በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለዘላለም መኖር ትችላለህ

ለዘላለም መኖር ትችላለህ

ለዘላለም መኖር ትችላለህ

በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ። ይህን በተመለከተ ዝርዝር ሁኔታው ከሃይማኖት ሃይማኖት የተለያየ ቢሆንም ተስፋ የሚያደርጉት ነገር ተመሳሳይ ነው፤ የሁሉም ተስፋ እሞታለሁ የሚል ስጋት ሳይኖር በተመቻቸ ሁኔታ ሥር በደስታ መኖር ነው። አንተስ የምትመኘው የዚህ ዓይነት ሕይወት አይደለም? እንዲህ ዓይነቱ እምነት ይህን ያህል ሊስፋፋ የቻለው ለምንድን ነው? የዘላለም ሕይወት ተስፋስ ይፈጸም ይሆን?  

ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያሳዩት ፈጣሪ ገና ከጅምሩ ይኸውም የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት በፈጠረበት ወቅት ለዘላለም የመኖር ፍላጎትን በሰዎች ውስጥ ተክሏል። አምላክ ‘በሰዎች ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ’ በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል—መክብብ 3:11

ይሁን እንጂ ይህ ፍላጎት ተሳክቶ ሰዎች ለዘላለም መኖር እንዲችሉ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አምላክ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የመወሰን መብት እንዳለው አምነው መቀበል ነበረባቸው። እንደዚያ ቢያደርጉ ኖሮ ይሖዋ ለእነርሱ ባዘጋጀላቸው መኖሪያ ማለትም በዔድን ገነት ውስጥ “ለዘላለም” መኖር ይገባቸዋል ብሎ በፈረደላቸው ነበር።—ዘፍጥረት 2:8፤ 3:22

ለዘላለም የመኖር መብታቸውን አጡ

አምላክ በገነት ውስጥ ‘መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለውን የዕውቀት ዛፍ’ እንዳበቀለ እንዲሁም አዳምና ሔዋን ከዚህ ዛፍ እንዳይበሉ እንደከለከላቸውና ከበሉም ሞት እንደሚጠብቃቸው የነገራቸው መሆኑን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ያሳያል። (ዘፍጥረት 2:9, 17) አዳምና ሔዋን ከዚህ ዛፍ ፍሬ አለመብላታቸው የአምላክን ሥልጣን መቀበላቸውን መብላታቸው ደግሞ ሥልጣኑን አለመቀበላቸውን ያሳያል። ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን የይሖዋን መመሪያ ሳይታዘዙ በመቅረት በአምላክ ሥልጣን ላይ ካመጸው መንፈሳዊ ፍጡር ማለትም ከሰይጣን ጎን ቆሙ። በመጨረሻም አምላክ አዳምና ሔዋን ለዘላለም ለመኖር ብቁ እንዳልሆኑ ወሰነ።—ዘፍጥረት 3:1-6

አምላክ ከፊታቸው ያቀረበላቸው የሕይወት ወይም የሞት በሌላ አነጋገር የመኖር ወይም ያለመኖር ምርጫ ነበር። አለመታዘዛቸው ሞት ይኸውም ፈጽሞ ከሕልውና ውጪ መሆንን ያስከትልባቸዋል። አዳምም ሆነ ሔዋን እንዲሁም የእነርሱ ዘር የሆነ ማንኛውም ሰው አስማታዊ ኃይል ባለው መድኃኒት አማካኝነት ወይም የማትሞት ነፍስ ኖሯቸው ለዘላለም መኖር አይችሉም። a

ሁሉም የአዳም ዝርያዎች በእርሱ አለመታዘዝ ምክንያት ለሥቃይ ተዳርገዋል። ይህ ድርጊት ያስከተለውን መዘዝ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል።”—ሮሜ 5:12

የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚቻልበት መንገድ

ሐዋርያው ጳውሎስ የአዳም ዘሮች ያሉበትን ሁኔታ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በባርነት ሥር ከነበሩ ሰዎች ሁኔታ ጋር አመሳስሎታል። የአዳምና የሔዋን ልጆች በወረሱት ኃጢአት ምክንያት “የኀጢአት ባሮች” ሆነው ከመወለድ አላመለጡም፤ በዚህም ሳቢያ መሞታቸው አይቀርም። (ሮሜ 5:12፤ 6:16, 17) በመሆኑም ይሖዋ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ነጻ ካላወጣቸው በቀር ከዚህ ዓይነቱ ባርነት መላቀቅ አይችሉም ነበር። ጳውሎስ “በአንድ ሰው [በአዳም] መተላለፍ የተነሣ ኲነኔ በሁሉ ሰው ላይ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ” በማለት ሁኔታውን ግልጽ አድርጎታል። ይህ “የጽድቅ ሥራ” ኢየሱስ ፍጹም ሕይወቱን ‘ለሰው ሁሉ ተመጣጣኝ ቤዛ አድርጎ’ እንዲሰጥ አስችሎታል። ይሖዋ፣ ቤዛው ከሕግ አንጻር የሰው ዘሮችን ‘ከፍርድ ኲነኔ’ ነጻ ለማውጣት የሚያስችል ኃይል እንዳለው ያውቃል።—ሮሜ 5:16, 18, 19፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6 NW

ሳይንቲስቶች በሰው ጂን ውስጥ የሚገኘውን ኮድ በማጥናት ሰው ለዘላለም እንዲኖር ማድረግ ያልቻሉት ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት የሚቻለው በዚህ መንገድ ባለመሆኑ ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ከሆነ የሰው ልጅ መሞት ዋነኛው ምክንያት ባዮሎጂያዊ ሳይሆን ከሥነ ምግባርና ከሕግ ጋር የተያያዘ ነው። የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ይኸውም የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕትም እንዲሁ ከሕግ ጋር የተያያዘ መሆን አለበት። ከዚህም በላይ ቤዛው የአምላክ ጽድቅና ፍቅራዊ ደግነት መግለጫ ነው። ታዲያ ከቤዛው በመጠቀም የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት እነማን ናቸው?

ያለመሞት ባሕርይ ስጦታ

ይሖዋ “ከዘላለም እስከ ዘላለም” የሚኖር አምላክ ነው። እርሱ አይሞትም። (መዝሙር 90:2) ይሖዋ ያለመሞት ባሕርይ የሰጠው የመጀመሪያው አካል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶአልና፣ ዳግመኛ እንደማይሞት እናውቃለንና፤ ሞት ከእንግዲህ በእርሱ ላይ ጒልበት አይኖረውም።” (ሮሜ 6:9) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን ከምድራዊ ገዥዎች ጋር በማነጻጸር ያለመሞት ባሕርይ ያለው እርሱ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል። ኢየሱስ ‘ሁልጊዜ በሕይወት ይኖራል።’ ሕይወቱ “ኢመዋቲ” ማለትም የማይጠፋ ነው።—ዕብራውያን 7:15-17, 23-25፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:15, 16

ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን ስጦታ ያገኘው ኢየሱስ ብቻ አይደለም። ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ለመግዛት የተመረጡት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችም የእርሱ ዓይነት ትንሣኤ ያገኛሉ። (ሮሜ 6:5) ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን ስጦታ የሚያገኙት 144,000 ሰዎች እንደሆኑ ተናግሯል። (ራእይ 14:1) እነርሱም የማይሞት ሕይወት ያገኛሉ። ጳውሎስ የሚያገኙትን ትንሣኤ አስመልክቶ “ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም . . . መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና” ብሏል። ሞት ይህን ትንሣኤ በሚያገኙት ሰዎች ላይ ሥልጣን የለውም።—1 ቆሮንቶስ 15:50-53፤ ራእይ 20:6

ይህ መለኮታዊ ራእይ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። መላእክት መንፈሳዊ ፍጥረት ቢሆኑም እንኳ ለዘላለም የማይጠፋ ሕይወት እንዲኖራቸው ተደርገው አልተፈጠሩም። ከሰይጣን ጋር ያበሩ መንፈሳዊ ፍጡራን ጥፋት የሚጠብቃቸው መሆኑ ይህን ሐቅ ግልጽ ያደርግልናል። (ማቴዎስ 25:41) በሌላ በኩል ግን የኢየሱስ ተባባሪ ገዥዎች የማይጠፋ ሕይወት ያገኛሉ። ይህም ይሖዋ ግለሰቦቹ ታማኝ ሆነው ስለመቀጠላቸው የማያወላውል ትምክህት እንዳለው ያሳያል።

እንዲህ ሲባል ግን የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት እስከ ዛሬ ድረስ በምድር ላይ ከኖሩት በቢሊዮን ከሚቆጠሩ የሰው ልጆች ጋር ሲወዳደሩ በቁጥር ትንሽ የሆኑት 144,000 ሰዎች ብቻ ናቸው ማለት ነው? አይደለም። እስቲ እንዲህ የምንልበትን ምክንያት እንመልከት።

ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር መብት ስለሚያገኙ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕዝቦች አስደሳች መግለጫ ይዟል። ከእነዚህ መካከል ትንሣኤ አግኝተው፣ ጤንነታቸውና የወጣትነት ብርታታቸው ተመልሶላቸው የሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ይገኙበታል። (ራእይ 7:9፤ 20:12, 13፤ 21:3, 4) እነዚህ ሁሉ ሰዎች ‘ከአምላክ ዙፋን ወደሚወጣውና እንደ መስተዋት ወደጠራው የሕይወት ውሃ ወንዝ’ ያመራሉ። በወንዙ ግራና ቀኝ ደግሞ “የሕይወት ዛፍ” ያለ ሲሆን “የዛፉም ቅጠሎች ሕዝቦች የሚፈወሱባቸው ነበሩ።” ይሖዋ አምላክም በደግነት “የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ” የሚል ግብዣ ያቀርባል።—ራእይ 22:1, 2, 17

እነዚህ ዛፎችም ሆኑ ውኃው በመካከለኛው ዘመን የኖሩ ኬሚስቶችና አሳሾች ከረጅም ዓመታት በፊት ሲፈልጉት የነበረው አስማታዊ ኃይል ያለው መድኃኒት ወይም ወጣትነትን መልሶ ያጎናጽፋል የሚባለው የውኃ ምንጭ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ የሰው ልጅ ወደ ፍጽምና እንዲመለስ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ያደረጋቸውን ዝግጅቶች የሚያመለክቱ ናቸው።

አምላክ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ለዘላለም በምድር ላይ ለማኖር የነበረው ዓላማ አልተለወጠም። ይሖዋ ታማኝ ስለሆነ ይህን ዓላማውን ከግብ ያደርሳል። መዝሙር 37:29 “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል። ይህ ተስፋ እኛም የማይጠፋ ሰማያዊ ሕይወት ካገኙት የሰው ልጆች ጋር በመተባበር “ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ ሆይ፤ ሥራህ ታላቅና አስደናቂ ነው። የዘመናት ንጉሥ ሆይ፤ መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው። ጌታ ሆይ፤ አንተን የማይፈራ፣ ስምህን የማያከብርስ ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ [“ታማኝ፣” NW] ነህና” ብለን እንድናወድስ ይገፋፋናል።—ራእይ 15:3, 4 

ውድ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ለማግኘት ትፈልጋለህ? ከሆነ “የዘመናት ንጉሥ” ለሆነው ለይሖዋ ታማኝ እንዲሁም ታዛዥ መሆን ይጠበቅብሃል። ስለ ይሖዋና ይህ ሕይወት እንዲገኝ ምክንያት ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መማር አለብህ። አምላክ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ያወጣውን መሥፈርት የሚቀበሉ ሁሉ “የዘላለም ሕይወት” ያገኛሉ።—ዮሐንስ 17:3

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከሞት በኋላ ስለሚኖረው ሁኔታ የተሟላ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ስንሞት ምን እንሆናለን? የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለዘመናት የዘለቀ ሕልም

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2ኛው ሺህ ዓመት እንደተጻፈ የሚገመተው ስለ ጊልጋሜሽ የሚናገረው የጀግንነት ግጥም ይህ ሰው ዘላለም ወጣት ሆኖ ለመኖር ስላደረገው ጥረት ይተርካል። የጥንት ግብጻውያን ደግሞ ዘላለማዊ እንደሆነች የምትገመተው ነፍስ ወደነበረችበት አካል ተመልሳ ልትገባ ትችላለች በሚል እምነት አስከሬን አድርቀው የማቆየት ልማድ ነበራቸው። በዚህም ምክንያት የአንዳንድ ግብጻውያን መቃብሮች ግለሰቡ ከሞት በኋላ አለ ለሚባለው ሕይወት ያስፈልገው ይሆናል ተብለው በሚታሰቡ ዕቃዎች ይሞሉ ነበር።

የመካከለኛው ዘመን ቻይናውያን ኬሚስቶች ቢያንስ ቢያንስ ከስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ፣ የሰውን አካል ዘላለማዊ ማድረግ እንደሚቻል ያምኑ የነበረ ሲሆን አስማታዊ በሆኑ መድኃኒቶች አማካኝነት ይህን እውን ለማድረግ መጣር የጀመሩት ግን በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። በመካከለኛው ዘመን የነበሩ የአውሮፓና የአረብ ኬሚስቶች ዕድሜ ቀጥል መድኃኒቶችን ለማግኘት ያፈላልጉና ለመቀመም ጥረት ያደርጉ ነበር። ከቀመሟቸው መድኃኒቶች መካከል አንዳንዶቹ የአርሴኒክ፣ የሜርኩሪና የድኝ ጨዋማ ንጥረ ነገሮች ይገኙባቸዋል። እነዚህን ነገሮች ወስደው ምን ያህል ሰዎች እንዳለቁ ቤቱ ይቁጠረው!

በተጨማሪም በአንድ ወቅት ወጣትነትን መልሶ ያጎናጽፋል ተብሎ ስለሚታመን የውኃ ምንጭ የሚናገር አፈ ታሪክ በሰፊው ይወራ ነበር። ከዚህ ምንጭ የጠጣ ሰው ሁሉ የቀድሞ ብርታቱ ይመለስለታል ተብሎ ይታመን ነበር።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የዘላለም ሕይወት አሰልቺ ይሆን?

አንዳንድ ሰዎች የዘላለም ሕይወት አሰልቺ እንደሚሆን በማሰብ ሐሳቡን ያጣጥሉታል። እነዚህ ሰዎች ሁኔታው “ትርጉም በሌላቸው የጊዜ ማሳለፊያዎች ዕድሜን ከማባከን” ተለይቶ የማይታይ ማብቂያ የሌለው የሕይወት እሽክርክሪት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ምናልባት እነርሱ የዘላለም ሕይወት ሲባል ዛሬ ያለው የሰዎች የአኗኗር ዘይቤና ሁኔታ ለዘላለም የሚቀጥል ይመስላቸዋል፤ ይህ ደግሞ ለብዙዎች አሰልቺና ትርጉም አልባ ይሆንባቸዋል። ይሁን እንጂ አምላክ እንደገና በሚያመጣው ገነት ውስጥ ሰዎች ‘በታላቅ ሰላም ሐሤት’ እንደሚያደርጉ ተስፋ ሰጥቷል። (መዝሙር 37:11) እንዲህ ያለው ሕይወት የሰው ልጆች ስለ ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ተጨማሪ ነገሮችን የማወቅ አጋጣሚ የሚከፍትላቸው ከመሆኑም ባሻገር በአሁኑ ጊዜ በምኞት ብቻ የቀሩትን በጣም ግሩም ሙያዎች፣ የጥናት ዘርፎችና ዝንባሌዎች ለማዳበር ሰፊ ጊዜ ለመመደብ ያስችላል።

በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የሰውን ዕድሜ ለማራዘም በሚደረግ ጥናት ላይ የተሰማሩት የጄኔቲክስ ተመራማሪ ዶክተር ኦብሪ ደ ግሬ “በዛሬው ጊዜ በሚገባ የተማሩና እውቀታቸውን ለመጠቀም የሚያስችል ጊዜ ያላቸው ሰዎች ፈጽሞ አይሰለቹም፤ እንዲሁም ልንሠራው የምንፈልገው አዲስ ነገር ይጠፋል የሚል ስጋት አያድርባቸውም” በማለት ተናግረዋል። ያም ሆኖ እንኳ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል የሰው ልጆች፣ “እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም” በማለት ይናገራል።—መክብብ 3:11