በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነትህ በአኗኗርህ በግልጽ ይታይ

እምነትህ በአኗኗርህ በግልጽ ይታይ

እምነትህ በአኗኗርህ በግልጽ ይታይ

“ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው።”—ያዕቆብ 2:17

1. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለእምነትም ሆነ ለሥራ ትኩረት የሰጡት ለምን ነበር?

 በጥቅሉ ሲታይ የጥንት ክርስቲያኖች እምነታቸውን በአኗኗራቸው በግልጽ ያሳዩ ነበር። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ [አትሁኑ]” በማለት ሁሉንም ክርስቲያኖች አሳስቧል። አክሎም “ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው” ብሏል። (ያዕቆብ 1:22፤ 2:26) ይህንን ደብዳቤ ከጻፈ ከ35 ዓመታት ገደማ በኋላም እንኳ በርካታ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ተገቢ በሆኑ ሥራዎች ማሳየታቸውን ቀጥለው ነበር። የሚያሳዝነው ግን አንዳንዶች እንዲህ አላደረጉም። ኢየሱስ በሰምርኔስ ያለውን ጉባኤ ቢያመሰግነውም በሰርዴስ ባለው ጉባኤ ውስጥ የሚገኙትን ብዙዎቹን ክርስቲያኖች “ሥራህን ዐውቃለሁ፤ በስም ሕያው ነህ፤ ነገር ግን ሞተሃል” ብሏቸዋል።—ራእይ 2:8-11፤ 3:1

2. ክርስቲያኖች እምነታቸውን በተመለከተ ራሳቸውን ምን ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል?

2 በዚህም የተነሳ ኢየሱስ የሰርዴስ ክርስቲያኖች ለክርስቲያናዊው እውነት የነበራቸውን የመጀመሪያ ፍቅር በሥራ እንዲገልጹና በመንፈሳዊ ንቁ እንዲሆኑ አበረታቷቸዋል፤ ይህ ምክር ለሰርዴስ ጉባኤ ብቻ ሳይሆን ከጊዜ በኋላ እነዚህን ቃላት ለሚያነቡ ሁሉ ይሠራል። (ራእይ 3:2, 3) እያንዳንዳችን እንዲህ በማለት ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን:- ‘እኔስ ስለ ተግባሬ ምን ማለት እችላለሁ? ከስብከቱ ሥራም ሆነ ከጉባኤ ስብሰባዎች ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ በሌላቸው ጉዳዮችም ጭምር የማደርጋቸው ነገሮች እምነቴን በሥራ ለማሳየት የምችለውን ያህል እየጣርኩ መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ?’ (ሉቃስ 16:10) ይህንን ማድረግ የምንችልባቸው የተለያዩ የሕይወት ዘርፎች ቢኖሩም በዚህ ርዕስ ሥር አንዱን ይኸውም ግብዣን እንመልከት፤ አብዛኛውን ጊዜ ከክርስቲያኖች ሠርግ ጋር በተያያዘ የሚዘጋጁት ግብዣዎችም በዚህ ርዕስ ውስጥ ይካተታሉ።

አነስ ያሉ ግብዣዎች

3. መጽሐፍ ቅዱስ ግብዣን በተመለከተ ምን ይላል?

3 አብዛኞቻችን ደስተኛ የሆኑ ክርስቲያኖች በሚያደርጉት ግብዣ ላይ ስንጠራ ደስ ይለናል። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹም ደስ እንዲላቸው የሚፈልግ “ደስተኛ አምላክ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) ሰሎሞን የሚከተለውን ሐቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲያሰፍር ያደረገውም እርሱ ነው:- “ለሰው፣ ከፀሓይ በታች ከመብላት፣ ከመጠጣትና ከመደሰት ሌላ የተሻለ ነገር ስለሌለ፣ በሕይወት ደስ መሰኘት መልካም ነው አልሁ።” (መክብብ 3:1, 4, 13፤ 8:15) ቤተሰብ አንድ ላይ ተሰባስቦ ሲመገብ ወይም እውነተኛ አምላኪዎች በሚሰባሰቡበት አነስተኛ ግብዣ ላይ እንዲህ ያለ ደስታ ይገኛል።—ኢዮብ 1:4, 5, 18፤ ሉቃስ 10:38-42፤ 14:12-14

4. ግብዣ የሚያዘጋጅ ግለሰብ ሊያስብበት የሚገባው ጉዳይ የትኛው ነው?

4 እንዲህ ያለ ግብዣ እያዘጋጀህ ከሆነና ሥነ ሥርዓቱን በተመለከተ ኃላፊነቱን የምትወስደው አንተ ከሆንክ ዝግጅቱን በጥንቃቄ ልታስብበት ይገባል። የጋበዝካቸው ወንድሞች ጥቂት በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ እንዲህ ማድረጉ ተገቢ ነው። (ሮሜ 12:13) ‘ከሰማይ በሆነችው ጥበብ’ ለመመራትና “ሁሉም በአግባብ” እንዲከናወን ለማድረግ እንደምትፈልግ ግልጽ ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:40፤ ያዕቆብ 3:17) ሐዋርያው ጳውሎስ “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። . . . መሰናክል አትሁኑ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 10:31, 32) በዚህ ረገድ ትኩረት ልናደርግባቸው የሚገቡ አንዳንድ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? እነዚህን ጉዳዮች አስቀድሞ መመርመሩ አንተም ሆንክ የጋበዝካቸው እንግዶች እምነታችሁን በተግባር እንድታሳዩ ይረዳችኋል።—ሮሜ 12:2

ግብዣው ምን ዓይነት ሊሆን ይችላል?

5. ጋባዡ የአልኮል መጠጥ ማቅረብን ወይም ሙዚቃን በተመለከተ በጥንቃቄ ማሰብ የሚገባው ለምንድን ነው?

5 በርካታ ጋባዦች የአልኮል መጠጥ ማቅረብ ያስፈልጋቸው እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን አስፈልጓቸዋል። ግብዣው አስደሳች እንዲሆን ለማድረግ የአልኮል መጠጥ የግድ አስፈላጊ አይደለም። ኢየሱስ በአንድ ወቅት ዳቦና ዓሣ በመባረክ ወደ እርሱ የመጡ ብዙ ሰዎችን እንደመገበ አስታውስ። ክርስቶስ በተአምራዊ መንገድ የወይን ጠጅ ማቅረብ እንደሚችልም እናውቃለን፤ ሆኖም ዘገባው እንዲህ እንዳደረገ አይገልጽም። (ማቴዎስ 14:14-21) አንተ ግን በግብዣህ ላይ የአልኮል መጠጥ ለማቅረብ ከወሰንክ በልክ አድርገው፤ የአልኮል መጠጥ የማይፈልጉ ሰዎችን ለማስደሰት ደግሞ ሌሎች አማራጮች እንዲኖሩ አድርግ። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 3, 8፤ 5:23፤ 1 ጴጥሮስ 4:3) ማንም ሰው ቢሆን ‘እንደ እባብ ሊናደፍ’ የሚችለውን የአልኮል መጠጥ እንዲወስድ ግፊት እንደተደረገበት እንዲሰማው ከማድረግ ተቆጠብ። (ምሳሌ 23:29-32) ሙዚቃን ወይም ዘፈንን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? በግብዣው ላይ ሙዚቃ የሚኖር ከሆነ የሙዚቃውን ምትም ሆነ ግጥሙን ግምት ውስጥ በማስገባት ዘፈኖቹን በጥንቃቄ እንደምትመርጥ ጥርጥር የለውም። (ቈላስይስ 3:8፤ ያዕቆብ 1:21) በርካታ ክርስቲያኖች የመንግሥቱን ጣዕመ ዜማዎች በማጫወት ወይም እነዚህን መዝሙሮች በአንድ ላይ በመዘመር አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ እንደሚቻል ተገንዝበዋል። (ኤፌሶን 5:19, 20) ከዚህም በላይ የሙዚቃው ድምፅ በጣም ከፍ ብሎ አስደሳች ጭውውት ለማድረግ እንቅፋት እንዳይፈጥር ወይም ጎረቤት እንዳይረብሽ መጠኑን መቆጣጠር ያስፈልጋል።—ማቴዎስ 7:12

6. አንድ ጋባዥ በግብዣው ላይ በሚደረገው ጭውውት ወይም በሌሎች ጉዳዮች ረገድ እምነቱ ሕያው እንደሆነ ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?

6 ክርስቲያኖች በግብዣ ላይ የተለያዩ ጉዳዮችን አንስተው ሊጫወቱ፣ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አንድ ጽሑፍ ሊያነቡ ወይም አስደሳች ተሞክሮዎችን ሊያወሩ ይችላሉ። ውይይቱ መሥመሩን ከሳተ ጋባዡ በዘዴ ሊያስተካክለው ይችላል። ከዚህም በላይ ጭውውቱን አንድ ሰው ብቻ እንዳይቆጣጠረው ንቁ ሆኖ መከታተል ይኖርበታል። ጋባዡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንደተፈጠረ ከተሰማው ጥበብ በተሞላበት መንገድ የውይይቱን አቅጣጫ ማስለወጥ ይችል ይሆናል፤ ምናልባትም ትናንሽ ልጆች እንዲናገሩ በማድረግ ወይም ተጋባዦቹ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ የሚገፋፋ ርዕስ በማንሳት ሌሎችም በጨዋታው እንዲካፈሉ ማድረግ ይችላል። ግብዣው እንደዚህ ዓይነት መልክ ሲኖረው ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ደስ ይላቸዋል። ግብዣውን ያዘጋጀኸው አንተ እንደመሆንህ መጠን ሁኔታዎችን በጥበብና በዘዴ የምትመራ ከሆነ ‘ምክንያታዊነትህ’ በቦታው በተገኙ ሁሉ ዘንድ ይታወቃል። (ፊልጵስዩስ 4:5 NW) ተጋባዦቹም በሁሉም የሕይወትህ ዘርፎች የሚታይ ሕያው እምነት እንዳለህ መገንዘብ ይችላሉ።

የጋብቻ ሥነ ሥርዓትና ድግሱ

7. ሠርግንና ከዚያ ጋር የተያያዙ ግብዣዎችን የማዘጋጀቱ ጉዳይ ሊታሰብበት የሚገባው ለምንድን ነው?

7 ደስታ ከሚያስገኙ ልዩ አጋጣሚዎች አንዱ የክርስቲያኖች ሠርግ ነው። ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን ጨምሮ የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች እንደዚህ ባሉት አስደሳች የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶችና ከዚያም ጋር ተያይዞ በሚዘጋጀው ግብዣ ላይ ተገኝተዋል። (ዘፍጥረት 29:21, 22፤ ዮሐንስ 2:1, 2) ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተሞክሮ እንደታየው ከሠርግ ጋር የተያያዙ ግብዣዎች፣ ማስተዋልና ክርስቲያናዊ ሚዛናዊነት እንዲንጸባረቅባቸው ከተፈለገ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲህ ያለው ግብዣ አንድ ክርስቲያን እምነቱን በተግባር ማሳየት እንዲችል አጋጣሚ የሚከፍትለት የሕይወት ዘርፍ ነው።

8, 9. በብዙ ሠርጎች ላይ የሚታዩት ነገሮች በ1 ዮሐንስ 2:16, 17 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?

8 የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች የማያውቁና ለእነዚህ መመሪያዎች ግድ የሌላቸው በርካታ ሰዎች፣ በሠርግ ወቅት ከተለመደው ወጣ ያለ ድርጊት መፈጸም እንደሚቻል ወይም ደግሞ እንዲህ ያለ ድርጊት ቢፈጸም ምንም ችግር እንደሌለው ይሰማቸዋል። አውሮፓ ውስጥ በሚታተም መጽሔት ላይ አንዲት ሚስት ሠርጓ “የነገሥታት ቤተሰብ” የሚያደርጉት ዓይነት እንደነበረ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- ‘እኛ በአራት ፈረሶች በሚጎተት ሠረገላ እንጓዝ የነበረ ሲሆን ከኋላችን 12 ሠረገላዎችና ሙዚቃ የሚጫወተውን ቡድን የያዘ አንድ ሌላ ሠረገላ ይከተሉን ነበር። ከዚያም በግሩም ሁኔታ የተሠራ ምግብ በላን፤ ሙዚቃውም ቢሆን አስደሳች ነበር፤ ሁሉም ነገር ፍጹም ድንቅ ነበር። ልክ እንደ ተመኘሁት በዕለቱ ንግሥት ሆኜ ነበር።’

9 የየአገሩ ባሕል የተለያየ ሊሆን ቢችልም ከላይ የተገለጸው አስተያየት ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው በማለት የጻፈውን ሐሳብ የሚያጠናክር ነው:- “በዓለም ያለው ሁሉ:- የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም።” የጎለመሱ ክርስቲያን ተጋቢዎች “የነገሥታት ቤተሰብ” የሚያደርጉት ዓይነት ሠርግና ድል ያለ ድግስ እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ይመስልሃል? ከዚህ በተቃራኒ ለሠርጋቸው እቅድ ሲያወጡ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” የሚለውን ምክር እንዳሰቡበት ማሳየት ይኖርባቸዋል።—1 ዮሐንስ 2:16, 17

10. (ሀ) ምክንያታዊነት የተንጸባረቀበት ሠርግ ለመደገስ እቅድ ማውጣት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ተጋቢዎቹ የሚጋብዟቸውን ሰዎች በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ የሚኖርባቸው እንዴት ነው?

10 ክርስቲያን ተጋቢዎች እውነታውን ግምት ውስጥ ማስገባትና ምክንያታዊ መሆን ይፈልጋሉ፤ በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳቸው ይችላል። የሠርጋቸው ቀን ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ቢሆንም ይህ ዕለት ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ሁለት ክርስቲያኖች የትዳር ሕይወታቸውን አንድ ብለው የሚጀምሩበት ቀን እንደሆነ ያውቃሉ። ትልቅ የሠርግ ድግስ የማዘጋጀት ግዴታ የለባቸውም። ግብዣ ለማዘጋጀት ከመረጡ ደግሞ ወጪውን ማስላትና ግብዣው ምን ዓይነት እንደሚሆን አስቀድመው ማሰብ ይፈልጋሉ። (ሉቃስ 14:28) እነዚህ ክርስቲያኖች ተጋብተው በሚኖሩበት ወቅት በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ባልየው ራስ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 5:22, 23) ስለዚህ የሠርጉን ግብዣ በተመለከተ በዋነኝነት ኃላፊነት የሚኖርበት ሙሽራው ነው። በእርግጥ በግብዣው ላይ ማንን መጥራት እንደሚፈልጉ ወይም አቅማቸው የሚፈቅደው ምን ያህል ሰዎችን ለመጋበዝ እንደሆነ ከእጮኛው ጋር ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይወያያል። ሙሽሮቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በሙሉ መጋበዝ አይችሉ ይሆናል፤ እንዲህ ማድረጉም አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። ስለዚህ አንዳንድ ውሳኔዎችን በሚያደርጉበት ጊዜ አቅማቸውን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። ተጋቢዎቹ አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በሠርጋቸው ላይ መጋበዝ ባይችሉ እነዚህ ክርስቲያኖች ሁኔታውን በመረዳት እንደማይቀየሟቸው እርግጠኞች ሊሆኑ ይገባል።—መክብብ 7:9 NW

የድግሱ አሳዳሪ

11. በሠርግ ግብዣ ላይ አሳዳሪው ምን ድርሻ ይኖረዋል?

11 ተጋቢዎቹ ሠርጋቸውን አስመልክተው ግብዣ ለማድረግ ከመረጡ ሥነ ሥርዓቱ ክብር የተላበሰ እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ ዓመታት ኢየሱስ በቃና ከተገኘበት ግብዣ ጋር በተያያዘ የተገለጸውን አንድ አሠራር ሲከተሉ ቆይተዋል። በቃናው ሠርግ ላይ “የድግሱ ኀላፊ” ወይም አሳዳሪ የነበረ ሲሆን ይህ ሰው ኃላፊነት የሚሰማው የእምነት ባልንጀራቸው ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐንስ 2:9, 10) በተመሳሳይም ብልህ የሆነ ሙሽራ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ይህንን ኃላፊነት የሚሸፍንለት በመንፈሳዊ የጎለመሰ አንድ ክርስቲያን ወንድም ሊመርጥ ይችላል። አሳዳሪው የሙሽራውን ፍላጎትና ምርጫ ካረጋገጠ በኋላ ከግብዣው በፊትም ሆነ በግብዣው ወቅት መከናወን ያለባቸውን ነገሮች ያደርጋል።

12. የአልኮል መጠጥን በተመለከተ ሙሽራው ሊያስብበት የሚገባው ጉዳይ ምንድን ነው?

12 በአንቀጽ 5 ላይ በተመለከትነው መሠረት አንዳንድ ተጋቢዎች በሠርጋቸው ላይ የአልኮል መጠጥ እንዳይቀርብ ይወስኑ ይሆናል፤ ይህም አንዳንዶች ከልክ በላይ ጠጥተው ሥነ ሥርዓቱን አስደሳችና ስኬታማ እንዳይሆን እንዳያደርጉት ጥበቃ ይሆናል። (ሮሜ 13:13፤ 1 ቆሮንቶስ 5:11) ሆኖም የአልኮል መጠጥ እንዲቀርብ ከወሰኑ ሙሽራው መጠጡ በልክ እንዲቀርብ ማድረግ ይኖርበታል። ኢየሱስ በቃና በተገኘበት ሠርግ ላይ ወይን የነበረ ከመሆኑም በላይ እርሱም ምርጥ ወይን እንዲቀርብ አስተዋጽኦ አድርጓል። የድግሱ ኃላፊ “ሰው ሁሉ በመጀመሪያ የሚያቀርበው ጥሩውን የወይን ጠጅ ነው፤ እንግዶቹም ብዙ ከጠጡ [“ከሰከሩ፣” የ1954 ትርጉም] በኋላ መናኛውን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቈይተሃል” ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዮሐንስ 2:10) ኢየሱስ ራሱ ስካርን ስለሚያወግዝ ሰዎች እንዲሰክሩ የሚያበረታታ ምንም ነገር እንዳላደረገ ግልጽ ነው። (ሉቃስ 12:45, 46) የድግሱ አሳዳሪ ስለ ወይን ጠጁ ጥራት የሰነዘረው ሐሳብ በሌሎች የሠርግ ድግሶች ላይ አንዳንድ ተጋባዦች መስከራቸውን እንደተመለከተ የሚያሳይ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 2:15፤ 1 ተሰሎንቄ 5:7) ስለዚህ ሙሽራውም ሆነ አሳዳሪ የመሆን ኃላፊነት የተሰጠው እምነት የሚጣልበት ክርስቲያን “በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና” የሚለውን ግልጽ መመሪያ በግብዣው ላይ የተገኙ ሁሉ ተግባራዊ ማድረጋቸውን መከታተል ይኖርባቸዋል።—ኤፌሶን 5:18፤ ምሳሌ 20:1፤ ሆሴዕ 4:11

13. ተጋቢዎቹ በሠርጉ ግብዣ ላይ ሙዚቃ እንዲኖር ካደረጉ ስለ የትኛው ጉዳይ ሊያስቡ ይገባል? ለምንስ?

13 እንደ ሌሎች ግብዣዎች ሁሉ በሠርግ ግብዣ ላይም ሙዚቃ የሚኖር ከሆነ የድምፁ መጠን ሰዎች መጨዋወት እንዳይችሉ የሚከለክል እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “ምሽቱ እየገፋ በሚሄድበት ጊዜ ጭውውቱ ሞቅ ሲል ወይም ጭፈራ ሲጀመር አንዳንድ ጊዜ የሙዚቃው ድምፅ ይጨመራል። ለስለስ ብሎ ይሰማ የነበረው ሙዚቃ በጣም ከመጮኹ የተነሳ መነጋገር አስቸጋሪ ይሆናል። የሠርግ ግብዣ አስደሳች ጭውውት ለማድረግ አጋጣሚ ይከፍታል። ከሙዚቃው ጩኸት የተነሳ እንዲህ ማድረግ ባይቻል ምንኛ ያሳዝናል!” ሙዚቀኞቹ ተቀጣሪ ይሁኑም አይሁኑ የሙዚቃውን ዓይነትና የድምፁን መጠን የመቆጣጠሩ ኃላፊነት ለእነርሱ መሰጠት አይኖርበትም፤ ከዚህ ይልቅ ሙሽራውና እርሱ የመረጠው አሳዳሪ ኃላፊነት ተሰምቷቸው አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ “በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” ሲል ጽፏል። (ቈላስይስ 3:17) ከሠርጉ ግብዣ በኋላ ተጋባዦቹ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በሠርጉ ላይ የነበረው ሙዚቃ ተጋቢዎቹ ሁሉን በኢየሱስ ስም እንዳደረጉት የሚያሳይ እንደነበረ ሊሰማቸው ይገባል።

14. አንድ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ጥሩ ትዝታ ጥሎ የሚያልፈው ዝግጅቱ ምን ዓይነት ከሆነ ነው?

14 አዎን፣ ጥሩ ዝግጅት የተደረገበት ሠርግ አስደሳች ትዝታ ይኖረዋል። በትዳር ውስጥ 30 ዓመታት ያሳለፉት አዳም እና ኢዲታ አንድን ሠርግ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “ክርስቲያናዊ የሆነ መንፈስ ነበረው። ይሖዋን የሚያወድሱ መዝሙሮች እንዲሁም ሌሎች ግሩም መዝናኛዎች ነበሩ። ዋናውን ቦታ የያዘው ጭፈራና ሙዚቃ አልነበረም። ሠርጉ አስደሳችና የሚያንጽ ከመሆኑም በላይ ሁሉም ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ነበር።” በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ሙሽራውና ሙሽራዋ እምነታቸውን በሥራ ለማሳየት ሊያደርጓቸው የሚችሏቸው ብዙ ነገሮች አሉ።

የሠርግ ስጦታዎች

15. የሠርግ ስጦታዎችን በተመለከተ የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል?

15 በብዙ አገሮች ውስጥ የሙሽሮቹ ወዳጆችና ዘመዶች ለአዲሶቹ ተጋቢዎች ስጦታ መስጠታቸው የተለመደ ነው። እንዲህ ለማድረግ ከወሰንክ ስለ የትኛው ጉዳይ ማሰብ ይኖርብሃል? ሐዋርያው ዮሐንስ ‘የኑሮ ትምክሕትን’ በተመለከተ የሰጠውን ሐሳብ አስታውስ። እንዲህ ያለውን ትምክሕት ወይም የይታይልኝ መንፈስ ያያያዘው እምነታቸውን በተግባር ከሚያሳዩ ክርስቲያኖች ጋር ሳይሆን ‘ከሚያልፈው ዓለም’ ጋር ነው። (1 ዮሐንስ 2:16, 17) ሁኔታውን ዮሐንስ በመንፈስ አነሳሽነት ከሰጠው ሐሳብ አንጻር ካየነው፣ አዲሶቹ ተጋቢዎች እያንዳንዱን ስጦታ ማን እንዳመጣላቸው በሕዝብ ፊት መናገር ይኖርባቸዋል? በመቄዶንያና በአካይያ የነበሩት ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም የነበሩትን ወንድሞቻቸውን ለመርዳት መዋጮ አድርገው ነበር፤ ሆኖም መዋጮውን ያደረጉት ሰዎች ስም በሕዝብ ፊት እንደተነገረ የሚጠቁም ሐሳብ አናገኝም። (ሮሜ 15:26) ስጦታ የሚሰጡ ብዙ ክርስቲያኖች አላስፈላጊ ትኩረት ወደ ራሳቸው ከመሳብ ይልቅ ስማቸው ባይጠቀስ ይመርጣሉ። በዚህ ረገድ ኢየሱስ በማቴዎስ 6:1-4 ላይ የሰጠውን ምክር ተመልከት።

16. አዲሶቹ ተጋቢዎች ከሠርግ ስጦታዎች ጋር በተያያዘ የሌሎችን ስሜት ላለመጉዳት ሊጠነቀቁ የሚችሉት እንዴት ነው?

16 እያንዳንዱን ስጦታ ማን እንዳመጣው መግለጹ ሰዎች የትኛው ስጦታ የተሻለ ወይም ውድ እንደሆነ እንዲያስቡ ስለሚያደርግ እርስ በርስ ‘የመጎነታተል [‘የመፎካከር፣’ NW]’ መንፈስ እንዲሰፍን ያደርጋል። አዲስ የተጋቡ አስተዋይ ክርስቲያኖች ስጦታዎቹን ያመጡላቸውን ሰዎች ስም በሕዝብ ፊት ከማስነገር ይቆጠባሉ። ስጦታዎቹን የሰጡትን ሰዎች ስም መናገር ይህን ማድረግ ያልቻሉ ተጋባዦችን ሊያሳቅቅ ይችላል። (ገላትያ 5:26፤ 6:10) እርግጥ ሙሽራውና ሙሽራይቱ ስጦታዎቹን ማን እንዳመጣላቸው ማወቃቸው ምንም ስህተት የለውም። ምናልባትም ከስጦታው ጋር የሚያያዘውን ካርድ በማንበብ የሰጪውን ማንነት ማወቅ ይችሉ ይሆናል፤ ሆኖም ይህ በሕዝብ ፊት መነበብ አያስፈልገውም። ሁላችንም የሠርግ ስጦታ በምንገዛበት፣ በምንሰጥበት እንዲሁም በምንቀበልበት ጊዜ እንደዚህ በመሳሰሉት የግል ጉዳዮች እንኳ እምነታችንን በሥራ መግለጽ የምንችልበት አጋጣሚ እናገኛለን። a

17. ክርስቲያኖች በእምነትና በሥራ ረገድ ምን ግብ ሊኖራቸው ይገባል?

17 እምነታችንን በተግባር መግለጽ በሥነ ምግባር ረገድ ንጹሕ ከመሆን፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት እንዲሁም በስብከቱ ሥራ ከመካፈል የበለጠ ነገርን እንደሚጨምር ግልጽ ነው። ሁላችንም በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ግልጽ ሆኖ የሚታይ ሕያው እምነት ይኑረን። አዎን፣ ከላይ የተወያየንባቸውን የሕይወት ዘርፎች ጨምሮ እምነታችንን “ፍጹም” በሆነ መንገድ በተግባር መግለጽ እንችላለን።—ራእይ 3:2

18. ከክርስቲያኖች ሠርግና ግብዣዎች ጋር በተያያዘ በዮሐንስ 13:17 ላይ ያለውን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

18 ኢየሱስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ግሩም ምሳሌ ከተወ በኋላ “እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 13:4-17) በዛሬው ጊዜ በምንኖርበት አካባቢ የሌሎችን፣ ለምሳሌ የእንግዶቻችንን እግር ማጠብ አስፈላጊ ወይም የተለመደ ነገር ላይሆን ይችላል። ሆኖም በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደተመለከትነው እምነታችንን ፍቅርና አሳቢነት በተንጸባረቀባቸው መንገዶች ማሳየት የምንችልባቸው ሌሎች የሕይወት ዘርፎች አሉ። ግብዣዎችና የክርስቲያኖች ሠርግም በዚህ ውስጥ ይካተታሉ። እኛ ራሳችን የምናገባ ብንሆን ወይም እምነታቸውን በሥራ ለማሳየት በሚፈልጉ ክርስቲያኖች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አሊያም ከዚያ በኋላ በሚደረገው አስደሳች የሆነ ክርስቲያናዊ ግብዣ ላይ ተጋብዘን ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማድረግ እንችላለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ሠርግንና ከሠርግ ጋር በተያያዘ የሚዘጋጀውን ግብዣ በተመለከተ “የሠርጋችሁ ቀን የሚያስደስትና የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግ” በሚለው በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ተጨማሪ ነጥቦች ማግኘት ይቻላል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ግብዣ በምታዘጋጅበት ወቅት፣

• በጋብቻው ሥነ ሥርዓት ወይም በግብዣው ላይ፣

• የሠርግ ስጦታ ስትሰጥ ወይም ስትቀበል

እምነትህን በተግባር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥቂት ሰዎችን በምትጋብዝበት ጊዜም እንኳ ‘ከሰማይ በሆነችው ጥበብ’ ተመራ