ይሖዋ ሚስዮናዊ ለመሆን የነበረኝን ፍላጎት አሳክቶልኛል
የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ ሚስዮናዊ ለመሆን የነበረኝን ፍላጎት አሳክቶልኛል
ሺላ ዊንፊልድ ዳ ኮንሳሶ እንደተናገረችው
በአንድ ወቅት ከአፍሪካ የመጣች አንዲት ሚስዮናዊ እህት፣ በተመደበችበት ቦታ ላሉ ሰዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በምትሰብክበት ወቅት ወደ ቤት እንድትገባ ጋብዘው በኋላ በትኩረት እንደሚያዳምጧት ነገረችን። እኔም ‘በዚህ ዓይነት የአገልግሎት ክልል ውስጥ ማገልገል በጣም የሚያጓጓ ነው!’ ብዬ አሰብኩ። ያኔ ገና 13 ዓመቴ ቢሆንም በወቅቱ የተደረገው ውይይት ሚስዮናዊ ሆኖ የማገልገል ፍላጎት በልቤ ውስጥ እንዲተከል አድርጓል።
ይሁን እንጂ ቤተሰባችን ስለ ይሖዋ መማር የጀመረው ከዚህ ቀደም ብሎ ነበር። በ1939 አንድ ቀን ጠዋት ላይ ሥርዓታማ የሆነ አለባበስ ያላቸው ሁለት ሰዎች ከታላቋ የለንደን ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው በሄመል ሄምፕስቲድ ያለውን ቤታችንን አንኳኩ። እነዚህ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። እርግጥ እኔ የተወለድኩት ይህ ከመሆኑ ከአንድ ዓመት በፊት ስለነበር ሁኔታውን አላስታውስም። እናቴ እንዲሄዱላት ስለፈለገች አባቴ ፍላጎት ሊኖረው እንደሚችል ገልጻ ነገር ግን እርሱ ከምሽቱ 3 ሰዓት በፊት እንደማይመጣ ነገረቻቸው። ይሁን እንጂ በዚያ ምሽት ተመልሰው ሲመጡ ምን ያህል ተደንቃ እንደነበር መገመት አያዳግትም! አባቴ ሄንሪ ዊንፊልድ ሰዎቹ ፖለቲካና ብሔራዊ ስሜትን በተመለከተ ያላቸው አቋም ምን እንደሆነ ካረጋገጠ በኋላ ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዛቸው፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ፈቃደኛ ሆነ። ከዚያም ፈጣን እድገት አድርጎ ተጠመቀ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ እናቴ ካትሊንም ጥናት የጀመረች ሲሆን በ1946 ተጠመቀች።
በ1948 የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ አዘውትሬ መሳተፍ ጀመርኩ። በአገልግሎት የማሳልፈውን ሰዓት በትክክል ለመመዝገብ የእጅ ሰዓት እንደሚያስፈልገኝ ተሰማኝ። በዚያ ወቅት ወላጆቻችን ጥሩ ጠባይ ካሳየን ሁልጊዜ ቅዳሜ ቅዳሜ ስድስት ፔንስ (ስድስት ሳንቲም) ለኪስ ገንዘብ ይሰጡን ነበር። በወቅቱ ርካሽ የሚባለውን
ሰዓት ለመግዛት ስል ይሰጠን የነበረውን ስድስት ፔንስ ለሁለት ዓመት ያህል አጠራቀምኩ። ይሁን እንጂ ታናሽ ወንድሜ ሬይ ሁልጊዜ ባለ ስድስት ፔንስ ድፍን ሳንቲም ሳይሆን እያንዳንዳቸው የሦስት ሣንቲም ዋጋ ያላቸው ሁለት ፔንሶች እንዲሰጠው ይጠይቅ ነበር። አንድ ቀን የሦስት ሳንቲም ዋጋ ያላቸው ሁለት ድፍን ፔንሶች ካልተሰጡኝ ብሎ ድርቅ ሲል አባቴ ተናደደ። በዚህ ጊዜ ሬይ እያለቀሰ ዝርዝር ፔንሶች እንዲሰጠው የሚፈልገው እርሱና ይሖዋ ብቻ የሚያውቁት ምስጢር ስላለ መሆኑን ተናገረ። በመጨረሻም ሬይ እንዲህ ያለ ጥያቄ የሚያቀርበው “አንደኛውን ባለ ሦስት ፔንስ ሳንቲም የመዋጮ ሣጥን ውስጥ ለመክተት ሌላኛውን ደግሞ ለራሴ ልወስደው ነው” በማለት በግልጽ ተናገረ። በዚህ ወቅት እናቴ የደስታ እንባ አነባች፤ አባቴም ወዲያውኑ እርሱ እንደሚፈልገው አድርጎ ሰጠው። እኔም ብሆን የመንግሥቱን ሥራ በገንዘብ የመደገፉን አስፈላጊነት ተማርኩ።አባቴ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ለማገልገል ዝግጅት ማድረግ የጀመረው በዚህ ጊዜ ነበር። በ1949 የእርሻ መሬቱን እንዲሁም የአሸዋና የጠጠር መሸጫ ቦታውን በመሸጥ አቅኚ ማለትም የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆነ። እኔ ደግሞ መስከረም 24, 1950 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በጥምቀት አሳየሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በበጋ ትምህርት ቤት ለእረፍት ሲዘጋ የእረፍት ጊዜ አቅኚ (በአሁኑ ጊዜ ረዳት አቅኚ የሚባለው ነው) በመሆን በየወሩ 100 ሰዓት ማገልገል ጀመርኩ። ይሁን እንጂ ይህ ጅምር ብቻ ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እውነተኛውን አምልኮ ይበልጥ ለማስፋፋት ልባዊ ፍላጎት አደረብኝ።
ሚስዮናዊ ለመሆን የነበረኝ ፍላጎት
በ1951 አባቴ በሰሜን ዴቨን ግዛት በምትገኘው ቢድፎርድ ተመደበ። እዚያ ከደረስን ከጥቂት ጊዜ በኋላ በመግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት በአፍሪካ ሚስዮናዊ ሆና የምታገለግለው እህት ወደ ጉባኤያችን መጣች። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሚስዮናዊ ለመሆን ያለኝ ፍላጎት በማደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። አስተማሪዎቼ ግቤ ምን እንደሆነ በማወቃቸው ሐሳቤን ቀይሬ ሰብዓዊ ግቦችን እንድከታተል የቻሉትን ያህል ጥረት አድርገዋል። ይሁን እንጂ ትምህርቴን የጨረስኩ ዕለት አስተማሪዎቼን ለማመስገን ብሎም ለመሰናበት ወደነበሩበት ክፍል ሄድኩ። በዚህ ጊዜ ከመካከላቸው አንዱ “እንኳን ደስ አለሽ! በሕይወትሽ ውስጥ ግብ ያወጣሽ ተማሪ አንቺ ብቻ ነሽ፤ ግብሽ ላይ እንደምትደርሺ ተስፋ እናደርጋለን” በማለት ተናገረ።
ከዚያም ብዙ ጊዜ ሳላጠፋ የግማሽ ቀን ሥራ ያዝኩና ታኅሣሥ 1, 1955 የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ቀጥሎ እናቴና ወንድሞቼም የዘወትር አቅኚዎች ሆኑ። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሁሉም የቤተሰባችን አባላት ለበርካታ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሳትፈዋል።
ወደ አየርላንድ ሄድኩ
ከአንድ ዓመት በኋላ በአየርላንድ እንዳገለግል ግብዣ ቀረበልኝ። ይህም ሚስዮናዊ የመሆን ግቤ ላይ ለመድረስ የሚያስችል አንድ እርምጃ ሆኖኛል። የካቲት 1957 ጁን ናፒየር እና ቤራል ባርከር ከተባሉ ሌሎች ሁለት ወጣት አቅኚዎች ጋር በደቡባዊ አየርላንድ ወደምትገኘው ወደ ኮርክ ደረስን።
በአየርላንድ ማገልግል በጣም አስቸጋሪ ነበር። የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይህን ሥራችንን እንዳንሠራ በጣም ትቃወመን ነበር። ወደ አንድ አፓርታማ ወይም ወደ አንድ
መንደር ስንገባ ድንገት ችግር ቢፈጠር እንኳ በየትኛው መንገድ ማምለጥ እንደምንችል አስቀድመን ለማወቅ እንጥራለን። ብስክሌቶቻችንን ከምናገለግልበት አካባቢ ትንሽ ራቅ አድርገን እንደብቅ ነበር፤ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ የሆነ ሰው የእኛ መሆናቸውን አውቆ ጎማዎቹን ይተለትልብን ወይም ያስተነፍስብን ነበር።አንድ ጊዜ እኔና ቤራል በአንድ መንደር ውስጥ ከቤት ወደ ቤት እያገለገልን እያለ ብዛት ያላቸው ልጆች በመጮህና በመሳደብ ድንጋይ ይወረውሩብን ጀመር። በዚህ ወቅት፣ ከአንድ ቤት ጋር ተያይዞ ወደተሠራ የወተት መሸጫ ሱቅ ገባን። ረብሸኞቹም ውጭ መሰባሰብ ጀመሩ። ቤራል ወተት ትወድድ ስለነበር ረብሸኞቹ ይበተኑ ይሆናል በሚል ስሜት በጣም ቀስ እያለች ሁለት ወይም ሦስት ብርጭቆ ወተት ጠጣች። ሆኖም እንዳሰበችው አልሆነም። በዚህ ጊዜ አንድ ወጣት ቄስ ወደ ሱቁ ገባ። እርሱም አገር ጎብኚዎች ስለመሰልነው አካባቢውን ሊያሳየን እንደሚፈልግ ነገርን። መጀመሪያ ግን በዚያ ቤት ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ሌላ ክፍል ይዞን ሄደ፤ እዚያም ሊሞቱ ለተቃረቡ አንድ አረጋዊ በጠና ለታመመ ሰው የሚደረገውን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት እስኪያደርግላቸው ድረስ ጸጥ ብለን ተቀመጥን፤ ሲጨርስ ከእርሱ ጋር ተያይዘን ወጣን። ረብሸኞቹም ከቄሱ ጋር እያወራን መውጣታችንን ሲመለከቱ ተበታተኑ።
ወደ ጊልያድ ተጠራሁ
በ1958 መለኮታዊ ፈቃድ የተሰኘ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ በኒው ዮርክ ተደርጎ ነበር። አባቴ ወደዚያ ለመሄድ አቅዶ ስለነበር እኔም የመሄዱ ፍላጎት አደረብኝ፤ ሆኖም ገንዘብ አልነበረኝም። በዚህ ሴት አያቴ ሳይታሰብ ሞቱ፤ እሳቸውም 100 ፖውንድ (280 የአሜሪካ ዶላር) ተናዝዘውልኝ ነበር። ስብሰባው ወደሚደረግበት ቦታ የደርሶ መልስ ትኬት ዋጋ 96 ፖውንድ ስለነበር ወዲያውኑ ተመዘገብኩ።
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካይ የሆነ አንድ ወንድም መጥቶ ለስብሰባው የምንሄደውን ልዩ አቅኚዎች በሙሉ ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብተን በሚስዮናዊነት ለመሠልጠን የምንፈልግ ከሆነ ማመልከት እንደምንችል ነገረን። ይህን ስሰማ ጆሮዬን ማመን አልቻልኩም! ይሁን እንጂ እኔ ገና ልጅ ስለነበርኩ ከእኔ በስተቀር ለሁሉም የማመልከቻውን ቅጽ ሰጣቸው። እኔም የትውልድ አገሬን ትቼ በውጭ አገር በሚስዮናዊነት እያገለገልኩኝ መሆኔን በመናገር ማመልከቻውን እንዲሰጠኝ ጠየቅሁት። ወንድም ለመሄድ መቁረጤን ተመልክቶ ፎርሙን ሰጠኝ። ተቀባይነት ማግኘት እንድችል አጥብቄ ጸለይኩ! መልሱም ቶሎ የመጣ ሲሆን ጊልያድ ገብቼ እንድማር ተጋበዝኩ።
በጣም ደስ የሚለው ከ14 አገራት ከመጡ 81 አቅኚዎች ጋር በ33ኛው ክፍል የጊልያድ ትምህርት ቤት የመካፈል መብት አገኘሁ። ኮርሱ የሚሰጥባቸው አምስት ወራት በፍጥነት አለፉ። ወደ መደምደሚያው አካባቢ ወንድም ናታን ኖር ለአራት ሰዓታት የቆየ ቀስቃሽ ንግግር አደረገልን። ነጠላ ሆነው ለመቀጠል የወሰኑ በውሳኔያቸው እንዲቀጥሉ አበረታታቸው። (1 ቆሮንቶስ 7:37, 38) ነገር ግን ወደፊት ለማግባት ለምንፈልግ፣ ተስማሚ የምንለው የትዳር ጓደኛ እንዲያሟላ የምንፈልገውን የግላችንን መሥፈርት አስቀድመን እንድናወጣ ነገረን። ከዚያም የትዳር ጓደኛ እንዲሆነን የምናስበው ሰው ሲያጋጥመን በእነዚህ መሥፈርቶች አማካኝነት እንድንመዝነው ሐሳብ አቀረበልን።
ለማግባት የምፈልገው ሰው ሊያሟላቸው ይገባል ብዬ ካወጣኋቸው መሥፈርቶች መካከል እንደ እኔው ሚስዮናዊ የሆነና ይሖዋን የሚወድ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱ ከእኔ የሚበልጥ፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቀጠል እንድንችል ከአርማጌዶን በፊት ልጅ እንዲኖረው የማይፈልግ፣ እንግሊዝኛ አቀላጥፎ መናገር የሚችል እንዲሁም ከእኔ በዕድሜ የሚበልጥ የሚሉት ይገኙበታል። በውጭ አገር እንዳገለግል በተመደብኩበት ወቅት ገና የ20 ዓመት ወጣት ስለነበርኩ እነዚህ አውጥቼያቸው የነበሩት መሥፈርቶች በጣም ረድተውኛል።
ብራዚል ተመደብኩ
እሁድ ነሐሴ 2, 1959 ከትምህርት ቤቱ ከተመረቅን በኋላ የምድብ ቦታችን ተነገረን። ቬሃኑሽ ያዜድጂያን፣ ሣራ ግሬኮ፣ ባልና ሚስት የሆኑት ሬይና ኢንገር ሃትፊልድ፣ ሶንያ ስፕሪንጌት፣ ዶሪን ሂንዝ እና እኔ ብራዚል ተመደብን። ይህን ስንሰማ በጣም ተደሰትን። ብራዚል ሲባል አስቤ የነበረው ጫካ፣ እባቦች፣ የጎማ ዛፍ እንዲሁም የአገሬው ተወላጅ የሆኑትን ሕንዶች ነበር። ሆኖም እዚያ ስደርስ በጣም ነበር የገረመኝ! ያገኘሁት ጥቅጥቅ ያለውን የአማዞን ደን ሳይሆን በወቅቱ የአገሪቱ ዋና ከተማ የሆነችውን ፀሐያማዋንና ዘመናዊቷን ሪዮ ዴ ጄኔሮን ነበር።
እዚያ እንደደረስን የገጠመን ተፈታታኝ ነገር ፖርቹጋልኛ መማር ነበር። በመጀመሪያው ወር በየቀኑ 11 ሰዓት ቋንቋውን እናጠና ነበር። ለጊዜው በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ አርፌ የተወሰነ ጊዜ ሪዮ ዴ ጄኔሮ ውስጥ ካገለግልኩ በኋላ በመጀመሪያ በሳኦ ፖሎ ግዛት ፔራሲካባ ከተማ ውስጥ ወዳለው ሚስዮናዊያን ቤት ቀጥሎም በፖርቱ አሌግሪ ውስጥ ወደሚገኘው ሚስዮናውያን ቤት ተዛወርኩ።
ከዚያም በ1963 መጀመሪያ አካባቢ በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ በሚገኘው የትርጉም ክፍል እንድሠራ ተጋበዝኩ። ብራዚል እንደደረስን ፓርቹጋልኛ ያስተማረን ፍሎሪያኖ ኤጋንዝ ዳ ኮንሳሶ የትርጉም ክፍሉ የበላይ ተመልካች ነበር። ወንድም ፍሎሪያኖ እውነትን የሰማው በ1944 ሲሆን በወቅቱ በብራዚል የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ወደ 300 ገደማ ነበር።። እንዲሁም 22ኛው ክፍል የጊልያድ ተመራቂ ነው። የተወሰኑ ወራት ካለፉ በኋላ አንድ ቀን ወንድም ፍሎሪያኖ ወደ ምሳ ከመግባታችን በፊት ሊያነጋግረኝ ስለፈለገ ለትንሽ ደቂቃ እንድቆይ ጠየቀኝ። ይህን ሲለኝ በመጀመሪያ ላይ ያጠፋሁት ነገር ይኖር ይሆን? ብዬ ፈርቼ ነበር። የምሳ ሰዓት መድረሱን የሚያስታውቀው ደውል ሲጮህ ሄጄ ለምን እንደፈለገኝ ጠየቅሁት። እርሱም “እኔን ለማግባት ፈቃደኛ ነሽ?” ሲል ጠየቀኝ። በጣም ከመደንገጤ የተነሳ አፌ እስርስር አለብኝ። ከዚያም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ማሰብ እንድችል ጊዜ እንዲሰጠኝ ጠይቄው በፍጥነት ወደ ምሳ ገባሁ።
ለጋብቻ ሲጠይቀኝ ወንድም ፍሎሪያኖ የመጀመሪያው ሰው አልነበረም። እስከዚያ ጊዜ ድረስ አውጥቼያቸው የነበሩትን የግል መሥፈርቶች የሚያሟላ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ አላገኘሁም ነበር። እነዚያ ያወጣኋቸው መሥፈርቶች የተሳሳተ ውሳኔ እንዳላደርግ እንደረዱኝ ይሰማኛል። በዚህ ወቅት ግን ሁኔታው የተለየ ነበር። ፍሎሪያኖ ሁሉንም መሥፈርቶች ያሟላል! ስለዚህም ግንቦት 15, 1965 ተጋባን።
ሕመም የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ ተቋቁሞ መኖር
ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙን የነበረ ቢሆንም ለእኔም ሆነ ለፍሎሪያኖ የትዳር ሕይወት አስደሳች ሆኖልን ነበር። ካጋጠሙን ችግሮች መካከል አንዱ ከተጋባን ብዙ ሳይቆይ ፍሎሪያኖ የገጠመው የጤና እክል ነበር። ከዓመታት በፊት የግራ ሳንባው ጉዳት ደርሶበት ስለነበር የዚያ መዘዝ አሁን ለብዙ ሥቃይ ዳረገው። በዚህ ምክንያት ከቤቴል ወጥተን በተራራማው የሪዮ ዴ ጄኔሮ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ቴሬዞፖሊስ በተባለች ከተማ ልዩ አቅኚ ሆነን ተመደብን። የዚያ አካባቢ የአየር ንብረት ከተስማማው ከሕመሙ ያገግማል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር።
በተጨማሪም በታኅሣሥ 1965 እናቴ ካንሰር ይዟት በጠና እንደታመመች የሚገልጽ መልእክት ደረሰኝ። ምንም እንኳ በየጊዜው ደብዳቤ እንጻጻፍ የነበረ ቢሆንም ለሰባት ዓመት ያህል አልተያየንም ነበር። ስለዚህም ወጪያችንን ሸፍናልን እርሷን ለማየት ወደ እንግሊዝ ተጓዝን። እናቴ ቀዶ ሕክምና ቢደረግላትም እንኳ ዶክተሮቹ ካንሰሩን ማስወገድ አልቻሉም። የአልጋ ቁራኛ የነበረችው እናቴ በወቅቱ በጣም ታምማ የነበረ ቢሆንም በአገልግሎት የመካፈል ፍላጎቷ እንደቀድሞው ነበር። በመኝታ ክፍሏ ውስጥ የጽሕፈት መኪና ስለነበር ሌሎችን በቃል በማስጻፍ በደብዳቤ ታገለግል ነበር። በተጨማሪም ሊጠይቋት ለሚመጡ ሰዎች አጭር ምሥክርነት ትሰጣለች። እናቴ ኅዳር 27, 1966 በሞት አንቀላፋች። በዚያ ወር ግን የአገልግሎት ሪፖርቷ አሥር ሰዓት ነበር! አባቴ በ1979 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በአቅኚነት አገልግሎቱ በታማኝነት ቀጥሎ ነበር።
እናቴ ከሞተች በኋላ እኔና ፍሎሪያኖ ወደ ብራዚል ማለትም እስካሁን ድረስ እያገለገልንበት ወዳለነው ሪዮ ዴ ጄኔሮ ግዛት ተመለስን። በመጀመሪያ ላይ በግዛቲቱ ዋና ከተማ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራ እንድናገለግል ተመደብን። ይሁን እንጂ ይህ ደስታ የዘለቀው ለጥቂት ጊዜያት ነበር፤ ምክንያቱም ፍሎሪያኖ በድጋሚ በጠና ታመመ። በመሆኑም ልዩ አቅኚ ሆነን ወደ ቴሬዞፖሊስ ተመለስን።
ለዓመታት ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትል ሕክምና ከተከታተለ በኋላ በ1974 ዶክተሮች የፍሎሪያኖን የግራ ሳንባ ሙሉ በሙሉ አስወገዱት። በዚያ ጊዜ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ወይም ልዩ አቅኚ ሆኖ ማገልገል አልቻለም። ይሁን እንጂ በሕሙማን መጠየቂያ ሰዓት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይመራ ነበር። ከአስጠናቸው ሰዎች መካከል ቦብ የሚባሉ ጡረታ የወጡ አሜሪካዊ ይገኙበታል። ቦብ እውነትን ተቀብለው ከጊዜ በኋላ ተጠምቀዋል። ፍሎሪያኖ ቀስ በቀስ እየተሻለው በመምጣቱ የዘወትር አቅኚ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
ይሖዋ አገልግሎቴን ባርኮልኛል
ለዓመታት ልዩ አቅኚ ሆኜ ማገልገሌን የቀጠልኩ ስሆን ይሖዋም አገልግሎቴን ባርኮልኛል። በቴሬዞፖሊስ ከ60 የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ የመርዳት አስደሳች መብት አግኝቻለሁ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ማንበብ ያስተማርኳት ጁፒራ ትገኝበታለች። ከጊዜ በኋላ ስምንት ልጆቿንም መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንቻቸዋለሁ። በአሁኑ ወቅት ጁፒራና ሌሎች ከ20 የሚበልጡ ዘመዶቿ ይሖዋን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል አንዱ የጉባኤ ሽማግሌ ሦስቱ የጉባኤ አገልጋዮች እንዲሁም ሁለቱ አቅኚዎች ናቸው።
ካሰለፍኩት ሕይወት ሰዎች እውነትን ሊቀበሉ ይችላሉ የሚል አዎንታዊ አመለካካት ማዳበር እንዳለብኝም ተምሬያለሁ። በአንድ ወቅት አልዘሚራ የምትባልን ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ሳስጠና ባለቤቷ አንቶኒዮ ቤታቸውን በፍጥነት ለቅቄ ካልወጣሁ ሁለት ትላልቅ ውሾች እንደሚለቅብኝ በመናገር አስፈራራኝ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ከአልዘሚራ ጋር መገናኘት አቆምን፤ ሆኖም ከሰባት ዓመት በኋላ አንቶኒዮን እንደምንም ፈቃድ ጠይቄ ጥናታችንን ቀጠልን። ያም ሆኖ ግን ለእርሱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳላነሳበት ከልክሎኝ ነበር። ይሁን እንጂ በአንድ ዝናባማ ቀን አንቶኒዮ ጥናታችን ላይ እንዲገኝ ጋበዝኩት። የዚያን ቀን የአንቶኒዮን ችግር ተረዳሁ፤ ለካስ ችግሩ ማንበብና መጻፋ አለማወቁ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፍሎሪያኖና ሌሎች ወንድሞች እርሱን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠኑት ከመሆኑም ሌላ ማንበብ አስተማሩት። በአሁኑ ወቅት አልዘሚራና አንቶኒዮ የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። አንቶኒዮ ብዙ ወጣት ክርስቲያኖችን ይዞ አገልግሎት በመውጣት ለጉባኤው ትልቅ እርዳታ በማበርከት ላይ ይገኛል።
እነዚህ ተሞክሮዎች ቴሬዞፖሊስ ባገለገልንባቸው ከ20 በሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ካገኘናቸው መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። በ1988 መጀመሪያ አካባቢ ኒትሮ ወደምትባል ከተማ ተዛውረን እንድናገለግል አዲስ ምድብ ተሰጠን። እዚያ ለአምስት ዓመታት ካገለገልን በኋላ ወደ ሳንቶ አላሹ ተዛወርን። ከዚያም በሪዮ ዴ ጄኔሮ ማዕከላዊ ቦታ ላይ ወደሚገኘው ወደ ጁፑባ ተዛውረን ሪቤራ የተባለውን አዲስ ጉባኤ የመመሥረትም መብት አግኝተናል።
ቀላል ግን የሚክስ ሕይወት
በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ እኔና ፍሎሪያኖ ከ300 የሚበልጡ ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው እንዲጠመቁ የመርዳት መብት አግኝተናል። በአሁኑ ጊዜ አንዳንዶቹ በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ሌሎች ደግሞ አቅኚዎች፣ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ብዙ ሰዎችን መረዳት እንድንችል አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ስለተጠቀመብን አመስጋኝ ነኝ!—ማርቆስ 10:29, 30
ፍሎሪያኖ ከከባድ በሽታ ጋር እየታገለ እንደሆነ አይካድም። የጤና ችግር ቢያጋጥመውም ከአቋሙ ፍንክች አላለም እንዲሁም ደስተኛና ሙሉ በሙሉ በይሖዋ የሚታመን ሰው ነው። አብዛኛውን ጊዜ ፍሎሪያኖ “በዛሬው ጊዜ ደስታ ከችግር ነጻ የሆነ ሕይወት በመምራት የሚገኝ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከችግሮቻችን ጋር ስንታገል ይሖዋ እንደሚረዳን በማወቃችን የምናገኘው ነገር ነው” በማለት ይናገራል።—መዝሙር 34:19
በ2003 በግራ ዓይኔ ላይ ካንሰር ተገኘ። ከዚያም ቀዶ ሕክምና ከተደረገልኝ በኋላ በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ መጽዳት በሚያስፈልገው ሰው ሰራሽ ዓይን ተተካልኝ። ይህ ችግር እያለብኝም ቢሆን ይሖዋ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል የሚያስችል ኃይል በመስጠት ባርኮኛል።
ቁሳዊ ነገሮችን በተመለከተ አኗኗሬ ቀላል ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ በተመደብኩባቸው ቦታዎች ሁሉ በመባረክ በመንፈሳዊ ሀብታም አድርጎኛል። ያቺ ሚስዮናዊ እህት በአፍሪካ ስላለው የስብከት ሥራ የሰጠችው ሐሳብ እኛም በብራዚል ላጋጠመን ሁኔታ በትክክል ይሠራል። በእርግጥም ይሖዋ ሚስዮናዊ ለመሆን የነበረኝን ፍላጎት አሳክቶልኛል!
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1953 ከቤተሰቦቼ ጋር
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
1957 በአየርላንድ ስመሠክር
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1959 በብራዚል አብረውኝ ከነበሩት ሚስዮናውያን ጋር፤ ከግራ ወደ ቀኝ:- እኔ፣ ኢንገር ሃትፊልድ፣ ዶሪን ሂንዝና ሶንያ ስፕሪንጌት
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ጋር