በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ጸሎት ሰሚ’ ወደሆነው አምላክ መቅረብ የሚቻለው እንዴት ነው?

‘ጸሎት ሰሚ’ ወደሆነው አምላክ መቅረብ የሚቻለው እንዴት ነው?

‘ጸሎት ሰሚ’ ወደሆነው አምላክ መቅረብ የሚቻለው እንዴት ነው?

“ጸሎትን የምትሰማ ሆይ፤ የሰው ልጆች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ።”—መዝሙር 65:2

1. ሰዎችን በምድር ላይ ከሚኖሩ ሌሎች ፍጥረታት የሚለያቸው ምንድን ነው? ይህስ ምን አጋጣሚ ይከፍታል?

 በምድር ላይ ከሚኖሩት በሺህ የሚቆጠሩ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል ፈጣሪን የማምለክ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። መንፈሳዊ ፍላጎት ያላቸውም ሆነ ይህን ፍላጎታቸውን ማሟላት እንዳለባቸው የሚሰማቸውም እነርሱ ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ ከሰማዩ አባታችን ጋር የግል ዝምድና ለመመሥረት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ይከፍትልናል።

2. ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ ኃጢአት መጥፎ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

2 አምላክ ሰውን ሲፈጥረው ወደ ፈጣሪው ለመቅረብ የሚያስችል ችሎታ ሰጥቶታል። አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ ኃጢአት አልነበረባቸውም። በመሆኑም አንድ ልጅ አባቱን በነጻነት እንደሚቀርበው እነርሱም አምላክን በነጻነት መቅረብ ይችሉ ነበር። ይሁንና ኃጢአት በመሥራታቸው ይህን ታላቅ መብት አጡ። አዳምና ሔዋን አምላክን ሳይታዘዙ በመቅረታቸው ከእርሱ ጋር የመሠረቱት ውድ ዝምድና ተበላሸ። (ዘፍጥረት 3:8-13, 17-24) ታዲያ ከዚያ በኋላ ፍጹም ያልሆኑት የአዳም ልጆች ወደ አምላክ መቅረብ አይችሉም ማለት ነው? በፍጹም፤ ይሖዋ አንዳንድ ብቃቶችን እስካሟሉ ድረስ ወደ እርሱ እንዲቀርቡ ፈቅዶላቸዋል። እነዚህ መሠረታዊ ብቃቶች ምንድን ናቸው?

ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚያስፈልጉ ብቃቶች

3. ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ወደ አምላክ መቅረብ የሚችሉት እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

3 ከሁለቱ የአዳም ልጆች ጋር ተያይዞ የተፈጸመውን ሁኔታ መመልከታችን አምላክ ፍጹም ያልሆኑ የሰው ልጆች ወደ እርሱ ለመቅረብ ምን እንደሚጠብቅባቸው ለመገንዘብ ይረዳናል። አቤልም ሆነ ቃየን መሥዋዕት በማቅረብ ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ጥረት አድርገዋል። ይሁንና አቤል ያቀረበው መሥዋዕት ተቀባይነት ሲያገኝ የቃየን ግን ሳያገኝ ቀረ። (ዘፍጥረት 4:3-5) እንዲህ የሆነው ለምንድን ነው? ዕብራውያን 11:4 “አቤል ከቃየል ይልቅ የበለጠ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ። . . . እርሱ በእምነት ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት” ይላል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ወደ አምላክ ለመቅረብ የግድ እምነት ያስፈልጋል። ሌላው ብቃት ደግሞ ይሖዋ “መልካም ብታደርግ ተቀባይነትን አታገኝምን?” በማለት ለቃየን በተናገራቸው ቃላት ውስጥ ተገልጿል። አዎን፣ ቃየን መልካም አድርጎ ቢሆን ኖሮ ወደ አምላክ ለመቅረብ ያደረገው ጥረት ተቀባይነት ያገኝ ነበር። ይሁንና ቃየን የአምላክን ምክር ለመቀበል አሻፈረኝ በማለት አቤልን ገደለው፤ በዚህም ሳቢያ ከሰዎች የተገለለ ሆነ። (ዘፍጥረት 4:7-12) በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ የተፈጸመው ይህ ክንውን ወደ አምላክ ለመቅረብ በመልካም ሥራ የተደገፈ እምነት አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ይገልጻል።

4. ወደ አምላክ መቅረብ ከፈለግን ምን ነገር አምነን መቀበል ይኖርብናል?

4 ወደ አምላክ ለመቅረብ የምንፈልግ ከሆነ ኃጢአተኞች መሆናችንን አምነን መቀበል ይኖርብናል። የሰው ልጆች በሙሉ ኃጢአተኞች ሲሆኑ ይህ ደግሞ ወደ አምላክ እንዳይቀርቡ እንቅፋት ይሆንባቸዋል። ነቢዩ ኤርምያስ እስራኤላውያንን አስመልክቶ “ኀጢአትም ሠርተናል፤ . . . ጸሎት እንዳያልፍ፣ ራስህን በደመና ሸፈንህ” በማለት ጽፏል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:42, 44) ያም ሆኖ ግን የሰው ልጆች ባሳለፏቸው የታሪክ ዘመናት በሙሉ አምላክ ታዛዥ የሆኑ ሰዎች በእምነትና በፍጹም ልብ የሚያቀርቡትን ጸሎት ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። (መዝሙር 119:145) ጸሎቶቻቸው ከተሰማላቸው መካከል እነማን ይገኛሉ? ካቀረቡትስ ጸሎት ምን እንማራለን?

5, 6. አብርሃም ወደ አምላክ ከቀረበበት መንገድ ምን እንማራለን?

5 ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ አብርሃም ነው። አምላክ አብርሃምን “ወዳጄ” ሲል መጥራቱ ወደ አምላክ ለመቅረብ ያደረገው ጥረት ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን ያሳያል። (ኢሳይያስ 41:8) አብርሃም ወደ አምላክ ከቀረበበት መንገድ ምን እንማራለን? ይህ ታማኝ የእምነት አባት “ያለ ልጅ የቀረሁ ስለ ሆንሁ፣ . . . ምን ትሰጠኛለህ?” ሲል ይሖዋን ስለ ወራሽ ጠይቆት ነበር። (ዘፍጥረት 15:2, 3፤ 17:18) በሌላ ጊዜ ደግሞ አምላክ በሰዶምና ገሞራ ይኖሩ በነበሩት ክፉ ሰዎች ላይ የጥፋት ፍርዱን ሊያስፈጽም ሲል በውስጧ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ደኅንነት እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር። (ዘፍጥረት 18:23-33) ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችን አስመልክቶ ልመና አቅርቧል። (ዘፍጥረት 20:7, 17) አቤል እንዳደረገው ሁሉ አብርሃምም አንዳንድ ጊዜ መሥዋዕት ይዞ ወደ ይሖዋ ይቀርብ ነበር።—ዘፍጥረት 22:9-14

6 በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ አብርሃም ከይሖዋ ጋር የሚነጋገረው በነጻነት ነበር። ይሁንና አብርሃም ከፈጣሪው ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ቦታውን ጠብቆ ተመላልሷል። በዘፍጥረት 18:27 ላይ የተጠቀሰውን የአብርሃምን አክብሮት የተላበሰ አነጋገር ልብ በል:- “እኔ ከንቱ፣ ትቢያና ዐመድ ሆኜ ሳለሁ ከጌታ ጋር ለመናገር አንዴ ደፍሬአለሁ።” እንዴት ያለ ሊኮረጅ የሚገባው ዝንባሌ ነው!

7. የእምነት አባቶች ወደ ይሖዋ የጸለዩባቸው አንዳንድ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

7 የእምነት አባቶች የተለያዩ ጉዳዮችን አስመልክተው የጸለዩ ሲሆን ይሖዋም ሰምቷቸዋል። ያዕቆብ ጸሎቱን ያቀረበው በስእለት መልክ ነበር። ያዕቆብ አምላክ እንዲረዳው ከጠየቀ በኋላ “ከምትሰጠኝም ሀብት ሁሉ፣ ከዐሥር እጅ አንዱን ለአንተ እሰጣለሁ” በማለት ተስሏል። (ዘፍጥረት 28:20-22) ቆየት ብሎም ከወንድሙ ጋር ለመገናኘት በሄደበት ወቅት “ከወንድሜ ከዔሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ . . . ፈርቻለሁና” በማለት ይሖዋ እንዲጠብቀው ተማጽኗል። (ዘፍጥረት 32:9-12) የእምነት አባት የሆነው ኢዮብም ቤተሰቡን በመወከል መሥዋዕት ይዞ ወደ ይሖዋ የመቅረብ ልማድ ነበረው። ሦስቱ ጓደኞቹ በንግግራቸው በበደሉ ጊዜ ኢዮብ እነርሱን ወክሎ የጸለየ ሲሆን ‘እግዚአብሔርም የኢዮብን ጸሎት ተቀብሎታል።’ (ኢዮብ 1:5፤ 42:7-9) እነዚህ ዘገባዎች ለይሖዋ በምንጸልይበት ጊዜ ጸሎታችን ምን ምን ነገሮችን ሊያካትት እንደሚገባው እንድንገነዘብ ይረዱናል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በተገቢው መንገድ ወደ እርሱ የሚቀርቡ ሰዎችን ጸሎት ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑን ያሳያሉ።

በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር

8. እስራኤላውያን በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር በነበሩ ጊዜ ሕዝቡን የተመለከቱ ጉዳዮች ወደ ይሖዋ የሚቀርቡት እንዴት ነበር?

8 ይሖዋ የእስራኤልን ብሔር ከግብጽ ምድር ነጻ ካወጣ በኋላ የሕጉን ቃል ኪዳን ሰጣቸው። ሕጉ በተሾሙት ካህናት በኩል ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ይገልጽ ነበር። አንዳንድ ሌዋውያን ሕዝቡን በመወከል ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ ተመደቡ። ብሔሩን የሚመለከት ትልቅ ጉዳይ ሲከሰት ሕዝቡን የሚወክል ሰው አንዳንዴም ንጉሡ ወይም በመካከላቸው ያለ ነቢይ ጉዳዩን አስመልክቶ ወደ ይሖዋ ይጸልያል። (1 ሳሙኤል 8:21, 22፤ 14:36-41፤ ኤርምያስ 42:1-3) ለምሳሌ ያህል፣ ቤተ መቅደሱ ለይሖዋ ሲወሰን ንጉሥ ሰሎሞን ከልብ የመነጨ ጸሎት አቅርቧል። በምላሹም ይሖዋ ቤተ መቅደሱን በክብሩ በመሙላትና ‘በዚህ ስፍራ የሚጸለየውን ጸሎት ጆሮዎቼ ያዳምጣሉ’ በማለት ሰሎሞንን መስማቱን አሳይቷል።—2 ዜና መዋዕል 6:12 እስከ 7:3, 15

9. በቤተ መቅደሱ ውስጥ ወደ ይሖዋ በተገቢው መንገድ ለመቅረብ ምን ያስፈልግ ነበር?

9 ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ በቤተ መቅደሱ ወደ እርሱ የሚቀርቡ ሰዎች ሊያሟሉት የሚገባውንም መሥፈርት ይዟል። ይህ መሥፈርት ምንድን ነው? ሊቀ ካህኑ የእንስሳት መሥዋዕት ከማቅረብ በተጨማሪ ማለዳና ምሽት ላይ መልካም መዓዛ ያለው ዕጣን በይሖዋ ፊት ማጤስ ነበረበት። ቆየት ብሎም የበታች ካህናት ጭምር ከሥርየት ቀን በስተቀር በሌላ ጊዜ ይህን አገልግሎት የማቅረብ መብት አገኙ። ካህናቱ እንዲህ የመሰለውን አክብሮት የተሞላበት አምልኮ ሳያቀርቡ ከቀሩ ይሖዋ በአገልግሎታቸው አይደሰትም።—ዘፀአት 30:7, 8፤ 2 ዜና መዋዕል 13:11

10, 11. ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚቀርቡ ጸሎቶችን እንደሚሰማ ምን ማረጋገጫ አለን?

10 በጥንቷ እስራኤል፣ ወደ አምላክ መቅረብ የሚቻለው በተመረጡ ተወካዮች አማካኝነት ብቻ ነበር? አልነበረም። ቅዱሳን ጽሑፎች፣ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚቀርቡ ጸሎቶችን ለመቀበል ፈቃደኛ እንደነበር ይነግሩናል። ሰሎሞን ቤተ መቅደሱ ለይሖዋ አምልኮ ሲወሰን እንደሚከተለው በማለት ጸልዮአል:- “ከሕዝብህ ከእስራኤል ማንም ሰው . . . እጁን ወደዚህ ቤተ መቅደስ በመዘርጋት ጸሎትና ልመና ቢያቀርብ፣ በሰማይ በማደሪያህ ሆነህ ስማ።” (2 ዜና መዋዕል 6:29, 30) የሉቃስ ዘገባ የመጥምቁ ዮሐንስ አባት የሆነው ዘካርያስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ዕጣን በሚያጥንበት ጊዜ ካህናት ያልሆኑ በርካታ የይሖዋ አምላኪዎች ‘በውጭ ሆነው’ ይጸልዩ እንደነበር ይነግረናል። ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ከወርቅ በተሠራው መሠዊያ ላይ ለይሖዋ የዕጣን መሥዋዕት ሲቀርብ ሕዝቡ ከቤተ መቅደሱ ውጭ ተሰብስበው የመጸለይ ልማድ ነበራቸው።—ሉቃስ 1:8-10

11 በመሆኑም ይሖዋ ሰዎች በትክክለኛው መንገድ ወደ እርሱ እስከቀረቡ ድረስ በብሔሩ ወኪሎችም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የሚያቀርቡለትን ልመናዎች ለመስማት ፈቃደኛ ነበር። በአሁኑ ወቅት የምንኖረው በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር አይደለም። ያም ሆኖ ጥንት እስራኤላውያን ወደ አምላክ በጸሎት ይቀርቡበት ከነበረው መንገድ ጠቃሚ ትምህርት መቅሰም እንችላለን።

ክርስትና ከተቋቋመ በኋላ

12. ክርስቲያኖች ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚያስችላቸው ምን ዝግጅት ተደርጎላቸዋል?

12 በአሁኑ ወቅት የምንመራው በክርስትና ሕግ ነው። በዛሬው ጊዜ፣ ካህናት መላውን የአምላክ ሕዝብ ወክለው ወደ እርሱ የሚቀርቡበትም ሆነ ጸሎታችንን የምናደርስበት ቤተ መቅደስ የለም። ያም ሆኖ ይሖዋ ወደ እርሱ ለመቅረብ የሚያስችለንን ዝግጅት አድርጎልናል። ይህ ዝግጅት ምንድን ነው? ክርስቶስ በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባና ሊቀ ካህን ተደርጎ ሲሾም መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ሥራውን ጀመረ። a ይህ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ለአምልኮ ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚያስችል አዲስ ዝግጅት ነው።—ዕብራውያን 9:11, 12

13. ጸሎትን በተመለከተ በኢየሩሳሌም ይገኝ በነበረው ቤተ መቅደስና በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ መካከል ምን ተመሳሳይነት ይታያል?

13 ጸሎትን ጨምሮ ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲደረጉ የነበሩት እንቅስቃሴዎች የመንፈሳዊውን ቤተ መቅደስ ልዩ ልዩ ገጽታዎች በጥሩ ሁኔታ ሊገልጹ ይችላሉ። (ዕብራውያን 9:1-10) ለምሳሌ ያህል፣ ቅድስት በተባለው የቤተ መቅደሱ ክፍል ውስጥ በሚገኘው የዕጣን መሠውያ ላይ ማለዳና ምሽት ይቀርብ የነበረው ዕጣን ምንን ይወክላል? የራእይ መጽሐፍ ‘ዕጣን የቅዱሳን ጸሎት መሆኑን’ ይናገራል። (ራእይ 5:8፤ 8:3, 4) ዳዊት “ጸሎቴ በፊትህ እንደ ዕጣን ትቈጠርልኝ” ብሎ ለመጻፍ ተገፋፍቷል። (መዝሙር 141:2) ይህም በመሆኑ በክርስትና ሥርዓት ውስጥ ጣፋጭ መዓዛ ያለው ዕጣን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ጸሎትና ውዳሴ ያመለክታል።—1 ተሰሎንቄ 3:10

14, 15. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች (ለ) “ሌሎች በጎች” ወደ ይሖዋ ስለሚቀርቡበት መንገድ ምን ለማለት ይቻላል?

14 በዚህ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደ አምላክ መቅረብ የሚችሉት እነማን ናቸው? ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ የማገልገል መብት የነበራቸው ካህናትና ሌዋውያን ሲሆኑ ወደ ቅድስቱ መግባት የሚችሉት ግን ካህናት ብቻ ነበሩ። ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለአምላክ ጸሎትና ምስጋና ለማቅረብ በሚያስችላቸው ልዩ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። የጥንቱ ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይና ቅድስቱ ለዚህ መንፈሳዊ ሁኔታ እንደ ጥላ ሆነው አገልግለዋል።

15 በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ስላላቸው ስለ ‘ሌሎች በጎችስ’ ምን ማለት ይቻላል? (ዮሐንስ 10:16) ነቢዩ ኢሳይያስ ‘በዘመኑ ፍጻሜ’ ላይ በርካታ ሕዝቦች ይሖዋን ለማምለክ እንደሚሰበሰቡ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 2:2, 3) ከዚህም በተጨማሪ “መጻተኞች” ከይሖዋ ጋር እንደሚቆራኙ ጽፏል። አምላክ ወደ እርሱ ለመቅረብ ያሳዩትን ጥረት መቀበሉን ሲገልጽ “በጸሎት ቤቴም ውስጥ ደስ አሰኛቸዋለሁ” ብሏል። (ኢሳይያስ 56:6, 7) ራእይ 7:9-15 አምላክን ለማምለክ እንዲሁም “ቀንና ሌሊት” እርሱን ለማወደስ በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውጨኛ አደባባይ ስለተሰበሰቡትና ‘ከሕዝብ ሁሉ’ ስለተውጣጡት ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ የሚገልጹ ተጨማሪ መረጃዎችን ይዟል። በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች አምላክ እንደሚሰማቸው እርግጠኛ በመሆን ወደ እርሱ በነጻነት መቅረብ እንደሚችሉ ማወቃቸው ምንኛ ያጽናናቸዋል!

ተቀባይነት የሚያገኙት ምን ዓይነት ጸሎቶች ናቸው?

16. የጥንት ክርስቲያኖች ካቀረቧቸው ጸሎቶች ምን እንማራለን?

16 የጥንት ክርስቲያኖች የጸሎት ሰዎች ነበሩ። ይሁንና የጸለዩት ስለምን ጉዳዮች ነበር? ክርስቲያን ሽማግሌዎች በድርጅቱ ውስጥ ኃላፊነት የሚሸከሙ ወንዶችን በሚመርጡበት ጊዜ መመሪያ ለማግኘት ጸልየዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:24, 25፤ 6:5, 6) ኤጳፍራ የእምነት አጋሮቹን አስመልክቶ ጸሎት አቅርቧል። (ቈላስይስ 4:12) በኢየሩሳሌም የነበረው ጉባኤ በእስር ላይ ይገኝ ስለነበረው ስለ ጴጥሮስ ልመና አቅርቧል። (የሐዋርያት ሥራ 12:5) የጥንት ክርስቲያኖች ይሖዋ ተቃውሞን ለመቋቋም የሚያስችል ድፍረት ይሰጣቸው ዘንድ “ጌታ ሆይ፤ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገር እንዲችሉ አድርጋቸው” በማለት ጸልየዋል። (የሐዋርያት ሥራ 4:23-30) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ክርስቲያኖች ችግር ሲገጥማቸው ጥበብን ለማግኘት ወደ አምላክ እንዲጸልዩ አበረታቷል። (ያዕቆብ 1:5) ለይሖዋ በምታቀርበው ልመና ላይ እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮችን ትጠቅሳለህ?

17. ይሖዋ የሚቀበለው የእነማንን ጸሎት ነው?

17 አምላክ ሁሉንም ጸሎቶች አይቀበልም። ይህ ከሆነ ታዲያ፣ ጸሎታችን ተቀባይነት እንደሚያገኝ እርግጠኛ ሆነን መጸለይ የምንችለው እንዴት ነው? ያቀረቡት ጸሎት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘላቸው ባለፉት ዘመናት የኖሩ ታማኝ ሰዎች ወደ እርሱ ይቀርቡ የነበረው በቅንነትና ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ በመያዝ ነበር። ከዚህ ባሻገር በመልካም ሥራ የተደገፈ እምነት አሳይተዋል። በዛሬው ጊዜም ቢሆን ይሖዋ በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ እርሱ የሚቀርቡትን ሰዎች እንደሚሰማቸው እርግጠኛ መሆን እንችላለን።

18. ክርስቲያኖች ጸሎታቸው እንዲሰማ ከፈለጉ የትኛውን ብቃት ማሟላት ይገባቸዋል?

18 ከዚህም ባሻገር ሊሟላ የሚገባው ተጨማሪ ብቃት አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሲገልጽ “በእርሱ አማካይነት በአንዱ መንፈስ ወደ አብ መቅረብ እንችላለን” ብሏል። ጳውሎስ “በእርሱ አማካይነት” ብሎ ሲጽፍ በማን ማለቱ ነው? በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ማለቱ ነው። (ኤፌሶን 2:13, 18) አዎን፣ ወደ አብ በነጻነት መቅረብ የምንችለው በኢየሱስ አማካኝነት ነው።—ዮሐንስ 14:6፤ 15:16፤ 16:23, 24

19. (ሀ) እስራኤላውያን የሚያቀርቡት የዕጣን መሥዋዕት በይሖዋ ፊት አጸያፊ የሆነው መቼ ነበር? (ለ) ለይሖዋ የምናቀርበውን ጸሎት ጣፋጭ መዓዛ እንዳለው ዕጣን እንዲሆን ምን ማድረግ እንችላለን?

19 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው እስራኤላውያን ካህናት ያቀርቡት የነበረው የዕጣን መሥዋዕት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን የታማኝ አገልጋዮቹን ጸሎት ያመለክታል። ይሁንና ይሖዋ እስራኤላውያን የሚያቀርቡትን ዕጣን የተጸየፈበት ጊዜ ነበር። ይህ የሆነው እስራኤላውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ የዕጣን መሥዋዕት እያቀረቡ በሌላ በኩል ደግሞ ለጣዖታት በሰገዱበት ጊዜ ነበር። (ሕዝቅኤል 8:10, 11) ዛሬም በተመሳሳይ ይሖዋ፣ እርሱን እናገለግላለን እያሉ ከትእዛዛቱ ጋር የሚቃረን ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን ጸሎት ልክ እንደ አጸያፊ ሽታ ይመለከተዋል። (ምሳሌ 15:8) በመሆኑም ጸሎታችን ለአምላክ ጣፋጭ መዓዛ እንዲሆን በማንኛውም የኑሯችን ዘርፍ በንጽሕና እንመላለስ። ይሖዋ በጽድቅ ጎዳና ላይ የሚመላለሱ ሰዎች በሚያቀርቡት ጸሎት ይደሰታል። (ዮሐንስ 9:31) ይሁን እንጂ፣ አሁንም ቢሆን መልስ ማግኘት የሚኖርባቸው አንዳንድ ጥያቄዎች አሉ። መጸለይ ያለብን እንዴት ነው? ስለ ምን ጉዳዮችስ መጸለይ እንችላለን? አምላክ ለጸሎታችን ምላሽ የሚሰጠን እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህና ለሌሎችም ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

ልታብራራ ትችላለህ?

• ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ተቀባይነት ባለው መንገድ ወደ አምላክ መቅረብ የሚችሉት እንዴት ነው?

• በምናቀርባቸው ጸሎቶች ረገድ የዕብራውያን አባቶችን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

• የጥንት ክርስቲያኖች ካቀረቧቸው ጸሎቶች ምን እንማራለን?

• ጸሎታችን ለአምላክ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን የሚሆነው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ የአቤልን መሥዋዕት ሲቀበል የቃየንን ግን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነው ለምንድን ነው?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘እኔ ከንቱ፣ ትቢያና ዐመድ ነኝ’

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ከዐሥር እጅ አንዱን ለአንተ እሰጣለሁ”

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምታቀርበው ጸሎት በይሖዋ ፊት ጣፋጭ መዓዛ እንዳለው ዕጣን ነው?