በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጽናትና የታማኝነት ምሳሌ የሆነው ኢዮብ

የጽናትና የታማኝነት ምሳሌ የሆነው ኢዮብ

የጽናትና የታማኝነት ምሳሌ የሆነው ኢዮብ

“አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው የለም።”—ኢዮብ 1:8

1, 2. (ሀ) ኢዮብ ምን ያልታሰቡ አሳዛኝ መከራዎች አጋጥመውት ነበር? (ለ) ኢዮብ እነዚህ አሳዛኝ መከራዎች ሳይደርሱበት በፊት ምን ዓይነት ኑሮ እንደነበረው ግለጽ።

 ሁሉም ነገር የተሟላለት የሚመስል አንድ ሰው ነበር፤ ይህ ሰው ሀብት፣ ክብር፣ ጥሩ ጤንነትና ደስተኛ ቤተሰብ ነበረው። ሆኖም በአንድ ወቅት ሦስት አሳዛኝ ክስተቶች በተከታታይ ደረሱበት። በአንድ ጀንበር ንብረቱን አጣ። ቀጥሎም ከዚያ በፊት ተከስቶ የማያውቅ አውሎ ነፋስ ልጆቹን በሙሉ ገደለበት። ይህ ከሆነ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መጥፎ በሽታ ይዞት መላ ሰውነቱን አቆሳሰለው። ይህ ሰው በስሙ በተሰየመው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ በዋነኝነት የተጠቀሰው ኢዮብ እንደሆነ ገምተህ ይሆናል።ኢዮብ ምዕራፍ 1 እና 2

2 ኢዮብ “ያለፈውንም ወራት ምንኛ ተመኘሁ!” በማለት ምሬቱን ገልጿል። (ኢዮብ 3:3፤ 29:2) መከራ ሲደርስበት ያለፈውን መልካም ጊዜ የማይናፍቅ ማን አለ? ኢዮብ ጥሩ ኑሮ የነበረው ከመሆኑም በላይ መከራ የሚደርስበት አይመስልም ነበር። ታላላቅ ሰዎች ያከብሩትና ምክር ይጠይቁት ነበር። (ኢዮብ 29:5-11) ሀብታም ቢሆንም ለገንዘብ ትክክለኛ አመለካከት ነበረው። (ኢዮብ 31:24, 25, 28) መበለቶች ወይም የሙት ልጆች ተቸግረው ሲያይ ከመርዳት ወደኋላ አላለም። (ኢዮብ 29:12-16) ለትዳር ጓደኛውም ቢሆን ታማኝ ነበር።ኢዮብ 31:1, 9, 11

3. ይሖዋ ለኢዮብ ምን አመለካከት ነበረው?

3 ኢዮብ አምላክን የሚያመልክ ሰው በመሆኑ ነቀፋ የሌለበት ሕይወት ይመራ ነበር። ይሖዋ ስለ ኢዮብ ሲናገር “በምድር ላይ እንደ እርሱ ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው የለም” ብሏል። (ኢዮብ 1:1, 8) ኢዮብ የሥነ ምግባር አቋሙን ቢጠብቅም እንኳን በአሳዛኝ መከራዎች ምክንያት ምቹ የነበረው ኑሮው ተመሰቃቅሎበታል። ለፍቶ ያገኘውን ሁሉ አጥቷል፤ እንዲሁም በደረሰበት ሕመም፣ ሥቃይና የሚያሳዝን ሁኔታ እውነተኛ ማንነቱ ተፈትኗል።

4. ኢዮብ የደረሰበትን ከባድ ችግር መመርመራችን ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

4 ከአምላክ አገልጋዮች መካከል በግለሰብ ደረጃ አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጠመው ኢዮብ ብቻ እንዳልሆነ እሙን ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ክርስቲያኖች ከኢዮብ ጋር በጣም የሚመሳሰል ሁኔታ እንዳጋጠማቸው ሊነግሩን ይችላሉ። በዚህ ምክንያት የሚከተሉትን ሁለት ጥያቄዎች መመርመር ያስፈልገናል:- ኢዮብ የደረሰበትን ከባድ ችግር ማስታወሳችን አሳዛኝ መከራ ሲያጋጥመን እንዴት ሊረዳን ይችላል? ሌሎች መከራ ሲደርስባቸው አዛኞች እንድንሆን ትምህርት የሚሰጠንስ እንዴት ነው?

የታማኝነት ጥያቄና የአቋም ጽናት ፈተና

5. እንደ ሰይጣን አባባል ከሆነ ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው ለምን ነበር?

5 ኢዮብ ያጋጠመው ሁኔታ ለየት ያለ ነበር። ምክንያቱም አምላክን የሚያገለግልበትን ዓላማ በተመለከተ ዲያብሎስ ጥያቄ እንዳስነሳ አላወቀም። መንፈሳዊ ፍጥረታት በሰማይ ስብሰባ ሲያደርጉ ይሖዋ ስለ ኢዮብ መልካም ባሕርያት በጠቀሰ ጊዜ ሰይጣን “በእርሱና በቤተ ሰቦቹ፣ ባለው ንብረትስ ሁሉ ዙሪያ ዐጥር ሠርተህለት የለምን?” የሚል መልስ ሰጠ። ሰይጣን በዚህ መንገድ፣ ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ እንደሆነ ተናግሯል፤ ይህ አባባሉ በተዘዋዋሪ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮችንም ሁሉ የሚነካ ነው። ሰይጣን ይሖዋን እንዲህ አለው:- “እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ንካበት፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።”ኢዮብ 1:8-11

6. ሰይጣን ምን አንገብጋቢ ጉዳይ አንስቷል?

6 የተነሳው ጉዳይ በጣም አንገብጋቢ ነው። ሰይጣን፣ ይሖዋ ሉዓላዊነቱን ስለሚጠቀምበት መንገድ ክርክር አስነስቷል። በእርግጥ አምላክ ጽንፈ ዓለምን በፍቅር መግዛት ይችላል? ወይስ ሰይጣን በተዘዋዋሪ መንገድ እንዳለው ምንጊዜም ቢሆን የሰዎች ራስ ወዳድነት በስተመጨረሻ ድል ያደርጋል? ይሖዋ አገልጋዩ ጽኑ አቋሙን እንደሚጠብቅና ታማኝነቱን እንደማያጓድል በመተማመን ዲያብሎስ ኢዮብን ፈትኖ ሐሳቡ ትክክል መሆን አለመሆኑን እንዲያረጋግጥ ፈቀደለት። ስለዚህ ሰይጣን ራሱ በኢዮብ ላይ በተከታታይ አሳዛኝ አደጋዎች እንዲደርሱበት አደረገ። ሰይጣን የመጀመሪያው ጥቃቱ አልሳካ ሲለው ኢዮብን በከባድ ሕመም እንዲሠቃይ አደረገው። ዲያብሎስ “‘ቍርበት ስለ ቍርበት ነው’ እንዲሉ ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል” በማለት ተከራክሯል።ኢዮብ 2:4

7. በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በኢዮብ ላይ የደረሱት ዓይነት መከራዎች የሚደርሱባቸው በምን መንገዶች ነው?

7 በዛሬው ጊዜ ብዙዎቹ ክርስቲያኖች የኢዮብን ያህል ሥቃይ ባይደርስባቸውም የተለያዩ መከራዎች ያጋጥሟቸዋል። አብዛኞቹ ስደት ወይም የቤተሰብ ችግር ያጋጥማቸዋል። የኢኮኖሚ ችግር ወይም የጤና መታወክም ከባድ ጉዳት ሊያስከትልባቸው ይችላል። አንዳንዶች ደግሞ ለእምነታቸው ሲሉ ሕይወታቸውን መሥዋዕት እስከማድረግ ደርሰዋል። በእርግጥ እየደረሰብን ያለውን እያንዳንዱን አሳዛኝ መከራ ያመጣብን ሰይጣን ነው ብለን ማሰብ የለብንም። ምክንያቱም አንዳንድ ችግሮች የሚደርሱብን በራሳችን ስህተት ወይም ከዘር በወረስነው እክል ምክንያት ሊሆን ይችላል። (ገላትያ 6:7) እንዲሁም ሁላችንም የዕድሜ መግፋትና የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያስከትሏቸው ችግሮች ያጋጥሙናል። በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ አገልጋዮቹን ከእነዚህ መከራዎች በተዓምር እንደማይጠብቃቸው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።መክብብ 9:11 NW

8. ሰይጣን ያሉብንን ችግሮች እንዴት ሊጠቀምባቸው ይችላል?

8 የሆነ ሆኖ ሰይጣን መከራዎችን እምነታችንን ለመሸርሸር ሊጠቀምባቸው ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የሰይጣን መልእክተኛ” ብሎ በጠራው ‘የሥጋ መውጊያ’ ይደርስበት ስለነበረው ‘ሥቃይ’ ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 12:7) ጳውሎስ የነበረበት የሥጋ መውጊያ፣ የማየት እክልን የመሠለ አካላዊ ሕመምም ይሁን ሌላ ነገር ሰይጣን ችግሩን ተጠቅሞ ተስፋ በማስቆረጥ ደስታ ሊያሳጣውና አቋሙን እንዲያላላ ሊያደርገው እንደሚሞክር ተገንዝቦ ነበር። (ምሳሌ 24:10) ዛሬም ሰይጣን የአምላክን አገልጋዮች በሆነ መንገድ ለማሠቃየት የቤተሰባቸውን አባላት፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸውን ወይም ደግሞ አምባገነን መንግሥታትን ሊጠቀም ይችላል።

9. መከራ ወይም ስደት የሚደርስብን መሆኑ ከመጠን በላይ ሊያስደንቀን የማይገባው ለምንድን ነው?

9 እነዚህን ችግሮች በሚገባ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? የሚደርሱብንን ችግሮች፣ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የምናሳይባቸውና በማንኛውም ጊዜ ለእርሱ ሉዓላዊነት የምንገዛ መሆናችንን ማረጋገጥ የምንችልባቸው አጋጣሚዎች እንደሆኑ አድርገን በመመልከት ነው። (ያዕቆብ 1:2-4) ችግር የሚደርስብን በማንኛውም ምክንያት ይሁን፣ ለአምላክ ታማኝ የመሆንን አስፈላጊነት መረዳታችን መንፈሳዊ ሚዛናችንን ለመጠበቅ ይረዳናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቲያኖች እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቍጠር አትደነቁ።” (1 ጴጥሮስ 4:12) ጳውሎስም እንዲህ ብሏል:- “በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ሰይጣን በኢዮብ ላይ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም የይሖዋ ምሥክሮች ጽኑ አቋማቸውን መጠበቃቸው አጠያያቂ እንደሆነ ይናገራል። እንዲያውም ሰይጣን በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት እንዳጠናከረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።ራእይ 12:9, 17

ሁኔታውን በትክክል አለመረዳትና የተሰጠው የተሳሳተ ምክር

10. ኢዮብ ምን የማያውቀው ነገር ነበር?

10 ኢዮብ ከእኛ የሚለይበት አንድ መንገድ አለ፤ ይኸውም እነዚያ ችግሮች ለምን እንደደረሱበት አለማወቁ ነው። ኢዮብ ‘ይሖዋ እንደሰጠውና ይሖዋ እንደነሣው’ ተሰምቶት ነበር። (ኢዮብ 1:21) ሰይጣን ሆነ ብሎ፣ ኢዮብ መከራ ያደረሰበት አምላክ እንደሆነ እንዲያስብ አድርጎት ሊሆን ይችላል።

11. ኢዮብ የደረሰበትን ችግር በተመለከተ ምን ተሰምቶት እንደነበር ግለጽ።

11 ኢዮብ ሚስቱ እንዳለችው አምላክን ባይረግምም በጣም ተስፋ ቆርጦ ነበር። (ኢዮብ 2:9, 10) ‘ኀጢአተኞች ከእኔ በጣም በተሻለ ሁኔታ ተሳክቶላቸዋል’ በማለት ተናግሮ ነበር። (ኢዮብ 21:7-9) ‘አምላክ የሚቀጣኝ ለምንድን ነው?’ ብሎ ጠይቆ መሆን አለበት። ሞትን የተመኘባቸው ጊዜያትም ነበሩ። “ምነው መቃብር ውስጥ በሰወርኸኝ! ቍጣህም እስከሚያልፍ በሸሸግኸኝ!” በማለት በምሬት ተናግሯል።ኢዮብ 14:13

12, 13. ኢዮብ ሦስቱ ወዳጆቹ የሰጡት አስተያየት ምን ስሜት አሳድሮበታል?

12 ኢዮብን ‘ለማስተዛዘንና ለማጽናናት’ በሚል ሦስት ወዳጆቹ ወደ እርሱ ሄደው ነበር። (ኢዮብ 2:11) ነገር ግን ‘የሚያስጨንቁ አጽናኞች’ መሆናቸው ተረጋግጧል። (ኢዮብ 16:2) ኢዮብ ችግሩን የሚያዋያቸው ጓደኞች ቢኖሩት ኖሮ እፎይታ ማግኘት ይችል ነበር፤ እነዚህ ሦስት ወዳጆቹ ግን የባሰ ግራ እንዲገባውና ጭንቀቱ እንዲበረታበት አድርገዋል።ኢዮብ 19:2፤ 26:2

13 ኢዮብ ‘ይህ ችግር በእኔ ላይ የደረሰው ለምንድን ነው? ምን አጥፍቼ ይሆን?’ ብሎ ራሱን ጠይቆ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። ወዳጆቹ ያካፈሉት ሐሳብ ፍጹም አሳሳች ነበር። ኢዮብ አንዳንድ ከባድ ኃጢአቶችን በመፈጸም በራሱ ላይ መከራ እንዳመጣ ገምተው ነበር። ኤልፋዝ “ንጹሕ ሆኖ የጠፋ፣ ማን ነው?” ሲል ጠይቆ ነበር። መልሱን ሲሰጥም እንዲህ ብሏል:- “እኔ እንዳየሁ፣ ክፋትን የሚያርሱ፣ መከራንም የሚዘሩ ያንኑ ያጭዳሉ።”ኢዮብ 4:7, 8

14. አንድ ሰው ላይ መከራ የደረሰበት መጥፎ ባሕርይ ስላለው ነው ለማለት መቸኮል የሌለብን ለምንድን ነው?

14 በመንፈስ ከመዝራት ይልቅ ሥጋዊ ምኞታችንን ለማርካት የምንዘራ ከሆነ ችግሮች ሊነሱ እንደሚችሉ የተረጋገጠ ነው። (ገላትያ 6:7, 8) ሆኖም ባሕርያችን ምንም ይሁን ምን በዚህ ሥርዓት ውስጥ ችግር ሊደርስብን ይችላል። ከዚህም በላይ ንጹሐን መከራ አያገኛቸውም ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው። ‘ንጹሕና ከኀጢአተኞች የተለየ’ የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ በመከራ እንጨት ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ሞቷል፤ ሐዋርያው ያዕቆብም መሥዋዕታዊ ሞት ሞቷል። (ዕብራውያን 7:26፤ የሐዋርያት ሥራ 12:1, 2) ኤልፋዝና ሁለቱ ጓደኞቹ ያቀረቡት የተሳሳተ ምክንያት ኢዮብ ስለ መልካም ስሙና ስለ ንጽሕናው በጥብቅ እንዲከራከር አድርጎታል። ቢሆንም ወዳጆቹ የእጅህን ነው ያገኘኸው ብለው መከራከራቸው ስለ አምላክ ፍትሕ ባለው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድርበት አልቀረም።ኢዮብ 34:5፤ 35:2

በመከራ ወቅት እርዳታ ማግኘት

15. ችግር በሚያጋጥመን ጊዜ ምን ዓይነት አስተሳሰብ መያዝ ይረዳናል?

15 ከኢዮብ ታሪክ ምን የምናገኘው ትምህርት አለ? ፈጽሞ ተገቢ ባልሆነ መንገድ አሳዛኝ መከራ፣ ሕመም ወይም ስደት እየደረሰብን እንዳለ ይሰማን ይሆናል። ሌሎች ሰዎች ግን እንዲህ ካሉ በርካታ ችግሮች ነጻ ሆነው የሚኖሩ ሊመስለን ይችላል። (መዝሙር 73:3-12) አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን የሚከተሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ልንጠይቅ እንችላለን:- “ምንም ነገር ቢከሰት ለአምላክ ያለኝ ፍቅር እርሱን እንዳገለግል ይገፋፋኛል? ይሖዋ ‘ለሚሰድበው መልስ’ እንዲሰጥ ከልቤ እፈልጋለሁ?” (ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም፤ ማቴዎስ 22:37) ሌሎች የሚሰጡን አሳቢነት የጎደለው አስተያየት በሰማይ ባለው አባታችን ላይ ጥርጣሬ እንዲዘራብን አንፍቀድ። ለበርካታ ዓመታት ሥር በሰደደ በሽታ ስትሠቃይ የኖረች ታማኝ ክርስቲያን በአንድ ወቅት እንዲህ ብላ ነበር:- “ይሖዋ ምንም ነገር ቢፈቅድ ልቋቋመው እንደምችል አውቃለሁ። አስፈላጊውን ኃይል እንደሚሰጠኝ አውቃለሁ። ሁልጊዜም የሚያስፈልገኝን ጥንካሬ ሲሰጠኝ ቆይቷል።”

16. የአምላክ ቃል መከራዎች ያጋጠሟቸውን ሰዎች የሚረዳው እንዴት ነው?

16 እኛ ከኢዮብ በተቃራኒ የሰይጣንን ዘዴዎች እናውቃቸዋለን። የእርሱን እኩይ ዘዴ ወይም “ዕቅድ አንስተውም።” (2 ቆሮንቶስ 2:11) በተጨማሪም ማስተዋል የምናገኝባቸው በርካታ ዝግጅቶች አሉልን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያዩ መከራዎችን የተቋቋሙ ታማኝ ሰዎችን ታሪክ እናገኛለን። ከበርካታ ክርስቲያኖች የበለጠ መከራ የቀመሰው ሐዋርያው ጳውሎስ “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና” ብሎ ጽፏል። (ሮሜ 15:4) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በእምነቱ ምክንያት የታሰረ በአውሮፓ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር የሦስት ቀን ምግቡን በመጽሐፍ ቅዱስ ቀይሮ ነበር። እንዲህ ብሏል:- “መጽሐፍ ቅዱስን በምግብ መቀየሬ በጣም ጠቅሞኛል! ቢርበኝም እንኳን እኔም ሆንኩ ሌሎች፣ በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት የደረሱብንን መከራዎች እንድንወጣ የረዳንን መንፈሳዊ ምግብ አግኝተናል። ያንን መጽሐፍ ቅዱስ እስከ አሁን ድረስ አስቀምጬዋለሁ።”

17. እንድንጸና የሚረዱን የትኞቹ መለኮታዊ ዝግጅቶች ናቸው?

17 ቅዱሳን ጽሑፎች ከሚሰጡን ማበረታቻዎች በተጨማሪ ችግሮችን ለመቋቋም የሚረዱ ጠቃሚ መመሪያዎችን የያዙ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥኛ መሣሪያዎች አሉልን። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫን (እንግሊዝኛ) ብትመለከት የአንተ ዓይነት ችግር የነበረበትን ክርስቲያን ተሞክሮ ልታገኝ ትችላለህ። (1 ጴጥሮስ 5:9) እንዲሁም ስላለህበት ሁኔታ ርኅሩኅ ከሆኑ የጉባኤ ሽማግሌዎች ወይም ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር መነጋገሩ ጠቃሚ ነው። ከሁሉም በላይ ስትጸልይ ከይሖዋና ከቅዱስ መንፈሱ በምታገኘው እርዳታ መተማመን ትችላለህ። ጳውሎስ ሰይጣን የሚያደርስበትን ‘ሥቃይ’ የተቋቋመው እንዴት ነው? በአምላክ ኃይል በመታመን ነው። (2 ቆሮንቶስ 12:9, 10) “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” ብሎ ጽፏል።ፊልጵስዩስ 4:13

18. ክርስቲያኖች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ጠቃሚ የሆነ ማበረታቻ መስጠት የሚችሉት እንዴት ነው?

18 ስለዚህ እኛን ለመርዳት የተደረጉ ዝግጅቶች ስላሉ ይህንን እርዳታ ከመፈለግ ወደኋላ አትበል። የምሳሌ መጽሐፍ “በመከራ ጊዜ ፈራ ተባ ካልህ፣ ዐቅምህ ምንኛ ደካማ ነው!” ይላል። (ምሳሌ 24:10) ምስጦች ከእንጨት የተሠራ ቤትን መጣል እንደሚችሉ ሁሉ ተስፋ መቁረጥም የአንድን ክርስቲያን ጽኑ አቋም ሊሸረሽር ይችላል። ይሖዋ ይህንን አደጋ መከላከል እንድንችል የእርሱ አገልጋዮች በሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻችን በኩል ይደግፈናል። ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት አንድ መልአክ ተገልጦለት አበረታቶታል። (ሉቃስ 22:43) ጳውሎስ ታስሮ ወደ ሮም ይጓዝ በነበረበት ወቅት አፍዩስ ፋሩስ በሚባል ገበያና ሦስት ማደሪያ በተባለ አካባቢ ወንድሞችን ሲያገኝ “እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ተጽናናም።” (የሐዋርያት ሥራ 28:15) አንዲት ጀርመናዊት የይሖዋ ምሥክር በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለች ራቨንስብሩክ የተባለ ማጎሪያ ካምፕ በደረሰችበት የጭንቀት ወቅት የተደረገላትን እርዳታ እስከ አሁን ድረስ ታስታውሳለች። እንዲህ ስትል ትውስታዋን ተናግራለች:- “ወዲያውኑ ከአንዲት ክርስቲያን የእምነት ባልንጀራዬ ጋር ተገናኘሁና ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገችልኝ። ሌላ ታማኝ እህትም ትረዳኝ የነበረ ሲሆን በመንፈሳዊም እንደ እናት ሆናልኝ ነበር።”

“ታማኝ ሁን”

19. ኢዮብ ሰይጣን የሚያደርገውን ጥረት እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው?

19 ይሖዋ ስለ ኢዮብ ሲናገር “ፍጹምነቱን እንደ ጠበቀ ነው” ብሏል። (ኢዮብ 2:3) ኢዮብ ተስፋ ቆርጦ የነበረ ቢሆንም እንዲሁም ችግር እየደረሰበት ያለው ለምን እንደሆነ ባያውቅም እንኳን መሠረታዊ በሆነው የታማኝነት ጉዳይ ረገድ ፈጽሞ አላቅማማም። ኢዮብ ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ለመኖር ሲል የከፈለው ማንኛውም መሥዋዕትነት መና ሆኖ እንዲቀር አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ “ጨዋነቴንም [“ታማኝነቴን፣” NW] እስክሞት ድረስ አልጥልም” በማለት አስረግጦ ተናግሯል።—ኢዮብ 27:5

20. መጽናት ምን ጥቅም ያስገኛል?

20 እኛም ተመሳሳይ የሆነ ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋችን ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ማለትም ፈተናዎች፣ ተቃውሞዎች ወይም መከራዎች ቢደርሱብን እንኳን ጽኑ አቋማችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። ኢየሱስ በሰምርኔስ የነበረውን ጉባኤ እንዲህ ብሎታል:- “ሊደርስብህ ያለውን መከራ አትፍራ። እነሆ፤ ዲያብሎስ ሊፈትናችሁ አንዳንዶቻችሁን ወደ እስር ቤት ይጥላል፤ ዐሥር ቀንም መከራ [ችግር፣ ሥቃይ ወይም ስደት] ትቀበላላችሁ። እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሁን፤ እኔም የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ።”ራእይ 2:10

21, 22. መከራ ሲደርስብን የሚያጽናናን ምንን ማወቃችን ነው?

21 በዚህ ሰይጣን በሚገዛው ሥርዓት ውስጥ ጽናታችንና ታማኝነታችን ይፈተናል። ቢሆንም ስለወደፊቱ ጊዜ ስናስብ የምንፈራበት ምክንያት እንደሌለ ኢየሱስ አረጋግጦልናል። አስፈላጊው ነገር ታማኝነታችንን ማረጋገጥ ነው። ጳውሎስ እንደተናገረው የሚደርስብን ‘መከራ ቀላልና ጊዜያዊ ሲሆን’ የምናገኘው “ክብር” ወይም ይሖዋ ቃል የገባልን ሽልማት ግን “ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ” ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:17, 18) ኢዮብ እንኳን ችግር ውስጥ ከመውደቁ በፊትና በኋላ ካሳለፋቸው የደስታ ዓመታት አንጻር ሲታይ የደረሰበት መከራ ጊዜያዊ ነበር።ኢዮብ 42:16

22 ቢሆንም በሕይወታችን ውስጥ ማብቂያ የሌለው መከራና ከአቅም በላይ የሆነ ሥቃይ እየደረሰብን እንዳለ የሚሰማን ጊዜ ይኖራል። በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ጽናትን በተመለከተ ከኢዮብ ታሪክ ምን ተጨማሪ ትምህርቶች እንደምናገኝ እንመረምራለን። እንዲሁም መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች ማጽናናት የምንችልባቸውን መንገዶች እንመለከታለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ሰይጣን የኢዮብን ጽኑ አቋም በተመለከተ ምን መሠረታዊ ጥያቄ አንስቷል?

• መከራ ሲደርስብን ከልክ በላይ የማንገረመው ለምንድን ነው?

• ይሖዋ እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምርምር ማድረግ፣ ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር መነጋገርና በጸሎት አማካኝነት የልባችንን ማፍሰስ እንድንጸና ይረዳናል