሻ ተፈትነዋል። ይሖዋ የሰዎችን ማንነት ሙሉ በሙሉ የሚያጣራ በመሆኑ ይህ ፈተና ምን ያህል የታሰበበት እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። የመጨረሻው ፈተና የመምረጥ ነጻነቱን በአግባቡ የማይጠቀምን ማንኛውንም ሰው ለማስወገድ እንደሚረዳ ልንተማመን እንችላለን። በመሆኑም ከመጨረሻው ፈተና ያለፉ ሰዎች በአምላክ ላይ ሊያምጹና በዚህም ሳቢያ ሊጠፉ ቢችሉም ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የመድረሱ አጋጣሚ ግን እጅግ ጠባብ ነው።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከመጨረሻው ፈተና በኋላ የሰው ልጆች የሚኖሩበት ሁኔታ አዳም ከነበረበት ሁኔታ ጋር ሊወዳደር የሚችለው በምን መልኩ ነው?