በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠን በላይ ጥብቅ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠን በላይ ጥብቅ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠን በላይ ጥብቅ ነው?

በፊንላንድ የሚኖር አንድ ወጣት “በልጅነቴ ምንም ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ተምሬ ሌላው ቀርቶ ስለ አምላክ ሲነሳ እንኳ ሰምቼ አላውቅም” በማለት ተናግሯል። በዛሬው ጊዜ የብዙዎች አስተዳደግ ከዚህ የተለየ አይደለም። ብዙ ሰዎች በተለይ ደግሞ ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ያለፈበት እንዲሁም የሚሰጠው ምክር ከመጠን በላይ ጥብቅ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ መመራት የሚፈልጉ ሰዎች፣ ገደብና ሕግ የበዛበት ሕይወት የሚመሩ የተጨቆኑ ሰዎች እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። ስለዚህ ብዙዎች መመሪያ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ ይልቅ ወደ ሌላ ምንጭ ዞር ማለት የተሻለ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ለዘመናት ካስመዘገቡት የጭቆና ታሪክ አንጻር ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ቢሰማቸው ምንም አያስገርምም። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ የታሪክ ጸሐፍት የጨለማ ዘመን ብለው በሚጠሩት ወቅት ላይ በአውሮፓ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሰዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ትቆጣጠር ነበር ለማለት ይቻላል። አንድ ሰው በድፍረት ቤተ ክርስቲያኒቱ በምትፈጽመው ድርጊት አልስማማም ቢል ከፍተኛ ሥቃይ ብሎም የሞት ቅጣት ይጠብቀው ነበር። ከጊዜ በኋላ ብቅ ያሉት የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናትም ቢሆኑ የግለሰቦችን ነጻነት አግደው ነበር። በዛሬው ጊዜ ሰዎች “ካልቪኒስቶች” ወይም “ፒዩሪታኖች” ስለሚባሉት የፕሮቴስታንት ሃይማኖቶች ሲሰሙ ቶሎ ወደ አእምሯቸው የሚመጡት የእነዚህ ሃይማኖቶች አባላት ብቻ ሳይሆኑ ከእነዚህ ቡድኖች ጋር በተያያዘ የተፈጸሙት የጭካኔ ድርጊቶች ጭምር ናቸው። ሰዎች አብያተ ክርስቲያናት ጨቋኞች ስለነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርት ጨቋኝ መሆን አለበት የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።

ከቅርብ መቶ ዓመታት ወዲህ ቢያንስ ቢያንስ በአንዳንድ አገሮች አብያተ ክርስቲያናት የሰዎችን ሕይወት የመቆጣጠር ኃይላቸውን በእጅጉ አጥተዋል። አብያተ ክርስቲያናት ያምኑባቸው የነበሩ በወግ ላይ የተመሠረቱ ሃይማኖታዊ እምነቶች ተቀባይነት ማጣት ከጀመሩ በኋላ ሰዎች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ራሳቸው የመወሰን መብት አላቸው የሚለው ፈሊጥ ሥር እየሰደደ መጣ። ይህስ ምን አስከተለ? በክሪሚኖሎጂና በጁዲሻል ሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት አህቲ ላይቲነን “ሰዎች ለሥልጣን ያላቸው አክብሮት ቀንሷል እንዲሁም ተቀባይነት ስላላቸውና ስለሌላቸው ነገሮች ያላቸው ግንዛቤ ይበልጥ እየደበዘዘ መጥቷል” በማለት ተናግረዋል። ነገሩ አስገራሚ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም እንኳ እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ይታይባቸዋል። አንድ ታዋቂ የሉተራን ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ከሥነ ምግባር ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከአንድ ሃይማኖታዊ ባለ ሥልጣን መፍትሔ ይገኛል የሚለውን አመለካከት መቀበል በጣም ይከብደኛል።”

ገደብ የለሽ ነጻነት መኖሩ ጥሩ ነው?

ገደብ የለሽ ነጻነት የሚለው ሐሳብ በተለይ ለወጣቶች ማራኪ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ብዙዎች የሌሎች የበታች መሆን አሊያም እንዲህ አድርግ አታድርግ በሚሉ ዝርዝር ደንቦች መመራት አይፈልጉም። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሰው የፈለገውን የማድረግ ነጻነት ሊኖረው ይገባል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ምንም ዓይነት የትራፊክ ሕግ የሌለበት አንድ ትልቅ ከተማ አለ እንበል። በዚህ ከተማ መኪና ለማሽከርከር መንጃ ፈቃድም ሆነ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት የሚሰጠውን ፈተና መውሰድ አያስፈልግም። ሰዎች እንደፈለጋቸው ማሽከርከር ይችላሉ፤ ሌላው ቀርቶ ሰክረው ያሽከረክራሉ። ስለ ፍጥነት መጠን፣ ስለ ትራፊክ ምልክቶች፣ ስለ መብራቶች፣ በአንድ አቅጣጫ ስለሚያስኬዱ መንገዶች ወይም ስለ እግረኞች ማቋረጫ መንገዶች አይጨነቁም። ታዲያ እንዲህ ያለው “ነጻነት” መኖሩ ጥሩ ነው? በፍጹም አይደለም! ይህ መሆኑ ትርምስ፣ ግራ መጋባት ብሎም ከባድ አደጋ ያስከትላል። የትራፊክ ሕግ መኖሩ የሰዎችን ነጻነት በተወሰነ መጠን የሚገድብ ቢሆንም መኪና አሽከርካሪውንም ሆነ እግረኞችን ከአደጋ እንደሚጠብቃቸው ግልጽ ነው።

በተመሳሳይም ይሖዋ ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን የሚገልጽ መመሪያ ይሰጠናል። ይህን ማድረጉ ለእኛ ጥቅም ነው። እንደነዚህ ያሉ መመሪያዎች ባይኖሩ ኖሮ ስለ አንድ ነገር የምንማረው በሙከራ ይሆን ነበር። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ደግሞ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን እንጎዳለን። ከሥነ ምግባር አንጻር ገደብ የለሽ ነጻነት መኖሩ ተገቢ ካለመሆኑም በላይ የሚያስከትለው አደጋ የትራፊክ ሕግ በሌለበት ከተማ መኪና ከማሽከርከር የማይተናነስ ይሆናል። ሐቁ ግልጽ ነው:- በእርግጥም የተወሰኑ መመሪያዎችና ሕጎች ያስፈልጉናል፤ ብዙ ሰዎች በዚህ ሐሳብ ያለአንዳች ማመንታት ይስማማሉ።

“ሸክሜም ቀላል ነው”

የትራፊክ ሕጎች ረጃጅምና ዝርዝር ደንቦችን ያካተቱ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች መኪና ከማቆም ጋር ብቻ እንኳ በተያያዘ የወጡት ደንቦች ብዛታቸው በጣም የሚያስደንቅ ነው። በአንጻሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸው ደንቦች ያን ያህል ብዛት ያላቸው አይደሉም። ከዚህ ይልቅ የያዘው ቁልፍ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ብቻ ነው፤ እነዚህም ቢሆኑ ከባድ ወይም ጨቋኝ አይደሉም። ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመኑ ለነበሩት ሰዎች “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና” በማለት አስደሳች ግብዣ አቅርቦላቸዋል። (ማቴዎስ 11:28, 30) ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ በጻፈው ደብደቤ ላይ “የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ ነጻነት አለ” ብሏል።—2 ቆሮንቶስ 3:17

ይህ ነጻነት ግን ገደብ የለሽ አይደለም። ኢየሱስ፣ አምላክ ባወጣቸው መመሪያዎች ውስጥ የተካተቱት አንዳንድ ትእዛዞች ቀላል እንደሆኑ በግልጽ ተናግሯል። ለምሳሌ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 15:12) ሁሉም ሰው ይህን ትእዛዝ ቢከተል የሰዎች ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር አስብ! ስለሆነም ክርስቲያኖች ያላቸው ነጻነት ገደብ የለሽ አይደለም። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ሆናችሁ በነጻነት ኑሩ እንጂ ነጻነታችሁን የክፋት መሸፈኛ አታድርጉት” በማለት ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 2:16

ምንም እንኳ ክርስቲያኖች በዝርዝር ሕጎች ሥር ባይሆኑም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት በራሳቸው አመለካከት አይመሩም። ሰዎች ከአምላክ ብቻ የሚገኘው መመሪያ ያስፈልጋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰው አካሄዱን በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል’ በግልጽ ይናገራል። (ኤርምያስ 10:23) የአምላክን መመሪያ ከታዘዝን ብዙ በረከት እናገኛለን።—መዝሙር 19:11

የአምላክን መመሪያዎች መታዘዛችን ከሚያስገኝልን ጥቅሞች አንዱ ደስታ ነው። ለምሳሌ ያህል መግቢያችን ላይ የተጠቀሰው ወጣት ይዋሽና ይሰርቅ እንዲሁም የጾታ ብልግና ይፈጽም ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ሲረዳ ከተማረው ነገር ጋር ራሱን ለማስማማት በሕይወቱ ላይ ለውጥ አደረገ። እንዲህ በማለትም ይናገራል:- “ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በአንድ ጊዜ ተግባራዊ ማድረግ ባልችልም ያላቸውን ጠቀሜታ ተገንዝቤያለሁ። የቀድሞ አኗኗሬ አሁን ያለኝን ደስታ አላስገኘልኝም ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈሩትን መመሪያዎች መከተል ሕይወትህን ቀላል ያደርግልሃል። የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ትረዳለህ በተጨማሪም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለይተህ ታውቃለህ።”

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ተሞክሮ አላቸው። እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በመከተላቸው በርካታ ጥቅሞችን አግኝተዋል። ለአብነት ያህል ከሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ተሻሽሏል፣ ለሥራ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት አዳብረዋል፣ ጎጂ ከሆኑ ልማዶች ርቀዋል እንዲሁም ደስተኛ ሕይወት መምራት ችለዋል። ከጊዜ በኋላ ለውጥ አድርጎ በመጽሐፍ ቅዱስ መመራት የጀመረ ማርቆስ a የተባለ አንድ ወጣት “በመጽሐፍ ቅዱስ መመራቴ ለራሴ ያለኝ አክብሮት እንዲጨምር አድርጓል” ብሏል። b

ምርጫህ ምንድን ነው?

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ጥብቅ ነው? አዎ፣ ጥብቅ ነው። ይህ የሆነው ግን ለሁላችንም ጥቅም ሲባል ነው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠን በላይ ጥብቅ ነው? በፍጹም አይደለም። ገደብ የለሽ ነጻነት ለችግር ከመዳረግ የበለጠ ፋይዳ የለውም። የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ሚዛናዊ መሆናቸው ደኅንነታችን የተረጋገጠ እንዲሆን ብሎም ደስታችን እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያበረክቱልናል። ማርቆስ “ጊዜ ባለፈ መጠን የአምላክን ቃል በሕይወት ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የጥበብ እርምጃ መሆኑን ይበልጥ እየተገነዘብኩ መጥቻለሁ። በጥቅሉ ሲታይ አኗኗሬ በብዙ መንገድ ከሌሎች ሰዎች የተለየ ቢሆንም እንኳ በሕይወቴ ውስጥ የረባ ነገር እያመለጠኝ ነው ብዬ ለጥቂት ደቂቃ እንኳ አላስብም” በማለት ተናግሯል።

በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች መሠረት መኖር የሚያስገኛቸውን በረከቶች ማጣጣም ስትጀምር ለአምላክ ቃል ያለህ አድናቆት እየጨመረ ይሄዳል። ይህ ደግሞ ከዚህ ወደሚበልጥ በረከት ይመራሃል። ይኸውም የቃሉ ምንጭ የሆነውን ይሖዋ አምላክን መውደድ ትጀምራለህ። “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም።”—1 ዮሐንስ 5:3

ይሖዋ ፈጣሪያችን እንዲሁም ሰማያዊ አባታችን ነው። እርሱ ለእኛ የሚበጀውን ያውቃል። ነጻነታችንን ከመገደብ ይልቅ ለእኛ ጥቅም ሲል ፍቅራዊ መመሪያዎችን ይሰጠናል። ይሖዋ እጅግ ማራኪ በሆነ አነጋገር “ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር” በማለት አሳስቦናል።—ኢሳይያስ 48:18

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስሙ ተቀይሯል።

b አምላካዊ አኗኗርን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 12 ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የአምላክ ሕጎች እረፍት የሚሰጡ እንደሆኑ ተናግሯል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን መመሪያዎች መታዘዝ ደስታ የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ ለራሳችን ያለን አክብሮት እንዲጨምር ያደርጋል