‘ታላቁ የይሖዋ ቀን ቀርቧል’
‘ታላቁ የይሖዋ ቀን ቀርቧል’
“ታላቁ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቀን ቅርብ ነው፤ ቅርብ ነው ፈጥኖም ይመጣል።”—ሶፎንያስ 1:14
1, 2. (ሀ) ክርስቲያኖች የሚጠባበቁት ልዩ ቀን የትኛው ነው? (ለ) ልናነሳቸው የሚገቡን ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው? ለምንስ?
ፊቷ በደስታ የፈካ አንዲት ወጣት የሠርጓን ቀን በጉጉት ትጠባበቃለች። ነፍሰ ጡር የሆነች አንዲት እናት ልጇ የሚወለድበትን ቀን በናፍቆት አሻግራ ትመለከታለች። በሥራ ሲደክም የቆየ ሠራተኛ ለረጅም ጊዜ ሲጠብቀው የነበረው የእረፍት ቀን የሚጀመርበትን ጊዜ በጉጉት ይጠብቃል። እነዚህን ሦስት ሰዎች የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው? ሁሉም በሕይወታቸው ላይ ለውጥ የሚያስከትለውን ልዩ ቀን ይጠባበቃሉ። ዓይነቱ የተለያየ ቢሆንም እንኳ ሁሉም ጥልቅ የሆነ ስሜት አላቸው። ይዋል ይደር እንጂ የሚጠባበቁት ቀን መድረሱ አይቀርም፤ በመሆኑም ራሳቸውን ዝግጁ አድርገው በጉጉት ይጠብቃሉ።
2 በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች የአንድን ልዩ ቀን መድረስ በጉጉት ይጠባበቃሉ። ይህ ቀን ታላቁ ‘የይሖዋ ቀን’ ነው። (ኢሳይያስ 13:9፤ ኢዩኤል 2:1፤ 2 ጴጥሮስ 3:12) እየቀረበ ያለው ‘የይሖዋ ቀን’ ምንድን ነው? የዚህ ቀን መድረስ በመላው የሰው ዘር ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? ከዚህም በተጨማሪ የቀኑን መድረስ ተዘጋጅተን እየጠበቅን መሆን አለመሆናችንን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? በአሁኑ ወቅት የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት መጣራችን እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም “ታላቁ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቀን ቅርብ ነው፤ ቅርብ ነው ፈጥኖም ይመጣል” የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት እውነተኛ መሆናቸውን ማስረጃዎች ያሳያሉ።—ሶፎንያስ 1:14
“ታላቁ የይሖዋ ቀን”
3. “ታላቁ የይሖዋ ቀን” ምንድን ነው?
3 “ታላቁ የይሖዋ ቀን” ምንድን ነው? “የይሖዋ ቀን” የሚለው አባባል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በብዙ ቦታዎች የሚገኝ ሲሆን ይሖዋ በጠላቶቹ ላይ የቅጣት እርምጃ በመውሰድ ታላቅ ስሙን ያስከበረበትን ልዩ ጊዜ ያመለክታል። ታማኝነታቸውን ያጓደሉት የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝቦች እንዲሁም ጨቋኞቹ የባቢሎንና የግብጽ ነዋሪዎች የይሖዋ የቅጣት ፍርድ በተፈጸመባቸው ጊዜ “የይሖዋ ቀን” መጥቶባቸዋል። (ኢሳይያስ 2:1, 10-12፤ 13:1-6፤ ኤርምያስ 46:7-10) ይሁን እንጂ አሁንም ታላቁ “የይሖዋ ቀን” ከፊታችን ይጠብቀናል። ይህ ጊዜ ይሖዋ ስሙን ባጎደፉ ሰዎች ላይ ፍርዱን የሚያስፈጽምበት “ቀን” ነው። የይሖዋ ቀን የሚጀምረው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ጥፋት ሲሆን የተቀረው ክፉ ሥርዓት በአርማጌዶን ጦርነት ድምጥማጡ ሲጠፋ ደግሞ ይደመደማል።—ራእይ 16:14, 16፤ 17:5, 15-17፤ 19:11-21
4. አብዛኛው የሰው ዘር በፍጥነት እየቀረበ ያለውን የይሖዋን ቀን ሊፈራ የሚገባው ለምንድን ነው?
4 አብዛኛው የሰው ዘር ተረዳውም አልተረዳው በፍጥነት እየቀረበ ያለው ይህ ቀን ሊፈራ ይገባዋል። ለምን? ይሖዋ በነቢዩ ሶፎንያስ አማካኝነት የሚከተለውን መልስ ሰጥቶናል:- “ያ ቀን የመዓት ቀን፣ የመከራና የጭንቀት ቀን፣ የሁከትና የጥፋት ቀን፣ የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ይሆናል።” በእርግጥም እጅግ የሚያስፈራ ቀን ነው! ከዚህም በላይ ነቢዩ “በሰዎች ላይ ጭንቀት አመጣባቸዋለሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአትን ሠርተዋልና” ብሏል።—ሶፎንያስ 1:15, 17
5. በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋን ቀን በተመለከተ ምን ብሩህ አመለካከት አላቸው? ለምንስ?
5 ይሁንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች የይሖዋን ቀን መምጣት በጉጉት ይጠባበቃሉ። ለምን? ይህ ለእነርሱ የመዳን ቀን መሆኑን ያውቃሉ፤ ከዚህም ባሻገር በዚህ ቀን ጻድቃን ነጻ የሚወጡ ሲሆን ይሖዋም በከፍተኛ ሁኔታ ይወደሳል ብሎም ታላቅ ስሙ ይቀደሳል። (ኢዩኤል 3:16, 17፤ ሶፎንያስ 3:12-17) አንድ ሰው ይህን ቀን የመፍራቱ ወይም በጉጉት የመጠበቁ ሁኔታ በአብዛኛው የተመካው በአሁኑ ጊዜ ሕይወቱን በሚመራበት መንገድ ነው። የዚህን ቀን መቅረብ እንዴት ትመለከተዋለህ? ለዚህ ቀን ተዘጋጅተሃል? የይሖዋ ቀን በጣም መቅረቡ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል?
“ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ”
6. ብዙ ሰዎች ‘የይሖዋን ቀን’ የሚመለከቱት እንዴት ነው? እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ የማይደነቁትስ ለምንድን ነው?
6 ጊዜው አጣዳፊ ቢሆንም አብዛኞቹ የምድር ነዋሪዎች “የይሖዋ ቀን” መቅረብ አያስጨንቃቸውም። እንዲያውም ቀኑ በጣም እንደቀረበ በሚያስጠነቅቋቸው ሰዎች ላይ ሲያሾፉና ሲያፌዙ ይታያል። ይህ ሁኔታ እውነተኛ ክርስቲያኖችን አያስደንቃቸውም። ሐዋርያው ጴጥሮስ ያሰፈረውን የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ያስታውሳሉ:- “ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ዕወቁ፤ በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ። እነርሱም፣ ‘“እመጣለሁ” ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል’ ይላሉ።”—2 ጴጥሮስ 3:3, 4
7. የጥድፊያ ስሜታችንን ጠብቀን እንድንኖር ምን ይረዳናል?
7 ይህን መሰሉን አፍራሽ አስተሳሰብ እንድንቋቋምና የጥድፊያ ስሜታችንን ጠብቀን እንድንኖር ምን ሊረዳን ይችላል? ጴጥሮስ እንደሚከተለው በማለት አሳስቦናል:- “የጻፍሁላችሁ ቅን ልቦናችሁን እንድታነቃቁ ለማሳሰብ ነው፤ ደግሞም ቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል እንዲሁም በሐዋርያት አማካይነት በጌታችንና በአዳኛችን የተሰጠውን ትእዛዝ እንድታስቡ ነው።” (2 ጴጥሮስ 3:1, 2) ለትንቢታዊ ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት መስጠታችን ‘ቅን ልቦናችንን ለማነቃቃት’ ይረዳናል። ምናልባትም እነዚህን ማሳሰቢያዎች በተደጋጋሚ ሰምተናቸው ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና አሁን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ለእነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት መስጠታችን እጅግ አስፈላጊ ነው።—ኢሳይያስ 34:1-4፤ ሉቃስ 21:34-36
8. ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ማሳሰቢያዎች ችላ የሚሉት ለምንድን ነው?
8 አንዳንዶች እነዚህን ማሳሰቢያዎች ችላ የሚሉት ለምንድን ነው? ጴጥሮስ ቀጠል በማድረግ እንዲህ ብሏል:- “ከጥንት ጀምሮ ሰማያት እንደነበሩ እንዲሁም ምድር በአምላክ ቃል ከውኃ በላይ ጸንታ እንደቆመችና በውኃ መሃል እንደነበረች ለማስተዋል ፈቃደኞች አይደሉም። በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም በውኃ ተጥለቅልቆ ጠፍቷል።” (2 ጴጥሮስ 3:5, 6 NW) አዎን፣ የይሖዋን ቀን መምጣት የማይፈልጉ ሰዎች ይኖራሉ። የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን የሚያስተጓጉል ነገር አይፈልጉም። ራስ ወዳድነት ስለሚንጸባረቅበት አኗኗራቸው በይሖዋ ዘንድ ተጠያቂ ለመሆን አይሹም! ጴጥሮስ እንደገለጸው እነዚህ ሰዎች ‘የራሳቸውን ክፉ ምኞት ሲከተሉ’ ኖረዋል።
9. በኖኅና በሎጥ ዘመን የነበሩ ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ነበራቸው?
9 እነዚህ ዘባቾች ይሖዋ ባለፉት ጊዜያት በሰው ልጆች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የገባበት ጊዜ መኖሩን አምነው ለመቀበል “ፈቃደኞች” ስላልሆኑ ይህን ሐቅ ሆነ ብለው ችላ ይላሉ። ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያው ጴጥሮስ ይሖዋ በሰው ልጆች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የገባባቸውን ሁለት ጊዜያት ጠቅሰዋል፤ አንደኛው ‘የኖኅ ዘመን’ ሲሆን ሌላው ‘የሎጥ ዘመን’ ነው። (ሉቃስ 17:26-30፤ 2 ጴጥሮስ 2:5-9) ከጥፋት ውኃ በፊት የነበሩ ሰዎች ኖኅ የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ አላስተዋሉም ነበር። በተመሳሳይም ከሰዶምና ገሞራ ጥፋት በፊት ሎጥን አማቾቹ እንደ ‘ቀልደኛ’ ሰው አይተውት ነበር።—ዘፍጥረት 19:14
10. ይሖዋ በማያስተውሉ ሰዎች ላይ ምን እርምጃ ይወስዳል?
10 በዛሬውም ጊዜ ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። ይሁንና ይሖዋ በማያስተውሉ ሰዎች ላይ ምን እርምጃ እንደሚወስድ ልብ በል:- “ተንደላቀው የሚኖሩትን፣ በዝቃጩ ላይ እንደ ቀረ የወይን ጠጅ የሆኑትን፣ ‘ክፉም ይሁን መልካም፣ እግዚአብሔር ምንም አያደርግም’ የሚሉትን ቸልተኞች እቀጣለሁ። ሀብታቸው ይዘረፋል፤ ቤታቸው ይፈራርሳል፤ ቤቶች ይሠራሉ፤ ነገር ግን አይኖሩባቸውም፤ ወይን ይተክላሉ፤ ጠጁን ግን አይጠጡም።” (ሶፎንያስ 1:12, 13) ሰዎች ምናልባት “የተለመደውን” የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ማድረግ ይቀጥሉ ይሆናል፤ ሆኖም ጥረው ግረው ካፈሩት ነገር ዘለቄታዊ ጥቅም አያገኙም። ለምን? ምክንያቱም የይሖዋ ቀን ድንገት ይደርስባቸዋል፤ እንዲሁም ያከማቹት ቁሳዊ ሀብት ከጥፋት አያድናቸውም።—ሶፎንያስ 1:18
“ጠብቀው”
11. የትኛውን ማሳሰቢያ ልብ ማለት ይገባናል?
11 በዙሪያችን ካለው ክፉ ዓለም በተለየ መልኩ እኛ ነቢዩ ዕንባቆም ያሰፈረውን የሚከተለውን ማሳሰቢያ ልብ እንላለን:- “ራእዩ የተወሰነለትን ጊዜ ይጠብቃልና፤ ስለ መጨረሻውም ይናገራል፤ እርሱም አይዋሽም፤ የሚዘገይ ቢመስልም ጠብቀው፤ በእርግጥ ይመጣል፤ ከቶም አይዘገይም።” (ዕንባቆም 2:3) ፍጹማን ባልሆንነው በእኛ አመለካከት ቀኑ የሚዘገይ መስሎ ቢታይም እንኳ ይሖዋ የሚዘገይ አምላክ እንዳልሆነ ማስታወስ ይገባናል። የይሖዋ ቀን ሰዎች ባልጠበቁት ሰዓት ሆኖም በተገቢው ጊዜ ይመጣል።—ማርቆስ 13:33፤ 2 ጴጥሮስ 3:9, 10
12. ኢየሱስ ስለምን ነገር አስጠንቅቋል? ታማኝ አገልጋዮቹስ ምን እርምጃ ወስደዋል?
12 ኢየሱስ፣ የይሖዋን ቀን መጠባበቅ አስፈላጊ መሆኑን ሲያጎላ ከተከታዮቹ አንዳንዶቹም እንኳ የጥድፊያ ስሜታቸው እንደሚቀዘቅዝ አስጠንቅቆ ነበር። ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች በተመለከተ እንዲህ በማለት አስቀድሞ ተናግሯል:- “ያ አገልጋይ ክፉ ቢሆንና ለራሱ፣ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ በማለት፣ ተነሥቶ ሌሎች አገልጋይ ባልንጀሮቹን መምታት ቢጀምር፣ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ እርሱ ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ጌታው መጥቶ፣ ይቈራርጠዋል።” (ማቴዎስ 24:48-51) በአንጻሩ ግን ታማኝና ልባም ባሪያ የጥድፊያ ስሜቱን በታማኝነት ይዞ ቆይቷል። የባሪያው ክፍል ነቅቶ እና ተዘጋጅቶ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ኢየሱስ ይህን ባሪያ በምድር ላይ በሚገኘው “ንብረቱ ሁሉ ላይ” ሾሞታል።—ማቴዎስ 24:42-47
የጥድፊያ ስሜት አስፈላጊነት
13. ኢየሱስ የጥድፊያ ስሜት ማሳየት ያለውን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?
13 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የጥድፊያ ስሜታቸውን ይዘው መቀጠላቸው የግድ አስፈላጊ ነበር። ኢየሩሳሌም “በጦር ሰራዊት ተከባ” በሚያዩበት ጊዜ በፍጥነት ከተማዋን ለቅቀው መሸሽ ነበረባቸው። (ሉቃስ 21:20, 21) ይህ ሁኔታ በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ፍጻሜውን አግኝቷል። ኢየሱስ በዚያን ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች የጥድፊያ ስሜት ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ሲገልጽ ምን እንዳለ ልብ በል:- “በቤቱ ጣራ ላይ የሚገኝ ማንም ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለማውጣት አይውረድ፤ በዕርሻ ቦታው የሚገኝ ማንም ሰው ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ።” (ማቴዎስ 24:17, 18) ታሪክ እንደሚያሳየው ኢየሩሳሌም የጠፋችው ይህ ከሆነ ከአራት ዓመታት በኋላ ነው። ታዲያ በጊዜው የነበሩት ክርስቲያኖች በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የኢየሱስን ቃላት ወዲያውኑ ተግባራዊ ማድረጋቸው አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?
14, 15. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ኢየሩሳሌም በሰራዊት ተከብባ ሲያዩ በጥድፊያ መሸሻቸው የግድ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?
14 የሮማውያን ሰራዊት ኢየሩሳሌምን ያጠፋው በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መሆኑ እውነት ቢሆንም አራቱ ዓመታት ከችግር ነጻ ነበሩ ማለት አይደለም። እንዲያውም ሁኔታው እጅግ የተለየ ነበር! እነዚህ አራት ዓመታት በዓመጽና በደም መፋሰስ የተሞሉ ነበሩ። አንድ የታሪክ ምሑር በዚያን ዘመን በኢየሩሳሌም ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጹ “ደም አፋሳሽ የሆነ ታላቅ የእርስ በርስ ጦርነት ብሎም አስከፊ የሆኑ የጭካኔ ድርጊቶች የተንሠራፋበት” እንደነበር ተናግረዋል። ወጣት ወንዶች የመከላከያ አቅምን እንዲያጠናክሩ፣ መሣሪያ እንዲታጠቁና በውትድርና ውስጥ እንዲያገለግሉ ይመለመሉ የነበረ ሲሆን በየዕለቱም ወታደራዊ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። የሚፈጸመውን የጭካኔ ድርጊት የሚቃወም ሰው እንደ ከሃዲ ይቆጠር ነበር። ስለሆነም ክርስቲያኖች ለጥቂት ጊዜ እንኳ በከተማዋ ውስጥ ለመቆየት ቢመርጡ ለከፋ ችግር መዳረጋቸው አይቀርም ነበር።—ማቴዎስ 26:52፤ ማርቆስ 12:17
15 ኢየሱስ መሸሽ መጀመር ያለባቸው በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ‘በይሁዳም ያሉ’ መሆናቸውን መናገሩን ልብ ልንለው ይገባል። ይህ በእርግጥም አስፈላጊ ነበር፤ ምክንያቱም የሮማውያን ሰራዊት ኢየሩሳሌምን ለቅቆ ከሄደ ከጥቂት ወራት በኋላ የጦርነት እንቅስቃሴውን በስፋት ማካሄድ ቀጥሏል። በመጀመሪያ ላይ በ67 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገሊላን በቁጥጥር ሥር አዋለ፤ ከዚያም በቀጣዩ ዓመት ይሁዳን በዘዴ ድል ማድረግ ቻለ። በዚህም ምክንያት በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሁሉ ለከባድ መከራ ተዳረጉ። ከዚህም በተጨማሪ ለማንኛውም አይሁዳዊ ኢየሩሳሌምን ለቅቆ መውጣት እያደር አስቸጋሪ እየሆነ ሄደ። የከተማዋ በሮች ይጠበቁ የነበረ ከመሆኑም በላይ ከተማዋን ጥሎ ለመውጣት መሞከር አይሁዳውያንን ለሮማውያን አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠር ነበር።
16. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ከአስጨናቂው ጊዜ በሕይወት ለመትረፍ ምን አመለካከት መያዝ ነበረባቸው?
16 እነዚህን ሁሉ ነገሮች በአእምሯችን መያዛችን ኢየሱስ የሁኔታውን አጣዳፊነት በተመለከተ አጥብቆ የተናገረበትን ምክንያት ለመረዳት ያስችለናል። ክርስቲያኖች በቁሳዊ ነገሮች ትኩረታቸው ሳይከፋፈል ለመኖር መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች መሆን ይገባቸዋል። የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ ለመታዘዝ ሲሉ ‘ያላቸውን ሁሉ ለመተው’ ፈቃደኞች መሆን አለባቸው። (ሉቃስ 14:33) የተሰጣቸውን ትእዛዝ በፍጥነት ተቀብለው ወደ ዮርዳኖስ ማዶ የሸሹ ሰዎች ሕይወታቸው ተርፏል።
ምንጊዜም የጥድፊያ ስሜታችንን ጠብቀን መኖር
17. የጥድፊያ ስሜታችን መጨመር ያለበት ለምንድን ነው?
17 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን መደምደሚያ ላይ መሆኑን በግልጽ ያመለክታሉ። በመሆኑም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የጥድፊያ ስሜታችንን መጨመር ይኖርብናል። አንድ ወታደር በሰላሙ ወቅት ጦርነት ላይ እያለ የሚሰማው ዓይነት ውጥረትና ስጋት ላይሰማው ይችላል። ይሁንና ነቅቶ መጠበቅ አጣዳፊ መሆኑን ሳይገነዘብ ቀርቶ ድንገት ጦርነት ቢጀመር አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ላይሆን ይችላል፤ ይህ ደግሞ አስከፊ ውጤት ያስከትልበት ይሆናል። በመንፈሳዊም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የጥድፊያ ስሜታችን እየቀዘቀዘ እንዲሄድ የምንፈቅድ ከሆነ የሚደርስብንን ጥቃት ለመከላከል ሳንዘጋጅ የይሖዋ ቀን በድንገት ሊደርስብን ይችላል። (ሉቃስ 21:36፤ 1 ተሰሎንቄ 5:4) ማንኛውም ሰው ‘አምላክን ከመከተል ወደ ኋላ ተመልሶ’ ከሆነ እርሱን በድጋሚ የሚፈልግበት ጊዜ አሁን ነው።—ሶፎንያስ 1:3-6፤ 2 ተሰሎንቄ 1:8, 9
18, 19. ‘የይሖዋን ቀን መምጣት’ አቅርበን እንድንመለከት ምን ሊረዳን ይችላል?
18 ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘የይሖዋን ቀን መምጣት’ አቅርበን እንድንመለከት ማሳሰቡ አያስገርምም! ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ “በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት” በመኖር ነው። (2 ጴጥሮስ 3:11, 12) መንፈሳዊነታችንን ሊያጎለብቱ በሚችሉ እንቅስቃሴዎች መጠመዳችን ‘የይሖዋን ቀን’ በጉጉት እንድንጠባበቅ ይረዳናል። የይሖዋ ቀን እስከሚደርስ ድረስ ያሉትን ቀናት በቶሎ ልናሳልፋቸው ወይም ልናፋጥናቸው እንደማንችል እሙን ነው። ሆኖም በአምላክ አገልግሎት ከተጠመድን ጊዜው ሳናስበው በፍጥነት ሊያልፍና የምንጠባበቀው ቀን ሊደርስ ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:58
19 ከዚህም በተጨማሪ በአምላክ ቃልና በውስጡ ባሉት ማሳሰቢያዎች ላይ ማሰላሰላችን ቀኑን ‘እየተጠባበቅን መምጫውን ለማፋጠን’ ያስችለናል፤ አዎን፣ ቀኑን “ያለማቋረጥ እንድንጠባበቅ” ይረዳናል። (2 ጴጥሮስ 3:12 በዊልያም ባርክሌይ የተዘጋጀው አምፕሊፋይድ ባይብል፣ ዘ ኒው ቴስታመንት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) እነዚህ ማሳሰቢያዎች የይሖዋ ቀን መድረሱን ብቻ ሳይሆን ይሖዋን ‘የሚጠባበቁ’ ሰዎች ስለሚያገኟቸው እጅግ ብዙ በረከቶች የሚናገሩ ትንቢቶችንም አካትተው ይዘዋል።—ሶፎንያስ 3:8
20. የትኛውን ጥብቅ ማሳሰቢያ ልብ ልንል ይገባል?
20 ነቢዩ ሶፎንያስ የሰጠንን የሚከተለውን ጥብቅ ማሳሰቢያ ልብ ልንለው በሚገባን ጊዜ ላይ እንገኛለን:- “የእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ በእናንተ ላይ ሳይመጣ፣ የእግዚአብሔር የመዓት ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ። እናንት የምድር ትሑታን ሁሉ፣ ትእዛዙን የምትፈጽሙ፣ እግዚአብሔርን እሹ፤ ጽድቅንና ትሕትናን ፈልጉ፤ በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን፣ ትሰወሩ ይሆናል።”—ሶፎንያስ 2:2, 3
21. በ2007 የአምላክ ሕዝቦች ቁርጥ ውሳኔ ምን መሆን አለበት?
21 በመሆኑም “ታላቁ የይሖዋ ቀን ቀርቧል” የሚሉት ቃላት የ2007 የዓመት ጥቅስ እንዲሆኑ መመረጣቸው ተገቢ ነው። የአምላክ ሕዝቦች ይህ ቀን ‘ቅርብ እንደሆነና ፈጥኖም እንደሚመጣ’ እርግጠኞች ናቸው። (ሶፎንያስ 1:14) ቀኑ ‘ከቶ አይዘገይም።’ (ዕንባቆም 2:3) ስለሆነም የቀኑን መምጣት በምንጠባበቅበት በዚህ ወቅት ትንቢቱ የመጨረሻ ፍጻሜውን የሚያገኝበት ጊዜ በጣም መድረሱን በመረዳት ከመቼውም ይበልጥ ነቅተን እንኑር!
የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልትመልስ ትችላለህ?
• “ታላቁ የይሖዋ ቀን” ምንድን ነው?
• ብዙዎች የጊዜውን አጣዳፊነት ችላ የሚሉት ለምንድን ነው?
• የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የጥድፊያ ስሜት ማሳየት የነበረባቸው ለምንድን ነው?
• የጥድፊያ ስሜታችንን ይበልጥ ማቀጣጠል የምንችለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የ2007 የዓመት ጥቅስ “ታላቁ የይሖዋ ቀን ቀርቧል” የሚል ነው።—ሶፎንያስ 1:14 NW
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኖኅ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ይሖዋ የሚወስደው እርምጃ ለዘባቾች ድንገተኛ ይሆንባቸዋል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ‘ኢየሩሳሌም በሰራዊት ተከብባ’ በሚመለከቱበት ጊዜ በፍጥነት ከተማዋን ለቅቀው መሸሽ ነበረባቸው