በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመዝሙር አምስተኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የመዝሙር አምስተኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የመዝሙር አምስተኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

ሀብታም የሆነ ሰው እንዲህ ይል ይሆናል:- “ወንዶች ልጆቻችን በወጣትነታቸው፣ የተሟላ ዕድገት እንዳገኘ ተክል፣ ሴቶች ልጆቻችንም ቤተ መንግሥት ለማስጌጥ፣ እንደ ተቀረጹ የማእዘን ዐምዶች ይሁኑ። ጐተራዎቻችን . . . የተሞሉ ይሁኑ፤ በጎቻችን እስከ ሺህ ይውለዱ።” ከዚህም በላይ ባለጠጎች ‘ይህ ባርኮት ገንዘቡ የሆነ ሕዝብ ደስተኛ ነው’ ብለው ሊናገሩ ይችላሉ። ከዚህ በተቃራኒ ግን መዝሙራዊው ‘እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ደስተኛ ነው’ ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 144:12-15) ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ይሖዋ ደስተኛ አምላክ በመሆኑ እርሱን እያመለኩ ያሉ ሰዎችም ደስተኞች መሆናቸው አይቀርም። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) የዚህ አባባል እውነተኝነት በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ከ107 እስከ 150 ያሉትን መዝሙራት በያዘው በመጨረሻው የመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል።

በተጨማሪም አምስተኛው የመዝሙር መጽሐፍ ፍቅራዊ ደግነትን፣ እውነተኝነትንና ቸርነትን ስለመሳሰሉት የይሖዋ ወደር የለሽ ባሕርያት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ስለ አምላክ ማንነት ጥልቅ ማስተዋል ባገኘን መጠን እርሱን እየወደድነውና እየፈራነው እንሄዳለን። ይህ ደግሞ ለደስታችን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከመዝሙር አምስተኛ መጽሐፍ ላይ በጣም ጠቃሚ የሆነ ትምህርት እናገኛለን!—ዕብራውያን 4:12

ከይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት የተነሳ ደስተኛ መሆን

(ከመዝሙር 107:1 እስከ 119:176)

ከባቢሎን ምርኮ የተመለሱት አይሁዳውያን “እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ [“ፍቅራዊ ደግነቱ፣” NW]፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት” በማለት ዘምረዋል። (መዝሙር 107:8, 15, 21, 31) ዳዊትም “ታማኝነትህ [“እውነተኝነትህ፣” NW] እስከ ጠፈር ትደርሳለች” በማለት አምላክን በመዝሙር አወድሷል። (መዝሙር 108:4) በተከታዩ መዝሙር ላይ ደግሞ “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ርዳኝ፤ እንደ ምሕረትህም [“ፍቅራዊ ደግነትህ፣” NW] አድነኝ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 109:18, 19, 26) መዝሙር 110 ስለ መሲሑ አገዛዝ የተነገረ ትንቢት ነው። በመዝሙር 111:10 ላይ “እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው” ይላል። ቀጥሎ ያለው መዝሙር እንደሚናገረው ደግሞ “እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ . . . የተባረከ [“ደስተኛ፣” NW] ነው።”—መዝሙር 112:1

ከ113 እስከ 118 ድረስ ያሉት መዝሙራት “ሃሌ ሉያ” ወይም “ያህን አመስግኑ” የሚሉትን አባባሎች በተደጋጋሚ ስለሚጠቀሙ የሃሌል መዝሙሮች ተብለው ይጠራሉ። ሚሽና የሚባለው በቃል ሲተላለፉ የቆዩ ጥንታዊ ወጎችን የያዘው የሦስተኛው መቶ ዘመን የጽሑፍ ሥራ እንደሚናገረው ከሆነ እነዚህ መዝሙራት በአይሁዳውያን የማለፍ በዓል እንዲሁም በሦስቱ ዓመታዊ በዓላት ላይ የሚዘመሩ ናቸው። ከመዝሙራትም ሆነ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች በጣም ረጅም የሆነው መዝሙር 119 ይሖዋ ስለገለጸው ቃል ወይም መልእክት ጎላ አድርጎ ይናገራል።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

109:23—ዳዊት “እንደ ምሽት ጥላ ከእይታ ተሰውሬአለሁ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? ዳዊት የመሞቻው ጊዜ በጣም መቅረቡ እንደተሰማው በምሳሌያዊ አነጋገር መግለጹ ነበር።—መዝሙር 102:11

110:1, 2—ዳዊት “ጌታዬ” ብሎ የጠራው ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት ወቅት ምን ይሠራ ነበር? ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በ1914 ንጉሥ ሆኖ እስከ ተሾመበት ጊዜ ድረስ በአምላክ ቀኝ ተቀምጦ ነበር። በእነዚያ ጊዜያት በመንፈስ በተቀቡት ተከታዮቹ ላይ ይገዛ ነበር። ይህን ያደረገው በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አመራር በመስጠትና በመንግሥቱ ከእርሱ ጋር ገዥ ለሚሆኑበት ጊዜ በማዘጋጀት ነበር።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:18-20፤ ሉቃስ 22:28-30

110:4—ይሖዋ ‘ሐሳቡን የማይለውጥበት መሐላ’ ምንድን ነው? ይህ መሐላ ይሖዋ ንጉሥና ሊቀ ካህን ሆኖ እንዲያገለግል ከሾመው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የሚያመለክት ነው።—ሉቃስ 22:29

113:3—የይሖዋ ስም “ከፀሓይ መውጫ እስከ መግቢያው ድረስ” የተመሰገነ የሚሆነው በምን መንገድ ነው? ይህ አባባል ለአምላክ የዕለት ተዕለት አምልኮ የሚያቀርቡት በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ጥቂት ሰዎች ብቻ እንዳልሆኑ ያመለክታል። ፀሐይ ከምትወጣበት ከምሥራቅ አንስቶ እስከምትጠልቅበት እስከ ምዕራብ ድረስ ብርሃኗ በመላው ምድር ላይ ያበራል። በተመሳሳይም ይሖዋ በምድር ዙሪያ መወደስ ይገባዋል። ይህ ደግሞ በደንብ መደራጀትን ይጠይቃል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን እርሱን የማወደስ እንዲሁም መንግሥቱን በማወጁ ሥራ ላይ በቅንዓት የመካፈል ትልቅ መብት አግኝተናል።

116:15—“የቅዱሳን ሞት፣ በእግዚአብሔር ፊት” ምን ያህል ‘ክቡር’ ነው? ይሖዋ አምላኪዎቹ በፊቱ በጣም ውድ ስለሆኑ በቡድን ደረጃ እንዲሞቱ መፍቀዱ ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚሆንበት አድርጎ ይቆጥረዋል። ይህ ሁኔታ እንዲከሰት ቢፈቅድ ጠላቶቹ ከእርሱ የበለጠ ኃይል ያላቸው ያህል ይሆናል። ከዚህም በላይ ለአዲሱ ዓለም መሠረት የሚሆኑ ሰዎች በምድር ላይ አይኖሩም ነበር።

119:71—በመከራ ውስጥ ማለፍ መልካም የሚሆነው እንዴት ነው? መከራ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እንድንታመን፣ ከልብ ወደ እርሱ እንድንጸልይ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት እንድናጠናና ያገኘነውን እውቀት ተግባራዊ እንድናደርግ ያስተምረናል። ከዚህም በላይ መከራ ሲደርስብን የምንወስደው እርምጃ ያለን ጉድለት ጎልቶ እንዲታይ ያደርጋል። መከራ እንዲያስተካክለን ወይም እንዲያጠራን የምንፈቅድ ከሆነ እንድንማረር አያደርገንም።

119:96—‘ለፍጹምነት ሁሉ ዳርቻ አለው’ ሲባል ምን ማለት ነው? መዝሙራዊው ስለ ፍጽምና የተናገረው ከሰው አመለካከት አንጻር ነው። እንዲሁም ሰው ስለ ፍጽምና ያለው እውቀት ውስን መሆኑን በአእምሮው ይዞ መሆን አለበት። በአንጻሩ ደግሞ የአምላክ ትእዛዝ እንዲህ ያለ ወሰን የለውም። የእርሱ መመሪያ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች የሚሠሩ ናቸው።

119:164—‘በቀን ሰባት ጊዜ’ አምላክን ማመስገን ሲባል ምን ማለት ነው? ሰባት ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው ሙላትን ነው። ስለዚህ መዝሙራዊው ይህን ሲል ይሖዋ ሁሉም ሊያመሰግነው የሚገባ መሆኑን ማመልከቱ ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

107:27-31 [የ1954 ትርጉም]:- የአርማጌዶን ጦርነት በሚጀምርበት ወቅት የዓለም ጥበብ ‘ይዋጣል።’ (ራእይ 16:14, 16) ይህ ጥበብ ማንንም ከጥፋት አያድንም። ከጥፋቱ በሕይወት ተርፈው ስለ ምሕረቱ ወይም ስለ ፍቅራዊ ደግነቱ ይሖዋን የሚያመሰግኑት መዳን ለማግኘት በእርሱ የሚተማመኑ ብቻ ናቸው።

109:30, 31፤ 110:5:- አንድ ወታደር አብዛኛውን ጊዜ ጋሻ የሚይዘው በግራ እጁ እንደመሆኑ መጠን ሰይፍ የሚይዝበት ቀኝ እጁ ለጥቃት የተጋለጠ ነው። በምሳሌያዊ አነጋገር ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ለመዋጋት ‘በቀኛቸው’ ይቆማል። በዚህ መንገድ ጥበቃ ያደርግላቸዋል እንዲሁም ይረዳቸዋል። ይህም እርሱን ‘እጅግ እንድናመሰግነው’ ትልቅ ምክንያት ይሆነናል!

113:4-9:- ይሖዋ እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ ‘በሰማይ ያሉትን ለማየት’ እንኳ ራሱን ወደ ታች ዝቅ ያደርጋል። ያም ሆኖ ግን ለድኻው፣ ለችግረኛውና ለመካኒቱ ሴት ርኅራኄ ያሳያል። ሉዓላዊ ጌታ የሆነው ይሖዋ ትሑት ሲሆን አምላኪዎቹም እንዲህ ያሉትን ሰዎች በዚህ መንገድ እንዲይዙ ይፈልጋል።—ያዕቆብ 4:6

114:3-7:- ይሖዋ ለሕዝቦቹ ሲል በቀይ ባሕር፣ በዮርዳኖስ ወንዝና በሲና ተራራ የፈጸማቸውን አስደናቂ ነገሮች ማወቃችን በጥልቅ ሊነካን ይገባል። “በምድር” የተመሰሉት የሰው ልጆች በጌታ በይሖዋ ፊት ‘ሊንቀጠቀጡ’ በሌላ አነጋገር በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ሊዋጡ ይገባቸዋል።

119:97-101:- ከአምላክ ቃል ጥበብና ማስተዋል ማግኘታችን ከመንፈሳዊ ጉዳት ይታደገናል።

119:105:- የአምላክ ቃል ለእግራችን መብራት የሚሆነው በጊዜያችን ለሚያጋጥሙን ችግሮች መፍትሔ እንድናገኝ ስለሚረዳን ነው። እንዲሁም የአምላክን የወደፊት ዓላማ ስለሚያሳውቀን በምሳሌያዊ ሁኔታ መንገዳችንን ያበራልናል።

መከራ እያለም ደስተኛ መሆን

(ከመዝሙር 120:1 እስከ 145:21)

በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎችን መጋፈጥም ሆነ የሚያጋጥሙንን መከራዎች መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? ከመዝሙር 120 እስከ 134 ያሉት መዝሙሮች ለዚህ ጥያቄ ግልጽ የሆነ መልስ ይሰጣሉ። ይሖዋ እንዲረዳን በመጠየቅ የሚያጋጥሙንን ችግሮች መቋቋም እንዲሁም ደስተኛ ሆነን መኖር እንችላለን። እነዚህ መዝሙራት የመዓርግ መዝሙር የሚባሉ ሲሆን ምናልባትም እስራኤላውያን ዓመታዊ በዓላትን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ በመንገድ ላይ የሚዘምሯቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

በመዝሙር 135 እና 136 ላይ ይሖዋ ምንም ከማይረቡ ጣዖታት በተቃራኒ የፈለገውን ማድረግ የሚችል አምላክ እንደሆነ ተገልጿል። መዝሙር 136 የተቀናበረው የእያንዳንዱ ጥቅስ ሁለተኛ ስንኝ ለመጀመሪያው ስንኝ እንደ ምላሽ ሆኖ እንዲዘመር ተደርጎ ነው። ቀጣዩ መዝሙር ደግሞ ይሖዋን በጽዮን ለማምለክ ቢፈልጉም በባቢሎን ምርኮ ሥር የቆዩት አይሁዳውያን ስለነበሩበት አሳዛኝ ሁኔታ ይናገራል። ከ138 እስከ 145 ያለውን መዝሙር ያቀናበረው ዳዊት ነው። ዳዊት ይሖዋን ‘በፍጹም ልቡ ሊያመሰግነው’ ይፈልግ ነበር። ለምን? እርሱ ራሱ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና” በማለት ምክንያቱን ተናግሯል። (መዝሙር 138:1፤ 139:14) በመጨረሻዎቹ አምስት መዝሙራት ላይ ዳዊት ከክፉ ሰዎች እንዲያድነው፣ በጽድቅ እንዲገሥጸው፣ ከአሳዳጆች እንዲታደገው እንዲሁም ባሕርይውን በተመለከተ መመሪያ እንዲሰጠው ወደ ይሖዋ ጸሎት አቅርቧል። የይሖዋ ሕዝቦች ያላቸውን ደስታም ጎላ አድርጎ ገልጿል። (መዝሙር 144:15) ዳዊት ስለ አምላክ ታላቅነትና ቸርነት ከገለጸ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል፤ ፍጡር ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ ቅዱስ ስሙን ይባርክ።”—መዝሙር 145:21

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

122:3—ኢየሩሳሌም “እጅግ እንደ ተጠጋጋች” ከተማ የሆነችው እንዴት ነው? በጥንት ዘመን እንደነበሩት ከተሞች ሁሉ በኢየሩሳሌም ያሉ ቤቶች ተጠጋግተው የተሠሩ ናቸው። ቤቶቿ ተጠጋግተው የተሠሩ መሆናቸው ጠላትን ለመከላከል አመቺ እንድትሆን አድርጓታል። ከዚህም በላይ የቤቶቹ አሠራር የከተማይቱ ነዋሪዎች እርዳታና ጥበቃ ለማግኘት አንዳቸው በሌላው ላይ እንዲተማመኑ አስችሏቸዋል። ይህ ሁኔታ 12ቱ የእስራኤል ነገዶች ለአምልኮ በሚወጡበት ጊዜ ያላቸውን መንፈሳዊ አንድነት ያመለክታል።

123:2—ስለ ባሪያዎቹ ዓይን የተነገረው ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው? ወንድም ሆኑ ሴት አገልጋዮች ወደ ጌታቸው ወይም እመቤታቸው እጅ የሚመለከቱት በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው። ጌታው ወይም እመቤቲቱ ምን እንደፈለጉ ለማወቅ እንዲሁም ጥበቃና ለሕይወታቸው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት ነው። እኛም በተመሳሳይ የይሖዋን ፈቃድ ለማወቅና የእርሱን ሞገስ ለማግኘት ወደ ይሖዋ እንመለከታለን።

131:1-3—ዳዊት ‘ጡት የጣለ ልጅ ዐርፎ እናቱ ላይ እንደሚቀመጥ ነፍሱን ጸጥና ዝም ያሰኛት’ እንዴት ነበር? ጡት የጣለ ልጅ በእናቱ እቅፍ ውስጥ መሆኑ እንደሚያረካውና እንደሚጽናናው ሁሉ ዳዊትም ‘ጡት እንዳስተዉት ሕፃን’ ነፍሱን ማጽናናትና ማረጋጋት እንዳለበት ተምሯል። እንዴት? በልቡ ባለመታበይ፣ በዐይኑም ታላቅ ለመሆን ባለመጓጓት እንዲሁም ከአቅሙ በላይ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት ባለመጣጣር ነው። ዳዊት ታዋቂ ለመሆን ከመፈለግ ይልቅ ያሉትን የአቅም ገደቦች ተገንዝቦ ትሕትና አሳይቷል። እኛም በተለይ በጉባኤ ውስጥ ወደ አንድ ልዩ መብት ስንደርስ የእርሱን ዝንባሌ መኮረጃችን ጥበብ ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

120:1, 2, 6, 7:- ስም የሚያጠፋ እንዲሁም ሽሙጥ የተቀላቀለበት ንግግር በሌሎች ላይ ከባድ ጭንቀት ሊፈጥር ይችላል። አንደበታችንን መግታታችን “ሰላም ፈላጊ” እንደሆንን የምናሳይበት አንዱ መንገድ ነው።

120:3, 4:- “ሐሰተኛ አንደበት” ያለውን ሰው ታግሶ መኖር ግድ ቢሆንብን ይሖዋ እርሱ በፈቀደው ቀን ሁኔታውን እንደሚያስተካክለው ማወቃችን ሊያጽናናን ይችላል። ስም አጥፊዎች ‘በጦረኛው’ እጅ መከራ ይደርስባቸዋል። እንዲሁም “በግራር ከሰል ፍም” ከተመሰለው ከአስፈሪው የይሖዋ ፍርድ ፈጽሞ አያመልጡም።

127:1, 2:- በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ የይሖዋን አመራር ለማግኘት ጥረት ማድረግ አለብን።

133:1-3:- በይሖዋ ሕዝቦች መካከል የሚታየው አንድነት የሚያረጋጋ፣ የሚያንጽ እንዲሁም መንፈስን የሚያድስ ነው። ነቃፊ በመሆን፣ ጠብ በመፍጠር ወይም በማጉረምረም ይህን ሰላም ማደፍረስ አይኖርብን።

137:1, 5, 6:- በግዞት የተወሰዱት የይሖዋ አምላኪዎች የአምላክን ድርጅት የምትወክለውን ጽዮንን ፈጽሞ አልረሱም ነበር። እኛስ? ይሖዋ ዛሬ ከሚጠቀምበት ድርጅት ጋር በታማኝነት ተጣብቀናል?

138:2 [የ1879 ትርጉም]:- ይሖዋ ‘ተስፋውን ከስሙ ሁሉ በላይ ማድረጉ’ በስሙ የገባው ማንኛውም ተስፋ የሚያገኘው ፍጻሜ እኛ ከምናስበው እጅግ እንደሚበልጥ ያሳያል። በእርግጥም ወደፊት እጅግ አስደናቂ ተስፋ ይጠብቀናል።

139:1-6, 15, 16:- ይሖዋ ሥራችንን፣ አስተሳሰባችንን እንዲሁም ምን ለመናገር እንዳሰብን ጭምር ያውቃል። ገና በእናታችን ማኅፀን እያለን ሌላው ቀርቶ እያንዳንዱ የሰውነታችን ክፍል እንኳ መለየት ከመጀመሩ በፊት ያውቀናል። አምላክ በግለሰብ ደረጃ ስለ እያንዳንዳችን ያለው እውቀት በጣም “ድንቅ” ይኸውም ከእኛ የመረዳት ችሎታ በላይ ነው። ይሖዋ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ መሆናችንን ብቻ ሳይሆን መከራው እያደረሰብን ያለውን ሥቃይ ጭምር እንደሚረዳልን ማወቃችን እንዴት የሚያጽናና ነው!

139:7-12:- አምላክ እኛን ለማበርታት ቦታ አያግደውም።

139:17, 18:- ከይሖዋ የሚገኘው እውቀት ደስታ አስገኝቶልናል? (ምሳሌ 2:10) ከሆነ ፈጽሞ የማይደርቅ የደስታ ምንጭ ሆኖልናል ማለት ነው። የይሖዋ ሐሳቦች ‘ከአሸዋ ይልቅ ብዙ ናቸው።’ ስለዚህ ምንጊዜም ቢሆን ስለ እርሱ ልንማረው የምንችለው ብዙ ነገር አለ።

139:23, 24:- ይሖዋ ውስጣዊ ማንነታችንን መርምሮ ‘የክፋት መንገድ’ ማለትም ተገቢ ያልሆኑ ሐሳቦች፣ ምኞቶችና ዝንባሌዎች ካሉብን እነዚህን ባሕርያት ነቅለን ማውጣት እንድንችል እንዲረዳን መፈለግ ይኖርብናል።

143:4-7:- ከባድ መከራ ሲገጥመን መጽናት የምንችለው እንዴት ነው? መዝሙራዊው ለዚህ ቁልፍ የሆኑት ነገሮች በይሖዋ ሥራዎች ላይ ማሰላሰል፣ በእጁ ሥራዎች ላይ ማውጠንጠን እንዲሁም እርሱ እንዲረዳን መጸለይ እንደሆኑ ተናግሯል።

“ሕዝቦች ሁሉ ያህን አመስግኑ!”

የመጀመሪያዎቹ አራት የመዝሙር መጻሕፍት የሚደመደሙት ይሖዋን በሚያወድሱ ቃላት ነው። (መዝሙር 41:13፤ 72:19, 20፤ 89:52፤ 106:48) አምስተኛውም መጽሐፍ ቢሆን ተመሳሳይ ነው። መዝሙር 150:6 [NW] “እስትንፋስ ያለው ሁሉ ያህን ያመስግን። ሕዝቦች ሁሉ ያህን አመስግኑ!” ይላል። ይህ ሁኔታ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጻሜውን ያገኛል።

አስደሳች የሆነውን ጊዜ በጉጉት ስንጠባበቅ እውነተኛውን አምላክ ከፍ ከፍ የምናደርግበትና ስሙን የምናወድስበት በቂ ምክንያት አለን። ይሖዋን በማወቃችን እንዲሁም ከእርሱ ጋር ጥሩ ዝምድና በመመሥረታችን ምክንያት የምናገኘውን ደስታ ስናስብ ልባችን በአመስጋኝነት መንፈስ ተሞልቶ እርሱን ለማወደስ አንገፋፋም?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ድንቅ ሥራዎች በአድናቆት ስሜት እንድንዋጥ ያደርጉናል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ሐሳቦች ‘ከአሸዋ ይልቅ ብዙ ናቸው’