ይሖዋን ተስፋ በማድረግ ደፋሮች ሁኑ
ይሖዋን ተስፋ በማድረግ ደፋሮች ሁኑ
“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፣ [“ደፋር ሁን፣” NW] በርታ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።”—መዝሙር 27:14
1. ተስፋ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ይህ ቃል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተሠራበት እንዴት ነው?
እውነተኛ ተስፋ እንደ ደማቅ ብርሃን ነው። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ከሚያጋጥሙን ችግሮች በስተጀርባ አሻግረን እንድንመለከትና የወደፊቱን ጊዜ በድፍረትና በደስታ ስሜት እንድንጠባበቅ ይረዳናል። የተረጋገጠ ተስፋ ሊሰጠን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ሲሆን ይህንንም የሚያደርገው በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ አማካኝነት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እንዲያውም “ተስፋ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ160 ጊዜ በላይ ተጽፎ የሚገኝ ሲሆን ቃሉ አንድን ጥሩ ነገርንም ሆነ ያንን ነገር ለመስጠት ተስፋ የገባውን አካል በጉጉትና በእርግጠኝነት ስሜት መጠባበቅን ያመለክታል። a እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ፣ ተጨባጭ መሠረት ከሌለው ወይም ሊፈጸም ከማይችል ተራ ምኞት እጅግ የላቀ ነው።
2. ተስፋ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ምን ሚና ተጫውቷል?
2 ኢየሱስ ችግርና መከራ በደረሰበት ጊዜ ከእነዚህ ነገሮች በስተጀርባ አሻግሮ በመመልከት በይሖዋ ላይ ተስፋ አድርጓል። “እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን [“የመከራውን እንጨት፣” NW] ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል።” (ዕብራውያን 12:2) ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን ያደረገው የይሖዋን ሉዓላዊነት በማረጋገጡና የአምላክን ስም በማስቀደሱ ላይ ስለነበር ምንም ያህል መሥዋዕትነት ቢጠይቅበት እርሱን ከመታዘዝ ፈቀቅ አላለም።
3. ተስፋ በአምላክ አገልጋዮች ሕይወት ውስጥ ምን ሚና ይጫወታል?
3 ንጉሥ ዳዊት በተስፋና በድፍረት መካከል ያለውን ግንኙነት ሲገልጽ “እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፣ [“ደፋር ሁን፣” NW] በርታ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ” ብሏል። (መዝሙር 27:14) እንድንበረታ ወይም ልባችን ጽኑ እንዲሆን ከፈለግን ተስፋችን እንዲደበዝዝ መፍቀድ አይኖርብንም፤ ከዚህ ይልቅ ዘወትር በአእምሯችንና በልባችን ልንይዘውና እንደ ውድ ሀብት አድርገን ልንመለከተው ይገባል። ይህን ማድረጋችን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲያከናውኑት በሰጣቸው ሥራ ላይ ስንካፈል የእርሱን ዓይነት ድፍረትና ቅንዓት ለማሳየት ይረዳናል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በእርግጥም ተስፋ የአምላክ አገልጋዮች በሕይወታቸው ውስጥ ከሚያንጸባርቋቸው ጸንተው ከሚኖሩ ባሕርያት ማለትም ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብሮ መጠቀሱ ተገቢ ነው።—1 ቆሮንቶስ 13:13
‘ተስፋችሁ የተትረፈረፈ’ ነው?
4. ቅቡዓን ክርስቲያኖችና አጋሮቻቸው የሆኑት “ሌሎች በጎች” ምን ተስፋ አላቸው?
4 የአምላክ ሕዝቦች ወደፊት አስደሳች ጊዜ ይጠብቃቸዋል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ ሆነው ከክርስቶስ ጋር የሚያገለግሉበትን ጊዜ በጉጉት ሲጠባበቁ “ሌሎች በጎች” ደግሞ ‘ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥተው [ለምድራዊ] የእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት የሚደርሱበትን’ ጊዜ ተስፋ ያደርጋሉ። (ዮሐንስ 10:16፤ ሮሜ 8:19-21፤ ፊልጵስዩስ 3:20) ይህ ‘ክብራማ ነጻነት’ ከኃጢአትና ኃጢአት ካስከተላቸው አስከፊ ችግሮች መላቀቅን ይጨምራል። በእርግጥም ‘የበጎ ስጦታና የፍጹም በረከት ሁሉ’ ምንጭ የሆነው ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን አብዝቶ ይባርካቸዋል።—ያዕቆብ 1:17፤ ኢሳይያስ 25:8
5. ‘ተስፋችን የተትረፈረፈ’ እንዲሆን ምን ማድረግ ይገባናል?
5 ክርስቲያናዊ ተስፋ በሕይወታችን ውስጥ ምን ያህል ትልቅ ሚና ሊጫወት ይገባል? በሮሜ 15:13 ላይ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “በእርሱ በመታመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ፤ ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተስፋ ተትረፍርፎ እንዲፈስላችሁ ነው።” አዎን፣ ተስፋ በጨለማ ውስጥ ጭል ጭል ከሚል ሻማ ሳይሆን ከደማቅ የጠዋት ፀሐይ ብርሃን ጋር የሚመሳሰል ሲሆን አንድ ሰው ሰላምና ደስታ የሰፈነበት እንዲሁም ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲኖረውና ደፋር እንዲሆን ይረዳዋል። ‘ተስፋችን የተትረፈረፈ’ የሚሆነው በጽሑፍ በሰፈረው የአምላክ ቃል ስናምንና መንፈስ ቅዱስን ስንቀበል መሆኑን ልብ በል። ሮሜ 15:4 “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል” ይላል። በመሆኑም እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የሚያነብ ጥሩ ተማሪ በመሆን ተስፋዬ ብሩህ ሆኖ እንዲቀጥል እያደረኩ ነው? የአምላክን መንፈስ ለማግኘት ዘወትር እጸልያለሁ?’—ሉቃስ 11:13
6. ተስፋችን ምንጊዜም ብሩህ እንዲሆን ራሳችንን ከምን ነገሮች መጠበቅ ይኖርብናል?
6 ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ከአምላክ ቃል ብርታት አግኝቷል። እኛም የእርሱን አርዓያ በጥብቅ መከተላችን ‘ዝለን ተስፋ እንዳንቆርጥ’ ያደርገናል። (ዕብራውያን 12:3) አምላክ የሰጠን ተስፋ ከአእምሯችንና ከልባችን እየጠፋ ከሄደ ወይም ደግሞ ቁሳዊ ነገሮችን አሊያም ዓለማዊ ግቦችን በመሳሰሉ ነገሮች ትኩረታችን ከተከፋፈለ ብዙም ሳይቆይ በመንፈሳዊ ልንዝል እንችላለን፤ ይህም ውሎ አድሮ የሞራል ጥንካሬም ሆነ ድፍረት እንድናጣ ያደርገናል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ ‘እምነታችን አደጋ ደርሶበት እንደሚጠፋ መርከብ’ ይሆናል። (1 ጢሞቴዎስ 1:19) በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛ ተስፋ እምነታችንን ያጠነክርልናል።
ተስፋ ለእምነት አስፈላጊ ነው
7. ተስፋ ለእምነት በጣም አስፈላጊ የሆነው በምን መንገዶች ነው?
7 መጽሐፍ ቅዱስ “እምነት ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈጸም እርግጠኛ የምንሆንበት፣ የማናየውም ነገር እውን መሆኑን የምንረዳበት ነው” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 11:1) በመሆኑም ተስፋ ከእምነት የሚያንስ ባሕርይ ሳይሆን ወሳኝ የሆነ የእምነት ክፍል ነው። ለምሳሌ አብርሃምን ተመልከት። ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ይሖዋ ወራሽ የሚሆን ልጅ እንደሚሰጣቸው ቃል ሲገባላቸው አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ልጅ መውለድ የሚችሉበት ዕድሜ አልፎ ነበር። (ዘፍጥረት 17:15-17) ታዲያ አብርሃም ምን ምላሽ ሰጠ? “ምንም ተስፋ በሌለበት፣ አብርሃም በተስፋ አምኖ የብዙ ሕዝብ አባት ሆነ።” (ሮሜ 4:18) አዎን፣ አምላክ የሰጠው ተስፋ አብርሃም ዘር እንደሚተካ ለማመን ጠንካራ መሠረት ሆኖታል። እምነቱ ደግሞ ተስፋውን ብሩህ ያደረገለት ከመሆኑም በላይ ስለ መፈጸሙ እርግጠኛ እንዲሆን አድርጎታል። ይህም በመሆኑ አብርሃምና ሣራ ቤታቸውንና ዘመዶቻቸውን ትተው ቀሪውን የሕይወት ዘመናቸውን በባዕድ አገር በድንኳን ውስጥ ለማሳለፍ እንዲነሳሱ ድፍረት ሰጥቷቸዋል!
8. ጽናት ተስፋችንን የሚያጠናክረው እንዴት ነው?
8 አብርሃም በጣም አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር አምላክን ሙሉ በሙሉ በመታዘዝ ተስፋውን አጽንቶ መያዝ ችሏል። (ዘፍጥረት 22:2, 12) በተመሳሳይም፣ ታዛዥ ከሆንንና በይሖዋ አገልግሎት ከጸናን እንደምንባረክ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ጳውሎስ “ጽናት የተፈተነ ባሕርይን”፣ የተፈተነ ባሕርይ ደግሞ ተስፋን እንደሚያስገኝ ከገለጸ በኋላ “ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም” ብሏል። (ሮሜ 5:4, 5) ጳውሎስ፣ “የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን” በማለት የጻፈው ለዚህ ነው። (ዕብራውያን 6:11) ከይሖዋ ጋር በመሠረትነው ጥብቅ ዝምድና ላይ የተገነባው እንዲህ ዓይነቱ አዎንታዊ አመለካከት ማንኛውንም ዓይነት መከራ በድፍረት ብሎም በደስታ እንድንቋቋም ይረዳናል።
“በተስፋ ደስተኞች ሁኑ”
9. ‘በተስፋ ደስተኞች ለመሆን’ ዘወትር ምን ማድረግ እንችላለን?
9 አምላክ የሰጠን ተስፋ ዓለም ከሚያቀርብልን ከማንኛውም ነገር እጅግ የላቀ ነው። መዝሙር 37:34 (የ1980 ትርጉም) እንዲህ ይላል:- “ተስፋህን በእግዚአብሔር ላይ አድርግ፤ ትእዛዙንም ፈጽም፤ እርሱም ምድርን በማውረስ ያከብርሃል፤ ክፉዎች ሲወገዱም ታያለህ።” አዎን፣ ‘በተስፋ ደስተኞች የምንሆንበት’ በቂ ምክንያት አለን። (ሮሜ 12:12) ይሁንና እንዲህ ለማድረግ ተስፋችን በአእምሯችን ውስጥ ብሩህ ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል። አምላክ በሰጠን ተስፋዎች ላይ ዘወትር ታሰላስላለህ? ጥሩ ጤንነት ኖሮህ፣ ከጭንቀት ነጻ በሆነና በምትወዳቸው ሰዎች በተሞላ ገነት ውስጥ እርካታ የሚያስገኝ ሥራ እየሠራህ ስትኖር በዓይነ ሕሊናህ ይታይሃል? በጽሑፎቻችን ላይ በሚወጡት የገነት ሥዕሎች ላይ ታሰላስላለህ? እንዲህ ያለው ማሰላሰል ከቤታችን ውጭ ያለን አንድ ግሩም አካባቢ በደንብ ለማየት ስንል የመስኮታችንን መስተዋት ከማጽዳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የመስኮታችንን መስተዋት ለማጽዳት ቸልተኞች የምንሆን ከሆነ ብዙም ሳይቆይ በቆሻሻና በአቧራ ስለሚሸፈን የአካባቢው ማራኪነት ጥርት ብሎ ላይታየን ይችላል። ትኩረታችንም በሌሎች ነገሮች ሊወሰድ ይችላል። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ እንዲደርስብን በፍጹም አንፍቀድ!
10. ወደፊት የምናገኘውን ሽልማት በጉጉት መጠበቃችን ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዳለን ሊያሳይ የሚችለው እንዴት ነው?
10 እውነት ነው፣ ይሖዋን የምናገለግልበት ዋናው ምክንያት ለእርሱ ያለን ፍቅር ነው። (ማርቆስ 12:30) ያም ሆኖ ወደፊት የምናገኘውን ሽልማት በጉጉት መጠበቃችን የተገባ ነው። ይሖዋም ቢሆን እንዲህ እንድናደርግ ይፈልጋል! ዕብራውያን 11:6 እንዲህ ይላል:- “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት።” ይሖዋ ዋጋ የሚከፍል አምላክ አድርገን እንድንመለከተው የሚፈልገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይህን ማድረጋችን በሰማይ የሚኖረው አባታችንን በደንብ እንደምናውቀውና ቸር እንዲሁም ልጆቹን የሚወድ አምላክ መሆኑን እንደምንገነዘብ ያሳያል። ‘ያማረ ፍጻሜና ተስፋ’ ባይኖረን ኖሮ ምን ያህል ልናዝን ብሎም ቶሎ ተስፋ ልንቆርጥ እንደምንችል አስብ።—ኤርምያስ 29:11
11. ሙሴ አምላክ የሰጠው ተስፋ ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንዲያደርግ የረዳው እንዴት ነው?
11 ትኩረታቸውን አምላክ በሰጠው ተስፋ ላይ በማድረግ ረገድ ግሩም ምሳሌ ከሆኑ ሰዎች መካከል ሙሴ ይገኝበታል። ሙሴ “የፈርዖን የልጅ ልጅ” እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ስለነበር በግብጽ ውስጥ ሥልጣን፣ ክብርና ሀብት የማግኘት አጋጣሚ ነበረው። ታዲያ ሙሴ እነዚህን ነገሮች ከማሳደድና ይሖዋን ከማገልገል የትኛውን ይመርጥ ይሆን? ሙሴ በድፍረት ይሖዋን ለማገልገል መርጧል። ለምን? ምክንያቱም ‘ብድራቱን ከሩቅ [“ትኵር ብሎ፣” የ1954 ትርጉም] ተመልክቶአል።’ (ዕብራውያን 11:24-26) አዎን፣ ሙሴ ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ በግዴለሽነት እንዳልተመለከተው ግልጽ ነው።
12. ክርስቲያናዊ ተስፋ ከራስ ቁር ጋር የተመሳሰለው ለምንድን ነው?
12 ሐዋርያው ጳውሎስ ተስፋን ከራስ ቁር ጋር አመሳስሎታል። ምሳሌያዊው የራስ ቁራችን አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል፤ እንዲሁም ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድናደርግ፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ እንድንሰጥና ጽኑ አቋም ይዘን እንድንቀጥል ይረዳናል። (1 ተሰሎንቄ 5:8) ምሳሌያዊውን የራስ ቁርህን ዘወትር ታጠልቃለህ? ከሆነ ልክ እንደ ሙሴና ጳውሎስ አንተም ተስፋ የምታደርገው “ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት” ላይ አይሆንም። እርግጥ ነው፣ የራስን ጥቅም ከማሳደድ ይልቅ ብዙኃኑ ለሚከተለው ጎዳና ጀርባን መስጠት ድፍረት ይጠይቃል፤ ሆኖም እንዲህ ማድረጋችን ፈጽሞ የሚያስቆጭ አይሆንም! ደግሞስ ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉና እርሱን የሚወዱ ሰዎች ከሚያገኙት ‘እውነተኛ ሕይወት’ ያነሰ ዋጋ ለምን እንቀበላለን?—1 ጢሞቴዎስ 6:17, 19
“ከቶ አልተውህም”
13. ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ምን ዋስትና ሰጥቷቸዋል?
13 በአሁኑ ሥርዓት ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች የዚህ ዓለም ‘ምጥ’ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ በሄደ መጠን ወደፊት ስለሚከሰተው አስፈሪ ሁኔታ በቁም ነገር ሊያስቡበት ይገባል። (ማቴዎስ 24:8) ይሁንና ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት አይታይባቸውም። እነዚህ ሰዎች ‘በሰላም ይኖራሉ፣ ክፉን ሳይፈሩም ያለ ሥጋት ይቀመጣሉ።’ (ምሳሌ 1:33) ተስፋ የሚያደርጉት አሁን ባለው ሥርዓት ባለመሆኑ ጳውሎስ የሰጣቸውን የሚከተለውን ማሳሰቢያ በደስታ ይቀበላሉ:- “ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ ‘ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም’ ብሎአል።”—ዕብራውያን 13:5
14. ክርስቲያኖች ስለ ቁሳዊ ፍላጎቶቻቸው ከልክ በላይ መጨነቅ የሌለባቸው ለምንድን ነው?
14 “ከቶ” እና “በፍጹም” የሚሉት አገላለጾች አምላክ እንደሚያስብልን በግልጽ ያሳያሉ። በተመሳሳይም ኢየሱስ የአምላክ ፍቅራዊ አሳቢነት እንደማይለየን ሲገልጽ የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጥቶናል:- “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ [ለሕይወት የሚያስፈልጉ ቁሳዊ ነገሮች] ይጨመሩላችኋል። ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና።” (ማቴዎስ 6:33, 34) ይሖዋ ለመንግሥቱ ቀናተኛ ከመሆን ጎን ለጎን ሥጋዊ ፍላጎቶቻችንን የማሟላት ኃላፊነታችንን መወጣት ከባድ መሆኑን ያውቃል። በመሆኑም የሚያስፈልጉንን ነገሮች የመስጠት ችሎታም ሆነ ፍላጎት እንዳለው በማመን ሙሉ ትምክህታችንን በእርሱ ላይ እንጣል።—ማቴዎስ 6:25-32፤ 11:28-30
15. ክርስቲያኖች ‘ጤናማ ዓይን’ ይዘው መቀጠል የሚችሉት እንዴት ነው?
15 ‘ጤናማ ዐይን’ ይዘን መኖራችን በይሖዋ ላይ እንደምንታመን ያሳያል። (ማቴዎስ 6:22, 23) ጤናማ ዓይን እውነተኛ፣ በቅን ልቦና የሚነሳሳና ከስግብግብነትና ከራስ ወዳድነት ምኞት የጸዳ ነው። ጤናማ ዓይን ይኖረናል ሲባል በከፋ ድህነት ሥር እንኖራለን አሊያም ቁሳዊ ፍላጎታችንን የማሟላት ኃላፊነታችንን ችላ እንላለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ አገልግሎት ቅድሚያውን በመስጠት ‘ራስን የመግዛት መንፈስ’ ወይም ጤናማ አስተሳሰብ እናንጸባርቃለን ማለት ነው።—2 ጢሞቴዎስ 1:7
16. ጤናማ ዓይን ይዘን ለመኖር እምነትና ድፍረት አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
16 ጤናማ ዓይን ይዞ መኖር እምነትና ድፍረት ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል፣ አሠሪህ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በሚደረጉበት ሰዓት ላይ ሥራ እንድትሠራ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሊያስገድድህ ቢሞክር ደፋር ሆነህ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠትህን ትቀጥላለህ? አንድ ሰው ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች እንደሚያሟላላቸው የገባውን ቃል መጠራጠር ከጀመረ፣ ሰይጣን ከውጭ የሚመጣበት ግፊት እንዲያይልበት በማድረግ ጭራሹኑ ከጉባኤ እንዲቀር ሊያደርገው ይችላል። አዎን፣ እምነት ማጣታችን ሰይጣን እንዲቆጣጠረን አጋጣሚ ይከፍትለታል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡንን ነገሮች የሚመርጥልን ይሖዋ ሳይሆን ሰይጣን ይሆናል ማለት ነው። ይህ እንዴት የሚያሳዝን ነገር ነው!—2 ቆሮንቶስ 13:5
“ተስፋህን በእግዚአብሔር ላይ አድርግ”
17. በይሖዋ የሚታመኑ ሰዎች በአሁኑ ጊዜም እንኳ በረከቶችን የሚያገኙት እንዴት ነው?
17 ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋን ተስፋ የሚያደርግና የሚታመን ሰው መቼም ቢሆን እንደማይወድቅ በተደጋጋሚ ይገልጻሉ። (ምሳሌ 3:5, 6፤ ኤርምያስ 17:7) እውነት ነው፣ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች አንዳንዴ በትንሽ ነገር ረክተው መኖር ይኖርባቸው ይሆናል፤ ሆኖም ይህ መሥዋዕትነት ከፊታቸው ከተዘረጉት በረከቶች አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። በዚህ መንገድ፣ ‘ተስፋቸውን በእግዚአብሔር ላይ ማድረጋቸውን’ እንዲሁም ይሖዋ ወደፊት ለታማኝ አገልጋዮቹ የልባቸውን መሻት እንደሚሰጣቸው ያላቸውን ሙሉ እምነት ያሳያሉ። (መዝሙር 37:4, 34 የ1980 ትርጉም) ከዚህ የተነሳ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ደስተኞች ናቸው። “የጻድቃን አለኝታ ደስታ ነው፤ የክፉዎች ተስፋ ግን ከንቱ ሆኖ ይቀራል።”—ምሳሌ 10:28
18, 19. (ሀ) ይሖዋ ምን ዓይነት ፍቅራዊ ዋስትና ሰጥቶናል? (ለ) ይሖዋን ‘በቀኛችን’ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
18 አንድ ትንሽ ልጅ የአባቱን እጅ ይዞ ሲራመድ የደኅንነት ስሜት ይሰማዋል። እኛም በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ጋር ስንሄድ ተመሳሳይ የሆነ ስሜት ይኖረናል። ይሖዋ እስራኤላውያንን “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ . . . እረዳሃለሁ፤ . . . እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ‘አትፍራ፤ እረዳሃለሁ’ ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁ” ብሏቸው ነበር።—ኢሳይያስ 41:10, 13
19 ይሖዋ እጅህን ይዞ ሲሄድ ይታይህ። ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ሥዕላዊ መግለጫ ነው! ዳዊት “እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አድርጌአለሁ፤ እርሱ በቀኜ ስላለ አልናወጥም” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 16:8) ይሖዋን ምንጊዜም ‘በቀኛችን’ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ቢያንስ በሁለት መንገዶች ይህን ማድረግ እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጃ በየትኛውም የሕይወታችን ዘርፍ በቃሉ መመራት ይኖርብናል፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ይሖዋ ከፊታችን በዘረጋልን አስደናቂ ሽልማት ላይ ማተኮር ይገባናል። መዝሙራዊው አሳፍ እንደሚከተለው ሲል ዘምሯል:- “ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፤ አንተም ቀኝ እጄን ይዘኸኛል። በምክርህ መራኸኝ፤ ኋላም ወደ ክብር ታስገባኛለህ።” (መዝሙር 73:23, 24) እኛም እንዲህ የመሰለ ዋስትና ስላለን የወደፊቱን ጊዜ በትምክህት መጋፈጥ እንችላለን።
‘መዳናችሁ ቀርቧል’
20, 21. ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል?
20 እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር ይሖዋን በቀኛችን አድርገን መጓዛችን ይበልጥ አጣዳፊ ነው። በቅርቡ የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ የሰይጣን ዓለም እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያውቅ መከራ ይገጥመዋል። (ማቴዎስ 24:21) እምነት የለሽ ሰዎች በፍርሃት ይዋጣሉ። ይሁንና በእነዚያ ቀውጢ ጊዜያት ደፋር የይሖዋ አገልጋዮች በተስፋ ደስ ይላቸዋል! ኢየሱስ “እነዚህ ነገሮች መፈጸም ሲጀምሩ፣ መዳናችሁ ስለ ተቃረበ፣ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ወደ ላይ ቀና አድርጉ” ብሏል።—ሉቃስ 21:28
21 በመሆኑም አምላክ በሰጠን ተስፋ እንድንደሰት እንዲሁም ሰይጣን ትኩረታችንን ለመከፋፈል በሚሸርባቸው አሳሳች ዘዴዎች እንዳንታለል ወይም ለፈተና እንዳንዳረግ እንጠንቀቅ። ከዚሁ ጎን ለጎን እምነትን፣ ፍቅርንና አምላካዊ ፍርሃትን ለማዳበር የተቻለንን ሁሉ እንጣር። እንዲህ ማድረጋችን በየትኛውም ሁኔታ ሥር ይሖዋን ለመታዘዝና ዲያብሎስን ለመቃወም የሚያስችል ድፍረት ያስገኝልናል። (ያዕቆብ 4:7, 8) አዎን፣ “እግዚአብሔርን ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ፤ በርቱ [“ደፋሮች ሁኑ፣” NW]፤ ልባችሁም ይጽና።”—መዝሙር 31:24
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ተስፋ” የሚለው ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በአብዛኛው የሚያመለክተው ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚያገኙትን ሰማያዊ ሽልማት ቢሆንም፣ በዚህ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ ቃሉ የተሠራበት ተስፋን በጥቅሉ ለማመልከት ነው።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ኢየሱስ የነበረው ተስፋ ደፋር እንዲሆን የረዳው እንዴት ነው?
• እምነትና ተስፋ ምን ተዛማጅነት አላቸው?
• ተስፋና እምነት ለአንድ ክርስቲያን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር እንዲያስቀድም ድፍረት የሚሰጡት እንዴት ነው?
• ‘ተስፋቸውን በይሖዋ ላይ የሚያደርጉ’ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በትምክህት መጠባበቅ የሚችሉት ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣትም ሆንክ አረጋዊ በገነት ውስጥ ስትኖር በዓይነ ሕሊናህ ይታይሃል?