በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቤተሰቦቼ ታማኝነት ጠቅሞኛል

የቤተሰቦቼ ታማኝነት ጠቅሞኛል

የሕይወት ታሪክ

የቤተሰቦቼ ታማኝነት ጠቅሞኛል

ካትሊን ኩክ እንደተናገረችው

በእናቴ በኩል ሴት አያቴ የሆነችው ማሬ ኤለን ቶምሰን በ1911 ዘመዶቿን ለመጠየቅ በስኮትላንድ ወደምትገኘው ግላስጎ ከተማ ሄዳ ነበር። እዚያ እያለች ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው በተጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን ውስጥ የጎላ ድርሻ የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል የሰጠውን ንግግር አዳመጠች። አያቴ በሰማችው ነገር እጅግ ተደስታ ነበር። ወደ ደቡብ አፍሪካ ስትመለስ በአካባቢው ከነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር ተገናኘች። ሚያዝያ 1914 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በደቡብ አፍሪካ ባደረጉት የመጀመሪያ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተጠመቁት 16 ሰዎች መካከል አንዷ አያቴ ነበረች። አያቴ ስትጠመቅ ኢዲት የተባለችው ሴት ልጅዋ (እናቴ) ስድስት ዓመቷ ነበር።

በ1916 የወንድም ራስልን ሞት ተከትሎ በዓለም ዙሪያ በነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መካከል መከፋፈል ተፈጥሮ ነበር። በደርባን የነበሩት ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቁጥር ከ60 ወደ 12 ወረደ። ከታማኞቹ ወንድሞች ጎን ጸንተው ከቆሙት መካከል የአባቴ እናት የሆነችው ኢንግቦርግ ሚይርዳል እንዲሁም በዚያው ጊዜ አካባቢ የተጠመቀውና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበረው ወንድ ልጅዋ ሄንሪ ሚይርዳል ይገኙበታል። በ1924 ሄንሪ ኮልፖርተር (በወቅቱ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሆነ። በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በደቡባዊ አፍሪካ ባሉ ብዙ ቦታዎች ሰብኳል። በ1930 ሄንሪና ኢዲት ተጋቡና ከሦስት ዓመት በኋላ እኔ ተወለድሁ።

ሠፊ ቤተሰብ

ለጥቂት ጊዜ በሞዛምቢክ ከኖርን በኋላ በ1939 ጓዛችንን ጠቅልለን ጆሃንስበርግ ወደሚገኘው የእናቴ ወላጆች ቤት ሄድን። ወንዱ አያቴ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ምንም ፍላጎት ስላልነበረው አንዳንዴ ሴት አያቴን ይቃወማት ነበር። ያም ቢሆን ግን በጣም እንግዳ ተቀባይ ነበር። በ1940 እህቴ ቴልማ ተወለደች፤ እኔም ሆንኩ ቴልማ ትልልቅ ሰዎችን መንከባከብን ተምረን ነበር። ብዙ ጊዜ በእራት ሰዓት በዕለቱ ስላጋጠመን ነገር ወይም ያለፈ ትዝታችንን እያነሳን ስናወራ እናመሽ ነበር።

ወንድሞችና እህቶች፣ በተለይም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩት ቤታችን ያርፉ ነበር። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በእራት ሰዓት በምናደርገው ጭውውት ይካፈሉ የነበረ ሲሆን የሚነግሩን ነገር ለመንፈሳዊ ውርሻችን ያለንን አድናቆት ጨምሮልናል። ይህም እኔና ቴልማ እንደ እነርሱ አቅኚዎች ለመሆን የነበረንን ፍላጎት አጠናክሮታል።

ገና ከሕፃንነታችን ጀምሮ በማንበብ ደስታ እንደሚገኝ ተምረን ነበር። እማማ፣ አባባና አያታችን ጥሩ ጥሩ የተረት መጽሐፎችን ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ያነቡልን ነበር። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና አገልግሎትም ለእኛ ልክ እንደምንተነፍሰው አየር የሕይወታችን ክፍል ሆነው ነበር። አባባ በጆሃንስበርግ ጉባኤ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ስለነበረ ስብሰባዎች ላይ ቀደም ብለን መድረስ ነበረብን። የአውራጃ ስብሰባ ሲኖረን አባባ ስብሰባውን ያደራጅ የነበረ ሲሆን እማማ ደግሞ ወደ ስብሰባው ለሚመጡ ልዑካን ማረፊያ በማዘጋጀት ትረዳ ነበር።

ለእኛ ልዩ ትርጉም የነበረው የአውራጃ ስብሰባ

በ1948 በጆሃንስበርግ የተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ልዩ ነበር። ከብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የተላኩ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት አባላት በስብሰባው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገኝተው ነበር። ናታን ኖርና ሚልተን ሄንሽል በደቡብ አፍሪካ በቆዩበት ጊዜ አባባ በመኪናው እንዲያመላልሳቸው ተመድቦ ነበር። እኔም በዚያ ስብሰባ ላይ ተጠመቅሁ።

ከዚያ በኋላ ጥቂት ቆይቶ አባባን በጣም ያስገረመው ነገር ተከሰተ። አባቱ፣ ከወንድም ራስል ሞት በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹን የከዱት ሰዎች ተጽዕኖ እንዲያደርጉበት መፍቀዱ እጅግ እንደሚጸጽተው ነገረው። አያቴ ይህን ከተናገረ ከጥቂት ወራት በኋላ ሞተ። ሴት አያቴ (የአባቴ እናት) ግን በ1955 ምድራዊ ሕይወቷን እስካጠናቀቀችበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት አገልግላለች።

ሕይወቴን የቀረጹት ክንውኖች

የካቲት 1, 1949 የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። በቀጣዩ ዓመት በኒው ዮርክ ከተማ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ እንደሚደረግ ማስታወቂያ ሲነገር ደስ አለን። ይሁን እንጂ ለመሄድ ብንመኝም የገንዘብ አቅሙ አልነበረንም። ከዚያም በየካቲት ወር 1950 የወንድ አያቴ (የእናቴ አባት) ሲሞት ሴት አያቴ በውርስ ያገኘችውን ገንዘብ ለአምስታችን መጓጓዣ እንዲሆን ተጠቀመችበት።

ለመሄድ ከመነሳታችን ከጥቂት ሳምንታት በፊት በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ደብዳቤ ደረሰኝ። ደብዳቤው በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በ16ኛው ክፍል እንድሠለጥን የተጋበዝኩበት ነበር። ገና 17 ዓመት እንኳ ሳይሞላኝ ይህን መብት በማግኘቴ በጣም ተደሰትኩ! ትምህርቱ ሲጀምር ከደቡብ አፍሪካ ከሄዱት አሥር ተማሪዎች መካከል ለመሆን በመታደሌ ባገኘሁት ታላቅ መብት ደስታዬ ወሰን አልነበረውም።

የካቲት 1951 ከተመረቅን በኋላ እኔን ጨምሮ ስምንታችን በደቡብ አፍሪካ ሚስዮናውያን ሆነን ለማገልገል ተመለስን። ለቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ አብዛኛውን ጊዜ የምንሰብከው አፍሪካንስ ተብሎ የሚጠራው ቋንቋ በሚነገርባቸው ትንንሽ ከተሞች ውስጥ ነበር። መጀመሪያ ላይ በዚያ ቋንቋ ሐሳቤን በደንብ መግለጽ አልችልም ነበር፤ አንድ ቀን ብስክሌቴን እየነዳሁ ወደ ቤት ስመለስ በአገልግሎቴ ውጤታማ ባለመሆኔ እያለቀስኩ እንደነበር አስታውሳለሁ። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የተሻሻልኩ ሲሆን ይሖዋም ጥረቴን ባርኮልኛል።

ጋብቻና የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ

በ1955 ከጆን ኩክ ጋር ተዋወቅሁ። ጆን ኩክ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊትና በኋላ በነበሩት ዓመታት በፈረንሳይ፣ በፖርቹጋልና በስፔን የስብከቱን ሥራ በማስጀመር ረገድ እርዳታ ያበረከተ ሲሆን ከእኔ ጋር በተዋወቅንበት ዓመት ደግሞ ሚስዮናዊ ሆኖ ለማገልገል ወደ አፍሪካ መምጣቱ ነበር። ከጊዜ በኋላ እንደሚከተለው ብሎ ጽፏል:- “በአንድ ሳምንት ውስጥ ሦስት ያልታሰቡ አስደሳች ነገሮች አገኘሁ። . . . አንድ በጣም ለጋስ የሆነ ወንድም አንዲት ትንሽ መኪና ሰጠኝ፤ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ እንዲሁም ፍቅር ያዘኝ።” a ከጆን ጋር ታኅሣሥ 1957 ተጋባን።

ለጋብቻ በምንጠናናበት ወቅት ጆን ከእሱ ጋር መኖር ፈጽሞ አሰልቺ እንደማይሆንብኝ ቃል ገብቶልኝ ነበር፤ ደግሞም ትክክል ነበር። በመላው ደቡብ አፍሪካ፣ በአብዛኛው ጥቁሮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ጉባኤዎችን እንጎበኝ ነበር። ጥቁሮች ብቻ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለማደር ይቅርና ለመግባት ብቻ እንኳ በየሳምንቱ ፈቃድ ማግኘት ስለሚያስፈልግ ሁኔታው ፈታኝ ነበር። በእነዚያ ጊዜያት አልፎ አልፎ፣ ጥቁሮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች አቅራቢያ በነጮች ክልል ውስጥ በሚገኙ ባዶ ሱቆች ወለል ላይ ተኝተን እናድር የነበረ ሲሆን በመንገድ የሚያልፍ ሰው እንዳያየን እንጠነቀቅ ነበር። በአብዛኛው ለጥቁሮች ክልል ቅርብ በሆነ የነጭ ወንድሞች ቤት ማደር የነበረብን ሲሆን ይህም ጥቁሮች ከሚኖሩበት ክልል ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆ የሚገኝ ነበር።

ሌላው ፈታኝ ሁኔታ ደግሞ ትልልቅ ስብሰባዎችን የምናደርገው በጫካ ውስጥ በተሠሩ ቀለል ያሉ መሰብሰቢያዎች መሆኑ ነበር። ሰዎች ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበራችን አድናቆት እንዲያድርባቸው የረዱ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ፊልሞችን እናሳይ ነበር። በእነዚያ አካባቢዎች በአብዛኛው መብራት ስላልነበረ የራሳችንን ጀነሬተር ይዘን እንሄድ ነበር። ከዚህም ሌላ ጽሑፎቻችን ከታገዱባቸው በብሪታንያ ሞግዚትነት ከሚተዳደሩ አገሮች ጋር በተያያዘ የገጠሙንን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መቋቋም ነበረብን። እንዲሁም የዙሉን ቋንቋ መማር ፈታኝ ሆኖብን ነበር። የሆነ ሆኖ ወንድሞቻችንን ለማገልገል በመቻላችን ተደስተናል።

ነሐሴ 1961 ጆን በደቡብ አፍሪካ የጉባኤ የበላይ ተመልካቾችን ለመርዳት በተደረገው የአራት ሳምንት የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት የመጀመሪያው አስተማሪ ሆነ። ጆን በማስተማር ጥበብ የተካነ በመሆኑ ቀላል በሆነ መንገድ በማስረዳትና ነጥቡን ቁልጭ አድርገው በሚያሳዩ ሕያው ምሳሌዎች በመጠቀም የተማሪዎቹን ልብ መንካት ችሏል። በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተከታታይ ሥልጠናዎችን ለመስጠት ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተጉዘናል። ጆን በሚያስተምርበት ጊዜ እኔ ደግሞ ከአካባቢው ወንድሞች ጋር በመስክ አገልግሎት እካፈል ነበር። ከዚያም ከሐምሌ 1, 1964 ጀምሮ በጆሃንስበርግ አቅራቢያ በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ እንድናገለግል የሚጋብዝ ደብዳቤ ሲደርሰን በጣም ተገረምን።

ይሁንና በዚህ ጊዜ የጆን ጤንነት ግራ እያጋባን ነበር። በ1948 ለተወሰነ ጊዜ የሳንባ ነቀርሳ ይዞት የነበረ ሲሆን ከዚያ ወዲህ ብዙ ጊዜ ይደክመዋል። አንዳንድ ጊዜ የጉንፋን ዓይነት ምልክቶች ይታዩበትና ለቀናት ታምሞ የሚተኛ ሲሆን በዚህ ጊዜ ምንም ነገር መሥራት ወይም ከማንም ጋር መገናኘት አይችልም። በቅርንጫፍ ቢሮው እንድናገለግል ከመጠራታችን ከጥቂት ጊዜ በፊት ያማከርነው ሐኪም የጆን ችግር የመንፈስ ጭንቀት እንደሆነ ነግሮን ነበር።

ሐኪሙ እንደመከረን በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ ለማድረግ አገልግሎታችንን መቀነስ ለእኛ የማይታሰብ ነገር ነበር። በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ጆን በአገልግሎት ክፍል የተመደበ ሲሆን እኔ ደግሞ የማጣሪያ ንባብ እንዳከናውን ተመደብኩ። የራሳችን ክፍል የተሰጠን መሆኑ ታላቅ በረከት ነበር! ጆን ከመጋባታችን በፊት የፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪዎች ባሉበት ክልል አገልግሎ ነበር። በመሆኑም በ1967፣ በጆሃንስበርግና በአቅራቢያው ለሚኖሩት ብዙ የቋንቋው ተናጋሪ ማኅበረሰቦች ምሥራቹን ሲሰብክ የነበረውን የፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ እንድናግዝ ተጠየቅን። ይህ ደግሞ ለእኔ ሌላ ተጨማሪ ቋንቋ መማር ይጠይቅብኝ ነበር።

የፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት ሰዎች በብዙ ቦታዎች ተበታትነው የሚኖሩ ስለነበሩ አንዳንድ ጊዜ ምሥራቹን ለማዳረስ እስከ 300 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ረጅም ጉዞ እናደርግ ነበር። በዚህ ጊዜ የፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ትልልቅ ስብሰባዎች በምናደርግባቸው ወቅቶች ከሞዛምቢክ እየመጡ ይጠይቁን ነበር፤ ይህም አዳዲሶች በእምነታቸው እንዲበረቱ ከፍተኛ እገዛ አበርክቷል። የፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪዎች ባሉበት ክልል በቆየንባቸው 11 ዓመታት ውስጥ 30 አባላት የነበሩበት ትንሹ ቡድናችን አድጎ አራት ጉባኤዎች ሲመሠረቱ ተመልክተናል።

ቤተሰቦቼ ያጋጠሟቸው ለውጦች

በዚህ መሃል በወላጆቼ ቤት አንዳንድ ለውጦች ተከስተው ነበር። በ1960 እህቴ ቴልማ ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣ ጆን ኧርባን የተባለ አቅኚ ወንድም አገባች። በ1965 ሁለቱም በጊልያድ 40ኛ ክፍል ሠልጥነው በብራዚል ሚስዮናውያን በመሆን ለ25 ዓመታት በታማኝነት አገልግለዋል። በ1990 የጆን ወላጆች በመታመማቸው እነርሱን ለመንከባከብ ወደ ኦሃዮ ተመለሱ። ይህ ሁኔታ ያስከተለባቸው ውጥረት ቢኖርም እስካሁንም ድረስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጸንተው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ሴት አያቴ (በእናቴ በኩል) እስከ 98 ዓመት ዕድሜዋ ለአምላክ ታማኝ ሆና ከኖረች በኋላ በ1965 ምድራዊ ሕይወቷን ጨረሰች። አባባ ከሰብዓዊ ሥራው ጡረታ የወጣውም በዚሁ ዓመት ነበር። ስለዚህ እኔና ጆን በአገሪቱ በሚገኘው የፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪዎች መስክ በማገልገል እንድንረዳ በተጠየቅን ጊዜ አባባና እማማም አብረውን ለማገልገል ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቀረቡ። አባባና እማማ በፖርቹጋል ቋንቋ የሚመራው ቡድን ሚዛኑን የጠበቀ እንዲሆን በመርዳት በጎ ተጽዕኖ ያሳደሩ ሲሆን ከጥቂት ወራት በኋላ የመጀመሪያው ጉባኤ ተቋቋመ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እማማ የካንሰር ሕመም ያስከተለባት ችግር እየባሰባት መጣና በ1971 ሕይወቷ አለፈ። አባባ ደግሞ ሰባት ዓመት ቆይቶ ሞተ።

የጆንን ሕመም መቋቋም

በ1970 የጆን ጤንነት መሻሻል እንዳላሳየ ግልጽ ሆነ። ቀስ በቀስም በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ የቤቴል ቤተሰብን ሳምንታዊ የመጠበቂያ ግንብ ጥናትና በማለዳ የሚደረገውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት መምራትን ጨምሮ በጣም የሚወዳቸውን የአገልግሎት መብቶቹን መተው ግድ ሆነበት። የሥራ ምድቡ ከአገልግሎት ክፍል ወደ መልእክት ክፍል ከዚያም ወደ አትክልተኝነት ተቀየረ።

የጆን የቆራጥነት መንፈስ ለውጥ እንዳያደርግ እንቅፋት ሆኖበታል። ቀስ ብሎ እንዲሠራ ስወተውተው ብዙውን ጊዜ ለእኔ ያለውን አድናቆት ለማሳየት እቅፍ ያደርገኝና የእግር ብረት እንደሆንኩበት በመግለጽ ይቀልድብኛል። በመጨረሻም በፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪዎች መስክ ማገልገላችንን ትተን በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ከሚሰበሰበው ጉባኤ ጋር ብናገለግል እንደሚሻል ተሰማን።

የጆን ሕመም እየባሰበት ሲሄድ ከይሖዋ ጋር ያለውን የቅርብ ዝምድና መመልከት በጣም ልብ የሚነካ ነበር። ጆን በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ተውጦ ሌሊት ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ ራሱን አረጋግቶ ይሖዋ እንዲረዳው ለመጸለይ የሚችልበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ እያወራን እንቆያለን። የኋላ ኋላም ራሱን አስገድዶ “ስለማናቸውም ነገር አትጨነቁ” የሚለውን የፊልጵስዩስ 4:6, 7ን ሐሳብ በቀስታ በመደጋገም እነዚያን መጥፎ ጊዜያት ብቻውን ለመቋቋም ችሏል። ይህን ሲያደርግ ለመጸለይ የሚያስችለው መረጋጋት ያገኛል። ብዙ ጊዜ እኔም ስለምነቃ ይሖዋን ከልቡ እየተማጸነ ከንፈሮቹን ሲያንቀሳቅስ ጸጥ ብዬ እመለከተው ነበር።

ቅርንጫፍ ቢሯችን በጣም ስለጠበበን ከጆሃንስበርግ ወጣ ብሎ አዲስ ትልቅ የቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ተጀመረ። እኔና ጆን ከከተማው ውካታና ብክለት ገለል ብሎ ወደሚገኘው ወደዚህ ሰላማዊ ቦታ አዘውትረን እንሄድ ነበር። የአዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ እዚያ ወደነበሩት ጊዜያዊ ማረፊያዎች እንድንዛወር መፈቀዱ ለጆን ጤንነት በጣም ረድቶት ነበር።

አዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎች

የጆን የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ ይበልጡን እየደከመ ሲመጣ የተመደበለትን ሥራ ማከናወን ይበልጥ አስቸጋሪ ሆነበት። ያም ሆኖ ጆን ለሚያደርገው ጥረት ሌሎች ድጋፋቸውን የሚሰጡበት መንገድ ልቤን ይነካው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም ምርምር ለማድረግ ወደ ሕዝብ ቤተ መጻሕፍት በሚሄድበት ጊዜ ጆንን ይዞት ይሄድ ነበር። ጆን ወጣ በሚልበት በዚህ ጊዜ ትራክቶችንና መጽሔቶችን በኪሱ ሞልቶ ይይዛል። ይህም ጆን በሥራው እርካታ እንዲያገኝና ጠቃሚ እንደሆነ እንዲሰማው ረድቶታል።

እያደር ኦልዛይመርስ የሚባለው በሽታ የማንበብ ችሎታውን አሳጣው። በካሴት የተቀረጹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችና የመንግሥቱ መዝሙሮች በመኖራቸው አመስጋኞች ነበርን። እነዚህን ካሴቶች ደጋግመን እናዳምጥ ነበር። ጆን ከእሱ ጋር ቁጭ ብዬ ካላዳመጥኩ ስለሚበሳጭ በእነዚያ ረጅም ሰዓታት እንደ ጥልፍና ሹራብ የመሳሰሉ ነገሮችን በመሥራት ራሴን በሥራ አስጠምድ ነበር። በዚህም የተነሳ ሹራብና አልጋ ልብስ ከቤታችን ጠፍቶ አያውቅም!

ከጊዜ በኋላ የጆን የጤንነት ሁኔታ ብዙ እንክብካቤ እንዳደርግለት የሚጠይቅብኝ እየሆነ መጣ። ብዙ ጊዜ ማንበብና ማጥናት እስኪያቅተኝ ድረስ በጣም ይደክመኝ የነበረ ቢሆንም እስከ መጨረሻው ድረስ እሱን መንከባከብ ልዩ መብት ነበር። ጆን እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ታማኝ ሆኖ በ85 ዓመት ዕድሜው በ1998 በእቅፌ እንዳለ ብዙም ሳይሰቃይ በሞት አንቀላፋ። ጆን ጤንነቱ ተመልሶና አእምሮው ተስተካክሎ በትንሣኤ ላገኘው በጣም እናፍቃለሁ!

እንደገና መታደስ

ጆን ከሞተ በኋላ ለብቻ መኖርን መልመዱ ከብዶኝ ነበር። ስለዚህ ግንቦት 1999 በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረውን እህቴን ቴልማንና ባሏን ለመጠየቅ ሄድኩ። እዚያም፣ በተለይ በኒው ዮርክ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በምንጎበኝበት ጊዜ ከብዙ ታማኝና ውድ ጓደኞቼ ጋር መገናኘት እንዴት የሚያስደስትና የሚያጽናና ነበር! በእርግጥም የሚያስፈልገኝ እንደዚህ ዓይነት መንፈሳዊ ማበረታቻ ነበር።

ስለምወዳቸው ታማኝ ሰዎች ሕይወት አስታውሼ መናገሬ ለእኔ ጠቃሚ የነበሩ ብዙ ነገሮችን እንዳስታውስ ይረዳኛል። ከእነርሱ ያገኘሁት ሥልጠና፣ ምሳሌነታቸውና እርዳታቸው በዜግነታቸውና በዘራቸው ከእኔ ለሚለዩ ሰዎች ልቤን ከፍቼ ፍቅር ማሳየትን አስተምሮኛል። ትዕግሥትን፣ ጽናትንና ከሁኔታዎች ጋር ራስን ማስማማትን ከእነርሱ ተምሬያለሁ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ጸሎት ሰሚ የሆነውን የይሖዋን ደግነት ቀምሻለሁ። እኔም “አንተ የመረጥኸው፣ ወደ ራስህ ያቀረብኸው፣ በአደባባይህም ያኖርኸው ምስጉን ነው! ከተቀደሰው መቅደስህ፣ ከቤትህም በረከት እንረካለን” በማለት እንደጻፈው መዝሙራዊ ይሰማኛል።—መዝሙር 65:4

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የነሐሴ 1, 1959 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 468-472 ተመልከት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሴት አያቴ ከሴት ልጆቿ ጋር

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1948 በተጠመቅሁ ጊዜ ከወላጆቼ ጋር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ ሬጂስትራር ከሆነው ከአልበርት ሽሮደርና ከደቡብ አፍሪካ ከመጡት ዘጠኝ ተማሪዎች ጋር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1984 ከጆን ጋር