በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ

የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ

የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ

“ተፈጥሮ እንደሚለወጥና ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንደሚመለስ አስባለሁ። . . . ሁኔታዎች በአንድ ጀንበር ይስተካከላሉ ብዬ ባልጠብቅም፣ ከረጅም ጊዜ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በሚኖሩበት ወቅት ይህ እንደሚፈጸም ተስፋ አደርጋለሁ።”—ፈረንሳዊው የሥነ ተፈጥሮ ጠበብት ዣን-ማሪ ፔልት

በአካባቢያቸው ያሉት ሁኔታዎችና ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች የሚያስጨንቋቸው ብዙ ሰዎች ፕላኔታችን ወደ ገነትነት ተለውጣ ለማየት ይናፍቃሉ። ሆኖም ይህ ምኞት በ21ኛው መቶ ዘመን ብቅ ያለ ነገር አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ተመልሳ ገነት እንደምትሆን ከረጅም ጊዜ በፊት ተስፋ ሰጥቷል። ኢየሱስ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና”፤ “ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት የተናገራቸው ቃላት መጽሐፍ ቅዱስ ከያዛቸው በጣም የታወቁ አባባሎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። (ማቴዎስ 5:5፤ 6:10) ይሁንና በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙዎች ምድር ገነት ሆና የዋህ በሆኑ ሰዎች ትሞላለች የሚል እምነት የላቸውም። እንዲያውም ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች የገነት ተስፋ ከናካቴው እንደጠፋ ያስባሉ።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንኳ በሰማይም ሆነ በምድር ላይ ይኖራል ስለሚባለው ገነት የነበራት እምነት እየደበዘዘ የሄደበትን ምክንያት አስመልክቶ ላ ቪ የተባለው የፈረንሳይ ሳምንታዊ መጽሔት እንዲህ ብሏል:- “ስለ ገነት የሚገልጹ ሐሳቦች ላለፉት 1,900 ዓመታት በካቶሊክ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ይዘው ከቆዩ በኋላ አሁን ከየገዳማቱ፣ እሁድ እሁድ ከሚሰጠው ስብከት እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምትሰጣቸው ሃይማኖታዊ ኮርሶችና የማስተማሪያ ፕሮግራሞች ውስጥ ጠፍተዋል።” ገነት የሚለው ቃል ራሱ “ምስጢራዊና ግራ የሚያጋባ” እንደሆነ ተደርጎ ስለሚታሰብ “ጥቅጥቅ ባለ ጭጋግ” የተሸፈነ ያህል ሆኗል። አንዳንድ ሰባኪዎች ደግሞ “ብዙውን ጊዜ በምድራዊ ደስታ ላይ ያተኩራል” በሚል ሰበብ ሆን ብለው ቃሉን ላለመጠቀም መርጠዋል።

ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያጠኑት ፍሬዴሪክ ለንዋር የተባሉ ሶሺዮሎጂስት ስለ ገነት የሚነገሩ ሐሳቦች “የተሰለቹ” መሆናቸውን ተናግረዋል። በተመሳሳይም የታሪክ ምሑር የሆኑትና በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ መጻሕፍትን ያዘጋጁት ዣን ዴሉሞ፣ ስለ ገነት የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ቃል በቃል ይፈጸማል ብለው እንደማያስቡ ሲገልጹ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “‘ታዲያ ስለ ገነት ምን ማለት ይቻላል?’ ለሚለው ጥያቄ የክርስትና ትምህርት እንዲህ የሚል መልስ ይሰጣል:- ለአዳኛችን ትንሣኤ ምስጋና ይግባውና አንድ ቀን እጅ ለእጅ ተያይዘን ተስፋችን ሲፈጸም እናያለን።”

ታዲያ በዛሬው ጊዜ፣ ምድራችን ወደ ገነትነት ትለወጣለች የሚለው መልእክት መታወጁ ተገቢ ነው? መጪው ጊዜ ለፕላኔቷ ምድራችን ምን ይዟል? ስለ ወደፊቱ ጊዜ በግልጽ ማወቅ ይቻል ይሆን? ቀጣዩ ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

COVER: Emma Lee/​Life File/​Getty Images