ልመናችሁን በአምላክ ፊት አቅርቡ
ልመናችሁን በአምላክ ፊት አቅርቡ
“በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ።”—ፊልጵስዩስ 4:6
1. ከማን ጋር የመነጋገር መብት አለን? ይህስ አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው?
የአገርህን መሪ ለማነጋገር ፈልገህ ጥያቄ ብታቀርብ ምን ምላሽ የምታገኝ ይመስልሃል? ጉዳዩ የሚመለከተው ቢሮ ትሕትና የታከለበት መልስ ሊሰጥህ ቢችልም ከመሪው ጋር በቀጥታ እንድትነጋገር ይፈቀድልሃል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ሆኖም የሁሉም ነገር ገዥና የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ በሆነው በይሖዋ አምላክ ዘንድ ሁኔታው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። በፈለግነው ቦታና ሰዓት እርሱን ማነጋገር እንችላለን። ተቀባይነት ያላቸው ጸሎቶች ምንጊዜም ወደ አምላክ ይደርሳሉ። (ምሳሌ 15:29) ይህ ምንኛ አስደናቂ ነው! ለዚህ ያለን የአመስጋኝነት ስሜት ‘ጸሎት ሰሚ’ ወደሆነው አምላክ ዘወትር በጸሎት እንድንቀርብ ሊገፋፋን አይገባም?—መዝሙር 65:2
2. ጸሎታችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ምን ያስፈልጋል?
2 ይሁንና አንድ ሰው ‘በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ጸሎቶች ምን ዓይነት ናቸው?’ የሚል ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ የምናቀርባቸው ጸሎቶች ተቀባይነት እንዲኖራቸው ከተፈለገ ምን ነገር መሟላት እንዳለበት ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት።” (ዕብራውያን 11:6) አዎን፣ በፊተኛው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው እምነት ወደ አምላክ ለመቅረብ ወሳኝ የሆነ ነገር ነው። አምላክ ወደ እርሱ የሚቀርቡ ሰዎች የሚያቀርቡትን ጸሎት ለመስማት ፈቃደኛ ነው፤ ሆኖም ጸሎታቸው እንዲሰማላቸው ከተፈለገ እምነት ማሳደር፣ ቀና የሆነውን ማድረግና ትክክለኛ የሆነ የልብ ዝንባሌ ማዳበር ይጠበቅባቸዋል።
3. (ሀ) በጥንት ጊዜ ይኖሩ በነበሩት ታማኝ አገልጋዮች ላይ እንደታየው በጸሎታችን ውስጥ ምን ምን ነገሮችን ማካተት እንችላለን? (ለ) ጸሎታችን ምን ይዘት ሊኖረው ይችላል?
3 ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሚያሳስቧቸውን ነገሮች በጸሎት አማካኝነት ለአምላክ የነገሩ በርካታ ሰዎችን ምሳሌ ይዟል። ከእነዚህ መካከል ሐና፣ ኤልያስ፣ ሕዝቅያስና ዳንኤል ይገኙበታል። (1 ሳሙኤል 2:1-10፤ 1 ነገሥት 18:36, 37፤ 2 ነገሥት 19:15-19፤ ዳንኤል 9:3-21) እኛም የእነርሱን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። የጳውሎስ ቃላት የምናቀርበው ጸሎት የተለያየ ይዘት ሊኖረው እንደሚችል እንደሚጠቁምም ልብ በል። ጳውሎስ ምስጋና ማቅረብ እንደምንችል የገለጸ ሲሆን ይህም አምላክ ላደረገልን ነገር የተሰማንን አድናቆት የምንገልጽበትን የጸሎት ዓይነት ያመለክታል። ከምስጋና ጋር ውዳሴም አክለን ማቅረብ እንችላለን። ምልጃ ከልብ በመነጨ ስሜት በትሕትና የምናቀርበውን ልመና ያመለክታል። እንዲሁም አንድ የምንፈልገውን ነገር በቀጥታ ጠቅሰን በመጸለይ ልመና ማቅረብ እንችላለን። (ሉቃስ 11:2, 3) በሰማይ የሚኖረው አባታችን በዚህ መልኩ የምናቀርበውን ማንኛውንም ጸሎት በደስታ ይቀበላል።
4. ይሖዋ ምን እንደሚያስፈልገን ቢያውቅም ልመናችንን ወደ እርሱ ማቅረብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
4 ሆኖም አንድ ሰው “ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ያውቅ የለም እንዴ?” በማለት ይጠይቅ ይሆናል። አዎን፣ ያውቃል። (ማቴዎስ 6:8, 32) ታዲያ አምላክ ወደ እርሱ ቀርበን ልመናችንን እንድናስታውቀው የሚፈልገው ለምንድን ነው? እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት:- የአንድ መደብር ባለቤት ለአንዳንድ ደንበኞቹ ስጦታ መስጠት ፈለገ እንበል። ይህን ስጦታ ማግኘት የፈለገ ደንበኛ ወደ መደብሩ ባለቤት ቀርቦ ስጦታው እንዲሰጠው መጠየቅ ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑ ደንበኞች ለስጦታው አድናቆት እንደሌላቸው ያሳያሉ። በተመሳሳይም በጸሎት አማካኝነት ልመናችንን ለማቅረብ አለመፈለጋችን ይሖዋ ለሰጠን ነገሮች አድናቆት እንደጎደለን ያሳያል። ኢየሱስ “ለምኑ ትቀበላላችሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 16:24) ይህን ስናደርግ በእርግጥ በአምላክ እንደምንታመን እናሳያለን።
አምላክን መቅረብ ያለብን እንዴት ነው?
5. በኢየሱስ ስም መጸለያችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5 ይሖዋ እንዴት መጸለይ እንዳለብን የሚገልጹ ድርቅ ያሉ ትእዛዛት አልጫነብንም። ያም ሆኖ ግን መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን በተገቢው መንገድ እንዴት መቅረብ እንዳለብን የሚሰጠንን ትምህርት መቅሰም ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ተከታዮቹን “አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል” በማለት አስተምሯቸዋል። (ዮሐንስ 16:23) ስለሆነም ኢየሱስ የሰው ልጆች የአምላክን በረከቶች ሊያገኙ የሚችሉበት ብቸኛ መስመር እንደሆነ በማመን በስሙ መጸለይ ይገባናል።
6. መጸለይ ያለብን እንዴት ሆነን ነው?
6 ጸሎታችን ተሰሚነት እንዲያገኝ እንዴት ሆነን መጸለይ አለብን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር የለም። (1 ነገሥት 8:22፤ ነህምያ 8:6፤ ማርቆስ 11:25፤ ሉቃስ 22:41) ቁም ነገሩ ያለው ለአምላክ የምንጸልየው በቅንነትና በትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ተገፋፍተን በመሆኑ ላይ ነው።—ኢዩኤል 2:12, 13
7. (ሀ) “አሜን” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) በጸሎታችን ውስጥ በተገቢው መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለውስ እንዴት ነው?
7 “አሜን” ስለሚለው ቃልስ ምን ለማለት ይቻላል? ቅዱሳን ጽሑፎች ይህ ቃል ጸሎት ስናቀርብ፣ በተለይ ደግሞ በሕዝብ ፊት ስንጸልይ ጸሎታችንን ልንቋጭበት የሚገባ ተስማሚ ቃል መሆኑን ይጠቁማሉ። (መዝሙር 72:19፤ 89:52) አሜን የሚለው የዕብራይስጥ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ “ይሁን” የሚል ነው። በማክሊንቶክ እና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ በጸሎት መደምደሚያ ላይ “አሜን” የሚባለው “ቀደም ብለው የተነገሩት ቃላት እውነተኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ብሎም ተሰሚነት እንዲያገኙ ልመና ለማቅረብ” እንደሆነ ገልጿል። በመሆኑም፣ አንድ ሰው በጸሎቱ መደምደሚያ ላይ ከልብ በመነጨ ስሜት “አሜን” ማለቱ የተናገራቸውን ቃላት በጥብቅ እንደሚያምንባቸው ያሳያል። አንድ ክርስቲያን ጉባኤውን ወክሎ ጸሎት ካቀረበ በኋላ ጸሎቱን በዚህ ቃል በሚደመድምበት ጊዜ ሲያዳምጡት የነበሩት ሰዎች በተጠቀሰው ጉዳይ ላይ መስማማታቸውን ለመግለጽ በልባቸው ወይም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “አሜን” ማለት ይችላሉ።—1 ቆሮንቶስ 14:16
8. የምናቀርባቸው አንዳንድ ጸሎቶች ያዕቆብ ወይም አብርሃም ካቀረቡት ጸሎት ጋር ሊመሳሰሉ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህስ ስለ እኛ ምን ያሳያል?
8 አንዳንዴ አምላክ በጸሎት የለመንነውን ነገር ምን ያህል አጥብቀን እንደምንሻው በግልጽ እንድናሳይ ይፈልጋል። በረከት ለማግኘት ሲል ከመልአክ ጋር ሲታገል እንዳደረው እንደ ጥንቱ ያዕቆብ መሆን ይኖርብን ይሆናል። (ዘፍጥረት 32:24-26) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሎጥን ጨምሮ በሰዶም ሊገኙ ይችላሉ ብሎ ያሰባቸው ጻድቅ ሰዎችን አስመልክቶ ወደ ይሖዋ ተደጋጋሚ ልመና እንዳቀረበው እንደ አብርሃም ማድረግ ይጠበቅብን ይሆናል። (ዘፍጥረት 18:22-33) እኛም በተመሳሳይ ከፍትሑ፣ ከፍቅራዊ ደግነቱና ከምሕረቱ ጋር የሚስማማ ጸሎት በማቅረብ ከፍ አድርገን የምንመለከታቸውን ነገሮች እንዲሰጠን ይሖዋን መለመን እንችላለን።
ስለ ምን ነገሮች መጸለይ እንችላለን?
9. በጸሎታችን ውስጥ ቅድሚያ ሊይዝ የሚገባው ምን መሆን ይኖርበታል?
9 ጳውሎስ “በነገር ሁሉ . . . ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ” ማለቱን አስታውስ። (ፊልጵስዩስ 4:6) በመሆኑም በግል የምናቀርባቸው ጸሎቶች ማንኛውንም ዓይነት የሕይወት ዘርፍ የሚዳስሱ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁንና በጸሎታችን ውስጥ የመጀመሪያ ቦታ ሊይዝ የሚገባው የይሖዋ ፍላጎት መሆን ይኖርበታል። በዚህ ረገድ ዳንኤል ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ዳንኤል፣ እስራኤላውያን በሠሩት ኃጢአት ሳቢያ ለቅጣት በተዳረጉ ጊዜ ምሕረት እንዲያሳያቸው “አምላኬ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል አትዘግይ” በማለት ይሖዋን ተማጽኗል። (ዳንኤል 9:15-19) የእኛስ ጸሎት በዋነኝነት የሚያሳስበን የይሖዋ ስም መቀደስና የፈቃዱ መፈጸም መሆኑን የሚያንጸባርቅ ነው?
10. በግል ስለሚያስፈልጉን ነገሮች መጸለያችን ተገቢ መሆኑን እንዴት እናውቃለን?
10 ያም ሆኖ ግን ስለ ግል ጉዳዮቻችንም መጸለያችን ተገቢ ነው። ለአብነት ያህል፣ ልክ እንደ መዝሙራዊው መንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ለማግኘት መጸለይ እንችላለን። መዝሙራዊው “ሕግህን እንድጠብቅ፣ በፍጹም ልቤም እንድታዘዘው፣ ማስተዋልን ስጠኝ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 119:33, 34፤ ቈላስይስ 1:9, 10) ኢየሱስ “ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው ጸሎትንና ልመናን” አቅርቧል። (ዕብራውያን 5:7) ይህም አንድ ሰው አደገኛ ሁኔታ ሲገጥመው ወይም ችግር ሲደርስበት ጥንካሬ ለማግኘት መጸለዩ ተገቢ መሆኑን ያሳያል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማራቸው የናሙና ጸሎት ላይ የበደል ይቅርታና የዕለት እንጀራ ለማግኘት ልመና ማቅረብን የመሳሰሉ የግል ጉዳዮችን አካቷል።
11. ጸሎት በፈተና እንዳንሸነፍ የሚረዳን እንዴት ነው?
11 በዚህ የናሙና ጸሎት ላይ ኢየሱስ “ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን እንጂ” የሚል ልመናም አካትቷል። (ማቴዎስ 6:9-13) ቆየት ብሎም “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ማቴዎስ 26:41) ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ መጸለያችን በጣም አስፈላጊ ነው። በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ቅዱስ ጹሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ችላ እንድንል ልንፈተን እችላለን። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች አጠያያቂ በሆኑ እንቅስቃሴዎች እንድንካፈል ሊጋብዙን ይችላሉ። የጽድቅ አቋማችንን የሚያጎድፍ ተግባር እንድንፈጽም ጥያቄ ይቀርብልንም ይሆናል። በእነዚህ ጊዜያት፣ በፈተና ከመውደቅ ይጠብቀን ዘንድ አምላክን በጸሎት እንድንጠይቅ ኢየሱስ የሰጠንን ምክር መከተላችን አስፈላጊ ነው። ከፈተና በፊትም ሆነ በፈተና ወቅት እንዲህ ማድረጋችን የጥበብ እርምጃ ነው።
12. ወደ ይሖዋ እንድንጸልይ የሚገፋፉን አንዳንድ አስጨናቂ ሁኔታዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ከይሖዋስ ምን ልንጠብቅ እንችላለን?
12 በዛሬው ጊዜ፣ የአምላክ አገልጋዮች በሕይወታቸው ውስጥ የተለያዩ ተጽዕኖዎችና አስጨናቂ ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል። ለብዙዎች የጭንቀት መንስኤ ከሆኑት ነገሮች መካከል ሕመምና የስሜት ቀውስ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። በአካባቢያችን የሚፈጸሙት የዓመጽ ድርጊቶች ሕይወታችንን አስጨናቂ ያደርጉታል። የኢኮኖሚ ችግሮች ሰዎች ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንዳያገኙ እንቅፋት ሆነዋል። ይሖዋ፣ እነዚህን የመሳሰሉትን ችግሮች አስመልክተው አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ልመና ለማድመጥ ፈቃደኛ መሆኑን ማወቃችን ምንኛ ያጽናናል! መዝሙር 102:17 ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “እርሱ ወደ ችግረኞች ጸሎት ይመለከታል፤ ልመናቸውንም አይንቅም” ይላል።
13. (ሀ) ስለ የትኞቹ የግል ጉዳዮቻችን መጸለያችን ተገቢ ነው? (ለ) ይህን የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
13 እውነት ነው፣ ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት ወይም ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና የሚነካብንን ማንኛውንም ነገር አስመልክተን መጸለያችን ተገቢ ነው። (1 ዮሐንስ 5:14) ጋብቻን፣ ሥራን ወይም የአገልግሎት እንቅስቃሴን ከፍ ማድረግን አስመልክቶ ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልግህ በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ ቀርበህ የእርሱን መመሪያ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። ለምሳሌ ያህል፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመካፈል ፍላጎት የነበራትን አንዲት በፊሊፒንስ የምትኖር ወጣት ሁኔታ ተመልከት። ይህች ወጣት በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት ትፈልግ የነበረ ቢሆንም ራሷን ለመደገፍ የሚያስችል ሥራ አልነበራትም። እንዲህ ትላለች:- “አንድ ቅዳሜ ጠዋት፣ አቅኚ ለመሆን እንደምፈልግ ለይቼ በመጥቀስ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ረፋዱ ላይ በመስክ አገልግሎት ላይ ላገኘኋት አንዲት በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ለምትገኝ ልጅ መጽሐፍ አበረከትኩላት። በዚህ ጊዜ ልጅቷ በድንገት ‘ሰኞ ጠዋት ወደ ትምህርት ቤታችን መሄድ አለብሽ’ አለችኝ። እኔም ‘ለምን?’ ስል ጠየኳት። እርሷም ትምህርት ቤታቸው ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ የሥራ ማስታወቂያ እንዳወጣ ገለጸችልኝ። እኔም በተባልኩት መሠረት ወደ ትምህርት ቤቱ ሄድኩና የዚያኑ ዕለት ተቀጠርኩ። ሁሉ ነገር የሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር።” በምድር ዙሪያ ተመሳሳይ ተሞክሮ ያጋጠማቸው በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። በመሆኑም ከልብ የመነጨ ልመናህን ለአምላክ ከማቅረብ ፈጽሞ ወደኋላ አትበል!
ኃጢአት በምንሠራበት ወቅት
14, 15. (ሀ) አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራም እንኳ ከመጸለይ ወደኋላ ማለት የሌለበት ለምንድን ነው? (ለ) ይህ ግለሰብ በመንፈሳዊ እንዲያገግም ራሱ ከሚያቀርበው ጸሎት በተጨማሪ ምን ሊረዳው ይችላል?
14 አንድ ሰው ኃጢአት ሲሠራ ጸሎት ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው? ኃጢአት የሠሩ አንዳንድ ሰዎች የሚሰማቸው የሃፍረት ስሜት እንዳይጸልዩ እንቅፋት ይሆንባቸዋል። ሆኖም ይህ ልንከተለው የሚገባ የጥበብ አካሄድ አይደለም። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- የአውሮፕላን አብራሪዎች፣ ድንገት አቅጣጫቸውን ስተው የት እንዳሉ ማወቅ ቢሳናቸው በምድር ላይ ካለው የበረራ ተቆጣጣሪ ጋር በመገናኘት እርዳታ ሊያገኙ እንደሚችሉ ያውቃሉ። ይሁን እንጂ አቅጣጫው የጠፋበት አንድ አብራሪ የሃፍረት ስሜት ተሰምቶት ከበረራ ተቆጣጣሪው ለመገናኘት ወደኋላ ቢልስ? አስከፊ አደጋ መድረሱ የማይቀር ነው! በተመሳሳይም ኃጢአት የሠራ ሰው ወደ አምላክ ለመጸለይ የሚያፍር ከሆነ የከፋ ችግር ሊገጥመው ይችላል። አንድ ሰው ኃጢአት መሥራቱ ያስከተለበት የሃፍረት ስሜት ወደ አምላክ ከመጸለይ ሊያግደው አይገባም። እንዲያውም አምላክ ከባድ ስህተት የፈጸሙ ሰዎችን ወደ እርሱ እንዲጸልዩ ግብዣ አቅርቦላቸዋል። ነቢዩ ኢሳይያስ በዘመኑ ይኖሩ የነበሩ ኃጢአት አድራጊዎችን “ይቅርታው ብዙ” መሆኑን በመግለጽ ወደ ይሖዋ እንዲጣሩ አሳስቧቸዋል። (ኢሳይያስ 55:6, 7) እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ‘የይሖዋን ፊት ለመፈለግ’ ትሑት በመሆን ከኃጢአት ጎዳና መመለስና ከልቡ ንስሐ መግባት ይኖርበታል።—መዝሙር 119:58፤ ዳንኤል 9:13
15 ኃጢአት የሠራ ሰው መጸለዩ አስፈላጊ የሚሆንበት ሌላም ምክንያት አለ። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ መንፈሳዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው ማድረግ ያለበትን ሲገልጽ ‘የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም ይጸልዩለት። ጌታም ያስነሣዋል’ ብሏል። (ያዕቆብ 5:14, 15) እውነት ነው፣ ግለሰቡ የሠራውን ኃጢአት በጸሎት አማካኝነት ለይሖዋ መናዘዝ ይገባዋል፤ ሆኖም ከዚህ ጎን ለጎን ሽማግሌዎችን መጥራትና እንዲጸልዩለት መጠየቅ ይችላል። ይህም በመንፈሳዊ እንዲያገግም ይረዳዋል።
ለጸሎታችን የምናገኘው ምላሽ
16, 17. (ሀ) ይሖዋ ለጸሎት ምላሽ የሚሰጠው እንዴት ነው? (ለ) ጸሎትና የስብከቱ ሥራ የተያያዙ መሆናቸውን የትኞቹ ተሞክሮዎች ያሳያሉ?
16 ጸሎቶቻችን ምላሽ የሚያገኙት እንዴት ነው? አንዳንድ ጸሎቶች ወዲያው እንዲሁም ግልጽ በሆነ መንገድ ምላሽ ያገኙ ይሆናል። (2 ነገሥት 20:1-6) ሌሎቹ ደግሞ ጊዜ ሊወስዱና በማናስተውለው መንገድ ሊመለሱ ይችላሉ። ኢየሱስ ወደ አንድ ዳኛ ሳትታክት ትመላለስ ስለነበረች አንዲት መበለት የተናገረው ምሳሌ እንደሚያሳየው ወደ አምላክ ደጋግሞ መጸለይ አስፈላጊ ነው። (ሉቃስ 18:1-8) ይሁን እንጂ ጸሎታችን ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እስከሆነ ድረስ መቼም ቢሆን፣ ይሖዋ ‘አታስቸግሩኝ’ እንደማይለን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሉቃስ 11:5-9
17 የይሖዋ ሕዝቦች ለአምላክ የቀረቡ በርካታ ጸሎቶች መልስ ሲያገኙ የመመልከት አጋጣሚዎች አግኝተዋል። ይህ ደግሞ በተለይ በአገልግሎታችን ላይ በተደጋጋሚ ያጋጥመናል። ለምሳሌ ያህል በፊሊፒንስ፣ ሁለት እህቶች በአንድ ገለልተኛ ክልል ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማሰራጨት ላይ እያሉ ለአንዲት ሴት ትራክት ያበረክቱላታል። በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ዓይኖቿ እንባ አቅርረው “ትናንት ማታ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምሩኝ ሰዎች እንዲልክልኝ አምላክን በጸሎት ስለምነው ነበር፤ በእርግጥ ይህ የጸሎቴ መልስ ነው” አለቻቸው። ብዙም ሳትቆይ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረች። በደቡብ ምሥራቅ እስያ በሚገኝ ሌላ አካባቢ የሚኖር አንድ ወንድም ደግሞ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት በአንድ መኖሪያ ሕንጻ ውስጥ ገብቶ ለመመሥከር ፈራ። ይሁን እንጂ አንድ ቀን ወደ ይሖዋ ከጸለየ በኋላ በድፍረት ወደ ሕንጻው አመራ። ከዚያም አንዱን መኖሪያ ሲያንኳኳ አንዲት ወጣት በሩን ከፈተችለት። ወንድም ወደ ቤታቸው የመጣው ለምን እንደሆነ በመግለጽ ላይ ሳለ ወጣቷ ማልቀስ ጀመረች። ወጣቷ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመገናኘት ትፈልግ እንደነበረና ይህን ማድረግ እንድትችልም አምላክ እንዲረዳት እንደ ጸለየች ነገረችው። ወንድም በአካባቢው ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጋር እንድትገናኝ ረዳት።
18. (ሀ) ጸሎታችን ምላሽ ሲያገኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለመጸለይ የምንጥር ከሆነ ስለምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
18 በእርግጥም ጸሎት አስደናቂ ዝግጅት ነው። ይሖዋ እኛን ለማዳመጥና ለጸሎቶቻችን መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ ነው። (ኢሳይያስ 30:18, 19) ይሁንና ይሖዋ ለጸሎታችን ምላሽ የሰጠን በምን መልኩ እንደሆነ ማስተዋል ይኖርብናል። መልስ የሚሰጠን ሁልጊዜ እኛ ይሆናል ብለን በጠበቅነው መንገድ ላይሆን ይችላል። ያም ሆኖ አምላክ መመሪያ እንደሰጠን ሲገባን ከልብ የመነጨ ምስጋና ማቅረባችንንና እርሱን ማወደሳችንን በፍጹም መዘንጋት የለብንም። (1 ተሰሎንቄ 5:18) ከዚህም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ” በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ ዘወትር አስታውስ። አዎን፣ በምታገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከአምላክ ጋር ለመነጋገር ጣር። በዚህ መንገድ፣ ጳውሎስ ጸሎታቸው ምላሽ ያገኙ ሰዎችን አስመልክቶ “የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” ሲል የተናገራቸው ቃላት በሕይወትህ ውስጥ ሲፈጸሙ መመልከት ትችላለህ።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ጸሎታችን ምን ዓይነት ይዘት ሊኖረው ይችላል?
• መጸለይ ያለብን እንዴት ነው?
• ስለምን ጉዳዮች መጸለይ እንችላለን?
• አንድ ሰው ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ ጸሎት ምን ዓይነት ሚና ይጫወታል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከልብ የመነጨ ጸሎት በፈተናዎች እንዳንሸነፍ ይረዳናል
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምስጋናችንን፣ የሚያሳስቡንን ነገሮችና ልመናችንን በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ ማቅረብ እንችላለን