በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰው ልጅ ለዘላለም ለመኖር ያደረገው ጥረት

የሰው ልጅ ለዘላለም ለመኖር ያደረገው ጥረት

የሰው ልጅ ለዘላለም ለመኖር ያደረገው ጥረት

የሰው ልጅ ከጥንት ጀምሮ ለዘላለም ለመኖር ሲያልም ቆይቷል። ይሁን እንጂ ማንም ቢሆን ሞትን ድል መንሳት የሚቻልበትን ዘዴ ማግኘት ስላልቻለ ይህ ሕልም እውን ሳይሆን ቀርቷል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በሕክምናው ዘርፍ የሚደረገው ምርምር የሰውን የሕይወት ዘመን ማርዘም የሚቻልበት መንገድ ይኖራል የሚለውን ተስፋ አለምልሞታል። በዚህ ረገድ በተለያዩ ሳይንሳዊ የምርምር ዘርፎች ምን ጥረት እየተደረገ እንዳለ እንመልከት።

የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች፣ ሴሎች ራሳቸውን የሚያድሱበት ሂደት እንዳይቆም ማድረግ የሚያስችል ዘዴ ለማግኘት ቴሎሜሬስ በሚባሉ ኢንዛይሞች ላይ ምርምር እያደረጉ ነው። ሳይንቲስቶች አሮጌ ሴሎች እንደሚሞቱና በአዲስ እንደሚተኩ ያውቃሉ። እንዲያውም አንድ ሰው በሕይወት ዘመኑ አብዛኛው የሰውነቱ ክፍል ይታደሳል። አንዳንድ ተመራማሪዎች ይህ የመታደስ ሂደት ቢቀጥል ኖሮ “የሰው አካል ራሱን በራሱ እያደሰ ለረጅም ጊዜ እንዲያውም ለዘላለም መቀጠል ይችል ነበር” ብለው ያምናሉ።

ቴራፒዮቲክ ክሎኒንግ በሚባለው አወዛጋቢ የምርምር መስክ ለሕሙማን በቤተ ሙከራ የተሠራ አዲስና ፍጹም ተስማሚ ጉበት፣ ኩላሊት ወይም ልብ መተካት ይቻላል የሚል ንድፈ ሐሳብ ቀርቧል። እነዚህ አካላት የሚሠሩት የሕመምተኛውን ስቴም ሴል በመጠቀም ነው።

ናኖቴክኖሎጂ በሚባል የምርምር ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ተመራማሪዎች ወደፊት ዶክተሮች የካንሰር ሴሎችንና ሌሎች ጎጂ ባክቴሪያዎችን መርጠው የሚያጠፉ የሴል መጠን ያላቸው ሮቦቶችን በደም ሥር የሚሰጡበት ጊዜ እንደሚመጣ ይሰማቸዋል። አንዳንዶች ይህ ሳይንሳዊ የምርምር ዘርፍ በጂን አማካኝነት በሚሰጠው ሕክምና ከታገዘ ውሎ አድሮ የሰው አካል ለዘላለም መኖር የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ያምናሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን በበረዶ ውስጥ አቀዝቅዘው የማቆየት ልማድ ያላቸው ቡድኖች አሉ። ክራዮኒክስ በመባል የሚታወቀው የዚህ ልማድ ደጋፊዎች ይህን የሚያደርጉት ወደፊት የሕክምናው ዘርፍ ትልቅ እመርታ አሳይቶ ዶክተሮች በሽታዎችን የሚፈውሱበት እንዲሁም የእርጅና ውጤቶችን የሚቀለብሱበትና ለሞቱ ግለሰቦች ሕይወትም ሆነ ጤንነት መልሰው የሚያጎናጽፉበት ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አስከሬኑ እንዳይፈርስ ለማድረግ ነው። አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ጄሪያትሪክ ሳይካትሪ ይህን ሐሳብ “ከጥንት ግብጻውያን ሬሳ አድርቆ የማቆየት ልማድ ጋር የሚመሳሰል ነው” ብሎታል።

የሰው ልጅ ለዘላለም ለመኖር ሲል የሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት ሰዎች ሞትን አምነው ለመቀበል ምን ያህል አዳጋች እንደሆነባቸው የሚያሳይ ነው። በእርግጥ የሰው ልጅ ለዘላለም መኖር ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል? የሚቀጥለው ርዕስ መልስ ይሰጠናል።