ሕይወትን እና ሰዎችን ይወድ የነበረ ሰው
ሕይወትን እና ሰዎችን ይወድ የነበረ ሰው
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል ሆኖ ለረጅም ዓመታት ያገለገለው ወንድም ዳንኤል ሲድሊክ በ87 ዓመቱ ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 18, 2006 ምድራዊ ሕይወቱን አጠናቅቋል። ወንድም ዳንኤል ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆኖ ወደ 60 ለሚጠጉ ዓመታት አገልግሏል።
የሚቀርቡት ጓደኞቹ በቁልምጫ ዳን ብለው የሚጠሩት ወንድም ዳንኤል ሲድሊክ ቤቴል የገባው በ1946 ነው። ወደ ቤቴል ከመምጣቱ በፊት በካሊፎርኒያ ልዩ አቅኚ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በገለልተኝነት አቋሙ ምክንያት የተወሰኑ ጊዜያት በወኅኒ አሳልፏል። በሰኔ 1, 1985 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ “አምላክ ሆይ፣ ያንተ ወዳጅ መሆን እንዴት ያለ ውድ መብት ነው!” በሚል ርዕስ በወጣው የሕይወት ታሪኩ ላይ በዚያ ወቅት ስላሳለፈው ሁኔታ በዝርዝር ተገልጿል።
ወንድም ዳንኤል ሲድሊክ ትሑትና በቀላሉ የሚቀረብ ሰው ነበር። ለቤቴል ቤተሰብ አባላት የማለዳ አምልኮ በሚመራበት ወቅት ዘወትር ፕሮግራሙን የሚከፍትባቸው “እውነተኛውንና ሕያው የሆነውን አምላክ ለማገልገል በሕይወት መኖር እንዴት ጥሩ ነው” የሚሉት የተለመዱ ቃላት ሕይወትን ይወድ እንደነበር በግልጽ ያሳያሉ። የሕዝብ ተናጋሪ በሚሆንበት ወቅትም ይህንን የእርሱን አመለካከት ሌሎችም እንዲያዳብሩ ይፈልግ ነበር። ከሚሰጣቸው ንግግሮች መካከል “ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው፣” “የይሖዋን ደስታ ማንጸባረቅ፣” “የመንፈስን እሳት አታዳፍኑ” እና “ወደር የሌለው በረከት ይጠብቀናል” የሚሉ ጭብጦች ያሏቸው ይገኙባቸዋል።
ወንድም ዳንኤል ሲድሊክ በ1970 “ከአምላክ የተገኘች ረዳት” ብሎ የጠራትን ማሪና ሆድሰን የምትባል እንግሊዛዊት አገባ። ከተጋቡ በኋላ ይሖዋን ከ35 ዓመት በላይ አንድ ላይ አገልግለዋል።
ወንድም ዳንኤል ሲድሊክ በቤቴል ቆይታው የሕትመትና የጽሑፍ ዝግጅት ክፍልን ጨምሮ በተለያዩ ዲፓርትመንቶች ውስጥ አገልግሏል። ደብሊው ቢ ቢ አር በተባለው የድርጅቱ ሬዲዮ ጣቢያ ውስጥም ሠርቷል። ከዚያም በኅዳር 1974 የበላይ አካል አባል ሆኖ የተሾመ ከመሆኑም በላይ ከጊዜ በኋላ በፐርሶኔል እንዲሁም በጽሑፍ ኮሚቴዎች ውስጥም ይሠራ ነበር።
ከ30 ዓመታት በላይ በፐርሶኔል ኮሚቴ ውስጥ ያገለገለው ወንድም ዳንኤል ሲድሊክ ለሰዎች በነበረው ጥልቅ ፍቅር ተለይቶ ይታወቃል። በዚያ በሚያስገመግም ድምጹ ይሖዋን የማገልገል መብታቸውን ሁሌም ቢሆን ከፍ አድርገው እንዲመለከቱት ብዙዎችን አበረታቷቸዋል። እውነተኛ ደስታ በውጫዊ ነገሮች ላይ የተመካ ሳይሆን ከይሖዋ ጋር ባለን ቅርርብ እንዲሁም ለሕይወት ባለን አመለካከት ላይ የተመካ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገር ነበር።
የቤቴል ቤተሰብ ወንድም ዳንኤልን በማጣቱ በጣም ቢያዝንም እንኳ ሕይወትንና ሰዎችን ከልብ በመውደድ ረገድ የተወውን ምሳሌ ዘወትር ያስታውሱታል። ወንድም ዳንኤል በራእይ 14:13 ላይ “ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ ሆነው የሚሞቱ ብፁዓን ናቸው . . . ሥራቸው ስለሚከተላቸው ከድካማቸው ያርፋሉ” ከተባለላቸው ሰዎች መካከል እንደሚሆን እርግጠኞች ነን።