በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለጥንቱ የምህንድስና ጥበብ ቅርስ የሆኑት የሮማውያን መንገዶች

ለጥንቱ የምህንድስና ጥበብ ቅርስ የሆኑት የሮማውያን መንገዶች

ለጥንቱ የምህንድስና ጥበብ ቅርስ የሆኑት የሮማውያን መንገዶች

‘ከሮማውያን ቅርሶች መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የትኛው ነው?’ ተብለህ ብትጠየቅ ‘በአሁኑ ጊዜ ሮም ውስጥ ፍርስራሹ የሚታየው ኮሎሲየም ነው’ በማለት ትመልሳለህ? ረጅም ዘመን ያስቆጠሩትን አሊያም ደግሞ በሰው ልጅ ታሪክ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩትን የሮማውያን ግንባታዎች ግምት ውስጥ የምናስገባ ከሆነ የሮማውያንን መንገዶች መዘንጋት አይኖርብንም።

በሮማውያን መንገዶች ላይ የሚጓጓዙት ወታደሮችና የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች ብቻ አልነበሩም። የኤፒግራፊ (የጥንታዊ ጽሑፎች ጥናት) ባለሞያ የሆኑት ሮሞሎ ስታኮሊ እንዳሉት ከሆነ እነዚህ መንገዶች ክርስትናን ጨምሮ የተለያዩ “አስተሳሰቦች፣ የጥበብ ግኝቶች፣ ፍልስፍናዎችና ሃይማኖታዊ ወጎች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆነዋል።”

በጥንት ዘመን የሮማውያን መንገዶች እንደ ታሪካዊ ቅርስ ይታዩ ነበር። ሮማውያን ለብዙ መቶ ዘመናት ሲያከናውኑት በቆዩት በዚህ የግንባታ ሥራ ከ80,000 ኪሎ ሜትር በላይ የሆነ ጠቃሚ የመገናኛ መሥመር መዘርጋት የቻሉ ሲሆን ይህም በዛሬው ጊዜ ከ30 የሚበልጡ አገሮችን ይሸፍናል።

ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የመጀመሪያው ቪያ ፐብሊካ ማለትም አውራ ጎዳና፣ ቪያ አፒያ ወይም አፒያን ዌይ ነበር። የመንገዶች ንግሥት በመባል የሚታወቀው ይህ አውራ ጎዳና ሮምን የምሥራቁ ዓለም መግቢያ ከነበረችው ብሩንዲዚየም (የአሁኗ ብሪንዲዚ) የተባለች የወደብ ከተማ ጋር ያገናኛል። መንገዱ የተሰየመው በ312 ከክርስቶስ ልደት በፊት መንገዱን ማሠራት በጀመረው አፒየስ ክላውዲየስ ሲከስ የተባለ ሮማዊ ባለ ሥልጣን ስም ነው። ከዚህም በላይ ሮም ቪያ ሳላሪያ እና ቪያ ፍላሚኒያ በሚባሉ መንገዶች ስትገለገል ቆይታለች። እነዚህ መንገዶች በስተ ምሥራቅ በኩል ወደ አድሪያቲክ ባሕር የተዘረጉ ሲሆኑ ከባልካን አገሮች እንዲሁም ከራየንና ከዳንዩብ አካባቢዎች ጋር ለመገናኘት አስችለዋል። ቪያ ኦሬሊያ በሰሜን በኩል ወደ ጎውልና ወደ አይቢሪያን ባሕረ ገብ መሬት የሚያቀና ሲሆን ቪያ ኦስቴንሲስ ደግሞ ሮማውያን ከአፍሪካ ጋር ለሚያደርጉት ግንኙነት ተመራጭ ወደባቸው ወደሆነው ወደ ኦስቲያ ያመራል።

የሮማውያን ታላቅ የግንባታ ፕሮጀክት

ሮም፣ ነዋሪዎቿ አዳዲስ መንገዶችን መገንባት ከመጀመራቸው በፊትም እንኳ መንገዶች ያስፈልጓት ነበር። ይህቺ ከተማ የተቆረቆረችው በጊዜው የነበሩት ጥንታዊ መንገዶች በሙሉ በሚገናኙበት የታይበርን ወንዝ ማቋረጥ በሚቻልበት በወንዙ የታችኛው ክፍል ላይ ነበር። አንዳንድ ጥንታዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሮማውያን እነዚህን ጥንታዊ መንገዶች አሻሽለው ለመሥራት የካርቴጅ ሰዎች የሚጠቀሙበትን ዘዴ ኮርጀዋል። ይሁንና ለሮማውያን ጥበብ ፈር ቀዳጅ የሆኑት የኢትሩሪያ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ሰዎች የሠሯቸውን መንገዶች ፍርስራሽ አሁንም ማግኘት ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ፣ ከሮማውያን ዘመን በፊትም ለብዙ ጊዜ አገልግሎት የሰጡ ጥርጊያ መንገዶች ይገኙ ነበር። እነዚህ መንገዶች እንስሳትን ከአንዱ የግጦሽ ስፍራ ወደ ሌላው ለማመላለስ የሚያገለግሉ ሳይሆኑ አይቀሩም። ሆኖም መንገዶቹ በበጋ ወራት በአቧራ ይሸፈኑ፣ በክረምት ደግሞ ይጨቀዩ ስለነበር ለጉዞ ምቹ አልነበሩም። ሮማውያን መንገዶቻቸውን የሠሩት በእነዚህ ጥርጊያ መንገዶች ላይ ነበር።

የሮማውያን መንገዶች በጥንቃቄ የተነደፉና ጠንካራ፣ ለብዙ ጊዜ የሚያገለግሉና ማራኪ እንዲሆኑ ተደርገው የተገነቡ ናቸው። መንገዶቹ የሚነሱበትን ቦታ ከመድረሻቸው ጋር ለማገናኘት አጭር በሆነው አቋራጭ ይጠቀሙ ስለነበር፣ ብዙዎቹ መንገዶች የተሠሩት ጠመዝማዛ ከመሆን ይልቅ ቀጥ ተደርገው ነው። ያም ሆኖ አብዛኞቹ መንገዶች የመልክአ ምድሩን አቀማመጥ ተከትለው መሠራታቸው አልቀረም። ሮማውያን መሃንዲሶች አቀበታማና ተራራማ በሆኑ አካባቢዎች ላይ አመቺ ከሆነላቸው መንገዶቹን ፀሐይ በሚያገኘው የተራራው ክፍል አጋማሽ ላይ ይሠሯቸዋል። ይህ ደግሞ ተጓዦችን በመጥፎ የአየር ሁኔታ ምክንያት ሊገጥሟቸው ከሚችሉ ችግሮች ይጠብቃቸዋል።

ሮማውያን መንገዶችን የሚሠሩት እንዴት ነበር? ይህን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ቢሰነዘሩም ቀጥሎ የተገለጹት ሐሳቦች በአርኪኦሎጂ የተገኙ መረጃዎችን መሠረት ያደረጉ ናቸው።

ሮማውያኑ በቅድሚያ መንገዱ የሚያልፍባቸውን ቦታዎች ይወስናሉ። ይህ ሥራ በዘመኑ ለነበሩ መንገድ ቀያሾች ይሰጣል። ከዚያም ወገብ የሚቆርጠውን የቁፋሮ ሥራ፣ ሮማውያን ወታደሮች ወይም የቀን ሠራተኞች አሊያም ደግሞ በባርነት የተያዙ ሰዎች እንዲሠሩት ይደረጋል። በዚህ ጊዜ ሁለት ትይዩ ቦዮች ይቆፈራሉ። በሁለቱ ቦዮች መካከል አነሰ ቢባል 2.4 ሜትር ርቀት እንዲኖር የሚደረግ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ግን 4 ሜትር፣ አንዳንዴም ኩርባ ላይ ከዚህ የበለጠ ስፋት ያለው ቦታ ይኖራል። ሙሉ በሙሉ ተሠርቶ የተጠናቀቀ መንገድ በሁለቱም ጎን ያሉትን የእግረኛ መሄጃዎች ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ሜትር ስፋት ይኖረዋል። ከዚህ በኋላ በሁለቱ ቦዮች መካከል ያለው መሬት ተቆፍሮ አፈሩ ይወጣል። ቁፋሮው ከታች እስካለው የመሬቱ ድንጋያማ ክፍል ድረስ ይቀጥላል፤ ከዚያም የተቆፈረው መሬት ሦስት ወይም አራት ዓይነት ድንጋዮችን አንዱን ባንዱ ላይ በመደራረብ ይሞላል። መጀመሪያ ላይ የሚሞላው ትላልቅ ድንጋይ ወይም የድንጋይ አሊያም የሸክላ ስብርባሪ ሳይሆን አይቀርም። ቀጥሎም በሲሚንቶ የተያያዘ ጠጠር ወይም ጠፍጣፋ ድንጋይ ይነጠፋል። በመጨረሻም ኮረትና ደቃቅ ድንጋይ በላዩ ላይ ፈሶበት በደንብ ይደለደላል።

ሮማውያን የሠሯቸው አንዳንዶቹ መንገዶች የላይኛው ንጣፋቸው የተጠቀጠቀ ጠጠር ብቻ ነው። ያም ሆኖ አብዛኞቹ በድንጋይ የተነጠፉ መንገዶች አሠራር በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች እጅግ ተደናቂ ያደርጋቸዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ መንገዶች በአካባቢው ከሚገኝ አለት ተጠርበው የተሠሩ ሰፋፊ ድንጋዮች ተነጥፈውባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ መንገዶቹ ከመሃል ከፍ ብለው ጎንና ጎናቸው ዝቅ እንዲል በመደረጉ በዝናብ ጊዜ ውኃው መንገዱ ላይ ከማቆር ይልቅ ጠርዝ ላይ ወዳሉት ቦዮች ይገባል። ይህ ዓይነቱ አሠራር ለመንገዶቹ ጥንካሬ የሰጣቸው ሲሆን አንዳንዶቹም እስከ ዘመናችን ድረስ መዝለቅ ችለዋል።

አፒያን ዌይ ከተሠራ ከ900 ዓመታት በኋላ ባይዛንታይናዊው ታሪክ ጸሐፊ ፕሮኮፒየስ ይህን መንገድ “ድንቅ” በማለት ጠርቶታል። ፕሮኮፒየስ በመንገዱ ላይ የነበሩትን የድንጋይ ንጣፎች አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “ረጅም ዕድሜ ያሳለፉ እንዲሁም ይህ ነው የማይባል ብዛት ያላቸው ሰረገላዎችና ሌሎች ተሽከርካሪዎች በየቀኑ ሲመላለሱባቸው የቆዩ ቢሆኑም አልተፈነቃቀሉም እንዲሁም አባጣ ጎባጣ አልሆኑም።”

እነዚህ መንገዶች እንደ ወንዝ የመሰሉ የተፈጥሮ መሰናክሎችን የሚያልፉት እንዴት ነው? አንዱ ጥሩ ዘዴ ድልድዮችን መጠቀም ነበር። በጊዜው ከተሠሩት ድልድዮች መካከል አንዳንዶቹ በዘመናችንም ጭምር የሚገኙ ሲሆን ሮማውያን ላቅ ያለ ችሎታ እንደነበራቸው ይመሠክራሉ። በሮማውያን መንገዶች ላይ ያሉት ዋሻዎች እምብዛም የማይታወቁ ቢሆኑም በዘመኑ ከነበረው ሥልጣኔ አንጻር ሲታይ መንገዶቹን ከመሥራት ይልቅ እነዚህን ዋሻዎች መፈልፈሉ ይበልጥ ተፈታታኝ ነበር። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “የሮማውያን ምህንድስና . . . ለብዙ መቶ ዘመናት አቻ ያልተገኘላቸውን ውጤቶች አስገኝቷል” ብሏል። ለዚህም ቪያ ፍላሚኒያ የተባለው ጎዳና በውስጡ የሚያልፈው በፉርሎ የሚገኝ ዋሻ ምሳሌ ይሆነናል። በ78 ከክርስቶስ ልደት በኋላ፣ ጥንቃቄ በተሞላበት ንድፍ የተገነባው ይህ ዋሻ 40 ሜትር ርዝመት፣ 5 ሜትር ስፋትና 5 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን ከአለት ተፈልፍሎ የተሠራ ነው። በወቅቱ ከነበሩት የግንባታ መሣሪያዎች አንጻር ይህ በጣም አስደናቂ ሥራ ነው። እንዲህ ያለው መንገድ የሰው ልጆች ካከናወኗቸው በጣም አስቸጋሪ ሥራዎች መካከል አንዱ ነው።

ተጓዦችና የአመለካከት መስፋፋት

በሮማውያን መንገዶች ላይ ወታደሮች፣ ነጋዴዎች፣ ሰባኪዎች፣ አገር ጎብኚዎች፣ ተዋናዮችና ግላዲያተሮች ይጓዙ ነበር። እግረኞች በእነዚህ መንገዶች ላይ በቀን ከ25 እስከ 30 ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ። መንገደኞች ምን ያህል ርቀት እንደተጓዙ ማወቅ ከፈለጉ አልፎ አልፎ በመንገዱ ዳርና ዳር የተቀመጡትን የርቀት ጠቋሚዎች መመልከት ይችላሉ። እነዚህ ርቀት ጠቋሚዎች ከድንጋይ የተሠሩና የተለያየ ቅርጽ ያላቸው ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ሞላላ ቅርጽ ያላቸው ሲሆኑ በየአንድ የሮማውያን ማይል ማለትም በየ1,480 ሜትር ርቀት ላይ ተተክለው ይገኛሉ። በመንገዶቹ ላይ ተጓዦች ፈረሶች የሚቀይሩባቸው፣ ምግብ የሚገዙባቸውና አንዳንዴም ሌሊቱን የሚያሳልፉባቸው ማረፊያ ቦታዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ ማረፊያዎች መካከል አንዳንዶቹ ቀስ በቀስ አነስተኛ ከተሞች ሆነዋል።

ከክርስትና መወለድ ጥቂት ቀደም ብሎ አውግስጦስ ቄሣር መንገዶቹን ማደስ ጀመረ። ይህንንም ለማድረግ ሲል አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ መንገዶችን ሁኔታ የሚከታተሉ ባለ ሥልጣኖችን በየቦታው ይሾም ነበር። አውግስጦስ ቄሣር በሮማ አደባባይ ሚልያሪዩም ኦሪየም ወይም ወርቃማው ርቀት ጠቋሚ የሚባል ዓምድ አቁሞ እንደነበር ይነገራል። በወርቅ በተለበጡ የነሐስ ፊደሎች የተጻፈው ይህ ርቀት መጠቆሚያ የተተከለበት ቦታ ሮማውያን በጣሊያን ውስጥ የሠሯቸው የሁሉም መንገዶች መድረሻ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። “ኦል ሮድስ ሊድ ቱ ሮም” ማለትም “መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም ያመራሉ” የሚለው አባባል የተገኘውም ከዚህ ነው። ከዚህም ባሻገር አውግስጦስ በመላው የሮም ግዛት የተዘረጉትን መንገዶች የሚያሳዩ ካርታዎች አሠርቶ ነበር። በዚያን ጊዜ የነበሩት የመገናኛ መሥመሮች የሕዝቡን ፍላጎት በበቂ ሁኔታ የሚያሟሉና ደረጃቸውን ጠብቀው የተሠሩ እንደነበሩ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።

አንዳንድ የጥንት አገር ጎብኚዎች ጉዟቸውን ይበልጥ ቀላል ለማድረግ ታስበው በተዘጋጁ በጽሑፍ የሠፈሩ የጉዞ መመሪያዎች ይጠቀሙ ነበር። እነዚህ የጉዞ መመሪያዎች በመንገዱ ላይ ባሉት ማረፊያ ስፍራዎች መካከል ያለውን ርቀትና በእነዚህ ማረፊያዎች ውስጥ ምን ዓይነት አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚቻል የሚገልጹ ዝርዝር መረጃዎችን ጭምር ይይዛሉ። ያም ሆኖ እነዚህ የጉዞ መመሪያዎች ዋጋቸው ውድ ስለነበር ማንኛውም ሰው የሚያገኛቸው አልነበሩም።

የሆነ ሆኖ ክርስቲያን ወንጌላውያን በርካታ የረጅም ርቀት ጉዞዎችን ለማድረግ ማቀድና ይህንንም ከግብ ማድረስ ችለዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩ ብዙ ሰዎች ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ ወደ ምሥራቅ ሲሄድ ብዙውን ጊዜ ነፋስ ስለሚኖር ለመጓዝ የሚመርጠው በመርከብ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 14:25, 26፤ 20:3፤ 21:1-3) በሜድትራንያን ባሕር ላይ በበጋ ወራት ከምዕራብ የሚመጣ ነፋስ ወደ ምሥራቅ ይነፍሳል። ሆኖም ጳውሎስ ወደ ምዕራብ ሲጓዝ የሮማውያንን መንገዶች ተጠቅሞ በየብስ መሄድን ይመርጥ ነበር። ጳውሎስ ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ሚስዮናዊ ጉዞውን ያደራጀው ይህን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 15:36-41፤ 16:6-8፤ 17:1, 10፤ 18:22, 23፤ 19:1) a በ59 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ፣ ጳውሎስ በአፒያን ዌይ ተጠቅሞ ወደ ሮም በመሄድ፣ ከሮም በስተ ደቡብ ምሥራቅ 74 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ሕዝብ የሚበዛበት የአፒ አደባባይ ወይም አፍዩስ ፋሩስ ላይ ከእምነት ባልደረቦቹ ጋር ተገናኝቷል። ሌሎች የእምነት አጋሮቹ ደግሞ ከዚህ ሥፍራ 14 ኪሎ ሜትር ወደ ሮም ቀረብ ብሎ በሚገኝ ሦስት ማደሪያ በተባለ ማረፊያ ቦታ ላይ ይጠብቁት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 28:13-15) በ60 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ጳውሎስ ምሥራቹ በዘመኑ በነበረው “ዓለም ዙሪያ” እንደተሰበከ ተናግሯል። (ቈላስይስ 1:6, 23) በዚያን ጊዜ የነበሩት መንገዶች ለዚህ ውጤት የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል።

በመሆኑም የሮማውያን መንገዶች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማሰራጨት ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ እንዲሁም አስደናቂና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ ቅርሶች መሆናቸውን አስመስክረዋል።—ማቴዎስ 24:14

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ‘መልካሚቱን ምድር ተመልከት’ በተባለው ብሮሹር ገጽ 33 ላይ ያለውን ካርታ ተመልከት።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሮማውያን ርቀት ጠቋሚ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥንታዊቷ ኦስቲያ፣ ጣሊያን የሚገኝ መንገድ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥንታዊ ሰረገላዎች ያጎደጎዱት መንገድ፣ ኦስትሪያ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአንድ የሮማውያን መንገድ የተወሰነው ክፍል ከርቀት መጠቆሚያዎቹ ጋር፣ ዮርዳኖስ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሮም ጫፍ ላይ የሚገኘው ቪያ አፒያ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሮም ወጣ ብሎ በቪያ አፒያ በኩል ያለ የመቃብር ፍርስራሽ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማርሽ አካባቢ የሚገኘውና ቪያ ፍላሚኒያ የተባለው መንገድ በውስጡ የሚያልፈው የፉርሎ ዋሻ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቪያ ኤሚልያ ላይ የሚገኘው የጢባርዮስ ድልድይ፣ ሪመኒ፣ ጣሊያን

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ ሕዝብ በሚበዛበት በአፒ አደባባይ ወይም በአፍዩስ ፋሩስ ከእምነት ባልደረቦቹ ጋር ተገናኝቷል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

በስተ ግራ ጫፍ ላይ፣ ኦስቲያ:- ©danilo donadoni/Marka/age fotostock; በስተ ቀኝ ጫፍ ላይ፣ ርቀት ጠቋሚዎች ያሉት መንገድ:- Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.