በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሚወድህን አምላክ ውደደው

የሚወድህን አምላክ ውደደው

የሚወድህን አምላክ ውደደው

“ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ።”—ማቴዎስ 22:37

1, 2. ከሕግ ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ትእዛዝ ነው የሚለው ጥያቄ የተነሳው ለምን ሊሆን ይችላል?

 የሙሴ ሕግ ከያዛቸው ከ600 በላይ የሚሆኑ ትእዛዛት መካከል የሚበልጠው የትኛው ነው? ይህ ጥያቄ በኢየሱስ ዘመን ይኖሩ በነበሩት ፈሪሳውያን ዘንድ ትልቅ የመከራከሪያ ነጥብ ነበር። ከሕግ ሁሉ የሚበልጠው፣ መሥዋዕት ከማቅረብ ጋር የተያያዘው ሕግ ነው? እርግጥ ነው፣ መሥዋዕቶች የሚቀርቡት የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘትና አምላክን ለማመስገን ነበር። ታዲያ ከሁሉ የሚበልጠው ሕግ ግርዘትን አስመልክቶ የተሰጠው ትእዛዝ ይሆን? ግርዘት ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን ያመለክት ስለነበር ይህም ቢሆን በጣም ያስፈልጋል።—ዘፍጥረት 17:9-13

2 በሌላ በኩል ደግሞ ወግ አጥባቂ የሆኑ ፈሪሳውያን፣ አንዳንድ ትእዛዛት አነስተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መስለው ቢታዩም እንኳ አምላክ የሰጠው እያንዳንዱ ሕግ እጅግ ጠቃሚ ስለሆነ አንዱን ሕግ ከሌሎቹ አስበልጦ መመልከት ስህተት ነው ብለው ይከራከሩ ነበር። በመሆኑም ፈሪሳውያን ስለዚህ አከራካሪ ጉዳይ ኢየሱስን ሊጠይቁት ወሰኑ። ምናልባት እርሱም ተአማኒነቱን ሊያሳጣው የሚችል አንድ ነገር ይናገር ይሆናል። ስለሆነም አንድ ፈሪሳዊ ወደ ኢየሱስ በመቅረብ “ከሕግ ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ትእዛዝ ነው?” ሲል ጠየቀው።—ማቴዎስ 22:34-36

3. ኢየሱስ ከሕግ ሁሉ እንደሚበልጥ የገለጸው የትኛውን ትእዛዝ ነው?

3 ኢየሱስ የሰጠው መልስ በዛሬው ጊዜ ላለነው እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ኢየሱስ በመልሱ ላይ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ምንጊዜም የነበረውንና ወደፊትም የሚኖረውን ወሳኝ ጉዳይ ጠቅለል አድርጎ ጠቅሷል። ኢየሱስ ዘዳግም 6:5ን በመጥቀስ “‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው” አለ። ፈሪሳዊው የጠየቀው ስለ አንድ ሕግ ቢሆንም ኢየሱስ ከዘሌዋውያን 19:18 ላይ ጠቅሶ “ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው” በማለት ሌላ ትእዛዝ ነገረው። ቀጠል አድርጎም ኢየሱስ እውነተኛው አምልኮ በእነዚህ ሁለት ሕግጋት ሊጠቃለል እንደሚችል አመልክቷል። ኢየሱስ ሌሎች ሕግጋትንም ካላቸው ጠቀሜታ አንጻር በቅደም ተከተል እንዲዘረዝርላቸው እንዳይጠይቁት “ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው” በማለት ደምድሟል። (ማቴዎስ 22:37-40) በዚህ ርዕስ ላይ ከእነዚህ ሁለት ትእዛዛት መካከል ላቅ ያለውን እንመረምራለን። አምላክን መውደድ ያለብን ለምንድ ነው? ይህንንስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ይህን የመሰለውን ፍቅር እንዴት ማሳደግ እንችላለን? ይሖዋን ለማስደሰት ከፈለግን እርሱን በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችንና ሐሳባችን መውደድ ስለሚገባን የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን እጅግ አስፈላጊ ነው።

የፍቅር አስፈላጊነት

4, 5. (ሀ) ፈሪሳዊው ኢየሱስ በተናገረው ነገር ያን ያህል ያልተደነቀው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ ከመሥዋዕትና ከቁርባን ይበልጥ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ምንን ነው?

4 ኢየሱስን የጠየቀው ፈሪሳዊ በተሰጠው ምላሽ የተከፋም ይሁን የተደነቀ አይመስልም። ብዙዎች ባያደርጉትም እንኳ አምላክን መውደድ የእውነተኛው አምልኮ ወሳኝ ክፍል መሆኑን ያውቃል። አይሁዳውያን በምኩራብ ውስጥ ሼማ በመባል የሚታወቀውን ጸሎት ድምፅ አውጥተው የመድገም ልማድ ነበራቸው፤ በዚህ ጸሎት ውስጥ ኢየሱስ የጠቀሰው የዘዳግም 6:4-9 ሐሳብ ይገኛል። በማርቆስ ወንጌል ላይ የሰፈረው ተመሳሳይ ዘገባ ፈሪሳዊው ኢየሱስን እንደሚከተለው እንዳለው ይገልጻል:- “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፣ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።”—ማርቆስ 12:32, 33

5 ሕጉ የሚቃጠል መሥዋዕትም ሆነ ሌሎች መሥዋዕቶች እንዲቀርቡ የሚያዝዝ ቢሆንም አምላክ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው አገልጋዮቹ ለሚያሳዩት ከልብ የመነጨ ፍቅር ነው። አምላክ ትክክለኛ ባልሆነ የልብ ዝንባሌ ከሚቀርቡለት ሺህ በጎች ይልቅ በፍቅርና በአክብሮት የምትቀርብለትን አንዲት ድንቢጥ ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (ሚክያስ 6:6-8) ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ ስላያት አንዲት ችግረኛ መበለት የሚናገረውን ዘገባ አስታውስ። ይህች መበለት በገንዘብ ማስቀመጫ ሣጥን ውስጥ የከተተቻቸው ሁለት ትንንሽ ሳንቲሞች አንዲት ድንቢጥ እንኳ መግዛት አይችሉም። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ይህቺ ሴት ለእርሱ ባላት ከልብ የመነጨ ፍቅር ተገፋፍታ ያደረገችውን መዋጮ ከትርፋቸው ብዙ ገንዘብ ይጥሉ ከነበሩት ባለጠጎች ይልቅ እጅግ ከፍ አድርጎ ተመልክቶታል። (ማርቆስ 12:41-44) ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ለእርሱ የምናሳየውን ፍቅር መሆኑን ማወቃችን ምንኛ ያጽናናል!

6. ጳውሎስ የፍቅርን አስፈላጊነት አስመልክቶ ምን በማለት ጽፏል?

6 ሐዋርያው ጳውሎስ ፍቅር በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ያለውን አስፈላጊነት እንደሚከተለው ሲል በአጽንኦት ገልጿል:- “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ነኝ። የትንቢት ስጦታ ቢኖረኝ፣ ምስጢርን ሁሉና ዕውቀትን ሁሉ ባውቅ፣ ተራራንም ከቦታው የሚነቅል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ያለኝን ሁሉ ለድኾች ብሰጥ፣ ሰውነቴንም እንዲቃጠል ለእሳት ብዳርግ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።” (1 ቆሮንቶስ 13:1-3) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምልኮታችን ይሖዋን የሚያስደስት እንዲሆን ከተፈለገ ፍቅር ማሳየታችን እጅግ አስፈላጊ ነው። ይሁንና ይሖዋን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የምናሳይበት መንገድ

7, 8. ለይሖዋ ያለንን ፍቅር እንዴት ማሳየት እንችላለን?

7 ብዙ ሰዎች ፍቅር ልንቆጣጠረው የማንችለው ስሜት እንደሆነ ይገልጻሉ፤ እንዲያውም በፍቅር ስለመውደቅ ሲናገሩ ይሰማል። ይሁንና እውነተኛ ፍቅር የስሜት ጉዳይ ብቻ አይደለም። ይህ ፍቅር በተግባር የሚገለጽ እንጂ እንዲያው ስሜት ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅርን ‘ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ’ እንዲሁም ‘ልንከታተለው’ የሚገባን ነገር እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። (1 ቆሮንቶስ 12:31፤ 14:1) ክርስቲያኖች “በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ” እንዳይዋደዱ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።—1 ዮሐንስ 3:18

8 ለአምላክ ያለን ፍቅር እርሱን የሚያስደስተውን ነገር እንድናደርግና በቃልም ሆነ በድርጊት ለሉዓላዊነቱ ጥብቅና እንድንቆም ያነሳሳናል። ዓለምን ከመውደድም ይሁን ከአምላክ የራቀውን አካሄዱን ከመከተል እንድንርቅ ይገፋፋናል። (1 ዮሐንስ 2:15, 16) አምላክን የሚወድዱ ሰዎች ክፋትን ይጠላሉ። (መዝሙር 97:10) በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው አምላክን መውደድ ጎረቤቶቻችንን መውደድንም ያካትታል። ከዚህም ባሻገር አምላክን መውደድ እርሱን መታዘዝን ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነው” በማለት ይናገራል።—1 ዮሐንስ 5:3

9. ኢየሱስ ለአምላክ ያለውን ፍቅር በተግባር ያሳየው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ አምላክን መውደድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በተግባር አሳይቷል። ለአምላክ ያለው ፍቅር በሰማይ ያለውን መኖሪያውን ትቶ ሰው ሆኖ ለመኖር ወደ ምድር እንዲመጣ ገፋፍቶታል። ይህ ፍቅር በአድራጎቱም ይሁን በትምህርቱ አባቱን እንዲያወድስ አነሳስቶታል። ሌላው ቀርቶ “እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ” እንዲሆን አድርጎታል። (ፊልጵስዩስ 2:8) የፍቅሩ መገለጫ የሆነው ይህ መሰሉ ታዛዥነት ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ለማግኘት የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በአንዱ ሰው [በአዳም] አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደ ሆኑ፣ በአንዱ ሰው [በኢየሱስ ክርስቶስ] መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።”—ሮሜ 5:19

10. አምላክን መውደድ ታዛዥ መሆንን ይጨምራል የምንለው ለምንድን ነው?

10 እኛም እንደ ኢየሱስ ለአምላክ ያለንን ፍቅር እርሱን በመታዘዝ እናሳያለን። ኢየሱስ ይወድደው የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ “ይህም ፍቅር፤ በትእዛዛቱ መሠረት እንመላለስ ዘንድ ነው” ሲል ጽፏል። (2 ዮሐንስ 6) ይሖዋን ከልባቸው የሚወድዱ ሰዎች አመራሩን ለማግኘት አጥብቀው ይሻሉ። አካሄዳቸውን በራሳቸው ማቅናት እንደማይችሉ ስለሚገነዘቡ በአምላክ ጥበብ ይታመናሉ እንዲሁም ለፍቅራዊ አመራሩ ይገዛሉ። (ኤርምያስ 10:23) እነዚህ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ መልእክቱን “በታላቅ ጒጒት” ከተቀበሉትና በጥንት ቤርያ ይኖሩ ከነበሩት አስተዋይ ሰዎች ጋር ይመሳሰላሉ። (የሐዋርያት ሥራ 17:11) የአምላክን ፈቃድ በተሟላ ሁኔታ ለመረዳት ሲሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥንቃቄ ይመረምራሉ፤ ይህ ደግሞ ይበልጥ ታዛዥ በመሆን ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳዩ ይረዳቸዋል።

11. አምላክን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ሐሳብ፣ በፍጹም ነፍስና በፍጹም ኃይል መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው?

11 ኢየሱስ እንዳለው አምላክን መውደድ ያለብን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ሐሳባችን፣ በፍጹም ነፍሳችንና በፍጹም ኃይላችን ነው። (ማርቆስ 12:30) ይህ ዓይነቱ ፍቅር ከልባችን የሚመነጭ ሲሆን ከስሜታችን፣ ከፍላጎታችንና ከውስጣዊ ሐሳባችን ጋር የተያያዘ ነው፤ እንዲሁም ይሖዋን የማስደሰት ከፍተኛ ፍላጎት እንዲያድርብን ያደርጋል። ይሖዋን በሐሳባችን ጭምር እንወደዋለን። ለይሖዋ ያለን ጥልቅ ፍቅር ጭፍን ሳይሆን እርሱን ማለትም ባሕርያቱን፣ የአቋም ደረጃዎቹን እንዲሁም ዓላማውን በማወቅ ላይ የተመሠረተ ነው። ነፍሳችንን ማለትም ሁለንተናችንንና ሕይወታችንን እርሱን ለማገልገልና ለማወደስ እንጠቀምበታለን። ኃይላችንንም ቢሆን ለተመሳሳይ ዓላማ እናውለዋለን።

ይሖዋን መውደድ ያለብን ለምንድን ነው?

12. አምላክ እንድንወደው የሚጠብቅብን ለምንድን ነው?

12 ይሖዋን የምንወድበት አንዱ ምክንያት እርሱ ራሱ ይህን ባሕርይ እንድናንጸባርቅ ስለሚጠብቅብን ነው። አምላክ የፍቅር ምንጭና ተምሳሌት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ አነሳሽነት “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:8) ሰዎች የተፈጠሩት በአምላክ አምሳል ነው፤ በመሆኑም ፍቅርን እንድናንጸባርቅ ተደርገን ተሠርተናል። እንዲያውም የይሖዋ ልዕልና የተመሠረተው በፍቅር ላይ ነው። ይሖዋ ተገዥዎቹ እንዲሆኑ የሚፈልገው የጽድቅ አገዛዙን የሚወዱትንና ለዚህ አገዛዝ ለመታዘዝ ፈቃደኛ የሆኑትን ብቻ ነው። በእርግጥም ፍቅር በሁሉም ፍጥረታት መካከል ለሚኖረው ሰላምና ስምምነት ቁልፍ ነገር ነው።

13. (ሀ) እስራኤላውያን ‘ይሖዋ አምላካችሁን ውደዱ’ የተባሉት ለምን ነበር? (ለ) ይሖዋ እርሱን እንድንወደው መጠበቁ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋን እንድንወደው የሚያነሳሳን ሌላው ምክንያት ደግሞ ላደረገልን ነገር ያለን አድናቆት ነው። ኢየሱስ ለአይሁዳውያን ‘ይሖዋን አምላካችሁን ውደዱ’ ብሏቸው እንደነበር አስታውስ። እነዚህ ሰዎች እንዲወዱት የተነገራቸው ከእነርሱ ርቆ ያለንና የማያውቁትን መለኮታዊ አካል ሳይሆን ፍቅሩን የገለጠላቸውን አምላክ ነው። ይሖዋ አምላካቸው ነበር። ከግብጽ ነጻ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ያስገባቸው እርሱ ነው። ሲጠብቃቸው፣ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እየሰጠ ሲንከባከባቸው እንዲሁም በፍቅር ሲገሥጻቸው የነበረውም እርሱ ራሱ ነው። በዛሬው ጊዜም ቢሆን፣ ይሖዋ አምላካችን ሲሆን የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል። ይሖዋ እርሱን እንድንወደው መጠበቁ በእርግጥም ምክንያታዊ ነው! እኛም በምላሹ የወደደንን አምላክ እንድንወደው ተጠይቀናል። ፍቅራችንን የምናሳየው ‘አስቀድሞ ለወደደን’ አምላክ ነው።—1 ዮሐንስ 4:19

14. የይሖዋ ፍቅር አንድ አፍቃሪ ወላጅ ከሚያሳየው ፍቅር ጋር የሚመሳሰለው በምን መንገድ ነው?

14 ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር አንድ አፍቃሪ ወላጅ ለልጆቹ ካለው ፍቅር ጋር ይመሳሰላል። አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ምንም እንኳ ፍጽምና ቢጎድላቸውም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለብዙ ዓመታት ልጆቻቸውን ይንከባከባሉ፤ ይህን ማድረግ ደግሞ በቁሳዊ ነገሮች ረገድም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ከፍተኛ መሥዋዕትነት መክፈል ይጠይቅባቸዋል። ወላጆች፣ ልጆቻቸው ደስተኞችና የተሳካላቸው እንዲሆኑ ስለሚፈልጉ መመሪያ፣ ማበረታቻ፣ ድጋፍና ሥልጠና ይሰጧቸዋል። ወላጆች ላደረጉት ነገር በምላሹ ምን ይጠብቃሉ? ልጆቻቸው እንዲወዷቸውና ለጥቅማቸው ሲሉ የሰጧቸውን መመሪያዎች በቁም ነገር እንዲመለከቱት ይፈልጋሉ። ፍጹም የሆነው የሰማዩ አባታችን ላደረገልን ነገሮች በፍቅር ተነሳስተን እንድናመሰግነው መፈለጉ ምክንያታዊ አይሆንም?

ለአምላክ ያለንን ፍቅር ማሳደግ

15. ለአምላክ ያለንን ፍቅር ለማሳደግ ልንወስደው የሚገባን የመጀመሪያ እርምጃ ምንድን ነው?

15 አምላክን አይተነውም ሆነ ድምፁን ሰምተን አናውቅም። (ዮሐንስ 1:18) ይሁንና ከእርሱ ጋር ወዳጃዊ ቅርርብ እንድንመሠርት ግብዣ አቅርቦልናል። (ያዕቆብ 4:8) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንድን ሰው ለመውደድ የምንወስደው የመጀመሪያ እርምጃ ስለ እርሱ ማወቅ ነው፤ ምክንያቱም የማናውቀውን ሰው ከልብ መውደድ አስቸጋሪ ነው። ይሖዋ ስለ እርሱ እንድናውቅ ሲል ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። ይሖዋ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር እንድናነብ በድርጅቱ አማካኝነት የሚያበረታታንም ለዚሁ ነው። ስለ አምላክ፣ ስለ ባሕርያቱ፣ ስለማንነቱና በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ከሰዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት መማር የምንችለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰፈሩት ዘገባዎች ላይ ስናሰላስል ለአምላክ ያለን አድናቆትና ፍቅር እያደገ ይሄዳል።—ሮሜ 15:4

16. በኢየሱስ አገልግሎት ላይ ማሰላሰላችን ለአምላክ ያለንን ፍቅር የሚያሳድግልን እንዴት ነው?

16 ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳደግ ከምንችልባቸው ወሳኝ መንገዶች አንዱ በኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ላይ ማሰላሰል ነው። እንዲያውም ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ በሚገባ ከማንጸባረቁ የተነሳ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” ለማለት ችሏል። (ዮሐንስ 14:9) ኢየሱስ የመበለቲቱን አንድያ ልጅ ከሞት ባስነሳበት ወቅት ባሳየው የርኅራኄ ስሜት ልብህ አልተነካም? (ሉቃስ 7:11-15) የአምላክ ልጅና በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ እጅግ ታላቅ ሰው የሆነው ኢየሱስ፣ የደቀ መዛሙርቱን እግር በትሕትና ማጠቡን ማወቅ ትኩረት የሚስብ አይደለም? (ዮሐንስ 13:3-5) ኢየሱስ ከማንም በላይ ታላቅና ጥበበኛ ቢሆንም ልጆችን ጨምሮ በሁሉም ሰው ዘንድ የሚቀረብ መሆኑ አንተም እንዲህ እንድታደርግ አያነሳሳህም? (ማርቆስ 10:13, 14) እንዲህ በመሰሉ ዘገባዎች ላይ በአድናቆት ማሰላሰላችን ጴጥሮስ “እርሱንም [ኢየሱስን] ሳታዩት ትወዱታላችሁ” ሲል እንደጻፈላቸው ዓይነት ክርስቲያኖች እንድንሆን ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 1:8) ለኢየሱስ ያለን ፍቅር በጨመረ መጠን ለይሖዋ ያለን ፍቅርም የዚያኑ ያህል ያድጋል።

17, 18. ይሖዋ ባደረገልን በየትኞቹ ፍቅራዊ ዝግጅቶች ላይ ማሰላሰላችን ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለማሳደግ ይረዳናል?

17 ለአምላክ ያለንን ፍቅር የምናሳድግበት ሌላው መንገድ ደግሞ ደስተኛ ሕይወት እንዲኖረን ሲል ባደረገልን በርካታ ፍቅራዊ ዝግጅቶች ላይ በማሰላሰል ነው። ከእነዚህ መካከል ማራኪ የሆኑ ፍጥረታት፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጣፋጭ ምግቦች፣ ከጥሩ ጓደኞቻችን ጋር ያለን ወዳጅነት እንዲሁም ደስታና እርካታ የሚያስገኙልን ሌሎች እጅግ በርካታ ነገሮች ይገኙበታል። (የሐዋርያት ሥራ 14:17) ስለ አምላካችን ይበልጥ ባወቅን መጠን ወደር የለሽ ጥሩነቱንና ቸርነቱን እንድናደንቅ የሚገፋፉን ተጨማሪ ምክንያቶች እናገኛለን። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ስላደረገልህ ነገሮች አስብ። በእርግጥም ይሖዋ ሊወደድ ይገባዋል ቢባል አትስማማም?

18 አምላክ ከሰጠን በርካታ ስጦታዎች መካከል፣ ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው አምላክ እንደሚያዳምጠን በመተማመን በማንኛውም ጊዜ ወደ እርሱ በጸሎት እንድንቀርብ የተከፈተልን አጋጣሚ ይገኝበታል። (መዝሙር 65:2) ይሖዋ ለውድ ልጁ የመግዛትና የመፍረድ ስልጣን ሰጥቶታል። ይሁን እንጂ ልጁንም ሆነ ሌሎችን የምናቀርበውን ጸሎት እንዲያዳምጡ አልወከላቸውም። የእያንዳንዳችንን ጸሎት የሚሰማው እርሱ ራሱ ነው። በመሆኑም ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚያሳየን ፍቅራዊ አሳቢነት ይበልጥ ወደ እርሱ እንድንቀርብ እንደሚፈልግ ያሳያል።

19. ይሖዋ የሰጠን የትኞቹ ተስፋዎች ይበልጥ ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይገፋፉናል?

19 ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ለሰው ልጆች ወደፊት ሊሰጣቸው ያዘጋጀላቸውን ነገሮች ማወቃችን ወደ እርሱ ይበልጥ እንድንቀርብ ይገፋፋናል። ይሖዋ በሽታን፣ ሐዘንንና ሞትን እንደሚያስቀር ቃል ገብቷል። (ራእይ 21:3, 4) የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና ደረጃ ከደረሱ በኋላ በመንፈስ ጭንቀት፣ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ወይም በአሳዛኝ ክስተት ሳቢያ የሚሠቃይ ሰው አይኖርም። ረሃብ፣ ድህነትና ጦርነት ጊዜ ያለፈባቸው ነገሮች ይሆናሉ። (መዝሙር 46:9፤ 72:16) ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች። (ሉቃስ 23:43) ይሖዋ እነዚህን በረከቶች አትረፍርፎ የሚሰጠን ተገድዶ ሳይሆን ስለሚወደን ነው።

20. ይሖዋን መውደድ የሚያስገኘውን ጥቅም አስመልክቶ ሙሴ ምን ብሏል?

20 በመሆኑም አምላክን እንድንወደውና ለእርሱ ያለንን ፍቅር እንድናሳድግ የሚገፋፉን አጥጋቢ ምክንያቶች አሉን። አምላክ በመንገድህ ሁሉ እንዲመራህ በመፍቀድ ለእርሱ ያለህ ፍቅር ይበልጥ እንዲጨመር ማድረግህን ትቀጥላለህ? ምርጫው የራስህ ነው። ሙሴ፣ ለይሖዋ ያለውን ፍቅር የማሳደጉንና ጠብቆ የመኖሩን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ስለነበር በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩትን እስራኤላውያን እንደሚከተለው ብሏቸዋል:- “አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤ ይኸውም አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድ፣ ቃሉን እንድታደምጥና ከእርሱ ጋር እንድትጣበቅ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወትህ ነው . . . ረጅም ዕድሜ ይሰጥሃል።”—ዘዳግም 30:19, 20

ታስታውሳለህ?

• ይሖዋን መውደዳችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• አምላክን እንደምንወደው እንዴት ማሳየት እንችላለን?

• ይሖዋን ለመውደድ የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉ?

• ለአምላክ ያለንን ፍቅር እንዴት ማሳደግ እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ሁላችንም ልናሳየው የምንችለውን ነገር ይኸውም ለእርሱ ያለንን ፍቅር ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“እኔን ያየ አብን አይቶአል።”—ዮሐንስ 14:9