በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ለቅዱስ ነገሮች ያለው አመለካከት አላችሁ?

ይሖዋ ለቅዱስ ነገሮች ያለው አመለካከት አላችሁ?

ይሖዋ ለቅዱስ ነገሮች ያለው አመለካከት አላችሁ?

“ከእናንተ ማንም . . . ሴሰኛ ወይም እግዚአብሔርን የማያከብር [“ለቅዱስ ነገሮች አድናቆት የጎደለው፣” NW] ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ።”—ዕብራውያን 12:15, 16

1. የይሖዋ አገልጋዮች በአሁኑ ጊዜ ያለውን የትኛውን ዝንባሌ አያንጸባርቁም?

 ይህ ዓለም ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች ያለው አድናቆት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሄዷል። ፈረንሳዊው ሶሺዮሎጂስት ኤድገር ሞሪን እንደሚከተለው ብለዋል:- “አምላክ፣ ተፈጥሮ፣ የትውልድ አገር፣ ታሪክና ምክንያታዊነትን የመሳሰሉ ለሥነ ምግባር መሠረት የሆኑ ነገሮች ቀደም ሲል የነበራቸውን ተቀባይነት አጥተዋል። . . . ሰዎች ያሻቸውን የሥነ ምግባር ደንብ ለመከተል መርጠዋል።” ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ “የዓለምን መንፈስ” ወይም ‘በማይታዘዙት ሰዎች ላይ የሚሠራውን መንፈስ’ የሚያንጸባርቅ ነው። (1 ቆሮንቶስ 2:12፤ ኤፌሶን 2:2) ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑና ለሉዓላዊነቱ በፈቃደኝነት የሚገዙ ሰዎች ግን እንዲህ ያለውን መጥፎ አስተሳሰብ አያንጸባርቁም። (ሮሜ 12:1, 2) እንዲያውም የአምላክ አገልጋዮች ለይሖዋ በሚያቀርቡት አምልኮ፣ ቅድስና ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይገነዘባሉ። በሕይወታችን ውስጥ ቅዱስ አድርገን ልንይዛቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው? ይህ ርዕስ ለሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ቅዱስ የሆኑ አምስት ነገሮችን ያብራራል። ቀጥሎ ያለው ርዕስ ደግሞ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ቅድስና ላይ ያተኩራል። ይሁንና “ቅዱስ” የሚለው ቃል ምን ማለት ነው?

2, 3. (ሀ) ቅዱሳን መጻሕፍት የይሖዋን ቅድስና ጎላ አድርገው የሚገልጹት እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋን ስም ቅዱስ አድርገን መያዝ የምንችለው እንዴት ነው?

2 መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ “ቅዱስ” የሚለው ቃል የተለዩ መሆንን ያመለክታል። ከአምልኮ ጋር በተያያዘ “ቅዱስ” የሚለው ቃል ለተለመደ ዓላማ ከሚውሉ ነገሮች ተለይቶ የተቀመጠን ወይም የተቀደሰን ነገር ያመለክታል። ይሖዋ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ቅዱስ ነው። ‘እጅግ ቅዱስ’ ተብሎም ተጠርቷል። (ምሳሌ 9:10 NW፤ 30:3 NW) በጥንቷ እስራኤል ሊቀ ካህኑ “ቅድስና ለይሖዋ” የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት ጠፍጣፋ ወርቅ በጥምጣሙ ላይ ያደርግ ነበር። (ዘፀአት 28:36, 37 NW) በሰማይ የይሖዋን ዙፋን ከብበው የሚገኙት ኪሩቤልና ሱራፌል “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር” ማለታቸው በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተጠቅሷል። (ኢሳይያስ 6:2, 3፤ ራእይ 4:6-8) ቅዱስ የሚለው ቃል መደጋገሙ ይሖዋ ቅዱስ፣ ንጹሕና ጽዱ በመሆን ረገድ አቻ የሌለው መሆኑን ጎላ አድርጎ ይገልጻል። እንዲያውም እርሱ የቅድስና ሁሉ ምንጭ ነው።

3 የይሖዋ ስም ቅዱስ ነው። መዝሙራዊው “ታላቁንና አስፈሪውን ስምህን ይወድሱ፤ እርሱ ቅዱስ ነው” ሲል በአድናቆት ተናግሯል። (መዝሙር 99:3) ኢየሱስም “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ” ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል። (ማቴዎስ 6:9) የኢየሱስ ሰብዓዊ እናት የሆነችው ማርያም “ነፍሴ ጌታን [“ይሖዋን፣” NW] ከፍ ከፍ ታደርገዋለች። ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው” ብላለች። (ሉቃስ 1:46, 49) የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ስሙን ቅዱስ አድርገን እንመለከታለን፤ እንዲሁም በዚህ ቅዱስ ስም ላይ ነቀፋ ሊያመጣ የሚችል ማንኛውንም ድርጊት ከመፈጸም እንቆጠባለን። ከዚህም በላይ ይሖዋ ስለ ቅዱስ ነገሮች ያለውን አመለካከት እንጋራለን፣ በሌላ አባባል ይሖዋ ቅዱስ አድርጎ የሚመለከታቸውን ነገሮች እኛም ቅዱስ አድርገን እንመለከታቸዋለን።—አሞጽ 5:14, 15

ለኢየሱስ ጥልቅ አክብሮት የምናሳየው ለምንድ ነው?

4. መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ቅዱስ” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው?

4 ኢየሱስ የቅዱሱ የይሖዋ አምላክ “አንድያ ልጅ” እንደመሆኑ መጠን ቅዱስ ተደርጎ ተፈጥሯል። (ዮሐንስ 1:14፤ ቈላስይስ 1:15፤ ዕብራውያን 1:1-3) ይህም በመሆኑ “አንድያ የእግዚአብሔር ቅዱስ” ተብሏል። (ዮሐንስ 6:69) ማርያም ኢየሱስን የጸነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ስለነበር ሕይወቱ ከሰማይ ወደ ምድር በተዘዋወረበት ጊዜም ቢሆን ቅድስናውን ጠብቋል። በወቅቱ አንድ መልአክ ለማርያም “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ . . . የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” ብሏት ነበር። (ሉቃስ 1:35) በኢየሩሳሌም የነበሩት ክርስቲያኖች ለይሖዋ ባቀረቡት ጸሎት ላይ የአምላክን ልጅ “ቅዱሱ ብላቴናህ” በማለት ጠርተውታል።—የሐዋርያት ሥራ 4:27, 30

5. ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሊፈጽመው የሚገባው ቅዱስ ተልእኮ ምን ነበር? የክርስቶስ ደም ክቡር የሆነው ለምንድን ነው?

5 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሊፈጽመው የሚገባው ቅዱስ ተልእኮ ነበረው። ኢየሱስ በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተጠመቀበት ጊዜ በታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሊቀ ካህን ሆኖ እንዲያገለግል ተቀብቷል። (ሉቃስ 3:21, 22፤ ዕብራውያን 7:26፤ 8:1, 2) ከዚህም በተጨማሪ መሥዋዕታዊ ሞት መሞት ነበረበት። የፈሰሰው ደሙ ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች መዳን እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን ቤዛ አስገኝቷል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዕብራውያን 9:14) በመሆኑም የኢየሱስን ደም ቅዱስ ወይም “ክቡር” አድርገን እንመለከተዋለን።—1 ጴጥሮስ 1:19

6. ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን አመለካከት አለን? ለምንስ?

6 ጳውሎስ ንጉሥና ሊቀ ካህናችን ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥልቅ አክብሮት የምናሳየው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጒልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊልጵስዩስ 2:9-11) የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንዲሁም መሪያችንና ንጉሣችን ለሆነው ለክርስቶስ ኢየሱስ በደስታ በመገዛት ይሖዋ ለቅዱስ ነገሮች ያለው አመለካከት እንዳለን ማሳየት እችላለን።—ማቴዎስ 23:10፤ ቈላስይስ 1:18

7. ለክርስቶስ እየተገዛን መሆናችንን የምናሳየው እንዴት ነው?

7 ለክርስቶስ መገዛት በእርሱ አመራር ሰጪነት የሚካሄደውን ሥራ በመምራት ረገድ ለሚጠቀምባቸው ሰዎች ተገቢ አክብሮት ማሳየትንም ይጨምራል። በመንፈስ የተቀባው የበላይ አካልና እርሱ የሾማቸው በቅርንጫፍ ቢሮዎች፣ በአውራጃዎች፣ በወረዳዎችና በጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ የበላይ ተመልካቾች ያላቸው ኃላፊነት ቅዱስ ተደርጎ መታየት ይኖርበታል። በመሆኑም ለዚህ ዝግጅት ጥልቅ አክብሮት ማሳየትና መገዛት ይገባናል።—ዕብራውያን 13:7, 17

ቅዱስ ሕዝብ

8, 9. (ሀ) እስራኤላውያን ቅዱስ ሕዝብ የነበሩት በምን መንገድ ነው? (ለ) ይሖዋ ለእስራኤላውያን ስለ ቅድስና መሠረታዊ ሥርዓት አጽንኦት ሰጥቶ ያሳሰባቸው እንዴት ነው?

8 ይሖዋ ከእስራኤል ብሔር ጋር ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር። ይህ ቃል ኪዳን አዲሱን ብሔር ልዩ መብት አጎናጽፎታል። እስራኤላውያን የተቀደሱ ወይም የተለዩ ነበሩ። ይሖዋ ራሱ እንዲህ ብሏቸዋል:- “እናንተ ለእኔ ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፤ የኔ ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ መካከል ለይቻችኋለሁ።”—ዘሌዋውያን 19:2፤ 20:26

9 የእስራኤል ብሔር ገና እንደተቋቋመ፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ስለ ቅድስና መሠረታዊ ሥርዓት አጽንኦት ሰጥቶ አሳስቧቸዋል። ሞት ስለሚያስከትል አሥርቱ ትእዛዛት የተሰጡበትን ተራራ እንኳ እንዳይነኩ ተከልክለው ነበር። ይህም የሲና ተራራ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ቅዱስ ተደርጎ ይታይ እንደነበር ያሳያል። (ዘፀአት 19:12, 23) ከዚህም በተጨማሪ የክህነት አገልግሎቱ፣ ማደሪያውና በውስጡ ያሉት ቁሳቁሶች ቅዱስ ተደርገው መታየት ነበረባቸው። (ዘፀአት 30:26-30) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለው ሁኔታስ ምን ይመስላል?

10, 11. የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ቅዱስ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? ይህስ “በሌሎች በጎች” ላይ ምን ስሜት አሳድሯል?

10 የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ በይሖዋ ፊት ቅዱስ ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:2) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ባይሆኑም እንኳ በየትኛውም ዘመን በምድር ላይ የኖሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በቡድን ደረጃ በቅዱስ ቤተ መቅደስ ተመስለዋል። ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ይኖራል። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በእርሱ [በኢየሱስ ክርስቶስ] ሕንጻ ሁሉ አንድ ላይ ተገጣጥሞ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል። እናንተም ደግሞ እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚኖርበት ማደሪያ ትሆኑ ዘንድ አብራችሁ እየተገነባችሁ ነው።”—ኤፌሶን 2:21, 22፤ 1 ጴጥሮስ 2:5, 9

11 ከዚህም በላይ ጳውሎስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች “እናንተ ራሳችሁ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ፣ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውስጣችሁ እንደሚኖር አታውቁምን? . . . የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፤ ያም ቤተ መቅደስ እናንተ ናችሁ” በማለት ጽፎላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:16, 17) ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ከቅቡዓኑ ጋር ‘ይኖራል’ እንዲሁም ‘በመካከላቸው ይመላለሳል።’ (2 ቆሮንቶስ 6:16) ይሖዋ ታማኝ ‘ባሪያውን’ ያለ ማቋረጥ ይመራዋል። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) በመሆኑም “ሌሎች በጎች” ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደ ውድ መብት ይቆጥሩታል።—ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 25:37-40

ከክርስቲያናዊ ሕይወታችን ጋር የተያያዙ ቅዱስ ነገሮች

12. በሕይወታችን ውስጥ ቅዱስ አድርገን ልንይዛቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለምንስ?

12 በመንፈስ ከተቀቡት የክርስቲያን ጉባኤ አባላትም ሆነ ከአጋሮቻቸው ሕይወት ጋር የተያያዙ ብዙ ነገሮች ቅዱስ ተደርገው የሚታዩ መሆናቸው የሚያስገርም አይደለም። ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ቅዱስ ነው። (1 ዜና መዋዕል 28:9፤ መዝሙር 36:7) ይህን ዝምድና ውድ አድርገን ስለምንመለከተው በአምላካችን በይሖዋና በእኛ መካከል ምንም ነገር ጣልቃ እንዲገባ አንፈቅድም። (2 ዜና መዋዕል 15:2፤ ያዕቆብ 4:7, 8) ጸሎት ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን የቅርብ ዝምድና ጠብቀን እንድንኖር በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ነቢዩ ዳንኤል ጸሎትን እጅግ ቅዱስ አድርጎ ይመለከተው ስለነበር ሕይወቱ አደጋ ላይ በወደቀበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር ወደ ይሖዋ የመጸለይ ልማዱን በታማኝነት ገፍቶበታል። (ዳንኤል 6:7-11) “የቅዱሳን ጸሎት” ማለትም የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጸሎት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለአምልኮ ይቀርብ በነበረው ዕጣን ተመስሏል። (ራእይ 5:8፤ 8:3, 4፤ ዘሌዋውያን 16:12, 13) ይህ ምሳሌያዊ ንጽጽር የጸሎትን ቅድስና አጉልቶ ያሳያል። ከአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ጋር መነጋገር መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ጸሎት በሕይወታችን ውስጥ ቅዱስ አድርገን ልንመለከተው የሚገባ ነገር መሆኑ ምንም አያስገርምም!

13. ቅዱስ የሆነው ኃይል የትኛው ነው? በሕይወታችን ውስጥ እንዲሠራ የምንፈቅደውስ እንዴት ነው?

13 በቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆነ በአጋሮቻቸው ሕይወት ውስጥ ምንጊዜም ቅዱስ ተደርጎ ሊያዝ የሚገባው አንድ ኃይል አለ፤ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ነው። ይህ መንፈስ የይሖዋ ኃይል ነው፤ ከዚህም ባሻገር ዘወትር ሥራውን የሚያከናውነው ቅዱስ ከሆነው አምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መልኩ በመሆኑ “መንፈስ ቅዱስ” ወይም ‘የቅድስና መንፈስ’ ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። (ዮሐንስ 14:26፤ ሮሜ 1:4) ይሖዋ አገልጋዮቹ ምሥራቹን እንዲሰብኩ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ኃይል ይሰጣቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ 4:31) ይሖዋ “ለሚታዘዙት” እንዲሁም እንደ ሥጋ ምኞት ሳይሆን ‘በመንፈስ ለሚኖሩት’ መንፈሱን ይሰጣቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:32፤ ገላትያ 5:16, 25፤ ሮሜ 8:5-8) ይህ ታላቅ ኃይል ክርስቲያኖች “የመንፈስ ፍሬ” የሆኑትን ግሩም ባሕርያት እንዲያፈሩ እንዲሁም ‘ቅዱስና እውነተኛ መንፈሳዊነት’ ያላቸው እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። (ገላትያ 5:22, 23፤ 2 ጴጥሮስ 3:11) መንፈስ ቅዱስን እንደ ቅዱስ ነገር አድርገን የምንመለከት ከሆነ ይህን መንፈስ ከሚያሳዝን ወይም በሕይወታችን ውስጥ የሚሠራውን ሥራ ከሚያስተጓጉል ማንኛውም ድርጊት እንርቃለን።—ኤፌሶን 4:30

14. ቅቡዓኑ ቅዱስ አድርገው የሚይዙት መብት የትኛው ነው? ሌሎች በጎችስ ይህን መብት የሚጋሩት እንዴት ነው?

14 ቅዱስ አድርገን የምንመለከተው ሌላው ነገር ደግሞ የቅዱሱን አምላክ የይሖዋን ስም የመሸከምንና የእርሱ ምሥክር የመሆን መብታችንን ነው። (ኢሳይያስ 43:10-12, 15) ቅቡዓን ክርስቲያኖች “የአዲሱ ኪዳን አገልጋዮች” የመሆን ብቃታቸውን ያገኙት ከይሖዋ ነው። (2 ቆሮንቶስ 3:5, 6) በዚህ መሠረት ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ የመስበክና ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት የማድረግ’ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ቅቡዓኑ ይህን ተልእኳቸውን በተሳካ ሁኔታ በመወጣት ላይ የሚገኙ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ በግ መሰል ሰዎችም በምሳሌያዊ መንገድ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ” በማለት ለመልእክቱ በጎ ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። (ዘካርያስ 8:23) እነዚህ ቅን የሆኑ ሰዎች፣ “የአምላካችን ባሮች” ለሆኑት ለቅቡዓኑ በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘አራሾችና’ ‘የወይን ተክል ሠራተኞች’ በመሆን በደስታ ያገለግሏቸዋል። ሌሎች በጎች በዚህ መንገድ ቅቡዓኑ በምድር ዙሪያ የሚያካሂዱትን አገልግሎት ከግብ እንዲያደርሱ ከፍተኛ እገዛ ያደርጉላቸዋል።—ኢሳይያስ 61:5, 6

15. ጳውሎስ የትኛውን ተግባሩን ቅዱስ አድርጎ ይመለከተው ነበር? እኛስ እንዲህ ዓይነት አመለካከት መያዝ ያለብን ለምንድን ነው?

15 ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን ክቡር ወይም ቅዱስ አድርጎ ይመለከተው ነበር። ጳውሎስ “በእግዚአብሔር ወንጌል የክህነት ተግባር [“ቅዱስ ተግባር፣” NW]፣ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ” በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል። (ሮሜ 15:16) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሲጽፍ አገልግሎቱ “የከበረ ነገር” ወይም ውድ ሀብት መሆኑን ጠቅሷል። (2 ቆሮንቶስ 4:1, 7) በአገልግሎታችን አማካኝነት “የእግዚአብሔርን ቃል [“ቅዱስ ቃል፣” NW]” እናሳውቃለን። (1 ጴጥሮስ 4:11) በመሆኑም፣ ቅቡዓንም እንሁን ሌሎች በጎች ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ መካፈላችንን እንደ ቅዱስ መብት አድርገን እንመለከተዋለን።

አምላክን በመፍራት ቅድስናን ፍጹም ማድረግ

16. ‘ለቅዱስ ነገሮች አድናቆት የጎደለን’ ሰዎች እንዳንሆን ምን ይረዳናል?

16 ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ለቅዱስ ነገሮች አድናቆት የጎደላቸው’ እንዳይሆኑ የእምነት አጋሮቹን አስጠንቅቋቸዋል። ከዚህ ይልቅ “ለመቀደስም ፈልጉ፣” “መራራ ሥር በቅሎ ችግር እንዳያስከትልና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ” በማለት መክሯቸዋል። (ዕብራውያን 12:14-16 NW) “መራራ ሥር” የሚለው አገላለጽ በጉባኤ ውስጥ ነገሮች የሚከናወኑበትን መንገድ የሚተቹ ጥቂት ክርስቲያኖችን ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል እነዚህ ሰዎች ይሖዋ የጋብቻን ቅድስና ወይም የሥነ ምግባር ንጽሕናን አስፈላጊነት አስመልክቶ ባለው አመለካከት አይስማሙ ይሆናል። (1 ተሰሎንቄ 4:3-7፤ ዕብራውያን 13:4) ወይም ደግሞ “ከእውነት ርቀው የሚባዝኑ” ከሃዲዎች በሚናገሩት ‘በማያስከብር [“ቅዱስ የሆነውን በሚቃወም፣” NW] ከንቱ ልፍለፋ’ ላይ ይካፈሉና የከሃዲዎቹን ሐሳብ ያሰራጩ ይሆናል።—2 ጢሞቴዎስ 2:16-18

17. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይሖዋ ስለ ቅድስና ያለውን አመለካከት ለማንጸባረቅ ያልተቋረጠ ጥረት ሊያደርጉ የሚገባቸው ለምንድን ነው?

17 ጳውሎስ ለቅቡዓን ወንድሞቹ “ወዳጆች ሆይ፤ . . . ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርገው” ሲል ጽፎላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ይህ አነጋገር “የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች” የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ይሖዋ ስለ ቅድስና ያለውን አመለካከት በመላው አኗኗራቸው ለማንጸባረቅ ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ያሳያል። (ዕብራውያን 3:1) በተመሳሳይም፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ የተወለዱ ወንድሞቹን “ታዛዦች ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ። ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” በማለት አጥብቆ መክሯቸዋል።—1 ጴጥሮስ 1:14, 15

18, 19. (ሀ) ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ ይሖዋ ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች ያለውን አመለካከት ማንጸባረቅ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውስጥ ቅዱስ አድርገን የምንመለከተውን የትኛውን ነገር እንመረምራለን?

18 “ከታላቁ መከራ” ስለሚተርፉት ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦችስ’ ምን ለማለት ይቻላል? እነርሱም ቢሆኑ ይሖዋ ስለ ቅዱስ ነገሮች ያለውን አመለካከት እንደሚጋሩ ማሳየት ይገባቸዋል። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ፣ እጅግ ብዙ ሕዝቦች በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ላይ “ቅዱስ አገልግሎት” እንደሚያቀርቡ ተደርገው ተገልጸዋል። በተጨማሪም በምሳሌያዊ አገላለጽ ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል’ ይኸውም በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት አሳድረዋል። (ራእይ 7:9, 14, 15) ይህ ደግሞ በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም እንዲኖራቸው አድርጓል፤ እንዲሁም ‘ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳቸውን በማንጻትና አምላክን በመፍራት ቅድስናቸውን ፍጹም የማድረግ’ ኃላፊነት ጥሎባቸዋል።

19 ቅቡዓን ክርስቲያኖችና አጋሮቻቸው ይሖዋን ለማምለክና ቃሉን ለማጥናት አዘውትሮ መሰብሰብን በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ ይሰጡታል። ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ አንድ ላይ መሰብሰባቸውን ቅዱስ አድርጎ ይመለከተዋል። በዚህ አስፈላጊ መስክ ረገድ ይሖዋ ያለውን የቅድስና አመለካከት ማንጸባረቅ ያለብን ለምን እንደሆነና ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።

ለክለሳ ያህል

• የይሖዋ አገልጋዮች የትኛውን የዓለም አስተሳሰብ አያንጸባርቁም?

• ይሖዋን የቅዱስ ነገሮች ሁሉ ምንጭ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

• ለክርስቶስ ቅድስና አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

• በሕይወታችን ውስጥ ቅዱስ አድርገን ልንይዛቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥንቷ እስራኤል የክህነት አገልግሎት፣ ማደሪያውና በውስጡ ያሉት ቁሳቁሶች ቅዱስ ተደርገው መታየት ነበረባቸው

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቅዱስ ቤተ መቅደስ ናቸው

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጸሎትና አገልግሎት ቅዱስ መብቶች ናቸው