በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች በረከት የሚሆኑ ተማሪዎችን የሚያሠለጥን ትምህርት ቤት

በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች በረከት የሚሆኑ ተማሪዎችን የሚያሠለጥን ትምህርት ቤት

በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች በረከት የሚሆኑ ተማሪዎችን የሚያሠለጥን ትምህርት ቤት

ከ200 በላይ በሚሆኑ አገሮች ውስጥ በሚገኙ ከ98,000 በሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የተለያየ የኑሮ ሁኔታ ያላቸው ሰዎች ከአምላክ እየተማሩ ነው። ዋነኛው የመማሪያ መጽሐፋቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን የዚህ ትምህርት ዓላማ ደግሞ ተማሪዎቹ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ተምረውና ከፈቃዱ ጋር ተስማምቶ መኖር የሚቻልበትን መንገድ አውቀው በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ መርዳት ነው። ይህንን ሥልጠና ያገኙ ሰዎች እጅግ ተጠቅመዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልእኮ ለመፈጸም የተማሩትን ለሌሎችም ያካፍላሉ።—ማቴዎስ 28:19, 20

የይሖዋ ምሥክሮች በጉባኤዎች ከሚካሄደው የማያቋርጥ የትምህርት ፕሮግራም በተጨማሪ በርከት ያሉ ልዩ ሥልጠና የሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶችን አቋቁመዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ነው። ይህ ትምህርት ቤት የጀመረው በጥቅምት ወር 1987 በፒትስበርግ፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን የመጀመሪያው ክፍል የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ 24 ተማሪዎችን ያቀፈ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኮርሱ በ43 አገሮች ውስጥ በ21 ቋንቋዎች ሲሰጥ ቆይቷል። እስካሁን ድረስ ከ90 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ያላገቡ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በትምህርት ቤቱ ተካፍለዋል። ተመራቂዎቹ ከስምንት ሳምንት በኋላ ኮርሱን ሲጨርሱ በአገራቸው ወይም በሌላ አገር የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ እንዲያገለግሉ ይመደባሉ። እስከ 2005 መገባደጃ ድረስ ከ22,000 በላይ የሚሆኑ ወንድሞች ኮርሱን ወስደዋል። እነዚህ ወንድሞች የመንግሥቱን ምሥራች ለማስፋፋትና ሌሎችን ለማገልገል የሚያደርጉት ትሕትና የታከለበት ጥረት በእጅጉ ተባርኳል።—ምሳሌ 10:22፤ 1 ጴጥሮስ 5:5

በትምህርት ቤቱ ለመካፈል ዝግጅት ማድረግ

በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለመካፈል አብዛኞቹ ተማሪዎች ከሰብዓዊ ሥራቸው ፈቃድ መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የሚፈጥረው ችግር አለ። በሃዋይ ሁለት ክርስቲያን ወንድሞች በትምህርት ቤቱ እንዲሠለጥኑ ሲጋበዙ አስተማሪ ሆነው ከሚሠሩበት ትምህርት ቤት ፈቃድ መጠየቅ ነበረባቸው። ይሖዋ እንደሚረዳቸው በመተማመን፣ በሥልጠናው መካፈል የሚፈልጉበትን ምክንያትና የሚያገኙትን ጥቅም ገልጸው ፈቃድ እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ሁለቱም ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ።

ብዙውን ጊዜ ፈቃድ የሚጠይቁ የይሖዋ ምሥክሮች ሲመለሱ ከሥራ እንደሚባረሩ ይነገራቸዋል። ይሁን እንጂ ወንድሞች በትምህርት ቤቱ ለመካፈል መሄዳቸው ሥራቸውን የሚያሳጣቸው ቢሆንም ከይሖዋ ድርጅት ሥልጠና ለማግኘት ይመርጣሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ፣ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ የሚጋብዝ ደብዳቤ ከአሠሪዎቻቸው ደርሷቸዋል። በዚህ ትምህርት ቤት ለመካፈል ያደረጉት ቁርጥ ውሳኔ በሚከተለው መንገድ ሊገለጽ ይችላል:- አሠሪህን ፈቃድ ጠይቅ፣ ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ፣ ከዚያም የቀረውን ለእርሱ ተወው።—መዝሙር 37:5

‘ከይሖዋ የተማሩ’

ለስምንት ሳምንታት በሚቆየው በዚህ ሥልጠና ወቅት ተማሪዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ያጠናሉ። ተማሪዎቹ፣ የይሖዋ ሕዝቦች የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ስለተደራጁበት መንገድ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት፣ በጉባኤ ስብሰባዎችና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይማራሉ።

ከትምህርት ቤቱ የተመረቀ አንድ ወንድም በትምህርት ቤቱ እንዲካፈል ለተጠራ ተማሪ እንዲህ በማለት ስለ ሥልጠናው የተሰማውን አድናቆት ገልጿል:- “ከዚህ በፊት አግኝተኸው የማታውቀውን ዓይነት ሥልጠና እንደምታገኝበት እርግጠኛ ነኝ። ‘ከይሖዋ ስለመማር’ የሚናገረው ጥቅስ ይበልጥ ትርጉም ያለው ይሆንልሃል። አጠቃላይ ትምህርቱ ልባችንንና ባሕርያችንን በመቅረጽ እንዲሁም በማጥራት የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ይበልጥ እንድንኮርጅ የሚረዳ ነው። በትምህርት ቤቱ ስትካፈል በሕይወትህ ውስጥ ልዩ ተሞክሮ ታገኛለህ።”—ኢሳይያስ 54:13

ወንጌላውያን፣ እረኞችና አስተማሪዎች

ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁ ተማሪዎች በአሁኑ ጊዜ በ117 አገሮች ውስጥ ያገለግላሉ። ይህ ደግሞ በአትላንቲክ፣ በካሪቢያንና በፓስፊክ የሚገኙ ደሴቶችን እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚገኙባቸውን አብዛኞቹን አገሮች ይጨምራል። ተማሪዎቹ ያገኙት ጥሩ ሥልጠና በወንጌላዊነት፣ በእረኝነትና በማስተማር ሥራቸው እየታየ መሆኑን ቅርንጫፍ ቢሮዎች ሪፖርት አድርገዋል። ያገኙት ሥልጠና በመስክ አገልግሎት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም እንዲችሉ አስታጥቋቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) በአገልግሎት የሚያጋጥሟቸው ሰዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር a የተባለውን መጽሐፍ አዘውትረው ይጠቀሙበታል፤ እንዲሁም ሌሎች የመንግሥቱ አስፋፊዎች ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ሥልጠና ይሰጣሉ። ተመራቂዎቹ የሚያሳዩት ቅንዓት ወደ ሌሎች የሚጋባ ሲሆን የሚያከናውኑት ሥራም ጉባኤዎችን የሚያጠናክር ነው።

የጉባኤ ሽማግሌዎች ‘መንጋውን የመጠበቅ’ ማለትም ሌሎችን በመንፈሳዊ የመርዳት መብት አላቸው። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) ይህንን ዝግጅት በተመለከተ አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “ቅርንጫፍ ቢሮው የአምላክን መንጋ በመጠበቅ ረገድ ያለብንን ኃላፊነት ለመወጣት እንድንችል የሚያግዙንን በሚገባ የሠለጠኑ ወንድሞችን ስለላከልን በጣም አመስጋኝ ነን።” በሩቅ ምሥራቅ የሚገኝ አንድ ቅርንጫፍ ቢሮም እንዲህ የሚል ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥቷል:- “ተመራቂዎቹ ለሌሎች በጣም ያስባሉ። በትጋት የሚሠሩ በመሆናቸው ጉባኤው በጥልቅ ያከብራቸዋል። ትሕትናቸው፣ ሞቅ ያለ ፍቅራቸውና ለሥራ ያላቸው ተነሳሽነት በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ ከመሆኑም በላይ በጣም ይደነቃል። ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ ሲሆን እረኞች ወደሚያስፈልጉባቸው ጉባኤዎችም ደስ እያላቸው ይሄዳሉ።” (ፊልጵስዩስ 2:4) እንደነዚህ የመሰሉ ወንዶች የእምነት ወንድሞቻቸውን የሚያበረታቱ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 16:18

ከዚህም በተጨማሪ በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የሚገኙት መምህራን፣ ተማሪዎቹ የሕዝብ ተናጋሪነት ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዷቸዋል። በርካታ ተመራቂዎች የሚሰጧቸውን ሐሳቦችና ምክሮች በሥራ ላይ በማዋላቸው በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ክፍል የማቅረብ መብት ማግኘት ችለዋል። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ተመራቂዎቹ “በጣም ግሩም ንግግሮችን እንደሚያቀርቡና ትምህርቱን ጥሩ አድርገው በማስረዳት ተግባራዊ ጠቀሜታውን እንደሚያጎሉ” ተናግሯል።—1 ጢሞቴዎስ 4:13

በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ወንድሞችን ለማሠልጠን ዝግጅት ተደረገ፤ ተመራቂዎቹ በአገሪቱ ውስጥ ከተመደቡ በኋላ በጉባኤ ስብስባዎች ላይ ትምህርት የሚቀርብበት መንገድ በእጅጉ ሊሻሻል ችሏል። ከትምህርት ቤቱ የተመረቁ ሽማግሌዎች ወንጌላውያን፣ እረኞችና አስተማሪዎች በመሆን ጉባኤውን በመንፈሳዊ በመገንባት ረገድ እርዳታ ያበረክታሉ።—ኤፌሶን 4:8, 11, 12

የተሻለ የጉባኤ አመራር

በበርካታ አካባቢዎች ተጨማሪ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ያስፈልጋሉ። አንዳንድ ጉባኤዎች ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቀ ወንድም ባይላክላቸው ኖሮ አንድም ሽማግሌ አይኖራቸውም ነበር። በመሆኑም በርካታ ተመራቂዎች እንዲህ ዓይነት እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደው እንዲያገለግሉ ይመደባሉ።

በርካታ ቅርንጫፍ ቢሮዎች እነዚህን ወንድሞች በተመለከተ እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርገዋል:- “ድርጅታዊውን አሠራር በሚገባ ያውቃሉ፣” “ኃላፊነታቸውን በቁም ነገር ይመለከታሉ፣” “ሌሎች የይሖዋን ድርጅት እንዲያደንቁና እንዲያከብሩ ይረዳሉ፣” እንዲሁም “በጉባኤያቸው ውስጥ ሞቅ ያለ ፍቅር እንዲኖርና ወንድሞች በመንፈሳዊ እንዲጠናከሩ ይረዳሉ።” ይህ የሆነበት ምክንያት የትምህርት ቤቱ ተመራቂዎች በራሳቸው ማስተዋል ከመደገፍ ወይም ጥበብ የመሰላቸውን ነገር ከማድረግ ይልቅ የአምላክ ቃል የሚለውን የሚከተሉ በመሆናቸው ነው። (ምሳሌ 3:5-7) እነዚህ ወንዶች ለተመደቡባቸው ጉባኤዎች መንፈሳዊ ስጦታዎች ናቸው።

በገለልተኛ ክልሎች ማገልገል

ልዩ አቅኚ ሆነው የተመደቡ አንዳንድ ተመራቂዎች በገለልተኛ አካባቢዎች የሚገኙ ቡድኖች ወደ ጉባኤ ደረጃ እንዲያድጉ ይረዳሉ። በጓቴማላ ገለልተኛ በሆነ አካባቢ የሚኖር አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ተመራቂዎቹ ላበረከቱት እርዳታ የተሰማውን አድናቆት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ለ20 ዓመታት ያህል ይህ ሰፊ ክልል እንዴት ይሸፈናል የሚለው ነገር ያሳስበኝ ነበር። ስለዚህ ጉዳይም በተደጋጋሚ ጸልያለሁ። ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁት ወንድሞች የተዋጣላቸው ተናጋሪዎች ከመሆናቸውም በላይ ድርጅታዊ አሠራርን በተመለከተ በሚገባ የሠለጠኑ ናቸው፤ በአሁኑ ጊዜ ይህ አካባቢ ትኩረት እየተሰጠው በመሆኑ በጣም አመስጋኝ ነኝ።”

ተመራቂዎቹ ተራርቀው ወደሚገኙ ትናንሽ መንደሮች ለመድረስ ተራራማ አካባቢዎችን አቋርጠው ረጅም ርቀት መጓዝ ቢያስፈልጋቸውም በእነዚህ አካባቢዎች በሚገኙ ክልሎች ውስጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመስበክ የሚያስችላቸውን ሥልጠና አግኝተዋል። በእነዚህ ገለልተኛ ቦታዎች ቡድኖችን ማቋቋም ለሌሎች አስፋፊዎች አዳጋች ሆኖባቸው ነበር። ተመራቂዎቹ ግን ወደ ክልሉ ከመጡ ብዙም ሳይቆዩ ቡድኖችን ማቋቋምና ማደራጀት ችለዋል። ለምሳሌ በኒጀር የሚገኝ አንድ ሽማግሌ ከትምህርት ቤቱ የተመረቁ ተማሪዎች እርሱ ወደሚኖርበት አካባቢ ቢመጡ ጥሩ ሥራ ሊያከናውኑ እንደሚችሉ ስለተሰማው ተመራቂዎቹ እንዲላኩለት ጠይቋል። በተለይ በገለልተኛ ክልሎች ውስጥ ልዩ አቅኚዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሆነው ማገልገል ላላገቡ ወንድሞች ቀላል ሊሆንላቸው ይችላል። እነዚህ ወንድሞች ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የወንዝ ሙላትና ወንበዴዎች’ የሚያስከትሉባቸውን ችግር እንዲሁም ‘በምድረ በዳ [የ1954 ትርጉም]’ የሚያጋጥማቸውን አደጋ መቋቋም አስፈልጓቸዋል፤ ከዚህም ሌላ የግል ችግሮች ይኖሯቸዋል እንዲሁም ስለሚያገለግሉበት ጉባኤ ይጨነቃሉ።—2 ቆሮንቶስ 11:26-28

ወጣቶችን መርዳት

ቅዱሳን መጻሕፍት ወጣቶች ፈጣሪያቸውን እንዲያስቡ ምክር ይሰጣሉ። (መክብብ 12:1) ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁ ቀናተኛ ወንድሞች ለክርስቲያን ወጣቶች ግሩም ምሳሌ ናቸው። ከትምህርት ቤቱ የተመረቁ ሁለት ወንድሞች በዩናይትድ ስቴትስ ወደሚገኝ አንድ ጉባኤ ሲላኩ፣ በጉባኤው የሚገኙ አስፋፊዎች በአገልግሎት ላይ የሚያሳልፉት ሰዓት በእጥፍ ጨምሯል። ከዚህም በተጨማሪ የዘወትር አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር ከ2 ወደ 11 ከፍ ብሏል። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በበርካታ ጉባኤዎች ውስጥ የሚታይ ነገር ነው።

ተመራቂዎቹ፣ በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲሠለጥኑ ወጣቶችን ያበረታቷቸዋል። ይህ ደግሞ አንዳንዶች በዚህ ዓይነቱ ሥልጠና የመካፈል መብት ለማግኘት ሲሉ የጉባኤ አገልጋዮች እንዲሆኑ አነሳስቷቸዋል። የኔዘርላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁት ተማሪዎች “በሕይወታቸው ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ለሚያስቡ ወጣቶች ሕያው ምሳሌዎች” እንደሆኑ ገልጿል።

በውጭ አገር ቋንቋ በሚካሄዱ ጉባኤዎች ውስጥ ማገልገል

በበርካታ አገሮች ውስጥ ለሰዎች ምሥራቹን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ለመመሥከር የሚደረገው ጥረት እየጨመረ ነው። ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁ ወንድሞች ብዙ ጊዜ ሌላ ቋንቋ ተምረው በርካታ የውጭ አገር ሰዎች በሚገኙበት ክልል ውስጥ ያገለግላሉ። ለምሳሌ በቤልጂየም የአልባኒያ፣ የፋርስና የራሽያ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ለመርዳት ተጨማሪ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይፈለጋሉ።

በሜክሲኮ፣ በብሪታንያ፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በጀርመንና በጣሊያን እንዲሁም በሌሎች አገሮች የሚገኙ በውጭ አገር ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችና ቡድኖች ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ከተመረቁ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ከፍተኛ ጥቅም እያገኙ ነው። በኮሪያ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ “ከ200 በላይ የሚሆኑ ከትምህርት ቤቱ የተመረቁ ወንድሞች በውጭ አገር ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችንና ቡድኖችን በመርዳት ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ” በማለት ሪፖርት አድርጓል።

በሌሎች የኃላፊነት ቦታዎች በትሕትና ማገልገል

ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁ ወንድሞች በውጭ አገር ቋንቋ በሚመሩ ጉባኤዎችና ቡድኖች ውስጥ ከማገልገል በተጨማሪ ሽማግሌዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮችና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሆነው ያገለግላሉ። አንዳንዶች በሌሎች አገሮች በሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የአገልግሎት ክፍሉ አስቸኳይ ሥራ ሲኖረው እርዳታ ያበረክታሉ። በግንባታ ሥራ ሙያ ያላቸው ከሆኑ ደግሞ በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮግራም መሳተፍ ይችሉ ይሆናል።

በዓለም ዙሪያ የሚታየው የጉባኤዎችና የወረዳዎች ቁጥር መጨመር ተጨማሪ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እንደሚያስፈልጉ የሚጠቁም ነው። ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ከተመረቁት ወንድሞች መካከል አንዳንዶች ተመርጠው ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆነው ለማገልገል የሚያስችላቸውን የአሥር ሳምንት ሥልጠና ያገኛሉ፤ ከዚያም ተተኪ ወይም ቋሚ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ይሆናሉ። በአሁኑ ጊዜ 1,300 የሚያህሉ ተመራቂዎች በ97 አገሮች ውስጥ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ያገለግላሉ። በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ ከሚገኙት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች 55 በመቶ ያህሉ ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁ ናቸው። በሌላ የአፍሪካ አገር ደግሞ 70 በመቶ የሚሆኑት በትምህርት ቤቱ ሥልጠና ያገኙ ናቸው።

በሩቅ ምሥራቅ አገሮች፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትምህርት ቤቱ ተመራቂዎች በሌሎች አገሮች ለየት ያለ እርዳታ በሚያስፈልግባቸው ቦታዎች እንዲያገለግሉ ተልከዋል። በዚህ መንገድ ትምህርት ቤቱ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ጥቅም እየሰጠ ነው።

ይሖዋ፣ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያከናውኑ ወንጌላውያንን፣ እረኞችንና አስተማሪዎችን ሰጥቶናል። ወደፊትስ የአምላክ ሕዝቦች ቁጥር ይጨምር ይሆን? ምንም ጥያቄ የለውም! በመሆኑም ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ለመቀበል የሚችሉ ራሳቸውን የወሰኑ ወንዶች ይበልጥ ያስፈልጋሉ። (ኢሳይያስ 60:22፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ራሳቸውንም ሆነ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሌሎች ሰዎችን በእጅጉ መጥቀም በሚያስችላቸው መንገድ አገልግሎታቸውን ለማስፋት ብቁ እንዲሆኑ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የመንግሥቱ ምሥራች በዓለም ዙሪያ እንዲስፋፋ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለመካፈልና ሌሎችን ለማገልገል አስበሃል?