የመክብብ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የመክብብ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የእምነት አባት የሆነው ኢዮብ “ከሴት የተወለደ ሰው፣ ዘመኑ አጭርና በመከራ የተሞላ ነው” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 14:1) አጭር የሆነውን ዕድሜያችንን አላስፈላጊ በሆኑ ጭንቀቶችና እንቅስቃሴዎች እንዲባክን አለማድረጋችን ወሳኝ ነገር ነው! ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ሀብታችንን ማዋል የሚኖርብን ለየትኞቹ እንቅስቃሴዎች ነው? ከየትኞቹ እንቅስቃሴዎችስ መቆጠብ ይኖርብናል? የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩት ጥበብ ያዘሉ ቃላት በዚህ ጉዳይ ላይ አስተማማኝ መመሪያ ይሰጡናል። ቃላቱ የሚያስተላልፉት መልእክት ‘የልብን ሐሳብና ምኞት የሚመረምር’ ከመሆኑም በላይ ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንመራ ያስችለናል።—ዕብራውያን 4:12
የመክብብ መጽሐፍ፣ በጥበቡ ስመ ጥር በሆነውና የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ በነበረው ሰሎሞን የተጻፈ ሲሆን ለሕይወት ጠቃሚ ስለሆነውም ይሁን ምንም እርባና ስለሌለው ነገር የሚናገር ተግባራዊ ምክር ይዟል። ሰሎሞን ያከናወናቸውን አንዳንድ የግንባታ ፕሮጀክቶች ስለጠቀሰ የመክብብን መጽሐፍ የጻፈው ከእውነተኛው አምልኮ ከማፈንገጡ በፊትና ግንባታውን ከጨረሰ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ መሆን ይኖርበታል። (ነህምያ 13:26) ይህም መጽሐፉ የተጻፈው ከ1000 ከክርስቶስ ልደት በፊት ቀደም ብሎ ይኸውም የ40ው ዓመት የሰሎሞን ግዛት መጨረሻ አካባቢ መሆኑን ይጠቁማል።
ከንቱ ያልሆነው ነገር ምንድን ነው?
“ከፀሓይ በታች ከሚለፋበት ተግባር ሁሉ፣ ሰው ምን ትርፍ ያገኛል?” ብሎ የጠየቀው ሰባኪው “ሁሉም ነገር ከንቱ ነው” ሲል ተናግሯል። (መክብብ 1:2, 3) “ከንቱ” እና “ከፀሓይ በታች” የሚሉት አባባሎች በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሰዋል። “ከንቱ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ትንፋሽ” ወይም “እንፋሎት” የሚል ቀጥተኛ ፍቺ ያለው ሲሆን እርባና ቢስ፣ ጊዜያዊ ወይም ዘላቂ ጥቅም የሌለው የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። “ከፀሓይ በታች” የሚለው አነጋገር ደግሞ “በዚህች ምድር ላይ” ወይም “በዚህ ዓለም ውስጥ” ማለት ነው። በመሆኑም ሰዎች የአምላክን ፈቃድ ችላ ብለው የሚሮጡለት ነገር ሁሉ ከንቱ ነው።
ሰሎሞን “ወደ እግዚአብሔር ቤት ስትሄድ እግርህን ጠብቅ” እንዲሁም ‘ለመስማት ቅረብ’ በማለት ተናግሯል። (መክብብ 5:1) ለይሖዋ አምላክ በሚቀርበው እውነተኛ አምልኮ ላይ መካፈል ከንቱ ነገር አይደለም። እንዲያውም ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት ቁልፉ ከይሖዋ ጋር ላለን ዝምድና ትኩረት መስጠት ነው።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:4-10—ተፈጥሯዊ ዑደቶች “አድካሚ” እንደሆኑ የተገለጸው ለምንድን ነው? ሰባኪው በምድር ላይ ሕይወት እንዲቀጥል ከሚያስችሉት መሠረታዊ ነገሮች መካከል ሦስቱን ይኸውም ፀሐይን፣ ነፋስንና የውኃን ዑደት ጠቅሷል። እንደ እውነቱ ከሆነ ብዙ ተፈጥሯዊ ዑደቶች ከመኖራቸውም ባሻገር እጅግ የተወሳሰቡ ናቸው። አንድ ሰው እነዚህን ዑደቶች በማጥናት ብቻ ዕድሜውን ሊጨርስ ይችላል። እንዲያም ሆኖ የተሟላ ግንዛቤ አያገኝም። በእርግጥም ይህ “አድካሚ” ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም አጭር የሆነውን ዕድሜያችንን ማለቂያ ከሌላቸው ተፈጥሯዊ ዑደቶች ጋር ማወዳደር ተስፋ አስቆራጭ ነው። ሌላው ቀርቶ አዳዲስ ነገሮችን ለመፈልሰፍ የሚደረጉት ጥረቶች እንኳ አድካሚ ናቸው። ደግሞም አዳዲስ ግኝቶች እውነተኛው አምላክ ያቋቋማቸውንና ቀደም ሲል በፍጥረት ሥራው ውስጥ የተጠቀመባቸውን ሕግጋት በመኮረጅ የተገኙ ከመሆን አያልፉም።
2:1, 2—ሳቅ “ሞኝነት” እንደሆነ የተገለጸው ለምንድን ነው? ሳቅ ለጊዜውም ቢሆን ችግራችንን እንድንረሳ ይረዳን ይሆናል። ፈንጠዝያ ደግሞ ችግራችንን አቅልለን እንድናይ ሊያደርገን ይችላል። ይሁን እንጂ ሳቅ ችግሮቻችን እንዲወገዱ አያደርግም። በመሆኑም በሳቅ አማካኝነት ደስታን ለማግኘት መሞከር “ሞኝነት” እንደሆነ ተገልጿል።
3:11—አምላክ “በጊዜው ውብ አድርጎ” የሠራው ነገር ምንድን ነው? ይሖዋ አምላክ በተገቢው ጊዜ “ውብ” ማለትም ትክክለኛና ጠቃሚ አድርጎ ከሠራቸው ነገሮች መካከል የአዳምና የሔዋን መፈጠር፣ የቀስተ ደመናው ቃል ኪዳን፣ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን፣ የዳዊት ቃል ኪዳን፣ የመሲሑ መምጣትና ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መሾሙ ይገኙበታል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በቅርቡ “ውብ” አድርጎ የሚሠራው አንድ ሌላ ነገር አለ። ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም በተገቢው ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—2 ጴጥሮስ 3:13
5:9—“ከምድሩ የሚገኘው ትርፍ ለሁሉም” የሚሆነው እንዴት ነው? በምድር የሚኖሩ ሁሉ ሕልውናቸው የተመካው ‘ምድር በምታስገኘው ትርፍ’ ማለትም በምትሰጠው ምርት ላይ ነው። የአንድ ንጉሥ ሁኔታም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። እርሱም ከእርሻው ምርት ማግኘት የሚችለው መሬቱን የሚያርሱለት አገልጋዮቹ ተግተው ሲሠሩለት ብቻ ነው።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:15:- በዛሬው ጊዜ የሚታየውን ጭቆናና ኢፍትሐዊ ድርጊት ለማስተካከል ጊዜንና ጉልበትን ማጥፋት ሞኝነት ነው። ክፋትን ጠራርጎ ማጥፋት የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው።—ዳንኤል 2:44
2:4-11:- እንደ ምሕንድስና፣ አትክልተኝነትና ሙዚቃ የመሳሰሉትን የጥበብ ሥራዎች ማከናወን አልፎ ተርፎም የድሎት ሕይወት መምራት ‘ነፋስን እንደ መከተል’ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት የማያስችሉ ከመሆናቸውም ሌላ ዘላቂ ደስታም አያመጡም።
2:12-16:- የሰው ልጆች ጥበብ የተወሰኑ ችግሮችን ለመፍታት ስለሚረዳ ከሞኝነት የላቀ ብልጫ አለው። ይሁን እንጂ ይህ ጥበብ ከሞት ጋር በተያያዘ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም። አንድ ሰው እንዲህ ዓይነት ጥበብ ያለው በመሆኑ ምክንያት ስመ ጥር ቢሆን እንኳ ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይረሳል።
2:24፤ 3:12, 13, 22:- ከድካማችን ባገኘነው ፍሬ መደሰታችን ምንም ስህተት የለውም።
2:26:- ደስታን የሚያስገኘው አምላካዊ ጥበብ የሚሰጠው ‘ይሖዋን ደስ ለሚያሰኝ ሰው’ ነው። አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ጥሩ ወዳጅነት ሳይመሠርት ይህን ጥበብ አገኛለሁ ብሎ ማሰቡ የማይመስል ነገር ነው።
3:16, 17:- በእያንዳንዱ ሁኔታ ሥር ፍትሕ ይኑር ብለን መጠበቃችን ምክንያታዊ አይደለም። በዓለማችን ላይ በሚከሰቱት ነገሮች ከመጨነቅ ይልቅ ይሖዋ ሁኔታዎችን ለማስተካከል እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ መጠበቅ ይኖርብናል።
4:4:- አንድን ከባድ ሥራ በቅልጥፍና ማከናወን እርካታ ያስገኛል። ነገር ግን ከሌሎች በልጦ ለመታየት ብቻ ተብሎ የሚሠራ ሥራ የፉክክር መንፈስ እንዲሰፍን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ የጥላቻና የቅናት ስሜት ሊፈጥር ይችላል። እኛም ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን በትጋት የምናከናውነው ከትክክለኛ የልብ ዝንባሌ በመነሳሳት ሊሆን ይገባል።
4:7-12:- ከሰዎች ጋር ያለን ዝምድና ከቁሳዊ ንብረት የላቀ ዋጋ ስላለው ሀብት ለማሳደድ ብለን ይህን ዝምድናችንን መሥዋዕት ማድረግ አይኖርብንም።
4:13:- ባለ ሥልጣን ወይም የዕድሜ ባለጠጋ መሆን ሁልጊዜ ያስከብራል ማለት አይቻልም። በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች የጥበብ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል።
4:15, 16 የ1980 ትርጉም:- የንጉሡን ቦታ የሚረከበው ወጣት መጀመሪያ ላይ ‘ስፍር ቁጥር የሌለውን ሕዝብ’ ድጋፍ ሊያገኝ ይችላል። በኋላ ላይ ግን “ስላደረገው ነገር ሁሉ የሚያመሰግነው አንድ ሰው እንኳ አይገኝለትም።” በእርግጥም ዝና በአብዛኛው የሚቆየው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው።
5:2:- ጸሎታችን የታሰበበትና ጥልቅ አክብሮት የተንጸባረቀበት ሊሆን ይገባዋል እንጂ የተንዛዛ መሆን አይኖርበትም።
5:3-7:- አንድ ሰው ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ መጨነቁ ስለ ግል ጥቅሙ ብቻ በማሰብ በቀን ቅዥት ውስጥ እንዲገባ ሊያደርገው ይችላል። በተጨማሪም ማታ በሚተኛበት ጊዜ ስለሚገላበጥና ቅዠት ስለሚበዛበት ጣፋጭ እንቅልፍ አያገኝም። አንድ ሰው ብዙ ማውራቱ በሌሎች ዘንድ እንደ ሞኝ የሚያስቆጥረው ከመሆኑም በላይ በችኮላ ለአምላክ ስዕለት እንዲሳል ሊያደርገው ይችላል። ‘እውነተኛውን አምላክ መፍራት’ ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ ይጠብቀናል።
6:1-9:- ሀብት፣ ክብርና ረጅም ዕድሜ ሌላው ቀርቶ ሰፊ ቤተሰብ ኖሮን በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በእነዚህ ነገሮች መደሰት ካልቻልን ምን ጥቅም አለው? “በምኞት ከመቅበዝበዝ” ማለትም የማይረካ ምኞትን ለማርካት ከመጣጣር ይልቅ ነገሮችን “በዐይን ማየት” ይኸውም እውነታውን ፊት ለፊት መጋፈጥ ይሻላል። ስለዚህ የተሻለው ነገር በሕይወታችን ውስጥ በምናገኛቸው አርኪ ነገሮች እየተደሰትንና ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት ጠብቀን ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች እያደረግን ‘ባለን ምግብና ልብስ’ ረክተን መኖር ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:8
ለጠቢብ ሰው የተሰጠ ምክር
ያተረፍነውን መልካም ስም ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው? ለሰብዓዊ ገዥዎችና ለምናያቸው ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ሙታን ምንም እንደማያውቁ ግልጽ ነው፤ ታዲያ የአሁኑን ሕይወታችንን እንዴት አድርገን ልንጠቀምበት ይገባል? ወጣቶች ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በጥበብ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው? ሰባኪው በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሰጠው ጠቃሚ ምክር ከመክብብ 7 እስከ 12 ባሉት ምዕራፎች ውስጥ ሰፍሮልናል።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
7:19—ጥበብ ‘ከዐሥር ገዦች’ ይልቅ ኀያል ልትሆን የቻለችው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አሥር ቁጥርን በምሳሌያዊ ሁኔታ ሙላትን ለማመልከት ይጠቀምበታል። ሰሎሞን ጥበብ አንድን ከተማ ከሚጠብቁ የተሟላ ቁጥር ካላቸው ጦረኞች ይልቅ የመጠበቅ ኃይል እንዳላት መናገሩ ነበር።
10:2—የአንድ ሰው ልብ ‘ወደ ቀኙ’ ወይም ‘ወደ ግራው’ ነው ሲባል ምን ማለት ነው? አብዛኛውን ጊዜ ቀኝ እጅ የሚያመለክተው ሞገስ ማግኘትን ስለሆነ የአንድ ሰው ልብ ወደ ቀኙ ነው ሲባል ልቡ ጥሩ ነገር እንዲያደርግ አነሳስቶታል ማለት ነው። መጥፎ ጎዳና እንዲከተል ካደረገው ደግሞ ልቡ ወደ ግራው ነው ሊባል ይችላል።
10:15—‘የሞኝ ሥራ ራሱን የሚያደክመው’ እንዴት ነው? አንድ ሰው ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ከሌለው ትጋት የተሞላበት ጥረት ቢያደርግም የረባ ውጤት አያገኝም። ከድካሙም የሚያገኘው እርካታ አይኖርም። ይህ ዓይነቱ ከፍተኛ ጥረት ራሱን ከማድከም ውጪ ምንም ትርፍ የለውም።
11:7, 8—“ብርሃን መልካም ነው፤ ፀሓይንም ማየት ለዐይን ደስ ያሰኛል” የሚለው አባባል ትርጉም ምንድን ነው? ብርሃንና ፀሐይ ለሕያዋን ፍጥረታት ደስታ ያመጣሉ። ሰሎሞን ይህን ሲል በሕይወት መኖር መልካም እንደሆነና የጨለማዎቹ ቀን ማለትም እርጅና፣ ጉልበታችንንና ኃይላችንን ከማሟጠጡ በፊት ‘መደሰት’ እንደሚገባን ማመልከቱ ነው።
11:10—“ወጣትነትና ጕብዝና” ከንቱ የሆኑት ለምንድን ነው? እነዚህ ነገሮች በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ካልዋሉ ከንቱዎች ናቸው። ምክንያቱም በወጣትነት ዕድሜ ላይ ያለው ብርታት ልክ እንደ እንፋሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠፋል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
7:6:- ተገቢ ባልሆነ ጊዜ መሳቅ ከድስት ሥር እንደሚንጣጣ የእሾኽ ማገዶ የሰዎችን ስሜት ከመረበሽ ውጪ ምንም ጥቅም የለውም። ከእንዲህ ዓይነቱ ሳቅ መቆጠብ ይኖርብናል።
7:21, 22:- ሌሎች ስለ እኛ ምን እንደሚሉ ለማወቅ ከልክ በላይ መጨነቅ አይኖርብንም።
8:2, 3፤ 10:4:- አለቃችን ወይም አሠሪያችን ሲቆጣን አሊያም ሲያርመን ራሳችንን አረጋግተን መቆየታችን የጥበብ እርምጃ ነው። እንዲህ ማድረጋችን ‘ከፊቱ ተጣድፈን ከመውጣት’ ማለትም ተቻኩለን ሥራችንን ከመልቀቅ የተሻለ ነው።
8:8፤ 9:5-10, 12:- ዓሦች መረብ ውስጥ ወይም ወፎች ወጥመድ ውስጥ የሚገቡት በድንገት እንደሆነ ሁሉ የእኛም ሕይወት ሳይታሰብ በአጭር ሊቀጭ ይችላል። ከዚህም በላይ ማንም ሰው ቢሆን በሞት ጊዜ የሕይወት እስትንፋስ እንዳይወጣ ሊያደርግም ሆነ ሞት በሰው ልጆች ላይ ከከፈተው ጦርነት ሊያመልጥ አይችልም። በዚህም ምክንያት ጊዜያችንን ያለ ሥራ ወዲያ ወዲህ እያልን ማባከን አይኖርብንም። ይሖዋ፣ ለሕይወት ከፍ ያለ ግምት እንድንሰጥና አስደሳች በሆነ መንገድ እንድንጠቀምበት ይፈልጋል። ይህን ማድረግ ከፈለግን ለይሖዋ አገልግሎት በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ መስጠት ይኖርብናል።
8:16, 17:- አምላክ ስለ ሠራው ማንኛውም ነገር ይሁን በሰው ልጆች ላይ እንዲደርሱ ስለፈቀዳቸው ሁኔታዎች እንቅልፍ አጥተን ለመመርመር ብንጥር እንኳ የተሟላ ግንዛቤ ማግኘት አንችልም። ስለተፈጸሙት መጥፎ ነገሮች መጨነቅ በሕይወታችን ውስጥ ልናገኘው የሚገባንን ደስታ ከመንጠቅ ውጪ ምንም ለውጥ አያመጣም።
9:16-18:- ብዙዎች ለጥበብ አድናቆት በሚያጡበት ጊዜም እንኳ ትልቅ ግምት ሊሰጠው ይገባል። ሞኝ ሰው በጩኸት ከሚናገራቸው ቃላት ይልቅ ብልኅ ሰው በረጋ መንፈስ የሚሰጠው ሐሳብ ተመራጭ ሊሆን ይገባል።
10:1:- ስለምንናገረውም ይሁን ስለምናደርገው ነገር ጠንቃቆች መሆን አለብን። አንድ የተከበረ ሰው ጥንቃቄ የጎደለው ድርጊት ቢፈጽም፣ ለምሳሌ ያህል ተናዶ ቢቆጣ፣ ለአንድ ጊዜ እንኳ አለልክ ቢጠጣ ወይም ለአንድ አፍታ የሥነ ምግባር ንጽሕናውን የሚያጎድፍ ተግባር ቢፈጽም የነበረውን ጥሩ ስም ያጣል።
10:5-11:- ችሎታ ሳይኖረው ሥልጣን የያዘ ሰው ሊቀናበት አይገባም። አንድ ሰው ቀላል ሥራዎችን ለማከናወን እንኳ ችሎታ የሚያንሰው መሆኑ መጥፎ ውጤት ያስከትላል። ‘ለውጤት የሚያበቃ ብልኀት’ ለማዳበር መጣጣር ግን ጠቀሜታ አለው። በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራችን የተካንን ሆነን መገኘታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
11:1, 2 NW:- ከልብ የመነጨ ልግስና ማሳየት ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን ሌሎች ለጋስ እንዲሆኑ ያነሳሳል።—ሉቃስ 6:38
11:3-6:- ስለ ወደፊቱ ጊዜ እርግጠኞች መሆን አለመቻላችን ውሳኔ በማድረግ ረገድ ቆራጦች እንዳንሆን ሊያደርገን አይገባም።
11:9፤ 12:1-7:- ወጣቶች በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ናቸው። ስለዚህ እርጅና መጥቶ ኃይላቸውን ከማሟጠጡ በፊት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን አምላክን ለማገልገል ሊጠቀሙበት ይገባል።
እኛን ለመምራት የተነገሩ “የጠቢባን ቃላት”
ሰባኪው ተመራምሮ ያገኘውንና በጽሑፍ ያሰፈረውን ‘ትክክለኛ ቃል’ እንዴት መመልከት ይኖርብናል? የሰዎች ጥበብ ከሰፈረባቸው “ብዙ መጻሕፍት” በተቃራኒ “የጠቢባን ቃላት እንደ ሹል የከብት መንጃ ናቸው፤ የተሰበሰቡ አባባሎቹም እጅግ ተቀብቅበው እንደ ገቡ ችንካሮች ሲሆኑ፣ ከአንድ እረኛ የተሰጡ ናቸው።” (መክብብ 12:10-12) “አንድ እረኛ” ከሆነው ከይሖዋ የተሰጡን የጥበብ ቃላት ‘እጅግ እንደተቀበቀበ ችካል’ ጸንተን እንድንኖር ይረዱናል።
በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር በተግባር ላይ ማዋላችን በእርግጥም ትርጉም ያለው አስደሳች ሕይወት እንድንመራ ያስችለናል። ከዚህም በላይ “እግዚአብሔርን የሚያከብሩ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎች መልካም” ይሆንላቸዋል የሚል ዋስትና ተሰጥቶናል። ስለዚህ እውነተኛውን አምላክ ‘ለመፍራትና ትእዛዛቱንም ለመጠበቅ’ ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ጸንተን እንቁም።—መክብብ 8:12፤ 12:13
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እጅግ ውብ ከሆኑት የአምላክ እጅ ሥራዎች መካከል አንዱ በተገቢው ጊዜ እውን ይሆናል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአምላክ ስጦታዎች መካከል ምግብ፣ መጠጥ እና በድካማችን ፍሬ መርካት ይገኙበታል