ይሖዋ ‘ይፈርዳል’
ይሖዋ ‘ይፈርዳል’
“እግዚአብሔርስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?” —ሉቃስ 18:7
1. ለአንተ የብርታት ምንጭ የሆኑልህ እነማን ናቸው? ለምንስ?
በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ለብዙ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩ ወንድሞችና እህቶች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ በግለሰብ ደረጃ የምታውቃቸው አሉ? ከረጅም ጊዜ በፊት የተጠመቁና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውታሪ የሆኑ አንዲት እህት ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል። አሊያም ደግሞ የጉባኤውን የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴ ከሳምንት እስከ ሳምንት ያለማቋረጥ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሲደግፉ የኖሩ አንድ በዕድሜ የገፉ ወንድም ትዝ ይሉህ ይሆናል። ከእነዚህ ታማኝ አገልጋዮች መካከል ብዙዎቹ፣ በአሁኑ ወቅት አርማጌዶን መጥቶ ሁሉ ነገር ይጠናቀቃል ብለው ሲያስቡ የነበሩ ናቸው። ሆኖም ይህ ኢፍትሐዊ ዓለም እስካሁን ድረስ መቆየቱ ይሖዋ በሰጠው ተስፋ ላይ ያላቸውን የመተማመን ስሜትም ይሁን ‘እስከ መጨረሻ ለመጽናት’ ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ እንዲያዳክምባቸው አልፈቀዱም። (ማቴዎስ 24:13) በእርግጥም እነዚህ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የሚያሳዩት ጥልቅ እምነት ለመላው ጉባኤ የብርታት ምንጭ ሆኗል።—መዝሙር 147:11
2. እንድናዝን የሚያደርግ ምን ሁኔታ አለ?
2 ይሁንና አንዳንዴ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር ሲከሰት እንመለከታለን። ለረጅም ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ውሎ አድሮ በይሖዋ ላይ ያላቸው እምነት በመዳከሙ ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል። የቀድሞ ወዳጆቻችን ይሖዋን ሲተዉ ማየት ያሳዝናል፤ በመሆኑም እያንዳንዱን ‘የጠፋ በግ’ ወደ መንጋው እንዲመለስ የመርዳት ልባዊ ፍላጎት አለን። (መዝሙር 119:176፤ ሮሜ 15:1) አንዳንዶች በታማኝነት ሲጸኑ ሌሎች ግን ይህን ሳያደርጉ መቅረታቸው ጥያቄዎች ያስነሳል። አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋ ላይ ያላቸውን እምነት ጠብቀው ሲኖሩ ሌሎች ግን እምነታቸው የተዳከመው ለምንድን ነው? ‘ታላቁ የይሖዋ ቀን’ እንደቀረበ ያለንን ጽኑ እምነት ይዘን ለመቀጠል በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ አለብን? (ሶፎንያስ 1:14) በሉቃስ ወንጌል ውስጥ የሚገኝ አንድ ምሳሌ እንመልከት።
“የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ” ለሚኖሩ ሰዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
3. ስለ አንዲት መበለትና ስለ አንድ ዳኛ ከሚናገረው ምሳሌ በተለይ እነማን ሊጠቀሙ ይችላሉ? ለምንስ?
3 በሉቃስ ምዕራፍ 18 ላይ ኢየሱስ ስለ አንዲት መበለትና ስለ አንድ ዳኛ የተናገረውን ምሳሌ እናገኛለን። ይህ ምሳሌ ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ከተመለከትነው ማለትም ለመጣበት እንግዳ የሚያቀርበው እንጀራ እንዲሰጠው ወዳጁን ስለነዘነዘው ሰው ከሚናገረው ምሳሌ ጋር ይመሳሰላል። (ሉቃስ 11:5-13) ይሁን እንጂ ስለ መበለቲቱና ስለ ዳኛው በሚናገረው ምሳሌ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ምሳሌው ፍጻሜውን የሚያገኘው “የሰው ልጅ” የመንግሥት ሥልጣኑን ይዞ “በሚመጣበት ጊዜ” ማለትም ከ1914 በኋላ በምድር በሚኖሩ ሰዎች ላይ መሆኑን ያመለክታል።—ሉቃስ 18:8 a
4. ኢየሱስ በሉቃስ 18 ላይ የሚገኘውን ምሳሌ ከመጥቀሱ በፊት ምን ተናገረ?
4 ኢየሱስ ስለ መበለቲቱና ስለ ዳኛው የሚገልጸውን ምሳሌ ከመናገሩ በፊት በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ላይ መገኘቱን የሚጠቁመው ምልክት ልክ ‘ሰማዩን ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ መብረቅ’ በግልጽና በስፋት እንደሚታይ ተናግሯል። (ሉቃስ 17:24፤ 21:10, 29-33) ዳሩ ግን ‘በፍጻሜው ዘመን’ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች በግልጽ ለሚታየው ለዚህ ማስረጃ ትኩረት አልሰጡም። (ዳንኤል 12:4) ለምን? ምክንያቱ በኖኅና በሎጥ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የይሖዋን ማስጠንቀቂያ ችላ እንዲሉ ካደረጋቸው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ‘እስከ ጠፉበት ቀን ድረስ ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡ፣ ይተክሉና ቤት ይሠሩ ነበር።’ (ሉቃስ 17:26-29) ሕይወታቸውን ያጡት በተለመዱት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸው በመዋጣቸው ሳቢያ ለአምላክ ፈቃድ ትኩረት ስላልሰጡ ነበር። (ማቴዎስ 24:39) በአጠቃላይ ሲታይ፣ በዛሬው ጊዜም ሰዎች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸው ስለተጠመዱ ከአምላክ የራቀው የዚህ ዓለም መጨረሻ መቅረቡን የሚያመለክቱትን ማስረጃዎች ማየት ተስኗቸዋል።—ሉቃስ 17:30
5. (ሀ) ኢየሱስ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ለእነማን ነው? ለምንስ? (ለ) አንዳንዶች እምነታቸውን እንዲያጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው?
5 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ተከታዮቹም እንኳ ‘ወደ ኋላ እስኪመለሱ’ ድረስ ሐሳባቸው በሰይጣን ዓለም ጉዳዮች ሊከፋፈል እንደሚችል ማወቁ አሳስቦት ነበር። (ሉቃስ 17:22, 31) በእርግጥም ይህ ሁኔታ በአንዳንድ ክርስቲያኖች ላይ ተከስቷል። እነዚህ ሰዎች ለብዙ ዓመታት ይሖዋ፣ ይህን ክፉ ዓለም የሚያጠፋበትን ጊዜ በናፍቆት ሲጠባበቁ ቆይተዋል። ይሁንና አርማጌዶን እነርሱ በጠበቁት ጊዜ ሳይመጣ በመቅረቱ ተስፋ ቆርጠዋል። የይሖዋ የፍርድ ቀን ስለመቅረቡ ያላቸው እምነት ተዳክሟል። ለአገልግሎት ያላቸው ቅንዓት ቀስ በቀስ እየቀዘቀዘ በመሄዱና በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴዎቻቸው በመጠመዳቸው ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸው ጊዜ ተመናምኗል። (ሉቃስ 8:11, 13, 14) ከጊዜ በኋላም ‘ወደ ኋላ ተመልሰዋል’፤ እንዴት የሚያሳዝን ነው!
‘ሳይታክቱ ሁልጊዜ የመጸለይ’ አስፈላጊነት
6-8. (ሀ) ስለ መበለቲቱና ስለ ዳኛው የሚገልጸውን ምሳሌ ተናገር። (ለ) ኢየሱስ ይህ ምሳሌ እንዴት በሥራ ላይ እንደሚውል ሲገልጽ ምን አለ?
6 ይሖዋ የሰጠን ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ያለን ጽኑ እምነት እንዳይዳከም ምን ማድረግ እንችላለን? (ዕብራውያን 3:14) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ክፉ ወደሆነው የሰይጣን ዓለም እንዳይመለሱ ካስጠነቀቃቸው በኋላ የዚህን ጥያቄ መልስ ሰጥቷል።
7 ሉቃስ “ደቀ መዛሙርቱ ሳይታክቱ ሁል ጊዜ መጸለይ እንደሚገባቸው ለማሳየት ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው” ሲል ዘግቧል። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “በአንዲት ከተማ የሚኖር እግዚአብሔርን የማይፈራና ሰውን የማያከብር አንድ ዳኛ ነበረ። በዚያችው ከተማ የምትኖር አንዲት መበለት ነበረች፤ እርሷ፣ ‘ከባላጋራዬ ጋር ስላለብኝ ጒዳይ ፍረድልኝ’ እያለች ወደ እርሱ ትመላለስ ነበር። ዳኛውም ለተወሰነ ጊዜ አልተቀበላትም ነበር፤ በኋላ ግን በልቡ እንዲህ አለ፤ ‘ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ፣ ሰውንም ባላከብር፣ ይህች መበለት ስለምትጨቀጭቀኝ እፈርድላታለሁ፤ አለበለዚያ ዘወትር እየተመላለሰች ታሰለቸኛለች።’”
8 ኢየሱስ ይህን ካላቸው በኋላ ይህ ምሳሌ እንዴት በሥራ ላይ እንደሚውል ሲናገር እንዲህ አለ:- “ዐመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። እግዚአብሔርስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? ከመጠን በላይስ ችላ ይላቸዋልን? እላችኋለሁ፤ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆንን?”—ሉቃስ 18:1-8
“ፍረድልኝ”
9. ስለ መበለቲቱና ስለ ዳኛው በተነገረው ምሳሌ ላይ ጎልቶ የወጣው ጭብጥ ምንድን ነው?
9 የዚህ ሕያው ምሳሌ ዋነኛ ጭብጥ በጣም ግልጽ ነው። ጭብጡ በኢየሱስ ንግግርም ሆነ በምሳሌው ውስጥ በተጠቀሱት ሰዎች ባሕርይ ላይ ተንጸባርቋል። መበለቲቱ “ፍረድልኝ” ስትል ተማጽናለች። ዳኛው ደግሞ “እፈርድላታለሁ” ብሏል። ኢየሱስም “እግዚአብሔርስ . . . ወደ እርሱ ለሚጮኹ ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?” ሲል ጠይቋል። ከዚያም ይሖዋን በሚመለከት “ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 18:3, 5, 7, 8) ታዲያ ይሖዋ ‘የሚፈርደው’ መቼ ነው?
10. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍርድ የተሰጠው መቼ ነው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ለሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮች የሚፈረድላቸው መቼና እንዴት ነው?
10 በመጀመሪያው መቶ ዘመን “የበቀል ጊዜ” የመጣው በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌምና በውስጧ ያለው ቤተ መቅደስ በጠፋበት ወቅት ነበር። (ሉቃስ 21:22) በአሁን ጊዜ ላሉት የአምላክ ሕዝቦች የሚፈረድላቸው ‘በታላቁ የይሖዋ ቀን’ ነው። (ሶፎንያስ 1:14፤ ማቴዎስ 24:21) በዚያን ጊዜ ይሖዋ በሕዝቡ ላይ ‘መከራን ለሚያመጡ መከራን የሚከፍላቸው’ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ “እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል።”—2 ተሰሎንቄ 1:6-8፤ ሮሜ 12:19
11. ፍርድ “ፈጥኖ” የሚመጣው በምን መንገድ ነው?
11 ይሁንና ይሖዋ “ፈጥኖ” እንደሚፈርድልን የሰጠውን ማረጋገጫ መረዳት ያለብን እንዴት ነው? የአምላክ ቃል፣ ይሖዋ ‘የሚታገሥ’ ቢሆንም በተገቢው ጊዜ ፈጥኖ የፍርድ እርምጃ እንደሚወስድ ያመለክታል። (ሉቃስ 18:7, 8 የ1954 ትርጉም፤ 2 ጴጥሮስ 3:9, 10) በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ በመጣ ጊዜ ክፉዎች ወዲያውኑ ጠፍተዋል። በሎጥ ዘመንም እንዲሁ እሳት ከሰማይ ሲዘንብ ክፉዎች ከሕልውና ውጭ ሆነዋል። ኢየሱስ “የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን እንደዚሁ ይሆናል” ብሏል። (ሉቃስ 17:27-30) በክፉዎች ላይ “ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል።” (1 ተሰሎንቄ 5:2, 3) በእርግጥም ይሖዋ የሰይጣንን ዓለም ፍትሑ ከሚፈቅደው ውጭ አንድ ተጨማሪ ቀን እንኳ እንዲቆይ እንደማያደርግ ልንተማመን እንችላለን።
“ይፈርድላቸዋል”
12, 13. (ሀ) ኢየሱስ ስለ መበለቲቱና ስለ ዳኛው በተናገረው ምሳሌ ላይ ትምህርቱን ያቀረበው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማና እንደሚፈርድልን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
12 ስለ መበለቲቱና ስለ ዳኛው የሚገልጸው ምሳሌ ሌሎች አስፈላጊ እውነቶችንም ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ኢየሱስ የምሳሌውን ተግባራዊ ጠቀሜታ በተናገረ ጊዜ “ዐመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። እግዚአብሔርስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?” ብሏል። እርግጥ ነው ኢየሱስ በምሳሌው ላይ ይሖዋን ከዳኛው ጋር ያወዳደረው አምላክ በእርሱ የሚያምኑትን ሰዎች በተመሳሳይ መንገድ ይይዛቸዋል ለማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ፣ በዳኛውና በአምላክ መካከል ያሉትን ልዩነቶች በማነጻጸር ደቀ መዛሙርቱን ስለ ይሖዋ አስተምሯቸዋል። በዳኛውና በአምላክ መካከል ያሉት ልዩነቶች ምንድን ናቸው?
13 በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ዳኛ “ዐመፀኛ” ሲሆን ‘አምላክ ግን ጻድቅ ዳኛ ነው።’ (መዝሙር 7:11፤ 33:5) ዳኛው ለመበለቲቱ በግለሰብ ደረጃ አላሰበላትም፤ ይሖዋ ግን የእያንዳንዱ ግለሰብ ሁኔታ ያሳስበዋል። (2 ዜና መዋዕል 6:29, 30) ዳኛው መበለቲቱን ለመርዳት ፈቃደኛ አልነበረም፤ ይሖዋ ግን አገልጋዮቹን ለመርዳት ፈቃደኛና ዝግጁ ነው። (ኢሳይያስ 30:18, 19) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ዓመጸኛው ዳኛ የመበለቲቱን ልመና ሰምቶ ከፈረደላት ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ይሖዋ የሕዝቦቹን ጸሎት እንደሚሰማና እንደሚፈርድላቸው ምንም ጥርጥር የለውም!—ምሳሌ 15:29
14. በመጪው የአምላክ የፍርድ ቀን ላይ እምነት ማጣት የሌለብን ለምንድን ነው?
14 በመሆኑም በመጪው የአምላክ የፍርድ ቀን ላይ ያላቸውን እምነት ያጡ ሰዎች ከባድ ስሕተት ሠርተዋል። ለምን? ‘ታላቁ የይሖዋ ቀን’ ቅርብ ስለመሆኑ ያላቸውን ጽኑ እምነት በማላላት ይሖዋ ቃሉን በታማኝነት በመጠበቁ ላይ ጥያቄ እንዳላቸው በተግባራቸው አሳይተዋል። ይሁንና ማንም ሰው ቢሆን ስለ አምላክ ታማኝነት ጥያቄ የማንሳት መብት የለውም። (ኢዮብ 9:12) ልናስብበት የሚገባን ተገቢ ጥያቄ ‘እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ ታማኝ እንሆናለን?’ የሚለው ነው። ኢየሱስም ስለ መበለቲቱና ስለ ዳኛው በተናገረው ምሳሌ መደምደሚያ ላይ ያነሳው ነጥብ ይህ ነው።
“የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ እንዲህ ያለ እምነት ያገኝ ይሆንን?”
15. (ሀ) ኢየሱስ ምን ጥያቄ አንስቶ ነበር? ለምንስ? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖብናል?
15 ኢየሱስ “የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ እምነትን [“እንዲህ ያለ እምነት፣” የአዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ] ያገኝ ይሆንን?” የሚል ትኩረት የሚስብ ጥያቄ አንስቷል። (ሉቃስ 18:8) ኢየሱስ “እንዲህ ያለ እምነት” ሲል ማንኛውንም ዓይነት እምነት ማለቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የመበለቲቷን የመሰለ እምነት ለይቶ መጥቀሱ ነበር። ኢየሱስ ላቀረበው ጥያቄ መልስ አልሰጠም። ጥያቄውን ያነሳው ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ያለ እምነት ይኖራቸው እንደሆነ ራሳቸውን እንዲመረምሩ ለማሳሰብ ፈልጎ ነበር። እምነታቸው ውሎ አድሮ የሚዳከምና ትተው ወደ መጡት ነገር እንዲመለሱ የሚያደርግ ነው ወይስ በምሳሌው ላይ እንደተጠቀሰችው መበለት የመሰለ እምነት አላቸው? እኛም በተመሳሳይ ‘“የሰው ልጅ” በልቤ ውስጥ የሚያገኘው እምነት ምን ዓይነት ይሆን?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።
16. መበለቲቷ ምን ዓይነት እምነት ነበራት?
16 ይሖዋ ከሚፈርድላቸው መካከል ለመሆን ከፈለግን የመበለቲቷን ዓይነት አካሄድ መከተል ይኖርብናል። የመበለቷ እምነት ምን ዓይነት ነው? መበለቷ ‘“ፍረድልኝ” እያለች ወደ እርሱ [ወደ ዳኛው] በመመላለስ’ እምነቷን አሳይታለች። መበለቲቱ ከአንድ ዓመጸኛ ሰው ፍርድ ለማግኘት ሳትታክት ተመላልሳለች፤ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮችም ፍርዱ ከጠበቁት በላይ የዘገየ ቢመስላቸውም እንኳ ይሖዋ እንደሚፈርድላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ አዘውትረው በመጸለይ እንዲያውም ‘ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ በመጮኽ’ አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት እንዳላቸው ያሳያሉ። (ሉቃስ 18:7) አንድ ክርስቲያን እንዲፈረድለት መጸለዩን ካቆመ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በማሰብ እርምጃ እንደሚወስድ ጥርጣሬ ገብቶታል ማለት ነው።
17. በጸሎት እንድንጸናም ሆነ ይሖዋ የሚፈርድበት ቀን ስለመምጣቱ ጽኑ እምነት እንዲኖረን የሚያበረታቱ ምን ምክንያቶች አሉ?
17 መበለቷ የነበረችበት ሁኔታ ያለማቋረጥ መጸለያችን ተገቢ መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ምክንያት ይዟል። እርሷ ባለችበት ሁኔታና በእኛ ሁኔታ መካከል ያለውን ልዩነት ልብ በል። መበለቷ ወደ ዳኛው ያለማቋረጥ ትመላለስ የነበረችው አይዞሽ ባይ ሳይኖራት ሲሆን እኛ ግን ‘በጸሎት እንድንጸና’ ከአምላክ ቃል ብዙ ማበረታቻ አግኝተናል። (ሮሜ 12:12) መበለቲቷ ጥያቄዋ ተቀባይነት ያግኝ አያግኝ እርግጠኛ አልነበረችም፤ ለእኛ ግን ይሖዋ እንደሚፈርድልን ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ይሖዋ በነቢዩ አማካኝነት “የሚዘገይ ቢመስልም ጠብቀው፤ በእርግጥ ይመጣል፤ ከቶም አይዘገይም” ብሎናል። (ዕንባቆም 2:3፤ መዝሙር 97:10) መበለቲቷ አቤቱታዋ ተቀባይነት እንዲያገኝ እርሷን ወክሎ የሚሟገትላት ሰው አልነበራትም፤ እኛ ግን ‘ከአምላክ ቀኝ ተቀምጦ ስለእኛ የሚማልድ’ ኢየሱስን የመሰለ ኃያል ረዳት አለን። (ሮሜ 8:34፤ ዕብራውያን 7:25) መበለቲቷ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩባትም እንኳ ይፈርድልኝ ይሆናል በሚል ተስፋ ዳኛውን ከመማጸን ወደኋላ ካላለች፣ የይሖዋ የፍርድ ቀን ስለመምጣቱ በሚናገረው እርግጠኛ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ጠብቀን መኖራችን ምንኛ ተገቢ ነው!
18. ጸሎት እምነታችን እንዲጠናከርም ሆነ እንዲፈረድልን የሚረዳን እንዴት ነው?
18 የመበለቷ ምሳሌ በጸሎትና በእምነት መካከል የተቀራረበ ዝምድና እንዳለና በጸሎት መጽናታችን እምነታችን እንዲዳከም የሚያደርጉ ተጽዕኖዎችን ለማሸነፍ እንደሚረዳን ይጠቁማል። ይህ ሲባል ግን ለይስሙላ የሚቀርብ ጸሎት እምነታችንን ከመጥፋት ይጠብቀዋል ማለት አይደለም። (ማቴዎስ 6:7, 8) ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ የተመካው በአምላክ ላይ መሆኑን በመገንዘብ ወደ እርሱ ለመጸለይ ስንገፋፋ ይበልጥ ወደ አምላክ እንቀርባለን፤ እንዲሁም እምነታችን ይጠናከራል። እምነት ለመዳን አስፈላጊ በመሆኑ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ‘ሳትታክቱ ሁልጊዜ ጸልዩ’ በማለት ማበረታታቱ ምንም አያስገርምም! (ሉቃስ 18:1፤ 2 ተሰሎንቄ 3:13) ‘ታላቁ የይሖዋ ቀን’ መምጣቱ የተመካው በመጸለያችን ላይ አለመሆኑ ግልጽ ነው፤ ጸለይንም አልጸለይን ቀኑ መምጣቱ አይቀርም። ይሁንና እኛ በግለሰብ ደረጃ የሚፈረድልን መሆናችን ወይም ከአምላክ ጦርነት በሕይወት መትረፋችን የተመካው በእምነታችንና ጸሎት በታከለበት የጽድቅ አካሄዳችን ላይ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።
19. አምላክ ‘እንደሚፈርድልን’ ጽኑ እምነት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
19 ኢየሱስ “የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ እንዲህ ያለ እምነት ያገኝ ይሆንን?” የሚል ጥያቄ ማቅረቡን እናስታውሳለን። ትኩረትን የሚስበው የዚህ ጥያቄ መልስ ምን ይሆን? በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በምድር ዙሪያ የሚኖሩ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በጸሎታቸው፣ በትዕግሥታቸውና በጽናታቸው እንዲህ ያለ እምነት እንዳላቸው ማሳየታቸው ምንኛ የሚያስደስት ነው! ኢየሱስ ያነሳው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ የሚያገኘው በዚህ መንገድ ነው። አዎን፣ የሰይጣን ዓለም በደል እያደረሰብን ቢሆንም አምላክ ‘ለምርጦቹ እንደሚፈርድላቸው’ ጠንካራ እምነት አለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የዚህን ምሳሌ ትርጉም በተሟላ ሁኔታ ለመረዳት ሉቃስ 17:22-33ን አንብብ። በሉቃስ 17:22, 24, 30 ላይ የተጠቀሰው “የሰው ልጅ” የሚለው አገላለጽ በሉቃስ 18:8 ላይ የሚገኘውን ጥያቄ ለመመለስ እንዴት እንደሚረዳን ለማስተዋል ሞክር።
ታስታውሳለህ?
• አንዳንድ ክርስቲያኖች እምነታቸውን እንዲያጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው?
• ስለ መጪው የይሖዋ የፍርድ ቀን ጠንካራ እምነት ማሳደር የምንችለው ለምንድን ነው?
• በጸሎት እንድንጸና የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉን?
• በጸሎት መጽናታችን እምነታችን እንዳይጠፋ የሚረዳን እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ መበለቲቷና ስለ ዳኛው የሚናገረው ምሳሌ ምን ነገር አጉልቶ ያሳያል?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክ ‘እንደሚፈርድላቸው’ ጠንካራ እምነት አላቸው