በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአንተ ጠቃሚ የሆነ አምልኮ

ለአንተ ጠቃሚ የሆነ አምልኮ

ለአንተ ጠቃሚ የሆነ አምልኮ

መዝሙራዊው አሳፍ “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” በማለት ተናግሯል። አሳፍ፣ የተመቻቸ ሕይወት ለመኖር ሲሉ አምላክን ችላ የሚሉ ሰዎችን መምሰል ሳይሻል እንደማይቀር ተሰምቶት ነበር። ወደ አምላክ የመቅረብን ጥቅም ካሰበበት በኋላ ግን ለእርሱም ይኸው እንደሚሻለው ተናግሯል። (መዝሙር 73:2, 3, 12, 28) በዛሬው ጊዜስ እውነተኛ አምልኮ ለአንተ ጠቃሚ ነው? ከሆነስ ሊጠቅምህ የሚችለው እንዴት ነው?

እውነተኛውን አምላክ ማምለክ በራስ ወዳድነት ላይ ብቻ ከተመሠረተ አኗኗር በተለየ መልኩ የላቀ አመለካከት እንዲኖርህ ይረዳሃል። የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ የሚሯሯጡ ሰዎች ፈጽሞ ደስታ አያገኙም፤ ምክንያቱም ‘የፍቅር አምላክ’ በዚህ መንገድ ደስታ እንድናገኝ አድርጎ አልፈጠረንም። (2 ቆሮንቶስ 13:11) ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” ብሎ በተናገረ ጊዜ ስለ ሰው ተፈጥሮ መሠረታዊ የሆነ እውነት አስተምሯል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ለጓደኞቻችንና ለቤተሰባችን መልካም ማድረግ የሚያስደስተን ለዚህ ነው። ይሁን እንጂ ከሁሉ የላቀ ደስታ የሚገኘው አምላክን በማገልገል ነው። ከማንም በላይ እርሱን ልንወደው ይገባል። የተለያየ ማኅበራዊ ሁኔታና አስተዳደግ ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ አምላክ በሚፈልገው መንገድ እርሱን ማምለክ ጥልቅ እርካታ እንደሚያስገኝ ተገንዝበዋል።—1 ዮሐንስ 5:3

ዓላማ ያለው ሕይወት

እውነተኛ አምልኮ ሕይወትህ ዓላማ እንዲኖረው ስለሚያደርግ ለአንተም ጠቃሚ ነው። ብዙ ጊዜ አንድ ጠቃሚ ነገር እንዳከናወንክ ሲሰማህ ደስታ እንደምታገኝ አስተውለሃል? አብዛኞቹ ሰዎች ከቤተሰባቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሥራቸው፣ ወይም ደስታ ለማግኘት ከሚያከናውኑት ነገር ጋር በተያያዘ በሕይወታቸው ውስጥ ዓላማ አላቸው። ሆኖም ሕይወት አስተማማኝ ባለመሆኑ የመሠረቷቸው ዝምድናዎችም ሆኑ ያፈሯቸው ንብረቶች ብዙውን ጊዜ ደስታ ሳያስገኙላቸው ይቀራሉ። (መክብብ 9:11) እውነተኛ አምልኮ ግን ሌሎቹ የሕይወትህ ዘርፎች ተስፋ አስቆራጭ በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ ቀጣይ የሆነ እርካታ እንድታገኝ የሚያደርግ ላቅ ያለ ዓላማ እንዲኖርህ ይረዳሃል።

እውነተኛ አምልኮ ይሖዋን ማወቅንና እርሱን በታማኝነት ማገልገልን ይጨምራል። እውነተኛውን አምልኮ የሚከተሉ ሰዎች ከአምላክ ጋር በጣም ይቀራረባሉ። (መክብብ 12:13፤ ዮሐንስ 4:23፤ ያዕቆብ 4:8) ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት በሚያስችል ደረጃ እርሱን ስለማወቅ ማሰቡም እንኳ ከባድ መስሎ ሊታይህ ይችላል። ነገር ግን እርሱ ከሰዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት በሚገልጸው የታሪክ ዘገባ ላይ በማሰላሰልና የፈጠረውን ነገር በመመልከት የባሕርይውን የተለያዩ ገጽታዎች መረዳት ትችላለህ። (ሮሜ 1:20) በተጨማሪም የአምላክን ቃል በማንበብ እዚህ ምድር ላይ የተፈጠርነው ለምን እንደሆነ፣ አምላክ ሥቃይ እንዲኖር ለምን እንደፈቀደ፣ ሥቃይ እንዲያከትም የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ከሁሉም ይበልጥ አስደናቂ የሆነውን ነገር ይኸውም በአምላክ ዓላማ ውስጥ ጠቃሚ ድርሻ ሊኖርህ የሚችለው እንዴት እንደሆነ መረዳት ትችላለህ። (ኢሳይያስ 43:10፤ 1 ቆሮንቶስ 3:9) እንዲህ ያለው እውቀት በሕይወትህ ውስጥ አዲስ ዓላማ እንዲኖርህ ሊያደርግ ይችላል!

የተሻልክ ሰው መሆን

እውነተኛ አምልኮ የተሻልክ ሰው እንድትሆን ስለሚረዳህ ይጠቅምሃል። እውነተኛውን አምልኮ ስትከተል ከሌሎች ጋር አስደሳች ዝምድና እንዲኖርህ የሚያስችል ባሕርይ ታዳብራለህ። ከአምላክ እና ከልጁ የምታገኘው ትምህርት ሐቀኛ እንድትሆን፣ ንግግርህ ደግነት የተሞላበት እንዲሆን እንዲሁም እምነት የሚጣልብህ ሰው እንድትሆን ይረዳሃል። (ኤፌሶን 4:20 እስከ 5:5) አምላክን እስክትወደው ድረስ በደንብ ስታውቀው እርሱን ለመምሰል ትገፋፋለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ” ይላል።—ኤፌሶን 5:1, 2

የአምላክን ፍቅር በሚኮርጁ ሰዎች ተከቦ መኖር አስደሳች አይደለም? ደስ የሚለው ነገር የእውነተኛው አምላክ አምልኮ ብቻህን የምትካፈልበት እንቅስቃሴ አይደለም። እውነተኛው አምልኮ ትክክልና መልካም የሆነውን ከሚወዱ ሌሎች ሰዎችም ጋር ያገናኝሃል። እርግጥ ነው፣ የተደራጀ ሃይማኖት የሚለው ሐሳብ ብዙም አያስደስትህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ባለፈው ርዕሰ ትምህርት ላይ እንዳየነው በአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ዘንድ ያለው ችግር መደራጀታቸው ሳይሆን በትክክለኛው መንገድና ለትክክለኛው ዓላማ አለመደራጀታቸው ነው። ብዙዎቹ የተደራጁ ሃይማኖቶች ዒላማ አድርገው የተነሱት ከክርስትና ጋር የሚቃረኑ ግቦችን ነው። የአምላክ ሕዝቦችን ደግሞ ይሖዋ ራሱ ለተከበረ ዓላማ አደራጅቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 14:33) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች እንዳደረጉት አንተም በጥሩ ሁኔታ ከተደራጁ ክርስቲያኖች ጋር መቀራረብህ ለወደፊቱ ጊዜ ባለህ አመለካከት ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ልትገነዘብ ትችላለህ።

ለወደፊቱ የሚኖርህ ተስፋ

አምላክ ከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ተርፈው “ጽድቅ የሚኖርበትን” አዲስ ምድር እንዲወርሱ እውነተኛ አምላኪዎቹን እያደራጃቸው መሆኑን ቅዱሳን ጽሑፎች ይገልጻሉ። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 7:9-17) በመሆኑም ለአንተ የሚጠቅም አምልኮ ለደስታህ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ማለትም ተስፋን ይሰጥሃል። አንዳንዶች የወደፊት ተስፋቸውን የመሠረቱት በመንግሥታት ጥንካሬ፣ በንግድ ወይም በጥሩ ጤንነትና በአስደሳች የጡረታ ዘመን ላይ ነው። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ነገሮች ውስጥ አንዳቸውም ቢሆኑ አስደሳች የወደፊት ሕይወት እንደሚኖረን ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት አይሆኑም። በሌላ በኩል ግን ሐዋርያው ጳውሎስ “በሕያው እግዚአብሔር ተስፋ [እናደርጋለን]” በማለት ጽፏል።—1 ጢሞቴዎስ 4:10

ጥንቃቄ የተሞላበት ፍለጋ ካካሄድክ እውነተኛ አምላኪዎችን ታገኛቸዋለህ። በዛሬው ጊዜ ባለው የተከፋፈለ ዓለም ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በፍቅራቸውና በአንድነታቸው ተለይተው ይታወቃሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡና የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው ቢሆኑም አንዳቸው ለሌላው እንዲሁም ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር አንድ ሆነዋል። (ዮሐንስ 13:35) እነሱ ያገኙትን ነገር አንተ ራስህ እንድትመለከተው ይጋብዙሃል። አሳፍ “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 73:28

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ