በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስኬታማ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

ስኬታማ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

ስኬታማ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

ወላጆች ለልጆቻቸው እንደሚያስቡና ስኬታማ እንዲሆኑላቸው እንደሚፈልጉ ሁሉ የሰማዩ አባታችንም ያስብልናል እንዲሁም ስኬታማ እንድንሆን ይፈልጋል። ለእኛ ካለው ፍቅራዊ አሳቢነት የተነሳ ስኬታማ ሊያደርጉንም ሆነ ወደ ውድቀት ሊመሩን የሚችሉ ነገሮችን በተመለከተ ብዙ መረጃዎችን ሰጥቶናል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ለአምላክ ቃል ትኩረት ስለሚሰጥ ሰው ሲናገር “የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” ይላል።—መዝሙር 1:3

ይህ ከሆነ ታዲያ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው ስኬታማ፣ ደስተኛና አርኪ ሊሆን ያልቻለው ለምንድን ነው? ከላይ ያለውን መዝሙር በጥልቀት መመርመራችን ለጥያቄው መልስ የሚሰጠን ከመሆኑም ሌላ ስኬታማ መሆን የምንችልበትን መንገድ ይጠቁመናል።

“በክፉዎች ምክር”

መዝሙራዊው “በክፉዎች ምክር” መሄድ ስለሚያስከትለው አደጋ አስጠንቅቋል። (መዝሙር 1:1) ቀንደኛው ‘ክፉ’ ደግሞ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። (ማቴዎስ 6:13) ቅዱሳን መጻሕፍት ሰይጣን “የዚህ ዓለም ገዥ” እንደሆነና “መላው ዓለምም በክፉው ሥር እንደ ሆነ” ይናገራሉ። (ዮሐንስ 16:11፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ስለዚህ በዓለም ላይ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች የሚሰጡን ምክር የክፉውን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ መሆኑ ምንም አያስደንቅም።

ክፉዎች የሚሰጡት ምክር ምን ዓይነት ነው? በጥቅሉ ሲታይ ክፉዎች አምላክን ይንቃሉ። (መዝሙር 10:13 የ1980 ትርጉም) አምላክን ችላ በማለት ወይም በመናቅ የሚሰጡት ምክር በሁሉም ቦታ ተስፋፍቶ ይገኛል። ዛሬ ያለው ኅብረተሰብ “የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት” እንዲስፋፋ አድርጓል። (1 ዮሐንስ 2:16) መገናኛ ብዙኃን ደግሞ “በሕይወትህ ማግኘት የምትችለውን ሁሉ አግኝ” የሚለውን ፍቅረ ንዋይ የሚንጸባረቅበት አመለካከት ያዥጎደጉዱብናል። በዓለም ዙሪያ ያሉ ድርጅቶች፣ ሰዎች ቢያስፈልጋቸውም ባያስፈልጋቸውም የእነርሱን ምርቶች እንዲገዙ ለማሳመን ሲሉ ለማስታወቂያ ብቻ በየዓመቱ ከ500 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚበልጥ ወጪ ያወጣሉ። ይህ ማስታወቂያ ደግሞ ሰዎች ዕቃ የመግዛት ልማድ እንዲጠናወታቸው በማድረግ ብቻ አልተወሰነም፤ ዓለም ለስኬት ያለው አመለካከት እንዲዛባም አድርጓል።

በዚህም ምክንያት ብዙዎች ከዓመታት በፊት ፈጽሞ ሊያገኟቸው የማይችሏቸውን ነገሮች ካገኙ በኋላም እንኳ ተጨማሪ ቁሳዊ ሀብት የማግኘት ጥማቸው አልረካም። እነዚህን ቁሳዊ ነገሮች ካላገኘህ ደስተኛ ወይም ስኬታማ መሆን አትችልም የሚል አስተሳሰብ አላቸው። ሆኖም ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ‘ከዓለም እንጂ ከአብ የመጣ’ ስላልሆነ የተሳሳተ ነው።—1 ዮሐንስ 2:16

ፈጣሪያችን እውነተኛ ስኬት ሊያስገኝልን የሚችለው ምን እንደሆነ ያውቃል። የፈጣሪ ምክር ‘ከክፉዎች ምክር’ የተለየ ነው። በመሆኑም በአንድ በኩል ዓለም ስኬት ይገኝበታል በሚለው ጎዳና ላይ እየተጓዙ በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት መጣር በሁለት የተለያዩ መንገዶች ላይ በአንድ ጊዜ ለመጓዝ የመሞከር ያህል ነው። እንዲህ ማድረግ ደግሞ ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ይህን ዓለም አትምሰሉ” ሲል ማስጠንቀቁ ምንም አያስደንቅም!—ሮሜ 12:2

ዓለም እንዲቀርጽህ አትፍቀድ

በሰይጣን ተጽዕኖ ሥር ያለው ዓለም ለደኅንነታችን የሚቆረቆር መስሎ ለመታየት ይሞክራል። ይሁን እንጂ ጠንቃቃ መሆን አለብን። ሰይጣን የራስ ወዳድነት ፍላጎቱን ለማርካት ሲል የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን እንዳሳታት ማስታወስ አለብን። ከዚያም በሔዋን ተጠቅሞ አዳምም ተመሳሳይ የኃጢአት ጎዳና እንዲከተል አድርጎታል። በዛሬው ጊዜም ሰይጣን የእርሱን በክፋት የተሞላ ምክር ለማስፋፋት በሰዎች ይጠቀማል።

ለምሳሌ ያህል፣ በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ዴቪድ፣ ትርፍ ሰዓት መሥራት ብሎም በሥራው ምክንያት ብዙ ጊዜ ከቦታ ቦታ መጓዝ ይጠበቅበት ነበር። ዴቪድ “ሰኞ ጠዋት ገና ሳይነጋ ወጥቼ ሐሙስ ማታ እመለሳለሁ” በማለት ተናግሯል። ለእርሱ መልካም የሚያስቡ ወዳጆቹ፣ ዘመዶቹና የሥራ ባልደረቦቹ በዓለም ላይ ስኬታማ ለመሆን እነዚህን የመሳሰሉ መሥዋዕቶችን መክፈል እንደሚያስፈልግ በማመን “ለቤተሰብህ ስትል ይህን ማድረግ ይኖርብሃል” በማለት ይጎተጉቱት ነበር። ይህ ሁኔታ የሚቀጥለው ለጥቂት ዓመታት ይኸውም ኑሮው እስኪደላደል ድረስ ብቻ እንደሆነ በመናገር ሊያሳምኑት ሞከሩ። ዴቪድ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ጠቀም ያለ ገንዘብ ማግኘት ስለምችል ይበልጥ ስኬታማ እንደምሆንና ይህም ለቤተሰቤ የተሻለ እንደሚሆን ይነግሩኝ ነበር። ወዳጆቼ፣ ከቤተሰቤ ጋር አብሬ ባልኖርም ለቤተሰቤ የበለጠ ነገር እያደረግኩ እንደሆነ አሳመኑኝ።” እንደ ዴቪድ ያሉ ብዙ ሰዎች ቤተሰባቸው እንደሚያስፈልገው የሚያስቡትን ነገር ሁሉ ለማሟላት ጠንክረው ይሠራሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን ምክር መከተል ወደ ስኬት ይመራል? ቤተሰብ በእርግጥ የሚያስፈልገው ምንድን ነው?

ዴቪድ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገው ነገር ምን እንደሆነ የተረዳው ለሥራ ወደ ሌላ ቦታ በሄደበት ወቅት ነበር። እንዲህ ይላል:- “አንጀሊካ ከተባለችው ልጄ ጋር በስልክ እያወራን ሳለ ‘አባባ፣ ከእኛ ጋር ቤት መሆን የማትፈልገው ለምንድን ነው?’ አለችኝ። በዚህ ጊዜ በጣም ደነገጥኩ።” ልጁ የተናገረችው ነገር ሥራውን ለመልቀቅ የነበረውን ፍላጎት አጠናከረለት። ዴቪድ፣ ቤተሰቡ በትክክል የሚፈልገውን ነገር ለመስጠት ይኸውም ከእነርሱ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ወሰነ።

የአምላክን ምክር በተግባር ማዋል ስኬታማ ያደርጋል

በዚህ ዓለም ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የተሳሳተ አመለካከት መከላከል የምትችለው እንዴት ነው? መዝሙራዊው፣ ስኬታማና ደስተኛ ስለሆነ ሰው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል።”—መዝሙር 1:2

አምላክ፣ ኢያሱን የእስራኤል ብሔር መሪ አድርጎ ሲሾመው የአምላክን ቃል “ቀንም ሆነ ሌት ከሐሳብህ አትለየው [“አንብበው፣” NW]” በማለት ነግሮት ነበር። አዎን፣ የአምላክን ቃል ማንበብና ማሰላሰል አስፈላጊ ነው፤ ሆኖም ኢያሱ ‘በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ በጥንቃቄ እንዲፈጽመውም’ ይጠበቅበት ነበር። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ብቻ በተአምር ስኬታማ እንድትሆን አያደርግህም። ያነበብከውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ አለብህ። ኢያሱ “ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም” ተብሏል።—ኢያሱ 1:8

አንድ ደስተኛ ልጅ አፍቃሪ በሆነው ወላጁ ጭን ላይ ተቀምጦ የሚወደውን ታሪክ አብረው ሲያነቡ በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር። ከዚህ ቀደም ታሪኩን ብዙ ጊዜ ያነበቡት ቢሆንም እነዚህ አስደሳች ጊዜያት ለእነርሱ ውድ ናቸው። በተመሳሳይም አምላክን የሚወድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የሚያነብበትን ጊዜ በሰማይ ካለው አባቱ ጋር አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። እንዲህ ያለው ሰው የይሖዋን ምክርና መመሪያ ስለሚከተል “በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።”—መዝሙር 1:3

መዝሙራዊው የጠቀሰው ዛፍ ያደገው እንዲያው በአጋጣሚ አይደለም። ውኃ ባለበት አካባቢ ከመተከሉም በላይ አንድ ገበሬ ይንከባከበዋል። በተመሳሳይም፣ በሰማይ ያለው አባታችን በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በሚገኘው ምክር አማካኝነት አስተሳሰባችንን ያስተካክልልናል እንዲሁም ያርመናል። ይህም በመንፈሳዊ እንድንበለጽግና አምላክ ከሰጠው ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ ፍሬዎችን እንድናፈራ ያደርገናል።

“ክፉዎች ግን እንዲህ አይደሉም።” እውነት ነው፣ ለተወሰነ ጊዜ የበለጸጉ ይመስል ይሆናል፤ የመጨረሻ ውጤታቸው ግን መጥፎ ነው። ክፉዎች “በፍርድ ፊት . . . መቆም አይችሉም።” ከዚህ ይልቅ “የክፉዎች መንገድ . . . ትጠፋለች።”—መዝሙር 1:4-6

በመሆኑም ይህ ዓለም፣ በምታወጣው ግብም ሆነ በሥነ ምግባር አቋምህ ረገድ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብህ ፈጽሞ አትፍቀድ። ልዩ ተሰጥኦና በዚህ ዓለም ስኬታማ ለመሆን የሚያስችል ሰፊ አጋጣሚ ያለህ ብትሆንም ያለህን ተሰጥኦ በጥንቃቄ ተጠቀምበት፤ ዓለም መጠቀሚያ እንዳያደርግህ ተጠንቀቅ። ፍሬ ቢስ የሆኑ ቁሳዊ ግቦችን ማሳደድ አንድ ሰው ‘እንዲጠወልግ’ ሊያደርገው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት እውነተኛ ስኬትና ደስታ ያስገኛል።

ስኬታማ መሆን የምትችልበት መንገድ

አንድ ሰው የአምላክን ምክር ከተከተለ ሁሉ ነገር እንደሚሳካለት የተገለጸው ለምንድን ነው? መዝሙራዊው እየተናገረ ያለው በዚህ ዓለም ውስጥ ስለሚገኘው ስኬት አይደለም። አምላክን የሚታዘዝ ሰው ስኬት፣ የአምላክን ፈቃድ ከማድረግ ጋር የተያያዘ ነው፤ የአምላክ ፈቃድ ደግሞ ሳይፈጸም አይቀርም። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል ስኬታማ እንድትሆን የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ቤተሰብ:- መጽሐፍ ቅዱስ ባሎች ‘ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው እንዲወዱ’ የሚመክራቸው ሲሆን አንዲት ክርስቲያን ሚስት ደግሞ “ባሏን ታክብር” የሚል መመሪያ ይዟል። (ኤፌሶን 5:28, 33) ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ለመጫወትና በሕይወት ውስጥ አስፈላጊ ስለሆኑ ነገሮች ለመወያየት አብረዋቸው ጊዜ እንዲያሳልፉ ተበረታተዋል። (ዘዳግም 6:6, 7፤ መክብብ 3:4) ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ቃል ወላጆችን “ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው” በማለት ይመክራቸዋል። ወላጆች ይህን ምክር ሲከተሉ ልጆች ‘ለወላጆቻቸው መታዘዝ’ እንዲሁም ‘አባታቸውንና እናታቸውን ማክበር’ ቀላል ይሆንላቸዋል። (ኤፌሶን 6:1-4) ይህን መለኮታዊ ምክር መከተል የቤተሰቡ ሕይወት ስኬታማ እንዲሆን ያደርጋል።

ጓደኞች:- ብዙ ሰዎች ጓደኞች እንዲኖሯቸው ይፈልጋሉ። ሁላችንም ለመውደድም ሆነ ለመወደድ የሚያስችለን አእምሯዊና ስሜታዊ ችሎታ አለን። ኢየሱስ ተከታዮቹን ‘እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ’ አዟቸዋል። (ዮሐንስ 13:34, 35) ከክርስቶስ ተከታዮች መካከል ልንወዳቸውና ልናምናቸው እንዲሁም ውስጣዊ ሐሳባችንንና ስሜታችንን ልንገልጽላቸው የምንችላቸው ጓደኞች እናገኛለን። (ምሳሌ 18:24) ከሁሉም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ‘ወደ ይሖዋ ልንቀርብና’ ልክ እንደ አብርሃም ‘የይሖዋ ወዳጅ’ ተብለን ልንጠራም እንችላለን።—ያዕቆብ 2:23፤ 4:8

የሕይወት ዓላማ:- እውነተኛ ስኬት ያገኙ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚመሩት እንዲያው በአጋጣሚ ሳይሆን በዓላማ ነው። ሕይወታቸው መረጋጋት በማይታይበት የዓለም ሁኔታ ላይ የተመሠረተ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ግባቸው ያተኮረው በእውነተኛው ሕይወት ላይ ነው፤ ይህ ደግሞ እውነተኛና ዘላቂ እርካታ ያስገኝላቸዋል። አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ዓላማ እንዲኖረው የሚረዳው ምንድን ነው? “እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።”—መክብብ 12:13

ተስፋ:- የአምላክ ወዳጅ መሆናችን የወደፊት ተስፋ እንዲኖረንም ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ” አሳስቧቸዋል። በዚህ መንገድ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራሳቸው ያከማቻሉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:17-19) በሰማይ የሚገኘው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ በምድር ላይ ገነትን በሚያቋቁምበት ጊዜ ይህን እውነተኛ ሕይወት እናገኛለን።—ሉቃስ 23:43

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ብታውልም እንኳ ከችግሮች ነጻ ትሆናለህ ማለት አይደለም። ሆኖም ክፉዎች በራሳቸው ላይ ከሚያመጡት የስሜት ሥቃይና ሐዘን ልትድን ትችላለህ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዴቪድና እንደ እርሱ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው መተግበራቸው ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝበዋል። ዴቪድ ከሁኔታው ጋር የሚስማማ ሥራ ካገኘ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር ስላለኝ ግንኙነት እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ ይሖዋ አምላክን ለማገልገል ስላገኘሁት መብት አመስጋኝ ነኝ።” ቀደም ሲል የተመለከትነው መዝሙር የአምላክን ምክር በሥራ ላይ ስለሚያውል ሰው ሲናገር “የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” ማለቱ ምንም አያስደንቅም!

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ግራፍ/ሰንጠረዥ]

ስኬታማ መሆን የሚቻልባቸው አምስት ዘዴዎች

1 የዚህ ዓለም አስተሳሰብ እንዲቀርጽህ አትፍቀድ።

መዝሙር 1:1፤ ሮሜ 12:2

2 የአምላክን ቃል በየዕለቱ አንብብ፤ እንዲሁም በቃሉ ላይ አሰላስል።

መዝሙር 1:2, 3

3 የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ አድርግ።

ኢያሱ 1:7-9

4 አምላክን ወዳጅህ አድርገው።

ያዕቆብ 2:23፤ 4:8

5 እውነተኛውን አምላክ ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ።

መክብብ 12:13

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስኬታማ ለመሆን የሚያስችሉህን ምክሮች በሥራ ላይ እያዋልክ ነው?