በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላክ ፍቅር አትውጣ!

ከአምላክ ፍቅር አትውጣ!

ከአምላክ ፍቅር አትውጣ!

‘ወዳጆች ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ስትጠባበቁ ሳለ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።’—ይሁዳ 20, 21

1, 2. ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?

 ይሖዋ መላውን የሰው ዘር ዓለም እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ አንድያ ልጁን ሰጥቷል። (ዮሐንስ 3:16) ይህን መሰሉን ፍቅር ማግኘት ምንኛ ያስደስታል! የይሖዋ አገልጋይ ከሆንክ አምላክ ለዘላለም እንዲወድህ እንደምትፈልግ ግልጽ ነው።

2 ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ መኖር የምትችለው እንዴት እንደሆነ ገልጿል። ይሁዳ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ ትጉ፤ በመንፈስ ቅዱስም ጸልዩ። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሳችሁን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ ሳለ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።” (ይሁዳ 20, 21) የአምላክን ቃል ማጥናትና ምሥራቹን መስበክ ‘እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነት’ ማለትም በክርስቲያናዊ ትምህርት እንድትታነጽ ይረዳሃል። ከይሖዋ ፍቅር ሳትወጣ ለመኖር “በመንፈስ ቅዱስ” ወይም በሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ ሥር ሆነህ መጸለይ ይኖርብሃል። ከዚህም በተጨማሪ የዘላለም ሕይወት ሽልማትን ለማግኘት በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ማመን ይገባሃል።—1 ዮሐንስ 4:10

3. አንዳንዶች የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው መቀጠል ያልቻሉት ለምንድን ነው?

3 ከዚህ ቀደም እምነት የነበራቸው አንዳንዶች ከአምላክ ፍቅር ወጥተዋል። የኃጢአትን ጎዳና ለመከተል በመምረጣቸው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው መቀጠል አልቻሉም። እንዲህ የመሰለ ሁኔታ እንዳይደርስብህ ምን ማድረግ ትችላለህ? በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ማሰላሰልህ ኃጢአት ከመሥራት ሊጠብቅህና ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ እንድትኖር ሊረዳህ ይችላል።

ለአምላክ ያለህን ፍቅር በተግባር አሳይ

4. ለአምላክ መታዘዝ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

4 ለአምላክ በመታዘዝ ለእርሱ ያለህን ፍቅር አሳይ። (ማቴዎስ 22:37) ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:3) ለአምላክ የመታዘዝ ልማድ ማዳበርህ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ የሚሰጥህ ከመሆኑም ባሻገር ደስተኛ እንድትሆን ያደርግሃል። መዝሙራዊው “በክፉዎች ምክር የማይሄድ . . . ሰው ብፁዕ ነው። ነገር ግን ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው” ብሏል።—መዝሙር 1:1, 2

5. ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ምን እንድታደርግ ይገፋፋሃል?

5 ለይሖዋ ያለህ ፍቅር በስሙ ላይ ነቀፌታ የሚያመጣ ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም እንድትቆጠብ ይገፋፋሃል። አጉር እንደሚከተለው ሲል ጸልዮአል:- “ድኽነትንም ሆነ ብልጽግናን አትስጠኝ፤ ብቻ የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ። ያለዚያ ግን ያለ ልክ እጠግብና እክድሃለሁ፤ ‘እግዚአብሔር ማን ነው?’ እላለሁ፤ ወይም ድኻ እሆንና እሰርቃለሁ፤ የአምላኬንም ስም አሰድባለሁ።” (ምሳሌ 30:1, 8, 9) አምላክን የሚያስነቅፍ ነገር በማድረግ ‘ስሙን ላለማሰደብ’ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። እንዲያውም ዘወትር አምላክን የሚያስከብሩ መልካም ነገሮችን ለማድረግ ተጣጣር።—መዝሙር 86:12

6. ሆን ብለህ ኃጢአት ብትሠራ ውጤቱ ምን ይሆናል?

6 ኃጢአት እንድትሠራ በሚገፋፋህ ማባበያ እንዳትሸነፍ በሰማይ የሚኖረው አፍቃሪ አባትህ እንዲረዳህ ዘወትር ጸልይ። (ማቴዎስ 6:13፤ ሮሜ 12:12) ጸሎትህ እንዳይከለከል የአምላክን ምክር መስማትህን አታቋርጥ። (1 ጴጥሮስ 3:7) ይሖዋ የዓመጸኞችን ጸሎት ላለመስማት በምሳሌያዊ ሁኔታ ራሱን በደመና ስለሚሸፍን ሆን ብለህ ኃጢአት ብትሠራ ውጤቱ የከፋ ይሆናል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:42-44) በመሆኑም የትሕትና መንፈስ አሳይ እንዲሁም ወደ አምላክ በጸሎት የመቅረብ መብትህን የሚያሳጣ ምንም ነገር እንዳትፈጽም ጸልይ።—2 ቆሮንቶስ 13:7

ለአምላክ ልጅ ያለህን ፍቅር አሳይ

7, 8. አንድ ሰው የኢየሱስን ምክር ተግባራዊ ማድረጉ ከኃጢአት ጎዳና እንዲርቅ የሚረዳው እንዴት ነው?

7 ለኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዛት በመገዛት ለእርሱ ፍቅር እንዳለህ አሳይ፤ ይህን ማድረግህ ከኃጢአት ጎዳና እንድትርቅ ይረዳሃል። ኢየሱስ “እኔ የአባቴን ትእዛዝ ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር፣ እናንተም ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 15:10) ታዲያ ከኢየሱስ ቃላት ጋር ተስማምተህ መኖርህ ከአምላክ ፍቅር እንዳትወጣ የሚረዳህ እንዴት ነው?

8 የኢየሱስን ቃላት በቁም ነገር መመልከትህ የሥነ ምግባር አቋምህን ጠብቀህ እንድትኖር ይረዳሃል። አምላክ ለእስራኤላውያን “አታመንዝር” የሚል ሕግ ሰጥቷቸዋል። (ዘፀአት 20:14) ሆኖም ኢየሱስ “ሴትን በምኞት ዓይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል” በማለት ከዚህ ሕግ በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት ገልጿል። (ማቴዎስ 5:27, 28) ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤ ውስጥ አንዳንዶች “ዐይናቸው ቅንዝር የተሞላ” እንደሆነና ‘ጽኑ ያልሆኑትን ነፍሳት እንደሚያስቱ’ ተናግሯል። (2 ጴጥሮስ 2:14) ከእነዚህ ሰዎች በተለየ መልኩ፣ አምላክንም ሆነ ክርስቶስን የምትወድና የምትታዘዝ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ያለህን ዝምድና አጥብቀህ የምትይዝ ከሆነ ከጾታ ብልግና መራቅ ትችላለህ።

የይሖዋ መንፈስ እንዲመራህ ፍቀድ

9. አንድ ሰው ኃጢአት መሥራቱን ቢቀጥል ውጤቱ ምን ይሆናል?

9 የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት ጸልይ፤ እንዲመራህም ፍቀድለት። (ሉቃስ 11:13፤ ገላትያ 5:19-25) ኃጢአት መሥራትህን የምትቀጥል ከሆነ አምላክ መንፈሱን ሊወስድብህ ይችላል። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር በተያያዘ ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ “ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 51:11) ንጉሥ ሳኦል ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የአምላክን መንፈስ አጥቷል። ሳኦል የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ፣ የአማሌቃውያንን በጎች፣ ፍየሎችና ከብቶች እንዲሁም ንጉሣቸውን ፈጽሞ ባለማጥፋት ኃጢአት ሠርቷል። በመሆኑም ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ከሳኦል ላይ ወሰደበት።—1 ሳሙኤል 13:1-14፤ 15:1-35፤ 16:14-23

10. ኃጢአት የመሥራት ሐሳቡን እንኳ ማስተናገድ የማይኖርብን ለምንድን ነው?

10 ሌላው ቀርቶ ኃጢአት የመሥራት ሐሳቡ እንኳን ሊኖርህ አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ “የእውነትን ዕውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆን ብለን በኀጢአት ጸንተን ብንመላለስ፣ ከእንግዲህ ለኀጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋዕት አይኖርም” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 10:26-31) ሆን ብለህ ኃጢአት ብትሠራ ውጤቱ እንዴት የሚያሳዝን ይሆናል!

ለሌሎች እውነተኛ ፍቅር እንዳለህ አሳይ

11, 12. ፍቅርና አክብሮት አንድን ሰው የጾታ ብልግና ከመፈጸም እንዲርቅ የሚያደርጉት በምን መንገዶች ነው?

11 ለሰዎች ያለህ ፍቅር የጾታ ብልግና ከመፈጸም እንድትርቅ ያደርግሃል። (ማቴዎስ 22:39) እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የሌላ ሰውን የትዳር ጓደኛ ትኩረት ከመሳብ ልብህን እንድትጠብቅ ያነሳሳሃል። ከዚህ በተቃራኒው የሌላውን የትዳር ጓደኛ ትኩረት ለመሳብ መሞከር ግን ምንዝር ወደ መፈጸም ሊመራህ ይችላል። (ምሳሌ 4:23፤ ኤርምያስ 4:14፤ 17:9, 10) ከሚስቱ ሌላ ለማንኛዋም ሴት አላስፈላጊ ትኩረት ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልነበረውና ቅን እንደሆነው እንደ ኢዮብ ሁን።—ኢዮብ 31:1

12 ለጋብቻ ቅድስና አክብሮት ማሳየት ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም እንድትርቅ ይረዳሃል። አምላክ ክቡር የሆነው ጋብቻም ሆነ የጾታ ግንኙነት እንዲኖር ያደረገበት ዓላማ ሰዎች እንዲባዙ ነው። (ዘፍጥረት 1:26-28) የጾታ ብልቶች ቅዱስ የሆነውን ሕይወት የማስገኘት ዓላማ እንዳላቸው መዘንጋት የለብህም። ዝሙትና ምንዝር የሚፈጽሙ ሰዎች ለአምላክ አይታዘዙትም፣ የጾታ ግንኙነትን ያራክሳሉ፣ ለጋብቻ ቅድስና አክብሮት የላቸውም እንዲሁም በገዛ አካላቸው ላይ ኃጢአት ይሠራሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ሆኖም አንድ ሰው ለአምላክና ለሰዎች ያለው ፍቅር እንዲሁም አምላክን ለመታዘዝ ያለው ፍላጎት ከክርስቲያን ጉባኤ እንዲወገድ የሚያደርገውን ድርጊት ከመፈጸም እንዲቆጠብ ያስችለዋል።

13. ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው ‘ሀብቱን የሚያባክነው’ በምን መንገድ ነው?

13 የምንወዳቸውን ሰዎች ላለማሳዘን ከፈለግን ወደ ኃጢአት ድርጊት ከሚገፋፉ አስተሳሰቦች መራቅ ይኖርብናል። ምሳሌ 29:3 “የአመንዝራዎች ወዳጅ ግን ሀብቱን ያባክናል” ይላል። አንድ ምንዝር የፈጸመ ሰው ንስሐ ካልገባ ከአምላክ ጋር ያለውን ወዳጅነት ከማበላሸቱም ባሻገር የቤተሰቡን አንድነት ያናጋል። ሚስቱም እርሱን ለመፍታት በቂ ምክንያት ይኖራታል። (ማቴዎስ 19:9) ኃጢአቱን የፈጸመው ባልየውም ሆነ ሚስትየዋ ጋብቻው መፍረሱ ታማኝ የሆነውን የትዳር ጓደኛ፣ ልጆቻቸውን እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን ለከፍተኛ ሐዘን ይዳርጋል። ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት መፈጸም ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ማወቃችን ይህን ዓይነቱን ድርጊት እንድንፈጽም የሚደርስብንን ፈተና እንድንቋቋም ሊገፋፋን ይገባል ቢባል አትስማማም?

14. ምሳሌ 6:30-35 ኃጢአት መሥራትን አስመልክቶ ምን ትምህርት ይዟል?

14 አንድ ሰው ምንዝር መፈጸሙ ያስከተለውን ጉዳት በምንም መንገድ ሊያካክስ እንደማይችል ማወቁ ከፍተኛ የሆነ የራስ ወዳድነት ስሜት ከሚንጸባረቅበት ከዚህ ድርጊት እንዲርቅ ሊገፋፋው ይገባል። ምሳሌ 6:30-35 ሌባ በመራቡ ምክንያት ቢሰርቅ ሰዎች ሊያዝኑለት እንደሚችሉ ከገለጸ በኋላ የሚያመነዝርን ሰው ግን መጥፎ በሆነው የልብ ዝንባሌው ምክንያት እንደሚንቁት ይገልጻል። የሚያመነዝር ሰው “ራሱን ያጠፋል።” እንደ ሙሴ ሕግ ቢሆን ኖሮ ይህ ሰው ይገደል ነበር። (ዘሌዋውያን 20:10) የሚያመነዝር ሰው የራሱን የጾታ ፍላጎት ለማርካት ሲል ብቻ በሌሎች ላይ ሐዘን የሚያስከትል ድርጊት ይፈጽማል። ከዚህም በተጨማሪ ምንዝር ፈጽሞ ንስሐ የማይገባ ሰው በአምላክ ፍቅር ውስጥ አይኖርም፤ ከዚህ ይልቅ ንጹሕ ከሆነው የክርስቲያን ጉባኤ ይወገዳል።

ምንጊዜም ንጹሕ ሕሊና ይኑርህ

15. “በጋለ ብረት የተጠበሰ” ሕሊና ምን ዓይነት ነው?

15 ከአምላክ ፍቅር እንዳንወጣ የምንፈልግ ከሆነ ሕሊናችን በኃጢአት እንዲደነዝዝ መፍቀድ የለብንም። የዓለምን የዘቀጠ የሥነ ምግባር ደንብ እንደማንቀበል የታወቀ ነው። ከዚህም ባሻገር ጓደኛን፣ የምናነባቸውን ጽሑፎችና መዝናኛን በመሳሰሉ ጉዳዮች ረገድ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርጫ ማድረግ ይኖርብናል። ጳውሎስ ‘በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች እምነትን ክደው አታላይ መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት ይከተላሉ። እንዲህ ያለው ትምህርት የሚመጣው ኅሊናቸው በጋለ ብረት የተጠበሰ ያህል ከደነዘዘባቸው ግብዝ ውሸታሞች ነው’ በማለት አስጠንቅቋል። (1 ጢሞቴዎስ 4:1, 2) “በጋለ ብረት የተጠበሰ” ሕሊና ስሜት አልባ ከሆነ ጠባሳ ጋር ይመሳሰላል። እንዲህ ያለው ሕሊና ከከሃዲዎችም ሆነ ከእምነት እንድንወጣ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች እንድንርቅ አያስጠነቅቀንም።

16. ንጹሕ ሕሊና መያዝ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

16 መዳናችን የተመካው ንጹሕ ሕሊና በመያዛችን ላይ ነው። (1 ጴጥሮስ 3:21) ‘ለሕያው አምላክ ቅዱስ አገልግሎት’ እናቀርብ ዘንድ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ ባለን እምነት አማካኝነት ሕሊናችን ከሙት ሥራዎች ነጻ ሆኗል። (ዕብራውያን 9:13, 14 NW) ሆን ብለን ኃጢአት ስንሠራ ግን ሕሊናችን ስለሚረክስ ለአምላክ አገልግሎት የምንበቃ ንጹሕ ሰዎች መሆናችን ያከትምለታል። (ቲቶ 1:15) ይሁን እንጂ በይሖዋ እርዳታ ንጹሕ ሕሊና ማግኘት እንችላለን።

መጥፎ ምግባር ከመፈጸም የምንርቅባቸው ሌሎች መንገዶች

17. ይሖዋን ‘በፍጹም ልብ መከተል’ ምን ጥቅም ያስገኛል?

17 በጥንቷ እስራኤል ይኖር እንደነበረው እንደ ካሌብ ይሖዋን ‘በፍጹም ልብህ ተከተል።’ (ዘዳግም 1:34-36) አምላክ የሚጠብቅብህን አድርግ እንዲሁም “ከአጋንንት ማዕድ” ስለመካፈል ፈጽሞ አታስብ። (1 ቆሮንቶስ 10:21) ክህደትን ተቃወም። በይሖዋ ማዕድ የሚቀርብልህን መንፈሳዊ ምግብ ብቻ በአመስጋኝነት ተመገብ፤ ይህን ማድረግህ ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ወይም ከክፉ መናፍስታዊ ኃይሎች ማታለያ ይጠብቅሃል። (ኤፌሶን 6:12፤ ይሁዳ 3, 4) መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትን፣ በስብሰባዎች መገኘትንና በመስክ አገልግሎት መካፈልን በመሳሰሉ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አተኩር። ይሖዋን በሙሉ ልብ እስከተከተልክና የጌታ ሥራ የበዛልህ እስከሆንክ ድረስ ደስተኛ እንደምትሆን እርግጠኛ ሁን።—1 ቆሮንቶስ 15:58

18. ለይሖዋ ያለህ ፍርሃት በምግባርህ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?

18 ‘በአክብሮትና በፍርሀት ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ’ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። (ዕብራውያን 12:28 NW) ለይሖዋ ያለህ አክብሮታዊ ፍርሃት ማንኛውንም የዓመጽ ጎዳና ከመከተል እንድትርቅ ይገፋፋሃል። ከዚህም በተጨማሪ ጴጥሮስ “ለሰው ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ የሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ፣ በዚህ ምድር በእንግድነት ስትኖሩ በፍርሀት ኑሩ” በማለት ለቅቡዓን ባልንጀሮቹ ከሰጣቸው ምክር ጋር ተስማምተህ እንድትኖር ይረዳሃል።—1 ጴጥሮስ 1:17

19. ከአምላክ ቃል የተማርካቸውን ነገሮች ዘወትር በተግባር ላይ ማዋል ያለብህ ለምንድን ነው?

19 ከአምላክ ቃል የምትማራቸውን ነገሮች ምንጊዜም በተግባር ላይ አውል። ይህም ‘መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳቸውን እንዳስለመዱ የበሰሉ ሰዎች’ እንድትሆን ስለሚያስችልህ ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም እንድትርቅ ይረዳሃል። (ዕብራውያን 5:14) ለአነጋገርህና ለምግባርህ ግዴለሽ ከመሆን ይልቅ በእነዚህ ክፉ ጊዜያት ‘ዘመኑን በሚገባ በመዋጀት’ ጥበበኛ ትሆን ዘንድ በጥንቃቄ ተመላለስ። ‘የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውል’ እንዲሁም ፈቃዱን ማድረግህን ቀጥል።—ኤፌሶን 5:15-17፤ 2 ጴጥሮስ 3:17

20. ከመጎምጀት መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?

20 ከመጎምጀት ይኸውም የሌላውን ሰው ንብረት በስግብግብነት ከመመኘት ፈጽሞ ራቅ። ከአሥሩ ትእዛዛት ውስጥ አንዱ “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ [“አትጎምዥ፣” ኒው ኢንተርናሽናል ቨርዥን]፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የእርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የእርሱ የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ” ይላል። (ዘፀአት 20:17) ይህ ሕግ የአንድን ሰው ቤት፣ ሚስት፣ አገልጋዮች፣ እንስሳትና የመሳሰሉ ነገሮችን ለመጠበቅ አገልግሏል። ከሁሉም በላይ ግን ኢየሱስ እንደተናገረው መጎምጀት አንድን ሰው ያረክሰዋል።—ማርቆስ 7:20-23

21, 22. አንድ ክርስቲያን ከኃጢአት ለመራቅ ሊወስዳቸው የሚችላቸው አንዳንድ የመከላከያ እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው?

21 ምኞት ወደ ኃጢአት እንዳይመራህ አንዳንድ የመከላከያ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብሃል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞትም ከፀነሰች በኋላ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 1:14, 15) ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ከዚህ ቀደም የመጠጥ ችግር ከነበረበት የአልኮል መጠጦችን ቤቱ ውስጥ ላለማስቀመጥ ይወስን ይሆናል። በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን በተቃራኒ ጾታ ላለመፈተን የሥራ ቦታውን መቀየር ወይም ሥራውን መልቀቅ ይጠበቅበት ይሆናል።—ምሳሌ 6:23-28

22 ሌላው ቀርቶ ወደ ኃጢአት ሊያደርስ የሚችለውን የመጀመሪያ እርምጃ እንኳ እንዳትወስድ ተጠንቀቅ። ማሽኮርመምና የብልግና ሐሳቦችን ማውጠንጠን ዝሙት ወይም ምንዝር ወደ መፈጸም ሊመሩን ይችላሉ። አንድ ሰው ጥቃቅን በሆኑ ጉዳዮች መዋሸት መጀመሩ በትላልቅ ጉዳዮችም እንዲዋሽ ሊያደፋፍረው ይችላል፤ ይህም ኃጢአት ወደሆነው የመዋሸት ልማድ ይመራዋል። ትናንሽ የሚመስሉ ነገሮችን መስረቅ የአንድን ሰው ሕሊና ሊያደነዝዘውና ትላልቅ የሆኑ ነገሮችን ወደ መስረቅ ሊያደርሰው ይችላል። አንድ ሰው ያን ያህል ክብደት የላቸውም የሚባሉ የክህደት አስተሳሰቦችን ማስተናገድ መጀመሩ የለየለት ከሃዲ እንዲሆን ያደርገው ይሆናል።—ምሳሌ 11:9፤ ራእይ 21:8

ኃጢአት ብትሠራስ?

23, 24. ከ2 ዜና መዋዕል 6:29, 30 እና ከምሳሌ 28:13 ምን ማጽናኛዎችን ማግኘት እንችላለን?

23 ሁሉም ሰዎች ፍጹማን አይደሉም። (መክብብ 7:20) ይሁንና ከባድ ኃጢአት ከሠራህ ንጉሥ ሰሎሞን የይሖዋ ቤተ መቅደስ በተመረቀበት ወቅት ካቀረበው ጸሎት ማጽናኛ ማግኘት ትችላለህ። ሰሎሞን እንደሚከተለው ሲል ጸልዮአል:- “ከሕዝብህ ከእስራኤል ማንም ሰው ጭንቀቱና ሕመሙ ተሰምቶት፣ እጁን ወደዚህ ቤተ መቅደስ በመዘርጋት ጸሎትና ልመና ቢያቀርብ፣ በሰማይ በማደሪያህ ሆነህ ስማ፤ ይቅርም በል፤ የሰውን ልብ የምታውቅ አንተ ብቻ ስለ ሆንህ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ክፈለው።”—2 ዜና መዋዕል 6:29, 30

24 አዎን፣ አምላክ የልባችንን ያውቃል እንዲሁም ይቅር ባይ ነው። ምሳሌ 28:13 “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል” ይላል። አንድ ሰው ከልብ ተጸጽቶ ከተናዘዘና ኃጢአት መሥራቱን ከተወ የአምላክን ምሕረት ማግኘት ይችላል። ይሁንና በመንፈሳዊ ከተዳከምህ ከአምላክ ፍቅር ውስጥ እንዳትወጣ ምን ሊረዳህ ይችላል?

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

• ለአምላክና ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ኃጢአት ከመሥራት እንድንርቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

• ለሰዎች ያለን እውነተኛ ፍቅር የጾታ ብልግና ከመፈጸም እንድንቆጠብ የሚያደርገን ለምንድን ነው?

• መጥፎ ምግባርን ለማስወገድ የሚያስችሉን አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሁዳ ከይሖዋ ፍቅር እንዳንወጣ ምን ማድረግ እንደምንችል ገልጾልናል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጋብቻ መፍረስ ታማኝ የሆነውን የትዳር ጓደኛና ልጆችን ለከፍተኛ ሐዘን ይዳርጋል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልክ እንደ ካሌብ ይሖዋን ‘በፍጹም ልብህ ለመከተል’ ቆርጠሃል?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ በፈተናዎች እንዳትሸነፍ እንዲያግዝህ ዘወትር ጸልይ