በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጊኒ መንፈሳዊ ሀብት ማግኘት

በጊኒ መንፈሳዊ ሀብት ማግኘት

በጊኒ መንፈሳዊ ሀብት ማግኘት

ለበርካታ ዘመናት አሳሾች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ሀብት ሲፈልጉ ኖረዋል። ይህንንም ለማድረግ በምዕራብ አፍሪካ ወደምትገኘው ጊኒ የሄዱ ደፋር ሰዎች ሁለት እጅግ የተለያዩ ሀብቶችን ማለትም ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብትን አግኝተዋል። አገሪቷ በአልማዝ፣ በወርቅ፣ በብረት ማዕድንና ጥራት ባለው ቦክሳይት (አሉሚኒየም የሚወጣበት ንጥረ ነገር) የበለጸገች ስትሆን ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ ይኖርባታል።

በአገሪቱ ውስጥ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች በብዛት ባይገኙም ሕዝቡ ለአምልኮ ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ ብዙዎቹ መንፈሳዊ ሀብትን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። ይህ ሀብት ምን ያመለክታል? በሐጌ 2:7 ላይ ‘የሕዝቦች ሀብት’ የተባሉትን የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች የሚያመለክት ነው።

መንፈሳዊ ሀብት

የተደበቀ ሀብት ለማግኘት ጥልቀት ያለው ቁፋሮ ማድረግ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። በተመሳሳይም በክርስቲያናዊ አገልግሎት መንፈሳዊ ሀብት ለማግኘት ትጋት የታከለበት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በጊኒ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ የጀመረው በ1950ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ በመካከለኛው የአገሪቱ ክፍል ሲሆን እስከ 1960ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ምሥራቹ በዋና ከተማዋ በኮናክሪ አልተሰበከም ነበር። በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ በአጠቃላይ 21 የሚያክሉ ጉባኤዎችና ቡድኖች እንዲሁም ወደ 900 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ።

በ1987 ሚስዮናውያን ወደ አገሪቱ የገቡ ሲሆን በኮናክሪ ከሚገኘው ብቸኛ ጉባኤ ጋር ያገለግሉ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በዋናው ከተማም ሆነ በመካከለኛው የአገሪቱ ክፍል ከ20 በላይ የሚሆኑ ሚስዮናውያን ይገኛሉ። እነዚህ ሚስዮናውያን በቅንዓት ጉባኤዎቹን ከማበረታታቸውም ሌላ በአካባቢው ከሚገኙ ወንድሞች ጋር ያገለግላሉ።

በኮናክሪ የሚኖረው ሉክ፣ ኤልበር የተባለን ወጣት ሐኪም መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናቱ ደስታ አስገኝቶለታል። ኤልበር ወደተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት በመሄድ እውነተኛውን ሃይማኖት ለማግኘት ጥረት ከማድረጉም ሌላ በመናፍስታዊ ድርጊቶች ይካፈል የነበረ ሰው ነው። አንድ መናፍስት ጠሪ መልካም ዕድል ያስገኝልሃል ብሎ የሰጠውን ቀለበት ያደርግ ነበር። ኤልበር እውነተኛውን ሃይማኖት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ስላልተሳካለት በጣም ተበሳጭቶ ቀለበቱን አውጥቶ በመጣል “አምላክ፣ በእርግጥ ካለህ አንተን እንዳውቅህና እንዳገለግልህ አድርግ። አለበለዚያ ሕይወቴን በፈለግኩት መንገድ እመራለሁ” በማለት ጸለየ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኤልበር እህቱን ለመጠየቅ ሲሄድ የእህቱ ልጅ ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ሰማ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኤልበር፣ ከሉክ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ዝግጅት ተደረገ።

ሉክ ምንም ቅር ሳይለው በየሳምንቱ ደርሶ መልስ ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ እየተጓዘ ያስጠናው ነበር። የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የሆነው ኤልበር፣ ሉክ የትምህርት ደረጃው ዝቅተኛ ቢሆንም በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለውና የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱን በተግባር ላይ እንደሚያውል ሲመለከት በጥልቅ ተነካ። ኤልበር ለሰው ልጆች ችግሮች ተጠያቂው አምላክ እንዳልሆነ እንዲሁም የይሖዋ ዓላማ ሁሉንም ዓይነት መከራ አስወግዶ ምድርን ወደ ገነትነት መለወጥ እንደሆነ ሲማር ምን ያህል ተደስቶ ይሆን? (መዝሙር 37:9-11) ኤልበር በመጽሐፍ ቅዱስ እውነትና በጉባኤ ውስጥ በተመለከታቸው ግሩም ባሕርያት ልቡ ሊነካ ችሏል።

ይሁን እንጂ አልማዝ እንዲያንጸባርቅ ከተፈለገ ጥሩ ችሎታ ባለው ባለሙያ በጥንቃቄ መቆረጥ እንዳለበት ሁሉ ኤልበርም ሕይወቱን ከአምላክ የጽድቅ አቋም ጋር ለማስማማት እንዲችል በርካታ ዓለማዊ ባሕርያትንና ድርጊቶችን ማስወገድ ነበረበት። ወደ መናፍስት ጠሪ መሄዱን፣ የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ መውሰዱንና ቁማር መጫወቱን አቆመ። ኤልበር ሲጋራ ማጨሱን ማቆም እጅግ አዳጋች ቢሆንበትም ወደ ይሖዋ ያለማቋረጥ በመጸለይ ሊሳካለት ችሏል። ከስድስት ወር በኋላ ትዳሩን ሕጋዊ አደረገ። ባለቤቱም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። አሁን ሁለቱም የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች ናቸው።

በጊኒ ከሚገኙት መንፈሳዊ አልማዞች መካከል አንዱ ሜርታን ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረው በ15 ዓመቱ በጌኬዱ ከተማ ነበር። የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑት ወላጆቹ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እንዳይገኝ ተቃወሙት። የሜርታንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አወደሙበት፤ እንዲሁም ሜርታንን ደብድበው ከቤት አባረሩት። ካርቦን የተባለው ንጥረ ነገር ለኃይለኛ ግፊት ሲጋለጥ አልማዝ እንደሚፈጠር ሁሉ ሜርታን የደረሰበት ስደትም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለውን ፍቅር አጠንክሮለታል። ከጊዜ በኋላ የወላጆቹ አመለካከት በመቀየሩ ወደ ቤት ተመለሰ። ወላጆቹ እንዲለወጡ ያደረጋቸው ምን ነበር? በሜርታንና በታናናሾቹ መካከል ያለው የባሕርይ ልዩነት ነበር፤ እህቱና ወንድሞቹ ዓመጸኞች ከመሆናቸውም ሌላ የጾታ ብልግና ይፈጽሙ ነበር። የሜርታን አባት ሜርታን የያዘው አዲስ እምነት ምን ያህል እንደጠቀመው በማየታቸው የጉባኤ አባላትን ወደ ቤት ይዞ እንዲመጣ ፈቀዱለት። የሜርታን እናትም፣ ወንድሞች ልጇን ለመርዳት ላደረጉት ጥረት ብዙ ጊዜ አመስግናቸዋለች። ሜርታን በ18 ዓመቱ የተጠመቀ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የመካፈል አጋጣሚ አገኘ፤ በአሁኑ ጊዜ ልዩ አቅኚ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

ከሌሎች አገሮች የመጡ መንፈሳዊ ሀብቶች

ጊኒ አብዛኛውን የተፈጥሮ ሀብቷን ወደ ውጭ አገሮች የምትልክ ቢሆንም አንዳንድ መንፈሳዊ ሀብቶቿ ግን ከሌላ አገር “የመጡ” ናቸው። ብዙ ሰዎች በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተሰድደው ወደ ጊኒ ይመጣሉ። አንዳንዶች ደግሞ ለረጅም ጊዜ ከዘለቁ በጭካኔ የተሞሉ ጦርነቶች ሸሽተው የመጡ ናቸው።

ኧርነስቲን ከካሜሮን ወደ ጊኒ ከመጣች 12 ዓመት ሆኗታል። ለብዙ ዓመታት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስታጠና ከመቆየቷም በላይ በስብሰባዎች ለይ የምትገኝ ቢሆንም አልተጠመቀችም። በ2003 የይሖዋ ምሥክሮች ባደረጉት የወረዳ ስብሰባ ላይ የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ሲከናወን ስታይ ዓይኖቿ እንባ አቀረሩ። የጥፋተኝነት ስሜት ስላደረባት ወደ ይሖዋ እንዲህ ስትል ጸለየች:- “51 ዓመት ሆኖኛል፤ ሆኖም ለአንተ ያደረግኩልህ ምንም መልካም ነገር የለም። አንተን ማገልገል እፈልጋለሁ።” ከዚያም ኧርነስቲን አምላክን በጸሎት በጠየቀችው መሠረት እርምጃ ወሰደች። ከእርሷ ጋር ይኖር ለነበረው ሰው፣ ግንኙነታቸው ቀጣይ እንዲሆን ከፈለገ በሕግ መጋባት እንዳለባቸው ነገረችው። እርሱም የተስማማ ሲሆን ኅዳር 2004 ስትጠመቅ የደስታ እንባ አነባች።

ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች ከላይቤሪያና ከሴራ ሊዮን ወደ ጊኒ የመጡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የይሖዋ አገልጋዮችም ይገኙበታል። ወንድሞች የስደተኞች ካምፕ እንደደረሱ አዘውትረው መሰብሰብ የሚችሉበትን ዝግጅት ያደረጉ ሲሆን የስብከቱን ሥራ ከማደራጀታቸውም በላይ የመንግሥት አዳራሽ ገነቡ። በስደተኛ ካምፑ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎችም ይሖዋን ማገልገል ጀምረዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ አይሳክ ይባላል። አይሳክ ከተጠመቀ በኋላ ቀድሞ ይሠራበት በነበረው በላይቤሪያ የሚገኝ ትልቅ ድርጅት ውስጥ የመሥራት አጋጣሚ አገኘ። ሆኖም አይሳክ በሌኔ በሚገኘው የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የዘወትር አቅኚ ሆኖ ማገልገልን መረጠ። እንዲህ ይላል:- “አሁን በጉባኤም ሆነ በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት አሠሪዬን ፈቃድ መጠየቅ አይኖርብኝም። ይሖዋን በነጻነት ማገልገል እችላለሁ።” በታኅሣሥ 2003 በካምፑ ከሚገኙት 30,000 ስደተኞች መካከል 150 የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ አደረጉ። የሚያስደስተው ስብሰባውን በምልክት ቋንቋ የተከታተሉ 9 መስማት የተሳናቸው ሰዎች ነበሩ፤ በስብሰባው ላይ በአጠቃላይ 591 ተሰብሳቢዎች የተገኙ ሲሆን አሥራ ሁለት ተጠማቂዎችም ነበሩ። ወንድሞች ይህን የመሰለ መንፈሳዊ ድግስ ለማዘጋጀት የተደረገውን ጥረት ከልብ አድንቀዋል።

‘የሕዝቦች ሀብት’ የተባሉት አስፈላጊውን ለውጥ አድርገዋል

ወርቅና አልማዝ የሚፈልጉ ሰዎች ማንኛውም መሰናክል አይበግራቸውም። በተመሳሳይም አዳዲሶች ይሖዋን ለማገልገል ብለው ማንኛውንም ዓይነት ችግር ለመቋቋም የሚያደርጉትን ጥረት መመልከቱ ልብ የሚነካ ነው። እስቲ የዜይኔብን ተሞክሮ እንመልከት።

ዜይኔብ በ13 ዓመቷ መኖሪያዋ ከሆነው ከአንድ የምዕራብ አፍሪካ አገር ወደ ጊኒ ተወስዳ በባርነት ለመኖር ተገደደች። ሃያ ዓመት ሲሆናት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ሰማች። ዜይኔብ የተማረችውን ነገር በተግባር ለማዋል በጣም ጓጉታ ነበር።

ለዜይኔብ አምልኮ ወደሚከናወንባቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መሄድ አስቸጋሪ ነበር። እሷ ግን ስብሰባዎቹን በጣም የምትወዳቸው ከመሆኑም በላይ ላለመቅረት ወስና ነበር። (ዕብራውያን 10:24, 25) ስብሰባ ስትሄድ መጽሐፎቿን ለመውሰድ እንድትችል ከቤት ውጭ ትደብቃቸው ነበር። ወደ እነዚህ መንፈሳዊ ስብሰባዎች በመሄዷ ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜያት “ባለቤቶቿ” በጭካኔ ደብድበዋታል።

ከጊዜ በኋላ ሁኔታዎች በመለወጣቸው ዜይኔብ ከባርነት ነጻ ወጣች። ወዲያውኑ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመረች ሲሆን ይህም በመንፈሳዊ ፈጣን እድገት እንድታደርግ አስችሏታል። ከፍተኛ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ ብታገኝም ክርስቲያናዊ መመሪያዎች ከሚሰጡባቸው ስብሰባዎች እንድትቀር ስለሚያደርጋት ሥራውን ሳትቀበለው ቀርታለች። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከመመዝገቧም ሌላ ያልተጠመቀች የመንግሥቱ አስፋፊ ሆነች፤ ከዚያም ራሷን ለይሖዋ መወሰኗን በውኃ ጥምቀት አሳየች። ከተጠመቀች በኋላ ወዲያውኑ ረዳት አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። ከስድስት ወራት በኋላ በዘወትር አቅኚነት ለማገልገል አመለከተች።

ለጥቂት ጊዜያት በስብሰባዎች ላይ የተገኘ አንድ ፍላጎት ያሳየ ሰው “በስብሰባዎች ላይ ስገኝ ድሃ እንደሆንኩ አይሰማኝም” በማለት ተናግሯል። ብዙ ሰዎች ትኩረታቸውን የሚስበው በጊኒ የሚገኘው ቁሳዊ ሀብት ብቻ ቢሆንም ይሖዋን የሚወዱ ግን መንፈሳዊ ሀብት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። አዎን፣ በአሁኑ ጊዜ ‘የሕዝቦች ሀብት ሁሉ’ የተባሉት ወደ ይሖዋ ንጹሕ አምልኮ እየመጡ ነው!

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጊኒ–2005

ከፍተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር:- 883

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች:- 1,710

የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ብዛት:- 3,255

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ጊኒ

ኮናክሪ

ሴራ ሊዮን

ላይቤሪያ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤልበር እና ሉክ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኮናክሪ የሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሜርታን

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኧርነስቲን

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዜይኔብ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

USAID