በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆችን ለማሳደግ የሚረዳ አስተማማኝ ምክር

ልጆችን ለማሳደግ የሚረዳ አስተማማኝ ምክር

ልጆችን ለማሳደግ የሚረዳ አስተማማኝ ምክር

ሩት የመጀመሪያ ልጇን ስታረግዝ ምን እንደተሰማት ስትናገር “በወቅቱ ከዘመድ አዝማድ ርቄ የምኖር የ19 ዓመት ልጅ የነበርኩ ሲሆን ለሁኔታው ፈጽሞ አልተዘጋጀሁም ነበር” ብላለች። እርሷ ራሷ ለወላጆቿ አንድ ልጅ ስለሆነች ወላጅ ስለመሆን ያን ያህል አስባበት አታውቅም ነበር። ታዲያ አስተማማኝ ምክር ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?

በሌላ በኩል አሁን ሁለት ትልልቅ ልጆች ያሉት ጃን እንዲህ ብሏል:- “መጀመሪያ ላይ በራሴ በጣም ተማምኜ ነበር። ሆኖም ተግባራዊ እውቀት እንደሚጎድለኝ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብኝም።” ቀድሞውኑ ብቁ እንዳልሆኑ የሚሰማቸውም ሆኑ ከጊዜ በኋላ ብቃት እንደሌላቸው የሚገነዘቡ ወላጆች ልጆቻቸውን ጥሩ አድርገው ለማሳደግ የሚያስችላቸውን እርዳታ ከየት ማግኘት ይችላሉ?

በዘመናችን ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ወላጆች ምክር ለማግኘት ኢንተርኔት ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ ‘ከኢንተርኔት የሚገኘው ምክር ምን ያህል ያስተማምናል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በዚህ ረገድ ጠንቃቃ መሆን የሚያስፈልግበት አጥጋቢ ምክንያት አለ። በኢንተርኔት የሚተላለፈውን ምክር የሚሰጡህን ሰዎች ትክክለኛ ማንነት ታውቃለህ? እነርሱስ የራሳቸውን ልጆች በማሳደግ ረገድ ምን ያህል ተሳክቶላቸዋል? ቤተሰብህን የሚነካ ነገር ሲመጣ ጉዳዩን በጥንቃቄ መመልከት እንደምትፈልግ አያጠራጥርም። ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው አንዳንድ ጊዜ አማካሪዎች የሚሰጡት ምክር እንኳ የማይሠራ ሆኖ ይገኛል። ታዲያ ጥሩ ምክር ከየት ማግኘት ትችላለህ?

ልጆችን ለማሳደግ የሚረዳ ከሁሉ የተሻለ ምክር ማግኘት የሚቻለው የቤተሰብ መሥራች ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ነው። (ኤፌሶን 3:15) ትክክለኛው አማካሪ እርሱ ብቻ ነው። አስተማማኝና ውጤታማ የሆነ ተግባራዊ ትምህርት በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል። (መዝሙር 32:8፤ ኢሳይያስ 48:17, 18) ይሁን እንጂ ትምህርቱን በተግባር ላይ ማዋል የእኛ ፋንታ ነው።

በርካታ ባልና ሚስቶች ልጆቻቸውን ሚዛናዊና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው እንዲሆኑ አድርገው ባሳደጓቸው ወቅት ያገኙትን ተሞክሮ እንዲያካፍሉ ተጠይቀው ነበር። እነዚህ ወላጆች ለስኬታቸው ትልቁን አስተዋጽኦ ያበረከተው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋቸው እንደሆነ ተናግረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ምክሮቹ አስተማማኝ እንደሆኑ ተገንዝበዋል።

ከልጆቻችሁ ጋር ጊዜ አሳልፉ

የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ካትሪን ከሁሉም በላይ ጠቃሚ ሆኖ ያገኘችው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር የትኛው እንደሆነ ስትጠየቅ ወዲያውኑ የጠቀሰችው ዘዳግም 6:7ን ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “[የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች] ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።” ካትሪን ይህን ምክር በተግባር ለማዋል ከፈለገች ከልጆቿ ጋር የግድ ጊዜ ማሳለፍ እንደሚኖርባት ተገንዝባ ነበር።

‘እንዲህ ማድረጉ የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም’ ብለህ ታስብ ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ሁለቱም ወላጆች የቤተሰባቸውን ፍላጎት ለሟሟላት ከቤት ውጪ እንዲሠሩ በሚገደዱበት በዚህ ወቅት ሥራ የሚበዛባቸው ባልና ሚስቶች ለልጆቻቸው ብዙ ጊዜ መስጠት የሚችሉት እንዴት ነው? በአሁኑ ጊዜ የራሱን ቤተሰብ የመሠረተ ልጅ ያለው ቶርሊፍ ወሳኙ ነገር በዘዳግም ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንደሆነ ተናግሯል። ልጆቻችሁን በምትሄዱበት ቦታ ሁሉ ውሰዷቸው፤ እንዲህ ካደረጋችሁ እርስ በርስ ለመጨዋወት የሚያስችላችሁ አጋጣሚ በቀላሉ መፈጠሩ አይቀርም። ቶርሊፍ እንዲህ ብሏል:- “በቤት ውስጥ መከናወን የሚገባቸውን ሥራዎች የምሠራው ከልጄ ጋር ነበር። በቤተሰብ ደረጃ ሽርሽር እንሄድ የነበረ ከመሆኑም በላይ አብረን እንመገባለን።” በዚህም ምክንያት “ልጃችን ሁልጊዜ ስሜቱን በነፃነት መግለጽ እንደሚችል ይሰማው ነበር” ሲል ተናግሯል።

ወላጆችና ልጆች በግልጽ የማይነጋገሩ፣ ቢነጋገሩ እንኳ የማይጣጣሙ ቢሆንስ? አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ልጆቹ ከፍ ሲሉ ሊከሰት ይችላል። በዚህ ጊዜም ቢሆን ከልጆቻችሁ ጋር የበለጠ ጊዜ ማሳለፋችሁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። የካትሪን ባለቤት ኬን፣ ልጃቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለች እርሷ የምትናገረውን ነገር ትኩረት ሰጥቶ እንደማያዳምጣት በመንገር ወቅሳው እንደነበር ትዝ ይለዋል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ተመሳሳይ ቅሬታ ማሰማታቸው የተለመደ ነው። ታዲያ ኬን ምን እርምጃ ወሰደ? ሁኔታውን በማስታወስ እንዲህ ብሏል:- “እኔና እርሷ ብቻችንን ሆነን የበለጠ ጊዜ በማሳለፍ ስለምታስበው ነገር፣ ስለ ስሜቷና ስለሚያስጨንቃት ነገር ለመወያየት ወሰንኩ። እንዲህ ማድረጋችን ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።” (ምሳሌ 20:5) ያም ሆኖ ኬን ዘዴው ውጤታማ ሊሆንለት የቻለው እቤታቸው ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ የተለመደ ስለነበር እንደሆነ ይሰማዋል። “ሁልጊዜም ከልጄ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረን። ስለዚህ በነፃነት ልታነጋግረኝ እንደምትችል ይሰማት ነበር” ብሏል።

የሚገርመው ነገር በቅርብ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በቂ ጊዜ አብረው እንዳላሳለፉ ቅሬታ ካሰሙ ወላጆች ቁጥር ይልቅ የልጆቹ በሦስት እጥፍ ይበልጣል። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ለምን አትከተልም? አቅምህ በፈቀደ መጠን ከልጆችህ ጋር ብዙ ጊዜ አሳልፍ። ይህን ደግሞ አረፍ ስትል፣ ሥራ ላይ እያለህ፣ እቤት ስትሆን፣ በምትጓዝበት ጊዜ እንዲሁም ጠዋት ከመኝታህ ከተነሳህ በኋላና ማታ ወደ መኝታ ከመሄድህ በፊት ልታደርገው ትችላለህ። የምትችል ከሆነ በምትሄድበት ቦታ ሁሉ ይዘሃቸው ሂድ። ዘዳግም 6:7 እንደሚያሳየው ከልጆችህ ጋር የምታሳልፈውን ጊዜ የሚተካ ምንም ነገር አይኖርም።

ተገቢ የሆኑ ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን አስተምሯቸው

የሁለት ልጆች አባት የሆነው ማሪዮም እንዲሁ “ለልጆቻችሁ ጥልቅ ፍቅር እንዳላችሁ አሳዩአቸው እንዲሁም አንብቡላቸው” ብሏል። ይሁን እንጂ እንዲህ የምታደርጉት የልጆቻችሁን አእምሮ ለማስፋት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር እንዴት መለየት እንደሚችሉ ማስተማር ስለሚኖርባችሁ ጭምር ነው። ማሪዮ “መጽሐፍ ቅዱስን አስጠኗቸው” ሲል አክሎ ተናግሯል።

መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በማስመልከት ለወላጆች የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷል:- “እናንተም ወላጆች ሆይ! በጌታ ኢየሱስ ሥነ ሥርዓትና ምክር አሳድጉአቸው እንጂ ልጆቻችሁን በማስቈጣት አታስመርሩአቸው።” (ኤፌሶን 6:4 የ1980 ትርጉም) በዘመናችን በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ ለሥነ ምግባር ትምህርት እምብዛም ትኩረት አይሰጥም። አንዳንድ ሰዎች፣ ልጆች አዋቂ ሲሆኑ የትኛውን ሥነ ምግባራዊ እሴት መከተል እንዳለባቸው ራሳቸው መወሰን ይችላሉ የሚል አስተሳሰብ አላቸው። አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል? የልጆች አካል ጠንካራና ጤናማ ሆኖ እንዲያድግ ተመጣጣኝ ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ አእምሯቸውና ልባቸውም ትምህርት ያስፈልገዋል። ልጆችህ የሥነ ምግባር ትምህርቶችን እቤት ውስጥ ካልተማሩ የክፍል ጓደኞቻቸውን፣ የአስተማሪዎቻቸውን ወይም በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡ ሰዎች ያላቸውን አመለካከት መቅሰማቸው አይቀርም።

ወላጆች ልጆቻቸው ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ ለመርዳት መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም ይችላሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ሁለት ልጆችን ያሳደገውና ጥሩ ተሞክሮ ያለው ጄፍ የተባለ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ፣ ለልጆች ተገቢ የሆኑ የሥነ ምግባር እሴቶችን ለማስተማር መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅሞ ማስተማር ልጆች እናትና አባታቸው ብቻ ሳይሆኑ ፈጣሪም ስለ አንድ ጉዳይ ምን እንደሚሰማው እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በአእምሮና በልብ ላይ አስደናቂ ውጤት እንደሚያስከትል አስተውለናል። አንድን የተሳሳተ ጠባይ ወይም አስተሳሰብ ለማረም የሚረዳ ተስማሚ ጥቅስ ለማግኘት ጊዜ ወስደን እንፈልግ ነበር። ከዚያም ልጃችን ጥቅሱን እንዲያነብ በግሉ እንነግረዋለን። አብዛኛውን ጊዜ ልጁ ጥቅሱን ካነበበ በኋላ እንባው ይመጣል፤ አንዳንዴም ያለቅሳል። ይህ ሁኔታ ያስደንቀን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እኛ በንግግርም ሆነ በድርጊት ማሳደር ከምንችለው ማንኛውም ተጽዕኖ የበለጠ ኃይል አለው።”

ዕብራውያን 4:12 “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ . . . የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል” ይላል። የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አምላክ ጸሐፊ አድርጎ የተጠቀመባቸው ሰዎች የግል አመለካከት ወይም ተሞክሮ እንደሆነ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ስለ ሥነ ምግባር ምን አመለካከት እንዳለው የሚያሳይ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ከሌሎች ምክሮች ሁሉ የተለየ እንዲሆን የሚያደርገው ይህ ነው። ልጆችህን ስታስተምር መጽሐፍ ቅዱስ የምትጠቀም ከሆነ በማንኛውም ጉዳይ ላይ አምላካዊ አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ እየረዳሃቸው ነው። በዚህ መንገድ የምትሰጠው ሥልጠና የበለጠ ኃይል ይኖረዋል፤ እንዲሁም የልጅህን ልብ ለመንካት ቀላል ይሆንልሃል።

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካትሪን በዚህ ሐሳብ እንደምትስማማ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “ሁኔታው እየከበደ በሄደ ቁጥር እኛም ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት እንጨምራለን። ይህንንም ውጤታማ ሆኖ አግኝተነዋል!” ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር እንዲለዩ ልጆችህን ስታስተምር መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ለመጠቀም ለምን ጥረት አታደርግም?

ምክንያታዊ ሁኑ

ሐዋርያው ጳውሎስ ልጆችን በጥሩ መንገድ ለማሳደግ ስለሚረዳ አንድ አስፈላጊ መሠረታዊ ሥርዓት ተናግሯል። የእምነት ባልንጀሮቹን “ገርነታችሁ [“ምክንያታዊነታችሁ፣” NW] በሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” በማለት አሳስቧቸዋል። (ፊልጵስዩስ 4:5) ምክንያታዊነታችንን ማሳየት የሚኖርብን ለልጆቻችን ጭምር እንደሆነ እሙን ነው። በተጨማሪም ምክንያታዊነት “ከሰማይ የሆነችው ጥበብ” ነጸብራቅ እንደሆነ አትዘንጋ።—ያዕቆብ 3:17 NW

ይሁን እንጂ ምክንያታዊነት ልጆችን ከማሠልጠን ጋር ምን ግንኙነት አለው? ለልጆቻችን አስፈላጊውን እርዳታ ሁሉ የምንሰጣቸው ቢሆንም እንኳ እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን አንቆጣጠርም። ለምሳሌ ያህል ቀደም ሲል የተጠቀሰውና የይሖዋ ምሥክር የሆነው ማሪዮ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ልጆቻችን እንዲጠመቁ፣ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲገቡና ሌሎች መንፈሳዊ ግቦችን እንዲያወጡ ሁልጊዜ እናበረታታቸው ነበር። ሆኖም ውሳኔያቸውን እነርሱ በመረጡት ጊዜ እንዲያደርጉ በግልጽ እንነግራቸው ነበር።” ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? አሁን ሁለቱም ልጆቻቸው የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሆነው እያገለገሉ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ አባቶችን “አባቶች ሆይ፤ ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው” ሲል መክሯቸዋል። (ቈላስይስ 3:21) ካትሪን ይህን ጥቅስ ትወደዋለች። አንድ ወላጅ ትዕግሥቱ ሲሟጠጥ በቀላሉ ሊናደድም ሆነ ከልጆቹ ብዙ ሊጠብቅ ይችላል። ያም ሆኖ ግን ካትሪን “ከራሳችሁ የምትጠብቁትን ያህል ከልጆቻችሁ አትጠብቁ” ብላለች። የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ካትሪን “ይሖዋን ማገልገል አስደሳች እንዲሆንላቸው አድርጉ” ስትል አክላ ተናግራለች።

ከላይ የተጠቀሰው ጄፍም የሚከተለውን ተግባራዊ ሐሳብ ሰጥቷል:- “ልጆቻችን ከፍ ከፍ ማለት ሲጀምሩ አንድ ወዳጃችን ልጆቹ አንድ ነገር ሲጠይቁት አይቻልም የሚልበት ጊዜ እንደሚበዛ ማስተዋሉን ነገረን። ይህ ደግሞ ልጆቹ ተስፋ እንዲቆርጡና እንደተጨቆኑ እንዲሰማቸው አድርጓል። ይህ ሁኔታ በእኛ ላይ እንዳይደርስ ለልጆቻችን እሺ የምንልባቸውን አጋጣሚዎች እንድንፈልግ ሐሳብ አቀረበልን።”

ጄፍ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “ምክሩን ጥሩ ሆኖ አግኝተነዋል። ልጆቻችን በእኛ ፈቃድ ከሌሎች ጋር አንዳንድ ነገሮችን የሚያደርጉበትን አጋጣሚ መፈላለግ ጀመርን። ስለዚህ ቀረብ ብለን ‘እገሌና እገሌ ይህን ወይም ያን እያደረጉ እንዳሉ ታውቃላችሁ? እናንተስ ለምን አትሄዱም?’ እንላቸዋለን። ወይም ደግሞ አንድ ቦታ እንድንወስዳቸው ከጠየቁን ቢደክመንም እንኳ ይዘናቸው ለመሄድ ጥረት እናደርጋለን። ይህን ሁሉ ያደረግነው ‘አይቻልም’ ላለማለት ነው።” ይህ የምክንያታዊነት ትክክለኛ መገለጫ ነው። ምክንያታዊነት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት ሳይጥሱ አግባብነት ያለውን ነገር ማድረግን፣ አሳቢነት ማሳየትንና እሺ ባይ መሆንን ያጠቃልላል።

አስተማማኝ ከሆነው ምክር ተጠቀሙ

ከላይ ከተጠቀሱት ባልና ሚስቶች አብዛኞቹ አያት ለመሆን በቅተዋል። እነርሱ የተጠቀሙባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ ልጆቻቸው የተዋጣላቸው ወላጆች እንዲሆኑ ሲረዷቸው በመመልከታቸው ደስተኞች ናቸው። አንተም ከመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተጠቃሚ ለመሆን ለምን አትሞክርም?

በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰችው ሩት ልጇን ከወለደች በኋላ እርሷና ባለቤቷ ጥሩ ምክር ከየት ማግኘት እንደሚችሉ ግራ የገባቸው ጊዜ ነበር። ሆኖም ምክር የሚለግሳቸው ምንም ነገር አልነበረም ማለት አይደለም። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው የላቀ ምክር አለላቸው። የይሖዋ ምሥክሮች፣ ወላጆችን ሊረዱ የሚችሉ በርከት ያሉ ግሩም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አዘጋጅተዋል። ከእነዚህም መካከል ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ (እንግሊዝኛ)፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ፣ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች እንዲሁም እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የሚሉት መጽሐፎች ይገኙበታል። የሩት ባለቤት የሆነው ቶርሊፍ “በዛሬው ጊዜ ወላጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ በርካታ ምክሮችን በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። ልጆቻቸው ሲያድጉ በሁሉም የኑሮ ዘርፍ እንዲሳካላቸው መርዳት የሚችሉት በእነዚህ ምክሮች እስከተጠቀሙ ድረስ ብቻ ነው” ብሏል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ስለ ልጅ አስተዳደግ አማካሪዎች ምን ይላሉ? መጽሐፍ ቅዱስስ?

ፍቅር ስለ ማሳየት:-

ዶክተር ጆን ብሮደስ ዋትሰን ዘ ሳይኮሎጂካል ኬር ኦቭ ኢንፋንት ኤንድ ቻይልድ (1928) በተባለው ጽሑፋቸው ላይ ልጆቻችሁን “ፈጽሞ አትቀፏቸው እንዲሁም አትሳሟቸው። ጭናችሁ ላይ እንዲቀመጡ አታድርጓቸው” በማለት ወላጆችን አሳስበዋል። ይሁን እንጂ በቅርቡ ዶክተር ቬራ ሌን እና ዶክተር ዶረቲ ሞሌኖ ልጆቻችን (የመጋቢት 1999) በተባለው መጽሔት ላይ “በወላጆቻቸው ያልታቀፉና ያልተዳበሱ እንዲሁም ፍቅር የተነፈጋቸው ትንንሽ ልጆች ብዙውን ጊዜ የተሟላ እድገት እንደማይኖራቸው የምርምር ውጤቶች ያሳያሉ” ብለዋል።

በአንጻሩ ግን ኢሳይያስ 66:12 ወላጅ ፍቅሩን የሚገልጽበትን መንገድ በመጠቀም አምላክ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር ይገልጻል። በተመሳሳይም ኢየሱስ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ እርሱ ሲያመጡ ደቀ መዛሙርቱ በከለከሏቸው ጊዜ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው” በማለት ትክክል እንዳልሆኑ ገልጾላቸው ነበር። “ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው።”—ማርቆስ 10:14, 16

ተገቢ የሆኑ ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን ስለ ማስተማር:-

ዶክተር ብሩኖ ቤተልሃይም በ1969 ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት ላይ በወጣ አንድ ርዕስ ሥር፣ አንድ ልጅ “[ወላጆቹ] ምንም ዓይነት ተጽዕኖ ሳያደርጉበት ከግሉ የሕይወት ተሞክሮ በመነሳት የራሱን አመለካከት የማዳበር መብት” እንዳለው ጠበቅ አድርገው ተናግረዋል። ከ30 ዓመታት በኋላ ደግሞ ዘ ሞራል ኢንተለጀንስ ኦቭ ችልድረን (1997) የተባለው ጽሑፍ ደራሲ የሆኑት ዶክተር ሮበርት ኮልስ ‘ልጆች በሕይወታቸው ውስጥ በወላጆቻቸውም ሆነ በሌሎች ትልልቅ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ዓላማና አመራር እንዲሁም የሥነ ምግባር መመሪያ በጣም ያስፈልጋቸዋል’ ብለዋል።

ምሳሌ 22:6 እንዲህ ሲል ወላጆችን ያሳስባል:- “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።” እዚህ ላይ ‘ማስተማር’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ማስጀመር የሚል ትርጉም አለው። ይህ ደግሞ ለሕፃኑ ገና መጀመሪያ ላይ የሚሰጠውን ትምህርት ያመለክታል። በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን ገና ከሕፃንነታቸው ጀምረው ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን እንዲያስተምሯቸው ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) በዚህ የጨቅላነት ዕድሜያቸው የሚሰጣቸው ትምህርት ካደጉም በኋላ ከውስጣቸው አይፋቅም።

ተግሣጽ ስለ መስጠት:-

ዶክተር ጄምስ ዶብሰን ዘ ስትሮንግ-ዊልድ ቻይልድ (1978) በተሰኘው ጽሑፋቸው ላይ “ልጆች በአፍቃሪ ወላጆቻቸው መገረፋቸው ጎጂ ባሕርያት እንዳያዳብሩ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ ነው” ብለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ዶክተር ቤንጃሚን ስፖክ ሕፃናትና የልጅ እንክብካቤ (1998) ከተባለው ተወዳጅ መጽሐፍ ሰባተኛ እትም ላይ አውጣጥተው ባዘጋጁት ጽሑፍ ውስጥ እንዲህ ብለዋል:- “ልጆች መመታታቸው በዕድሜም ሆነ በጉልበት ከእነርሱ የሚበልጣቸው ያ የቀጣቸው ሰው ትክክልም ይሁን አይሁን የፈለገውን ነገር የማስደረግ ኃይል እንዳለው ያስገነዝባቸዋል።”

መጽሐፍ ቅዱስ ተግሣጽ መስጠትን በተመለከተ “የተግሣጽ በትር ጥበብን ታጐናጽፋለች” ይላል። (ምሳሌ 29:15) ይሁን እንጂ ሁሉም ልጆች መገረፍ አያስፈልጋቸው ይሆናል። ምሳሌ 17:10 “መቶ ግርፋት ተላላን ከሚሰማው ይልቅ፣ ተግሣጽ ለአስተዋይ ጠልቆ ይሰማል” በማለት ይነግረናል።

[ሥዕል]

የልጆቻችሁን ልብ ለመንካት መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቀሙ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው የሚዝናኑበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ