በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነን ለመቀጠል ያደረግነው ትግል

በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነን ለመቀጠል ያደረግነው ትግል

የሕይወት ታሪክ

በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነን ለመቀጠል ያደረግነው ትግል

ሮልፍ ብሩገማየር እንደተናገረው

እስር ቤት እያለሁ የደረሰኝ የመጀመሪያው ደብዳቤ ከአንድ ጓደኛዬ የተላከ ነበር። እናቴና ሦስቱ ታናናሽ ወንድሞቼ ማለትም ፒተር፣ ዮከንና ማንፍሬድ እንደታሰሩ ጻፈልኝ። በዚህም የተነሳ ሁለቱን ትንንሽ እህቶቼን የሚንከባከባቸው አልነበረም። የምሥራቅ ጀርመን ባለ ሥልጣናት ቤተሰባችንን እንዲህ የሚያሳድዱት ለምን ነበር? በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነን እንድንቀጥልስ የረዳን ምንድን ነው?

ለተኛው የዓለም ጦርነት ሰላም የሰፈነበትን የልጅነት ሕይወታችንን አደፈረሰው። ጦርነትን ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ በገዛ ዓይናችን ተመልክተናል። አባታችን ከጀርመን የጦር ሰራዊት ጋር የተቀላቀለ ሲሆን ተማርኮ እስር ቤት እያለ ሞተ። በዚህም የተነሳ፣ ቤርታ የተባለችው እናቴ ከአንድ እስከ 16 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ስድስት ልጆች ብቻዋን የመንከባከብ ኃላፊነት ወደቀባት።

እናቴ ትከታተለው የነበረው እምነት ሃይማኖትን ጨርሶ እንድትጠላ ስላደረጋት ስለ አምላክ ምንም መስማት አትፈልግም ነበር። ይሁን እንጂ በ1949 አንድ ቀን ኢልዜ ፉክስ የተባለች እጥር ምጥን ያለች አንዲት ብልህ ሴት ስለ አምላክ መንግሥት ልታወያየን ቤታችን መጣች። ይህች ሴት የምታቀርበው ጥያቄና ማስረጃ የእናቴን የማወቅ ፍላጎት አነሳሳው። እናቴ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቷ ተስፋዋን አለመለመው።

መጀመሪያ ላይ እኔና ወንድሞቼ ጥርጣሬ አድሮብን ነበር። ናዚዎች በኋላም ኮሚኒስቶች የሰጡን አስደሳች ሆኖም ያልተፈጸሙ ተስፋዎች ምንም አልፈየዱልንም። በመሆኑም የትኛውንም አዲስ ተስፋ እንጠራጠር ነበር። ያም ሆኖ ግን ጦርነትን ባለመደገፋቸው ምክንያት በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ስለነበሩ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ስናውቅ በጣም ተደነቅን። በቀጣዩ ዓመት እኔ፣ እናቴና ፒተር ተጠመቅን።

ትንሹ ወንድማችን ማንፍሬድ የተጠመቀ ቢሆንም ልቡ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አልተነካም ነበር ማለት ይቻላል። ኮሚኒስቶች በ1950 ሥራችንን ካገዱት በኋላ በክፋታቸው የሚታወቁት ሽታዚ የተባሉት የደኅንነት ፖሊሶች ሲያስፈራሩት ስብሰባ የምናደርግበትን ቦታ ተናገረ። እናቴና ሌሎቹ ወንድሞቼ ወደ ወኅኒ ቤት እንዲወርዱ ያደረጋቸው ክስተት ይህ ነበር።

በእገዳ ሥር ማገልገል

ሥራችን ሲታገድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ምሥራቅ ጀርመን በድብቅ ማስገባት ነበረብን። ሥራችን በበርሊን ምዕራባዊ ክፍል ስላልታገደ ጽሑፎቹን ጠረፍ አቋርጦ በማጓጓዙ ሥራ እንደ መልእክተኛ ሆኜ አገለግል ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜያት ከፖሊሶች እጅ ባመልጥም ኅዳር 1950 ላይ ግን ተይዤ እስር ቤት ገባሁ።

ሽታዚዎች ምንም መስኮት በሌለው አንድ ምድር ቤት ውስጥ አሰሩኝ። ቀን ቀን እንድተኛ አይፈቀዱልኝም፤ ማታ ማታ ደግሞ በጥያቄ ሲያጣድፉኝ አንዳንዴም ሲደበድቡኝ ያድራሉ። እናቴ፣ ፒተርና ዮከን በ1951 ፍርድ ቤት በቀረብኩበት ወቅት መጥተው እስካየኋቸው ጊዜ ድረስ ከማንኛውም የቤተሰቤ አባል ጋር ተገናኝቼ አላውቅም ነበር። ፍርድ ቤቱም የስድስት ዓመት እስራት በየነብኝ።

እኔ ፍርድ ቤት ከቀረብኩ ከስድስት ቀናት በኋላ ፒተር፣ ዮከንና እናቴ ታሰሩ። በኋላ ላይ አንዲት የእምነት ባልንጀራችን የ11 ዓመቷን እህቴን ሃነሎሬን እርሷ ጋር እንድትኖር አደረገች። አክስቴ ደግሞ የ7 ዓመቷን ሳቢኔን ለመንከባከብ ወደ ቤቷ ወሰደቻት። ሽታዚዎች እናቴንና ወንድሞቼን እንደ አደገኛ ወንጀለኞች በመቁጠር የጫማ ማሰሪያቸውን ክር እንኳ ወሰዱባቸው። ምርመራ በሚደረግባቸው ጊዜ ሁሉ እንዲቆሙ ያስገድዷቸው ነበር። በኋላም እያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት ዓመት ተፈረደባቸው።

በ1953 እኔና ሌሎች አንዳንድ የይሖዋ ምሥክር እስረኞች፣ በአንድ የጦር አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እንድንካፈል ብንታዘዝም ለመሥራት ፈቃደኞች አልሆንም። ባለ ሥልጣናቱ ለ21 ቀናት ብቻችንን በማሰር፣ በሌላ አባባል ምንም ሥራ እንዳንሠራና ፈጽሞ ደብዳቤ እንዳይደርሰን እንዲሁም በጣም ጥቂት ምግብ እንዲሰጠን በማድረግ ቀጡን። አንዳንድ ክርስቲያን እህቶቻችን የሚታደላቸው ራሽን በጣም ትንሽ ቢሆንም ከዚያችው ላይ ዳቦ አስተርፈው በድብቅ ይልኩልን ነበር። ይህም ከአኒ ጋር እንድንተዋወቅ መንገድ ከፈተልኝ። እርሷ በ1956 እኔ ደግሞ በ1957 የተፈታን ሲሆን በኋላም ተጋባን። ከተጋባን ከአንድ ዓመት በኋላ ልጃችን ሩት ተወለደች። ፒተር፣ ዮከንና ሃነሎሬም ያገቡት በተመሳሳይ ወቅት ነው።

ከወኅኒ ቤት ከወጣሁ ሦስት ዓመት ገደማ እንደሆነኝ እንደገና ታሰርኩ። አንድ የሽታዚ መኮንን ለእነርሱ ሰላይ እንድሆንላቸው ሊያሳምነኝ ሞክሮ ነበር። “ውድ ሚስተር ብሩገማየር፣ እባክህ ምክንያታዊ ሁን። የእስር ቤት ሕይወት ምን እንደሚመስል ታውቀዋለህ፤ እኛ ደግሞ ያ ሁሉ [መከራ] እንደገና እንዲደርስብህ አንፈልግም። የይሖዋ ምሥክር ሆነህ መቀጠል፣ በጥናትህ መግፋትና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያሰኘህን መናገር ትችላለህ። እኛ የምንፈልገው ወቅታዊ መረጃ ማግኘት ብቻ ነው። ደግሞም ስለ ባለቤትህና ስለ ትንሿ ልጅህ አስብ” አለኝ። መጨረሻ ላይ የተናገረው ነገር በጣም ረበሸኝ። ሆኖም ይሖዋ እስር ቤት ብገባም ቤተሰቦቼን እኔ ላደርግላቸው ከምችለው በላይ እንደሚንከባከባቸው አውቅ ነበር። ደግሞም አድርጎታል!

ባለ ሥልጣናቱ፣ አኒ ሙሉ ቀን እንድትሠራ በማስገደድ በአዘቦቱ ቀናት ሩትን ሌሎች ሰዎች እንዲይዙላት ለማድረግ አስበው ነበር። አኒ ግን ቀን ቀን ሩትን እየጠበቀች ሌሊት በመሥራት ሁኔታውን ተቋቁማለች። መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ባለቤቴን በጣም ይንከባከቧት እንዲሁም ለሌሎች ለማካፈል እስኪተርፋት ድረስ ብዙ ነገር ይሰጧት ነበር። በዚህ መሃል ለተጨማሪ ስድስት ዓመት ያህል በእስር ቤት ውስጥ ቆየሁ።

እስር ቤት እያለን በእምነታችን ለመጽናት ያደረግነው ጥረት

እንደገና ወኅኒ ቤት ስገባ አንድ ክፍል ውስጥ አብረውኝ የታሰሩት ወንድሞች በቅርቡ ምን አዳዲስ ነገሮች እንደታተሙ ለማወቅ ጓጉተው ነበር። እስር ቤት ከመግባቴ በፊት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችን በትጋት ማጥናቴና በስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ መገኘቴ እንዴት እንዳስደሰተኝ መግለጽ ያቅተኛል! ምክንያቱም ለወንድሞች የመንፈሳዊ ብርታት ምንጭ መሆን ችያለሁ።

ጠባቂዎቹ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሰጡን ስንጠይቃቸው እንዲህ አሉን:- “ለይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ መስጠት ማለት ወኅኒ ቤት ላለ ዘራፊ እንዲያመልጥ የሚረዱትን መሰርሰሪያ መሣሪያዎች እንደ መስጠት ነው።” በኃላፊነት ላይ ያሉ ወንድሞች በዕለቱ የምናስብበት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይመርጣሉ። በቅጥር ግቢው የእግር ጉዞ እንድናደርግ በየቀኑ በሚሰጠን ግማሽ ሰዓት ውስጥ ስፖርት ከመሥራትም ሆነ ንጹሕ አየር ከማግኘት ይልቅ የሚያጓጓን የዕለቱን ጥቅስ መስማት ነበር። በአምስት ሜትር ርቀት እንድንራራቅ ይጠበቅብን ነበር፤ በዚህ ጊዜ እንድናወራ ባይፈቀድልንም እንኳ ስለ ጥቅሱ የምንነጋገርበት መንገድ አላጣንም። ወደታሰርንባቸው ክፍሎች ስንመለስ እያንዳንዳችን የሰማነውን በመነጋገር የዕለቱን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይታችንን እናደርጋለን።

ከጊዜ በኋላ አንድ ሰላይ እንቅስቃሴያችንን ስላጋለጠብን በአንድ ክፍል ውስጥ ብቻዬን እንድታሰር ተደረግሁ። በዚያን ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃሌ አጥንቼ ስለነበር በጣም ደስ አለኝ! አለምንም ሥራ ብቻዬን በታሰርኩበት በዚያን ወቅት በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማሰላሰል ጊዜዬን አሳልፍ ነበር። በኋላም ወደ ሌላ እስር ቤት ስዛወር ጠባቂው ከሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር አንድ ክፍል ውስጥ አሰረኝ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሰጠን ደግሞ ደስታችን እጥፍ ድርብ ሆነ። ለስድስት ወራት ብቻዬን ከታሰርኩ በኋላ ከእምነት ባልንጀሮቼ ጋር እንደገና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት መቻሌ አስደሰተኝ።

ወንድሜ ፒተር በሌላ እስር ቤት ውስጥ በነበረበት ወቅት ጸንቶ እንዲቀጥል የረዳውን ነገር ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሕይወት በአዲሱ ዓለም ምን እንደሚመስል አስብ እንዲሁም በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ አሰላስል ነበር። የይሖዋ ምሥክር የሆንነው እስረኞች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን በመጠያየቅ ወይም አንዳችን ለሌላው ቅዱስ ጽሑፋዊ ፈተናዎችን በማቅረብ እርስ በርስ እንበረታታ ነበር። ሆኖም ሕይወት ቀላል አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ አሥራ አንዳችንም 12 ካሬ ሜትር በሆነ ክፍል ውስጥ እንታጨቃለን። ለምግብ፣ ለመኝታ፣ ለመታጠቢያ ሌላው ቀርቶ ለመጸዳጃ ቤትነት እንኳ የተጠቀምነው ይህንኑ ክፍል ነው። በዚህ ምክንያት በቀላሉ እንበሳጭና እንረበሽ ነበር።”

ሌላው ወንድሜ ዮከን ደግሞ እስር ቤት ስላጋጠመው ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ከመዝሙር መጽሐፋችን ላይ የማስታውሳቸውን መዝሙሮች እዘምር እንዲሁም ቀደም ሲል ባጠናሁት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ በየቀኑ አሰላስል ነበር። ከእስር ቤት ከተፈታሁ በኋላም መንፈሳዊ ትምህርቶችን የመቅሰም ልማዴን ቀጠልኩ። በየቀኑ ከቤተሰቤ ጋር ሆኜ የዕለቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አነባለሁ። እንዲሁም ለሁሉም ስብሰባዎች እንዘጋጃለን።”

እናቴ ከወኅኒ ቤት ተለቀቀች

እናቴ ሁለት ዓመት ከጥቂት ወራት ከታሰረች በኋላ ተፈታች። ነፃነቷን በመጠቀም ሃነሎሬንና ሳቢኔን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናቻቸው። ይህ ደግሞ ለእምነታቸው አስተማማኝ መሠረት ጥሎላቸዋል። ከዚህም በላይ በአምላክ ላይ ባላቸው እምነት የተነሳ በትምህርት ቤት የሚያጋጥሟቸውን ሁኔታዎች እንዴት መወጣት እንደሚችሉ ታስተምራቸው ነበር። ሃነሎሬ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “ቤት ውስጥ እርስ በርስ ስለምንበረታታ በአቋማችን ምክንያት ሊደርሱብን ስለሚችሉት ችግሮች አንጨነቅም። ቤተሰባችን በጣም ይቀራረብ ስለነበር የደረሰብንን ማንኛውንም ችግር መቋቋም ችለናል።”

ሃነሎሬ እንዲህ ስትል አክላ ተናግራለች:- “በተጨማሪም እስር ቤት ላሉት ወንድሞቻችን መንፈሳዊ ምግብ እናደርስላቸው ነበር። በሰም በተለቀለቀ ወረቀት ላይ ሙሉውን መጠበቂያ ግንብ በትንንሽ የእጅ ጽሑፍ እንገለብጠዋለን። ከዚያም ውኃ በማያርሰው ወረቀት እንጠቀልለውና በየወሩ በምንልክላቸው የፕሪም ዘቢብ ጥቅልል ውስጥ እንደብቀዋለን። ፕሪሞቹ ‘በጣም እንደሚጣፍጡ’ የሚገልጽ መልስ ሲደርሰን ይሰማን የነበረውን ደስታ መግለጽ ያዳግተኛል። በሥራችን በጣም እንመሰጥ ስለነበር በእርግጥም አስደሳች ጊዜ ሆኖልን ነበር ማለት እችላለሁ።”

በእገዳ ሥር መኖር

ፒተር፣ በምሥራቅ ጀርመን በሥራችን ላይ በተጣለው እገዳ ሥር ለበርካታ አሥርተ ዓመታት መኖር ምን ይመስል እንደነበር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በትንንሽ ቡድኖች ተከፋፍለን በግል ቤቶች ውስጥ የምንሰበሰብ ሲሆን በቦታው የምንደርሰውም ሆነ ከስብሰባ የምንወጣው በተለያየ ሰዓት ነበር። በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ስንገናኝ ለቀጣዩ ጊዜ ዝግጅት እናደርጋለን። ሽታዚዎች በተደጋጋሚ ጊዜ በስውር እያዳመጡ ስላስቸገሩን ይህን የምናደርገው በምልክትና ማስታወሻዎች ጽፈን በመለዋወጥ ነበር።”

ሃነሎሬም እንዲህ ብላለች:- “በካሴት የተቀዱ የትልልቅ ስብሰባ ፕሮግራሞችን አንዳንድ ጊዜ እናገኝ ነበር። ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ ደግሞ ሁልጊዜም አስደሳች ስብሰባ እንድናደርግ ምክንያት ይሆናል። ጥቂት አባላት ያሉት ቡድናችን በአንድ ላይ ተሰባስቦ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለበርካታ ሰዓታት ያዳምጣል። ተናጋሪዎቹን ባናያቸውም እንኳ ፕሮግራሙን በትኩረት የምንከታተል ከመሆኑም በላይ ማስታወሻም እንይዛለን።”

ፒተር እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በሌሎች አገራት የሚገኙ ወንድሞቻችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለእኛ ለማድረስ ይህ ነው የማይባል ጥረት አድርገዋል። የበርሊን ግንብ በ1989 ከመውደቁ በፊት በነበረው አሥር ዓመት ውስጥ በልዩ ሁኔታ የታተሙ ትንንሽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ያዘጋጁልን ነበር። አንዳንዶች መንፈሳዊ ምግቦችን ወደ ምሥራቅ ጀርመን ለማስገባት ሲሉ መኪናቸውንና ገንዘባቸውን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች የነበሩ ሲሆን ሌላው ቀርቶ ነፃነታቸውን እንኳ አደጋ ላይ ጥለው ነበር። አንድ ምሽት ላይ እንጠብቃቸው የነበሩ ባልና ሚስት ሳይመጡ ቀሩ። ፖሊሶች ጽሑፎቻቸውን የያዙባቸው ከመሆኑም ሌላ መኪናቸውንም ወረሱባቸው። ለአደጋ ተጋልጠን የነበርን ቢሆንም እንኳ ሥራችንን አቁመን የተረጋጋ ሕይወት ለመምራት ፈጽሞ አስበን አናውቅም።”

በ1950 ለሽታዚዎች አሳልፎ የሰጠን ታናሽ ወንድሜ ማንፍሬድ እምነቱን እንደገና እንዲያድስና ይበልጥ እንዲያሳድገው የረዳው ምን እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ለጥቂት ወራት ታስሬ ከቆየሁ በኋላ ወደ ምዕራብ ጀርመን ሄድኩ፤ ከእውነት ጎዳናም ወጣሁ። በ1954 ወደ ምሥራቅ ጀርመን ተመለስኩና በቀጣዩ ዓመት ትዳር መሠረትኩ። ብዙም ሳይቆይ ባለቤቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበለች ሲሆን በ1957 ተጠመቀች። እየዋለ ሲያድር ሕሊናዬ ይቆረቁኝ ጀመር፤ በኋላም በባለቤቴ እገዛ ወደ ጉባኤ ተመለስኩ።”

አክሎም እንዲህ ብሏል:- “እውነትን ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት የሚያውቁኝ ወንድሞች ምንም እንዳልተፈጠረ በፍቅር ተቀበሉኝ። ሞቅ ያለ ፈገግታ በማሳየት እቅፍ አድርገው ሰላም ሲሉኝ ተገረምኩ። ከይሖዋም ሆነ ከወንድሞቼ ጋር በመታረቄ በጣም ተደስቻለሁ።”

መንፈሳዊ ትግላችን ቀጥሏል

እያንዳንዱ የቤተሰባችን አባል ለእምነቱ ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ ነበረበት። ወንድሜ ፒተር እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ዛሬ፣ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሐሳብን በሚከፋፍሉ በርካታ ነገሮች እንዲሁም በቁሳዊ ማባበያዎች ተከበናል። በእገዳ ሥር እያለን ባለን ነገር እንረካ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ማንኛችንም ለግል ጉዳያችን ብቻ ብለን ከሌላ የጥናት ቡድን ጋር ለመካፈል አንፈልግም ነበር፤ እንዲሁም ማናችንም ብንሆን ስብሰባዎቹ የሚደረጉበት ቦታ በጣም ሩቅ እንደሆነ ወይም እንደሚመሽብን በመግለጽ አማርረን አናውቅም። ከስብሰባው ቦታ በየተራ ስንወጣ አንዳንዶቻችን እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት ድረስ መጠበቅ ቢኖርብን እንኳ ሁላችንም አንድ ላይ በመሰብሰባችን ደስተኞች ነበርን።”

በ1959 እናቴ የ16 ዓመት ልጅ የነበረችውን ሳቢኔን ይዛ ወደ ምዕራብ ጀርመን ለመሄድ ወሰነች። የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ማገልገል ስለፈለጉ ቅርንጫፍ ቢሮው ባደን-ወርጀምበርክ ውስጥ ወደምትገኘው ወደ ኤልቫንገን ከተማ ላካቸው። እናቴ የጤና እክል እያለባትም ያሳየችው ቅንዓት ሳቢኔ በ18 ዓመቷ አቅኚ እንድትሆን አነሳሳት። ሳቢኔ ትዳር ስትይዝ እናቴ በስብከቱ ሥራ ይበልጥ ለመሳተፍ በማሰብ በ58 ዓመቷ መኪና መንዳት ተማረች። እናቴ በ1974 በሞት እስካንቀላፋችበት ጊዜ ድረስ አገልግሎቷን ከፍ አድርጋ ትመለከተው ነበር።

ወደ እኔ ስንመጣ ደግሞ፣ ለሁለተኛ ጊዜ በእስር ቤት ለስድስት ዓመት ገደማ ከቆየሁ በኋላ ለቤተሰቦቼ ሳይነገራቸው በ1965 ወደ ምዕራብ ጀርመን ተወሰድኩ። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ባለቤቴ አኒ እንዲሁም ልጃችን ሩት እኔ ወዳለሁበት መጡ። ቅርንጫፍ ቢሮው አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ እንዲመድበን ስጠይቅ በኖርትሊንገን፣ ባቫሪያ እንድናገለግል ግብዣ ቀረበልን። ሩትና ታናሿ ዮሐንስ ያደጉት በዚያ ነው። በዚህ ጊዜ አኒ አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። አኒ ያሳየችው መልካም ምሳሌነት ሩትም ትምህርቷን እንደጨረሰች አቅኚነት እንድትጀምር አነሳሳት። የሁለቱም ልጆቻችን የትዳር ጓደኞች አቅኚዎች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ልጆቻችን ቤተሰብ ያፈሩ ከመሆኑም ሌላ የሚያማምሩ ስድስት የልጅ ልጆችን ለማየት በመብቃታችን ተባርከናል።

በ1987 ዕድሜዬ ሳይደርስ ጡረታ ለመውጣት የሚያስችለኝን አጋጣሚ ስላገኘሁ ከአኒ ጋር በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። ከሦስት ዓመት በኋላ ሴትለርስ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ በማስፋፋቱ ሥራ እንድካፈል ተጋበዝኩ። በኋላም በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ውስጥ በምትገኘው በግላሃው ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገነባው የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የግንባታ ሥራ ላይ ተካፈልን። በተጨማሪም ይህን አዳራሽ ለመንከባከብ በዚያ መኖር ጀመርን። አሁን በጤንነት እክል ምክንያት ከሴት ልጃችን ጋር ለመኖር የተመለስን ሲሆን በኖርትሊንገን ጉባኤ አቅኚ ሆነን በማገልገል ላይ እንገኛለን።

የሚያስደስተው ነገር ሁሉም ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲሁም አብዛኞቹ የቤተሰቦቻችን አባላት በጣም ልዩ የሆነውን አምላካችንን ይሖዋን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነን እስከቀጠልን ድረስ በመዝሙር 126:3 ላይ ያሉትን ቃላት እውነተኝነት መመልከታችን እንደማይቀር ካለፉት ዓመታት ተምረናል:- “እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አደረገልን፤ እኛም ደስ አለን።”

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1957 በሠርጋችን ዕለት

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1948 ከቤተሰቦቼ ጋር:- (ፊት ለፊት፣ ከግራ ወደ ቀኝ) ማንፍሬድ፣ ቤርታ፣ ሳቢኔ፣ ሃነሎሬ፣ ፒተር፤ (ከኋላ፣ ከግራ ወደ ቀኝ) እኔና ዮከን

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በእገዳው ሥር እያለን እንጠቀምበት የነበረ በትንሽ መጠን የተዘጋጀ መጽሐፍ፤ “ሽታዚዎች” በድብቅ ለማዳመጥ ይጠቀሙበት የነበረው መሣሪያ

[ምንጭ]

Forschungs- und Gedenkstätte NORMANNENSTRASSE

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከወንድሞቼና እህቶቼ ጋር:- (ፊት ለፊት፣ ከግራ ወደ ቀኝ) ሃነሎሬና ሳቢኔ፤ (ከኋላ፣ ከግራ ወደ ቀኝ) እኔ፣ ዮከን፣ ፒተርና ማንፍሬድ