በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በተንጣለለው ውቅያኖስ ላይ የጉዞን አቅጣጫ ማወቅ

በተንጣለለው ውቅያኖስ ላይ የጉዞን አቅጣጫ ማወቅ

በተንጣለለው ውቅያኖስ ላይ የጉዞን አቅጣጫ ማወቅ

የማርሻል ደሴቶች ሪፑብሊክ፣ ከባሕር ወለል በላይ አነስተኛ ከፍታ ያላቸው ከ1,200 የሚበልጡ ትላልቅና ትናንሽ ደሴቶችን የያዘ ነው። አንድ ሰው በባሕሩ ላይ ትንሽ እንደተጓዘ ደሴቶቹ ከእይታው ይሰወራሉ። ሆኖም ታንኳ ይጠቀሙ የነበሩት የጥንት የማርሻል ደሴት ባሕረተኞች በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ 2 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር በሚያህለው የደሴቶቹ ክልል ውስጥ ከአንዱ ደሴት ወደ ሌላው በሚጓዙበት ጊዜ አቅጣጫቸውን ፈጽሞ አይስቱም ነበር። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነበር? የእንጨት ሰንጠረዦች በሚባሉት ቀላል ሆኖም በጣም ውጤታማ በሆኑት “ካርታዎች” በመመራት ነበር።

በውቅያኖስ ላይ የብስ በሚኖርበት ጊዜ የሚፈጠረው ሞገድ የተለየ ቅርጽ እየሠራ ስለሚሄድ የማርሻል ደሴት ባሕረተኞች ከልምድ በመነሳት በ30 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የሚገኝ አንድ ደሴት የሚገኝበትን ቦታ ማወቅ ይችላሉ። ሞገዱ በውኃው ላይ የሚፈጥረው ቅርጽ የተለያየ ዓይነት በመሆኑ ይህ የእንጨት ሰንጠረዥ አንዱን ከሌላው ለይቶ ለማወቅ ይረዳቸዋል። ታዲያ እነዚህ የእንጨት ሰንጠረዦች ምን ይመስላሉ? በሥዕሉ ላይ መመልከት እንደሚቻለው የፓንዳኑስ ዛፍ ሥሮችን ወይም ቅጠሉ የተመለመለ የኮከናት ቅርንጫፍን አንድ ላይ እያሰሩ ከባሕሩ ሞገድ ጋር የሚመሳሰል ቅርጽ ይሠራሉ። ከዚያም ደሴቶቹ ያሉበትን አካባቢ ለመጠቆም በሰንጠረዦቹ ላይ ዛጎል ያስሩበታል።

የእንጨት ሰንጠረዦቹ አጠቃቀም ለተመረጡ ሰዎች ካልሆነ በስተቀር ለብዙ ዓመታት ምስጢር ሆኖ ቆይቷል። አንድ ወጣት ባሕረተኛ የእንጨት ሰንጠረዥ እንዴት መጠቀም እንደሚችል የሚማረው በምን መንገድ ነው? ሥልጠና በመውሰድና የተማረውን ነገር በመለማመድ ነው። ተሞክሮ ያለው አንድ ባሕረተኛ ወጣቱን ባሕረተኛ ቀረብ ወዳሉት ደሴቶች ይዞት በመጓዝ ሊሆን ይችላል ለብቻው ያስተምረዋል። የሚለማመደው ወጣት ሞገዱ የሚፈጥረውን የቅርጽ ዓይነት መለየት ከተማረ በኋላ በራሱ የእንጨት ሰንጠረዥ እየተመራ የመጓዝ ድፍረት እያገኘ ይሄዳል። ውሎ አድሮ ራሱን ችሎ በውቅያኖሱ ላይ መጓዝ ይችላል።

በተመሳሳይም የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ለሕይወት ጉዟችን መመሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። መጀመሪያ ላይ አንድ ሰው ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት መሠረታዊ ግንዛቤ እንዲኖረን ረድቶን ይሆናል። ከዚያም የአምላክን ቃል ማጥናታችንን ስንቀጥልና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በተግባር ላይ ስናውል ቃሉ በሚናገረው ነገር መተማመን እንጀምራለን። የእስራኤላውያን መሪ የነበረው ኢያሱ ‘የተጻፈውን ሁሉ በጥንቃቄ መፈጸም’ እንዲችል የአምላክን ቃል በየዕለቱ እንዲያነብ ተነግሮት ነበር። አምላክ ለኢያሱ “ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም” ብሎታል። (ኢያሱ 1:8) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛውንና ስኬታማ የሚያደርገንን የሕይወት ጎዳና እንድንከተል ሊጠቁመን ይችላል።

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Greg Vaughn