በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማዕበሉን መቋቋም ትችላለህ

ማዕበሉን መቋቋም ትችላለህ

ማዕበሉን መቋቋም ትችላለህ

በዚህ አስጨናቂ ዘመን ብዙዎች ማዕበል መሰል መከራዎች ያጋጥሟቸዋል። ይሁንና ክርስቲያኖች ለአምላክ ያላቸው ፍቅርና ለመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ያላቸው ታማኝነት የሚያጋጥሟቸውን መከራዎች እንዲቋቋሙ ይረዷቸዋል። እንዴት? ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው አንድ ምሳሌ መልሱን ይሰጠናል። ኢየሱስ ታዛዥ ደቀ መዛሙርቱን ‘ቤቱን በዐለት ላይ ከሠራ ብልኅ ሰው’ ጋር አመሳስሏቸዋል። እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንን ቤት መታው፤ በዐለት መሠረትም ላይ ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።”—ማቴዎስ 7:24, 25

በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ግለሰብ ብልኅ ቢሆንም እንኳ በዝናብ፣ በጎርፍና በአውሎ ነፋስ የተመሰሉ መከራዎች እንዳጋጠሙት ልብ በል። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ሙሉ በሙሉ ከችግሮች ነፃ በመሆን የማይደፈርስ ሰላምና የተረጋጋ ሕይወት እንደሚኖራቸው አልተናገረም። (መዝሙር 34:19፤ ያዕቆብ 4:13-15) ከዚህ ይልቅ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች እነዚህን የመሳሰሉ ከባድ መከራዎችና ችግሮች እንደሚደርሱባቸው መጠበቅና ችግሮቹን መቋቋም እንዳለባቸው ተናግሯል።

ኢየሱስ ምሳሌውን የጀመረው “ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል፣ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራን ብልኅ ሰው ይመስላል” በማለት ነበር። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ቃል በቃል ቤቶችን ስለ መሥራት ሳይሆን ጥሩ ዝንባሌና አመለካከት ስለ ማዳበር ነው። የክርስቶስን ቃል የሚሰሙ ሰዎች ማስተዋልና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ይጠቀማሉ። የተማሯቸውን ነገሮች ተግባራዊ በማድረግ ዝንባሌያቸውና ተግባራቸው እንደ ዓለት ጽኑ በሆኑት የክርስቶስ ትምህርቶች ላይ እንዲመሠረት ያደርጋሉ። ይህ ምሳሌያዊ ዓለት በላይኛው የመሬት ክፍል ላይ የሚገኝ አይደለም። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሰው ይህን ዓለት ለማግኘት ‘ጥልቀት ያለው ቁፈራ’ ማድረግ ይኖርበታል። (ሉቃስ 6:48) በተመሳሳይም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚያስችሏቸውን ባሕርያት ለማዳበር ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋሉ።—ማቴዎስ 5:5-7፤ 6:33

የክርስቶስ ተከታዮች ጽኑ አቋማቸውን የሚፈታተኑ ማዕበል መሰል መከራዎች ሲያጋጥሟቸው ምን ያደርጋሉ? የክርስቶስን ትምህርቶች በፈቃደኝነት መታዘዛቸው እንዲሁም ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበራቸው በአስቸጋሪ ጊዜ በተለይ ደግሞ በቅርቡ በሚነሳው የአርማጌዶን ማዕበል ወቅት የብርታት ምንጭ ይሆንላቸዋል። (ማቴዎስ 5:10-12፤ ራእይ 16:15, 16) አዎን፣ ብዙዎች የክርስቶስን ትምህርቶች በመከተል በማዕበል የተመሰሉ ችግሮችን በመቋቋም ላይ ይገኛሉ። አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ።—1 ጴጥሮስ 2:21-23