በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሠርጋችሁ ቀን የሚያስደስትና የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግ

የሠርጋችሁ ቀን የሚያስደስትና የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግ

የሠርጋችሁ ቀን የሚያስደስትና የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግ

ስድሳ ለሚያክሉ ዓመታት በጋብቻ የቆዩት ጎርደን እንዲህ ይላሉ:- “የሠርጌ ቀን በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከምሰጣቸውና በጣም ከተደሰትኩባቸው ቀናት አንዱ ነበር።” እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሠርጋቸው ቀን ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለምንድን ነው? ይህ ቀን በጥልቅ ለሚወዷቸው ሁለት አካላት ማለትም ለይሖዋ እና ለትዳር ጓደኛቸው ቅዱስ ቃል ኪዳን የሚገቡበት ዕለት ነው። (ማቴዎስ 22:37፤ ኤፌሶን 5:22-29) በእርግጥም ለማግባት የሚያስቡ ወንድና ሴት የሠርጋቸው ቀን አስደሳች እንዲሁም የጋብቻ መሥራች ለሆነው አምላክ ክብር የሚያመጣ እንዲሆን ይፈልጋሉ።—ዘፍጥረት 2:18-24፤ ማቴዎስ 19:5, 6

ሙሽራው ይህ አስደሳች ወቅት ይበልጥ ክብር ያለው እንዲሆን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? ሙሽራዋስ ለባሏና ለይሖዋ አክብሮት እንዳላት እንዴት ማሳየት ትችላለች? በዝግጅቱ ላይ የሚገኙ ተጋባዦችስ የሠርጉ ቀን ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መመልከት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከማስገኘቱም በላይ እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ማዋል አስደሳች በሆነው በዚህ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉትን ችግሮች ለመቀነስ ይረዳል።

ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ማን ነው?

በበርካታ አገሮች የማጋባት ሥልጣን የተሰጠው አንድ የይሖዋ ምሥክር የጋብቻው ውል ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲፈጸም ያደርግ ይሆናል። ጋብቻው በክብር መዝገብ ሹም ፊት መፈጸም ባለበት አገርም እንኳ ተጋቢዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር እንዲደረግላቸው ይፈልጉ ይሆናል። በዚህ ንግግር ላይ ሙሽራው አምላክ የሰጠውን የቤተሰብ ራስ የመሆን ኃላፊነት እንዲያስብበት ይጠየቃል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) በመሆኑም ሙሽራው በሠርጉ ወቅት ለሚከናወኑት ነገሮች ሁሉ ተቀዳሚውን ኃላፊነት ይወስዳል። እርግጥ ነው፣ ለጋብቻ ሥነ ሥርዓቱም ሆነ ከዚያ በኋላ ሊደረግ ለሚችለው ማንኛውም ግብዣ የሚያስፈልገው ዝግጅት ብዙውን ጊዜ አስቀድሞ ይደረጋል። እነዚህን ነገሮች ማዘጋጀት ለሙሽራው አስቸጋሪ የሚሆንበት ለምን ሊሆን ይችላል?

ለዚህ አንደኛው ምክንያት፣ ሙሽራዋ ወይም የሙሽራዋም ሆነ የሙሽራው ዘመዶች የሠርጉን ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ስለሚፈልጉ ይሆናል። ሮዶልፎ የተባለ በርካታ ሙሽሮችን ያጋባ ሰው እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “አንዳንድ ጊዜ፣ በተለይ ደግሞ ሠርጉን ለመደገስ ዘመዶች የሚረዱት ከሆነ ሙሽራው እነርሱ የሚያደርጉበትን ከፍተኛ ግፊት መቋቋም ይኖርበታል። በጋብቻ ሥነ ሥርዓቱም ሆነ በግብዣው ላይ መደረግ ያለባቸውን ነገሮች በተመለከተ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩ ይሆናል። ይህ ደግሞ በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ሙሽራው በሥነ ሥርዓቱ ላይ ያለውን ኃላፊነት መጋፋት ይሆናል።”

ከ35 ዓመታት በላይ የተለያዩ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶችን ያከናወነው ማክስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ሙሽራው የሠርጉን ዝግጅትም ሆነ በድግሱ ላይ መከናወን ያለበትን ነገር በተመለከተ ሐሳብ ለመስጠት አጋጣሚ እንደማያገኝና ቅድሚያውን በመውሰድ የምትወስነው ሙሽራዋ እንደሆነች መመልከት ችያለሁ።” በተመሳሳይም በርካታ ሙሽሮችን ያጋባው ዴቪድ እንዲህ በማለት ሐሳብ ይሰጣል:- “ሙሽራው አመራር የመስጠት ልምድ አይኖረው ይሆናል፤ እንዲሁም ብዙውን ጊዜ በሠርጉ ዝግጅት ላይ በቂ ተሳትፎ አያደርግም።” ታዲያ ሙሽራው ኃላፊነቱን በተሳካ መንገድ መወጣት የሚችለው እንዴት ነው?

በግልጽ መነጋገር ደስታን ይጨምራል

ሙሽራው በሠርጉ ዝግጅት ውስጥ ያለውን ኃላፊነት በተሳካ መንገድ ለመወጣት እንዲችል በግልጽ የመነጋገር ችሎታ ሊኖረው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 15:22) ሆኖም ሙሽራው የሠርጉን ዝግጅት አስመልክቶ ከሙሽራዋና ከቤተሰብ አባላት እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ግሩም ምክሮችን ሊሰጡ ከሚችሉ ሌሎች ሰዎች ጋር ቀደም ብሎ መወያየቱ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ሊቀንስ ይችላል።

በእርግጥም እጮኛሞቹ በመጀመሪያ ስለ ዝግጅቱም ሆነ ስለ ሌሎች ነገሮች መወያየታቸው አስፈላጊ ነው። ለምን? የተለያየ ባሕል ያላቸው ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት ደስታ የሞላበት የትዳር ሕይወት ያሳለፉት አይቫንና ባለቤቱ ዴልዊን የሰጧቸውን አንዳንድ ሐሳቦች እንመልከት። የሠርጋቸውን ዝግጅት በማስታወስ አይቫን እንዲህ ይላል:- “በሠርጌ ቀን ሁሉም ጓደኞቼ የሚገኙበት ድግስ እንደሚደረግ፣ የሠርግ ኬክ እንደሚኖር፣ ሙሽራዋ ነጭ ቬሎ እንደምትለብስና የመሳሰሉትን ዝግጅቶች ጨምሮ በግልጽ የተቀመጡ እቅዶች ነበሩኝ። በሌላ በኩል ዴልዊን የምትፈልገው አነስ ያለ፣ የሠርግ ኬክ የሌለበትና ያልተንዛዛ ሠርግ ነበር። እንዲያውም የሙሽራ ቀሚስ ከመልበስ ይልቅ ሌላ ልብስ ብትለብስ ትመርጥ ነበር።”

እነዚህ እጮኛሞች በመካከላቸው የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት ምን አደረጉ? ደግነትና ሐቀኝነት የተንጸባረቀበት ውይይት በማድረግ ልዩነታቸውን ሊፈቱት ችለዋል። (ምሳሌ 12:18) አይቫን እንዲህ ይላል:- “የሚያዝያ 15, 1984 መጠበቂያ ግንብን (እንግሊዝኛ) የመሰሉ ስለ ሠርግ የሚናገሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አጠናን። a እነዚህ ጽሑፎች የሠርጋችንን ወቅት በተመለከተ መንፈሳዊ አመለካከት እንዲኖረን ረድተውናል። አስተዳደጋችን የተለያየ በመሆኑ በግል ምርጫዎቻችን ረገድ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሁለታችንም አመለካከታችንን ማስተካከል አስፈልጎናል።”

አሬትና ፔኒ የተባሉ ባልና ሚስትም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል። አሬት ስለ ሠርጋቸው ቀን እንዲህ ይላል:- “እኔና ፔኒ በሠርጉ ቀን ማድረግ የምንፈልጋቸውን ነገሮች በተመለከተ ባለን ልዩነት ላይ ተወያየን፤ ይህ ደግሞ አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ አስችሎናል። በሠርጋችን ቀን የይሖዋ በረከት እንዳይለየን ጸለይን። ወላጆቻችንም ሆኑ በጉባኤያችን የሚገኙ የጎለመሱ ባለትዳሮች ምክር እንዲሰጡኝ ጠየቅኩ። የሰጡኝ ምክር እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ ሠርጋችን አስደሳች ሊሆን ችሏል።”

የሚያስከብር አለባበስና አጋጌጥ

ሙሽራውም ሆነ ሙሽራዋ በሠርጋቸው ቀን አምረው ለመታየት እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። (መዝሙር 45:8-15) ለሠርጉ ተገቢ የሆነ ልብስ ማግኘት ጊዜ፣ ጥረትና ገንዘብ ይጠይቅባቸዋል። ተጋቢዎቹ የሚያምር ሆኖም የሚያስከብር ልብስ እንዲመርጡ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊረዷቸው ይችላሉ?

እስቲ ሙሽራዋ ለሠርጉ ቀን የምትለብሰውን ልብስ እንደ ምሳሌ እንመልከት። እርግጥ ነው፣ በዚህ ረገድ የሚደረገው ምርጫ ከሰው ወደ ሰው እንዲሁም ከአገር ወደ አገር የሚለያይ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ግን በየትም ቦታ ይሠራል። ሴቶች “በጨዋነትና ራስን በመግዛት ተገቢ የሆነ ልብስ [እንዲለብሱ]” ተመክረዋል። ይህ ደግሞ የሠርጋቸውን ቀን ጨምሮ ክርስቲያን ሴቶች ሁልጊዜ ሊሠሩበት የሚገባ ምክር ነው። እንዲያውም ሠርግ አስደሳች እንዲሆን “ዋጋቸው ውድ በሆኑ ልብሶች” ማጌጥ የግድ አስፈላጊ አይደለም። (1 ጢሞቴዎስ 2:9፤ 1 ጴጥሮስ 3:3, 4) ይህ ምክር በሥራ ሲውል ምንኛ ደስ ያሰኛል!

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዴቪድ እንዲህ ይላል:- “ብዙ ባልና ሚስት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመከተል ጥረት የሚያደርጉ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ሆኖም የሙሽራዋና የሚዜዎቿ ልብስ ጡት እስከሚያሳይ ድረስ ደረቱ በጣም የተገለጠጠ ወይም ስስ ሆኖ ሰውነትን በግልጽ የሚያሳይ በመሆኑ ልከኛ ያልሆነ አለባበስ የታየባቸው ጊዜያት አሉ።” አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ሽማግሌ ቀደም ብሎ ከሙሽራውና ከሙሽሪት ጋር በሚገናኝበት ጊዜ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ሊረዳቸው ይችላል። ይህን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? በዚያን ጊዜ ሊለብሱት ያሰቡት ልብስ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ሊሆን የሚችል ልከኛ ልብስ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል። እርግጥ የልብሱ ዓይነት ሁልጊዜ ለስብሰባ ከምንለብሰው ልብስ ሊለይ እንዲሁም በአካባቢው ያለውን ባሕል የሚያንጸባርቅ ሊሆን ቢችልም ላቅ ካሉት ክርስቲያናዊ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ልከኛ መሆን አለበት። በዓለም የሚገኙ አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሕግ ጥብቅ እንደሆነ አድርገው ቢመለከቱትም እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ዓለም በሚፈልገው መንገድ እነርሱን ለመቅረጽ የሚያደርገውን ጥረት በመቋቋማቸው ደስተኞች ናቸው።—ሮሜ 12:2፤ 1 ጴጥሮስ 4:4

ፔኒ እንዲህ ትላለች:- “እኔና አሬት ለምንለብሰው ልብስ ወይም ለድግሱ ትልቅ ቦታ ከመስጠት ይልቅ ትኩረት ያደረግነው መንፈሳዊ በሆነው የዝግጅቱ ክፍል ላይ ነበር። ይህ ደግሞ በዕለቱ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ነው። በሠርጌ ቀን ከተከናወኑት ሁኔታዎች መካከል ልዩ ቦታ ሰጥቼ የማስታውሰው፣ የለበስኩትን ልብስ ወይም የበላሁትን ምግብ ሳይሆን አብረውን ከነበሩ ሰዎች ጋር ያሳለፍኩትን ጊዜ እንዲሁም የምወደውን ሰው በማግባቴ የተሰማኝን ደስታ ነው።” ክርስቲያን ተጋቢዎች ለሠርጋቸው እቅድ ሲያወጡ እነዚህን ነገሮች በአእምሯቸው መያዝ ይገባቸዋል።

የመንግሥት አዳራሹ—ክብር ያለው ቦታ

በርካታ ክርስቲያን ተጋቢዎች የሠርጋቸው ሥነ ሥርዓት ከተቻለ በመንግሥት አዳራሽ እንዲከናወን ይፈልጋሉ። ይህንን ቦታ የሚመርጡት ለምንድን ነው? አንድ ባልና ሚስት ይህን ቦታ የመረጡበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ይናገራሉ:- “ጋብቻ የይሖዋ ቅዱስ ዝግጅት መሆኑን ተገንዝበን ነበር። የአምልኮ ቦታችን በሆነው በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ መጋባታችን ይሖዋ ገና ከጅምሩ የትዳራችን ክፍል መሆን እንዳለበት እንድናስታውስ አድርጎናል። የሠርጉ ሥነ ሥርዓት በሌላ ቦታ ከሚሆን ይልቅ በመንግሥት አዳራሽ መሆኑ ያለው ሌላ ጥቅም ደግሞ፣ በሠርጉ ላይ የተጋበዙት የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ዘመዶቻችን ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ለእኛ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማየት የሚያስችላቸው መሆኑ ነው።”

የመንግሥት አዳራሹን ኃላፊነት ወስደው የሚከታተሉ የጉባኤው ሽማግሌዎች ሠርጉ በዚያ እንዲካሄድ ከፈቀዱ ተጋቢዎቹ ወንድና ሴት፣ የሚያደርጉትን ዝግጅት በተመለከተ ቀደም ብለው ሽማግሌዎቹን ማማከር ያስፈልጋቸዋል። ሙሽራውና ሙሽራዋ በሠርጋቸው ዕለት ለተጋበዙት እንግዶች ተገቢውን አክብሮት የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ ሰዓት አክብሮ ለመገኘት ቁርጥ አቋም መውሰድ ነው። እንዲሁም ሁሉም ነገር በሚያስከብር ሁኔታ የሚከናወን መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። b (1 ቆሮንቶስ 14:40) በመሆኑም በዓለም እንደሚታዩት አብዛኞቹ ሠርጎች የማይገቡ ነገሮችን ከማድረግ ይቆጠባሉ።—1 ዮሐንስ 2:15, 16

ተጋባዦቹም ይሖዋ ለጋብቻ ያለው ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው ማሳየት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ትልቅ የሠርግ ድግስ የማዘጋጀት ውድድር ያለ ይመስል ሠርጉ ከሌሎች ክርስቲያኖች ሠርግ ልቆ እንዲገኝ መጠበቅ የለባቸውም። ከዚህም በላይ የጎለመሱ ክርስቲያኖች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርቶ የሚቀርበውን ንግግር ለማዳመጥ በመንግሥት አዳራሹ መገኘት ከዚያ በኋላ በሚደረገው ግብዣ ወይም ድግስ ላይ ከመገኘት ይልቅ እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን ይገነዘባሉ። አንድ ክርስቲያን ካለው ጊዜ ወይም ከሁኔታዎች አንጻር መገኘት የሚችለው በአንዱ ቦታ ላይ ብቻ ከሆነ በመንግሥት አዳራሹ ቢገኝ ይመረጣል። ዊልያም የተባለ አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “ተጋባዦች ከመንግሥት አዳራሽ በማይረባ ምክንያት ቀርተው በኋላ በድግሱ ላይ የሚገኙ ከሆነ ቅዱስ ለሆነው ለዚህ ሥነ ሥርዓት አድናቆት እንደሚጎድላቸው ያሳያል። ድግሱ ላይ ባንጠራም እንኳ በመንግሥት አዳራሹ በሚደረገው ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታችን በጋብቻቸው መደሰታችንን ለሙሽሮቹ ለመግለጽ ከማስቻሉም በላይ በመንግሥት አዳራሹ ለተገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላልሆኑ ዘመዶች ጥሩ ምሥክርነት ይሰጣል።”

ከሠርጉ ቀን ባሻገር የሚዘልቅ ደስታ

የሠርግ ድግስ፣ የንግዱ ዓለም ትርፍ የሚያገኝበት መስክ ሆኗል። አንድ በቅርቡ የወጣ ሪፖርት በዩናይትድ ስቴትስ መካከለኛ የሚባለው ሠርግ “22,000 የአሜሪካ ዶላር ወይም አንድ አሜሪካዊ [በዓመት] በአማካይ ከሚያገኘው ገቢ ግማሹን” እንደሚያስወጣ ገልጿል። የንግዱ ዓለም የሚያሰራጨው ፕሮፖጋንዳ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው አዲስ ተጋቢዎች ወይም ቤተሰቦቻቸው ለዚያች አንድ ቀን ሲሉ ለዓመታት ሊወጡት በማይችሉት ከባድ ዕዳ ውስጥ ይዘፈቃሉ። ሆኖም ትዳርን በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ መጀመር የጥበብ መንገድ ነው? የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የማያውቁ ወይም ችላ የሚሉ ተጋቢዎች እንዲህ ያለ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ሠርግ ለመደገስ ይመርጡ ይሆናል፤ ሆኖም በእውነተኛ ክርስቲያኖች ዘንድ ሁኔታው የተለየ ነው።

በርካታ ክርስቲያን ተጋቢዎች መጠነኛና አቅማቸውን ግምት ውስጥ ያስገባ ሠርግ በማዘጋጀታቸው እንዲሁም በዝግጅቱ መንፈሳዊ ክፍል ላይ ይበልጥ በማተኮራቸው፣ ራሳቸውን ለአምላክ ሲወስኑ ከገቡት ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ጊዜያቸውንና ሀብታቸውን መጠቀም ችለዋል። (ማቴዎስ 6:33) ትዳር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት 17 ዓመታት ያሳለፉትን የሎይድና የአሊጅዛንድራን ምሳሌ እንመልከት። ሎይድ እንዲህ ይላል:- “አንዳንዶች የሠርጋችንን ዝግጅት አነስ ያለ እንደሆነ አድርገው ተመልክተውት ሊሆን ቢችልም እኔና አሊጅዛንድራ ግን እጅግ ተደስተንበታል። የሠርጋችን ቀን በገንዘብ ረገድ ከፍተኛ ጫና እንዲፈጥርብን ከመፍቀድ ይልቅ ይሖዋ፣ ሁለት ሰዎች ከፍተኛ ደስታ እንዲያገኙ ያደረገውን ዝግጅት እንደምናደንቅ በሚያሳይ መንገድ አሳልፈነዋል።”

አሊጅዛንድራም እንዲህ ትላለች:- “ከመጋባታችን በፊት አቅኚ ስለነበርኩ ከአቅማችን በላይ የሆነ ሠርግ ለመደገስ ብዬ ይህን ልዩ መብት መተው አልፈለግኩም። የሠርጋችን ዕለት በጣም ልዩ ነበር። ይሁን እንጂ አብረን የምናሳልፈው ሕይወት ገና መጀመሩ ነበር። ለማግባት በሚደረገው ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንዳናደርግ የተሰጠንን ምክር የሠራንበት ከመሆኑም በላይ ተጋብተን በሚኖረን ሕይወት የይሖዋን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው። ይህ ደግሞ የይሖዋን በረከት እንዳስገኘልን ምንም ጥርጥር የለውም።” c

እውነት ነው፣ የሠርጋችሁ ቀን ልዩ የሆነ ጊዜ ነው። በዚያን ቀን የሚኖራችሁ አመለካከትና የምታደርጓቸው ነገሮች በትዳር የምታሳልፉት ሕይወት ምን እንደሚመስል ይጠቁማሉ። ስለዚህ መመሪያ ለማግኘት በይሖዋ ታመኑ። (ምሳሌ 3:5, 6) የሠርጋችሁን ቀን በተመለከተ መንፈሳዊው ነገር ቀዳሚውን ስፍራ እንዲይዝ አድርጉ። አምላክ የሰጣችሁን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ እርስ በርሳችሁ ተደጋገፉ። እንዲህ ካደረጋችሁ ለትዳራችሁ ጠንካራ መሠረት መጣል ትችላላችሁ፤ ይሖዋም ስለሚባርካችሁ ከሠርጋችሁ ቀን ባሻገር የሚዘልቅ ደስታ ይኖራችኋል።—ምሳሌ 18:22

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የመጋቢት 2002 ንቁ! ተመልከት።

b ሙሽሮቹ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የሚካሄደውን ሥነ ሥርዓት ፎቶግራፍ የሚያነሳ ወይም ቪዲዮ የሚቀርጽ ሰው ለማዘጋጀት ካሰቡ የሠርጉን ክብር የሚቀንስ ምንም ነገር የማይደረግ መሆኑን በቅድሚያ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለመጋባት ያሰቡ አንድ ወንድና ሴት ሠርጉን በተመለከተ በግልጽ ሆኖም በአክብሮት መወያየት ይኖርባቸዋል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሠርጋችሁ ቀን መንፈሳዊው ነገር ቀዳሚውን ስፍራ እንዲይዝ አድርጉ