በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!”

“አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!”

“አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!”

ዝሙር 119፣ ጸሐፊው በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ለተጻፈው መልእክት ወይም ቃል ያለውን ስሜት የሚገልጽ ነው። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።” “በሥርዐትህ ደስ ይለኛል።” “ዘወትር ደንብህን በመናፈቅ፣ ነፍሴ እጅግ ዛለች።” “ምስክርነትህ ለእኔ ደስታዬ ነው።” “ድንጋጌህን ናፈቅሁ።” “እኔ እወደዋለሁና፣ በትእዛዝህ ደስ ይለኛል።” “ሥርዐትህንም አሰላስላለሁ።” “አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።”—መዝሙር 119:11, 16, 20, 24, 40, 47, 48, 97

መዝሙራዊው አምላክ በግልጽ ላሰፈረው ቃል ልባዊ አድናቆት አሳይቷል! አንተስ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን መልእክት በተመለከተ እንዲህ ይሰማሃል? ለመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዲኖርህ ትፈልጋለህ? የምትፈልግ ከሆነ፣ በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ከተቻለም በየዕለቱ የማንበብ ልማድ ማዳበር ይኖርብሃል። ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:4) በሁለተኛ ደረጃ፣ ባነበብከው ነገር ላይ ማሰላሰል አለብህ። ስለ አምላክ፣ ስለ ባሕርያቱ፣ ስለ ፈቃዱና ስለ ዓላማው በሚገልጸው እውነት ላይ ማሰላሰልህ ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለህን አድናቆት ይጨምርልሃል። (መዝሙር 143:5) ከሁሉም በላይ ደግሞ ጠቃሚ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በዕለት ተዕለት ሕይወትህ በሥራ ላይ አውል።—ሉቃስ 11:28፤ ዮሐንስ 13:17

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኙት ሐሳቦች ፍቅር ማዳበርህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው? መዝሙር 119:2 ‘የአምላክን ምስክርነት [“ማሳሰቢያዎች፣” NW] የሚጠብቁ የተባረኩ ናቸው’ ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ማሳሰቢያዎች በሕይወትህ ውስጥ የሚገጥሙህን ችግሮች በሚገባ እንድትወጣ ይረዱሃል። (መዝሙር 1:1-3) ‘እግርህን ከክፉ መንገድ ሁሉ ለመከልከል’ የሚያስችልህን ጥበብና ማስተዋል ታገኛለህ። (መዝሙር 119:98-101) ስለ አምላክና ለምድር ስላለው ዓላማ እውነቱን ማወቅህ ሕይወትህ ይበልጥ ትርጉም እንዲኖረውና የወደፊቱ ተስፋህ ብሩህ እንዲሆን ያደርጋል።—ኢሳይያስ 45:18፤ ዮሐንስ 17:3፤ ራእይ 21:3, 4

የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ መረዳት እንዲችሉና ለመልእክቱ ፍቅር እንዲኖራቸው የመርዳት ልባዊ ፍላጎት አላቸው። ቀጥሎ ለቀረበው ግብዣ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ እናበረታታዎታለን።