በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የአይሁድን ሸንጎ በአንድነት ሰበሰቡ’

‘የአይሁድን ሸንጎ በአንድነት ሰበሰቡ’

‘የአይሁድን ሸንጎ በአንድነት ሰበሰቡ’

ሊቀ ካህናቱና የአይሁድ መሪዎች የሚያደርጉት ጠፍቷቸዋል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ሽብር ማስቆም የሚችሉት እንዴት ይሆን? ኢየሱስ ክርስቶስን ለማስገደል ያደረጉት ጥረት የተሳካላቸው ቢሆንም ደቀ መዛሙርቱ ከሞት የመነሳቱ ዜና በኢየሩሳሌም በሙሉ እንዲናፈስ እያደረጉ ነው። ታዲያ እነርሱን ዝም ማሰኘት የሚችሉት እንዴት ነው? ይህን ጉዳይ ለመወሰን ሊቀ ካህናቱና ደጋፊዎቹ ሳንሄድሪን በመባል የሚታወቀውን ከፍተኛውን ፍርድ ቤት ማለትም ‘የአይሁድን ሸንጎ በአንድነት ሰበሰቡ።’—የሐዋርያት ሥራ 5:21

በመጀመሪያው መቶ ዘመን በእስራኤል ገዥ የነበረው ሮማዊው ጳንጥዮስ ጲላጦስ በጊዜው ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። ይሁን እንጂ በሳንሄድሪንና በጲላጦስ መካከል የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? እያንዳንዳቸው ሕግ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመወሰን ረገድ ምን ሥልጣን ነበራቸው? የሳንሄድሪን አባላት የተውጣጡት ከየት ነው? ሸንጎው ሥራውን የሚያከናውነው እንዴት ነበር?

የሳንሄድሪን ታሪካዊ አመጣጥ

“ሳንሄድሪን” የሚለው ግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “አብሮ መቀመጥ” የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን ስብሰባን የሚያመለክት የወል መጠሪያ በመሆን ያገለግላል። በአይሁድ ወግ መሠረት አብዛኛውን ጊዜ ሃይማኖታዊ ፍርድ ቤትን ወይም ሸንጎን ያመለክታል።

ኢየሩሳሌም በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከጠፋች በኋላ ባሉት ዓመታት የተዘጋጀው የታልሙድ ጸሐፊዎች ሳንሄድሪንን እጅግ ጥንታዊ አካል እንደሆነ አድርገው ገልጸውታል። እነዚህ ሰዎች፣ ሳንሄድሪንን ያቀረቡት በአይሁድ ሕግ ላይ ለመወያየት ከተሰበሰቡ ሊቃውንት የተውጣጣና ሙሴ እስራኤልን በመምራት ረገድ እንዲያግዙት 70 ሽማግሌዎችን ከሾመበት ጊዜ አንስቶ የነበረ አካል እንደሆነ አድርገው ነው። (ዘኍልቍ 11:16, 17) የታሪክ ምሑራን ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። ፋርሳውያን እስራኤልን በቁጥጥር ሥር እስካዋሉበት ወቅት ድረስ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ሳንሄድሪን ጋር ተቀራራቢነት ያለው አካል እንዳልተመሠረተ ይጠቁማሉ። በተጨማሪም የታሪክ ምሑራኑ፣ የታልሙድ ጸሐፊዎች የጠቀሱት ሐሳብ የሚመሳሰለው ከሳንሄድሪን ጋር ሳይሆን በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው መቶ ዘመን ከነበሩት የረቢዎች ሸንጎ ጋር እንደሆነ ያምናሉ። ታዲያ ሳንሄድሪን የተቋቋመው መቼ ነበር?

መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ባቢሎን በግዞት ተወስደው የነበሩት እስራኤላውያን ነጻ ወጥተው በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ ይሁዳ ሲመለሱ ብሔሩን የሚያስተዳድር አካል እንዳቋቋሙ ይገልጻል። ነህምያና ዕዝራ እንደተናገሩት በወቅቱ ሽማግሌዎች፣ መኳንንትና ሹማምንት ነበሩ። ምናልባትም እነዚህ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ለተቋቋመው ሳንሄድሪን መሠረት ሳይሆኑ አልቀሩም።—ዕዝራ 10:8፤ ነህምያ 5:7

የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተጽፈው ከተጠናቀቁበት ጊዜ አንስቶ የማቴዎስ ወንጌል መጻፍ እስከጀመረበት ድረስ ያለው ጊዜ በአይሁድ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ አለመረጋጋት የሰፈነበት ወቅት ነበር። በ332 ከክርስቶስ ልደት በፊት ታላቁ እስክንድር ይሁዳን ተቆጣጠረ። እስክንድር ከሞተ በኋላ ይሁዳ፣ እርሱን በተኩት ሁለት የግሪክ አገዛዞች ማለትም በመጀመሪያ በቶሎሚዎች ቀጥሎም በሰሉሲዶች መተዳደሯን ቀጠለች። በ198 ከክርስቶስ ልደት በፊት በጀመረው በሰሉሲድ አገዛዝ ሥር በነበሩት መዝገቦች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ አይሁድ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የሚገልጹ ማስረጃዎችን እናገኛለን። ይህ ሸንጎ ያለው ሥልጣን ውስን የነበረ ቢሆንም አይሁዶች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት አካል እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር።

በ167 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰሉሲዳዊው ንጉሥ አንታይከስ አራተኛ (ኤፒፋነስ) አይሁዶች የግሪክን ባሕል እንዲቀበሉ ተጽዕኖ ማድረግ ጀመረ። ለዚየስ የሚሆን የአሳማ መሥዋዕት በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚገኘው መሠዊያ ላይ በማቅረብ የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ አረከሰ። ይህ ሁኔታ፣ አይሁዶች እንዲያምጹ ያደረገ ሲሆን መቃብያን በዚህ ወቅት የሰሉሲዳውያንን አገዛዝ ገርስሰው በምትኩ የሃስሞናውያንን አገዛዝ አቋቋሙ። a በዚህ ጊዜ ዓመጹን ይደግፍ የነበረውን ተራውን ሕዝብ የሚመሩት ጻፎችና ፈሪሳውያን ካህናቱ ብሔሩን በማስተዳደር ረገድ የነበራቸውን ሥልጣን በእጃቸው አስገቡ።

ከዚያም በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተጠቀሰው ሳንሄድሪን መልክ መያዝ ጀመረ። በኋላም ብሔሩን የሚቆጣጠር የአስተዳደር አካልና የአይሁድ ሕግ የሚተነተንበት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለመሆን በቃ።

የሥልጣን ሚዛን

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሁዳ በሮም አገዛዝ ሥር ነበረች። ሆኖም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አይሁዶች ከፍተኛ ነጻነት ነበራቸው። የሮማውያን ፖሊሲ በግዛታቸው ውስጥ ያሉት ሕዝቦች ራሳቸው በመረጡት አገዛዝ የመተዳደር ነጻነት እንዲኖራቸው ይደነግግ ነበር። በመሆኑም የሮም ባለ ሥልጣናት የአካባቢው ሸንጎ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ እጃቸውን አያስገቡም ነበር፤ ይህም በባሕል ልዩነት ሳቢያ ሊነሱ ይችሉ ከነበሩት ችግሮች ጠብቋቸዋል። የሮማውያን ፖሊሲ ዋና ዓላማ ተገዥዎቻቸው ወጋቸውን ሳይተዉ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በመፍቀድ በሰላምና በታማኝነት እንዲገዙላቸው ማድረግ ነበር። ሮማውያን፣ የሳንሄድሪን ሊቀ መንበር የሚሆነውን ሊቀ ካህን ይሾሙና ይሽሩ እንዲሁም ቀረጥ ያስከፍሉ የነበረ ቢሆንም ሉዓላዊነታቸውና ጥቅማቸው እስካልተነካ ድረስ በአይሁዶች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም ነበር። ከኢየሱስ የፍርድ ሂደት መገንዘብ እንደሚቻለው ሮም፣ የሞት ፍርድን የመሳሰሉ ከፍተኛ ብይኖችን የማሳለፍ ሥልጣኗን ለሳንሄድሪን አሳልፋ አልሰጠችም ነበር።—ዮሐንስ 18:31

በመሆኑም አብዛኛውን የአይሁዶችን የውስጥ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው ሳንሄድሪን ነበር። ሳንሄድሪን ሰዎችን የማሰር ሥልጣን ያላቸው ጠባቂዎች ነበሩት። (ዮሐንስ 7:32) የበታች ፍርድ ቤቶች ያለ ሮማውያን ጣልቃ ገብነት አነስተኛ ወንጀሎችን ይዳኙና የመብት ጥያቄዎችን ያስከብሩ ነበር። ከዚህም ሌላ የበታች ፍርድ ቤቶቹ ለአንድ ጉዳይ እልባት መስጠት ሲሳናቸው ጉዳዩ የመጨረሻ ብይን ወደሚያገኝበት ወደ ሳንሄድሪን ይላካል።

ሳንሄድሪን ይህን ዓይነቱን ሥልጣን እንደያዘ ለመቀጠል በሕዝቡ መካከል ሰላም እንዲሰፍን ማድረግና የሮማውያኑን አገዛዝ መደገፍ ነበረበት። ይሁንና ሮማውያኑ አንድ ዓይነት የፖለቲካ ተቃውሞ ይነሳል ብለው ከጠረጠሩ በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ተገቢ ነው ያሉትን እርምጃ ይወስዳሉ። ከዚህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች መካከል የሐዋርያው ጳውሎስ እስራት የሚጠቀስ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 21:31-40

የሸንጎው አባላት

ሳንሄድሪን 71 አባላት ያሉት ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዱ ሊቀ ካህን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ የአይሁድ መሪዎች ነበሩ። በሮማውያን ዘመን ሳንሄድሪን የካህናት ዘር ከሆኑ መኳንንት (በተለይም ደግሞ ሰዱቃውያን)፣ ካህናት ካልሆኑ ባላባቶችና የፈሪሳውያን ወገን ከሆኑ የተማሩ ጸሐፍት የተውጣጡ ሰዎችን ያቅፍ ነበር። ከሸንጎው ውስጥ አብዛኛውን መቀመጫ የያዙት ታዋቂ በሆኑ ሰዎች የሚደገፉት ከካህናት ዘር የሆኑ ባላባቶች ነበሩ። b ሰዱቃውያን ወግ አጥባቂዎች የነበሩ ሲሆን ፈሪሳውያን ደግሞ ለዘብተኞችና በዋነኝነት ከተራው ሕዝብ የተውጣጡ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸው ሰዎች ናቸው። ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ እንደዘገበው ሰዱቃውያን ፈሪሳውያንን ለመታዘዝ ያን ያህል ፈቃደኛ አልነበሩም። ጳውሎስ ሳንሄድሪን ፊት በቀረበበት ወቅት በሁለቱ ቡድኖች መካከል የነበረውን የተቀናቃኝነት መንፈስና የእምነት ልዩነት በመጠቀም የመከላከያ ሐሳቡን አቅርቧል።—የሐዋርያት ሥራ 23:6-9

አብዛኞቹ የሳንሄድሪን አባላት የገዥው መደብ ክፍል የሆኑ ባላባቶች መሆናቸው አባላቱ እስከ ዕድሜያቸው ፍጻሜ በሥልጣን ላይ እንዲቆዩና አዲስ አባል የሚሾሙትም ራሳቸው አባላቱ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሚሽና እንደሚለው ከሆነ ለአባልነት የሚታጩ ሰዎች “ካህናት፣ ሌዋውያን እንዲሁም ሴት ልጆቻቸው ከካህናቱ ጋር እንዲጋቡ የተፈቀደላቸው እስራኤላውያን” ማለትም የዘር ሐረጋቸው እንዳልተቀላቀለ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል። በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱትን የፍርድ ሂደቶች የሚቆጣጠረው ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመሆኑ በበታች ፍርድ ቤቶች የሚገኙ ዝና ያተረፉ ሰዎች እድገት አግኝተው የሳንሄድሪን አባላት እንዲሆኑ ይደረግ ነበር ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይመስላል።

ሥልጣን

አይሁዳውያን ለሳንሄድሪን ከፍተኛ አክብሮት ነበራቸው፤ በበታች ፍርድ ቤት የሚሠሩ ዳኞችም የሳንሄድሪንን ውሳኔ ካልተቀበሉ የሞት ቅጣት ይጠብቃቸው ነበር። የሳንሄድሪን ፍርድ ቤት ኢየሩሳሌምን፣ ቤተ መቅደሱንና በቤተ መቅደሱ የሚቀርበውን አምልኮ እንዲሁም የካህናቱን ብቃት በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮችን ትኩረት ሰጥቶ ይከታተላል። እውነት ነው፣ ሳንሄድሪን በኅብረተሰቡ ላይ ያለው እንዲህ ዓይነቱ ሥልጣን የሚሠራው በይሁዳ ውስጥ ብቻ ነበር። ያም ሆኖ ሳንሄድሪን ሕጉን በመተንተን ረገድ የመጨረሻው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን እንደሆነ ተደርጎ ስለሚታይ በየትኛውም የምድር ክፍል በሚገኝ የአይሁድ ኅብረተሰብ የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ሊቀ ካህናቱና ሸንጎው የክርስቶስ ተከታዮችን በማሰሩ ተግባር ላይ ትብብር እንዲያደርጉ በደማስቆ የሚገኙትን የምኩራብ አለቆች አዘዋቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 9:1, 2፤ 22:4, 5፤ 26:12) በተመሳሳይም፣ በዓላትን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የሄዱት አይሁዶች ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ጊዜ ስለ ሳንሄድሪን ማውራታቸው አይቀርም።

እንደ ሚሽና ዘገባ ከሆነ ሳንሄድሪን ሕግ በተላለፉ ዳኞች፣ በሐሰት ነቢያትና እነዚህን በመሳሰሉ ብሔሩን የሚመለከቱ ከፍተኛ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ሥልጣን ያለው ብቸኛ ሕጋዊ አካል ነበር። ኢየሱስና እስጢፋኖስ ተሳድባችኋል ተብለው የተከሰሱት፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ በመንግሥት ላይ እንዳሴሩና ጳውሎስ ደግሞ ቤተ መቅደሱን እንዳረከሰ ተደርገው ክስ የተመሰረተባቸው በዚህ ፍርድ ቤት ነው።—ማርቆስ 14:64፤ የሐዋርያት ሥራ 4:15-17፤ 6:11፤ 23:1፤ 24:6

በኢየሱስና በደቀ መዛሙርቱ ላይ የተበየነው ፍርድ

የሳንሄድሪን ሸንጎ በሰንበትና በበዓል ቀናት ካልሆነ በቀር ማለዳ ላይ ከሚቀርበው መሥዋዕት አንስቶ እስከ ምሽት መሥዋዕት ድረስ በፍርድ ወንበር ላይ ይሰየማል። የፍርድ ሂደቱ የሚካሄደው በቀን ብቻ ነበር። የሞት ቅጣት ከተላለፈ ብይኑ የሚገለጸው ችሎቱ በታየበት ቀን ማግስት ስለነበር እንዲህ ዓይነቶቹ ጉዳዮች በሰንበት ወይም በበዓል ዋዜማ ላይ ለውይይት አይቀርቡም ነበር። ለምሥክርነት የቀረቡ ሰዎች የንጹሕ ሰው ደም ማፍሰስ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በጥብቅ ይነገራቸዋል። በመሆኑም በበዓል ዋዜማ በቀያፋ ቅጥር ግቢ ውስጥ የኢየሱስን ጉዳይ ለማየት በምሽት የተሰየመው ችሎትና በእርሱ ላይ የተላለፈው ፍርድ ሕገ ወጥ ነው። ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ ኢየሱስ እንዲገደል ጲላጦስን ለማሳመን ሲሉ ራሳቸው ዳኞቹ የሐሰት ምሥክሮችን ማፈላለጋቸው ነው።—ማቴዎስ 26:57-59፤ ዮሐንስ 11:47-53፤ 19:31

በሞት ሊያስቀጡ የሚችሉ ክሶችን ለማየት የተሰየሙ ዳኞች የቀረቡላቸውን መረጃዎች ጊዜ ወስደው በጥንቃቄ እስኪመረምሩ ድረስ ተከሳሽን ከጉዳት የመጠበቅ ግዴታ ነበረባቸው። ሆኖም ከእርሱ በፊት እንደነበረው እንደ ኢየሱስ ሁሉ እስጢፋኖስም ይህን ዓይነቱን አጋጣሚ አላገኘም። ከዚህ ይልቅ በሳንሄድሪን ፊት ያቀረበው የመከላከያ ሐሳብ ተቃዋሚዎቹ በድንጋይ ወግረው እንዲገድሉት ምክንያት ሆኗል። ሮማውያን ጣልቃ ባይገቡ ኖሮ የጳውሎስም መጨረሻ ተመሳሳይ በሆነ ነበር። እንዲያውም የሳንሄድሪን ዳኞች ሊገድሉት ዶልተዋል።—የሐዋርያት ሥራ 6:12፤ 7:58፤ 23:6-15

ሆኖም መልካም ምግባር የነበራቸው አንዳንድ የሸንጎው አባላትም አልጠፉም። ኢየሱስን ቀርቦ ያነጋገረው ወጣት የአይሁድ አለቃ የሳንሄድሪን አባል ሳይሆን አይቀርም። ይህ ሰው ያለው ሀብት እንቅፋት ቢሆንበትም ኢየሱስ ተከታዩ እንዲሆን ግብዣ ያቀረበለት መልካም ባሕርይ ስለነበረው መሆን አለበት።—ማቴዎስ 19:16-22፤ ሉቃስ 18:18, 22

“ከአይሁድ አለቆች አንዱ” የሆነው ኒቆዲሞስ አብረውኝ የሚሠሩት ዳኞች ምን ይሉኛል በሚል ፍርሃት ወደ ኢየሱስ የሄደው ጨለማን ተገን አድርጎ ነበር። ይሁንና ኒቆዲሞስ እንደሚከተለው ብሎ በመጠየቅ በሳንሄድሪን ፊት ለኢየሱስ የመከላከያ ሐሳብ አቅርቧል:- “ሕጋችን፣ አስቀድሞ አንድን ሰው ሳይሰማና ምን እንዳደረገ ሳይረዳ ይፈርድበታልን?” ቆየት ብሎም ይህ ሰው የኢየሱስን አስከሬን ለመገነዝ የሚያገለግል “የከርቤና የእሬት ቅልቅል” አምጥቷል።—ዮሐንስ 3:1, 2፤ 7:51, 52፤ 19:39

የአርማትያሱ ዮሴፍ የሚባል ሌላ የሳንሄድሪን አባል ደግሞ በድፍረት ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ከለመነ በኋላ አዲስ ባስወቀረው መቃብር ውስጥ እንዲቀበር አድርጓል። ዮሴፍ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ” የነበረ ቢሆንም አይሁድን ስለፈራ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆኑ በይፋ እንዲታወቅ አልፈለገም ነበር። ይሁንና ዮሴፍ፣ የሳንሄድሪን ዳኞች ኢየሱስን ለመግደል በጠነሰሱት ሴራ ውስጥ ተካፋይ ባለመሆኑ ሊመሰገን ይገባዋል።—ማርቆስ 15:43-46፤ ማቴዎስ 27:57-60፤ ሉቃስ 23:50-53፤ ዮሐንስ 19:38

የሳንሄድሪን አባል የነበረው ገማልያል ለሥራ ባልደረቦቹ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት እንዲተዉአቸው በመንገር ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቷቸዋል። ቀጠል አድርጎም “እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል” ብሏቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:34-39) ታዲያ፣ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የአምላክ ድጋፍ አላቸው ብሎ ለማመን እንቅፋት የሆነበት ነገር ምንድን ነው? የሳንሄድሪን ዳኞች ኢየሱስ ያደረጋቸውን ተአምራት አምነው ከመቀበል ይልቅ የሚከተለውን ማሳበቢያ አቅርበው ነበር:- “ይህ ሰው ብዙ ታምራዊ ምልክቶችን እያደረገ ስለ ሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል? እንዲሁ ብንተወው ሰው ሁሉ በእርሱ ያምናል፤ ሮማውያንም መጥተው ሥፍራችንንና ሕዝባችንን ይወስዱብናል።” (ዮሐንስ 11:47, 48) የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለሥልጣን የነበረው ጥም ፍትሕ እንዳያስከብር እንቅፋት ሆኖበት ነበር። በተመሳሳይም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሰዎችን በፈወሱ ጊዜ በጊዜው የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች በነገሩ ደስ ከመሰኘት ይልቅ ‘በቅናት ተሞልተዋል።’ (የሐዋርያት ሥራ 5:17) ፈራጆች እንደመሆናቸው መጠን አምላክን መፍራትና ታማኝ መሆን ነበረባቸው፤ ሆኖም አብዛኞቹ ፍርድ የሚያዛቡና ታማኝነት የጎደላቸው ሆነዋል።—ዘፀአት 18:21፤ ዘዳግም 16:18-20

መለኮታዊ ፍርድ

እስራኤላውያን፣ የአምላክን ሕግ ባለመታዘዛቸውና መሲሑን አንቀበልም በማለታቸው ምክንያት ይሖዋ እነርሱን እንደ ምርጥ ሕዝቦቹ አድርጎ ማየቱን አቆመ። በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሮማውያን ኢየሩሳሌምንና በዚያ ይገኝ የነበረውን ቤተ መቅደስ አወደሙ፤ ይህም የአይሁድ ሥርዓት በአጠቃላይና ውሎ አድሮም የሳንሄድሪን መጨረሻ ሆነ።

ይሖዋ የሾመው ዳኛ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ ከነበሩት የሳንሄድሪን አባሎች መካከል ከሞት የሚነሱት አሊያም በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት በመሥራታቸው ሳቢያ ትንሣኤ የማያገኙት እነማን እንደሚሆኑ ይወስናል። (ማርቆስ 3:29፤ ዮሐንስ 5:22) ኢየሱስ እነዚህን ውሳኔዎች የሚያደርገው ፍጹም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንደሚሆን ልንተማመን እንችላለን።—ኢሳይያስ 11:3-5

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስለ መቃብያንና ስለ ሃስሞናውያን ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኅዳር 15, 1998 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 21-24⁠ንና የሰኔ  15, 2001 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 27-30⁠ን ተመልከት።

b መጽሐፍ ቅዱስ “የካህናት አለቆች” ብሎ የሚጠራቸው ቀደም ሲል ሊቀ ካህን የነበሩትንም ሆነ በወቅቱ ያሉትን ሊቀ ካህናት እንዲሁም ወደፊት በክህነት ሥርዓቱ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ይቀበላሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸውን የእነዚህን ሰዎች የቤተሰብ አባላት ነው።—ማቴዎስ 21:23