በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐቀኛ መሆን ይክሳል

ሐቀኛ መሆን ይክሳል

ሐቀኛ መሆን ይክሳል

ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት መፈጸም የተጀመረው በኤደን የአትክልት ሥፍራ ነው። ያም ሆኖ በአብዛኞቹ ባሕሎችና ማኅበረሰቦች ውስጥ ለሐቀኝነት የላቀ ግምት የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ መዋሸትና ማታለል ይወገዛሉ እንዲሁም እንደ አስጸያፊ ድርጊት ይታያሉ። በእርግጥም እምነት የሚጣልበት ሰው ሆኖ መገኘት ያኮራል። ይሁን እንጂ በዚህ ዘመናዊ ኅብረተሰብ ውስጥ ለመኖር ከተፈለገ ሐቀኛ ሆኖ መኖር አይቻልም የሚለው አመለካከት እየተለመደ መጥቷል። አንተስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል? ሐቀኝነት ልናዳብረው የሚገባ ባሕርይ ነው? ሐቀኝነትን ወይም ሐቀኝነት የጎደለውን ድርጊት የምትለካበት መሥፈርት ምንድን ነው?

አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን በአነጋገራችንም ይሁን በአኗኗራችን ሐቀኞች ልንሆን ይገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልደረቦቹን “እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ኤፌሶን 4:25) በተጨማሪም ጳውሎስ ‘በሁሉም መንገድ በመልካም አኗኗር [“በሐቀኝነት፣” NW] ለመኖር እንናፍቃለን’ ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 13:18) ሐቀኞች እንድንሆን የሚያነሳሳን የሌሎችን ውዳሴ ለማግኘት ያለን ፍላጎት አይደለም። ሐቀኛ የምንሆነው ፈጣሪያችንን ስለምናከብርና እርሱን ማስደሰት ስለምንፈልግ ነው።

ማንነትህን አትደብቅ

በብዙ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች አንዳንድ ጥቅሞችን ለማግኘት ሲሉ ስለ ራሳቸው የተዛባ መረጃ ያቀርባሉ። ወደ አንድ አገር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመግባት ወይም ብቃቱ ሳይኖራቸው አንድን ሥራ አሊያም ሥልጣን ለማግኘት ሲሉ የተጭበረበሩ ሰነዶችን፣ ዲፕሎማዎችንና መታወቂያዎችን ይጠቀማሉ። አንዳንድ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸው ትምህርት የሚያገኙበትን ጊዜ ለማራዘም ሲሉ በልጆቻቸው የልደት ካርድ ላይ የተሳሳተ መረጃ እንዲሰፍር ያደርጋሉ።

አምላክን ማስደሰት የምንፈልግ ከሆነ ግን ከማታለል መራቅ ይኖርብናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ “የእውነት አምላክ” ስለሆነ ከእርሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የሚፈልጉ ሰዎችም እውነተኛ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል። (መዝሙር 31:5) ከይሖዋ ጋር ጥብቅ የሆነ ወዳጅነት መመሥረት ከፈለግን ‘እውነትን የማይናገሩ ሰዎችን’ ማለትም ‘ማንነታቸውን የሚደብቁትን’ መምሰል አይኖርብንም።—መዝሙር 26:4 NW

በተጨማሪም ሰዎች ስሕተት ከፈጸሙ በኋላ ከሚደርስባቸው ቅጣት ለማምለጥ ሲሉ እውነታውን መደበቃቸው የተለመደ ነው። ሌላው ቀርቶ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለ ሰው እንኳ እንደዚህ ለማድረግ ይፈተን ይሆናል። ለአብነት ያህል፣ በአንድ ጉባኤ ውስጥ የነበረ ወጣት አንዳንድ የኃጢአት ድርጊቶችን እንደፈጸመ ለሽማግሌዎች ተናገረ። ሆኖም ስርቆት እንደፈጸመ የሚያጋልጥ መረጃ እያለም መስረቁን አላመነም። በመጨረሻም መዋሸቱ ስለተረጋገጠ ከጉባኤ ተወገደ። እውነቱን ሙሉ በሙሉ ተናግሮ ከይሖዋ ጋር ያለውን ውድ ዝምድና እንደገና እንዲያድስ የሚያስችለውን እርዳታ ቢቀበል ኖሮ የተሻለ አይሆንም ነበር? መጽሐፍ ቅዱስም እንዲህ ይላል:- “የጌታን ቅጣት አታቃል፤ በሚገሥጽህም ጊዜ ተስፋ አትቊረጥ፤ ምክንያቱም ጌታ የሚወደውን ይገሥጻል።”—ዕብራውያን 12:5, 6

አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ለማገልገል የሚፈልግ አንድ ወንድም ያሉበትን ችግሮች አሊያም ቀደም ሲል የፈጸማቸውን መጥፎ ድርጊቶች ለመደበቅ ይሞክር ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል የማመልከቻ ቅጽ ሲሞላ እውነቱን ከገለጸ ይህን መብት ለማግኘት ላይበቃ እንደሚችል በማሰብ ጤንነትንና ሥነ ምግባርን በተመለከተ ለቀረቡት ጥያቄዎች የተሟላ መረጃ ላይሰጥ ይችላል። ምናልባት ይህ ሰው “አልዋሸሁም” ብሎ ያስብ ይሆናል፤ ሆኖም ግልጽና ሐቀኛ ሆኗል ሊባል ይቻላል? በምሳሌ 3:32 ላይ የሰፈረውን ነጥብ ልብ በል:- “እግዚአብሔር ጠማማን [“አታላይ የሆነን ሰው፣” NW] ሁሉ ይጸየፋልና፤ ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል።”

ሐቀኛ መሆን ሲባል በዋነኝነት ለራሳችን ሐቀኛ መሆን ማለት ነው። አብዛኛውን ጊዜ፣ ትክክል ወይም እውነት የሆነውን ነገር ከማመን ይልቅ እኛ ደስ ያለንን ማመን ይቀለናል። ጥፋታችንን በሌሎች ላይ ማላከክ ምንኛ ቀላል ነው! ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ሳኦል የታዘዘውን ሳይፈጽም የቀረው ለምን እንደሆነ ሲናገር ጥፋቱን በሌሎች ላይ አሳቧል። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ንጉሥ እንዳይሆን ንቆታል። (1 ሳሙኤል 15:20-23) እንደሚከተለው ብሎ ወደ ይሖዋ የጸለየው ንጉሥ ዳዊት ግን ከሳኦል የተለየ ነበር:- “ኀጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፤ በደሌንም አልሸሸግሁም፤ ደግሞም ‘መተላለፌን ለእግዚአብሔር እናዘዛለሁ’ አልሁ፤ አንተም የኀጢአቴን በደል፣ ይቅር አልህ።”—መዝሙር 32:5

ሐቀኝነት በረከት ያስገኛል

ሐቀኛ መሆንህ ወይም አለመሆንህ ሌሎች ስለ አንተ ባላቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሰዎች፣ አንድ ጊዜ ብቻ እንኳ እንዳታለልካቸው ከተገነዘቡ በአንተ ላይ ያላቸው እምነት ይጠፋል፤ ይህን መልሶ ማግኘት ደግሞ ቀላል አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛና ሐቀኛ ከሆንክ እምነት የሚጣልበት ታማኝ ሰው በመሆንህ ትታወቃለህ። የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ የመሰለውን ስም አትርፈዋል። አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።

የአንድ ድርጅት ዲሬክተር አብዛኞቹ ሠራተኞች መሥሪያ ቤቱን እንዳጭበረበሩ ስለተገነዘበ ለፖሊስ አመለከተ። ዲሬክተሩ፣ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ ሠራተኛ ከሌሎቹ ጋር አብሮ እንደታሰረ ሲያውቅ ሠራተኛውን ወዲያውኑ ለማስፈታት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደ። ይህን ያደረገው ለምን ነበር? ምክንያቱም ይህ ሠራተኛ ሐቀኛ ብሎም ከወንጀሉ ንጹሕ እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ነው። ይህ የይሖዋ ምሥክር ሥራውን የቀጠለ ሲሆን ሌሎቹ ግን ከሥራ ተባረሩ። ሌሎቹ የይሖዋ ምሥክሮችም ይህ ወንድም በምግባሩ የይሖዋን ስም ስላስከበረ በጣም ተደስተዋል።

መልካም ምግባር ልብ ሳይባል አይታለፍም። በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ በሚገኝ ሰፊ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ ላይ የተዘረጋ ድልድይ ላይ ተነጥፈው የነበሩ ጣውላዎች ስለ ተሰረቁ ጥገና ያስፈልገው ነበር። የመንደሩ ነዋሪዎች ገንዘብ አሰባስበው ጣውላዎቹን ለመተካት ወሰኑ፤ ይሁን እንጂ ገንዘቡን በታማኝነት ሊይዝላቸው የሚችለው ማን ነው? ሁሉም፣ ‘ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ መሆን አለበት’ የሚል ስምምነት ላይ ደረሱ።

በሌላ የአፍሪካ አገር ውስጥ የፖለቲካና የዘር ግጭት ተጧጡፎ በነበረበት ጊዜ በአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ በሒሳብ ሞያ የሚሠራ የይሖዋ ምሥክር ሕይወቱ አደጋ ላይ ወደቀ። በዚህ ጊዜ መሥሪያ ቤቱ ይህ የይሖዋ ምሥክር ወደ ሌላ ቦታ ተዛውሮ እንዲሠራ አደረገ። ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ድረስ የይሖዋ ምሥክሩ ወጪው ተሸፍኖለት በሌላ አገር ውስጥ ለበርካታ ወራት እንዲሠራ ዝግጅት ተደረገ። እንዲህ ዓይነት ዝግጅት የተደረገለት ለምን ነበር? ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ድርጅቱን ለማጭበርበር ሴራ ጠንስሰው ከነበሩ ሰዎች ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አልነበረም። አስተዳደሩ ይህ ሠራተኛ በሐቀኝነቱ ፈጽሞ እንደማይታማ ተገንዝቧል። ይህ ሠራተኛ በማታለል ድርጊቱ የታወቀ ቢሆን ኖሮ እርሱን ለመርዳት ፈቃደኛ ይሆኑ ነበር?

ምሳሌ 20:7 “ጻድቅ ነቀፋ የሌለበት ሕይወት ይመራል” ሲል ይናገራል። አንድ ሰው ሐቀኛ ነው ከተባለ ያለ ነቀፋ ይመላለሳል ማለት ነው። ሰዎችን አያጭበረብርም ወይም አያታልልም። አንተ ከሌሎች የምትጠብቀው ይህንኑ አይደለም? ሐቀኝነት በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ሐቀኝነት ለአምላክና ለጎረቤቶቻችን ፍቅር እንዳለን የምንገልጽበት መንገድ ነው። ሐቀኞች በመሆን፣ ኢየሱስ የሰጠውን ሥነ ምግባራዊ መመሪያ መከተል እንደምንፈልግ እናሳያለን። “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው” ብሏል።—ማቴዎስ 7:12፤ 22:36-39

በማንኛውም ጊዜ ሐቀኛ ሆኖ መገኘት መሥዋዕትነት ቢጠይቅም እንዲህ በማድረግ የሚገኘው ንጹሕ ሕሊና መሥዋዕት ከምናደርገው ማንኛውም ነገር ይበልጣል። ሐቀኛና ቀና የሆነ ሰው ውሎ አድሮ ከሁሉ የላቀ በረከት ያገኛል። በእርግጥም ከይሖዋ ጋር ያለን ጥሩ ዝምድና በዋጋ ሊተመን እንደማይችል የታወቀ ነው። ታዲያ በሰዎች ዘንድ አክብሮት ለማትረፍ ወይም ሕገ ወጥ የሆኑ አንዳንድ ጥቅሞችን ለማግኘት ስንል ሐቀኝነታችንን በማጉደል ይህን ዝምድናችንን ለምን እናጣለን? ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን መዝሙራዊው እንዲህ ብሎ በተናገራቸው ቃላት እንተማመን:- “እግዚአብሔርን መታመኛው ያደረገ፣ ወደ ትዕቢተኞች የማይመለከት፣ የሐሰት አማልክትን [“ሐሰትን፣” የግርጌ ማስታወሻ] ወደሚከተሉት የማያይ፣ ሰው ብፁዕ ነው።”—መዝሙር 40:4

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እውነተኛ ክርስቲያኖች የተጭበረበሩ ሰነዶችን አይገዙም እንዲሁም አይጠቀሙም