በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምትወዱት ሰው ይሖዋን ማምለኩን ሲያቆም

የምትወዱት ሰው ይሖዋን ማምለኩን ሲያቆም

የምትወዱት ሰው ይሖዋን ማምለኩን ሲያቆም

ማርክና ሉዊዝ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። a መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን ወላጆችን በሚያዘው መሠረት በፍቅርና በአሳቢነት በመነሳሳት ለልጆቻቸው ቅዱሳን ጽሑፎችን አስተምረዋቸዋል። (ምሳሌ 22:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:15) ልጆቻቸው እያደጉ ሲሄዱ ግን ይሖዋን ማገልገላቸውን የቀጠሉት ሁሉም አለመሆናቸው የሚያሳዝን ነው። ሉዊዝ “ልጆቼ ይሖዋን ማምለካቸውን ሲያቆሙ ልቤ በሐዘን ተሰበረ” በማለት ተናግራለች። አክላም “ያስከተለብኝን ከፍተኛ ጉዳት ደብቄ መኖር እንዴት እችላለሁ? ሌሎች ስለ ልጆቻቸው ሲናገሩ የሆነ ስሜት የሚተናነቀኝ ከመሆኑም በላይ እንባ በዓይኔ ግጥም ይላል” ብላለች።

አንድ ሰው ከይሖዋ ሲርቅ እንዲሁም በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በተገለጸው የዘላለም ሕይወት ጎዳና መመላለሱን ሲተው ታማኝ የሆኑት የቤተሰቦቹ አባላት ጥልቅ የሆነ የሐዘን ስሜት እንደሚሰማቸው የተረጋገጠ ነው። አይሪን የተባለች አንዲት ሴት “እህቴን በጣም ስለምወዳት ወደ ይሖዋ እንድትመለስ የማላደርገው ነገር የለም!” በማለት ተናግራለች። ማሪያ ወንድሟ ጀርባውን ለይሖዋ በመስጠት ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር በመጀመሩ የተሰማትን ስሜት እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “በሌሎች ነገሮች ረገድ ጥሩ ወንድሜ በመሆኑ ሁኔታውን ለመቋቋም በጣም ከብዶኛል። በተለይም በርካታ ዘመዶቻችን በሚገኙባቸው የቤተሰብ ዝግጅቶች ላይ ስለማይገኝ በጣም ይሰማኛል።”

በጣም ከባድ የሆነው ለምንድን ነው?

ልጅ ወይም ሌላ የሚወዱት ሰው ይሖዋን ማገልገሉን ሲተው ክርስቲያን ዘመዶቹ ይህን መሰሉ ጥልቅ ሐዘን የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት እስከ መጨረሻው ለይሖዋ ታማኝ ሆነው የሚቀጥሉ ብቻ እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገር ስለሚያውቁ ነው። (መዝሙር 37:29፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3-5) ይህንን ደስታ የተሞላበት ሕይወት ከትዳር ጓደኛቸው፣ ከልጆቻቸው፣ ከወላጆቻቸው፣ ከእህትና ከወንድሞቻቸው እንዲሁም ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ማጣጣም ይፈልጋሉ። ይሖዋን ማምለክ የተዉ እነዚህ ዘመዶቻቸው ይህን ሕይወት እንደማያገኙት ሲያስቡ በጣም ያዝናሉ! በተጨማሪም ክርስቲያኖች፣ ይሖዋ ያወጣቸው ሕጎች እንዲሁም መሠረታዊ ሥርዓቶች በዛሬው ጊዜም ቢሆን እነርሱን የሚጠቅሙ እንደሆኑ ይገነዘባሉ። ስለዚህ የሚወዷቸው ሰዎች እነዚህን ሕጎች ባለመጠበቃቸው መራራ ውጤት ሲያጭዱ መመልከታቸው ያሳዝናቸዋል።—ኢሳይያስ 48:17, 18፤ ገላትያ 6:7, 8

ምናልባት ይሖዋን ማምለኩን የተወ ዘመድ የሌለው አንድ ሰው ሥቃዩ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መረዳት ሊከብደው ይችላል። ይሁን እንጂ የአንድን ሰው አጠቃላይ ሕይወት የሚነካ ነው። ሉዊዝ “በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሲስቁና ሲነጋገሩ መስማት እንዲሁም ማየት በጣም ከባድ ነገር ነው” በማለት ተናግራለች። አክላም “የምትወዱት ሰው አብሯችሁ ባለመኖሩ ምክንያት አስደሳች የሆነው ወቅት እንኳ የባዶነት ስሜት ያጠላበት ይሆናል” ብላለች። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የእንጀራ ልጁ ለአራት ዓመታት ይሖዋን ማገልገሏን ባቆመች ጊዜ የሆነውን አስታውሶ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “አብዛኛውን ጊዜ፣ የመዝናኛ ጊዜያችን እንኳ ሳይቀር አስቸጋሪ ይሆን ነበር። ለባለቤቴ ስጦታ ሳመጣላት ወይም ቅዳሜንና እሁድን ለማሳለፍ ወደ አንድ አስደሳች ቦታ ስወስዳት ልጅዋ የደስታችን ተካፋይ አለመሆኗን በማሰብ ማልቀስ ትጀምራለች።”

እነዚህ ክርስቲያኖች ነገሩን ከተገቢው በላይ አጋነውት ይሆን? እንደዚያ ማለት አይቻልም። እንዲያውም በተወሰነ መጠንም ቢሆን፣ በአምሳሉ የፈጠረንን የይሖዋን ባሕርያት ያንጸባርቃሉ። (ዘፍጥረት 1:26, 27) ይህ ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋ ሕዝቡ የሆኑት እስራኤላውያን ባመጹበት ወቅት ምን ተሰማው? ከመዝሙር 78:38-41 ዘገባ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ በጣም አዝኖ ነበር። ይሁን እንጂ እርሱ በትሕትና ያስጠነቀቃቸውና የገሠጻቸው ከመሆኑም በላይ ከልብ ንስሐ ሲገቡ በተደጋጋሚ ጊዜያት ይቅር ብሏቸዋል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ ከፍጡራኑ ማለትም ‘ከእጆቹ ሥራዎች’ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያለው ሲሆን በቀላሉ ተስፋ ቆርጦ አይተዋቸውም። (ኢዮብ 14:15፤ ዮናስ 4:10, 11) ሰዎችም ይህ መሰሉ ጥብቅ የመዋደድ ስሜት እንዲኖራቸው አድርጎ የፈጠራቸው ሲሆን በተለይ የቤተሰብ አባላትን የሚያስተሳስራቸው ሰንሰለት በጣም ጠንካራ ነው። ስለዚህ የሚወዱት ሰው ከክርስቲያን ጉባኤ ሲርቅ ዘመዶቹ ማዘናቸው ሊያስደንቀን አይገባም።

በእርግጥም፣ የሚወዱት ሰው ከእውነት መንገድ መውጣት በእውነተኛ አምላኪዎች ላይ ከሚደርሱት ከባድ ፈተናዎች መካከል አንዱ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 14:22) ኢየሱስ እርሱ እየሰበከ ያለው መልእክት በቤተሰብ መካከል መለያየት እንደሚፈጥር ተናግሯል። (ማቴዎስ 10:34-38) እንዲህ ሲባል ግን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ቤተሰብ ይከፋፍላል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የማያምነው ወይም ታማኝ ያልሆነው የቤተሰብ አባል የክርስትናን መንገድ ሲተው ወይም ሲቃወም በቤተሰቡ መካከል ልዩነት ይፈጠራል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ የሚደርስባቸውን ፈተና መቋቋም የሚችሉበትን እርዳታ ስለሚሰጣቸው አመስጋኞች ነን። የምትወዱት ሰው ከእውነት መንገድ በመራቁ የሐዘን ስሜት ተሰምቷችሁ ከሆነ ሐዘናችሁን እንድትቋቋሙ እንዲሁም እርካታና ደስታ እንድታገኙ የሚረዷችሁ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

ችግሩን መቋቋም የሚቻልበት መንገድ

“ራሳችሁን ለማነጽ ትጉ፤ . . . በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።” (ይሁዳ 20, 21) አሁን ካላችሁበት ሁኔታ አንጻር ይሖዋን ማገልገል ላቆመው የቤተሰብ አባል ምንም ማድረግ አትችሉ ይሆናል። የሆነ ሆኖ ራሳችሁንና በታማኝነት ይሖዋን እያገለገሉ ያሉትን የቤተሰባችሁን አባላት በመንፈሳዊ ማነጽ ትችላላችሁ፤ ደግሞም እንደዚያ ማድረግ ይኖርባችኋል። ቬሮኒካ ካሏት ሦስት ወንድ ልጆች መካከል ሁለቱ ይሖዋን ማገልገላቸውን ባቆሙበት ወቅት እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “እኔና ባለቤቴ ልጆቻችን ወደ ልባቸው በሚመለሱበት ወቅት እነርሱን ለመቀበል እንድንችል ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ይዘን መቀጠል እንዳለብን ምክር ተሰጥቶን ነበር። ኮብላዩ ልጅ ወደ ቤቱ በሚመለስበት ወቅት አባቱ እርሱን ለመቀበል በሚያስችል ጥሩ ሁኔታ ሥር ባይሆን ኖሮ የልጁ መጨረሻ ምን ይሆን ነበር?”

ጠንካራ አቋም ይዛችሁ ለመቀጠል ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ በሁሉም መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ መካፈል ይገባችኋል። ይህም ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግንና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን ያጠቃልላል። ሁኔታህ በፈቀደልህ መጠን ሌሎች የጉባኤ አባላትን ለመርዳት ራስህን አቅርብ። እንዲህ ማድረጉ መጀመሪያ አካባቢ ሊከብድህ እንደሚችል እሙን ነው። ቬሮኒካ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “በመጀመሪያ ላይ የወሰድኩት እርምጃ እንደ ቆሰለ እንስሳ ራሴን ማግለል ነበር። ነገር ግን ባለቤቴ መደረግ ያለባቸውን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንድንቀጥል አበረታታኝ። ከስብሰባዎች እንዳንቀር አስፈላጊውን ጥረት ያደርግ ነበር። የአውራጃ ስብሰባ የሚደረግበት ጊዜ ሲደርስ የሰው ፊት ማየት ስለፈራሁ ራሴን ማደፋፈር አስፈልጎኛል። ይሁን እንጂ ስብሰባው ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ አድርጎናል፤ በተለይም በታማኝነት ይሖዋን ማገልገሉን የቀጠለው ልጃችን በዚህ የአውራጃ ስብሰባ በጣም ታንጿል።”

ከላይ የተጠቀሰችው ማሪያ በመስክ አገልግሎት ራስን ማስጠመድ ጠቃሚ ሆኖ ያገኘችው ሲሆን በአሁኑ ወቅት አራት ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ላይ ትገኛለች። በተመሳሳይም ላውራ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “አሁንም ቢሆን በየዕለቱ አለቅሳለሁ። ሆኖም ልጆቼን በማሳደግ ረገድ እንደሌሎቹ ወላጆች ባይሳካልኝም በዚህ የመጨረሻ ዘመን ቤተሰቦችን ሊጠቅም የሚችል ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።” ኬን እና ኢሌኖር ልጆቻቸው አድገው በክርስቲያን ጉባኤ መሰብሰብ ሲያቆሙ የመንግሥቱ ምሥራች ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ለማገልገል ሁኔታቸውን በማመቻቸት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀምረዋል። ይህም ነገሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንዲያዩ ያስቻላቸው ከመሆኑም ባሻገር ከመጠን በላይ በሐዘን እንዳይዋጡ ረድቷቸዋል።

ተስፋ አትቁረጡ። ፍቅር “ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል።” (1 ቆሮንቶስ 13:7) ከላይ የተጠቀሰው ኬን እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ልጆቻችን የእውነትን መንገድ ትተው ሲወጡ የሞቱ ያህል ተሰምቶኝ ነበር። እህቴ ስትሞት ግን ይህ አመለካከቴ ተቀየረ። ልጆቼ ቃል በቃል ስላልሞቱብኝ እንዲሁም አሁንም ቢሆን ይሖዋ ወደ እርሱ እንዲመለሱ መንገዱን ክፍት አድርጎ እንደሚጠብቃቸው ማወቄ ያስደስተኛል።” በእርግጥም ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የእውነትን ቤት ትተው የወጡ ብዙዎች ከጊዜ በኋላ ተመልሰዋል።—ሉቃስ 15:11-24

ራሳችሁን አትኮንኑ። አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች አንዳንድ ነገሮችን በማስታወስ እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ ብለው ራሳቸውን መኮነን ይቀናቸዋል። ይሁን እንጂ ሕዝቅኤል 18:20 አንድ ሰው ኃጢአት ሲሠራ በሁኔታው እርሱ ራሱ እንጂ ወላጆቹ ተጠያቂ እንደማይሆኑ በግልጽ ይናገራል። ደስ የሚለው ግን የምሳሌ መጽሐፍ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግ እንደሚገባቸው በርካታ ምክሮችን የሚለግስ ቢሆንም ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲሰሙና እንዲታዘዙ ከአራት የሚበልጡ ምክሮችን በውስጡ ይዟል። ስለዚህ ልጆች ፍጹማን ያልሆኑ ወላጆቻቸው የሚሰጧቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ሥልጠና የመቀበል ኃላፊነት አለባቸው። በወቅቱ የምትችሉትን ሁሉ አድርጋችሁ እንደሚሆን እሙን ነው። አንዳንድ ስህተቶችን እንደሠራችሁና በእርግጥ ጥፋቱ የእናንተ እንደሆነ ቢሰማችሁ እንኳ የምትወዷቸው ሰዎች እውነትን ትተው ለመውጣታቸው ምክንያቱ የእናንተ ስህተት ነው ማለት ላይሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ “እንዲህ ባደረግኩ ኖሮ” እያሉ ባለፈ ነገር መብከንከን ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። ከሠራችሁት ስህተት ተማሩ፣ እንዲሁም ላለመድገም ጥረት አድርጉ በተጨማሪም ይሖዋ ይቅር እንዲላችሁ ጸልዩ። (መዝሙር 103:8-14፤ ኢሳይያስ 55:7) ከዚህም በላይ ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንጂ ስላለፈው ነገር አታስቡ።

ሌሎችን ታገሡ። በተለይ ሰዎች እንዲህ ያለ ሁኔታ ገጥሟቸው የማያውቅ ከሆነ ምን ብለው ማበረታታት ወይም ማጽናናት እንዳለባቸው ላያውቁ ይችላሉ። ከዚህም ሌላ ሰዎች የሚያበረታታና የሚያጽናና ነው ብለው የሚያስቧቸው ነገሮች የተለያዩ ናቸው። በመሆኑ አንድ ሰው አጽናናለሁ ብሎ የሚያበሳጭ ነገር ቢናገራችሁ ሐዋርያው ጳውሎስ በቈላስይስ 3:13 ላይ “እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ” በማለት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ አድርጉ።

ለይሖዋ የተግሣጽ ዝግጅት አድናቆት ይኑራችሁ። አንድ ዘመዳችሁ ከጉባኤ ሽማግሌዎች ተግሣጽ ቢሰጠው ይህ የይሖዋ ዝግጅት እንደሆነና ኃጢአት የሠራውን ግለሰብ ጨምሮ ለሁሉም ጥቅም እንደሆነ አስታውሱ። (ዕብራውያን 12:11) ስለዚህ በሽማግሌዎች ወይም እነርሱ ባስተላለፉት ውሳኔ ላይ ስህተት የመፈላለግ ዝንባሌ እንዳይኖራችሁ ተጠንቀቁ። የተሻለ ውጤት የሚያስገኘው ነገሮችን በይሖዋ መንገድ መሥራት እንደሆነ አትዘንጉ። በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋን ዝግጅት መቃወም ለሌላ ችግር ይዳርጋል።

እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ ከወጡ በኋላ ሙሴ በዳኝነት አገልግሏል። (ዘፀአት 18:13-16) እርሱ ያስተላለፈው ውሳኔ አንደኛውን ወገን አስደስቶ ሌላኛውን ቅር ሊያሰኝ እንደሚችል የታወቀ ነው፤ ስለዚህ ባስተላለፈው ውሳኔ ያልተደሰቱ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም። አንዳንዶች ሙሴ ባስተላለፋቸው ውሳኔዎች ላይ ስህተት መፈላለጋቸው በእርሱ ሥልጣን ላይ ወደማመጽ መርቷቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሕዝቡን ለመምራት ሙሴን ይጠቀምበት ስለነበር እርሱን ሳይሆን ዓመጸኞቹንና በድርጊቱ የተባበሯቸውን የቤተሰብ አባላት ቀጥቷል። (ዘኍልቍ 16:31-35) ዛሬም ቢሆን ቲኦክራሲያዊ ሥልጣን ያላቸው ወንድሞች የሚያሳልፉትን ውሳኔ ማክበርና ከውሳኔው ጋር መተባበር እንዳለብን ከዚህ ትምህርት እናገኛለን።

በዚህ ረገድ ደሎረስ ልጅዋ ተግሣጽ በተሰጣት ወቅት ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ከብዷት እንደነበር ተናግራለች። “ይሖዋ ያደረገው ይህ ዝግጅት ምክንያታዊ እንደሆነ የሚናገሩ ጽሑፎችን ደጋግሜ ማንበቤ ረድቶኛል” ብላለች። አክላም “ከሕዝብ ንግግሮችና ከአንዳንድ ጽሑፎች ችግሩን ለመቋቋምና ይሖዋን ማገልገሌን ለመቀጠል የሚረዱኝን ነጥቦች የምጽፍበት ልዩ የማስታወሻ ደብተር አዘጋጀሁ” በማለት ተናግራለች። ይህም ችግሩን ለመቋቋም ወደሚያስችል ሌላ ጠቃሚ መንገድ ይመራናል።

ስሜታችሁን አውጥታችሁ ተናገሩ። ሊያጽናኗችሁ ለሚችሉ ለአንድ ወይም ለሁለት ወዳጆቻችሁ ስሜታችሁን ማካፈል ጥሩ ሆኖ ታገኙት ይሆናል። ይህን በምታደርጉበት ጊዜ አዎንታዊ አመለካከት እንድትይዙ ሊረዷችሁ የሚችሉ ጓደኞችን ምረጡ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ‘ልባችሁን በጸሎት ለይሖዋ ማፍሰሳችሁ’ የበለጠ ውጤት አለው። b (መዝሙር 62:7, 8) ለምን? ምክንያቱም እርሱ ነገሩ ምን ያህል ስሜታችሁን እንደጎዳው ሙሉ በሙሉ ይረዳል። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ያለው የስሜት ቀውስ ሊሰማኝ አይገባም ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ለነገሩ ይሖዋን የተዋችሁት እናንተ አይደላችሁም። ስለ ሁኔታው ተገቢ አመለካከት መያዝ እንድትችሉ ስሜታችሁን ለይሖዋ በጸሎት ንገሩት።—መዝሙር 37:5

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ስሜታችሁን በተሻለ መንገድ መቆጣጠር ትችሉ ይሆናል። እስከዚያው ድረስ ግን በሰማይ የሚኖረውን አባታችሁን ለማስደሰት የምታደርጉትን ጥረት አታቁሙ፤ እንዲሁም ጥረታችሁ ዋጋ እንደሌለው አይሰማችሁ። (ገላትያ 6:9) ይሖዋን መተዋችን ችግሩን እንደማያስወግደውም አትዘንጉ። በሌላ በኩል ደግሞ ለእርሱ ታማኝ ሆነን ከተገኘን የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንድንወጣ የሚያስችለንን እርዳታ እናገኛለን። ይሖዋ ያላችሁበትን አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚረዳላችሁና የሚያስፈልገውን ኃይል በጊዜው እንደሚሰጣችሁ እርግጠኛ ሁኑ።—2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ፊልጵስዩስ 4:13፤ ዕብራውያን 4:16

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

b ለተወገደ ዘመድ መጸለይን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የታኅሣሥ 1, 2001 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30-31 ተመልከት።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ችግሩን መቋቋም የሚቻልበት መንገድ

“ራሳችሁን ለማነጽ ትጉ፤ . . . በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።”—ይሁዳ 20, 21

ተስፋ አትቁረጡ።—1 ቆሮንቶስ 13:7

ራሳችሁን አትኮንኑ።—ሕዝቅኤል 18:20

ሌሎችን ታገሡ።—ቈላስይስ 3:13

ለይሖዋ የተግሣጽ ዝግጅት አድናቆት ይኑራችሁ።—ዕብራውያን 12:11

ስሜታችሁን አውጥታችሁ ተናገሩ።—መዝሙር 62:7, 8

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ይሖዋን ማምለክ ትተሃል?

ከሆነ፣ ከይሖዋ የራቅህበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ከእርሱ ጋር ያለህ ወዳጅነት እንዲሁም የወደፊት ተስፋህ አደጋ ላይ ወድቋል ማለት ነው። ምናልባት ወደ ይሖዋ መመለስ ትፈልግ ይሆናል። ታዲያ ፍላጎትህን ከግብ ለማድረስ ልባዊ ጥረት እያደረግህ ነው? ወይስ ወደፊት “አንድ ቀን መመለሴ አይቀርም” እያልክ ጊዜውን ታስተላልፈዋለህ? የአርማጌዶን ጥቁር ዳመና በፍጥነት እየቀረበ መሆኑን አትዘንጋ። ከዚህም በላይ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሕይወት አጭር ከመሆኑም በላይ አስተማማኝ አይደለም። ሌላው ቀርቶ ነገ ስለመኖርህ እንኳ እርግጠኛ መሆን አትችልም። (መዝሙር 102:3፤ ያዕቆብ 4:13, 14) በማይድን በሽታ መያዙን ያወቀ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ይህ በሽታ የያዘኝ ይሖዋን በሙሉ ጊዜ እያገለገልኩ ሳለሁ በመሆኑ እንድሸማቀቅ ወይም እንዳፍር የሚያደርገኝ ምንም ነገር የለም፤ ይህ መሆኑ አሁን ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኛል።” ይህ ወንድም በሽታው የያዘው “አንድ ቀን ወደ ይሖዋ መመለሴ አይቀርም!” በሚልበት ወቅት ላይ እያለ ቢሆን ኖሮ ምን ይሰማው እንደነበር ገምት። ከይሖዋ ርቀህ ከሆነ ወደ እርሱ ለመመለስ የተሻለው ጊዜ አሁን ነው።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ በሁሉም መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈልህ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖርህ ይረዳሃል