በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ የዕድሜ ልክ በረከት ያስገኛል

ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ የዕድሜ ልክ በረከት ያስገኛል

የሕይወት ታሪክ

ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ የዕድሜ ልክ በረከት ያስገኛል

ፖል ኩሽኒር እንደተናገረው

በ1897 አያቶቼ ከዩክሬን ወደ ካናዳ ተሰድደው በሳስካችዋን ግዛት ዮርክተን ከተማ አቅራቢያ መኖር ጀመሩ። በዚያን ወቅት ሦስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ነበራቸው። ማሪንካ የተባለችው ሴት ልጃቸው በ1923 እኔን ወለደች፤ ለእርሷም ሰባተኛ ልጇ ነበርኩ። በወቅቱ ኑሮው ያን ያህል የተቀናጣ ባይሆንም አስተማማኝ ነበር። ገንቢ ምግብ እንመገባለን፣ ቅዝቃዜውን መቋቋም የሚያስችል ልብስ እንለብሳለን እንዲሁም መንግሥት ሕዝቡ ማግኘት ያለበትን መሠረታዊ ነገሮች ያቀርብ ነበር። አንዳንድ ከባድ ሥራዎችን ከጎረቤቶቻችን ጋር በደቦ እንሠራ ነበር። በ1925 የክረምት ወራት ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው ከሚጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መካከል አንዱ ቤታችን መጥቶ አነጋገረን። የዚያን ቀን ያደረግነው ውይይት እስካሁን ድረስ የምደሰትበትን ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ እንድንችል ረድቶናል።

ቤተሰባችን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሰማ

እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሰጧትን የተወሰኑ ቡክሌቶች ካነበበች በኋላ እውነትን እንዳገኘች ወዲያው ተረዳች። ከዚያም ፈጣን መንፈሳዊ እድገት አድርጋ በ1926 ተጠመቀች። እናታችን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ መሆኗ ቤተሰባችን ለሕይወት ያለውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ለወጠው። ቤተሰባችን እንግዳ ተቀባይ ሆነ። በዚያን ወቅት ፒልግሪምስ እየተባሉ የሚጠሩት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እንዲሁም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜ እኛ ቤት ያርፉ ነበር። በ1928 አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” ቀለል ባለ መንገድ የቀረበበትን “ዩሬካ ድራማ” የተባለውን ስላይድ ፊልም አሳየን። ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ጫን ሲሉት ድምጽ የሚሰጥ የእንቁራሪት ቅርጽ ያለውን መጫወቻ ከእኛ ተዋሰ። እንቁራሪቷ ድምጽ ስታሰማ ፊልሙ ይቀየራል። ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ፊልሙን ለማሳየት የእኛን መጫወቻ በመጠቀሙ ኩራት ተሰማን!

ኤመል ዛሪስኪ የተባለ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ብዙውን ጊዜ እንደ ቤት በሚገለገልባት መኪና እየመጣ ይጠይቀን ነበር። አንዳንድ ጊዜ ትልቁን ልጁን ይዞ ይመጣ የነበረ ሲሆን ይህ ልጅ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ወይም አቅኚዎች የመሆን ግብ እንዲኖረን ያበረታታን ነበር። እንዲሁም ብዙ አቅኚዎች እኛ ቤት ያርፉ ነበር። አንድ ቀን እናቴ ለአንድ አቅኚ የእርሱን ሸሚዝ እስክትሰፋለት ድረስ ሌላ ሸሚዝ አዋሰችው፤ ሆኖም ይህ ወንድም ሸሚዙን በስህተት ይዞት ሄደ። ከብዙ ጊዜ በኋላ በማቆየቱ ይቅርታ ጠይቆ ሸሚዙን በፖስታ ቤት በኩል ላከልን። ያቆየበትንም ምክንያት ሲገልጽ “ለፖስታ ቤት የምከፍለው አሥር ሳንቲም ስላልነበረኝ ነው” በማለት ጻፈልን። ሁላችንም ምናለበት ሸሚዙን ቢያስቀረው ኖሮ ብለን አሰብን። እኔም ወደፊት የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ አቅኚዎችን ምሳሌ እንደምኮርጅ ይሰማኝ ነበር። እናታችን ስለነበራት የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አመሰግናታለሁ። እንዲህ ያለው ባሕርይዋ ጥሩ የሕይወት ተሞክሮ እንድናገኝ ብሎም ለወንድሞች ያለን ፍቅር እንዲጎለብት አስችሎናል።—1 ጴጥሮስ 4:8, 9

አባታችን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ባይሆንም እንኳ አይቃወመንም ነበር። እንዲያውም በ1930 ወንድሞች ግቢያችን ውስጥ ያለውን ሰፊ ዳስ የአንድ ቀን ትልቅ ስብሰባ እንዲያደርጉበት ፈቅዶላቸው ነበር። በዚያ ወቅት ምንም እንኳ የሰባት ዓመት ልጅ ብሆንም ስብሰባው አስደሳችና ክብር የተላበሰ መሆኑ በጣም አስደንቆኛል። አባቴ በ1933 በመሞቱ እናቴ ስምንት ልጆችን ብቻዋን የምታሳድግ መበለት ሆነች። ይሁን እንጂ ልጆቿ ከእውነተኛው አምልኮ ጎዳና እንዳይወጡ ለመርዳት ካደረገችው ቁርጥ ውሳኔ ትንሽ እንኳ ፈቀቅ አላለችም። እናቴ ወደ ስብሰባዎች ይዛኝ ትሄድ የነበረ ሲሆን እኔ ግን ስብሰባዎቹ በጣም ረጅም ስለሚሆኑብኝ ውጪ እንዲጫወቱ ከሚፈቀድላቸው ልጆች ጋር ለመጫወት እጓጓ ነበር። ነገር ግን እናቴን አከብራት ስለነበር እንደዚያ አድርጌ አላውቅም። ከዚህም በላይ እናቴ ምግብ በምታበስልበት ወቅት የአንድን ጥቅስ ሐሳብ ትነግረኝና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የት ቦታ ላይ እንደሚገኝ ትጠይቀኝ ነበር። በ1933 ከእርሻ ቦታችን ከወትሮው የተለየ ከፍተኛ ምርት አገኘን። እናቴ ከሽያጩ ያገኘችውን ተጨማሪ ገንዘብ መኪና ገዛችበት። አንዳንድ ጎረቤቶቻችን ገንዘብ እንዳባከነች በማሰብ ተችተዋት ነበር። ሆኖም እርሷ ይህን ያደረገችው መኪናዋ ለምናደርጋቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንደምትጠቅመን በማሰብ ነበር። ደግሞም ልክ ነበረች።

ሌሎች ትክክለኛ ምርጫ እንዳደርግ ረድተውኛል

አንድ ወጣት የሆነ ደረጃ ላይ ሲደርስ የሚያደርገው ውሳኔ የወደፊት ሕይወቱን እንደሚነካበት እሙን ነው። ሔለንና ኬይ የተባሉት ታላላቅ እህቶቼ እንዲህ ያለው ወቅት ላይ ሲደርሱ አቅኚ ሆነው ማገልገል ጀምሩ። በአንድ ወቅት ጆን ጃዙስኪ የተባለ በጣም ግሩም አቅኚ ወንድም እኛ ቤት በእንግድነት አርፎ ነበር። እናቴ በእርሻ ሥራ እንዲረዳን ስለፈለገች እኛ ቤት እንዲቆይ ሐሳብ አቀረበችለት። ከዚያ በኋላ ጆንና ኬይ ተጋብተው ከቤታችን ብዙም ሳይርቁ አቅኚ ሆነው ማገልገል ጀመሩ። የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ ትምህርት ቤት ለእረፍት ሲዘጋ ወደ እነርሱ ሄጄ አብሬያቸው እንዳገለግል ጋበዙኝ። እንደዚያ ማድረጌ የአቅኚነትን ሕይወት እንድቀምስ አጋጣሚ ፈጥሮልኛል።

ከጊዜ በኋላ እርሻውን በተወሰነ መጠንም ቢሆን እኔና ወንድሜ ጆን ማስተዳደር ጀመርን። ይህም እናታችን በሐምሌና በነሐሴ ወራት በአሁኑ ጊዜ ረዳት አቅኚ እየተባለ በሚጠራው የአቅኚነት ዘርፍ ለመካፈል የሚያስችል አጋጣሚ ከፈተላት። ለአገልግሎትም በአንድ ያረጀ ፈረስ የሚጎተት ጋሪ ትጠቀም ነበር። ይህ ፈረስ አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ አባቴ ሳኦል የሚል ስም አውጥቶለት የነበረ ቢሆንም ለእናቴ ግን በቀላሉ ይታዘዝላት ነበር። እኔና ጆን የእርሻውን ሥራ የወደድነው ቢሆንም እንኳ እናታችን አገልግሎት ቆይታ ስትመጣ የምትነግረን ተሞክሮ ከግብርናው ይልቅ ወደ አቅኚነት አገልግሎት እንድናደላ አደረገን። በ1938 በመስክ አገልግሎት የማሳልፈውን ጊዜ ከፍ አደረግሁና የካቲት 9, 1940 ተጠመቅሁ።

ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በጉባኤ ውስጥ አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። የጉባኤውን መዛግብት የምይዘው እኔ ስለነበርኩ የጉባኤያችንን እድገት ማየት እችል ነበር። ከቤታችን አሥራ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ አንዲት ከተማ ውስጥ የግል የአገልግሎት ክልል ነበረኝ። በጣም ቀዝቃዛ በሆነው የክረምት ወራት በየሳምንቱ በእግሬ ወደዚያ እየሄድኩ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት ባሳዩ ሰዎች ቤት ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ያህል ከቤታቸው ጣሪያ ሥር ባለ ክፍል ውስጥ አድር ነበር። አንድ ጊዜ በዚያች ከተማ ከሚገኝ የሉተራን ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ ጋር ውይይት ካደረግን በኋላ የእርሱን ቤተ ክርስቲያን አባላት ማነጋገሬን ካላቆምኩ በፖሊስ እንደሚያስይዘኝ በመናገር አስፈራራኝ። እርግጥ እኔም ብልሃት ይጎድለኝ ነበር። ይሁን እንጂ የእርሱ ማስፈራሪያ ወደኋላ እንድል ሳይሆን ይበልጥ እንድቀጥልበት አደረገኝ።

በ1942 እህቴ ኬይና ባለቤቷ ጆን በክሌቭላንድ፣ ኦሃዮ፣ ዩ ኤስ ኤ በሚደረግ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወስነው ነበር። በወቅቱ አብሬያቸው እንድሄድ በመጋበዜ በጣም ተደስቼ ነበር። ያ ስብሰባ በሕይወቴ ከገጠሙኝ ነገሮች በሙሉ የሚበልጥ ሲሆን ያወጣኋቸውን ግቦች አጠናክሮልኛል። በወቅቱ ዓለም አቀፉን ሥራ በበላይነት ይመራ የነበረው ወንድም ናታን ኖር በስብሰባው ላይ 10,000 አቅኚዎች እንደሚያስፈልጉ የሚገልጽ ጥሪ ባቀረበበት ወቅት ከእነርሱ መካከል አንዱ ለመሆን ወዲያውኑ ወሰንኩ!

በጥር 1943 ሄንሪ የሚባል አንድ ተጓዥ አገልጋይ ጉባኤያችንን በጎበኘበት ወቅት ለተግባር የሚያነሳሳ ቀስቃሽ ንግግር አቀረበ። በሚቀጥለው ቀን ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ነበር፤ ከሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ የሚነፍሰው ኃይለኛ ነፋስ ደግሞ ቀኑን ይበልጥ እንዲቀዘቅዝ አደረገው። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለ የአየር ጠባይ በሚኖርበት ወቅት ከቤት አንወጣም፤ ሄንሪ ግን አገልግሎት ለመውጣት በጣም ጓጉቶ ነበር። በመሆኑም እርሱና ሌሎች ወንድሞች የማሞቂያ ምድጃ ባለው በበረዶ ላይ የሚንሸራተት የፈረስ ጋሪ ተጠቅመው 11 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኝ አንዲት መንደር ሄዱ። እኔ ደግሞ አምስት ልጆች ያሉትን አንድ ቤተሰብ ለመጠየቅ ሄድኩ። የዚህ ቤተሰብ አባላት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ የሰጡ ከመሆኑም በላይ ከጊዜ በኋላ እውነትን ተቀብለዋል።

በእገዳ ሥር ሆኖ መስበክ

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የስብከቱ ሥራ በካናዳ በመታገዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን መደበቅ ግድ ሆኖብን ነበር። የእርሻ ቦታችን ደግሞ ለዚህ አመቺ ሆኖልናል። ፖሊሶች በተደጋጋሚ ጊዜያት መጥተው ቤታችንን ቢፈትሹም ምንም ነገር ማግኘት አልቻሉም። በምንሰብክበት ወቅት እንጠቀም የነበረው መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ነው። የምንሰበሰበው በትናንሽ ቡድኖች ሲሆን እኔና ወንድሜ ጆን በድብቅ መልእክት የማቀበል ሥራ ተሰጠን።

በጦርነቱ ወቅት ጉባኤያችን ኢንድ ኦቭ ናዚዝም የተባለውን ቡክሌት በማሰራጨቱ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ተሳትፏል። ከቤታችን እኩለ ሌሊት ላይ ወጥተን ወደ እያንዳንዱ ቤት በር ቀስ ብለን በመጠጋት የምናሰራጨውን ቡክሌት አስቀምጠን እንሄዳለን። ወደ ቤቶቹ በምጠጋበት ወቅት በጣም እፈራ ነበር። ይህ ሥራ እስከዛሬ ከሠራኋቸው ሥራዎች ሁሉ የሚያስፈራ ነው። የቡክሌቱን የመጨረሻ ቅጂ በር ላይ ባስቀመጥን ጊዜ የተሰማን እፎይታ ይህ ነው አይባልም! ከዚያም በፍጥነት ወደ መኪናችን ሄደን ሁላችንም መሰባሰባችንን ካረጋገጥን በኋላ ቶሎ ከአካባቢው እንሰወራለን።

አቅኚነት፣ የእስር ቤት ሕይወትና ትልልቅ ስብሰባዎች

ግንቦት 1, 1943 እናቴን ተሰናብቼ ከቤት ወጣሁ። ወደ መጀመሪያው የአቅኚነት ምድቤ የሄድኩት አንዲት ትንሽ ሻንጣና 20 ዶላር ይዤ ነበር። በሳስካችዋን ክፍለ ሀገር ውስጥ በምትገኘው በክዊል ሌክ የሚኖረው ወንድም ቶም ትሩፕና ሰው አፍቃሪ የሆኑት ቤተሰቦቹ በእንግድነት ተቀበሉኝ። በቀጣዩ ዓመት እዚያው በሳስካችዋን ክፍለ ሀገር በምትገኘው በዌበርን ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ገለልተኛ ክልል ሄድኩ። ታኅሣሥ 24, 1944 መንገድ ላይ እያገለገልኩ ሳለ ተያዝኩና ታሰርኩ። ከዚያም የተወሰነ ጊዜ በአካባቢው በሚገኝ ወኅኒ ቤት ካሳለፍኩ በኋላ በጃስፐር፣ አልበርተ ወደሚገኘው የጉልበት ሥራ የሚሠራበት ካምፕ ተዛወርኩ። በካምፑ ውስጥም ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘን ሲሆን ዙሪያችን የይሖዋን ድንቅ ሥራዎች በሚያሳዩት የካናዳ ድንጋያማ ተራራዎች የተከበበ ነበር። በ1945 መጀመሪያ አካባቢ በኤድመንተን፣ አልበርተ በሚደረግ ስብሰባ ላይ እንድንካፈል የካምፑ ባለ ሥልጣናት ፈቀዱልን። በስብሰባው ላይም ወንድም ኖር በዓለም ዙሪያ ስላለው እድገት የሚገልጽ አስደሳች ሪፖርት አቀረበልን። እኛም የእስር ጊዜያችን የሚያበቃበትንና እንደገና በአገልግሎት ሙሉ በሙሉ የምንካፈልበትን ጊዜ ናፍቀን ነበር።

ከእስር እንደተፈታሁ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከዚያም ብዙ ሳይቆይ በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ “ኦል ኔሽንስ ኤክስፓንሽን” የተባለ የአውራጃ ስብሰባ እንደሚደረግ ተነገረ። አቅኚ ሆኜ በተመደብኩበት ቦታ የሚኖር አንድ ወንድም ያለውን የጭነት መኪና አግዳሚ ወንበር ካደረገበት በኋላ 20 ተሳፋሪዎችን ሊይዝ በሚችል ሁኔታ አመቻቸው። ነሐሴ 1, 1947 7,200 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍነውን ጉዞ ጀመርን፤ በሣር የተሸፈኑ ሜዳዎችን፣ በረሃዎችን፣ ማራኪ የሆኑ መልክዓ ምድሮችንና የለውስቶን እንዲሁም ዮስማይት የተባሉትን ፓርኮች አቆራርጠን በጠቅላላው ለ27 ቀናት ያደረግነው ይህ ጉዞ በጣም አስደሳች ነበር!

ስብሰባውም ቢሆን የማይረሱ ተሞክሮዎች ያካበትንበት ነው። በስብሰባው ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ ቀን ላይ አስተናጋጅ ማታ ማታ ደግሞ ጠባቂ ሆኜ ሠርቻለሁ። በሚስዮናዊነት አገልግሎት ለመካፈል ከሚፈልጉ ጋር በተደረገው ስብሰባ ላይ ከተገኘሁ በኋላ ይሳካል ብዬ ብዙም ባልጠብቅም የማመልከቻውን ቅጽ ሞላሁ። እስከዚያው ድረስ ግን በ1948 የካናዳ አንድ ግዛት በሆነችው በኩቤክ አቅኚ ሆኜ ለማገልገል ራሴን በፈቃደኝነት አቀረብኩ።—ኢሳይያስ 6:8

ጊልያድና ከዚያ በኋላ ያለው ጊዜ

በ1949 በ14ኛው ክፍል የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንድካፈል ግብዣ ሲቀርብልኝ በጣም ደስ አለኝ። እዚያ ያገኘሁት ሥልጠና እምነቴን ያጠናከረልኝ ከመሆኑም ሌላ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድቀርብ አድርጎኛል። ጆንና ኬይ ቀደም ብለው በ11ኛው ክፍል ላይ ከተመረቁ በኋላ በሰሜናዊ ሮዴዥያ (የአሁኗ ዛምቢያ) ሚስዮናዊ ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ። ወንድሜ ጆንም ቢሆን በ1956 ከጊልያድ የተመረቀ ሲሆን እስከሞተበት ዕለት ድረስ ከባለቤቱ ከፍሬዳ ጋር በብራዚል ለ32 ዓመታት አገልግሏል።

ከጊልያድ በተመረቅሁበት ዕለት ማለትም በየካቲት ወር 1950 የደረሱኝ ሁለት የቴሌግራም መልእክቶች በጣም አበረታተውኛል፤ አንደኛውን የላከችልኝ እናቴ ስትሆን ሌላውን ደግሞ ክዊል ሌክ የሚኖረው የወንድም ትሩፕ ቤተሰብ ነው። ከወንድም ትሩፕ ቤተሰብ የተላከው የቴሌግራም መልእክት “ለተመራቂው የተሰጠ ምክር” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን “ይህ ቀን ለአንተ ከቀኖች ሁሉ የሚበልጥ ቀን ነው፤ መቼም ቢሆን ትልቅ ግምት የምትሰጠው ቀን ነው፤ በሕይወትህ ደስተኛና ስኬታማ እንድትሆን እንመኝልሃለን” ይላል።

ከጊልያድ ከተመረቅሁ በኋላ በኩቤክ እንዳገለግል ተመደብኩ፤ ሆኖም ለተወሰነ ጊዜ የጊልያድ ትምህርት ቤት በሚገኝበት በኒው ዮርክ የእርሻ ቦታ እንዳገለግል ተነገረኝ። አንድ ቀን ወንድም ኖር ወደ ቤልጅየም መሄድ እፈልግ እንደሆነ ጥያቄ አቀረበልኝ። ይሁን እንጂ ከጥቂት ቀናት በኋላ ኔዘርላንድ ብመደብ ምን እንደሚሰማኝ ጠየቀኝ። የምድብ ቦታዬን የሚያሳውቀው ደብዳቤ “የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ” ሆኜ እንዳገለግል መመደቤን የሚናገር ነበር። ይህ ደግሞ ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ተሰማኝ።

ነሐሴ 24, 1950 በመርከብ 11 ቀን የሚፈጀውን ወደ ኔዘርላንድ የማደርገውን ጉዞ ጀመርኩ። ይህ ጉዞ አዲስ ወጥቶ የነበረውን የአዲስ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ለማንበብ ጊዜ እንዳገኝ አስችሎኛል። መስከረም 5, 1950 ሮተርዳም ስደርስ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሁሉን ነገር ድምጥማጡን አጥፍቶ የነበረ ቢሆንም እንኳ ወንድሞች ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያቸውን እንደገና ለመጀመር በትጋት ይሠሩ ነበር። የተለያዩ ከባድ ስደቶችን እንዴት እንደተቋቋሙ የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ስሰማ ለእነዚህ ወንድሞች በአንድ ልምድ በሌለው ወጣት የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ ሥር ሆኖ መሥራት በጣም አዳጋች እንደሚሆንባቸው ተሰማኝ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ፍርሃቴ መሠረተ ቢስ መሆኑን ተረዳሁ።

እርግጥ ነው ትኩረት የሚፈልጉ አንዳንድ ነገሮች ነበሩ። እዚያ የደረስኩት የአውራጃ ስብሰባ ሊደረግ ትንሽ ሲቀረው ስለነበር በሺህ የሚቆጠሩ እንግዶች ስብሰባው በሚደረግበት ቦታ ላይ አርፈው ስመለከት በጣም ተገረምኩ። በሚቀጥለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ወንድሞች በግለሰብ ቤቶች እንዲያርፉ ሐሳብ አቀረብኩ። ወንድሞች ሐሳቡ ጥሩ እንደሆነ ሆኖም በእነርሱ አገር እንደማይሠራ ነገሩኝ። በጉዳዩ ላይ ከተወያየንበት በኋላ ግማሽ የሚያህሉት እንግዶች እዚያው ስብሰባው የሚደረግበት ቦታ እንዲያርፉ ቀሪዎቹ ደግሞ ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ የይሖዋ ምሥክር ባልሆኑ ሰዎች ቤት እንዲያርፉ ተስማማን። በውጤቱ በጣም ስለተደሰትኩ ወንድም ኖር ለስብሰባው በመጣበት ወቅት ሁኔታውን ነገርኩት። ይሁን እንጂ በኔዘርላንድ ያደረግነውን ስብሰባ አስመልክቶ በመጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን ሪፖርት ሳነብ የተሰማኝ ስሜት እንደ ጉም በንኖ ጠፋ። ሪፖርቱ በኔዘርላንድ የሚገኙ “ወንድሞች በሚቀጥለው ጊዜ ስብሰባ ሲያደራጁ እምነት ሊኖራቸውና ለስብሰባው የሚመጡት እንግዶች ምሥክርነት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ በሚፈጥርላቸው ቦታ [ይኸውም የይሖዋ ምሥክር ባልሆኑ ሰዎች ቤት ውስጥ] እንዲያርፉ ለማድረግ ብርቱ ጥረት እንደሚያደርጉ እንተማመናለን” የሚል ነበር። እኛም “በሚቀጥለው ጊዜ” ያደረግነው ይህንኑ ነበር!

ሐምሌ 1961 ለንደን ውስጥ ከቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች ጋር በተደረገው ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ከእኛ ቅርንጫፍ ቢሮ ሁለት ተወካዮች ተጋብዘው ነበር። በስብሰባው ላይ ወንድም ኖር የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉምን የደች ቋንቋን ጨምሮ በሌሎች ብዙ ቋንቋዎች ለማዘጋጀት እንደታቀደ ተናገረ። እንዴት ደስ የሚል ዜና ነው! እርግጥ የትርጉም ሥራው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አናውቅም ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም በ1963 በኒው ዮርክ ተደርጎ በነበረ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የአዲስ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በደች ቋንቋ መውጣቱ ሲነገር በስብሰባው ላይ መገኘቴ በጣም አስደስቶኛል።

ያደረግሁት ውሳኔና አዲስ ምድብ

በነሐሴ 1961 ላይደ ቫመሊንክ የተባለች እህት አገባሁ። ቤተሰቦቿ እውነትን የሰሙት በ1942 ናዚ ስደት ያደርስ በነበረበት ወቅት ነው። ላይደ አቅኚነት የጀመረችው በ1950 ሲሆን በ1953 ደግሞ በቤቴል እንድታገለግል ተጠራች። በቤቴልም ሆነ በጉባኤ ውስጥ የምታደርገው እንቅስቃሴ በእርግጥም ታማኝ አጋር እንደምትሆነኝ የሚጠቁም ሆኖ ተሰማኝ።

ከተጋባን አንድ ዓመት እንዳለፈ አሥር ወር ለሚቆይ ተጨማሪ ሥልጠና ወደ ብሩክሊን ተጠራሁ። ያን ጊዜ ሚስቶች ከባሎቻቸው ጋር እንዲሄዱ የተደረገ ዝግጅት አልነበረም። ላይደ ጤንነቷ ጥሩ የነበረ ባይሆንም በፍቅር ተነሳስታ ግብዣውን እንድቀበል አበረታታችኝ። እንዲያውም እየዋለ እያደር ያለባት የጤና ችግር በጣም እየከፋ ሄደ። መጀመሪያ ላይ በቤቴል መሥራታችንን ለመቀጠል አስበን ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ግን ከቤቴል ወጥተን በሌላ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መስክ ብንሰማራ እንደሚሻል ወሰንን። ስለዚህ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆነን ማገልገል ጀመርን። ብዙም ሳይቆይ ባለቤቴ ከባድ ቀዶ ሕክምና አደረገች። ወንድሞችና እህቶች ባደረጉልን ፍቅራዊ እርዳታ ችግሩን ልንወጣው ቻልን፤ እንዲያውም ከዓመት በኋላ የአውራጃ የበላይ ተመልካችነት ሥራችንን ቀጥለን ነበር።

ለሰባት ዓመታት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አስደሳች ሥራ ሠርተናል። ከዚያም ሌላ ከባድ ውሳኔ የሚጠይቅ ነገር ገጠመን፤ እርሱም በቤቴል በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት እንዳስተምር መጠራቴ ነው። ምንም እንኳ የተጓዥ የበላይ ተመልካችነቱን ሥራ ወደነው የነበረ ቢሆንም ግብዣውን ተቀበልነው። እያንዳንዳቸው ሁለት ሳምንታት የሚፈጁት የዚህ ትምህርት ቤት 47 ክፍሎች ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር መንፈሳዊ ቁም ነገሮችን ለመካፈል የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ አስገኝተውልኛል።

እናቴን በ1978 ሄጄ ለመጠየቅ እቅድ የነበረኝ ቢሆንም ሳላስበው ሚያዝያ 29, 1977 ማረፏን የሚገልጽ የቴሌግራም መልእክት ደረሰኝ። ከዚያ በኋላ ፍቅር የሚንጸባረቅበትን ያን ድምጿን እንደማልሰማው እንዲሁም ላደረገችልኝ ነገሮች በሙሉ አመስጋኝ መሆኔን ደግሜ ልነግራት እንደማልችል ስገነዘብ በጣም አዘንኩ።

በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ኮርስ መደምደሚያ ላይ የቤቴል ቤተሰብ አባላት እንድንሆን ተጠየቅን። በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት የቅርንጫፍ ኮሚቴው አስተባባሪ ሆኜ አገልግያለሁ። ከጊዜ በኋላ የበላይ አካሉ በቦታው የተሻለ ሊሠራ የሚችል አዲስ አስተባባሪ ሾመ። ለዚህም በጣም አመስጋኝ ነኝ።

ዕድሜያችን በፈቀደልን መጠን ማገልገል

በአሁኑ ጊዜ እኔም ሆንኩ ላይደ 83 ዓመታችን ነው። ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አስደሳች ጊዜ አሳልፌያለሁ። ከእነዚህም ውስጥ 45ቱን ዓመታት ያገለገልኩት ከታማኟ ባለቤቴ ጋር ነው። ላይደ በየትኛውም የሥራ ምድብ ለእኔ የምታደርገውን ድጋፍ ለይሖዋ የምታቀርበው አገልግሎት ክፍል አድርጋ ትመለከተዋለች። በአሁኑ ጊዜ በቤቴልም ሆነ በጉባኤ ውስጥ አቅማችን የፈቀደውን ያህል በመሥራት ላይ እንገኛለን።—ኢሳይያስ 46:4

በሕይወታችን ውስጥ ያሳለፍናቸውን አንዳንድ ነገሮች እያሰብን እንደሰታለን። በይሖዋ አገልግሎት በሠራነው ሥራ ፈጽሞ አንቆጭም። ገና በወጣትነት ዕድሜያችን ላይ ያደረግናቸው ምርጫዎች በጣም ትክክል እንደሆኑ እናምናለን። ይሖዋን በሙሉ ኃይላችን ማገልገላችንንም ሆነ እርሱን ማክበራችንን ለመቀጠል ቆርጠናል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከታላቅ ወንድሜ ከቢልና ሳኦል ከሚባለው ፈረሳችን ጋር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነሐሴ 1961 በሠርጋችን ዕለት

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከላይደ ጋር በአሁኑ ጊዜ