በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን ለማወደስ በአንድነት መገንባት

አምላክን ለማወደስ በአንድነት መገንባት

አምላክን ለማወደስ በአንድነት መገንባት

ከሰሎሞን ደሴቶች በአንዷ ላይ የሚኖሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ሲገነቡ ተመለከቱ። ከእነርሱም መካከል አንዲት ሴት እንዲህ በማለት ጠይቃ ነበር:- “በእኛ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እርዳታ ለማሰባሰብ የተለያዩ ነገሮች ይደረጋሉ። አባሎቻችንንም ገንዘብ እንዲያዋጡ እንጠይቃቸዋለን፤ ነገር ግን እስካሁን አዲስ ቤተ ክርስቲያን ለመገንባት የሚያስችል ገንዘብ ማግኘት አልቻልንም። እናንተ የይሖዋ ምሥክሮች ገንዘቡን የምታገኙት ከየት ነው?” የተጠየቀችውም የይሖዋ ምሥክር “እኛ ይሖዋን የምናመልከው በመላው ዓለም እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነን ነው። በዓለም ዙሪያ ያሉት ጉባኤዎችም ሆኑ ወንድሞች አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ለመገንባት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ያዋጣሉ። ይሖዋ በሁሉም ነገር አንድ እንድንሆን አስተምሮናል” በማለት መለሰችላት።

የይሖዋ ምሥክሮች በሺህ የሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾችን መገንባትን ጨምሮ በሚያከናውኗቸው በሌሎች ነገሮች ሁሉ አንድነት አላቸው። እንዲህ ያለው ግንባታ ሲካሄድ ይህን መሰሉን አንድነት መመልከት አዲስ ነገር አይደለም። በአምላክ ሕዝቦች መካከል በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት የኖረ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

የማደሪያው ድንኳንና የቤተ መቅደሱ ግንባታ

ከ3,500 ዓመት በፊት ይሖዋ እስራኤላውያን “መቅደስ እንዲሠሩልኝ አድርግ” በማለት ለሙሴ ነግሮት ነበር። (ዘፀአት 25:8) አክሎም የሚሠራውን ግንባታ ንድፍ በተመለከተ ይሖዋ “ማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ ያለውን ዕቃ ሁሉ ልክ እኔ በማሳይህ ዕቅድ መሠረት ሥሩት” በማለት ተናገረ። (ዘፀአት 25:9) ከዚያም ይሖዋ ስለ ዋናው መቅደስ አሠራር፣ በውስጡ ስለሚገቡት ዕቃዎች እንዲሁም ስለማጋጊያጫዎቹ ዝርዝር መመሪያ ሰጠው። (ዘፀአት 25:10 እስከ 27:19) “ማደሪያው” ወይም ድንኳኑ ለሁሉም እስራኤላውያን የእውነተኛ አምልኮ ማዕከል ሆኖ ያገለግል ነበር።

ምንም እንኳ በሥራው ላይ የተሳተፉት ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ ባናውቅም ሁሉም እስራኤላውያን ሥራውን እንዲደግፉ ተጋብዘው ነበር። ሙሴ “ካላችሁ ንብረት ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት [“መዋጮ፣” NW] አቅርቡ፤ ፈቃደኛ የሆነ ማንም ለእግዚአብሔር . . . ያምጣ” በማለት ነገራቸው። (ዘፀአት 35:4-9) የእስራኤላውያን ምላሽ ምን ይመስል ነበር? ዘፀአት 36:3 እንዲህ በማለት ይናገራል:- “የመቅደሱን የግንባታ ሥራ ለማከናወን እስራኤላውያን ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ከሙሴ ተቀበሉ፤ ሕዝቡ የበጎ ፈቃድ ስጦታዎችን በየማለዳው ማምጣታቸውን ቀጠሉ።”

ወዲያውኑ በጣም ብዙ የስጦታ ዕቃዎች የተከመሩ ቢሆንም ሕዝቡ ማምጣቱን አላቆመም ነበር። የመቅደሱን ሥራ ያከናውኑ የነበሩ ባለሙያዎች ለሙሴ “ሕዝቡ እግዚአብሔር እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከበቂ በላይ እያመጡ ነው” በማለት ነገሩት። በመሆኑም ሙሴ “ማንም ወንድ ወይም ሴት ለመቅደሱ ሌላ ምንም ስጦታ ማድረግ የለበትም” የሚል ትእዛዝ አስተላለፈ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? “ሥራውን ሁሉ ለማከናወን በእጃቸው ያለው ከበቂ በላይ ነበረ።”—ዘፀአት 36:4-7

እስራኤላውያን ባሳዩት ልግስና ምክንያት የማደሪያው ድንኳን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀቀ። (ዘፀአት 19:1፤ 40:1, 2) የአምላክ ሕዝቦች እውነተኛውን አምልኮ በመደገፍ ይሖዋን ያከብራሉ። (ምሳሌ 3:9) እስራኤላውያን ወደፊት ከዚህ የበለጠ ስፋት ያለው የግንባታ ፕሮጀክት ይጠብቃቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ሙያ ይኑራቸውም አይኑራቸውም ፍላጎት ያላቸው ሁሉ በግንባታ ፕሮጀክቱ መካፈል ይችላሉ።

እስራኤላውያን የማደሪያ ድንኳኑን ከገነቡ ከአምስት መቶ ዓመታት በኋላ ለማለት ይቻላል በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ መገንባት ጀመሩ። (1 ነገሥት 6:1) በጣም ድንቅ የሆነው ይህ ቤተ መቅደስ እንደ ማደሪያው ድንኳን ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን ከድንጋይና ከእንጨት የሚሠራ ቋሚ ሕንጻ ይሆናል። (1 ነገሥት 5:17, 18) ይሖዋ የቤተ መቅደሱን የግንባታ ንድፍ ‘በመንፈስ ቅዱስ’ አማካኝነት ለዳዊት ሰጠው። (1 ዜና መዋዕል 28:11-19) ነገር ግን የግንባታውን ሥራ እንዲያካሂድ የመረጠው የዳዊትን ልጅ ሰሎሞንን ነበር። (1 ዜና መዋዕል 22:6-10) ዳዊት ግንባታውን በሙሉ ልቡ ደግፏል። የከበሩ ድንጋዮችን፣ እንጨቶችንና ሌሎች የግንባታ ቁሳቁሶችን እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅና ብር በስጦታ አበርክቶ ነበር። በተጨማሪም “ከእናንተስ መካከል በፈቃዱ ለእግዚአብሔር በልግሥና የሚሰጥ ሌላ ማን አለ?” በማለት ሌሎች እስራኤላውያንን ለጋሶች እንዲሆኑ አበረታቷቸዋል። ሕዝቡ ምን ዓይነት ምላሽ ሰጠ?—1 ዜና መዋዕል 29:1-5 የ1980 ትርጉም

ሰሎሞን የቤተ መቅደሱን ግንባታ በጀመረበት ወቅት በሺህ ቶን የሚቆጠር ወርቅና ብር ነበረው። እንዲሁም እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ሊመዘን የማይቻል ናስና ብረት ነበር። (1 ዜና መዋዕል 22:14-16) በይሖዋ እርዳታና ሁሉም እስራኤላውያን ባደረጉት ድጋፍ ግንባታው በሰባት ዓመት ተኩል መጠናቀቅ ችሏል።—1 ነገሥት 6:1, 37, 38

‘የአምላክ ቤት’

የማደሪያ ድንኳኑም ሆነ ቤተ መቅደሱ “የእግዚአብሔር ቤት” ተብለው ተጠርተዋል። (መሳፍንት 18:31፤ 2 ዜና መዋዕል 24:7) ይሖዋ መጠለያ ቤት በፍጹም አያስፈልገውም። (ኢሳይያስ 66:1) እነዚህ ግንባታዎች እንዲካሄዱ ያደረገው ለሰው ልጆች ጥቅም ሲል ነው። በእርግጥም ሰሎሞን ቤተ መቅደሱ በተመረቀበት ወቅት “አምላክ በእርግጥ በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማይ፣ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ እንኳ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምኑ ሊበቃ!” በማለት ጠይቆ ነበር።—1 ነገሥት 8:27

ይሖዋ በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል “ቤቴ፣ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራልና” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 56:7) በቤተ መቅደሱ የሚቀርበው መሥዋዕትም ሆነ ጸሎት እንዲሁም በዚያ የሚከናወኑት ሌሎች ሥነ ሥርዓቶች አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው ሰዎች አይሁዳዊም ሆኑ አልሆኑ ወደ እውነተኛው አምላክ እንዲቀርቡ ያስችሏቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች በቤቱ በማምለካቸው ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት ከመመሥረታቸውም በላይ ጥበቃ አግኝተዋል። ሰሎሞን ቤተ መቅደሱ ለይሖዋ አገልግሎት በተወሰነበት ወቅት ያቀረበው ጸሎት ይህንን እውነታ ግልጽ ያደርገዋል። ለአምላክ ያቀረበውን ይህን ልብ የሚነካ ጸሎት በ1 ነገሥት 8:22-53 እና በ2 ዜና መዋዕል 6:12-42 ላይ ማንበብ ትችላለህ።

ይህ የእውነተኛው አምላክ ጥንታዊ ቤት ከጠፋ ረጅም ዘመን አስቆጥሯል፤ ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ብዙ ሰዎች እጅግ በሚበልጠው መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ይሖዋን ለማምለክ የሚሰበሰቡበት ጊዜ እንደሚመጣ ይጠቁማል። (ኢሳይያስ 2:2) ጥንት በቤተ መቅደሱ ይቀርብ በነበረው የእንስሳ መሥዋዕት የተተካው የአምላክ አንድያ ልጅ የከፈለው ፍጹም መሥዋዕት ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚያስችል መንገድ ሆኖ ያገለግላል። (ዮሐንስ 14:6፤ ዕብራውያን 7:27፤ 9:12) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን እንዲህ ባለው የላቀ መንገድ እያመለኩት ሲሆን ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ በመርዳት ላይ ይገኛሉ።

በዘመናችን የሚካሄዱ የግንባታ ፕሮጀክቶች

በዓለም ዙሪያ የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛውን አምላክ በማገልገል ላይ ናቸው። እንዲሁም ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ “ብርቱ ሕዝብ” እየሆኑ ነው። (ኢሳይያስ 60:22 የ1954 ትርጉም) የይሖዋ ምሥክሮች ዋነኛ የመሰብሰቢያ ቦታ የመንግሥት አዳራሽ ነው። a በሺህ የሚቆጠሩ እነዚህ አዳራሾች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ ያስፈልጋሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች አስፈላጊ የሆኑትን እነዚህን የመንግሥት አዳራሾች ለመገንባት ራሳቸውን ‘በፈቃዳቸው’ ያቀርባሉ። (መዝሙር 110:3) ይሁን እንጂ በአብዛኛው እንደሚታየው የመንግሥት አዳራሽ በሚገነባባቸው አካባቢዎች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የግንባታ እውቀት የሚጎድላቸው ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ እድገት ያለባቸው አንዳንዶቹ ቦታዎች ከባድ ድህነት የሚያጠቃቸው ናቸው። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ይህን ችግር ለመቅረፍ በ1999 የመንግሥት አዳራሽ ግንባታን ለማገዝ የሚያስችል አንድ ፕሮግራም አቋቋመ። በዚህ ፕሮግራም መሠረት የግንባታ ሙያ ያላቸው ወንድሞች ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ተጉዘው ችሎታው ለሌላቸው ወንድሞችና እህቶች ማሠልጠኛ ሰጥተዋል። እነዚህ የሠለጠኑ ወንድሞች ደግሞ ባሉበት አካባቢ የመንግሥት አዳራሽ መገንባታቸውን ቀጥለዋል። በዚህ ልዩ ጥረት ምን ውጤት ተገኘ?

የይሖዋ ምሥክሮች የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች ውስጥ እስከ የካቲት 2006 ድረስ ከ13,000 በላይ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት ችለዋል። በእነዚህ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች እየተጠቀሙ ያሉ አንዳንድ ወንድሞች የሰጡትን አስተያየት ተመልከት።

“የጉባኤው አማካይ የተሰብሳቢ ቁጥር 160 ነበር። አዲሱ የመንግሥት አዳራሽ ከተገነባ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ስብሰባ ላይ የተሰብሳቢው ቁጥር ወደ 200 ከፍ አለ። በአሁኑ ጊዜ ማለትም ከስድስት ወራት በኋላ ተሰብሳቢው 230 ደርሷል። ይሖዋ ልከኛና ምቹ የሆኑትን የእነዚህን የመንግሥት አዳራሾች ግንባታ እንደባረከ ግልጽ ነው።”—በኢኳዶር ያለ የወረዳ የበላይ ተመልካች

“ሰዎች ለዓመታት፣ ‘በጽሑፎቻችሁ ላይ እንደሚታየው ያለ የመንግሥት አዳራሽ የሚኖራችሁ መቼ ነው?’ እያሉ ይጠይቁን ነበር። ለይሖዋ ምሥጋና ይግባውና በመጨረሻ ላይ ተስማሚ የሆነ የማምለኪያ ቦታ ማግኘት ችለናል። ስብሰባዎችን የምናደርገው በአንድ ወንድም መጋዘን ውስጥ የነበረ ሲሆን ያኔ አማካይ የተሰብሳቢ ቁጥር 30 ነበር። በአዲሱ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንሰበሰብ 110 ሰዎች ተገኝተዋል።”—በኡጋንዳ የሚገኝ ጉባኤ

“የዘወትር አቅኚ የሆኑ ሁለት እህቶች የመንግሥት አዳራሽ ከተገነባ ወዲህ አገልግሎት ይበልጥ አስደሳች እንደሆነላቸው ሪፖርት አድርገዋል። ሰዎች ከቤት ወደ ቤት ስንሰብክም ሆነ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በምንሰጥበት ወቅት ለመስማት ይበልጥ ፈቃደኞች ሆነዋል። እነዚህ እህቶች በአሁኑ ጊዜ 17 ጥናቶች የሚመሩ ሲሆን ከጥናቶቻቸው መካከል አብዛኛዎቹ በስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ።”—የሰሎሞን ደሴቶች ቅርንጫፍ ቢሮ

“በአዲሱ የመንግሥት አዳራሽ አቅራቢያ የሚኖሩ አንድ ፓስተር አዳራሹ ለሠፈሩ ክብር እንደጨመረለት እንዲሁም የአካባቢው ሰው እንደሚኮራበት ተናግረዋል። በዚያ የሚያልፉ ብዙ ሰዎች ስለ መንግሥት አዳራሹ ውበት ይናገራሉ። ይህም ወንድሞች ለመመሥከር የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። በጣም ብዙ ሰዎችም እኛ ስላለን ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ለማወቅ ይፈልጋሉ። ለዓመታት ስብሰባ ላይ መገኘት አቁመው የነበሩ ብዙ ሰዎች አሁን አዘውትረው መሰብሰብ ጀምረዋል።”—የማያንማር ቅርንጫፍ ቢሮ

“አንዲት እህት ፍላጎት ያሳየን አንድ ሰው በአቅራቢያው እየተካሄደ ወዳለ የግንባታ ቦታ ጋበዘችው። ግለሰቡም በኋላ ላይ እንዲህ ሲል ተናግሯል ‘ሠራተኞቹ ያስገቡኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር። የሚገርመው ምሥክሮቹ በደግነት ሰላም አሉኝ። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ምንም ጊዜ ሳያባክኑ በትጋት ይሠራሉ። እርስ በርስ የሚስማሙ ከመሆናቸውም በላይ ጥሩ መንፈስ ይታይባቸዋል።’ ይህ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጀመረ ሲሆን በስብሰባዎች ላይም ይገኛል። ከጊዜ በኋላ እንዲህ በማለት ተናግሯል ‘አስተሳሰቤ ተቀይሯል፤ ያገኘሁትን አምላክ አልተወውም።’”—የኮሎምቢያ ቅርንጫፍ ቢሮ

የኛ ድጋፍ አስፈላጊ ነው

የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት ለይሖዋ ከምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት ዓበይት ክፍሎች መካከል አንዱ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በገንዘብም ሆነ በሌላ መንገድ በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ ለመደገፍ የሚያደርጉት ጥረት የሚያስመሰግናቸው ነው። የቅዱስ አገልግሎት ሌሎች ገጽታዎችም ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸው መዘንጋት የለብንም። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች የተፈጥሮ አደጋ ሰለባ ስለሚሆኑ በዚህም ወቅት የእኛን እርዳታ ይፈልጋሉ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማተም እያቀረብን ያለነውን ቅዱስ አገልግሎት በማገዝ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ብዙዎቻችን ጥሩ አመለካከት ባላቸው ሰዎች እጅ የገቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መጽሔቶች ወይም መጽሐፎችን ምን ያህል ኃይል እንዳላቸው ማስተዋል ችለናል። በተጨማሪም ሚስዮናውያንንና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ የተሠማሩ ሌሎች ወንድሞችንና እህቶችን መርዳት በጣም አስፈላጊ ነው። እነዚህ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደረጉ ክርስቲያኖች በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የስብከቱ ሥራ እንዲስፋፋ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።

ቤተ መቅደሱ በተገነባበት ወቅት ስጦታ ያመጡ ሰዎች በጣም ተደስተው ነበር። (1 ዜና መዋዕል 29:9) በዛሬውም ጊዜ ቢሆን መዋጮ በማድረግ እውነተኛውን አምልኮ መደገፋችን ደስታ ያስገኝልናል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) የመንግሥት አዳራሽ ግንባታን ለማገዝ ታስቦ በተዘጋጀ የመዋጮ ሣጥን ውስጥ ገንዘብ ስንከትም ሆነ ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ስናደርግ እንዲህ ያለውን ደስታ እናገኛለን። እንዲህ ያለውን መዋጮ ማድረጋችን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከመስበክ ጋር የተያያዙ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ ያስችለናል። የይሖዋ ምሥክሮች በዛሬው ጊዜ በእውነተኛ አምልኮ በሚያስደንቅ ሁኔታ አንድ ሆነዋል። ሁላችንም ይህን እውነተኛ አምልኮ በመደገፍ ደስተኞች እንሁን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “የመንግሥት አዳራሽ” የሚለውን ስም አመጣጥ ለመረዳት የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ገጽ 319 ተመልከት።

[በገጽ 20 እና 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

አንዳንዶች መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች

ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረጉ መዋጮዎች

ብዙዎች “ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩት የተወሰነ ገንዘብ ያስቀምጣሉ ወይም ይመድባሉ።

ጉባኤዎች የተዋጣውን ገንዘብ በአገራቸው ሥራውን ለሚቆጣጠረው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ በየወሩ ይልካሉ። ከዚህ በተጨማሪ በፈቃደኝነት የሚደረጉ የገንዘብ መዋጮዎችን በቀጥታ Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, c/o Office of the Secretary and Treasurer, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአገራችሁ ለሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ቼኮች “ለይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት። ከውድ ማዕድናት የተሠሩ ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም መስጠት ይቻላል። የተላከው ዕቃ ሙሉ በሙሉ ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ ተያይዞ መላክ ይኖርበታል።

ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ የሚሰጥበት ዝግጅት

አንድ ሰው የሰጠው ገንዘብ እንዲመለስለት ከፈለገ መልሶ ሊያገኝ የሚችልበትን ልዩ ዝግጅት በማድረግ መስጠት ይችላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከላይ በተገለጸው አድራሻ መጠየቅ ይቻላል።

በእቅድ የሚደረግ ስጦታ

ገንዘብ በስጦታ ከመለገስና ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ከመስጠት በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ መደገፍ የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ይህም የሚከተሉትን ያጠቃልላል:-

ኢንሹራንስ:- የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሕይወት ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል።

የባንክ ሒሳብ:- የአገሩ ባንክ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል።

አክሲዮኖችና ቦንዶች:- አክሲዮኖችንና ቦንዶችን በስጦታ መልክ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር መስጠት ይቻላል።

የማይንቀሳቀስ ንብረት:- ሊሸጥ ሊለወጥ የሚችል ቋሚ ንብረት በስጦታ መስጠት ወይም መኖሪያ ቤት በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ባለ ንብረቱ በሕይወት እስካለ ድረስ ተጠቅሞበት ከዚያ በኋላ ማውረስ ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ከማዛወሩ በፊት በአገሩ ከሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር መነጋገር ይኖርበታል።

የስጦታ አበል:- የስጦታ አበል አንድ ሰው ገንዘቡን ወይም የባለቤትነት መብትን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ለማዛወር የሚያደርገውን ዝግጅት ያመለክታል። በምላሹም ለጋሹ ወይም እርሱ የወከለው ግለሰብ በሕይወት እስካለበት ጊዜ ድረስ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በየዓመቱ በአበል መልክ ይከፈለዋል። ለጋሹ የስጦታ አበሉን ለማስተላለፍ ከተስማማበት ጊዜ አንስቶ የገቢ ግብር ቅናሽ ያገኛል።

ኑዛዜዎችና አደራዎች:- ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተቀባይነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በውርሻ ሊሰጥ ወይም ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዘዋወር ይችላል። አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች አሉ።

“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች በሰጪው በኩል እቅድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያሳያሉ። የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ ሥራ በእቅድ በሚደረግ ስጦታ ለመደገፍ ለሚፈልጉ ግለሰቦች ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ዓለም አቀፉን የመንግሥት ሥራ ለመደገፍ በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር በእንግሊዝኛና በስፓንኛ ተዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ስጦታዎችን፣ ኑዛዜዎችንና አደራዎችን በተመለከተ ለቀረቡት በርካታ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ታስቦ ነው። በተጨማሪም ብሮሹሩ ከማይንቀሳቀስ ንብረት፣ ከገንዘብና ከቀረጥ ክፍያ ጋር በተያያዘ እቅድ ማውጣትን አስመልክቶ ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ መረጃዎችን የያዘ ነው። ከዚህም ሌላ ብሮሹሩ ሰዎች ስጦታ ለመስጠት ወይም በሚሞቱበት ጊዜ በኑዛዜ ውርስ ለመተው የሚችሉባቸውን መንገዶች ይጠቁማል። ይህን ብሮሹር ካነበቡ በኋላ ከራሳቸው የሕግ ወይም የባጀት አማካሪዎችና በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ ከሚከታተለው ቢሮ ጋር በመማከር ብዙዎች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ለመርዳት ከመቻላቸውም በላይ እንዲህ ማድረጋቸው ከቀረጥ ጋር በተያያዘ የተሻለ ጥቅም እንዲያገኙ የሚያስችል ሁኔታ ፈጥሯል። ይህን ብሮሹር ለማግኘት በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ የሚከታተለውን ቢሮ በቀጥታ መጠየቅ ይቻላል።

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከታች ያለውን አድራሻ ተጠቅመህ ወይም በአገርህ ለሥራው አመራር ለሚሰጠው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ በመጻፍ ወይም በመደወል መጠየቅ ትችላለህ።

Charitable Planning Office

Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania

100 Watchtower Drive,

Patterson, New York 12563-9204

ስልክ፦ (845) 306-0707

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምናደርገው የተባበረ ጥረት በዓለም ዙሪያ የሚያምሩ የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት አስችሏል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጋና የሚገኝ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ