በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኢሳይያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1

የኢሳይያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የኢሳይያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1

ይሖዋ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” በማለት ላቀረበው ግብዣ የአሞጽ ልጅ የሆነው ኢሳይያስ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” በማለት ምላሽ ሰጥቷል። (ኢሳይያስ 1:1፤ 6:8) በዚህ ጊዜ ኢሳይያስ ነቢይ ሆኖ እንዲያገለግል ተልእኮ ተሰጠው። በነቢይነቱ ወቅት ያከናወነው ሥራ በስሙ በሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።

የኢሳይያስን መጽሐፍ የጻፈው ራሱ ነቢዩ ሲሆን ዘገባው ከ778 እስከ 732 ከክርስቶስ ልደት በፊት ያሉትን 46 ዓመታት ይሸፍናል። ምንም እንኳ መጽሐፉ ይሖዋ፣ በይሁዳና በእስራኤል እንዲሁም በዙሪያዋ ባሉ መንግሥታት ላይ ያስተላለፈውን የፍርድ መልእክት የያዘ ቢሆንም ዋነኛ ጭብጡ ግን የፍርድ መልእክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ስለ ‘አምላካችን ማዳን’ የሚናገር መጽሐፍ ነው። (ኢሳይያስ 25:9) ኢሳይያስ የሚለው ስምም ቢሆን “የይሖዋ ማዳን” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ርዕሰ ትምህርት ከኢሳይያስ ምዕራፍ 1:1 እስከ 35:10 ድረስ ያሉትን የመጽሐፉን ጎላ ጎላ ያሉ ነጥቦች ይከልሳል።

“የተረፉት ይመለሳሉ”

(ኢሳይያስ 1:1 እስከ 12:6)

በኢሳይያስ መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ አምስት ምዕራፎች ውስጥ የሚገኘው ትንቢታዊ መልእክት የተነገረው ኢሳይያስ ነቢይ ሆኖ ከመሾሙ በፊት ይሁን ወይም ከዚያ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የሚለው ነገር የለም። (ኢሳይያስ 6:6-9) የሆነ ሆኖ፣ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ‘ከእግር ጥፍራቸው እስከ ራስ ጠጕራቸው’ ድረስ በመንፈሳዊ ሁኔታ ታመው እንደነበር ግልጽ ነው። (ኢሳይያስ 1:6) የጣዖት አምልኮ ተስፋፍቷል፣ መሪዎቻቸው በሙስና የተዘፈቁ ሲሆኑ ሴቶቻቸው ደግሞ ትዕቢተኞች ሆነዋል። ሕዝቡ እውነተኛውን አምላክ እርሱ በሚፈልገው መንገድ ማምለካቸውን ትተዋል። ኢሳይያስም ለማያስተውሉት እንዲሁም ልብ ለማይሉት ለእነዚህ ሰዎች በተደጋጋሚ እንዲናገር ተልእኮ ተሰጠው።

ይሁዳ፣ የእስራኤልና የሶርያ ጥምር ጦር ወረራ አስፈርቷታል። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ኢሳይያስንና ልጆቹን እንደ “ምልክትና ድንቅ” አድርጎ በመጠቀም የሕብረ ብሔሩ ጦር እንደማይሳካለት ለይሁዳ አረጋገጠላት። (ኢሳይያስ 8:18) ይሁንና ዘላቂ ሰላም የሚመጣው “የሰላም ልዑል” በሆነው ገዥ አማካኝነት ብቻ ነው። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ይሖዋ፣ አሕዛብን ለመቅጣት በተጠቀመበት ‘የቍጣው በትር’ በሆነው በአሦር ላይም ይፈርዳል። ውሎ አድሮ ይሁዳ በምርኮ የምትወሰድ ብትሆንም “የተረፉት ይመለሳሉ።” (ኢሳይያስ 10:5, 21, 22) “ከእሴይ ግንድ” በሚወጣው ምሳሌያዊው “ቍጥቋጥ” አገዛዝ ሥር እውተኛ ፍትሕ ይሰፍናል።—ኢሳይያስ 11:1

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

1:8, 9—የጽዮን ሴት ልጅ “በወይን አትክልት ውስጥ እንዳለ ዳስ፣ በዱባ ተክል ውስጥ እንደሚገኝ ጐጆ” የተተወች የሆነችው እንዴት ነው? በአሦራውያን ወረራ ወቅት ኢየሩሳሌም ልክ በወይን አትክልት ውስጥ እንዳለ ዳስ ወይም በዱባ ተክል ውስጥ እንዳለ በቀላሉ የሚፈርስ ጎጆ አቅመ ቢስ መስላ ትታያለች። ነገር ግን ይሖዋ ስለሚረዳት እንደ ሰዶምና ገሞራ አትሆንም።

1:18—“ኑና እንዋቀስ” የሚሉት ቃላት ምን ትርጉም አላቸው? ይህ አባባል ሁለቱም ወገኖች በጉዳዩ ላይ ተወያይተው አንዳንድ ነገሮችን በመተው ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የቀረበ ግብዣ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጥቅሱ፣ ፍትሕን ለማስጠበቅ ሲባል ችሎት እንደተሰየመና ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ይሖዋ፣ እስራኤላውያን አካሄዳቸውን ለውጠው ራሳቸውን እንዲያነጹ አጋጣሚ እንደሰጣቸው የሚጠቁም ነው።

6:8ሀ—“ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” በሚሉት አገላለጾች ውስጥ የሚገኙት ‘እኔ’ እንዲሁም ‘እኛ’ የሚሉ ተውላጠ ስሞች ማንን የሚያመለክቱ ናቸው? ‘እኔ’ የሚለው ተውላጠ ስም ይሖዋን የሚያመለክት ሲሆን በብዙ ቁጥር የተቀመጠው ‘እኛ’ የሚለው አገላለጽ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለን ሌላ አካል ያመለክታል። ይህም ከይሖዋ ‘አንድያ ልጅ’ በቀር ማንም ሊሆን አይችልም።—ዮሐንስ 1:14፤ 3:16

6:11—ኢሳይያስ “ጌታ ሆይ፤ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ምን ማለቱ ነበር? ኢሳይያስ ልበ ደንዳና ለሆኑ ሰዎች መስበኩን የሚቀጥለው እስከ መቼ እንደሆነ መጠየቁ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በመንፈሳዊ የታመመው ሕዝብ የአምላክን ስም እያረከሰ የሚኖረው እስከ መቼ እንደሆነ ለማወቅ ፈልጎ ነው።

7:3, 4—ይሖዋ ክፉ የሆነውን ንጉሥ አካዝን ከወራሪዎቹ ያዳነው ለምንድን ነው? የሶርያና የእስራኤል ነገሥታት ግንባር ፈጥረው ንጉሥ አካዝን ከሥልጣን ካስወገዱ በኋላ በምትኩ፣ የዳዊት ዘር ያልሆነውን የጣብኤልን ልጅ በዙፋን ላይ በማስቀመጥ የአሻንጉሊት መንግሥት ለመመሥረት አስበው ነበር። ይህ ሰይጣናዊ የሆነ እቅድ፣ ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባው የመንግሥት ቃል ኪዳን እንዳይፈጸም እንቅፋት የሚፈጥር ነው። ይሖዋ ለአካዝ ምሕረት ያሳየው፣ ተስፋ የተሰጠበት “የሰላም ልዑል” የሚመጣበትን የዘር ሐረግ ጠብቆ ለማቆየት ነው።—ኢሳይያስ 9:6

7:8—የኤፍሬም ሕዝብ በ65 ዓመት ውስጥ ‘የተበታተነው’ እንዴት ነው? አሥሩን ብሔር ባቀፈው መንግሥት ሥር የነበረው ሕዝብ በግዞት እየተወሰደ በምትኩ ሌሎች ባዕድ ሕዝቦች በእስራኤል ምድር መስፈር የጀመሩት ኢሳይያስ ይህን ትንቢት ከተናገረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ማለትም “በእስራኤል ንጉሥ በፋቁሔ ዘመን” ነበር። (2 ነገሥት 15:29) የሰናክሬም ልጅና ተተኪ የአሦር ንጉሥ በሆነው በአስራዶን ዘመነ መንግሥትም ይህ ሁኔታ ቀጥሎ ነበር። (2 ነገሥት 17:6፤ ዕዝራ 4:1, 2፤ ኢሳይያስ 37:37, 38) በኢሳይያስ 7:8 ላይ ኤፍሬም በ65 ዓመታት እንደሚበተን የተነገረው ትንቢት፣ አሦራውያን ሕዝቡን ከሰማርያ በግዞት ወስደው ሌሎች ሕዝቦችን በሥፍራው ሲያሰፍሩ በነበሩባቸው ዓመታት ፍጻሜውን አግኝቷል።

11:1, 10—ኢየሱስ ‘ከእሴይ ግንድ የወጣ ቍጥቋጥ’ እንዲሁም “የእሴይ ሥር” የሚሆነው እንዴት ነው? (ሮሜ 15:12) የዘር ሐረጉን ስንመለከት ኢየሱስ ‘ከእሴይ ግንድ የወጣ ቍጥቋጥ’ ሊባል ይችላል። በእሴይ ልጅ በዳዊት በኩል የእሴይ ዘር ነው። (ማቴዎስ 1:1-6፤ ሉቃስ 3:23-32) ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተቀበለው ንጉሣዊ ሥልጣን ከቅድመ አያቶቹ ጋር በሚኖረው ዝምድና ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ኢየሱስ ታዛዥ የሆኑ ሰዎች በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ለማድረግ ኃይልና ሥልጣን ስለተሰጠው ለእነዚህ ሰዎች “የዘላለም አባት” ይሆንላቸዋል። (ኢሳይያስ 9:6) በዚህም ምክንያት እሴይን ጨምሮ ለቅድመ አያቶቹ በሙሉ “ሥር” ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን

1:3:- ፈጣሪያችን በሚፈልግብን መንገድ ለመኖር ፈቃደኛ አለመሆን የበሬ ወይም የአህያ ያህል እንኳ እውቀት እንደሌለን ያሳያል። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ላደረገልን ነገሮች አድናቆት ማዳበራችን ማስተዋል በጎደለው መንገድ ከመመላለስና እርሱን ከመተው እንድንጠበቅ ያደርገናል።

1:11-13:- ለይስሙላ የሚደረጉ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችና ለደንቡ ተብለው የሚቀርቡ ጸሎቶች ይሖዋን አያስደስቱትም። ድርጊታችንም ሆነ ጸሎታችን ከትክክለኛ የልብ ዝንባሌ የመነጨ መሆን ይኖርበታል።

1:25-27፤ 2:2፤ 4:2, 3:- ንስሐ የገቡ ቀሪዎች ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው እውነተኛውን አምልኮ መልሰው ሲያቋቁሙ፣ ሕዝቡ በባርነት የሚኖርበትና ይሁዳ ባድማ ሆና የምትቆይበት ጊዜ ያበቃል። ይሖዋ ንስሐ ለሚገቡት ክፉ አድራጊዎች ምሕረት ያሳያል።

2:2-4:- የመንግሥቱን ወንጌል በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት መካፈላችን ከብዙ ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች የሰላምን መንገድ እንዲማሩ ብሎም እርስ በርሳቸው ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።

4:4:- ይሖዋ የሥነ ምግባር ርኩሰትን እና የደም ዕዳን ያስወግዳል ወይም አጥቦ ያነጻል።

5:11-13:- በመዝናኛ ምርጫ ረገድ ገደብ የለሽ መሆንና ልክን አለማወቅ በእውቀት አለመኖር ነው።—ሮሜ 13:13

5:21-23:- ክርስቲያን ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች “በራሳቸውም አመለካከት ጥበበኛ” ከመሆን ሊቆጠቡ ይገባል። በተጨማሪም ‘የወይን ጠጅ በመጠጣት’ ረገድ ልከኛ መሆን የሚጠበቅባቸው ሲሆን አድልዎ ከማሳየትም መራቅ አለባቸው።

11:3ሀ:- የኢየሱስ ምሳሌ እንዲሁም ትምህርቶች እንደሚያሳዩት ይሖዋን በመፍራት ደስታ ይገኛል።

‘አምላክ ለያዕቆብ ይራራለታል’

(ኢሳይያስ 13:1 እስከ 35:10)

ኢሳይያስ ምዕራፍ 13 እስከ 23 ይሖዋ በብሔሩ ላይ ስላስተላለፈው የፍርድ መልእክት ይናገራል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሁሉም የእስራኤል ነገዶች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ በማድረግ “ለያዕቆብ ይራራለታል።” (ኢሳይያስ 14:1) ከምዕራፍ 24 እስከ 27 ላይ ሰፍሮ የሚገኘውና ስለ ይሁዳ ባድማነት የሚናገረው መልእክት ከግዞት የመመለስ ተስፋም በውስጡ ይዟል። ይሖዋ ‘የኤፍሬም [የእስራኤል] ሰካራሞች’ ከሶርያ ጋር ስምምነት በማድረጋቸው እንዲሁም የይሁዳ ‘ካህናትና ነቢያት’ ከአሦር ጋር ኅብረት ለመመሥረት በመፈለጋቸው ቁጣውን ገልጿል። (ኢሳይያስ 28:1, 7) “አርኤል [ኢየሩሳሌም]” እርዳታ ለማግኘት ‘ወደ ግብፅ በመውረዷ’ ወዮታ ይጠብቃታል። (ኢሳይያስ 29:1 የአዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ፤ 30:1, 2) የሆነ ሆኖ በይሖዋ ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ግለሰቦች መዳን እንደሚያገኙ አስቀድሞ ተተንብዮ ነበር።

ልክ ‘የሰበረውን ይዞ እንደሚያገሣ አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል’ ይሖዋ ‘የጽዮን ተራራን’ ይጠብቃል። (ኢሳይያስ 31:4) “እነሆ፤ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል” የሚል ተስፋም ተሰጥቷል። (ኢሳይያስ 32:1) አሦር በይሁዳ ላይ ስጋት መፍጠሯ “የሰላም መልእክተኞችም አምርረው” እንዲያለቅሱ ቢያደርግም ይሖዋ፣ ለሕዝቡ እንደሚፈወሱና ‘ኀጢአታቸው ይቅር እንደሚባል’ ቃል ገብቶላቸዋል። (ኢሳይያስ 33:7, 22-24) “እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ ተቈጥቶአል፤ ቍጣውም በሰራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው።” (ኢሳይያስ 34:2) ይሁዳ ባድማ ሆና አትቀርም። ከዚህ ይልቅ “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፤ በረሓው ሐሤት ያደርጋል፤ ይፈካል፤ እንደ አደይም ያብባል።”—ኢሳይያስ 35:1

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

13:17—ሜዶናውያን ለብር ደንታ እንደማይኖራቸው በወርቅም ደስ እንደማይሰኙ የተነገረው ለምንድን ነው? ሜዶናውያንና ፋርሳውያን በምርኮ ከሚያገኙት ንብረት ይልቅ ከፍ አድርገው የሚመለከቱት በጦርነት የሚያገኙትን ድል ነበር። ናቡከደነፆር ከይሖዋ ቤተ መቅደስ የዘረፋቸውን የወርቅና የብር ዕቃዎች ቂሮስ ከምርኮ ለተመለሱት እስራኤላውያን መመለሱ የዚህን አባባል እውነተኝነት ያረጋግጣል።

14:1, 2—የይሖዋ ሕዝቦች ‘የማረኳቸውን የሚማርኩት፤ የጨቈኗቸውንም የሚገዟቸው’ እንዴት ነው? እንዲህ ያለ ሁኔታ የተፈጸመበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ዳንኤል በሜዶንና ፋርስ መንግሥት ሥር የባቢሎን ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ሆኖ ተሾሟል፤ እንዲሁም አስቴር የፋርስ ንግሥት ሆናለች። በተጨማሪም መርዶክዮስ በመላው የፋርስ ግዛት ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኖ ነበር።

20:2-5—ኢሳይያስ ለሦስት ዓመት ያህል ዕርቃኑን ሄዷል? ምናልባት ኢሳይያስ ከላይ ያለውን መደረቢያ አውልቆ ‘ከውስጥ በለበሳት ልብስ ብቻ’ ሄዶ ይሆናል።—1 ሳሙኤል 19:24የአዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ

21:1—‘በባሕሩ ዳር ያለው ምድረ በዳ’ የተባለው አካባቢ የትኛው ነው? ምንም እንኳ በባቢሎን አካባቢ ቃል በቃል ባሕር ባይኖርም ይህች አገር በዚህ መልኩ ተገልጻለች። ይህም የሆነበት ምክንያት የኤፍራጥስና የጤግሮስ ወንዞች በየዓመቱ እየሞሉ አካባቢውን በማጥለቅለቅ ረግረጋማ ‘ባሕር’ ይፈጥሩ ስለነበረ ነው።

24:13-16—“የወይራ ዛፍ ሲመታ፣ የወይንም ዘለላ ሲቈረጥ ቃርሚያ እንደሚቀር ሁሉ፣ . . . በሕዝቦችም ላይ እንዲሁ ይሆናል” የሚለው አባባል በአይሁዳውያን ላይ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው? ከመከር በኋላ በዛፉ ወይም በወይኑ ተክል ላይ የሚቀር የተወሰነ ፍሬ እንደሚኖር ሁሉ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ከሚመጣው ጥፋት የሚተርፉት ጥቂቶች ብቻ ይሆናሉ። ከጥፋት የተረፉት ሰዎች የትም ይሁኑ የት፣ ሌላው ቀርቶ ‘ወደ ምሥራቅ [ወደ ባቢሎን]’ ወይም ‘ወደ ባሕር ደሴቶች [ወደ ሜድትራኒያን]’ ቢወሰዱ እንኳ ይሖዋን ያወድሳሉ።

24:21—‘በሰማያት ያሉት ኀይሎች’ እና ‘በምድር ያሉት ነገሥታት’ የተባሉት እነማን ናቸው? ‘በሰማያት ያሉ ኀይሎች’ የሚለው አባባል ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎችን በትክክል ይገልጻል። ‘በምድር ያሉ ነገሥታት’ የሚለው ደግሞ ኃይለኛ በሆነው የአጋንንት ተጽዕኖ ሥር ያሉትን የምድር ገዢዎች ያመለክታል።—1 ዮሐንስ 5:19

25:7—‘በሕዝብ ሁሉ ላይ የተጣለው መጋረጃ፣ በመንግሥታት ላይ የተዘረጋው መሸፈኛ’ የተባለው ምንድን ነው? ከመጋረጃና ከመሸፈኛ ጋር በንጽጽር የቀረቡት ሁለት ነገሮች የሰው ልጅ ጠላቶች የሆኑት ኃጢአትና ሞት ናቸው።

ምን ትምህርት እናገኛለን

13:20-22፤ 14:22, 23፤ 21:1-9:- በባቢሎን ላይ እንደታየው የይሖዋ ትንቢታዊ ቃል ምንጊዜም ይፈጸማል።

17:7, 8:- ምንም እንኳ በእስራኤል ይኖሩ የነበሩ አብዛኛዎቹ ሰዎች ለመስማት ፈቃደኛ ባይሆኑም በግለሰብ ደረጃ ወደ ይሖዋ የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ዛሬም በተመሳሳይ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች ለመንግሥቱ ምሥራች ምላሽ ይሰጣሉ።

28:1-6:- እስራኤላውያን በአሦራውያን እጅ የሚወድቁ ቢሆኑም እንኳ አምላክ ታማኝ የሆኑት እንዲተርፉ ያደርጋል። የይሖዋ ፍርድ ጻድቃንን ያለ ተስፋ አይተዋቸውም።

28:23-29:- ይሖዋ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች በግለሰብ ደረጃ እንዲሁም ከሁኔታቸው ጋር በሚስማማ መንገድ የሚያስፈልጋቸውን ማስተካከያ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።

30:15:- የይሖዋን ማዳን ለማግኘት ከፈለግን “በማረፍ” ወይም በሰው ልጆች ዝግጅት አማካኝነት መዳን ለማግኘት ከመጣር በመቆጠብ እምነታችንን ማሳየት ይኖርብናል። እንዲሁም “በጸጥታ” ወይም ለፍርሃት እጃችንን ባለመስጠት፣ ይሖዋ እኛን ለማዳን ባለው ኃይል እንደምንታመን እናሳያለን።

30:20, 21:- ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ባስጻፈው ቃሉ እንዲሁም ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል የሚነግረንን ሰምተን ተግባራዊ በማድረግ እርሱን ‘ማየትና’ ለመዳን የሚረዳንን ድምፁን ‘መስማት’ እንችላለን።—ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም

የኢሳይያስ ትንቢት በአምላክ ቃል ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል

በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሮ ለሚገኘው የአምላክ መልእክት ምንኛ አመስጋኞች ነን! እስካሁን ፍጻሜያቸውን ያገኙት ትንቢቶች ከይሖዋ ‘አፍ የሚወጣው ቃል በከንቱ ወደ እርሱ እንደማይመለስ’ ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል።—ኢሳይያስ 55:11

በኢሳይያስ 9:7 እና 11:1-5, 10 ላይ ስላሉት መሲሐዊ ትንቢቶችስ ምን ማለት ይቻላል? በይሖዋ የማዳን ዝግጅት ላይ ያለንን እምነት አያጠናክሩም? እንዲሁም መጽሐፉ በዘመናችን ዋነኛ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ያሉ ወይም ወደፊት የሚፈጸሙ ትንቢቶችንም ይዟል። (ኢሳይያስ 2:2-4፤ 11:6-9፤ 25:6-8፤ 32:1, 2) በእርግጥም የኢሳይያስ መጽሐፍ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው” ስለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ይሆነናል!—ዕብራውያን 4:12

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢሳይያስና ልጆቹ “ለእስራኤል ምልክትና ድንቅ” ሆነው ነበር

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሩሳሌም “በወይን አትክልት ውስጥ እንዳለ ዳስ” ሆና ነበር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕዝቦች “ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ” የሚያደርጉት እንዴት ነው?