በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቅዱስ ለሆኑት ስብሰባዎቻችን አክብሮት ማሳየት

ቅዱስ ለሆኑት ስብሰባዎቻችን አክብሮት ማሳየት

ቅዱስ ለሆኑት ስብሰባዎቻችን አክብሮት ማሳየት

“ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤ በጸሎት ቤቴም ውስጥ ደስ አሰኛቸዋለሁ።”—ኢሳይያስ 56:7

1. ለስብሰባዎቻችን ተገቢውን አክብሮት ማሳየት እንዳለብን የሚጠቁሙ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች አሉ?

 ይሖዋ ሕዝቡ የሆኑትን ቅቡዓን ክርስቲያኖችንና አጋሮቻቸውን እርሱን ወደሚያመልኩበት ‘ወደ ተቀደሰው ተራራው’ ሰብስቧቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ “ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት” በሆነው መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ማለትም ‘በጸሎት ቤቱ’ ውስጥ ደስ እንዲሰኙ እያደረጋቸው ነው። (ኢሳይያስ 56:7፤ ማርቆስ 11:17) ይሖዋ ሕዝቦቹ እርሱን ለማምለክ በአንድነት እንዲሰበሰቡ ማድረጉ ለእርሱ የሚቀርበው አምልኮ ቅዱስ፣ ንጹሕና ከምንም በላይ ከፍ ያለ መሆኑን ይጠቁማል። እኛም ለጥናትና ለአምልኮ ለምንገናኝባቸው ስብሰባዎች ተገቢ አክብሮት በመስጠት ይሖዋ ለቅዱስ ነገሮች ያለውን አመለካከት እንደምናንጸባርቅ ማሳየት እንችላለን።

2. ይሖዋ ለአምልኮቱ የመረጠውን ስፍራ ቅዱስ አድርጎ እንደሚመለከተው የሚያሳየን ምንድን ነው? ኢየሱስም ተመሳሳይ አመለካከት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

2 በጥንቷ እስራኤል ይሖዋ ለእርሱ አምልኮ የመረጠው ስፍራ ቅዱስ ተደርጎ ይታይ ነበር። የማደሪያው ድንኳን እንዲሁም በውስጡ ያሉት ዕቃዎችና ቁሳቁሶች “እጅግ የተቀደሱ ይሆኑ ዘንድ” ይቀቡና ይቀደሱ ነበር። (ዘፀአት 30:26-29) የዚህ መቅደስ ሁለት ክፍሎች “ቅድስት” እና “ቅድስተ ቅዱሳን” በመባል ይታወቃሉ። (ዕብራውያን 9:2, 3) በኋላም የማደሪያው ድንኳን ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው ቤተ መቅደስ ተተካ። ኢየሩሳሌም የይሖዋ አምልኮ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን ‘ቅድስት ከተማ’ የሚል መጠሪያ ነበራት። (ነህምያ 11:1፤ ማቴዎስ 27:53) ኢየሱስ በምድር ላይ ባገለገለበት ወቅት ለቤተ መቅደሱ ጥልቅ አክብሮት እንዳለው አሳይቷል። ሕዝቡ አክብሮት በጎደለው መንገድ የቤተ መቅደሱን ግቢ ለንግድና መንገድ ለማቋረጥ ሲጠቀምበት ማየቱ በጣም አበሳጭቶታል።—ማርቆስ 11:15, 16

3. የእስራኤላውያን ጉባኤዎች ቅዱስ መሆናቸውን የሚያሳየው ምንድን ነው?

3 እስራኤላውያን ይሖዋን ለማምለክና ሕጉ ሲነበብ ለማድመጥ ዘወትር ይሰበሰቡ ነበር። ከሚያከብሯቸው ክብረ በዓላት ውስጥ የተወሰኑ ቀኖችን የተቀደሱ ጉባኤዎች ወይም ዋና ጉባኤዎች ብለው ይጠሯቸው ነበር፤ ይህም እነዚህ ስብሰባዎች ቅዱስ መሆናቸውን ያመለክታል። (ዘሌዋውያን 23:2, 3, 36, 37 የ1954 ትርጉም) በዕዝራና በነህምያ ዘመን ሌዋውያን ‘ሕጉን ለሕዝቡ ያስረዱ’ ነበር። ይሁንና “ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሚሰሙበት ጊዜ ያለቅሱ” ስለ ነበር ሌዋውያኑ ‘ይህች ቀን የተቀደሰች ስለሆነች ዝም በሉ፤ አትዘኑም’ በማለት ሕዝቡን ሁሉ አረጋጉ። ከዚያም እስራኤላውያን ሰባት ቀን የሚፈጀውን የዳስ በዓል ‘በታላቅ ደስታ’ አከበሩ። ከዚህም በላይ “ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ፣ ዕዝራ በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ [ለሕዝቡ] ያነብ ነበር። እነርሱም በዓሉን ሰባት ቀን አከበሩ፤ በስምንተኛውም ቀን በሕጉ መሠረት የተቀደሰ ጉባኤ ተደረገ።” (ነህምያ 8:7-11, 17, 18) በእርግጥም ይህ ወቅት በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች በአክብሮት ሊመለከቱት የሚገባ ቅዱስ በዓል ነበር።

ስብሰባዎቻችን ቅዱስ ናቸው

4, 5. ስብሰባዎቻችን ቅዱስ መሆናቸውን የሚጠቁሙት የትኞቹ ገጽታዎች ናቸው?

4 እውነት ነው፣ በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በምድር ላይ ለእርሱ አምልኮ የተወሰነ ልዩ ቤተ መቅደስ ያለበት ቅዱስ ከተማ የለውም። ይሁን እንጂ ይሖዋን ለማምለክ የምናደርጋቸው ስብሰባዎች ቅዱስ መሆናቸውን መዘንጋት አይኖርብንም። በሳምንት ሦስት ጊዜ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማንበብና ለማጥናት እንሰበሰባለን። በነህምያ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም የይሖዋ ቃል ‘እየተተረጎመ ይተነተንልናል።’ (ነህምያ 8:8) ሁሉም ስብሰባዎች የሚከፈቱትና የሚደመደሙት በጸሎት ነው፤ እንዲሁም በአብዛኞቹ ላይ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙሮችን እንዘምራለን። (መዝሙር 26:12) የጉባኤ ስብሰባዎቻችን የአምልኮታችን ክፍል በመሆናቸው በእርግጥም ከፍተኛ ትኩረት ልንሰጣቸውና በአክብሮት ልንመለከታቸው ይገባል።

5 ይሖዋ ሕዝቦቹ እርሱን ለማምለክ፣ ቃሉን ለማጥናትና ከክርስቲያን ወዳጆቻቸው ጋር አስደሳች ቅርርብ ለመፍጠር ሲሉ አንድ ላይ በመሰብሰባቸው ይባርካቸዋል። ስብሰባ ላይ ስንሆን ይሖዋ ‘በረከቱን ባዘዘበት’ ቦታ ላይ እንደተገኘን ልንተማመን እንችላለን። (መዝሙር 133:1, 3) በመሆኑም በስብሰባ ላይ የምንገኝና መንፈሳዊ ፕሮግራሞቹን በጥሞና የምንከታተል ከሆነ ከበረከቱ ተካፋዮች እንሆናለን። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ “ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት መካከል በዚያ እገኛለሁ” ብሏል። ጥቅሱ በዋነኝነት የሚናገረው በግለሰቦች መካከል የሚነሱ ከባድ ችግሮችን ለመፍታት ስለሚሰበሰቡ የጉባኤ ሽማግሌዎች ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ግን ለሁሉም ስብሰባዎች ይሠራል። (ማቴዎስ 18:20) ክርስቲያኖች በስሙ በሚሰበሰቡበት ጊዜ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በመካከላቸው የሚገኝ ከሆነ በእርግጥ እነዚህ ስብሰባዎች ቅዱስ ተደርገው መታየት አይኖርባቸውም?

6. ትላልቅም ሆኑ ትናንሽ፣ ስለ አምልኮ ስፍራዎቻችን ምን ለማለት ይቻላል?

6 ይሖዋ የሰው እጅ በሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ እንደማይኖር የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ የመንግሥት አዳራሾቻችን እውነተኛው አምልኮ የሚከናወንባቸው ስፍራዎች ናቸው። (የሐዋርያት ሥራ 7:48፤ 17:24) በእነዚህ አዳራሾች ውስጥ የምንሰበሰበው የይሖዋን ቃል ለማጥናት፣ ወደ እርሱ ለመጸለይና የውዳሴ መዝሙር ለመዘመር ነው። በትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ውስጥ ስንሰበሰብም ዓላማችን ተመሳሳይ ነው። ከዚህም በላይ የአውራጃ ስብሰባ ለማድረግ የምንከራያቸው ሰፋፊ አዳራሾች፣ የኤግዚቢሽን ማዕከሎች አሊያም ስታዲየሞች ቅዱስ በሆኑት በእነዚህ ስብሰባዎች ወቅት የአምልኮ ስፍራዎች ሆነው ያገለግላሉ። ትላልቅም ይሁኑ ትናንሽ፣ ለአምልኮ ለምንሰበሰብባቸው ቦታዎች ጥልቅ አክብሮት ማሳየት ይገባናል፤ እንዲህ ያለው አክብሮት በዝንባሌያችንና በባሕርያችን መንጸባረቅ ይኖርበታል።

ለስብሰባዎቻችን አክብሮት የምናሳይባቸው መንገዶች

7. ለስብሰባዎቻችን አክብሮት እንዳለን በምን ተጨባጭ መንገድ ማሳየት እንችላለን?

7 ለስብሰባዎቻችን ያለንን አክብሮት በግልጽ ማሳየት የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ በሰዓቱ ተገኝተን የመንግሥቱን መዝሙሮች በመዘመር ነው። አብዛኞቹ መዝሙሮች የጸሎት ይዘት ስላላቸው በአክብሮት ልንዘምራቸው ይገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ መዝሙር 22ን በመጥቀስ ስለ ኢየሱስ “ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፤ በጒባኤም መካከል ምስጋናህን እዘምራለሁ” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 2:12) በመሆኑም የስብሰባው ሊቀ መንበር መዝሙሩን ከማስተዋወቁ በፊት ስፍራችንን የመያዝና የመዝሙሩ ቃላት ያላቸውን ትርጉም እያሰብን የመዘመር ልማድ ማዳበር ይኖርብናል። አዘማመራችን “በቅኖች ሸንጎ፣ በጉባኤም መካከል፣ ለእግዚአብሔር በፍጹም ልቤ ምስጋና አቀርባለሁ” በማለት የጻፈውን መዝሙራዊ ስሜት የሚያንጸባርቅ እንዲሆን እንጣር። (መዝሙር 111:1) አዎን፣ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር የማቅረብ ፍላጎታችን በጉባኤ ላይ ቀድመን ለመገኘትና እስከ መደምደሚያው ድረስ ለመቆየት የሚገፋፋን አንድ ጥሩ ምክንያት ነው።

8. በስብሰባዎቻችን ላይ የሚቀርቡትን ጸሎቶች ትኩረት ሰጥተን በአክብሮት ልንከታተላቸው እንደሚገባ የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ያሳያል?

8 ሁሉም ስብሰባዎቻችን በመንፈሳዊ ይበልጥ ጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ሌላው ገጽታ ደግሞ ተሰብሳቢዎቹን በመወከል የሚቀርበው ከልብ የመነጨ ጸሎት ነው። በአንድ ወቅት በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አንድ ላይ ከተሰበሰቡ በኋላ “ድምፃቸውን በአንድነት ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርገው” ከልብ የመነጨ ጸሎት አቀረቡ። እነዚህ ክርስቲያኖች በወቅቱ ስደት እየደረሰባቸው የነበረ ቢሆንም እንዲህ ማድረጋቸው ‘የእግዚአብሔርን ቃል በድፍረት መናገራቸውን’ እንዲቀጥሉ አስችሏቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 4:24-31) በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች ጸሎቱ በሚቀርብበት ጊዜ በሐሳብ የባዘኑ ይመስልሃል? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ የጸለዩት “በአንድነት” ወይም በአንድ ልብ ሆነው ነበር። በስብሰባዎቻችን ላይ የሚቀርቡት ጸሎቶች የሁሉንም ተሰብሰቢዎች ስሜት ያንጸባርቃሉ። በመሆኑም ትኩረት ሰጥተን በአክብሮት መከታተል ይገባናል።

9. ቅዱስ ለሆኑት ስብሰባዎች ያለንን አክብሮት በአለባበሳችንና በምግባራችን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

9 ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ለሆኑት ስብሰባዎቻችን ጥልቅ አክብሮት እንዳለን በአለባበሳችን ማሳየት እንችላለን። አካላዊ ሁኔታችን ማለትም አለባበሳችንም ይሁን የፀጉር አበጣጠራችን ለስብሰባዎቻችን ክብር ይጨምራል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል መክሯል:- “ወንዶች በሁሉም ቦታ ያለ ቊጣና ያለ ክርክር የተቀደሱ እጆቻቸውን ወደ ላይ በማንሣት እንዲጸልዩ እፈልጋለሁ። እንዲሁም ሴቶች በጨዋነትና ራስን በመግዛት ተገቢ የሆነ ልብስ ይልበሱ እንጂ በሹሩባ ወይም በዕንቊ ወይም ዋጋቸው ውድ በሆኑ ልብሶች አይሽቀርቀሩ፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን የሚሉ ሴቶች ሊያደርጉ እንደሚገባ በመልካም ተግባር ይዋቡ።” (1 ጢሞቴዎስ 2:8-10) መጠለያ በሌላቸው ስታዲየሞች ውስጥ በሚደረጉ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ አለባበሳችን ከአየሩ ሁኔታ ጋር የሚስማማ ቢሆንም እንኳ ልከኛ መሆን ይገባዋል። ከዚህም ባሻገር ለስብሰባዎች ያለን አክብሮት ስብሰባዎች በመካሄድ ላይ እያሉ ምግብ ከመብላትና ማስቲካ ከማኘክ እንድንቆጠብ ያደርገናል። በስብሰባዎቻችን ላይ የሚኖረን ተገቢ አለባበስና ጥሩ ባሕርይ ይሖዋ አምላክን፣ አምልኮቱንና የእምነት ባልንጀሮቻችንን ያስከብራል።

ለአምላክ ቤት የሚስማማ ምግባር

10. ሐዋርያው ጳውሎስ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር ደረጃዎችን መጠበቅ እንዳለብን ያመለከተው እንዴት ነው?

10 በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 14 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዴት መመራት እንዳለባቸው የሚገልጽ ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቷል። ከዚያም “ሁሉም በአግባብና በሥርዐት ይሁን” በማለት ምክሩን ደምድሟል። (1 ቆሮንቶስ 14:40) ስብሰባዎቻችን ክርስቲያን ጉባኤ ከሚያካሂዳቸው አስፈላጊ እንቅስቃሴዎች መካከል ስለሆኑ ለይሖዋ ቤት የሚስማማ ምግባር ልናሳይ ይገባል።

11, 12. (ሀ) በስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ልጆች ምን ነገር ሊገነዘቡ ይገባል? (ለ) በስብሰባዎቻችን ላይ ልጆች በየትኛው ተገቢ መንገድ እምነታቸውን መግለጽ ይችላሉ?

11 በተለይም ልጆች በስብሰባዎች ላይ ምን ዓይነት ጠባይ ሊኖራቸው እንደሚገባ መማር ይኖርባቸዋል። ክርስቲያን ወላጆች፣ የመንግሥት አዳራሾችና የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት የሚደረጉባቸው ቦታዎች የመጫወቻ ስፍራዎች አለመሆናቸውን ለልጆቻቸው ማስረዳት ይገባቸዋል። እነዚህ ቦታዎች ይሖዋን ለማምለክና ቃሉን ለማጥናት የምንገለገልባቸው ናቸው። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ‘ወደ እግዚአብሔር ቤት ስትሄድ እግርህን ጠብቅ። ለመስማትም ቅረብ’ ሲል ጽፏል። (መክብብ 5:1) ሙሴ፣ እስራኤላውያንን ‘ልጅ’ አዋቂ ሳይሉ በአንድነት እንዲሰበሰቡ ያስተማራቸው ሲሆን እንደሚከተለውም ብሏቸዋል:- “ይሰሙና አምላካችሁን እግዚአብሔርን መፍራት ይማሩ ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ በጥንቃቄ እንዲከተሉ ሕዝቡን . . . ሰብስብ። . . . ይህን ሕግ የማያውቁት ልጆቻቸውም መስማትና አምላካችሁን እግዚአብሔርን መፍራት ሊማሩ ይገባቸዋል።”ዘዳግም 31:12, 13

12 ዛሬም በተመሳሳይ፣ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር የሚሰበሰቡበት ዋነኛ ዓላማ ለመስማትና ለመማር ነው። ልጆች ትኩረት ሰጥተው መከታተልና መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መረዳት ከጀመሩ በስብሰባ ላይ አጠር ያሉ ሐሳቦችን በመስጠት ስለ እምነታቸው ‘መመስከር’ ይችላሉ። (ሮሜ 10:10) አንድ ትንሽ ልጅ ለተጠየቀው ጥያቄ እርሱ የተረዳውን ያህል ጥቂት ሐሳብ በመስጠት እንዲህ ማድረግ ሊጀምር ይችላል። በመጀመሪያ ላይ መልስ የሚሰጠው በማንበብ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ቀስ በቀስ ሐሳቡን በራሱ አባባል ለመግለጽ ይሞክራል። ይህ ደግሞ ለልጁ ጠቃሚና አስደሳች ይሆንለታል፤ ከዚህም ባሻገር እምነቱን በራሱ አባባል ሲገልጽ የሚሰሙትን ትላልቅ ሰዎች ልብ ደስ ያሰኛል። ወላጆች ራሳቸው ሐሳብ በመስጠት ረገድ ምሳሌ መሆን እንዳለባቸው እሙን ነው። የሚቻል ከሆነ ልጆች የራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ፣ መዝሙር መጽሐፍና የሚጠናው ጽሑፍ ቅጂ ቢኖራቸው ጥሩ ነው። ለእነዚህ ጽሑፎች ተገቢ አክብሮት ማሳየት እንዳለባቸው ሊማሩ ይገባል። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ልጆች ስብሰባዎች ቅዱስ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ያስችሏቸዋል።

13. በስብሰባዎቻችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኙ ሰዎችን በተመለከተ ምኞታችን ምንድን ነው?

13 እውነት ነው፣ ስብሰባዎቻችን ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ጋር እንዲመሳሰሉ አንፈልግም። ይህም ሲባል ቅዝቅዝ ያሉና ሞቅ ያለ የወዳጅነት ስሜት የማይንጸባረቅባቸው እንዲሁም ኮሽታ እንኳ የማይሰማባቸው ወይም አጉል መመጻደቅ የሚታይባቸው እንዲሆኑ አንፈልግም ማለት ነው። አሊያም ደግሞ በሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ እንደሚታየው ጫጫታና ሁካታ የበዛባቸው እንዲሆኑም አንፈልግም። በመንግሥት አዳራሾቻችን ውስጥ የምናደርጋቸው ስብሰባዎች የፍቅር ስሜት የሚንጸባረቅባቸውና ማራኪ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፤ ይህ ሲባል ግን የመዝናኛ ክበብ እስኪመስል ድረስ ዘና እንላለን ማለት አይደለም። የምንሰበሰበው ይሖዋን ለማምለክ ነው፤ በመሆኑም ስብሰባዎቻችን ምንጊዜም ክብር የተላበሱ ሊሆኑ ይገባል። ምኞታችን፣ በስብሰባዎች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኙ ሰዎች የሚሰጠውን ትምህርት ካዳመጡ እንዲሁም የእኛንና የልጆቻችንን ባሕርይ ከተመለከቱ በኋላ “እግዚአብሔር በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” ሲሉ መስማት ነው።—1 ቆሮንቶስ 14:25

ቋሚ የሆነው የአምልኮታችን ክፍል

14, 15. (ሀ) ‘የአምላካችንን ቤት ቸል ከማለት’ የምንርቀው እንዴት ነው? (ለ) ኢሳይያስ 66:23 ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

14 ቀደም ሲል እንደተገለጸው ይሖዋ ሕዝቦቹ እንዲሰበሰቡና በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ማለትም ‘በጸሎት ቤቱ’ ውስጥ ደስ እንዲላቸው እያደረገ ነው። (ኢሳይያስ 56:7) ታማኙ ሰው ነህምያ አይሁዳውያን ወንድሞቹ ቁሳዊ እገዛ በማድረግ ለቤተ መቅደሱ ተገቢውን አክብሮት እንዲያሳዩ አሳስቧቸዋል። ነህምያ “እኛም የአምላካችንን ቤት ቸል አንልም” ብሏል። (ነህምያ 10:39) እኛም ይሖዋ ‘በጸሎት ቤቱ’ ውስጥ ተገኝተን እንድናመልከው ያቀረበልንን ግብዣ ችላ ማለት የለብንም።

15 ነቢዩ ኢሳይያስ ለአምልኮ አንድ ላይ አዘውትረን መሰብሰባችን ያለውን አስፈላጊነት ሲገልጽ “‘ከአንዱ ወር መባቻ እስከ ሌላው፣ እንዲሁም ከአንዱ ሰንበት እስከ ሌላው፣ የሰው ልጅ ሁሉ በፊቴ ሊሰግድ ይመጣል’ ይላል እግዚአብሔር” በማለት ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 66:23) ይህ ትንቢት በዛሬው ጊዜ በመፈጸም ላይ ነው። ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች ዘወትር ይኸውም በወር ውስጥ በየሳምንቱ ይሖዋን ለማምለክ አንድ ላይ ይገናኛሉ። ይህን ከሚያደርጉባቸው መንገዶች መካከል በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መገኘትና ለሕዝብ በሚሰጠው ምሥክርነት መካፈል ይገኙበታል። አንተስ አዘውትረው ‘ከሚመጡትና በይሖዋ ፊት ከሚሰግዱት’ መካከል ነህ?

16. አዘውትሮ መሰብሰብ የሕይወታችን ቋሚ ክፍል መሆን ያለበት ለምንድን ነው?

16 ኢሳይያስ 66:23 ይሖዋ ቃል በገባው አዲስ ዓለም በሚኖረው ሕይወት ውስጥ ሙሉ ፍጻሜውን ያገኛል። በዚያን ጊዜ “የሰው ልጅ ሁሉ” ቃል በቃል ከሳምንት እስከ ሳምንት፣ ከወር እስከ ወር ለዘላለሙ በይሖዋ ‘ፊት ለመስገድ ይመጣል’ ወይም እርሱን ያመልካል። ይሖዋን ለማምለክ አንድ ላይ መሰብሰብ በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ የመንፈሳዊ ሕይወታችን ቋሚ ክፍል የሚሆን ከሆነ ቅዱስ በሆኑት ስብሰባዎቻችን ላይ አዘውትሮ መገኘቱን በአሁኑ ጊዜም የሕይወታችን ክፍል ማድረግ አይገባም?

17. ‘ቀኑ በቀረበ መጠን አብልጠን’ መሰብሰባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

17 መጨረሻው እየቀረበ በመጣ መጠን ይሖዋን ለማምለክ በምንገናኝባቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ለመገኘት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። ቅዱስ ለሆኑት ስብሰባዎቻችን ያለን አክብሮት በሰብዓዊ ሥራ፣ በትምህርት ቤት በሚሰጠው የቤት ሥራ ወይም በማታ ትምህርት ምክንያት ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ዘወትር መሰብሰባችንን ችላ እንዳንል ሊያደርገን ይገባል። አብሮ መሰብሰብ የሚያስገኘው ጥንካሬ ለሁላችንም ያስፈልገናል። የጉባኤ ስብሰባዎች እርስ በርሳችን በደንብ እንድንተዋወቅ፣ እንድንበረታታ እንዲሁም ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ’ እንድንነቃቃ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይከፍቱልናል። ‘ቀኑ ሲቀርብ እያየን አብልጠን’ እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። (ዕብራውያን 10:24, 25 የ1954 ትርጉም) እንግዲያው አዘውታሪ ተሰብሳቢ በመሆን፣ በተገቢ ሁኔታ በመልበስና ጥሩ ባሕርይ በማሳየት ቅዱስ ለሆኑት ስብሰባዎቻችን ምንጊዜም አክብሮት እንዳለን እናሳይ። እንዲህ በማድረግ ይሖዋ ለቅዱስ ነገሮች ያለውን አመለካከት እንደምናንጸባርቅ እናሳያለን።

ለክለሳ ያህል

• የይሖዋ ሕዝቦች የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ቅዱስ ተደርገው መታየት እንዳለባቸው ምን ይጠቁማል?

• ስብሰባዎቻችን ቅዱስ መሆናቸውን የሚያሳዩት የትኞቹ ገጽታዎች ናቸው?

• ልጆች ቅዱስ ለሆኑት ስብሰባዎች አክብሮት እንዳላቸው ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

• አዘውትሮ በስብሰባ ላይ መገኘትን የሕይወታችን ቋሚ ክፍል እንዲሆን ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የትም ቦታ ይካሄዱ ይሖዋን ለማምለክ የምናደርጋቸው ስብሰባዎች ቅዱስ ናቸው

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች በስብሰባዎች ላይ የሚገኙት ለማዳመጥና ለመማር ነው