በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቶስ ተቃዋሚ ማንነት ተጋለጠ

የክርስቶስ ተቃዋሚ ማንነት ተጋለጠ

የክርስቶስ ተቃዋሚ ማንነት ተጋለጠ

ገዳይ የሆነ ወረርሽኝ በአካባቢህ በፍጥነት እየተዛመተ እንደሆነ ብታውቅ ራስህን ለመከላከል ምን ታደርጋለህ? አብዛኛውን ጊዜ እንደሚደረገው፣ በሽታ የመከላከል አቅምህን ለማጠናከርና በሽታውን ሊያስተላልፉ ከሚችሉ ሰዎች ለመራቅ ትጥራለህ። በመንፈሳዊ ረገድም ቢሆን እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ ተቃዋሚ “አሁንም እንኳ በዓለም አለ” በማለት ይነግረናል። (1 ዮሐንስ 4:3) በዚህ ሕመም “እንዳንያዝ” በሽታው “ያለባቸውን” ሰዎች ለይተን ማወቅና ከእነርሱ መራቅ ይኖርብናል። ደስ የሚለው መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሚሰጠን መሆኑ ነው።

የክርስቶስ ተቃዋሚ የሚለው አገላለጽ፣ ክርስቶስን የሚቃወሙ ወይም ክርስቶስ እንደሆኑ የሚናገሩ አሊያም በሐሰት የእሱ ወኪሎች ነን የሚሉትን ሁሉ ያጠቃልላል። ኢየሱስ ራሱ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል [ወይም የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው]፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብም ይበትናል።”—ሉቃስ 11:23

እርግጥ ነው፣ ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ተቃዋሚ የጻፈው ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ካረገ ከ60 ዓመታት የሚበልጥ ጊዜ ካለፈ በኋላ ነው። ስለዚህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ማን መሆኑን ማወቅ የምንችለው በምድር ላይ ባሉት ታማኝ የኢየሱስ ተከታዮች ላይ በሚያደርሰው ነገር ነው።—ማቴዎስ 25:40, 45

የክርስቶስ ተቃዋሚ የክርስቲያኖችም ተቃዋሚ ነው

ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን አብዛኛው የዓለም ክፍል እንደሚጠላቸው ሲያስጠነቅቅ እንዲህ ብሏል:- “ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችኋል፣ በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ብዙዎች ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችን ያስታሉ።”—ማቴዎስ 24:9, 11

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ‘በኢየሱስ ስም ምክንያት’ የሚሰደዱ ከሆነ፣ አሳዳጆቹ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች እንደሆኑ ግልጽ ነው። ‘ሐሰተኛ ነቢያትም’ ከዚህ ጎራ የሚመደቡ ሲሆን ከእነርሱም መካከል አንዳንዶቹ በፊት ክርስቲያኖች ነበሩ። (2 ዮሐንስ 7) ዮሐንስ ስለ እነዚህ “ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች” ሲናገር “ከእኛ መካከል ወጡ፤ ይሁን እንጂ ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር” በማለት ጽፏል።—1 ዮሐንስ 2:18, 19

ኢየሱስም ሆነ ዮሐንስ የተናገሯቸው ቃላት በግልጽ እንደሚያሳዩት የክርስቶስ ተቃዋሚ አንድ ግለሰብ ሳይሆን ክርስቶስን የሚቃወሙ ብዙ ሰዎች ናቸው። ከዚህም በላይ ሐሰተኛ ነቢይ እንደመሆናቸው መጠን ዋነኛ ዓላማቸው በሃይማኖታዊ ማታለያዎች ተጠቅሞ ሰዎችን ማሳሳት ነው። ሰዎችን የሚያታልሉባቸው አንዳንድ ዘዴዎች ምንድን ናቸው?

ሃይማኖታዊ ውሸቶችን ማሠራጨት

ሐዋርያው ጳውሎስ የሥራ ባልደረባው የነበረውን ጢሞቴዎስን፣ “ትምህርታቸው እንደማይሽር ቊስል ይሠራጫል” ከተባለላቸው እንደ ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ያሉ ከሃዲዎች ከሚያስተላልፉት ትምህርት እንዲርቅ አስጠንቅቆት ነበር። ጳውሎስ አክሎም “እነዚህም ከእውነት ርቀው የሚባዝኑ ናቸው። እነርሱም ትንሣኤ ሙታን ከዚህ በፊት ሆኖአል እያሉ የአንዳንዶቹን እምነት ይገለብጣሉ” ብሏል። (2 ጢሞቴዎስ 2:16-18) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ትንሣኤ ምሳሌያዊ እንደሆነና ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሁኔታ ትንሣኤ እንዳገኙ ማስተማር ጀምረው ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሲሆን በአምላክ ፊት ሕያው ሆኖ እንደሚታይ ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ በግልጽ ተናግሯል። (ኤፌሶን 2:1-5) ነገር ግን ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ የሚያስተምሩት ትምህርት፣ ኢየሱስ በአምላክ መንግሥት ሥር እንደሚኖር የተናገረውን የሙታን ትንሣኤ የሚያጣጥል ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29

ከጊዜ በኋላ፣ ትንሣኤ ምሳሌያዊ እንደሆነ የሚገልጸውን አመለካከት ግኖስቲክስ ተብለው የሚጠሩ ቡድኖች አስፋፍተው ነበር። ግኖስቲክሶች፣ እውቀት (በግሪክኛው ግኖሲስ) የሚገኘው ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ ነው ብለው ያምኑ ስለነበር የክህደት ክርስትናን ከግሪክ ፍልስፍና እንዲሁም ከሩቅ ምሥራቃውያን እምነቶች ጋር ደባለቁት። ለምሳሌ፣ ቁስ አካል ሁሉ ክፋትን እንደሚያመለክት ስለሚያምኑ ኢየሱስ ሰብዓዊ አካል ያለው ይመስላል እንጂ በሥጋ አልመጣም የሚል አመለካከት ነበራቸው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሐዋርያው ዮሐንስ ግልጽ ማስጠንቀቂያ የሰጠው እንዲህ ካለው ትምህርት እንድንጠበቅ ነበር።—1 ዮሐንስ 4:2, 3፤ 2 ዮሐንስ 7

ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ የተፈጠረው ሌላኛው ውሸት ደግሞ፣ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዲሁም የአምላክ ልጅ እንደሆነ የሚያስተምረው ቅዱስ ሥላሴ ተብሎ የሚጠራው መሠረተ ትምህርት ነው። ዘ ቸርች ኦቭ ዘ ፈርስት ስሪ ሴንቸሪስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ዶክተር አልቫን ላምሰን እንደተናገሩት የሥላሴ መሠረተ ትምህርት “ከአይሁዳውያንም ሆነ ከክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች የመነጨ አይደለም፤ ይህን መሠረተ ትምህርት ያዳበሩትም ሆነ በክርስትና ውስጥ የጨመሩት የፕላቶኒዝም ተከታይ የሆኑ አባቶች ናቸው።” እነዚህ “የፕላቶኒዝም ተከታይ የሆኑ አባቶች” እነማን ናቸው? በአረማዊው የግሪክ ፈላስፋ በፕሌቶ ትምህርቶች የተማረኩ ከሃዲ ቀሳውስት ናቸው።

የክርስቶስ ተቃዋሚ የሥላሴን ትምህርት በረቀቀ መንገድ ወደ ክርስትና በማስገባቱ ዓላማውን ለመፈጸም የሚያስችለው ትልቅ ሥራ አከናውኗል ማለት ይቻላል፤ ይህ ተቃዋሚ በዚህ ትምህርት አማካኝነት አምላክ ምሥጢራዊ እንደሆነ ከማስመሰሉም በላይ በእርሱና በልጁ መካከል ያለው ዝምድና ግራ የሚጋባ እንዲሆን አድርጓል። (ዮሐንስ 14:28፤ 15:10፤ ቈላስይስ 1:15) እስቲ አስበው፣ አምላክ ምሥጢር ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያበረታታው አንድ ሰው እንዴት ‘ወደ አምላክ መቅረብ’ ይችላል?—ያዕቆብ 4:8

ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በበኩረ ጽሑፉ ውስጥ ከ7,000 ጊዜ በላይ የሚገኝ ቢሆንም እንኳ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ይህን ስም ከተረጎሟቸው መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ ማውጣታቸው ሰዎች ይበልጥ ግራ እንዲጋቡ አድርጓል! በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ምሥጢራዊ ብቻ ሳይሆን ስም የሌለው ምሥጢራዊ አካል ለማድረግ መሞከር ለፈጣሪያችንና እርሱ ላስጻፈው ቃሉ አክብሮት ማጣት ነው። (ራእይ 22:18, 19) ከዚህም በላይ መለኮታዊውን ስም ጌታ፣ አምላክ ወይም እግዚአብሔር በሚሉት ስሞች የተኩት ሲሆን ይህ ደግሞ ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ “ስምህ ይቀደስ” ብሎ ከተናገረው ጋር ይጋጫል።—ማቴዎስ 6:9

የክርስቶስ ተቃዋሚዎች የአምላክን መንግሥት አይቀበሉም

የክርስቶስ ተቃዋሚዎች አሁን በምንኖርበት “በመጨረሻው ዘመን” በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በዘመናችን ያሉት የእነዚህ አታላዮች ዋነኛ ግብ፣ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆን የሚጫወተውን ሚና ሰዎች እንዳይረዱት ማድረግ ነው፤ ይህ መንግሥት በሰማይ የሚገኝ መስተዳድር ሲሆን በቅርቡ መላዋን ምድር ይገዛል።—ዳንኤል 7:13, 14፤ ራእይ 11:15

ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች የአምላክ መንግሥት በሰዎች ልብ ውስጥ ያለ ነገር እንደሆነ አድርገው ይሰብካሉ፤ ይህ ትምህርት ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የለውም። (ዳንኤል 2:44) አንዳንዶች ክርስቶስ በሰብዓዊ መንግሥታትና ድርጅቶች በመጠቀም እንደሚሠራ አድርገው ይናገራሉ። ነገር ግን ኢየሱስ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:36) ደግሞም “የዚህ ዓለም ገዥ” እንዲሁም “የዚህ ዓለም አምላክ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እንጂ ክርስቶስ አይደለም። (ዮሐንስ 14:30፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4) ይህም፣ ኢየሱስ በቅርቡ ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት ደምስሶ የመላዋ ምድር ብቸኛ ገዢ የሚሆንበትን ምክንያት ግልጽ ያደርግልናል። (መዝሙር 2:2, 6-9፤ ራእይ 19:11-21) ሰዎች “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት ሲጸልዩ ይህ እንዲሆን መጠየቃቸው ነው።—ማቴዎስ 6:10

ብዙ የሃይማኖት መሪዎች የዓለም የፖለቲካ ሥርዓትን ስለሚደግፉ፣ የአምላክን መንግሥት እውነት የሚሰብኩ ሰዎችን ይቃወማሉ ብሎም ያሳድዳሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራዕይ መጽሐፍ “በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ” ስለታየች አንዲት ምሳሌያዊ ጋለሞታ ማለትም ስለ “ታላቂቱ ባቢሎን” መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው። (ራእይ 17:4-6) እርሷም በምድር “ነገሥታት” ወይም በፖለቲካ መሪዎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስትል ለእነርሱ ድጋፍ በመስጠት መንፈሳዊ ግልሙትና ትፈጽማለች። ይህች ምሳሌያዊ ሴት ከሐሰት ሃይማኖት ሌላ ማንም ልትሆን አትችልም። ከክርስቶስ ተቃዋሚዎች መካከል ትልቁን ቦታ የያዘችው እርሷ ናት።—ራእይ 18:2, 3፤ ያዕቆብ 4:4

የክርስቶስ ተቃዋሚ ‘ጆሮ የሚያሳክክ ትምህርት’ ይሰጣል

ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ካለመቀበላቸውም ሌላ፣ በሥነ ምግባር ረገድ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን አካሄድ በመከተል የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደንቦች ወደኋላ ገሸሽ አድርገዋል። ይህ እንደሚሆን የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “[አምላክን እናገለግላለን የሚሉ] ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 4:3) አስተማሪ ነን የሚሉትን እነዚህን አጭበርባሪዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ “የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለዋውጡ፣ ሐሰተኞች ሐዋርያትና አታላዮች ሠራተኞች” በማለትም ይጠራቸዋል። አክሎም “ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል” በማለት ይናገራል።—2 ቆሮንቶስ 11:13-15

እነዚህ ሰዎች ‘አስነዋሪ ድርጊቶችን’ የሚፈጽሙ ሲሆን ይህም ለላቁት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ዓይን ያወጣ ንቀት እንዳላቸው ያሳያል። (2 ጴጥሮስ 2:1-3, 12-14) ቁጥራቸው እያደገ የመጣ ሃይማኖታዊ መሪዎችና ተከታዮቻቸው፣ እንደ ግብረ ሰዶምና ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የመሳሰሉ ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ወይም ሲፈቅዱ አልተመለከትንም? እስቲ ጥቂት ጊዜ ወስደህ ይህን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘን አመለካከት እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤ መጽሐፍ ቅዱስ በዘሌዋውያን 18:22፤ በሮሜ 1:26, 27፤ በ1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ በዕብራውያን 13:4፤ በይሁዳ 7 ከሚሰጠው ሐሳብ ጋር አወዳድር።

“በመንፈስ የተነገሩ ቃላትን መርምሩ”

ከላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች አንጻር፣ ሐዋርያው ዮሐንስ ሃይማኖታዊ እምነታችንን አቅልለን መመልከት እንደሌለብን የሰጠንን ምክር ልንሠራበት ይገባል። እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ፤ [“በመንፈስ የተነገሩ ቃላትን መርምሩ፣” NW] ምክንያቱም ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።”—1 ዮሐንስ 4:1

በመጀመሪያ መቶ ዘመን በቤርያ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ “አስተዋይ” ሰዎች የተዉትን ጥሩ ምሳሌ ተመልከት። እነዚህ ሰዎች ጳውሎስና ሲላስ የተናገሩት ነገር “እንደዚህ ይሆንን እያሉ መጻሕፍትን በየዕለቱ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጒጒት ተቀብለዋል።” (የሐዋርያት ሥራ 17:10, 11) የቤርያ ሰዎች ምንም እንኳ የማወቅ ጉጉት ቢኖራቸውም ሰምተው የሚቀበሏቸው ነገሮች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን እርግጠኛ መሆን ፈልገው ነበር።

ዛሬም በተመሳሳይ እውነተኛ ክርስቲያኖች በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ባገኙ አመለካከቶች ከመወሰድ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አጥብቀው ይይዛሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅራችሁ በጥልቅ [“በትክክለኛ፣”NW] እውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ እጸልያለሁ” በማለት ጽፏል።—ፊልጵስዩስ 1:9

እስካሁን እንዲህ አላደረግህ ከሆነ ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በማጥናት ‘ትክክለኛ እውቀትና ማስተዋል’ ለማግኘት ግብ አውጣ። የቤርያ ሰዎችን የሚኮርጁ ሰዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች በሚያሰራጩት ‘የፈጠራ ታሪክ’ አይታለሉም። (2 ጴጥሮስ 2:3) ከዚህ ይልቅ እውነተኛው ክርስቶስ እንዲሁም የእርሱ እውነተኛ ተከታዮች ባስተማሩት መንፈሳዊ እውነት አማካኝነት ነጻ ይወጣሉ።—ዮሐንስ 8:32, 36

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ ተቃዋሚ ምን ይላል?

“ልጆች ሆይ፤ ይህ የመጨረሻው ሰዓት [ሐዋርያት የኖሩበት ዘመን ማብቂያ] ነው፤ እንደሰማችሁትም የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል፤ አሁን እንኳ ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጥተዋል።”1 ዮሐንስ 2:18

“ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ሐሰተኛ ማነው? ይህ አብንና ወልድን የሚክደው የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።”1 ዮሐንስ 2:22

“ኢየሱስን የማይቀበል መንፈስ ግን ከእግዚአብሔር አይደለም፤ እንደሚመጣ የሰማችሁት የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ይህ ነው፤ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።”1 ዮሐንስ 4:3

“ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ወጥተዋል። እንዲህ ያለ ማንኛውም ሰው አታላይና የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።”2 ዮሐንስ 7

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የተለያየ ገጽታዎች ያሉት አታላይ

“የክርስቶስ ተቃዋሚ” የሚለው አገላለጽ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን የሚክዱ፣ የእርሱን መንግሥት የሚቃወሙ እንዲሁም ተከታዮቹን የሚያሳድዱ ሰዎችን ሁሉ የሚያመለክት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በሐሰት ክርስቶስን እንወክላለን የሚሉ ወይም ክርስቶስ ብቻ ሊያመጣው የሚችለውን እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት እነርሱ እንደሚያመጡ ቃል እየገቡ የመሲሑን ድርሻ ለመወጣት በመሞከር የሚዳፈሩ ግለሰቦችን፣ ድርጅቶችንና መንግሥታትን ሁሉ ያመለክታል።

[ምንጭ]

አውጉስቲን:- ©SuperStock/age fotostock

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ቤርያ ሰዎች ‘መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር’ አለብን